May 17, 2012

ማ/ቅዱሳን በዋልድባ አካባቢ ስለሚገነባው የስኳር ፕሮጄክት “መልካምነት” ባለመዘገቡ ተጠየቀ፤ መልስ እንዲሰጥ ይጠበቃል


(ደጀ ሰላም፤ ግንቦት 9/2004 ዓ.ም፤ May 17/ 2012/ READ THIS IN PDF)፦ ማ/ቅዱሳን መንግሥት በዋልድባ አካባቢው ሊሠራው ስላቀደው ግዙፍ የስኳር ሮጄክት “መልካምነት” ባለመዘገቡ ሊወነጀል ነው። አዲስ በተሾሙት የሰንበት ት/ቤቶች ማ/መምሪያ ኃላፊ በመምህር ዕንቁ ባሕርይ ተከስተ ተፈርሞ የወጣውና “በዋልድባ አካባቢ መንግሥት ሊሠራ ያቀደውን ግዙፍ የስኳር ፋብሪካን በማስመልከት በዋልድባ ይዞታ ላይ ያደረሰው ተጽእኖ መኖር አለመኖሩን የሚያጣራ ኮሚቴ ተቋቁሞ ከሚመለከታቸው አካላት ጋር ሁሉ ተፈላጊውን የማጣራት ሥራ አከናውኖ” ከተመለሰ በኋላ “ጋዜጣዊ መግለጫ መሰጠቱና … የማኅበረ ቅዱሳን ጋዜጠኞች መከታተላቸው መሣተፋቸውና የሚፈልጉትን ጥያቄ በይፋ አቅርበው ምላሽ መሰጠቱ”ን በመጥቀስ ይጀምራል።


አስከትሎም “ስለሆነም ማንኛውም ጋዜጠኛ በተለይም ደግሞ የቤተ ክርስቲያኒቱ ልሣን የሆነው የማኅበሩ ጋዜጣና መጽሔት መረጃ ከወሰደ በኋላ መግለጫውን አለማውጣቱ አግባብነት የሌለው ከመሆኑም በላይ የሚዲያ ሥነ ምግባርንም ያልተከተለ ስለሆነ” ጽሑፉ ያልወጣበትን ምክንያት ማኅበሩ በጽሑፍ ይገልጽ ዘንድ ከሕዝብ ግንኙነት መምሪያ መታዘዙን ያብራራል።
የመምሪያው ደብዳቤ አክሎም “ጋዜጣዊ መግለጫውን በሚዲያ ለማውጣት ተስማምታችሁ ሪፖርት እንድታደርጉ ከወሰናችሁ በኋላ ዘገባው የቀረበት ምክንያት በጽሑፍ ለማደራጃ መምሪያው” እንዲመለስ እንደሚጠብቅ ይገልጻል። ደብዳቤው በአድራሻ ለማኅበሩ ከተላከ በኋላ ደግሞ ለቤተ ክህነቱ የተለያዩ አካላትና በመንግሥትም በኩል “ለፌዴራል ጉዳዮች ሚኒስቴር፣ ለብሔራዊ ደኅንነት አገልግሎትና ለፌዴራል ፖሊስ ኮሚሽን” ግልባጭ ተደርጓል።

የቅ/ሲኖዶስ ጽ/ቤት፣ የብፁዕ ወቅዱስ ፓትርያርክ ልዩ ጽ/ቤት. የመንበረ ፓትርያርክ ጠቅላይ ጽ/ቤት፣ የሕዝብ ግንኙነት መምሪያ እና ሕግ አገልግሎት መምሪያ የቤተ ክርስቲያናችን አካላት ስለሆነ በቀጥታም ባይሆን ጉዳዩ ሊያገባቸው ይችላል። ከላይ ስማቸው የተዘረዘሩት የመንግሥት መሥሪያ ቤቶች በምን አግባብ ነው ስለ አንድ ማኅበር፣ ያውም በአንድ መምሪያ ሥር ስላለ አካል ግልባጭ የሚደረግላቸው? መንግስታዊ መሥሪያ ቤቶቹ ከሚዲያ ጋር የተገናኙ እንኳን ቢሆኑ በግድምድሞሽ “ግንኙነት አላቸው” ይባል ይሆናል። ፌዴራል ጉዳዮች፣ ደኅንነት፣ ፖሊስ … መጠቀሳቸው ለምን ያስፈልጋል? እሰሩልን፣ ግደሉልን፣ ቀፍዱድልን ለማለት ካልሆነ።

በእውነት በአገሩ ሕግ የለም ማለት ነው? በየትኛው አገር ነው አንድ ጋዜጠኛም ሆነ የሚዲያ ተቋም ስለዘገበው ሳይሆን ስላልዘገበው ነገር የሚጠየቀው? ስለጻፈው ሳይሆን ሳይጽፍ ስለቀረው የሚፈረድበት? ይህ በዓይነቱ በየትም ዓለም ታይቶም ተሰምቶም የማይታወቀው ክስ መጨረሻው ምን እንደሚሆን ለማወቅ በጣም ያጓጓል። ደብዳቤው “የጋዜጠኝነት ሥነ ምግባርን ማጉደል” ያለውን ይህንን ላልጻፉት ጽሑፍ የመወንጀልን ጉዳይ በዓለም የጋዜጠኝነት ታሪክ ውስጥ በብቸኝነቱ ሊያስመዘግብ የሚችለውን ጉዳይና ውጤቱን ወደፊት የምናየው ይሆናል።

ብራቮ ቤተ ክህነት!!!!!

ቸር ወሬ ያሰማን፣
አሜን


ቸር ወሬ ያሰማን፤ አሜን
Post a Comment

Blog Archive

የአቡነ ጳውሎስ "ሐውልተ ስምዕ"

ነጻ ፓትርያርክ ምርጫ ቢሆን ኖሮ ማንን ይመርጡ ነበር? እንበልና ሁሉም ነገር ሥርዓቱን ጠብቆ የተከናወነ የእጩዎች ምርጫ ቢሆን ኖሮ፣ አሁን የምናነሣቸው ጉድለቶች ባይኖሩ ኖሮ፣ 6ኛው ፓትርያርክ እንዲሆን የምትመርጡት ማንን ነበር? (ማሳሰቢያ፦ አሁን ያለው ክፍፍል እና የመንግሥት ተጽዕኖ ባይኖር ኖሮ ተብሎ የሚመለስ ጥያቄ ነው። የምን “ባይኖር ኖሮ ነው” የሚል አስተያየት ካለዎትም እናከብራለን።)