June 8, 2012

ስለ ደብረ ይድራስ ቅ/ጊዮርጊስ ቤተ ክርስቲያንና ስለ ፖሊስ ጉዳይ ከተጨማሪ መረጃዎች ጋር


(ደጀ ሰላም፤ ሰኔ 1/2004 ዓ.ም፤ ጁን 8/ 2012/ READ THIS ARTICLE IN PDF)፦ በአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት ኮልፌ ቀራንዮ ክፍለ ከተማ በሚገኘው ደብረ ይድራስ ቅዱስ ጊዮርጊስ ቤተ ክርስቲያን ከይዞታ ማስከበር ጋራ በተያያዘ ግንቦት 27 ቀን 2004 ዓ.ም ጠዋት በፖሊስ እና በአጥቢያው ምእመናን መካከል ግጭት ተቀስቅሷል፤ በግጭቱ የአንድ ፖሊስ ሕይወት አልፏል፤ በርካታ የአዲስ አበባ ፖሊሶችና ምእመናንም ተጎድተዋል፤ ቁጥራቸው ከ70 - 80 የሚሆኑ የአጥቢያው ወጣትና ዐዋቂ ምእመናን ከየመንደሩ በፌዴራል ፖሊስ አባላት እየተሰበሰቡ መታሰራቸው ነው የተነገረው፡፡ ይህ ዜና እስከተጠናቀረበት ሰዓት ድረስ ወዴት እንደተወሰዱም ለማወቅ አልተቻለም፤ ከፖሊሶቹ ከራሳቸው÷ በዐይን ምስክሮች አነጋገር ደግሞ በቦታው ላይ አመራር ይሰጡ ከነበሩት አመራሮች በአንዱ÷ በተተኰሰ ጥይት እንደሞተ በሚነገረው የወረዳው ፖሊስ አባል ሳቢያ የታሰሩት ወጣቶች ለከፋ ጉዳት እንዳይዳረጉ ብዙዎች ስጋታቸውን በመግለጽም ላይ ናቸው፡፡ግጭቱ እየቀጠለ በነበረበት ኹኔታ ለጸሎተ ቅዳሴ የተሰበሰበውን ሕዝብ ለመበተን በሚል ፖሊስ በቤተ መቅደሱ የሰሜንና ደቡብ በሮች አስለቃሽ ጢስ ወደ ውስጥ መተኰሱ፤ በዚህም በመካሄድ ላይ የነበረው ጸሎተ ቅዳሴ ታጉሏል፤ ለቍርባን የተዘጋጁ ሕፃናት፣ ሌሎች ምእመናንና አገልጋዮችም ለሕይወት በሚያሰጋ ደረጃ ለአደጋ ተዳርገዋል፡፡ የሕንፃ ቤተ ክርስቲያኑ በሮችና መስኰቶች መንሥኤው ከፖሊስ በተተኰሱ ጥይት የተበሳሱ ሲሆን የደብሩ አስተዳደር ቢሮዎች፣ የጥምቀተ ክርስትና ቤትና ሌሎችም በሮች ‹‹የተደበቁ ሰዎችን ለማሰስ›› በሚል መዝጊያዎቻቸው እየተሰበረ ፍተሻ እንደተካሄደባቸው ተገልጧል፡፡

ከንቲባ ኩማ ደመቅሳና ‹የፓትርያሪኩ ልዩ ሀገረ ስብከት› በሚል ከሚታወቀው የአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት የረዳት ሊቀ ጵጵስና ሓላፊነታቸው እየለቀቁ ያሉት ብፁዕ አቡነ ቀውስጦስ በጉዳዩ ላይ በስልክ መነጋገራቸው ተሰምቷል፤ በግጭቱ አንድ ፖሊስ መሞቱንና ሌሎች አባላት መቁሰላቸውን ትኩረት በመስጠት በኀይለ ቃል ተናግረዋል የተባሉት ከንቲባ ኩማ የታሰሩት ምእመናን እንዲፈቱ ብፁዕ ሊቀ ጳጳሱ ያቀረቡላቸውን ጥያቄ እንዳልተቀበሉ ተሰምቷል፡፡ በግጭቱ የሰው ሕይወት ማለፉ የሚያሳዝንና መጣራት እንደሚገባው አስተያየታቸውን የሰጡ አባቶች÷ በጸሎት ቅዳሴው ካህናቱ ድርገት በሚወርዱበት ሰዓት የምእመናኑን ተማኅፅኖ ባለመቀበል፣ የቤተ ክርስቲያንን ክብር በመዳፈርና ሥርዐተ ቤተ ክርስቲያንን በመጣስ ፖሊስ በርካታ የአስለቃሽ ጢስ ተተኳሾችን ወደ ቤተ መቅደሱ መተኰሱ፣ ካህናቱንና ምእመናኑን ለጉዳት መዳረጉ በብርቱ እንዳስቆጣቸው ተናግረዋል፡፡

ግጭቱ ከቆመ በኋላ የደብሩ የክብረ በዓል (ንግሥ)ና መስቀል ደመራ ስፍራ የነበረውን ይዞታ የኮልፌ ቀራንዮ ክፍለ ከተማ ለመከለል የጀመረው ሂደት እንዲቆም ተደርጎ ለውዝግቡ መፍትሔ ለመስጠት በጠቅላይ ቤተ ክህነትና በአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት የተሠየመ የጋራ ኮሚቴ በመሥራት ላይ እንደሚገኝ ተመልክቷል፡፡

ጠዋት ሦሰት ሰዓት ግድም ተቀስቅሶ እስከ ምሽት አንድ ሰዓት የዘለቀው ግጭት ከመቀስቀሱ ቀደም ብሎ የአጥቢያው አስተዳደር፣ አገልጋዮችና ምእመናን በፖሊስ ታጅቦ የመጣውን ቡድን በባንዲራው እያሉ ሲማፀኑ ነበር፤ እነርሱ ራሳቸው ይዞታቸውን ለማስከበር በተደጋጋሚ ሲያመለክቱ እንደቆዩና አሁንም ከፓትርያሪኩ ጋራ እየተነጋገሩበት በመኾኑ ግብረ ኀይሉ ወደ ርምጃ ከመግባት እንዲከለከልና ሁለት ቀናት እንዲሰጣቸው ሲጠይቁም እንደነበር ተዘግቧል፡፡

ምእመናኑ የኢትዮጵያን ሰንደቅ ዓላማ ይዘው ለሚያቀርቡት ተማፅኖ ቦታ ያልሰጠው ቡድን÷ የቦታ መከለል ሥራ በመጀመሩ ምእመናኑ ርምጃውን ድንጋይ በመወርወር ሲከላከሉ የአድማ ብተና ፖሊስ ደግሞ በቆመጥና በአስለቃሽ ጭስ ምእመናኑን ለመበተን መሰማራቱ ተገልጧል፤ ጥይትም ተተኩሷል፡፡ የችካል ምልክቱ የሚያርፍበት ቦታ ከዐውደ ምሕረቱ ያለው ርቀት ከ30 - 50 ሜትር እንደማይበልጥ የዐይን እማኞች ተናግረዋል፡፡ የደብሩ አስተዳደር በዚህ ይዞታው ላይ የአንደኛ ደረጃ ት/ቤት ግንባታና ሌሎችንም የራስ አገዝ ልማት ትልሞች ዐቅዶ እየተንቀሳቀሰ እንደነበር ለመረዳት ተችሏል፡፡

በደብረ ይድራስ ቅዱስ ጊዮርጊስ ቤተ ክርስቲያን ችግሩ በዘገባው በተጠቀሰው ደረጃ እንዲባባስ ያደረገው እስከ ዐውደ ምሕረቱ የዘለቀው የይዞታ መንጠቅ ብቻ ሳይሆን÷ ቀደም ብሎ ክፍለ ከተማው የደብሩ ካህናት መኖሪያ ቤት ተሠርቶበት የነበረውን ቦታ በመውሰድ ክሊኒክ የክፍለ ከተማው መሬት አስተዳደር ጽ/ቤት ሲሠራበት በዝምታ በመታለፉ መሆኑን አስተየየታቸውን ለዜና ሰዎች የሰጡ የሰበካው ምእመናን ገልጸዋል፡፡ በኮልፌ ቀራንዮ ክፍለ ከተማ (ከፍተኛ 24 ቀበሌ 14÷ 59 ቁጥር ማዞርያ) አውግስታ ሸሚዝ ፋብሪካ አካባቢ የሚገኘው የደብረ ይድራስ ቅዱስ ጊዮርጊስ ቤተ ክርስቲያን 23 ዓመት በፊት፣ 1981 . የተመሠረተ ደብር ነው፡፡ ይድራስ የዱድያኖስ ጭፍሮች የሊቀ ሰማዕታት ቅዱስ ጊዮርጊስን ዐፅም ፈጭተውና አቃጥለው  የበተኑበት ተራራ ስም እንደኾነ ይታወቃል፡፡

በሌላ በኩል በአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት የሚገኙ 120 አድባራትና ገዳማት ከአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ፍትሕ ቢሮ በሚያዝያ ወር 2004 ዓ.ም የይዞታ ባለቤትነት ማረጋገጫ ካርታ መረከባቸው ተዘግቧል፡፡ ለአብያተ ክርስቲያኑ መንፈሳዊ አገልግሎት፣ ለሚያበረክቱት ማኅበራዊና ልማታዊ ተግባራት ትልቅ እገዛ በሚያደርገው በዚሁ የይዞታ ባለቤትነት ካርታ የጠበል፣ የመካነ መቃብር፣ የመስቀል ደመራ፣ የበዓለ ጥምቀት ማክበርያና የልማት ቦታዎቻቸው ሳይቀናነሱ እንዲከበሩላቸው መደረጉ ተገልጧል፡፡ የአዲስ አበባ ከተማን የወደፊት የዕድገትና ልማት አቅጣጫ ታሳቢ በማድረግ ከተማዋ በፕላን እንድትመራ የተጀመረው እንቅስቃሴ አካል መኾኑ የተመለከተው ይኸው የይዞታ ባለቤትነት ማረጋገጫ ተጠቃሚ ያደረገው ግን ከ1998 ዓ.ም የተሠሩትን አብያተ ክርስቲያን ብቻ እንደኾነ ተመልክቷል፡፡

ከከተማው አስተዳደርና ከጠቅላይ ቤተ ክህነቱ ተወጣጥቶ የተቋቋመው የጋራ ኮሚቴ የአብያተ ክርስቲያናትን ነባር ይዞታ ለመለየትና ለማረጋገጥ የጀመረውን ተግባር በመቀጠል ከ1998 ዓ.ም በኋላ ለተተከሉትም አድባራትና ገዳማት የይዞታ ባለቤትነት መስጠቱን እንደሚቀጥል ተገልጧል፡፡

የይዞታ ባለቤትነትን ማረጋገጥ ከጊዜው ቢዘገይም ሊበረታታና የሁሉንም አብያተ ክርስቲያን መብት በሚያስከብር አኳኋን መፈጸም የሚገባው ተግባር ነው እንላለን፤ ነገር ግን ኹኔታውን እንደ ምቹ አጋጣሚ በመውሰድ ከባለሀብት ነን ባይ ግለሰቦችና ድርጅቶች ጋራ በቤተ ክርስቲያንን መሬት ላይ እየተደራደሩ የግል ሀብት በማከማቸት ላይ እንዳሉ በሰፊው የሚወራባቸው የአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት ቁንጮ ሓላፊዎች በሙስና መዘፈቅ እያዩ ለተመሳሳይ ተግባር የተነሣሡ አንዳንድ የአድባራትና ገዳማት አስተዳዳሪዎች አካሄድ ግን ፈጽሞ ችላ ሊባል የማይገባው በመሆኑ ሂደቱ/አፈጻጸሙ በጥንቃቄ መታየት እንደሚገባው ደጀ ሰላም ታሳስባለች፡፡

ለአብነት ያህል፡- በየረር ቅድስት ሥላሴ ንቡረ እዱ ‹ራእይ ታየኝ› በሚል ለዓመታት እያጨበረበረ ከሚገኘው ቃሲም ከተባለ ግለሰብ ጋራ የገቡበት የጥቅም ግንኙነት፣ በገዳመ ኢየሱስ የቤተ ክርስቲያኑን መሬት ለግለሰብ ለማስረከብ ፓትርያሪኩ በአጥቢያው አስተዳደር ላይ የፈጠሩት ጫና፣ በኮተቤ ደብረ ልዑል ቅዱስ ገብርኤል የቤተ ክርስቲያኑን ይዞታ ለግለሰብ ጥቅመኞችና ለፕሮቴስታንታቶች ሳይቀር ተላልፎ በመሰጠቱ የአገልጋዩና ምእመኑ ቁጣ ተቀስቅሶ ችግር ከመፈጠሩ በፊት የየካ ክፍለ ከተማ በጉዳዩ እንዲያስብበት የወረዳው ፖሊስ ጽ/ቤት ያቀረበው ጥያቄ፣ ከአዲስ አበባም ውጭ በምሥራቅ ሸዋ ሀገረ ስብከት አድዓ ወረዳ የባቦጋያ ምሥራቀ ፀሐይ መድኃኔዓለም ቤተ ክርስቲያንን የታቦት ማደርያና መስቀል ደመራ ቦታ የፓትርያሪኩ ወዳጅ እንደኾነ የሚነገርለት የኩሪፍቱ ሪዞርትና ስፓ ባለቤትና ሥራ አስኪያጅ አቶ ታዴዎስ ጌታቸው በለጠ በሊዝ ጠቅልሎ ለመውሰድ የሚያደርገው ሙከራ ሊጠቀሱ ይችላሉ፡፡

ተጨማሪ ዜናዎችን ይከታተሉ
ቸር ወሬ ያሰማን፤
አሜን፡፡
3 comments:

Anonymous said...

'በግጭቱ አንድ ፖሊስ መሞቱንና ሌሎች አባላት መቁሰላቸውን ትኩረት በመስጠት በኀይለ ቃል ተናግረዋል የተባሉት ከንቲባ ኩማ ደመቅሳ...' ደጀሰላም:: ሃይለ ቃል ለተጎጂዋ ቤተክርስቲያን? ስርአቷ ተከብሮ የኖረው ጨካብኝ ተብሎ በሚነገርለት ጓድ ሊቀመንበር መንግስቱ እንኳን ያልተደፈረው ይህች ታላቅ ቤተክርስቲያን የተደፈረች መሆንዋ ሳያንሳት ለሃገራችን ባለውለታ ለሆነችው ለዚህች ቅድስት ቤተክርስቲያን ሃይለ-ቃል ይገባታልን? ፖሊሱ በመሞቱ: ሰዎችም በመጎዳታቸውና በመታሰራቸው በጣም እናዝናለን:: ህይወቱ ያለፈው ፖሊስ እግአብሔር ለነፍሱ ምህረትን ሰጥቶ በገነት እንዲያሳርፋት ጾሎታችን ነው:: ፖሊሱ ነፍሱ ያለፈው በሌላ ፖሊስ ለህዝብ በተተኮሰ ጥይት መሆኑን ግን ትምህርት እንዲሆነን መዘንጋት የለብንም:: ያ ደግሞ የእግዚአብሔር ቁጣ ላለመሆኑና ሌሎችም በቤተክርስቲያን ላይ እጃቸውን የሚያነሱባት ሁሉ በራሳቸው መሳርያ ወይም በሌላ አይነት መቅሰፍት የማያልቁ ላለመሆናቸው እርግጠኞች አይደለንም:: በርግጠኝነት የምናውቀው ነገር ቢኖር እግዚብሔር ለምህረት የሚፈጥነውን ያህል ለቁጣ የማይፈጥን መሆኑንና ለቤቱ ግን ቀናተኛ አምላክ መሆኑን ብቻ ነው:: በቤቱ የሚፈጸምን ማንኛውንም ስርአት አልባ የሆነን ነገር አያልፈውም:: የምህረት አምላክ በመሆኑ የቁጣ በትሩን በቶሎ አያሳርፍብን ይሆናል እንጂ መቼም ቢሆን ግን ከቅጣቱ አናመልጥም:: ለአቶ ኩማ ደመቅሳና ለመንግስት ማለት የምፈልገው ቢኖር ያ የቁጣ በትር ከፈጣሪ ከመምጣቱ በፊት እጃችንን ከቤተክርስቲያን ላይ እንድናስወግድ ነው:: የቁጣ በትሩ የተላከ ቀን ግን መዘዙ ለሁላችንም ይተርፋል:: አሁንም እባካችሁ ይህችን ቤተክርስቲያን ተዉዋት::

Anonymous said...

Please correct the date it was Ginbot 28/2004 not Ginbot 27/2004

asbet dngl said...

አባት ሆይ በዝች አገር ላይ ዝምታህ በዛ ልበልህ ይሆን? ምነው የምህረት ፍርድህ ቅርብ ቤሆንልን?? ስለአገር᎒ ስለአለም᎒ ስለምእመን ጫማቸውን አውልቀው መጸለይ የሜገባቸው አባት እስቴ አሁን ከመሬት ስጦታ ምን እግር ጣላቸው?ይገርማል::
የድንግል ልጅ እባክህን እችን አገርና ሐይማኖት ጠብቅ:: አሜን!

Blog Archive

የአቡነ ጳውሎስ "ሐውልተ ስምዕ"

ነጻ ፓትርያርክ ምርጫ ቢሆን ኖሮ ማንን ይመርጡ ነበር? እንበልና ሁሉም ነገር ሥርዓቱን ጠብቆ የተከናወነ የእጩዎች ምርጫ ቢሆን ኖሮ፣ አሁን የምናነሣቸው ጉድለቶች ባይኖሩ ኖሮ፣ 6ኛው ፓትርያርክ እንዲሆን የምትመርጡት ማንን ነበር? (ማሳሰቢያ፦ አሁን ያለው ክፍፍል እና የመንግሥት ተጽዕኖ ባይኖር ኖሮ ተብሎ የሚመለስ ጥያቄ ነው። የምን “ባይኖር ኖሮ ነው” የሚል አስተያየት ካለዎትም እናከብራለን።)