April 23, 2012

መንፈሳዊ ሙግት በመንፈሳዊ ፍርድ ቤት


(Reporter Newspaper):- ይህ ወቅት በክርስትና እምነት ተከታዮች የትንሳኤ በዓል የሚከበርበት ጊዜ ነው፡፡ ይህንን ወቅት የኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያን ምዕመናን መንፈሳዊና ትውፊታዊ በሆኑ ሥርዓቶች ያከብሯቸዋል፡፡ በትንሳኤው ዕለት ነጭ መልበስ፣ ያሬዳዊ ዜማ መዘመር፣ ጧፍና ሻማ ማብራት የበዓሉ መገለጫ ናቸው፡፡ ትውፊታዊ ሥርዓቶችም አሉ፡፡ በበዓለ ሆሳዕና ዘንባባ መታሰሩ፣ በዕለተ ሐሙስ የእግር እጥበት ሥርዓት መኖሩ፣ ጉልባን የመመገብ ሥርዓት ወዘተ በዚህ ወቅት የሚታዩ መንፈሳዊ ሥርዓቶች ናቸው፡፡ የትንሳኤ በዓል ከሌሎቹ መንፈሳዊ በዓላት የሚለየው መንፈሳዊ ይዘቱ ከፍ ያለ በመሆኑ ነው፡፡ በገና የገና ጨዋታ፣ በጥምቀት መተጫጨትን የመሳሰሉ ልማዶች በዘመነ ፋሲካ አይስተዋሉም፡፡ የትንሳኤን መንፈሳዊ አከባበር ካነሳን ደግሞ የሥርዓቱ ፈጻሚዎች፣ አገልጋዮችና መምህራንን ማሰብ አይቀርም፡፡ በዚህ ጽሑፍም የኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያንንና የመንፈሳውያን ግንኙነት የሚዳኙበትን ሁኔታ፣ በመደበኛው የፍትሕ ሥርዓት የተሰጡ ውሳኔዎቻችንና በሕገ መንግሥቱ መሠረት ያላቸውን ቦታ በአጭሩ እንዳስሳለን፡፡

መነሻ ነገር
ለዚህ ጽሑፍ መነሻ የሆነኝ የፌዴራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ሰበር ችሎት በሰበር መዝገብ ቁጥር 18419 ግንቦት 4 ቀን 1998 ዓ.ም. የሰጠው ገዥ የሕግ ትርጉም /Precedent/ ነው፡፡ ይህ ፍርድ የተሰጠው በሐመረ ወርቅ ቅድስት ማርያም ቤተ ክርስቲያንና በስድስት ዲያቆናት መካከል በነበረ የሥራ ክርክር ጉዳይ ነው፡፡ ዲያቆናቱ ያለአግባብ ከሥራ ስለተሰናበትን ወደ ሥራችን እንድንመለስ በሚል ዳኝነት የጠየቁ ሲሆን፣ ጉዳዩ የቀረበለት የፌዴራል የመጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤት ጉዳዩን ተቀብሎ፣ ማስረጃ ሰምቶ ስንብቱ ሕገወጥ በመሆኑ ዲያቆናቱ ወደሥራቸው ይመለሱ ሲል ፍርድ ሰጠ፡፡ ይግባኝ የቀረበለትም የፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት የሥር ውሳኔውን አጸና፡፡ ቤተ ክርስቲያኗ ከፍተኛው ፍርድ ቤት ያጸናው ውሳኔ መሠረታዊ የሕግ ስህተት ተፈጽሞበታል በሚል ለሰበር ችሎት አቅርባ ችሎቱ የሥር ፍርድ ቤቶችን ውሳኔ ሽሯል፡፡

የሦስቱ ፍርድ ቤቶች የአቋም ልዩነት መነሻው የአሠሪና ሠራተኛ ጉዳይ አዋጅ ‹‹የሃይማኖት ወይም የበጎ አድራጎት ድርጅቶች በሚመሠርቱት የሥራ ግንኙነቶች ላይ አዋጁ ተፈጻሚ እንዳይሆን የሚኒስትሮች ምክር ቤት በደንብ ሊወሰን ይችላል፤›› በሚል የደነገገው አንቀጽ ነው፡፡ የሥር ፍርድ ቤቶች የሚኒስትሮች ምክር ቤት የተባለውን ደንብ እስካላወጣ ድረስ የሃይማኖት ተቋማቱ በሚመሠርቱት የሥራ ግንኙነቶች ላይም አዋጁ ተፈጻሚ ይሆናል የሚል አቋም ይዘዋል፡፡ ሰበር ችሎቱ ደግሞ የዚህ ድንጋጌ አተረጓጎም በሃይማኖት ተቋማት ውስጥ የሚኖረውን የተለየ የሥራ ግንኙነት ሊያገናዝብ ይገባል ይላል፡፡ በችሎቱ አመለካከት አንዳንድ የሃይማኖት ተቋማት የሥራ ግንኙነቶች ተቋማቱ ከሚከተሉት እምነት ጋር ቀጥተኛ ግንኙነት ያለውና ከእምነቱ ጋር ተነጥሎ ሊታይ የማይችል ሠራተኛን፣ እንደ ቄስ፣ ካህን፣ ዲያቆን ወዘተ የሚመለከቱ ሲሆን፣ በሌላ በኩል ደግሞ የሚሰጡት አገልግሎት ከእምነቱ ጋር ያልተቆራኘ እንደ ሒሳብ ሠራተኛ፣ የንብረት ክፍል ሠራተኛ፣ የስታትስቲክስ ሠራተኛ ወዘተ ጋር የሚመሠረቱ ግንኙነቶች ናቸው፡፡ ችሎቱ ሁለተኛው ግንኙነት ከእምነቱ ጋር የማይያያዝ በመሆኑ በማንኛውም የአሠሪና ሠራተኛ ጉዳይ ከሚነሱ ሁኔታዎች የተለየ አይደለም ሲል ‹‹የመንፈሳዊ ሥራ ግንኙነት የሚያስነሳቸው የአሠሪና ሠራተኛ ጉዳዮች ከእምነቱ ተነጥለው የሚታዩ ባለመሆናቸው በሥራ ግንኙነቱ ውስጥ ጣልቃ መግባቱ በእምነት ውስጥ ጣልቃ መግባትን ያስከትላል፤›› በማለት የሥር ፍርድ ቤቶች መንፈሳዊ ሥራ የሚሰጡ የዲያቆናትን ክርክር ለማየት ሥልጣን የሌላቸው መሆኑን በመግለጹ ክርክሮቹ የሃይማኖት ተቋማቱ በሚኖራቸው አለመግባባቶችን በሚፈቱበት መንገድ የሚታዩ እንደሆኑ ገልጿል፡፡ ሰበር ችሎቱ በሌላ መዝገብ (የሰበር መዝገብ ቁጥር 47806) ተመሳሳይ ውሳኔ ሰጥቷል፡፡

የሰበር ችሎቱ አንድምታ

የሰበር ችሎቱ የኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያን ከመንፈሳውያን አገልጋዮች ጋር ባሉት ግንኙነት የሚመነጩ የሥራ ክርክሮች በመደበኛ ፍርድ ቤቶች እንደማይታዩ ገልጿል፡፡ የችሎቱ ውሳኔ በሃይማኖት ነፃነት፣ በሃይማኖትና መንግሥት ግንኙነትና በመንፈሳዊ ፍርድ ቤቶች ላይ የራሱ የሆነ ተፅዕኖ አለው፡፡ ሲጀምር የሃይማኖት ነፃነት አማኞች ሊከተሉት የሚገባውን ዶግማ፣ ሥርዓትና አፈጻጸም የመደንገግንና መንፈሳዊ ሥርዓቶች ሳይከበሩም የሚስተካከሉበትን ሁኔታ የመወሰን ሥልጣን ለሃይማኖት ተቋማት መስጠት ነው፡፡ ሃይማኖቶች የራሳቸውን ጉዳይ በራሳቸው መንገድ ካልፈቱ የሃይማኖት ነፃነት ጥያቄ ውስጥ ይገባል፡፡ ሁለተኛው በመንግሥትና በሃይማኖት መካከል የሚኖረው ግንኙነት ላይ የራሱ አንድምታ አለው፡፡ ይህን ሰበር ችሎቱም በውሳኔው ላይ አስፍሮታል፡፡ የኢትዮጵያ ፌዴራላዊ ዲሞክራሲያዊ ሪፐብሊክ ሕገ መንግሥት አንቀጽ 11 ‹‹መንግሥትና ሃይማኖት የተለያዩ ናቸው፤ መንግሥት በሃይማኖት ጉዳዮች ጣልቃ አይገባም፤›› በማለት ግልጽ ድንጋጌ አስቀምጧል፡፡ የሚኒስትሮች ምክር ቤት የመንፈሳዊ ሥራ ግንኙነትን በሚመለከት ሕግ የሚያወጣ ከሆነ፣ ዳኞችም የሃይማኖት ዶግማዎችንና ቀኖናዎችን እየመረመሩ ውሳኔ የሚሰጡ ከሆነ መንግሥት በሃይማኖት ጉዳዮች ጣልቃ እንዲገባ መፍቀድ በመሆኑ ሕገ መንግሥታዊ ተቀባይነት አይኖረውም፡፡ የሰበር ችሎቱ የሰጠው ፍርድ ገዥ ቢሆንም፣ አሁንም የሥር ፍርድ ቤቶች መንፈሳዊ የሃይማኖት ጉዳዮችን ሲመለከቱ መስተዋሉ የሕገ መንግሥቱ መሠረታዊ መርሕ መዘንጋቱን ልብ ይሏል፡፡ በአንድ የሥራ ክርክር ጉዳይ አንድ ግለሰብ በቅድስት ሥላሴ መንፈሳዊ ኮሌጅ መንፈሳዊ ትምህርት ለመከታተል ያመለክታል፡፡ መንፈሳዊ ኮሌጁ ተማሪዎቹን የሚቀበልበት የራሱ መስፈርት ያለው ሲሆን፣ ውሳኔውንም በዚሁ መሠረት ይሰጣል፡፡ አመልካቹ በታየበት የመንፈሳዊነት፣ አገልግሎትና የሥነ ምግባር ጉድለት ምክንያት በኮሌጁ መንፈሳዊ ትምህርቱን መከታተል እንደማይችል ተገለጸለት፡፡ ግለሰቡም ክልከላውን በመቃወም ጉዳዩን ወደ መደበኛ ፍርድ ቤት የወሰደው ሲሆን፣ ፍርድ ቤቱም ጉዳዩን ተቀብሎ አስተናገደ፤ ፍሬ ነገሩን መርምሮ ውሳኔ እስኪሰጥበትም አመልካቹ ትምህርቱን እየተከታተለ እንዲቆይ ብይን ሰጠ፤ ኋላም በመንፈሳዊው ኮሌጅ ተማሪ ሆኖ እንዲቀጥል ወሰነ፡፡ ይህ ጉዳይ በግልጽ በሕገ መንግሥቱ አንቀጽ 11 ስለመንግሥትና የሃይማኖት ልዩነት (Secularism) የተደነገገውን የጣሰ ስለመሆኑ ሰፊ ትንታኔ አያስፈልገውም፡፡ ፍርድ ቤቱ ተማሪው መንፈሳዊ ስለመሆን አለመሆኑ የተቀመጠውን የሃይማኖት ተቋሙን ሕግ ለመተርጎም ስለሚገደድ በሃይማኖቱ ውስጥ ጣልቃ እንዲገባ አድርጎታል፡፡

ሌላው የሰበር ችሎቱ ውሳኔ የመንፈሳዊ ፍርድ ቤትን አስፈላጊነት አመላካች ነው፡፡ መንፈሳውያን አገልጋዮች በሃይማኖት ተቋማት ላይ ያላቸውን ቅሬታ በመደበኛ ፍርድ ቤት እንደማያቀርቡ ፍርድ ከተሰጠ እንዲህ ዓይነት ጉዳዮች የሚታዩበት የሃይማኖት ፍርድ ቤት ማቋቋም የሃይማኖት ተቋማቱ ግዴታ ይሆናል፡፡ መንፈሳውያን አገልጋዮች መብታቸውን በመደበኛ ፍርድ ቤትም ሆነ በሃይማኖት ፍርድ ቤት መጠየቅ ካልቻሉ ፍትሕ የማግኘት መሠረታዊ መብታቸው (Access to Justice) የሚጣስ ይሆናል፡፡

የሕግ መሠረት

ለሃይማኖት/መንፈሳዊ ፍርድ ቤቶች የሕግ መሠረት የሚሰጠው ሕገ መንግሥቱ ነው፡፡ ሕገ መንግሥቱ በአንቀጽ 27 ማንኛውም ሰው የሃይማኖት ነፃነት እንዳለው ይደነግጋል፡፡ ይህን መሠረት በማድረግም የሕግ ብዙህነት (Legal pluralism) በሃይማኖትም የሚገለጽበትን ሁኔታ አስፍቷል፡፡ ሕገ መንግሥቱ በአንቀጽ 34(5) ዜጎች የግልና የቤተሰብ ጉዳዮችን በተመለከተ ራሳቸው ከፈቀዱ በሃይማኖቱ ወይም በባህል ሕጎች መሠረት መዳኘትን እንደማይከለክል አስቀምጧል፡፡ ሕጉ የሃይማኖት ሕጎች በሥራ ላይ ሊውሉ እንደሚችሉ በግልጽ ዕውቅና ሰጥቷል፡፡ ሕገ መንግሥቱ በሃይማኖት ወይም በባህል ሕጎች መዳኘት አይከለከልም በማለት ብቻ አያቆምም፡፡ እነዚህን ጉዳዮች ሥራ ላይ ለማዋል፤ ባለጉዳዮችም ጉዳያቸውን ሥልጣን ላለው አካል ማቅረብ እንደሚችሉ በማሰብ በአንቀጽ 78(5) ‹‹የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤትና የክልል ምክር ቤቶች የሃይማኖትና የባህል ፍርድ ቤቶችን ሊያቋቁሙ ወይም ዕውቅና ሊሰጡ ይችላሉ፡፡ ይህ ሕገ መንግሥት ከመፅደቁ በፊት ዕውቅና አግኝተው ሲሠራባቸው ለነበሩ የሃይማኖቶችና የባህል ፍርድ ቤቶች በዚህ ሕገ መንግሥት መሠረት ዕውቅና አግኝተው ይደራጃሉ፤›› በማለት የሕግ መሠረት አስቀምጧል፡፡ ስለዚህ የሃይማኖት ተቋማት መንፈሳዊ ፍርድ ቤት ቢያቋቁሙ ወይም ከሕገ መንግሥቱ በፊት የተቋቋመ ካለ ዕውቅና ቢጠይቁ ዕውቅና ሊሰጣቸው እንደሚችል መገንዘብ ይቻላል፡፡

የኢትዮጵያ ተሞክሮ
አቶ አበራ ጀምበሬ “Legal History of Ethiopia 1934-1974” በሚለው መጽሐፋቸው ቅድመ 1928 ዓ.ም. በሃይማኖት መሠረት የተፈጸመ ጋብቻንና ፍቺ፣ የቤተ ክርስቲያን አስተዳደርና ንብረቶችን በተመለከተ የሚነሱ ጉዳዮች ለመንፈሳዊ ፍርድ ቤቶች ይቀርቡ እንደነበር ገልጸዋል፡፡ ፍርድ ቤቶች በአዲስ አበባና በሌሎች አገር ስብከቶችም የተቋቋሙ ሲሆኑ፣ የሚያስችሉትም እጨጌዎች ነበሩ፡፡ አቶ አበራ በወቅቱ የይግባኝ ሥርዓት እንደነበረ ያስታወሱ ሲሆን፣ የገዳማት አበምኔቶችና የአንዳንድ ኀቢያተ ክርስቲያናት አለቆች ቀለል ያሉ የፍትሐ ብሔርና የወንጀል ጉዳዮችን የማየት ሥልጣን እንደነበራቸው ገልጸዋል፡፡ እነዚህ መንፈሳዊ ፍርድ ቤቶች ኢትዮጵያ ከጣሊያን ቁጥጥር ነፃ ከወጣች በኋላ እስከ 1966 ዓ.ም. ድረስ ሲሠራባቸው ቆይተዋል፡፡ ሙሉጌታ ጌጡ የተባሉ የሕግ ባለሙያ በመንፈሳዊ ፍርድ ቤቶች ዙሪያ በሠሩት ጥናትም የኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያን በ1935 ዓ.ም. የቤተ ክርስቲያን ደንብ በሚል ሕግ የዳኝነት አካል እንደነበረ አመልክተዋል፡፡ የዚህ ደንብ አንቀጽ 10 ‹‹ቤተ ክርስቲያኗ ምዕመናን በንስሐ የምትሠራበት የምትቀጣበት የግል ዳኝነት አላት፡፡ ዳግመኛም የውስጥ ቤተሰቦቿ የሆኑ ካህናትን በመንፈሳዊ ተግሳጽ እያስማማች ታስተዳድራለች፡፡ በዓላማዊ ዳኝነት ግን በመንግሥት የሚሸሙ ዳኞች እየጠበቁ ያስተዳድራሉ፡፡ ለዓላማዊ ዳኝነት የሚበቁ ሰዎች የመንፈሳዊ ጉባዔ ለማቅረብ ይችላል፡፡ የሚሾሙትም በንጉሠ ነገሥቱ ነው፤›› በሚል መደንገጉን አቶ ሙሉጌታ በጥናታቸው አመልክተዋል፡፡

በመንፈሳዊ ፍርድ ቤት ረገድ በአገራችን ከ1934 ዓ.ም. ጀምሮ የሸሪዓ ፍርድ ቤቶች የጠነከረ አደረጃጀት ያላቸው ሲሆን፣ በአሁኑ ወቅትም በተለያዩ የእርከን ደረጃዎች የጋብቻ፣ የፍቺና የተወሰኑ የፍትሐ ብሔር የሃይማኖት ጉዳዮችን ይመለከታሉ፡፡ የኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያን የሸረዓ ፍርድ ቤት ዓይነት የተጠናከረ መንፈሳዊ ፍርድ ቤት የሌላት ሲሆን፣ መንፈሳዊ ይዘት ያላቸው ክርክሮች በመደበኛ ፍርድ ቤቶች ብዙ ጉዳዮች በመስተናገድ ላይ መሆናቸው ይስተዋላል፡፡

ምን እየተደረገ ነው?

ስመዐ ጽድቅ ጋዜጣ በህዳር 15-30 ቀን 2004 ዓ.ም. ዕትም ባስነበበው ርዕሰ አንቀጽ የኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያን ቅዱስ ሲኖዶስ ጥቅምት 30 ቀን 2004 ዓ.ም. ባሳለፈው ውሳኔ መንፈሳዊ ፍርድ ቤቶችን ማጠናከሪያ ሕግ ማፅደቁን ዘግቧል፡፡ በዘገባው መሠረት ቤተ ክርስቲያኗ መንፈሳዊ ፍርድ ቤቶች የሚጠናከሩበትን ጥናት በመንፈሳዊ አባቶችና በሕግ ባለሙያዎች በማስጠናት በዝርዝር ሕግ እንደገና እንዲደራጁ ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ጥያቄው መቅረቡን ገልጿል፡፡ ቤተ ክርስቲያኗ በመዋቅሯ አጠቃላይ አሠራር፣ በአገልጋዮቹና ምዕመናን እንዲሁም በተቋማቱ ውስጥ የሚከሰቱ ጉዳዮች በመደበኛዎቹ የፍትሕ አካላት ከመታየታቸው ይልቅ ለቤተ ክርስቲያኗ ልዕልና፣ ለአገልጋዮቿ ካህናት ሃይማኖታዊ ክብር፣ የአገልግሎቱን መንፈሳዊ ሥርዓትና ምስጢራት ሒደትና አፈጻጸም ወዘተ በሚገባ መርምሮና ተገንዝቦ አስፈላጊው ፍትሕ ለመስጠት መንፈሳዊ ፍርድ ቤቶች የተሻለ አማራጭ መሆናቸውን አምናለች፡፡

ይህ የቤተ ክርስቲያኗ ዕርምጃ የሃይማኖት ፍርድ ቤት እንደገና የመቋቋማቸውን አስፈላጊነት ወቅታዊ ያደርገዋል፡፡ ሕገ መንግሥቱ ግልጽ ድንጋጌ መያዙና የፍላጐት ዳሰሳውም አስፈላጊነቱን በሚጠቁምበት ወቅት ፍርድ ቤቶቹን ማቋቋም ብዙ ጠቀሜታ ይኖረዋል፡፡ መንፈሳዊ ፍርድ ቤቶች ከተቋቋሙ የሃይማኖት ነፃነት ይጠበቃል፣ የቤተ ክርስቲያኗ ምዕመናንና መንፈሳዊ አገልጋዮች ፍትሕ የማግኘት መብታቸው ይከበራል፣ የሕግ ብዙህነት በሕገ መንግሥቱ በተደነገገው መልኩ በተግባር ይተረጎማል፣ የመደበኛ ፍርድ ቤት ጫና ይቃለላል፣ ፈጣንና ጥራት ያለው ውሳኔ በአነስተኛ ወጪ በፍርድ ቤቶች ማግኘት ይቻላል፡፡ ሌሎችም ብዙ ጥቅሞቹ ይኖሩታል፡፡ ይሁን እንጂ ማቋቋሙና ማደራጀቱ ብዙ ሥራ እንደሚያስፈልገው ሊዘነጋ አይገባም፡፡ ራሱን የቻለ ማቋቋሚያ አዋጅ ማዘጋጀት፣ የሸሪዓ ፍርድ ቤቶችንና በሌሎች አገሮች ያሉ መንፈሳዊ ፍርድ ቤቶችን ልምድ መርጦ መውሰድ፣ በገንዘብ፣ በሰው ኃይልና በአደረጃጀት የሚኖራቸውን ድጋፍ ማሰብ ከቤተ ክርስቲያኗ፣ ከመደበኛ ፍርድ ቤቶችና ከመንግሥት የሚጠበቁ ሥራዎች ይሆናሉ፡፡ መንፈሳዊ ሙግቶች መሠረት የሚያደርጉት መንፈሳዊ ሕጎችን (ዶግማና ቀኖና)  በመሆኑ ሊከናወኑ የሚገባው በመንፈሳዊ ፍርድ ቤቶች ብቻ ነው፡፡

ከአዘጋጁ፡-  ጸሐፊውን በኢሜይል አድራሻቸው getukow@gmail.com ማግኘት ይቻላል፡፡

8 comments:

lamelame europe said...

manefasawe ferede bate manoreo becha sayehone bawesetome manefasawe daga yasefalegalr.ahone enedalawe bate kehenate enedaiehonee.

Anonymous said...

Deje Selam thank you very mach melkam neger asemashin Papasu- Melkusew presitu- Diyakonu - Zeemariw -Sebakiwe Balem Fird Bet mewal mekiret alebet Ayer Tsina Kidane Mihiret Kahinat tamemu Minalbat yekedesut bicha sietamemu Sigawna Demu YImermer tebilo Hospital mehedun awkaleu yasazinal ahun Kidus Sinodos yihinn kaderege melkam new Bemejemerya asteyayet Yesetsutn Edegifalehu Lefird betu Melkam Daga yasfelgewl Yehayimanotin neger lemayet hayimanot yalew sew yasfelgal yetmaru &Behig yetemereku kahinat yinoralu Mahibere Kidusanim Bizu yetemaru kahinat Alut

ብዕሩ ዘ-አትላንታ said...

ዉድ ደጀ ሰላሞች ለዚህች ቤተ ክርስቲያን ሥርዓት መጠበቅ በየጊዜዉ የምታስነብቡን መልእክቶች በወቅቱ ሊከወኑና ምላሽ ሊሰጥባቸዉ የሚገቡ ነበሩ። ግን ምን ያደርጋል ከላይ ከአናት ያሉ ሁሉ ተናጋሪ ብቻ ሆኑና ፈጻሚና አድማጭ ጠፋ። እናንተ ግን አይዟችሁ በርቱ ቁስላችሁን የሚጋሩ አያሌዎች አሉና። ለዛሬ ስለቀረበዉ የፍትሕ ሀሳብ የሚኖረኝ አስተያየት የሚቀጥለዉ ነዉ።
ፍትሕ በተዛባበት ሀገር ስለምንኖር ተገቢዉን ፍርድ ለማግኘት መቸገር ግድ ነዉ። የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ ክርስቲያን ለትክክለኛዉ ማንኛዉም ዉሳኔ ያላትን አቅም ያጣችዉ በራስዋ መሪዎች መሆኑ አንዱ ገጽታ ነዉ። በመጀመሪያ እንዲህ አይነቱን መንፈሳዊ የፍትህ ተቋም ለማደራጀት ከዉስጥ መጥራት የሚገቡ ሰንኮፎች አሉ። እነዚህ ሰንኮፎች የቤተ ክርስቲያንትዋን ህልዉና በሚፈታተን መልኩ የተደራጁ የመንግሥት የፖለቲካ እጄታዎች ናቸዉ። ቀጥሎም የአንዳን የቤተ ክርስቲያኗ መሪዎች በእግዚአብሔር ከመታመን ይልቅ ለመንግሥት ማጎብደዳቸዉና የዕድሜ ማራዘሚያ እንክብላቸዉ መንግሥት ምስሎ የታያቸዉ ናቸዉ። ለሃይማኖታቸዉና ለቤተ ክርስቲያን አገልግሎት መሾማቸዉን እስከ መዘንጋት የደረሱ ከአባ ጳዉሎስ ጀምሮ እንዳሉ መዘንጋት ያለን አይመስለኝም። ትንሽ ስንቆይ ቅዳሴ ለመቀደስ፣የምህላ ጸሎት ለማድረስ… ወዘተ…. የመንግሥትን ፈቃድ እንዳንጠይቅ እሰጋለሁ……
ከተቻለ ለዚህ ለቀረበዉ ዝርዝር ሀሳብ ተፈጻሚነት እንደ ቤተ ክርስቲያን ልጅነታችን በጋራ ምን ማድረግ እንዳለብን ጠቁሙን።
እስኪ ደግሞ ነገ አያችኋለሁ። ብዕሩ ዘ-አትላንታ

Anonymous said...

መንፈሳዊ ፍርድ ቤት ቢኖር ጥሩ ነበር ነገር ግን ችግሩ ከአናቱ ስለሆነ ፍርድ ቤቶችን አቶ መለስ የበቀል መሳሪያ አድርጓቸዋል:: ዳኞችም ለሱ መሳሪያ ሆነዋል ይህ የተመሰቃቀለና ጭምልቅልቁ የወጣ የፍተህ አሰጣጥ ያስጠላቸው የህግ ባለሞያወች እራሳቸውን አግለዋል ሌሎቹም ህሊናቸውን ያልሸጡ የህግ ባለሞያወች በስደት ወይንም በቃሊቲ ይገኛሉ :: አባ ጳውሎስ የመለስ ጉዳይ አስፈጻሚ እስከሆኑ ድረስ ቤተ ክነትም ሆዳሞች ለገንዘብ የቆሙ ስለሆነ መንፈሳዊ ፍርድ ቤት ቢኖረንም የነሱ መጨማለቂያ ከመሆን አያልፍም:: እንዲያውም እንደ ተሀድሶ አይነቶች አላማቸውን በመንፈሳዊ ፍርድ ቤት እያስወሰኑ ይባሱን ያስቸግራሉ :: መንፈሳዊ ፍርድ ቤት ቢኖር ከሆነ የተማሩ ዳኞች የሚሰሩበት ከአባ ጳውሎስና ከቤተ ክህነት ነጻ የሆነና እነሱም ሊዳኙበት የፍትህ ቦታ ሊሆን ይገባል እላለሁ::

Anonymous said...

Kirstos tense'a e'mutan beabiy hayle wesiltan. . . Wegenoche, b/kirstian yehulu neger minch mehonua emun new. Astedader, hekemna, yedagninet sereatu ena hulum neger yetegegnut kebetekirstian new. Ye-abayin lij wuha temat endilu, b/k yerasua yehone ferd bet kelelat mechiw gize asichegari new yemihonew. Leparlama tiyakew mekrebu des yemiyasegn bihonim beyegizew mastawes yemigeba yimesilegnal. Kir yalegn neger binor, Abatochin mezlef sus eyehonebin yemeta yimesilegnal. Enitseliyilachew enji anizilefachew! Ke-abatochachin silemanibelit. 1nege19:4

Anonymous said...

TIRU TSHUF NEW

Anonymous said...

ይህ በዓለም የሚታየው ነገር ሁሉ ሊሆን ግድ ነው ፡፡ የነበረው፣ ያለው እና የሚኖረው አልፋና ኦሜጋ ሁሉን ቻይ የሆነው አምላከ ቅዱሳን፣ ክቡራን፣ ንዑዳንና ብፁዓን እግዚአብሔር የሚያደርገውን ሁሉን ያውቃልና መሰዳደቡን፣ ጥላቻውን፣ በሰው ሞት መደሠቱን፣ ወሬ ማናፈሱን፣ የሰውን ስሜት በክፉ መፈተኑን ትተን የአምላክን ሥራ (እንቅልፍ የሌለበትን ትጉህ እረኛ) በትዕግሥት እንጠብቅ!! እርሱ የቅዱሳኑን ሥፍራ ለክፉ ነገር አያውልም፡፡ እኛ በእምነት ያለን ሰዎች በፀሎት እንትጋ፡፡ ምናልባት የሕዝቡን ስሜት / ደም / በክፉ ኃሣብና ሥራ ለማሞቅ የሚፈልጉ ሰዎች ከዚህ ድርጊታቸው ቢቆጠቡ መልካም ነው፡፡ ምነው የጣልያን ወረራን፣ የነ ግራኝ መሐመድንና የነ ዮዲት ጉዲትን ታሪክ ብናወሳ በፀሎት መሰለኝ እኮ አገራችን የእግዚአብሔርን እርዳታ ያገኘችው እንጂ የትኛው የመሣሪያ ብዛት እና ሥልጣኔዋ ነው ለማንኛውም በቅድሥት ሥላሴ የምታምን ዜጋ ሁሉ ወደ ራስህ ተመልከት እና አንድ አቡነ ዘበሰማያት ድገም ይህ መሰለኝ የሚሻለሁ፡፡ ለሁላችንም ልቡና ይስጠን፤፤፤

Anonymous said...

'ሰው ዝም ብሎ የእግዚአብሔርን ማዳን ቢጠብቅ መልካም
ነው'

ተብሎ በቃሉ እንደተነገረን ሁሉን ማድረግና ማንም ሊቀድመው ለሚችል አምላክ በእውነትና በመንፈስ ሁነን ብናስረክበው መልካም ውጤት ማስመዝገብ ይቻላል:: የእግዚአብሔር መንግሥት የወሬ ጉዳይ ሳይሆን በራሱ በመንፈስ ቅዱስ ኃይልና ስልጣን የሚሠራ መሆኑን በሚገባ ብንረዳ አስተዋይነት ነው::

ስለዚህ ፍከራውንና ሌላውን የሥጋ ነገር ትተን በመንፈስ አንድነት በልምድ ሳይሆን በቃሉ መረዳት ላይ ያተኮረ ሥራ እጅለእጅ ተያይዘን ብንሰር መልካም ይሆናል ብየ አምናለሁ::

ቸር ይግጠመን

እውነቱ

Blog Archive

የአቡነ ጳውሎስ "ሐውልተ ስምዕ"

ነጻ ፓትርያርክ ምርጫ ቢሆን ኖሮ ማንን ይመርጡ ነበር? እንበልና ሁሉም ነገር ሥርዓቱን ጠብቆ የተከናወነ የእጩዎች ምርጫ ቢሆን ኖሮ፣ አሁን የምናነሣቸው ጉድለቶች ባይኖሩ ኖሮ፣ 6ኛው ፓትርያርክ እንዲሆን የምትመርጡት ማንን ነበር? (ማሳሰቢያ፦ አሁን ያለው ክፍፍል እና የመንግሥት ተጽዕኖ ባይኖር ኖሮ ተብሎ የሚመለስ ጥያቄ ነው። የምን “ባይኖር ኖሮ ነው” የሚል አስተያየት ካለዎትም እናከብራለን።)