May 7, 2012

በዋልድባ ጉዳይ ደብዳቤዎች ለቅ/ሲኖዶስ እና ለጠ/ሚኒስትሩ ተላኩ


(ደጀ ሰላም፤ ሚያዚያ 30/2004 ዓ.ም፤ May 8/2012/ READ THIS ARTICLE INPDF)፦ “ዋልድባን ለመታደግ የሚንቀሳቀስ ዓለም አቀፍ ጊዚያዊ ኮሚቴ” የተሰኘ ስብስብ “ታሪካዊ የዋልድባ ገዳማችን ይዞታና የመነኮሳት ሰብዓዊ መብት” ይከበር ሲል ጥያቄውን ለቅ/ሲኖዶስ እና ለጠ/ሚኒስትር መለስ ዜናዊ አቅርቧል። መቀመጫውን በዋሺንግተን ዲሲ ያደረገው እና ከዚህ በፊት ዋሺንግተን ዲሲ በሚገኘው የኢትዮጵያ ኤምባሲ ፊት ለፊት ታላቅ ሰላማዊ ሰልፍ ያዘጋጀ ኮሚቴ ሲሆን የላካቸውን ሁለት ደብዳቤዎች ከዚህ በታች ያንብቡ። ፒ.ዲ.ኤፍ ማንበብ ለሚፈልጉ በስተመጨረሻ ማግኘት ይቻላል።
ቸር ወሬ ያሰማን፣ አሜን

ደብዳቤ አንድ፦ ለጠቅላይ ሚኒስትሩ የተላከ (PDF)
ለአቶ መለስ ዜናዊ
ለኢ.ፌ.ዲ.ሪ. ጠቅላይ ሚኒስቴር
አዲስ አበባ

ጉዳዩ  ፦  ታሪካዊ  የዋልድባ ገዳማችን ይዞታና  የመነኮሳት ሰብዓዊ መብት  እንዲከበርልን  ስለመጠየቅ
የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ለኢትዮጵያ ታሪክ ማኅበራዊና ሥነ- ጥበብ እድገት ያበረከተችው  አስተዋጽዖ ከኢትዮጵያ አልፎ በመላው ዓለም የሚታወቅ አውነታ ነው ። ቤተ ክርስቲያናችን ባላት  ታሪክና መንፈሳዊ  ሀብት ለበርካታ ቱሪስቶች ወደ ኢትዮጵያ መምጣት ትልቁን ድርሻ የምትይዝ ሲሆን  በዚህም መንግሥትንና የተለያዩ ተቋማትን ተጠቃሚ እያደረገች ስትገኝ ፤ ወደ ኢትዮጵያ የሚመጡ ቱሪስቶችም በዋነኛነት የቤተ ክርስቲያናችንን  ጥንታዊያን ገዳማት አድባራት እና እንደ ጥምቀት መስቀል/ደመራ/ እና ልደት የመሳሰሉ ታላላቅ በዓላት መንፈሳዊ  አከባበርን ለመመልከት እንደሚመጡ   ዘወትር የሚመሰክሩት ነው ።  በአጠቃላይ  ለኢትዮጵያ ማኅበራዊ  ኢኮኖሚያዊ እና ሥነ ጥበብ እድገት ያበረከተችውን አስተዋጽዖ በየትኛውም ዘመን የነበረ እና ወደፊትም የሚኖር  በመሆኑ የኢትዮጵያ መንግሥት ይዘነጋዋል ብለን አንጠብቅም። በተለይም አሁን አገሪቱን እያስተዳደረ ያለው መንግሥት  የባህልና ቱሪዝም ኮሚሽንን የበለጠ አጠናክሬ እሰራለሁ ብሎ በተነሳበት ፤ በዚህ ሰዓት  የኢኮኖሚ ተጠቃሚ የሆነባትን ቤተ ክርስቲያን ገዳማቷ እና  አድባራቷ እንዲጠበቁ ማድረግ  መንግሥታዊ  የአስተዳደር ኃላፊነቱ ነው ።
ከተወሰኑ ዓመታት ወዲህ ከፍተኛ ጥቃት በኢትዮጵያ ገዳማትና አድባራት እንዲሁም ሕዝበ ክርስቲያኑ ላይ መድረሱ ፤ በወቅቱም መፍትሔ ሳይገኝላቸው እየተባባሱ መምጣታቸው የእምነቱን ተከታዮች የበለጠ እያሳሰበን መጥቷል።  በእነዚህ ገዳማት እና አድባራት ላይ እየደረሰ ያለው ጉዳት እንዳይከሰት ማድረግ ፤ ጥፋቱን ያከናወኑ ሰዎችም በወቅቱ ፍርድ እንዲያገኙ  አለመደረጉ ፤ መንግሥትም የቤተ ክርስቲያንን ይዞታ እና መብት በመጠበቅ ለሌሎች ጭምር ምሳሌ መሆን ሲገባው አገርን ለማስተዳደር ከወሰደው ኃላፊነት  አንጻር የተከሰቱትን ችግሮች ስንመለከት በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ  መንገድ መንግሥትን ተጠያቂ እንደሚያደርገው አምነንበታል ። አንድን መንግሥት ትክክለኛ መንግሥት  የሚያሰኘው ከሚያስተዳድራቸው ሕዝቦችና የሃይማኖት ተቋማት የሚቀርቡትን  አቤቱታ  ሰምቶ በወቅቱ ትክክለኛ ፍርድ እና አስተዳደራዊ ውሳኔ በመስጠት እንጂ የሚመራው ሕዝብና የሃይማኖት ተቋማት እንዲሰቀቁ  የሚያደርግ ምላሽና እርምጃ በመውሰድ አይደለም ።  የሕዝብን ድምጽ አለመስማት ፤ የቤተ ክርስቲያንንም አቤቱታ አለመቀበል  ትዕግሥትን የሚፈታተን ፤ መፍትሔ ካልተሰጠውም ወደ አልተፈለገ አቅጣጫ ነገሮች እንዲሔዱ  የሚያደርግ፡ አገርን የሚጎዳ፡ ታሪክንም የሚያበላሸ ክስተትን መሆኑ ሊታወቅ ይገባል ። እኛም ይህንን ደብዳቤ የምንጽፈው መንግሥት አገርን  የማስተዳደር ኃላፊነት ያለበት መሆኑን በመገንዘብና በኢትዮጵያ ገዳማትና አድባራት ላይ እየደረሰ ያለው ጥቃት በአስቸኳይ እንዲቆም ለመጠየቅና የተሰማንን ሐዘን በምሬት  ለመግለጽ ነው ።
ይህ ችግር ከተከሰተበት ጊዜ ጀምሮ በሰሜን አሜሪካ እና በተለያዩ ዓለማት የምንገኝ  የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን እምነት ተከታዮች በየሳምንቱ በስልክ እንዲሁም በአካል በመገናኘት ይህንን አሳሳቢ ጉዳይ በመነጋገር ላይ  እንገኛለን። ይህንን ጉዳይ ለማሳሰብ በአሜሪካና ካናዳ የተለያዩ ግዛቶች በርካታ የኦርቶዶክስ ተዋሕዶ እምነት ተከታዮች በተገኙበት በኢትዮጵያ ኤምባሲ ፊት ለፊት እና ጉዳዩ በሚመለከታቸው ዓለማቀፋዊ ተቋማት ቢሮዎች ሰላማዊ ሰልፍ አድርገናል። አሁንም ጉዳዮን  ለኢትዮጵያ መንግሥትና  ለተለያዩ ዓለም አቀፍ ተቋማት ለማሳሰብና የዋልድባ ገዳም የቦታ ይዞታ  እና የመነኮሳትም ሰብዓዊ መብት እንዲከበር ግንቦት 27 ቀን 2004 ዓ. ም በአሜሪካና በካናዳ የተለያዩ ከተሞች ሰላማዊ ሰልፍ ጥሪ ተላልፏል ።
የዋልድባ ገዳም መነኮሳት እያቀረቡ ያለውን አቤቱታ  ትኩረት ሳይሰጠው የተከበረው የቅድስና ቦታ ለልማት በሚል ሰበብ መንፈሳዊ ስሜትን በሚጎዳና ለቤተ ክርስቲያን  እየተሰጠ ያለውን ንቀት በሚያመላክት ደረጃ በመንግሥት ጭምር አሳዛኝ ምላሽ መሰጠቱ  ከፍተኛ ቁጣ  ፈጥሮብናል ። ስለዚህ የሚከተሉትን ጥያቄዎች ለኢትዮጵያ መንግሥት ስናቀርብ  ለጥያቄዎቻችን ዘላቂ መፍትሔ እንደሚሰጠን ተስፋ በማድረግ ነው ፦
  1.    የዋልድባ ገዳም የኢትዮጵያውያን ሁሉ መንፈሳዊ ሀብትና የተቀደሰ ቦታ በመሆኑ የገዳሙ መነኮሳት ባቀረቡት አቤቲታ መሠረት  የገዳሙ ክልል በማንኛውም ወገን እንዳይደፈርና ለልማታዊ ተግባር በሚል ሰበብ  የተጀመረው የወልቃይት ስኳር ፋብሪካ ፕሮጀክት እንቅስቃሴ አሁን ባለበት ቦታ በከፍተኛ ሁኔታ ሃይማኖታዊ ህልውናችንን ስለሚዳፈር በአስቸኳይ እንዲቆምልን እና ከገዳሙ ክልል ወደ ሌላ ቦታ እንዲዛወር እንጠይቃለን ፤
  2.    የኢትዮጵያ ገዳማት እና አድባራት ለኢትዮጵያውያን ሁሉ መንፈሳዊ ሀብትና የቅድስና ቦታዎች ስለሆኑ የቦታ ይዞታቸው በማንም እንዳይደፈር ማረጋገጫ  በመንግሥት  እንዲሰጥ፤
  3.    በኢትዮጵያ ገዳማትና አድባራት እና ክርስቲያኖች  ላይ የሚደርሰው ጉዳት በግልጽ በመንግሥት መገናኛ ብዙኃን አንዲዘገብ ፤
  4.    የቤተ ክርስቲያንን መልካም ስም በሚያጎድፍ መልኩ ጥላቻቸውን የሚያንጸባርቁ የመንግሥት ባለሥልጣናት    ከዚህ ተግባራቸው ተቆጥበው  ሕዝቡን  በትክክለኛ አስተዳደር እንዲመሩ  እንዲደረግልን ፤
  5.     የቤተ ክርሰቲያንን መብት ለማስጠበቅ የሚንቀሳቀሱ አባቶች እና ክርስቲያኖቸ ላይ ዛቻና አንግልት እንዲቆም እንጠይቃለን ።
  6.    በመንሥት ባለስልጣናት ገዳማውያኑ ላይ የተለየ የፖለቲካ ተልዕኮ ያላችሁ ናችሁ በሚል ሰበበ የሚደርስባቸው እንግልት በአስቸኳይ እንዲቆም።
  7.    በአሁን ሰዓት በገዳሙ ዙሪያ የምደርሰውን ዝርፊያና ምዝበራ መንግስት ለገዳማውያኑም ሆነ ለቅርሶቹ አስፈላጊውን ጥበቃና ክብካቤ እንዲያደርግ እንጠይቃለን።
                           እግዚአብሔር አገራችንን  እና ገዳማችንን ይጠብቅልን
ግልባጭ
·         ለአፊዲሪ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር
·         ለአፊዲሪ ፌደራል ጉዳዮች ሚኒስቴር
·         ለአማራ ብሔራዊ ክልላዊ መንግሥት
·         ለትግራይ ብሔራዊ ክልላዊ መንግሥት
·         ለኢትዮጵያ ኤምባሲ  ዋሽንግተን ዲሲ
·         ለኢትዮጵያ ኤምባሲ ኦታዋ
·         ለቅዱስ ሲኖዶስ ጽ/ቤት
·         ለብፁዕ ወቅዱስ ፓትርያርክ ልዩ ጽ/ቤት
·         ለመንበረ ፓትርያርክ ጠቅላይ ጽ/ቤት
·         ለብፁዓን አባቶች በያሉበት

ደብዳቤ ሁለት፦ ለቅ/ሲኖዶስ ተላከ (PDF)
ለኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን
ቅዱስ ሲኖዶስ ጽ/ቤት
አዲስ አበባ
ጉዳዩ  ፦  የታሪካዊ  የዋልድባ ገዳማችን ይዞታና  የመነኮሳት ሰብዓዊ መብት  እንዲከበርልን  ስለመጠየቅ
የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ገዳማትና አድባራት ለኢትዮጵያ ኢኮኖሚያዊና ማኅበራዊ እድገት ያደረጉት አስተዋጽዖ ከፍተኛ መሆኑን በአገር አቀፍና ዓለም አቀፍ ደረጃ የታወቀ ነው። የቤተ ክርስቲያንን እና የክርስቲያኖችን መብት የማስጠበቅ ፤ እውነትን የመመስከር እና ምእመናንን በትክክለኛው መንገድ የመምራት ኃላፊነት ያለበት ቅዱስ ሲኖዶስ እንደሆነ ይታወቃል፣  ቅዱስ ሲኖዶስ የገዳማት የቦታ ይዞታ እና የመነኮሳት መብት በሚጣስበት በአሁኑ ወቅት ትክክለኛ አመራር ለመላው ሕዝበ ክርስቲያን  መስጠት ይጠበቅበታል ። 
ከቅርብ ጊዜያት ወዲህ በታላቁና በታሪካዊ የዋልድባ ገዳም ላይ መንግሥት የስኳር ፋብሪካ ልማት በሚል ሰበብ የገዳሙን እና ገዳማውያኑን መብት በሚጥስ መልኩ እና እንግልት እያደረሰ ለመሆኑ በተለያዩ መገናኛ ብዙኅን ሰምተናል።  ይህ ችግር ከተከሰተበት ጊዜ ጀምሮ በሰሜን አሜሪካ እና በተለያዩ የዓለማት የምንገኝ  የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን እምነት ተከታዮች በተለያዩ የአሜሪካን፣ የካናዳ ከተሞች እና በተለየዩ የዓለማችን ክፍሎች በየሳምንቱ በስልክ እንዲሁም በአካል በመገናኘት ይህንን አሳሳቢ ጉዳይ በመነጋገር ላይ  እንገኛለን። ይህንን ጉዳይ ለማሳሰብ በአሜሪካ ፣ በካናዳ የተለያዩ ከተሞች እንዲሁም በተለለያዩ ዓለማት በርካታ የኦርቶዶክስ ተዋሕዶ እምነት ተከታዮች በተገኙበት በኢትዮጵያ ኤምባሲ ፊት ለፊት እና ጉዳዩ በሚመለከታቸው ዓለም አቀፍ ተቋማት ሰላማዊ ሰልፍ አድርገናል። አሁንም ጉዳዮን  ለኢትዮጵያ መንግሥትና  ለተለያዩ ዓለም አቀፍ ተቋማት ለማሳሰብና የዋልድባ ገዳም የቦታ ይዞታ  እና የመነኮሳትም ሰብዓዊ መብት እንዲከበር ግንቦት ፳፯ ቀን ፳፻፬ ዓ. ም በዋናዋና የአሜሪካ ከተሞችና በካናዳ ከተሞች ሰላማዊ ሰልፍ ጥሪ ተላልፏል ። ከዚህ በፊት ከመንበረ ፓትርያርክ ጠቅላይ ቤተ ክህነት ተወክለው የሄዱትና ሪፖርት ያቀረቡት ዓለም ያወቀውን ጸሐይ የሞቀውን ጉዳይ ለቤተ ክርስቲያን ወገንተኝነት በሌለው መልኩ ያቀረቡት የማደናገሪያ ሪፖርት ሁላችንንም አሳዝኖናል ። የቅዱስ ሲኖዶስ አባላት በተሰጣችሁ መንፈሳዊ ኃላፊነት የተነሳ እውነቱን መናገርና የገዳማትን መብት የማስከበር ከፍተኛ ገድል ስለሚጠበቅባችሁ ይህንን በተመለከተ ቤተ ክርስቲያናችን ያላትን አቋም በትክክል ለመንግሥታና ለዓለም አቀፍ ተቋማት እንዲገለጽ እየጠየቅን በሰሜን አሜሪካ የምንገኝ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ እምነት  ተከታዮች በሙሉ ከቅዱስ ሲኖዶስ አባላት ጋር ለእውነት የምንቆም መሆናችንን ማረጋገጥ እንወዳለን ። ተመሳሳይ ደብዳቤ ለኢትዮጵያ መንግሥት  የተላከ መሆኑን እንገልጻለን
እግዚአብሔር ገዳማችንን ይጠብቅልን
ግልባጭ
  •          ለብፁዕ ወቅዱስ ፓትርያርክ ልዩ ጽ/ቤት
  •          ለመንበረ ፓትርያርክ ጠቅላይ ጽ/ቤት
  •      ለብፁዓን አባቶች በያሉበት9 comments:

lamelame europe said...

egea bareawacho enenasalane Egizeabehare yakanawenale.
Egizabehare yeredane

Muhammad & Gebriel said...

ብርሌ ከነቃ አይሆንም እቃ ።
===============
ፓትርያርኩ ቤተ ክርስቲያንዋን ወደ ተሳሳተ መንገድ ስትሄድ እያዩ እሳቸው ከኋላ ሁነው እየገፏት ነው። ለዚሁም ማስረጃ ቆመው ለራሳቸው ምስል ማሰራታቸው ትልቅና በቂ ምስክር ነው። ቀን በቀን ምስላቸው ግዙፍ እየሆነ እሳቸው ግን ትንሽ እየሆኑ ነው። ሽጉጣቸው አንሳቸውና መትረጌስ ፈልገው ከሆነ የአቶ መለስን ጔደኝነት የፈለጉት፤ ይህ አያዋጣም። ኢትዮጵያ ለማንም ለምንም የማታስደፍረው ሃብቷ ፣ ጌጧ ፣ ፍቅሯ ፣ ምግቧና ነፍሷ እምነቷ ነው። ዛሬ ሊቀ ጳጳሱ እና አቶ መለስ የኢትዮጵያ እምነቶች እያወኩ ነው፤ አላማቸው ኦርቶዶክስ አማኙንና እስልምና አማኙን ህዝብ ለማጋጨት ይመስላል። እኒህን የነቁ ብርሌወች የኢትዮጵያ ሕዝብ እንዲነቃባቸው በጥብቅ አሳስባለሁ። የኢትዮጵያ እምነቶች ፣ ቋንቋዎችና የቆዳ ቀለሞች በአንድ ሰፊ ሜዳ ላይ እነደአበቡ የተለያዩ አበባወች ኢትዮጵያን የሚያስጌጡና የሚያስከብሩአት ሃብቶቿ ናቸው። ስለዚህ ኢትዮጵያዊ ወገኔ ንቃባቸው ፤ ብርሌ ከነቃ አይሆንም እቃ ።

Gofa Geberal said...

enkune le berhane ledetua adersachu
listen this -learning geeze
http://vocaroo.com/i/s0ascJ8huRxB

Anonymous said...

Girum yibel yemiyasegne talak ermeja, E/G mechereshawin yasamirew.

Anonymous said...

Girum yibel yemiyasegne talak ermeja, E/G mechereshawin yasamirew.

Anonymous said...

Wogenoch ewnet belachehual. Labatachenem hone Lato Meles Tiru Meleket new Egizabher Azigne Lebonan yestelen. Embetachen Dingel Woladite Amlak Timtalen Tdegefen. Amen. FETARIACHEN Melkamun YASEMAN AMEN.

Unknown said...

Woow what a progress! If we continue expressing our anger like this, Meles will terfiy n look back z situation...otherwise he would take all our property! EPRDF is a shamless party!

Anonymous said...

+++

ከፓትርያርኩ ጀምሮ አባቶች ቤ/ያን ስትበደል ዝም የሚሉት ለምድን ነው?

እግዚአብሔር ይርዳን

Anonymous said...

O MY GOD I saw this please 22 years ago and i know there is a lot of blessed monks.i stayed for two weeks and i know what i saw.i would say the last stage for Ethiopian gv.you already touch that your done.wladeba means heaven on the earth. he touch that very soon he will get the result punishment very soon from god.i am very sure on this.unless they have to stop and they have to say sorry.stopping by it self it will not stop the punishment from god.they must say sorry.when ever who is involve to this bad thing they will get one by one.THIS IS TRUE.WEATHER THEY LIKE IT OR NOT GOD WILL PROTECTE WALDEBA .GOD BLESS ETHIOPIA.DR KIFF DAVE.

Blog Archive

የአቡነ ጳውሎስ "ሐውልተ ስምዕ"

ነጻ ፓትርያርክ ምርጫ ቢሆን ኖሮ ማንን ይመርጡ ነበር? እንበልና ሁሉም ነገር ሥርዓቱን ጠብቆ የተከናወነ የእጩዎች ምርጫ ቢሆን ኖሮ፣ አሁን የምናነሣቸው ጉድለቶች ባይኖሩ ኖሮ፣ 6ኛው ፓትርያርክ እንዲሆን የምትመርጡት ማንን ነበር? (ማሳሰቢያ፦ አሁን ያለው ክፍፍል እና የመንግሥት ተጽዕኖ ባይኖር ኖሮ ተብሎ የሚመለስ ጥያቄ ነው። የምን “ባይኖር ኖሮ ነው” የሚል አስተያየት ካለዎትም እናከብራለን።)