April 27, 2012

በስዊዲን “አዲስ ቤተ ክርስቲያን ይከፈታል" መባሉን ምዕመናን ተቃወሙ


(ደጀ ሰላም፤ ሚያዚያ 19/2004 ዓ.ም፤ 4/27/2012 READ THIS ARTICLE IN PDF)፦ በስዊዲኗ የስቴክሆልም ከተማ በመጪው እሑድ “ይከፈታል” የተባለ ቤተ ክርስቲያንን አስመልክቶ ምእመናን ተቃውሟቸውን እያሰሙ ነው። የተቃውሟቸውን እና ምክንይቱን ዝርዝር እንደሚከተለው አቅርበነዋል።
ቸር ወሬ ያሰማን፤ አሜን 

በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን
ለሥጋዊ ጥቅምና ለበቀል ብቻ ሲባል ቤተክርስቲያን ”የመክፈት” እንቅስቃሴ፣ በስቶክሆልም ስዊድን
ውድ አንባቢያን በቅድሚያ እንኳን ለብርሃነ ትንሣኤው በሰላም አደረሳችሁ እያልን:- የዚህ ጽሑፍ ዓላማ የግለሰቦችን ስም እያነሱ ማሳጣት ሳይሆን እያካሄዱት ያሉትን ሥጋዊ እና ሕገ ወጥ እንቅስቃሴ እኛ የተረዳነውን ያክል ለሌሎች ምእመናን እንዲሁም ለአባቶቻችን ካህናት አሳውቀን በአንድነት ሥርዓተ ቤተክርስቲያንን ለማስከበር እንድንነሳ መሆኑን እንድትረዱልን በአክብሮት እንጠይቃችኋለን።
ለዚህ ጽሁፍ መነሻ የሆነን ”ኢትዮጵያ ዛሬ” በሚባል ድረ ገጽ ላይ አንድ ”መንፈሳዊ” ጥሪ መመልከታችን ነው (http://ethiopiazare.com/images/doc/pdf/public_announcement/2012/120429stockholm-kyrka.pdf)። ማስታወቂያው   ”ታላቅ የምስራች ለሁሉም የኦርቶዶክስ ተዋህዶ እምነት ተከታዮች ለሆናችሁ በሙሉ” በማለት ይጀምራል:: ከዚያም ወደ ዉስጡ ሲገባ የሚነበብዉ ነገር ለህሊና የሚከብድ፤ ኢ-ኦርቶዶክሳዊ የሆነ፤ የቤተክርስቲያንን ሥርዓት፣ ከዚያም አልፎ የምእመናንን አንድነት የሚንድ እኩይ ተግባር ሆኖ እናገኘዋለን::  ማስታወቂያው ሲነበብ “... በስቶክሆልም ስዊድን ሶላንቱና ሴንትሩም አካባቢ በዓይነቱ  ልዩ የሆነና በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን ዶግማና ቀኖና መሠረት የሚመራ፤ በካህናት አባቶች የተመሠረተ፤ ንብረትነቱም ሆነ ባለቤቱ በግልጽ በስቶክሆልም ስዊድን በስደት የሚኖረው ኢትዮጵያዊ ሕዝብ የሆነ ቤተክርስቲያኑ የሚገኝበት የቦታው አቀማመጥ በዓይነ ሕሊናችን ወደ ሀገራችን ታላላቅ የእምነት ገዳማት የሚያስጉዝ በውስጥ አደረጃጀቱ ብቃት ያለዉ... ወዘተ” በማለት ጸሐፊዉ ”በአይነቱ ልዩ የሆነ ቤተክርስቲያን ”እንደሚከፈት”  ያትትና በዕለቱ  የቅድስት ድንግ ማርያምን ፤  የአቡነ ተክለሐይማኖትንና የአቡነ አረጋዊን የቃል ኪዲን ታቦታት አካትቶ የያዘ አዲስ ቤተክርስቲያን የፊታችን ሚያዝያ 21/ 2004 ዓ.ም ወይም እ.ኤ.አ. ኤፕሪሌ 29/ 2012፤ እሁድ  በብፁዕ አቡነ ኤያስ ጸሎትና ቡራኬ ተመርቆ ”ይከፈታል” ብሎ ጥሪዉን ያጠናቅቃል:: 
ታዲያ አዲስ ቤተክርስቲያን መክፈት ምን ችግር ኖሮት ነው ”ለሥጋዊ ጥቅምና ለበቀል...” ያላችሁት ተብሎ ይጠየቅ ይሆናል::  ይህንን ጥያቄ ለመመለስ የዚህን እንቅስቃሴ ሕገወጥነት የሚያመላክቱ ነጥቦችን በጥቂቱ ብቻ እንደሚከተለው በዝርዝር እናቀርባለን።
1.         የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን ነባራዊ ሁኔታ በስቶክሆልም
እንደ አለመታደል ሆኖ በእኛ ዘመን በተፈጠረ መከፋፈል ቤተክርስቲያናችን አፅራረ ቤተክርስቲያን ካደረሱባት እና እያደረሱባት ካሉት መከራዎች ባልተናነሰ ልጆቿ ነን በሚሉትም እየተፈተነች ትገኛለች:: በሰሜን አሜሪካ እንዳለው ሁሉ በስዊድን ሀገርም ሦስት ዓይነት የቤተክርስቲያን አስተዳደር ክፍፍል አለ።  እነዚህም:-  ኢትዮጵያ ዉስጥ ባለ ሲኖዶስ፣  በስደት ባለ ሲኖዶስ  እና ከሁለቱም አይደለሁም በሚል ”ገለልተኛ” የሚመሩ ናቸው:: እነዚህ ሁሉ ምንም እንኳን አባቶች በቤተክርስቲያን ቀኖና ላይ በመወጋገዛቸው ተለያይተዉ አገልግሎት ቢፈጽሙም፤ አንድ ቀን ዉግዘቱ ተነስቶ አብረን አምላካችንን በጋራ እናገለግላለን በሚል ተስፋ በማናቸዉም እንቅስቃሴ አንዱ ሌላዉን ሳያሳዝን ተከባብረው ኖረዋል::
በስደት በሚገኘዉ ሲኖዶስ የሚተዳደረው በስቶክሆልም መድኃኔዓለም ቤተክርስቲያን የቅዱስ ሚካኤልና የእመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ታቦታት ተደርበው የሚገኙ ሲሆን፤ ከዚህ በተጨማሪም የጎተንበርግ ቅዱስ ገብርኤልን  ቤተክርስቲያን ያስተዳድራል:: በሀገር ቤት ባለው ሲኖዶስ ደግሞ የስቶክሆልም መንበረ ጸባኦት ቅድስት ስላሴ ቤተክርስቲያን የፃድቁ አባታችን አቡነ አረጋዊን ታቦተ ሕግ  ደርቦ ምእመኑን ያገለግላል:: በገለልተኛነት ያሉት ደግሞ የእመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያምን ቤተክርቲያን ”ከፍተዋል”:: 
ይህ ሆኖ እያለ በቅድስት ስላሴ ቤተክርስቲያን የሚገለገሉ ምእመናን የቅዱስ ገብርኤልና የቅዱስ ሚካኤል ታቦታት ተደርበው እንዲከብሩላቸው ጥያቄ ባቀረቡበት ሰዓት ለቤተክርስቲያን ሰላምና አንድነት ሲባል (በተለይም ወደፊት ይወርዳል ተብሎ በተስፋ ለሚጠበቀው እርቀ ሰላም ሲባል) ከላይ ቅዳሴ ቤታቸው እንዲከበር የተጠየቁት ታቦታት በስደት  ባለው ሲኖዶስ  በሚተዳደሩ አብያተክርስቲያናት ዉስጥ ስለሚገኙ በወቅቱ በስቶክሆልም ቅድስት ስላሴ ሰበካ ጉባኤና ካህናት መልካምና ቅን አስተሳሰብ  የቅዱስ ገብርኤልና የቅዱስ ሚካኤል ቅዳሴ ቤታቸውን ማክበር ቀርቶ በምትኩ የጻድቁ አቡነ አርጋዊ ቅዳሴ ቤት እንዲከበር ተደረገ::
ይህ በተደረገበት ከተማ ዉስጥ ብፁዕ አቡነ ኤልያስ  የእመቤታችን ታቦተ ህግ እርሳቸው በሚያስተዳድሩት ደብር እንዲሁም በገለልተኛው ቤተክርስቲያን እያለ፤ የጻድቁ አባታችን አቡነ አረጋዊ ታቦት ደግሞ በሀገር ቤቱ ሲኖዶስ በሚተዳደረው የስቶክሆልም መንበረ ጸባኦት ቅድስት ስላሴ ቤተክርስቲያን ውስጥ መደረቡ እየታወቀ:-  የቅድስት ድንግል ማርያምን፣ የአቡነ አረጋዊንና የአቡነ ተክለሐይማኖትን ታቦታት (ሦስት ጽላቶችን በአንድ ጊዜ!)  ያካተተ ቤተክርስቲያን ”እንከፍታለን” ብለው ለተነሱት፤ በገለልተኛው ቤተክርስቲያን ሲያገለግሉ ቆይተው ከታች በዝርዝር በተገለጸው የሥነ-ምግባር ችግር ለተባረሩት ለ”ቄስ” ፍስሃና ለ”አባ” ኒቆዲሞስ ለመባረክ መስማማታቸው እጅግ አሳዝኖናል።  
2.       ቤተከርቲያኑን ለመክፈትና ለመምራት እየተሯሯጡ ያሉ ግለሰቦች
በዚህ ቤተክርስቲያን ”መከፈት” ውስጥ ሁለት ወሳኝ ግለሰቦች ይጠቀሳሉ፤ እነዚህም ”ቄስ” ፍስሃና ”አባ” ኒቆዲሞስ ናቸው:: ”ቄስ” ፍስሃን ስንመለከት መጀመሪያ በአሁኑ ወቅት ሀገር ዉስጥ ባለው መንግስት በካድሪነት ያገለግል የነበረ በኋላም መንግስት ለስልጠና ወደ ውጭ ልኮት በዚሁ ከድቶ የቀረ ነው::  እዚህ ስቶክሆልም እንደመጣ የስደተኞች ካምፕ ውስጥ ገባ ከዚያም ”ቄስ” ነኝ አለና ገለልተኛ ነን ባሉት የማርያም ቤተክርስቲያን ዉስጥ አገልጋይ ሆኖ ተቀጠረ::  በወቅቱ ስደተኛም ሆነ የሀገር ቤት ሲኖዶስ የለም ብሎ ”በማስተማሩ” ለጊዜው ደጋፊ አገኘ በኋላ ግን ጸባዩን ሲያስተዉሉት ሥራ የማይወድ፣ ዝም ብሎ ከቤተክርስቲያን  እና ከስዊድን መንግስት የሚሰጠዉን የማህበራዊ ድጎማ ገንዘብ  እየወሰደ ፓልቶክ ላይ ተቀምጦ ከፖለቲካ ሥራው በተጨማሪ በውጪ ሀገር የሚገኙ እና በአገር ቤት ሲኖዶስ የሚተዳደሩ አብያተክርስቲያናትን እንዴት ማድከም ከተቻለም ማጥፋት እንደሚቻል ዘወትር መምከርና እቅድ ማውጣት ጀመረ::
ይህን የሰሙት የቤተርስርቲያኑ ሰበካ ጉባኤ  አባላት አንዱን ምረጥ ካህን ነኝ ካልክ ካህን ሁን ፖለቲከኛ ነኝ ካልክ ደግሞ ፖለቲከኛ ሁን በሚል ክርክር ስምምነት ላይ ባለመድረሳቸው ከሥራዉ አሰናበቱት:: በዚህ ጊዜ ከቤተክርስቲያን የሚያገኘው ገቢ ስለተቋረጠ፣ ከመንግስት የሚሰጠዉ ገንዘብ ስላልበቃዉና እንደሌላው ኢትዮጵያዊ በጉልበቱ ሰርቶ መኖር ስለማይወድ አዲስ መላ መጣለት:: በቅርብ ጊዜ ከሀገር ቤት ተሰደዉ ወደ ስቶክሆልም የመጡት ”አባ” ኒቆዲሞስ  የጥገኝነት አቤቱታቸው ተቀባይነት ባለማግኘቱ በዚሁ ”ቄስ” ምክር አዲስ  ቤተክርስያን ከፍቶ መኖር እንደሚቻል በማሳመን ለወትሮዉ ሲያጥላላቸው ከነበሩት ከአቡነ ኤልያስ ጋር በመጠጋት በፊት ሲያገለግልበት ከነበረበት ቤተክርስቲያን አንድ ፌርማታ ብቻ ርቀት ላይ የታቦታትን ክብር ባልጠበቀና ምድራዊ በቀል ለመፈፀም ሲባል በታሰበ (ቀድሞ የነበረበትን ቤተክርስቲያን ”ለመበቀል”)፤ ልክ እንደ ምድራዊ የንግድ ሥራ በርካታ ምእመናንን ይሰበስብልኛል ብሎ በማሰብ እና በዓመት ብዙ ጊዜ የንግስ በዓል በማድረግ ከምእመናን ገንዘብ ለመሰብሰብ ያስችለኛል ብሎ በማሰብ በአንድ ጊዜ ሦስት ታቦታትን ልናከብር ነዉ ብሎ ማስታወቂያ ለጠፈ:: ይህ ሁሉ ሥርዓተ ቤተክርስቲያንን የጣሰ አሳዛኝና አሳፋሪ ተግባር በመሆኑ አንባቢ ሁሉ ያስተዉል እንላለን:: የቃለኪዳኑ ታቦት የሚከበረው ለሰማያዊ ጽድቅ እንጅ ለምድራዊ ድሎት፤ ለገንዘብ፤ ለፖለቲካ እና ለመሳሰሉት ጥቅሞች ሊሆን አይገባም::
3.       ይድረስ ለብፁዕ አቡነ ኤልያስ ዘስቶክሆልም
ሀ. ይህ እርስዎ ባርከውይከፍቱታል” የሚባለው ቤተክርስቲያን ከላይ እንደገለጽነው በበጎ ሕሊና ያልታቀደ በመሆኑ ዘርፈ ብዙ ችግሮችን ሊያስከትል ይችላል። ይልቁንም እርስዎም ጭምር ተሳታፊ በሆኑበት ቤተክርስቲያንን አንድ ለማድረግ የሚደረገውን ጥረት በብዙ እርምጃዎች ወደ ኋላ የሚመልስ (በተለይ በስቶክሆልም እና አካባቢው ያለችዋን ቤተክርስቲያን) ስለሆነ ስለቤተክርስቲያን ሰላምና አንድነት ሲሉ ራስዎን ከዚህ እንቅስቃሴ እንዲያገሉ በትህትና ልናሳስብዎ እንወዳለን።
ለ. የእርስዎ መንበረ ጵጵስና በሆነው የስቶክሆልም መድኃኔዓለም ቤተክርስቲያን የእመቤታችን ጽላት (በተጨማሪም የቅዱስ ሚካኤል) መኖሩ እየታወቀ ሌላ ተጨማሪ የእመቤታችን ጽላት ለምን አስፈለገ? በእመቤታችን ስም ተጨማሪ ሶስተኛ ቤተክርስቲያን እንዲመሰረት የተስማሙት በውኑ በስቶክሆልም ከተማ ለሚኖሩ ምእመናን የአምልኮ ቦታ አንሶ ነውን? ቢሆንስ አሁን ካለው ቤተክርስቲያን በአንድ ፌርማታ ልዩነት ብቻ ተመሳሳይ ስያሜ ያለው ሌላ አዲስ ደግሞ መክፈቱ ዛሬም ሆነ ወደፊት የሚፈጥረው ችግር ከእርስዎ የተሰወረ ይሆንን? ይልቁንም የተጣሉትን አስታርቆ ሁሉም በአንድነት እና በስምምነት አምልኮ እግዚአብሔርን በፍቅር እንዲፈጽም ማድረጉ እንደ እርስዎ ካለ የእድሜ ባለጸጋ አባት ይጠበቅ ነበር።
ሐ. ስምዎ በገጸ ድር ማስታወቂያው ላይ ከመውጣቱ በተጨማሪ ከሳምንት በፊት እርስዎ መድኃኔዓለም ቤተክርስቲያን ውስጥ እያሉ የዚሁ አዲስ ቤተክርስቲያንመከፈት” ዜና በበራሪ ወረቀት ሲበተን በይሁንታ ተቀብለው ሲያበቁ በብዙ ክብር ሊታጀብ የሚገባውን ታቦተ ሕግ እንዲያጅቡ በዕለቱ ለተገኙት ምእመናን ለወትሮው እንደሚያደርጉት ሁሉ በአንደበትዎ አለመናገርዎ ከምእመናን ሊገጥምዎ የሚችለውን ተቃውሞ አስቀድመው እንደተረዱ እንድናስብ አድርጎናል። የአዲሱ ቤተክርስቲያንመከፈትም” ለጥሩ ዓላማ ነው ብለን እንዳናስብ ተጨማሪ ማስረጃ ሆኖናል፤ አለዚያማ በአንደበትዎ ለሁሉም ምእመናን ማስረዳት በቻሉ ነበር። እኛም በጽሑፍ ፋንታ ፊት ለፊት እንጠይቅዎ ነበር። አሁንም ጊዜው ገና ነው። ሁልጊዜ ስለሚያስተምሩትየቀኖና መጠበቅ” ያለዎትን ተቆርቋሪነት በተግባር ያሳዩን፤ ለእልህ መወጫና ለሥጋዊ ጥቅም ብቻ ሲባል ቤተክርስቲያንአይከፈትምና”። ስለዚህ ከተጠያቂነት ስለማያመልጡ መቃወም እንኳን ባይችሉ ምንም አይነት ትብብር ከማድረግ ከወዲሁ እንዲቆጠቡ በታላቅ ትህትና እንጠይቅዎታለን።
በተጨማሪም ዛሬ ቁጭ ብለው የሰቀሏቸው ግለሰቦች ነገ እርስዎ በሰጧቸው እውቅና ተጠቅመው አላስፈላጊ ጥቅማ ጥቅሞችን ሲያሳድዱ እርስዎ ከሚያስተዳድሩት ቤተክርስቲያን ሳይቀር ከባድ ተግዳሮት እንደሚገጥምዎ ሊያስቡበት ይገባል። ምን ማለታችን እንደሆነ በደንብ ስለሚረዱን የዚህን ዝርዝር እንተወዋለን።
4.         በስቶክሆልም እና አካባቢው ባሉ አጥቢያዎች ለምትገኙ አባቶች ካህናት በሙሉ:- ከላይ እንደተገለጸው ሥርዓተ ቤተክርስቲያንን በማስከበር የአባትነት ድርሻችሁን እንድትወጡ እናሳስባለን። ሌላ ማድረግ ባትችሉ ቢያንስ በእንዲህ አይነቱ ሕገ ወጥ ተግባር ባለመተባበር እና እውቅና ባለመስጠት ቤተክርስቲያን የጣለችባችሁን ኃላፊነት እንድትወጡ እናሳስባለን። ”እያንዳንዱ ካህን በሕገ ቤተክርስቲያን መሠረት የቤተክርስቲያንን ሥርዓት ጠብቆ ማስጠበቅ ግዴታው ነው።” (ቃለ ዓዋዲ አንቀጽ ፷፥ ቁ.፪. ረ)።

5.         ለምእመናን በአጠቃላይ:- ከላይ ለአባቶች ካህናት እንዳሳሰብነው ሁሉ የድርሻችንን ልንወጣ ይገባል። በተለይም የዚህ ሕግ ወጥ እንቅስቃሴ የመጀመሪያ ደረጃ ተጠቂዎች እናንተ ስለሆናችሁ በብዙ ድካም በስደት አገር የሰበሰባችሁትን ገንዘብ ለሥርዓት-አልበኞች ጉልበት ማጠንከሪያ እንዳታውሉት ልናሳስባችሁ እንወዳለን። ሥርዓተ ቤተክርስቲያንን ማክበር እና ማስከበር የሁላችን ኃላፊነት ነው።


6.         አዲስ ቤተክርስቲያን ለመክፈት ለተነሳችሁት ለሁለቱአባቶች”:- ፖለቲከኛ መሆን ኃጥያት ባይሆንም ቤተክርስቲያንን ለፖለቲካ ሥራ ማስኬጃ፣ ለግል ጥቅም (ለመኖሪያ ፈቃድ ማግኛ)፣ እንዲሁም ለገንዘብ መሰባሰቢያ ማድረግ ተገቢ አይደለም። ሀገራችን ፖለቲከኞችም ካህናትም ያስፈልጓታል፤ ነገር ግን ሁሉም የሚያምረው በተገቢው ቦታና ጊዜ ሲፈጽሙት ብቻ ነው። ቤተክርስቲያን ሰማያዊት እንጂ ምድራዊት አይደለችም፤ ዓላማዋም ወንጌልን በመስበክ ምእመናን የእግዚአብሔርን መንግስት እንዲወርሱ ማድረግ ነው። እናንተ ግን ለምድራዊ ጥቅም ማራመጃ ልታደርጓት እየሞከራችሁ ትገኛላችሁ። ይህም በምድርም ሆነ በሰማይ ስልሚያስጠይቃችሁ እና ስለሚጎዳችሁ ወደ ልቦናችሁ ተመለሱ። ቄስ ሥራው ማስተማር፣ ማጥመቅ፣ ቀድሶ ማቁረብ፣ መባረክ፣ ማሠርና መፍታት፣ መናዘዝ ነው።” (ፍት.መን.አን.፮ ረስጣ ፶፰) ስለዚህ ካሰባችሁት ተገቢ ካልሆነ ተግባር ተቆጥባችሁ በእውነት እግዚአብሔርን ለማገልገል ተዘጋጁ።

ጸልዩ በእንተ ሰላመ ቤተክርስቲያን
የቤተክርስቲያን አንድነት ከሚናፍቃቸው እና የሥርዓቷ መጣስ ከሚቆጫቸው ምእመናን

Post a Comment

Blog Archive

የአቡነ ጳውሎስ "ሐውልተ ስምዕ"

ነጻ ፓትርያርክ ምርጫ ቢሆን ኖሮ ማንን ይመርጡ ነበር? እንበልና ሁሉም ነገር ሥርዓቱን ጠብቆ የተከናወነ የእጩዎች ምርጫ ቢሆን ኖሮ፣ አሁን የምናነሣቸው ጉድለቶች ባይኖሩ ኖሮ፣ 6ኛው ፓትርያርክ እንዲሆን የምትመርጡት ማንን ነበር? (ማሳሰቢያ፦ አሁን ያለው ክፍፍል እና የመንግሥት ተጽዕኖ ባይኖር ኖሮ ተብሎ የሚመለስ ጥያቄ ነው። የምን “ባይኖር ኖሮ ነው” የሚል አስተያየት ካለዎትም እናከብራለን።)