May 15, 2012

የኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያን ከመቸውም በባሰ ሁኔታ 'አደጋ' የሚለው ቃል የማይገልጠው አደጋ ላይ ነች


(ጌታቸው በቀለ/ ኦስሎ/ http://gudayachn.blogspot.com/ PDF)
መግቢያ
«ተዋሕዶ» ከልሣነ ግእዝ የመነጨ ቃል ሲሆን፡ ትርጒሙም «አንድ ሆኖ» ማለት ነው።  በኦርቶዶክስ ተዋሕዶ አብያተ ክርስትያናት ቃሉ  የክርስቶስ ባሕርይ በ«ሰብዓዊ» እና በ«መለኮታዊ» ተለይቶ ሳይሆን መለኮት ከስጋ ጋር ተዋሃደ - አንድ ሆነ  ማለት ነው።


በ443 ዓ.ም. (451 እ.ኤ.አ.) በሮማው ንጉሥ መርቅያን ዘመነ መንግሥት 650 ኤጲስ ቆጶሳት በተገኙበት የተሰበሰበው የኬልቄዶን ጉባኤ ከሮማው ሊቀ ጳጳሳት ቀዳማዊ ልዮን "ክርስቶስ ሁለት የተለያዩ ባሕርያት አሉት" የሚል ጽሑፍ አቅርቦላቸው ነበር። ዳሩ ግን የእስክንድርያው ፓትርያርክ ቅዱስ ዲዮስቆሮስ "ጌታ ሁለት ባሕርያት አሉት" የሚለው ትምሕርት ስሕተት ነው ብሎ ልዮንን አውገዘው። ከዚያን ጊዜ ጀምሮ ሁለቱ አብያተ ክርስቲያናት በእምነት ተለያዩ። የቅዱስ ዲዮስቆሮስን ትምሕርት የሚከተሉ ዛሬ የአርሜኒያ፣ የሕንደ፣ የግብጽ፣ የሶርያ፤ የኤርትራ እና የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ አብያተ ክርስትያናት ናቸው። የቤተክርስቲያን መመስረት በኢትዮጵያ የተጀመረው በ ቅዱስ ፊልጶስ መሆኑ ይታወሳል (ሐዋርያት ምዕራፍ 8)፦ «እነሆም፥ ህንደኬ የተባለች የኢትዮጵያ ንግሥት አዛዥና ጃንደረባ የነበረ በገንዘቧም ሁሉ የሰለጠነ አንድ የኢትዮጵያ ሰው ሊሰግድ ወደ ኢየሩሳሌም መጥቶ ነበር...» (ሐዋርያት ምዕራፍ 8)። በዚህ ንባብ ዘንድ ፊልጶስ ጃንደረባውን  በክርስትና አጠመቀው። ንግሥት ግርማዊት ህንደኬ 7ኛ ከ34 ዓ.ም. እስከ 44 ዓ.ም. ገደማ በኢትዮጵያ የነገሡ ናቸው።

በ4ኛ ምዕተ ዘመን በወንድማማቾቹ በንጉሥ ኤዛና እና በንጉሥ ሳይዛና ዘመን በፍሬምናጦስ አማካይነት ክርስትናየኢትዮጵያ ይፋዊ ሃይማኖት ሆነ። ይህ ፍሬምናጦስ በኢትዮጵያ «አባ ሰላማ ከሣቴ ብርሃን» ተብሎ ይታወቃል። በወጣትነት ዕድሜው ከአጎቱ ከፈላስፋው ከመሮፔዎስ እና ከወንድሙ ከሲድራኮስ ጋራ መርከባቸው ስለሰመጠች ከወንድሙ ጋር ከሞት ተርፈው ምጽዋ አጠገብ ተገኙ። ወደ ንጉሦቹም ግቢ አመጡዋቸውና ቀስ በቀስ ከፍተኛ ተጽእኖ ያለበት ደረጃ አገኙ። ንጉስ ኤዛና ደግሞ ወደ ክርስትና ለውጠው እንዲጠመቁ አደረጉ። ኤዛና ፍሬምናጦስን ለኢትዮጵያ አቡነ እንዲሾም ለመጠይቅ ወደ እስክንድርያ ላኩዋቸውና የእስክንድርያ ጳጳስ አትናቴዎስ ፍሬምናጦስን ሾሞ ላከው። ፍሬምናጦስ የመጀመሪያው የኢትዮጵያ ሊቀ ጳጳስ ሲሆን የመጀመሪያው ኢትዮጵያዊ ፓትርያርክ አቡነ ባስልዮስ ደግሞ 111ኛው መሆናቸው ነው።

'አደጋ' የሚለው ቃል የማይገልጠው አደጋ
ባለፈው ሳምንት የተጀመረው በገር ቤት የሚገኘው ቅዱስ ሲኖዶስ እንደተለመደው አሳዛኝ ዜናዎች እየተነበቡበት ጉባዔውን ጀምሯል። ካለፉት ሶስት ተከታታይ ዓመታት ወዲህ ቅዱስ ሲኖዶስ አግባብነት የሌላቸውን የ ፓትሪያሪኩ ድርጊቶች በ አደባባይ በመኮነን እና ውሳኔ በማሳለፍ ላይ በመሆኑ ከፍተኛ መዋከብ ውስጥ ሆን ተብሎ እንዲገባ እየተደረገ ነው። አሁን ፍንትው ብለው የሚታዩ አደጋዎች ከመቸውም ወቅት በላይ በ ቤተ ክርስቲያን ላይ እያንዣበቡ ነው። የወቅቱ የ ቤተ ክርስቲያን አደጋ መገለጫዎች፣አደጋው በ ቤተ ክርስቲያን ላይ እና በ ሃገር ላይ የሚያመጣው መዘዝ ምን ሊሆኑ ይችላሉ? መፍትሄዎቹስ?

1/ የወቅቱ የ ቤተ ክርስቲያን አደጋ መገለጫዎች
·         ልክ ያጣ ሙስና፣
·         እግዚርን የማይፈሩ፣ ሰውን የማያፍሩ  የቤተ ክርስቲያንን አስተዳደር የፕትርክናውን ስልጣን ሳይቀር መያዛቸው፣
·         እነኚሁ እግዚአብሔርን የማይፈሩ፣ሰውን የማያፍሩቱ በተለይ ባለፉት ሃያ አመታት የ መንግስት የ ካድሬ ካባ ለብሰው ከ ሹመኞች ጋር በመሞዳሞድ ከስራቸው ሌሎች መሰሎቻቸውን በብዛት ወደ ቤተ ክርስቲያን መዋቅር( ከ አጥብያ ጀምሮ እስከ መንበረ ዽዽስና ድረስ) ማስረግ መቻላቸው፣
·         የነበረውን የ ቅድስት ቤተ ክርስቲያን አስተምሮ ለመበረዝ የተነሱ ጸረ ተዋህዶ ቡድኖች፣
·         ይህ ቡድን በ ቤተ ክርስቲያን ገንዘብ እርስ በርሱ ሲጎራረስ የከረመ ከመሆኑም በላይ በገንዘቡ የማፍያ ቡድን ለማደራጀት ሁሉ የቻለ መሆኑ። ለምሳሌ የመጎራረሱ መታወቂያዎች ለ ፓትሪያሪኩ 'ጥይት የማይበሳው መኪና አጥብያ አብትያተ ክርስቲያናት' ገዙላቸው ብሎ ከመሳለቅ ጀምሮ ከ ሶስት መቶ ሺህ ብር በላይ የሚያወጣ ሃውልት ከ ስርዓተ ቤተ ክርስቲያን ውጪ በ ቦሌ ደብረ ሳሌም መድሃኔ ዓለም፣መጥምቀ መለኮት ወ አቡነ አረጋዊ ቤተ ክርስቲያን እስከመስራት የደረሰ ታላቅ ድፍረት የሚሉት ይጠቀሳሉ።

2/  በዝምታ የተፈታ ችግር የለም!

ላለፉት ሃያ ዓመታት  በ ቤተ ክርስቲያን ላይ የደረሱት አስነዋሪ አስተዳደራዊ ብልሹነት እና ሃይማኖታዊ መዳፈሮች የሚከተሉትን መዘዞች እንደሚያስከትሉ ሳይታለም የተፈታ ነው። መዘዙን ስላላወራነው የማይመጣ መስሎን እጅ እና እግራችንን አመሳቅለን የተቀመጥን ካለን እንደተሳሳትን መረዳት አለብን።አሁን በ ቤተ ክርስቲያን ላይ የደረሰው በዝምታ ከታየ ነገ ሊደርስ ከሚችለው ጋር ሲነጻጸር ኢምንት አይሆንም ብሎ የሚናገር ማን ሊኖር ይችላል?

ቀደም ብሎ በሁለት ሲኖዶስ ግራ የተጋባችው  ቤተ ክርስቲያን  ይብሱን በገር ቤት ያለውን ሲኖዶስ ለሁለት በተለያየ መንገድ ለመክፈል (በአባቶች ጽናት እና በእግዚአብሔር ቸርነት ከሸፈ እንጂ) በየቅዱስ ሲኖዶስ ጉባዔያት ላይ የታየ እውነታ ነው። ይህ ሙከራ ግን ከ አሁን በሁዋላ ገዝፎ እና 'የ እምነት ነጻነት' በሚሉ ሃረጎች ተሸፍነው አስገራሚዎቹ የ ልደታ በታች ፍርድ ቤቶች አይወስኑም ማለት ካለፈው ተሞክሮ አለመማር ብቻ ሳይሆን ቸልተኝነትም ጭምር ነው ሊያሰኝ ይችላል። ይህ ሁኔታ ደግሞ የ ክልል መንግስታት እስኪገነጠሉ መብታቸው ነው ተብሎ በድፍረት በሚነገርባት 'አስደናቂት' ሃገር ውስጥ አይደረግም ብሎ ማለት አይቻልም። 'አንተ እምነትህን ልትጭንበት ነው?' የሚሉ  ቃላት እየተጠቀሙ ቤተ ክርስቲያንን የመክፈል አዝማሚያዎች ሊኖሩ እንደሚችሉ መገመት እና ከመሆኑ በፊት ዛሬ ላይ ሆኖ ተው የሚባለው ተው መባል ያለበት ጊዜ ነገ ሳይሆን አሁን ነው።

3/መፍትሄዎቹ በማን እጅ ናቸው?

በሃይማኖት ከሚመለከው አምላክ በላይ መፍትሄ ለጋሺም ሆነ ነሺ የለም። ይህ ሁሉንም ያስማማል። እግዚብሔር ግን የሚሰራበት ሰው ይፈልጋል። ነዳያን የ እለት ጉርስ የ አመት ልብስ እንዲመጸወቱ ያደረገው በ አንዲት ቀን ሃብታም ማድረግ አቅቶት አይደለም። ወይንም የሚሰጠው ጎድሎበት አይደለም። ነገር ግን ለ እኛ መፈተኛ ብሎም መጽደቅያ መንገድ ሲያመቻችልን እንጂ። ስለ እዚህ የ እግዚአብሔር ራ የመኖሩን ያህል የሰውም ራ አለ ማለት ነው። አልአዛርን ከሞት ማስነሳት የአምላክ ራ የመቃብሩን ድንጋይ ማንሳትና መግነዙን መፍታት የሰው ስራ እንደሆነ ሁሉ።

በሊቃነ ጳጳሳት እጅ ያሉ መፍትሔዎች

ከሁሉም በላይ የ እግዚአብሔርን አደራ ተቀብለው  ምዕመኑን የመምራት አደራ የያዙት ሊቃነ ጳዻሳት ወሳኝ እና እጅግ ቁልፍ የሆነ ወቅት ላይ መሆናቸውን መረዳት አለባቸው። ቤተክርስቲያን ዛሬ የገጠማት ጠላት ከቀደሙት የሚለየው ፊት ለፊት ያፈጠጠ ሳይሆን በ ሰላ አካሂያድ መነሻ እና ግብ አስቀምጦ የሚንቀሳቀስ አውሬ መሆኑ ነው። ለእዚህ ነው ከመስዋዕትነት ያላነሰ ዋጋ መክፈልን መጠበቅ አባቶቻችንን ማዘናጋት የሚሆነው።

ጽድቅና ኩነኔን በሚያምኑ ባለ ልጣናት እጅ ያሉ መፍትሔዎች

አንድ ወጣት የቤተ ክርስቲያን ተመራማሪ አንድ ጊዜ ሲናገር ''ኢትዮዽያን ይበልጥ ባወቅናት ቁጥር ይበልጥ የምታንገበግብ ሃገር ናት'' ማለቱን አልዘነጋውም። የኢትዮዽያ ቤተ ክርስቲያን ለገሪቱ ያለፈ ታሪክም ሆነ አሁን ላለችበት እሷነቷ፣ ክብርዋና ሞገስዋ ወሳኝ ሚና ያላት መሆኑን ተረድታችሁ ለእውነት የምትቆሙበት፣ በጽድቅ እና ኩነኔ መሃል ያለውን ልዩነት ያህል ያፈጠጠ መሆኑን ልትረዱ ይገባችኋል። በተሳሳተ መንገድ በስውር እጃቸውን በቤተ ክርስቲያን ላይ ያሳረፉ ሁሉ እንዲያነሱ ማገዝ እና በስውር በ አጀንዳነት የተያዙ አጀንዳዎችም ለ ህዝብ ይፋ እንዲሆኑ ማድረግ ይገባል።

በምዕመኑ እጅ ያሉ መፍትሄዎች

የኢትዮዽያ ኦርቶዶክስ ተዋዶ ቤተ ክርስቲያን ምዕመናን የችግሩ ገፈት ቀማሾች ስለሆኑ የማያውቁት ጓዳ ጎድጓዳ የለም። አሁን በመፍትሄነት እንደዚህ አስቡ ሳይሆን አሁን አድርጉ ማለት ብቻ ነው አስፈላጊው።

ምዕመናን ምን ያድርጉ?
· በየአጥቢያቸው መፍታት ያሉባቸውን መለስተኛ አለመግባባቶች መፍታት፣
· የሰንበት ትምህርት ቤቶች በመረጃ፣ በጉልበት፣ ወቅቱ በሚፈልገው ሁሉ ለመገኘት እና ቤተ ክርስቲያናቸውን ለመታደግ ወስነው መነሳት፣
· ባለማወቅ የሚያጠፋውን አውቆ ከሚያጠፋው መለየት፣
· የምግባር ችግር ያለበትን የ ሃይማኖት ችግር ካለበት መለየት እና እንደየችግሩ ስፋት እና ግዝፈት በ ሁሉም አጥቢያዎች ቅራኔዎችን ማምከን፣
· በመጨረሻም በ ቅድስት ቤተ ክርስቲያን ላይ የሚነሱ ችግሮችን በ አንድነት እንደ አንድ ቃል ተናጋሪ እንደ አንድ ልብ መካሪ ሆኖ መመከት ብሎም ቤተ ክርስቲያንን ለሚመጣው ትውልድ ከ እነ ክብር እና ማዕረጓ ማስተላለፍ።

ይቆየን

 መግቢያ ማጣቀሻየቤተ ክርስቲያን ታሪክ ከሉሌ መልአኩ፤ ሦስተኛ እትም - ፲፱፻፹፮ ዓ.ም

Post a Comment

Blog Archive

የአቡነ ጳውሎስ "ሐውልተ ስምዕ"

ነጻ ፓትርያርክ ምርጫ ቢሆን ኖሮ ማንን ይመርጡ ነበር? እንበልና ሁሉም ነገር ሥርዓቱን ጠብቆ የተከናወነ የእጩዎች ምርጫ ቢሆን ኖሮ፣ አሁን የምናነሣቸው ጉድለቶች ባይኖሩ ኖሮ፣ 6ኛው ፓትርያርክ እንዲሆን የምትመርጡት ማንን ነበር? (ማሳሰቢያ፦ አሁን ያለው ክፍፍል እና የመንግሥት ተጽዕኖ ባይኖር ኖሮ ተብሎ የሚመለስ ጥያቄ ነው። የምን “ባይኖር ኖሮ ነው” የሚል አስተያየት ካለዎትም እናከብራለን።)