April 17, 2012

ሪፖርታዥ፦ የዋልድባ መድኃኔዓለም ተሳላሚዎች ምስክርነት


  • READ THIS ARTICLE IN PDF.
  • ገዳሙ በከፍተኛ የፖሊስ ኀይል ስምሪት ውስጥ ወድቋል
  •  መነኰሳት በአባትነታቸው አይከበሩም፤ ይዘለፋሉ፤ ይታሰራሉ፤ ጸሎተ ምሕላ በማኅበር እንዳያደርሱ ተከልክለዋል
  • ከአንድ ኪ.ሜ ያላነሰ የገዳሙ መሬት የፕሮጀክቱ አካል ኾኗል
  •  “ስለሚታረሰው አያገባችኹም፤ ስለተተኮሰባችኹና ስለተደበደባችኹት አያገባንም” /አቡነ ኤልሳዕ ለተሳላሚዎቹ ጥያቄ የሰጡት ምላሽ/። 
  •  “እውነቱን ከማኅበረ ቅዱሳን ልኡካን ሪፖርትና መግለጫ እንጠብቃለን” /ተሳላሚ ምእመናኑ/

(ደጀ ሰላም፤ ሚያዚያ 8/2004 ዓ.ም፤ April 16/2012)፦ መጋቢት 20 ቀን 2004 ዓ.ም፤ የመድኃኔዓለምን በዓል በአብረንታንት ዋልድባ ገዳም ለማክበር ወደዚያው ለማምራት ተዘጋጅተናል፡፡ መነሻችን ከጎንደር ከተማ ነው፡፡ ካለፉት ዓመታት ጋራ ሲነጻጸር ዘንድሮ  የተሳላሚው ቁጥር አንሶ ይታያል፤ ከጉዟችን በፊት መንገዱ እንደሚዘጋና በርካታ የፌዴራል ፖሊስ ኀይል እንደተላከ አብዝቶ በመሰማቱ የቀረው ሰው ብዙ ነው፡፡

ይኹንና ከከተማው 44 አጥቢያ አብያተ ክርስቲያናት ሰንበት ት/ቤቶች፣ 18 ወጣት ማኅበራት እና 10 የጉዞ ማኅበራት የተውጣጡ ምእመናን በሚኒባሶች እና በሁለት አውቶቡሶች ተጓጉዘን ዓዲ አርቃይ ደርሰናል፤ የእግር ጉዞውም የሚጀመረው ከዚያው ከዓዲ አርቃይ ነው፤ መንገዱ እስከ ዋልድባ ገዳም ድረስ ለበረታው የ12 ሰዓት ለሚያዘግመውም ከ16 - 18 ሰዓታት ይወስዳል፡፡
ከዓዲ አርቃይ ተነሥተን ዶንዶሮቃ የሚባል ገዳም ደረስን፤ ዶንዶሮቃ ገዳም የዋልድባ ገዳም አካል ነው፡፡ ከዚህ ጀምሮ ፍተሻው ከባድ ነው፡፡ ፖሊሶቹ መታወቂያ አምጡ እያሉ እንግልት ያደረሱብን፣ ሻንጣችንንና ለመንገድ የያዝነውን ኮቸሮ ሳይቀር የበረበሩት ከዶንዶሮቃ ጀምሮ ነው፤ ስንከላከላቸው መልሳቸው ሌላ ነው፡፡
ዶንዶሮቃ ገዳም ጠበል አለ፤ ከጠበሉ ቦታ ላይ ገላቸውን በሳሙና የሚታጠቡ ሰዎች አገኘን፡፡ ባለማወቅ ስሕተት የሚሠሩ መንገደኞች ናቸው በሚል ልናስተምራቸው ስንሞክር “አያገባችኹም” ብለው ሰደቡን፤ ልብሳቸውን ሲለብሱም እነርሱ [ፖሊሶቹ] ኾነው ተገኙ፤ በያዙት መሣርያ ስላስፈራሩን ለምነናቸው ጉዟችንን ቀጠልንና ማይ ለበጣ ገባን፡፡ ከማይ ለበጣ ወደ ዋናው ገዳመ ዋልድባ - መድኃኔዓለም ቤተ ክርስቲያን ደረስን፡፡


በገዳሙ ዙሪያ የፌዴራል ደንብ ልብስ የለበሱ ፖሊሶች በብዛት ይታያሉ፤ እኔና ጓደኞቼ ለበዓል ወደ ዋልድባ ገዳም ስንመጣ ይህ ለአምስተኛ ጊዜ ነው፤ ለወትሮው በተወሰነ መልኩ ከሚታየው ሚሊሻ በስተቀር ይህን ያህል ብዛት ያለው ኀይል ገጥሞን አያውቅም፤ አሁን ግን ሁልጊዜም በገዳሙ የሚታየው ሰላማዊ ኹኔታ ጨርሶ ጠፍቶ የጦርነት ድባብ የሰፈነ ነው የሚመስለው፡፡ እንደገባን ያገኘናቸው አባቶችም “ለሚዲያ መግለጫ ሰጥታችኋል፤ በሳተላይት ስልክ ትደዋወላላችኹ” በሚል የታሰሩና የሚፈለጉ አንዳንድ አባቶች እንዳሉ ነው የነገሩን፡፡
መቃብረ አቡነ ሳሙኤልን ተሳለምን፤ በ485 ዓ.ም ከሰሜን ሸዋ ቡልጋ የተነሡ ምእመናን በጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ መሪነት መጋቢት 27 ቀን ወደ ዋልድባ ገዳም ከገቡ በኋላ ምእመናኑ “እኛም ከአንተ አብረን ከአንተ ጋራ” ብለው የመድኃኔዓለም ሎሌ መኾናቸውን በገለጹበት ቃል አብረንታንት ተብሎ የተሰየመውን ጌታችንና ከምእመናኑ የተሰወረበትን ሃሌ ሉያ ዋሻ ተመለከትን፡፡


በመቀጠል ማየ ዮርዳኖስ ወደሚባለው የገዳሙ ጠበል ቤት ገብተን ተጠምቀናል፤ ጠበል ቤቱ የራሱ ቅጽር አለው፤ ከጎኑ ለመጠጥ የሚኾን ውኃም ይቀዳበታል፡፡ ወደ ጠበል ቤቱም ይኹን የመድኃኔዓለም ቤተ ክርስቲያን ወዳለበት ቅጽር የሚገባው ጫማ ተወልቆ ቢኾንም ፖሊሶቹ ከነጫማቸው ሲገቡና ሲወጡ ተመልክተናል፡፡ ከትግራይም ከአማራም ገጠሮች ከመጡ ተሳላሚዎች ብዛት የተነሣ ለመጠመቅም ይኹን የሚጠጣ ውኃ ለመቅዳት በሰልፍ ነበር፤ ምእመኑ እየተገፋፋም ቢኾን ራሱን በራሱ ማስተናበር ልማድ ስላደረገው መብዛቱ ችግር አልነበረም፡፡ ዘንድሮ ግን ፖሊሶቹ በሥርዐት ማስከበር ስም ተሰልፎ ከቆመው ሕዝብ መሀል ገብተው በዘፈቀደ መደብደብና የታጠቁትን መሣርያ ቃታ እያቀባበሉ መደንፋትና ማስፈራራት ሥራቸው አድርገውት ነበር፤ ምላሽ በሚሰጣቸው ሰው ላይማ ይብሱ ነበር፡፡ በዚህ አኳኋን በቦክስ፣ በርግጫ እና በብትር የተመቱ ብዙዎች ናቸው፡፡ በተለይ ፖሊሶቹ ጫማቸውን ለምን እንደማያወልቁ የጠየቀ አንድ ልጅ ዐይኑ ላይ በቦክስ መትተውት ፊቱ አብጦ ነበር፡፡ ለመጸዳዳት ወጣ ስንል እንኳ ወከባው ተመሳሳይ ነበር፡፡ ሃይማኖተኝነቱ ቢጠፋ እንዴት ሰብአዊነቱ እንኳ ይጠፋል?


እስከ አሁን ባለው ቆይታችን ብዙ ወከባ ስላየን ወደ ፕሮጀክቱ አካባቢ ተቃርበን ለማየት በነበረን ዕቅድ ላይ ስጋት ገባን፤ የተፈለገውም ይኸው የፍርሃት ቆፈን እንዲያሳስረን ይመስለኛል፡፡ በመጨረሻ መወሰን ነበረብንና የመጣውን ለመቀበል ቆርጠን 17 ያህል ልጆች በሁለት ቡድን ተከፍለን የውኃው ግድብ ወደሚሠራበት አካባቢ ለመጓዝ ተዘጋጀን፡፡ ከአብረንታንት መድኃኔዓለም ተነሥተን ለሦስት ሰዓት ያህል የእግር ንገድ ተጓዝን፤ አባ ነጻ የተሰኘው ቦታም ደረስን፡፡ ከዚህ በኋላ ግድቡ ወደሚሠራበት የፕሮጀክት ስፍራ ለመድረስ ግማሽ ሰዓት (30 ደቂቃ) ብቻ ነው የወሰደብን፡፡


ግድቡ በሚሠራበት ቦታ ዙሪያ ገባውን ተመለከተን፤ በእይታችን ያረጋገጥነው ሐቅ “አንድ አካፋ አፈር እንኳ አልተዛቀም፤”  እየተባለ ሲሰጡ ከነበሩት መግለጫዎች ጋራ ፈጽሞ የሚጋጭ ነው፡፡ ዶዘሮች፣ ኤክስካቬተር፣ ግሬደር የተባሉት ከባድ ተሽከርካሪዎች በሜዳው ላይ ይታያሉ፡፡ በጄኔሬተር የሚሠራ ባውዛ መብራት ተተክሎ የግድቡ ሥራ ሌት ተቀን እየተፋጠነ መሆኑን ጠይቀን ተረድተናል፡፡ በዚህ ሥራ በዋልድባ በኩል ካለው ተራራ ወደ አባ ነጻ አቅጣጫ ባለው የገዳሙ መሬት ጥምዝምዝ (ዚግዛግ) ጎዳና ያወጣ መሬት ተቆፍሯል፡፡ በዐይን ግምት በዶዘር እየፈረሰ የተቆፈረው መሬት ርዝመት ከአንድ ኪሎ ሜትር አያንስም፡፡ ቁፋሮው የግድቡ መዋቅሮች ግንባታ አካል መኾኑም ተነግሮናል፡፡ወደ አባ ነጻ ተመለስን፡፡ አባ ነጻ ላይ አባቶችን አግኝተናል፡፡ እዚያው እንደ ቆመን አንድ የፕሮጀክቱ ኤክስካቫተር መኪና መጥታ አፈር እያነሣች ስትቆልል አይተናል፡፡ ስለጉዳዩ አባቶችን ስንጠይቅ “ግድቡ ምን ያህል የደለል ችግር ሊኖረው ይችላል የሚለውን ለመመርመር ተብሎ ነው የሚል ምላሽ ነው የሰጡን” ብለውናል፡፡ የብዙ ቅዱሳን ዐፅም በክብር ከፈለሰበትና ከረገፈበት በዚሁ በአባ ነጻ ከሚገኘው የአቡነ ተስፋ ሐዋርያት ቤተ ክርስቲያን በቁፋሮው ምክንያት የፈለሱት ዐፅሞች ጉድጓድ ተቆፍሮ በሲሚንቶ በተለሰነ ቤት ውስጥ መከማቸታቸው ተነግሮናል፡፡ በዚሁ ቦታ አሳዛኙ እውነት ግን በአፈር ምርመራ ስም በገዳሙ ሜዳ ላይ ይህን ሥራ ከሚሠሩ ሠራተኞች መካከል አምስቱ ባልታወቀ ምክንያት መሞታቸው ነው፡፡

የዋልድባ መሬት ከመታረሱ አልፎ የሚፈርሱትን እንደ ዕጣኖ ማርያም፣ ጊዮርጊስ ያሉ አብያተ ክርስቲያናትን ባንሄድባቸውም ያሉበትን አቅጣጫ ጠቁመው አሳይተውናል፡፡ ግድቡ ሲገደብ ወደ ገዳሙ ያለው መልክአ ምድር በጣም ሜዳማ በመሆኑ እስከ አባ ነጻ ያለውን መሬት ላለመጠቀማቸው ምንም ዋስትና የለም፡፡ ይህን ያህል ሚልዮን ብር አውጥተው ገድበው ውኃው ወደ አንድ አቅጣጫ ሊሰፋ አይችልም፤ በዋልድባ ወዲህና ወዲያ ማዶ ባሉት ተራሮች መካከል የሚፈሰው የዛሬማ ወንዝ ሲገደብ ውኃው ወዲህም ወዲያም እኩል ስለሚሰፋ ወዲህ ወደ አባ ነጻ አይገቡበትም ብሎ በርግጠኝነት መናገር ያስቸግራል፤ ሁሉንም ነገር ሲጀመር ቀስ በቀስ ነውና፡፡ ይህን ማረጋገጥ የሚቻለው ደግሞ የፕሮጀክቱ ሓላፊዎች አባ ነጻ ላይ ለተሰበሰቡት አባቶች የነገሯቸውን ስንመለከት ነው፡፡ ምንድን ነው ያሏቸው? - “ውኃ እንሰጣችኋለን፤ ሙዝ የምታጠጡበት ከፈለጋችኹ ወደ እናንተም ስለሚመጣ” ነው ያሏቸው፡፡ የአባ ነጻ አባቶችም እንዲህ በማለት ነው የተከላከሏቸው - “አባቶች ያቆዩን በዚህች ውኃ፣ በዚህች ቋርፍ፣ በዚህች ሙዝ ነው፤ እኛም ባለን ነው የምንቆይ፤ ውኃ አንፈልግም አልናቸው፤” ብለውናል፡፡
እኛ ባይናችን እንዳየነው በመጀመሪያ የግድቡ ውኃ በጣም ብዙ ስለሚሆን የገዳሙ መሬት የመጥለቅለቅ አደጋ ሊያጋጥመው ይችላል፡፡ ሁለተኛ ደግሞ አባቶች በዕጣኖ ማርያም ቤተ ክርስቲያኑ ከሚፈርስበት ላይ የቋርፍ ተክል የሚያለሙበት፣ ሲታመሙ የሚያርፉበት (ሞፈር ቤት የሚባለው) 10 ሄ/ር ያህል መሬት አላቸው፡፡ የፕሮጀክቱ ሓላፊዎች ይህን 10 ሄ/ር መሬት በዕጥፍ አድርገን 20 ሄ/ር ምትክ መሬት ሌላ ቦታ እንሰጣችኋለን እንዳሏቸው የአባ ነጻ አባቶች ነግረውናል፡፡


ከማይ ለበጣ ወዲህ “እህል አይዘራብሽ፤ ኀጢአት አይሻገርብሽ” የሚል ትእዛዝ አለ፤ በፀለምት መሥመር እስከ ዕጣኖ ማርያም መሬቱ በግድቡ ውኃና ብዙ መሬት በሚጠይቀው በሸንኮራ እርሻ ይሞላል፡፡ ለዚህም ሲባል ከ8 - 10 የገጠር ቀበሌዎች ነዋሪዎች ቁጥራቸውን ለጊዜው በውል ከማናውቃቸው አብያተ ክርስቲያናት ጋራ ተነሥተው በሌላ አዲስ መንደር ይሰፍራሉ፡፡ በዚህ ዐይነት በዕጥፍ እንሰጣችኋለን የሚባለው ምትክ መሬት ከገዳሙ በጣም ይርቃል ማለት ነው፡፡ አባቶች ለዚህ ማግባቢያ ያላቸው አስተያየት “አስፋልት ዳር ወስዶ ሊያፈሰን ነው” የሚል ነው፡፡ በእውነቱ በጣም ይረብሻል፡፡ የገጠር አብያተ ክርስቲያናቱ መፍረስ ከሕዝቡ መነሣት ጋራ የተያያዘ ምክንያት ቢሰጠውም በገዳሙ ይዞታ ውስጥ ያለው የቋርፍ ቦታና አብያተ ክርስቲያናቱ መፍረስ ጉዳይ ግን በቀላሉ የሚታይ አይደለም፡፡


በሌላ በኩል የስኳር ፋብሪካው ሲተከል ከፋብሪካው ግዙፍነት ጋራ ሌሎች የአገልግሎት መስጫ /መገልገያ/ ተቋማት አብሮ ይተከላል፤ መኖርያ ቤት፣ መዝናኛ. . .ወዘተ፡፡ መንገዱ በዛሬማ በኩል ለዋናው ገዳም እንዲቀርብ ኾኖ እየተሠራ ነው፤ አሁንም ለኮንስትራክሽኑ ተብሎ መኪና እየገባ ነው፡፡ ከዚህም ጋራ አብሮ የሚመጣውን ጣጣ መገመት አይከብድም፡፡


እነርሱ እንደነገሩን ከሰሜን ምዕራብ ትግራይ - ሽሬ ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ እና የምሥራቃዊ ትግራይ - ዓዲግራት ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ በተገኙበት የፕሮጀክቱ ባለሥልጣናቱ ከማኅበረ መነኰሳቱ ጋራ ስብሰባ አድርገው ነበር፡፡ በስብሰባው ላይ ማኅበረ መነኰሳቱ በልማት ፕሮጀክቱ ላይ ያላቸውን ጥያቄ አንሥተው ሲሟገቱ ከጳጳሳቱ አንዳቸው ስብሰባውን በጸሎት ከመክፈት ሌላው በጸሎት ከመዝጋት በቀር አንዳችም አስተያየት አለመስጠታቸው አስገራሚ ነበር፡፡


የአባ ነጻ አባቶች እንደሚናገሩት የችግሩ መፍትሔ መታገሥና ጸሎት ማድረግ ነው፡፡ ይኹንና በማኅበር ጸሎተ ምሕላ እንዳያደርጉ በግልጽ ተከልክለዋል፡፡ የበርካታ መነኰሳት በኣት ከውጭ በሩ ተቆልፎ አይተናል፡፡ ከእኒህ መነኰሳት ብዙዎቹ በየዋሻው መሸሸጋቸውን ተረድተናል፡፡ ከማኅበረ መነኰሳቱ ለአንዳንዶቹ እንደመሰላቸውወጣት መጥቶ ጦርነት እንደሚያነሣ፣ መነኰሳቱም ወጣቱም እንደሚያልቁአስበው ነበር፡፡ በቡድን ወደ ስፍራው የሄድነው ተሳላሚዎች ግን የዕለት ውዳሴ ማርያም እየደገምን ጸሎተ ምሕላ እናደርስ ነበር፡፡


ወደ ዋናው የአብረንታንት መድኃኔዓለም ቤተ ክርስቲያን ተመለስን፡፡ እናቶች በአንዲቷ ገጣሚነት እየተመሩ ደረታቸውን እየደቁ፣ ጭናቸውን እየመቱ በትግርኛ የሚቀበሉትን ዜማ ቆመን ስንሰማ ነበር፤ እንዲህ ያለ ዜማ የሰማነው ለክብረ በዓል አኵስም ጽዮን ማርያም ሄደን በነበረ ጊዜ ነው፤ በጣም ያሳዝናል፡፡ አስተርጉመን ስንሰማው “ጌታዬ ለእኛ ስትል ተንገላታኽ፤ ለእኛ ስትል ተሰቅለኽ ሞትኽ” የሚል ነበር፡፡ ከቆይታ በኋላ እኛ ቆመን እያየን ፖሊሶቹ መጥተው መሪዋን እናት ከሌሎች ለይተው እያዋከቡ ይዘዋት ሄዱ፤ የተቀሩትም እናቶች ተበታተኑ፡፡ ለምንድን ነው ብለን ስንጠይቅ አቀንቃኟ በግጥሞችዋ ውስጥ “ዋልድባ ታረሰ፣ ታረሰ፤ ዛሬ ነው ወይ የሚታረስ፤ ቤትኽን ጠብቅ አንተ፤” የሚሉ ሐረጎችን በመጨመሯ እንደ ኾነ ነገሩን፡፡ የገጠሩን ሰው እንዲህ በዱላ ሲጨረግዱት ስናይ ፍጹም ሰላም በምንጠብቅበት ቦታ ላይ ሰላም እንደሌለ ስንረዳ አዘንን፤ ጸሎተ ምሕላ አደረስን፡፡


ወደ ዋልድባ ገዳም ከገባን ስድስተኛ ቀን ኾኖናል፡፡ በማግስቱ የመድኃኔዓለም ክብረ በዓል ነው፡፡ በየዓመቱ አንድ ጊዜ ተራ በተራ ለሚከናወነው ጸሎተ ቅዳሴ የዘንድሮ ተረኛ የቤተ ሚናስ ማኅበረ መነኰሳት ነበር፡፡ የዛሬ ዓመት የቅዳሴ ተራው የቤተ ጣዕማ ማኅበረ መነኰሳት (ዘጠኝ መለኰት ይላሉ የሚባሉት) ነበር፤ ልማቱን እንደግፋለን እያሉ ስለመፈረማቸው የሚነገርላቸውና በሚዲያ እየቀረቡ የምናያቸው ቤተ ጣዕማዎች ናቸው፡፡ በጣም የሚገርመው መባዕ ለመሰብሰብ ብቻ ተብሎ የጥንቱን መቃብረ ሳሙኤል ትተው ለእነርሱ በሚያመች ቦታ ሌላ መቃብረ ሳሙኤል ሠርተው ምእመኑ እየተሳሳተ ሲማፀንበትና መባዕ ሲጥልበት ነበር፤ በኋላ ተሳላሚው ወጣት አፈራረሰው፡፡ በዚህ የተነሣ የተፈጠረውን ጠብ የመንግሥት አካል ጣልቃ ገብቶ አስማማቸው ተብሏል፡፡ ዞሮ ዞሮ ያን ያህል ደክመን ሄደን ይህ ዐይነቱ ክፍፍል እዚያ ቦታ ላይ ማየት በተለይ በእምነቱ ላልጠነከረው ምእመን በጣም ጎጂ ነው፡፡


የክብረ በዓሉን ቅዳሴ ጨርሰን ከቀኑ ዘጠኝ ሰዓት ላይ ለመልስ ጉዞ ተነሣን፡፡ ማይ ለበጣ ላይ ገዳሙ ለመድኃኔዓለም በዓል ንፍሮና ጠላ በማዘጋጀት ተሳላሚዎችን ይዘክራል፡፡ እኛም እንደሌላው ተጓዥ እዚያው ቆመን ተዘክረን ማይ ለበጣን ወጥተን ሜዳውን ልናቋርጥ ስንል አንድ አባት በፖሊስ ተይዘው እየተነዱ ሲወሰዱ አየን፡፡ ለነገሩ ቀደም ሲልም የሚፈለጉ፣ የታሰሩም አባቶች እንዳሉ ሰምተናል፡፡


እኚህ አባት ከሕዝቡ ጋራ ተቀላቅለው እየወጡ ነበር፡፡ ፖሊሶቹ ትእዛዝ ተቀብለን ነው በሚል መነኰሱን ወደ ገዳሙ እንዲመለሱ ቢያዝዟቸውም እርሳቸው “መጥሪያ አምጣልኝ፤ አልያ አልሄድም” በሚል ይመላለሳሉ፡፡ ምንድን ነው ብለን ወደያዟቸው አባት ስንቃረብ ፖሊሶቹ “በጭራሽ እንዳትጠጉ! እግር እግርኽን ነው የምሠብርኽ” ብለው መሣርያ አቀባበሉብን፡፡ እንዴ፤ ችግሩ ምንድን ነው? አናግሩን እንጂ እያልን ከመነኩሴው ጋራ እኛም እየተነዳን ስንጠይቃቸው የያዟቸውን አባት ወደ ጥግ አቆሙና ወደ ጎን ይኹን ወደ ላይ ተኮሱ፡፡


ከመሃላችን የተመታብን ሰው እንደሌለ ብናረጋግጥም የመሣርያ ተኩስ ባልጠበቅንበት ቦታ ተኩስ በመስማታችን በጣም አዘንን፤ “ይግደሉን” እያሉ የሚጮኹ ወጣቶችም ነበሩ፡፡ ከመሀላችን አንድ ሰው በተኩሱ ተመቶ ቢቆስል ወይም ቢሞት ዓለም ይደባለቅ ነበር፡፡ ብዙዎቻችን በእኛ የተነሳ ችግሩ እንዳይባባስ ውዝግቡን አብርደን ከፊት ቀድመን፣ ፖሊሶቹና የተያዙት አባት ደግሞ ከኋላ ኾነው ወደ ዶንዶሮቃ መጣን፡፡ ዶንዶሮቃ ከደረስን በኋላ የተያዙት አባት “እኔ የመነኰስኹት ለመከራ ነው፤ ይበለኝ፤ ተመለሱ ልጆቼ” በማለት ለእኛ ሰግተው መከታተላችንን እንድናቆም ስለመከሩን፣ ፖሊሶቹም “ምን ይገትርኻል” እያሉ ስላስፈራሩን ክትትላችንን ብናቋርጥም መነኩሴውን እስከ ዶንዶሮቃ ዘልቀው በሚገቡ የገጠር መንገድ ሥራ ድርጅት መኪና ወደ ማይ ፀብሪ ለመውሰድ በሬዲዮ ትእዛዝ ሲቀበሉ ሰምተናቸዋል፡፡ ፖሊሶቹ መነኰሳቱን እንደ አባት ሲያከብሩ ለማየት አልታደልንም፡፡


ማይ ለበጣ እንደተረገው ሁሉ በዶንዶሮቃና በየቀበሌው ሁሉ እንዲሁ የመድኃኔዓለም ዝክር ነበርና እያረፍን ዝክሩን እየቀማመስን ወደ ዓዲ አርቃይ መንገዳችንን ቀጠልን፡፡ ዓዲ አርቃይ ገብተን ከመካከላችን የጎደለ ሰው እንደሌለ ካረጋገጥን በኋላ ወደ ጎንደር ከመጓዛችን በፊት ዓዲ አርቃይ ፖሊስ ጣቢያ ጎራ ብለን የኾነውን ነገር ሁሉ አስረዳን፡፡ የፖሊስ ጣቢያው ዋና አዛዥ ሪፖርታችንን ከሰሙ በኋላ “እንኳን እናንተ በሰላም መጣችኹ፤ ለተተኮሰውም ለድብደባውም ሁሉንም ነገር እንከታተላለን፤” አሉን፡፡


ረፋድ ላይ ከዓዲ አርቃይ ተነሣን፡፡ ደባርቅ ላይ ምሳ አድርገን ጎንደር ገብተን ከመበታተናችን በፊት ወደ ሀገረ ስብከቱ ጽ/ቤት ሄደን የኾነውን ሁሉ ማስረዳት አለብን በሚል ተስማማን፡፡ ለምን ቢባል በቀደመው ስብሰባ አልታረሰም ያሉት ገዳም ታርሶ አየን፤ አባቶች ሲንገላቱ ተመለከትን፤ በሽብር ምክንያት ገዳሙን ትተው ሊሰደዱ ነው፤ እንደገና ደግሞ በሰላሙ ቦታ ሰላም አጥተናል፤ በእኛ ላይ ተተኩሶብናል፤ ተደብድበናል፤ በሳምንት የዋልድባ ቆይታችን ጀርባና ትክሻቸውን በብትር የተመቱትን ሳንቆጥር ዐይኑን በቦክስ ተመቶ ፊቱ ያበጠው የጎንደር መድኃኔዓለም ዲያቆን ኹኔታ በጣም የሚያሳዝን ነበር፡፡ እኒህን እንኳር ነጥቦች ይዘን ምንም እንኳ በቀደመው ስብሰባ ጥሩ ባይናገሩም ከማንም በላይ ሀገረ ስብከቱ ሓላፊነት አለበት ብለን ሁሉም ተጓዥ ከመኪናው ውስጥ እንዳለ ወደ ሀገረ ስብከቱ ጽ/ቤት አመራን፡፡


በሀገረ ስብከቱ ጽ/ቤት ስንደርስ ሥራ አስኪያጁን መልአከ ሕይወት ቀለም ወርቅን አገኘናቸው፡፡ ሁሉም ሰው ከአውቶቡሱ ሲወርድ “ይህ ሽብር መፍጠር ነው” በማለት ሊያናግሩን ፈቃደኛ አልኾኑም፡፡ ከመካከላችን ስድስት ሰዎች መርጠን ሰደድን፡፡ ለምን እንደመጣን ስንነግራቸው “ስብሰባ ውለን እየወጣን ስለሆነ ብፁዕነታቸው የሚያናግሯችኹ አይመስለኝም” ብለው ጠቅጠቀውን ሊያልፉ ቢሞክሩም ከብዙ ጭቅጭቅ በኋላ ከመረጥናቸው ስድስት ሰዎች ሁለቱ እንዲገቡ ተፈቀደ፤ እንደምንም ከጥበቃ ጋራ ተጋፍተን ሦስተኛ ሰው ጨርንና ገባን፡፡


ሲጀመር በታላቁ ገዳም በመሰንበታችን የበለጠውን ቡራኬ እዚያ ካሉት አባቶች ተቀብለናል፤ ብፁዕነታቸውም ወጥተው እንኳን ደኅና መጣችኹ ብለው በቡራኬ ሊቀበሉን ይገባ ነበር፡፡ የእርሳቸው ቡራኬ ይቅርና እኒያ የላክናቸውን ሦስት ልጆች እንኳ በአግባቡ ተቀብለው አላናገሯቸውም፡፡ ልጆቹ አምስት ደቂቃ ያህል ሳይቆዩ እሳት ለብሰው እሳት ጎርሰው ተመለሱ፡፡ ተወካዮቻችን የገዳሙ መሬት ስለ መታረሱ፣ አባቶች እየተንገላቱ ገዳሙ ሰላም ስለማጣቱ፣ እኛም እንደ ተተኮሰብንና እንደተደበደብን ለሊቀ ጳጳሱ ለማስረዳት ቢሞክሩም የብፁዕነታቸው ምላሽ ግን “ስለሚታረሰው አያገባችኹም፤ ስለተተኮሰባችኹና ስለተደበደባችኹት አያገባንም” የሚል አባታዊነትና መንፈሳዊነት በእጅጉ የጎደለው ንግግር ነበር፡፡


ልጆቹ ይህን አማርኛ ከነገሩን በኋላ ጥቂት የማይባል ተሳፋሪ ከአውቶቡሱ ወርዶ ለመዛለፍ ሞከረ፡፡ በዚህ አኳኋን ብንቆይ ሌላ ነገር ስለሚከተለን “አባ ሳሙኤል ዘዋልድባ፤ መነኰስ ኀያል” የሚለውን የዲያቆን እንግዳወርቅ በቀለ መዝሙር በድምቀት እየዘመርን ወደ መስቀል አደባባይ ሄደን በጸሎት እንደተነሣን በጸሎት ዘግተን ወደ የቤታችን ተበታትነናል፡፡


እኛ በመጨረሻ ነገሩን አወጣነው አወረድነው፤ ከእግዚአብሔር ውጭ ምንም አቅም እንደሌለን ነው የተረዳነው፡፡ በርሓው ላይ ተተኩሶብናል፤ እነርሱም መነኰሳቱም ያልቃሉ እንጂ በሰላም ይመለሳሉ ያለንም አልነበረም፤ በከተማውም እንዲህ አይኾንም ለማለት አይቻልም፡፡ ብዙዎቻችን ቤተ ክርስቲያን እንዲህ ስትዋረድና ስትናቅ አይተን አናውቅም፡፡ ያለን አማራጭ ጸሎት ብቻ ነው፡፡ ወደ ዘጉ አባቶች ቀርበን የእናንተ ጸሎትኮ አይወድቅም ስንላቸው “እናንተም ባላችኹ አቅም በጸሎት ትጉ” ነው ያሉን፡፡
ቤተ ክህነቱ ቤተ ክሕደት ኾኗል፤ አባቶች እንደመከሩን የመጣውን የሚያቆም ምንም ዐይነት ሰብአዊ ኀይል የለም፤ መፍትሔው ይግባኝ ለክርስቶስ ማለት ብቻ ነው የሚያዋጣው፤ እኒያ የትግራይ እናቶች እንዳሉት መድኃኔዓለም ራሱ በአንዳች ተኣምር ቤቱን ይጠብቃልና!!


ከዚህም ጋራ ደግሞ ሌላው ተስፋችን በዋልድባ ሳለን ያገኘናቸው ከአዲስ አበባና ጎንደር የመጡ የማኅበረ ቅዱሳን ልኡካን ናቸው፡፡ መረጃውና ሪፖርቱ ቀርቦ የማኅበሩ አመራር በጋራ ከተመለከተው በኋላ ይፋዊ መግለጫ እንደሚሰጥ አረጋግጠውልናል፡፡ አሁን እኛም ኾነ ሌሎቹ ማኅበራት የእነርሱን ትክክለኛ መግለጫና ሪፖርት እየጠበቅነ ነው፡፡ በእውነቱ እነርሱ የፕሮጀክቱን አካባቢ ለማየት ፈቃድ ስላላቸው፣ ባለሥልጣናቱንና አባቶችን አነጋግረው የድምፅም የምስልም ማስረጃ ስለሚይዙ ከሪፖርታቸው ትልቅ እውነታ ነው የምንጠብቀው፡፡


ቸር ወሬ ያሰማን፤
አሜን፡፡

15 comments:

bante views said...

ቤተ ክህነቱ ቤተ ክሕደት ኾኗል

Anonymous said...

Hi Daer Dejeselamawian and the followers of Orthodox, Is it really fair only to say prey only and just wait what God to do? Ofcourse yes, but we need to stand up together, fight for our religion. As to me, even if, I am fully committed to our discipline, I need everyone of us to stand up together!!

lelr said...

ebakachohe malketa LAEWenate lakomo abatoche nawe.batame azanen amenalaho yekoye enje batakeresetaine tasheanefalache.wayawe lakahadeyane....

solomonretta said...

ሰላም ወንድሞቼ እና እህቶቼ የተሳላሚዎቹ ምስክርነት አሳዛኝ እውነት ነው መፍትሄም ያለው ከሱ ከባለቤቱ ከፈጣሪ ነው ከኛ ደግሞ ምህላና ጰሎት ያስፈልጋል። አንዳንዶቹ ብጵአን ኣባቶችና ቅዱስ ፓትርያርኩ እነርሱማ የሾማቸውን እግዚአብሔርን ረስተው የወያኔ ጉዳይ አስፈጳሚ ሆነዋል። አምላካችን ሀገራችንና በተክርስቲያናችንን ይጠብቅልን።

ዘ ሐመረ ኖህ said...

ይህ በጣምአሳዛኝና አሳፋሪ ነው
መንገድ እንደሚዘጋና የፖሊስ ኀይል እንደተላከ ስለሰማን ብቻ ከገዳም የቀረን ሰዎች: ክርስቲያን ያውም የተዋህዶ ልጆች መሆናችን በእጅጉ ያጠራጥራል፡፡ እውን እኛ የአባቶቻችን ልጆች ነን? ከፊታችሁ ፖሊስ ሳይሆን ሰይፍ ይጠብቃችኋለ ብንባልማ ባለንበት ቦታ ምን እንድምንሆን እግዚአብሔር ይወቅ፡፡ በጥንት ዘመን አጼ ሱስኒዮስ በአዋጅ ተዋህዶን ለመሻር ሲሞክሩ እውነተኞቹ አባቶቻችን ሰማእትነት አያምልጣችሁ ተባብለው በመጠራራት በአንድ ቀን ወደ 8 ሺ ሰው ተሰውቶ የተዋህዶ እምነትና ሃገራችን ከፋሽስት የሃገርና የሃይማኖት ወረራ ልትተርፍ መቻሏን ለአብነት ያክል መጥቀስ ይቻላል። ታድያ እኛ የነዚህ ሰማእታት ልጆች ነን? ታድያ መንግስት ቢንቀንና ቤተክርስቲያናትን ቢያፈርስብን ገዳማትን ቢያርስብን ይፈረድበታል እድሜ ይስጠን እንጂ ገና እንደ በሬ ጠምዶ ያርስብናል የሰው ልጅ ተራ መብቶቹን እንኳን አላስነካም ካላለ ከእንስሳ በምን ይለያል ? አሕዛብ ከኛ መማር ሲገባቸው እኛ ከነሱ መማር ያቅተን ለጥቂት መብታቸው እንዴት እንደሚታገሉ አልሰማን ይሆን?

Anonymous said...

no one is responsible for not doing anything against this project, except who are Christians. so if we are let us do something, let us reveal who we are because we are insulted by this government. please be together pray and do what we can do. We have many options from network to street jamming

Anonymous said...

I wish I was born 10 generations back. It's just so sad!

Anonymous said...

I believe that God will keep His children, the father monks in that Monastery. Gin Merdokios leaster endalat new; behual kehizibish satihogn endatikeri endatazignim Egziabehre hizbun bemiadinibet menged yadenachewal endale. Truly, prayers require. We need more than that, we now need activists, beka. I may not be wronged if I suspect the report from MK would also be a mild one. Everything is seen with suspicion from the side of the government. So, it may intervene and tries to put pressure on the team or the association not to disclose the real problem in a way inducing us come out and ask for our rights. In that case we just see what will happen (what God will do) to the project and the people engaged in that project and the ruling party itself. Or some from us may die. Or if it may be the end of the ruling party then no one will do nothing but remain and see what will happen in near future. Bertuna tseliyu. YeIsrael chuhet eyarihon kitir mafires kechale ye 40 mn hizibe kiristian and abunezebesemayatema, keewinet kelib kehone nekuan yeand yesikuar factory yikir ena lelam maferes bechale neber....Nabute yet ale, Atnasius yet hede, Kidus Yohannes Afework....

well said...

ይድረስ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ሊቃነ ጳጳሳት! እንደ ዶቅልጥያኖስ ዘመን አብያተ ክርስቲያናት ይዘጉ የኢአማንያ ቤቶች ይከፈቱ ተብሎ እንደታወጀ ያህል በአሁንኑ ሰዓት በሀገራችን ኢትዮጵያ ተዋሕዶ ሐይማኖትን ለማጥፋት እየተፈጸመ ያለው ግፍ በተለይ ጥንታውያ አብያተ ክርስቲያናትና አገልጋዮቿ ታሪኳና ሥነ ጽሁፏ ባህሏ.. ለመደምሰስ እየተደረገ ያለውን መከራ እያያችሁ የእናተ ሥራ ምንድነው? በመላው ኢትዮጵያ አብያተ ክርስቲያናት ላይ የሚደርሰውን በደል እያያችሁ ለምን ዝም ትላላችሁ? ሥጋዊ ድሎት ለእናተ በውኑ አስፈለጋችሁን? ምዕመናን እንዲህ ለቤተ ክርስቲያኒቱ ሲሟገቱ ሲንገላቱ ሲደበደቡ... እናተ ምን ይሰማችሁ የሆን? እባካችሁ ምሳሌ ሁኑ " ቅዱስ ሲኖዶስ የተባለ ምንም ሥራ የማይሰራ ቅዱስን ስም ይዞ ግን አሳፋሪ ምን እየተሰራ ነው? አሁን ለሁላችሁም አልታያችሁም እግዚአብሔር ይፈርዳል ብቻችሁን ትቆማላችሁ ትውልዱ ሲረግማችሁ ነው የሚኖረው አንድ ቀን እግዚአብሔር ለቤተ ክርስቲያናችን እውነተኛ አባቶችን ያነሳና እንባችንን ያብስልናል ይልቁንም አሁን ነው ሰማዕትነት የምትቀበሉበት ሰዓት ተጠቀሙበት ከእናተ መካክል ከዚህ ዓለም ቦት የተለዩ ይህን ጉድ ሳያዩ ያለፉ አባቶች እጅግ የታደሉ ናቸው አሁንም ብጹአን አባቶች እባካችሁ ከክርስቶስ የተሰጣችሁን አደራ ተወጡ አትፍረሩ ሥጋችሁን እንቺ ነፍሳችሁን ሊነካ የሚችል የለም ይልቁንም እጅግ መፍራት ነፍስና ሥጋ በአንድነት ወደ ሲኦል የሚጥለውን ፍሩ። ስለወላዲተ አምላክ ድንግል ማርያም ስለቅዱሳን ስለሰማዕታት ሁሉን ቻይ በሆነው በእግዚአብሔር ብላችሁ ተነሱ ተናገሩ ሐይማቶታችንን አስከብሩልን እውነተኛ የሐይማኖት አባት አለን ብለን እንኩራ

lele said...

ya8000 abatoche.yaletadalachohe.wayawe laega enaneta zeme betelo denegaye yameanager AMELAKE alane,

መላኩ said...

"እነሆ፥ እሳት የምታነድዱ የእሳትንም ወላፈን የምትታጠቁ ሁላችሁ፥ በእሳታችሁ ነበልባል ባነደዳችሁትም ወላፈን ሂዱ፤ ይህ ከእጄ ይሆንባችኋል፤ በኀዘን ትተኛላችሁ።" ትንቢተ ኢሳይያስ ምዕራፍ 50፡11

Anonymous said...

ውድ የኛ አባቶች... ሌላው እስላማዊ መንግስት ሊመሰርት ሲታገል እናንተ ደግሞ ..የፓርቲ መታወቂያችሁ እንዳይወሰድባችሁ ፈርታችሁ ገዳማችሁን አሳርሱት፡፡ እግዚኦ መሃረነ ክርስቶስ!!!!!

Anonymous said...

ይድረስ ለሰሜን ጎንደር ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ አቡነ ኤልሳዕ

ብጹእነተዎ የደቡብ ጎንደር ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ በነበሩበት ወቅት ወቅቱ ቁማርተኛው አባ ጳዉሎስ የቤተልሄምን የድጓ ማስመስከሪያ ትምህርት ቤት ለማዘጋት ሌት ተቀን ሲቋምጡ በነበረበት ወቅት ከጀግናው የቤተልሄም እና የጋይንት ህዝብ ጋር ሆነው ሴራውን ማክሸፈዎ ይታወቃል:: ይህ ስራዎ በትውልድ ዘንድ ሲያስመሰግነዎት ይኖሪል:: በአሁኑ ዘመን ሀገራችን ካፈራቻቸው ዳግማዊ "አቡነ ጴጥሮስ" መካከል አንዱ ሊሆኑ ይችላሉ ተብለው ተስፋ ከተጣለባቸው አባቶች መካከል ነበሩ::

ነገር ግን በአሁኑ ወቅት ያ አቋመዎ እልም ብሎ ጠፍቶ የፖለቲካ አስፈጻሚ ሆነው ለቤተ ክርስቲያን ትልቅ ፈተና ሆነዋል::ቅዱስ ጳውሎስ እንዳለው " እስከመጨረሻ የሚፀና እሱ ይድናል" ስለሚል ፈጥነው ንስሀ ይግቡ እግዚአብሄር መሀሪ ነው ይቅር ይለዎታል::

በቅዱስ ሲኖዶስ ዙሪያ የተሰበሰባችሁ የያዛችሁት መስቀል ታሪክ የማይረሳው አርበኛ "አቡነ ጴጥሮስ" የያዘውን ነው:: በያዛችሁት መስቀል "ባለ ሀውልቱን ጳውሎስን" አውግዙበት አልባለዚያ መስቀላችሁን ሁሉ ለቤተ ክርስቲያን መልሱ:: እነናቡቴን እግዚአብሄር ከምእመኑ ያስነሳ እንደሆነ ማን ያውቃል::

እግዚአብሄር ቸር ወሬ ያሰማን

Anonymous said...

ዶንዶሮቃ ገዳም ጠበል አለ፤ ከጠበሉ ቦታ ላይ ገላቸውን በሳሙና የሚታጠቡ ሰዎች አገኘን፡፡ ባለማወቅ ስሕተት የሚሠሩ መንገደኞች ናቸው በሚል ልናስተምራቸው ስንሞክር “አያገባችኹም” ብለው ሰደቡን፤ ልብሳቸውን ሲለብሱም እነርሱ [ፖሊሶቹ] ኾነው ተገኙ፤ በያዙት መሣርያ ስላስፈራሩን ለምነናቸው ጉዟችንን ቀጠልን

ወደ ጠበል ቤቱም ይኹን የመድኃኔዓለም ቤተ ክርስቲያን ወዳለበት ቅጽር የሚገባው ጫማ ተወልቆ ቢኾንም ፖሊሶቹ ከነጫማቸው ሲገቡና ሲወጡ ተመልክተናል፡፡

ዘንድሮ ግን ፖሊሶቹ በሥርዐት ማስከበር ስም ተሰልፎ ከቆመው ሕዝብ መሀል ገብተው በዘፈቀደ መደብደብና የታጠቁትን መሣርያ ቃታ እያቀባበሉ መደንፋትና ማስፈራራት ሥራቸው አድርገውት ነበር፤ ምላሽ በሚሰጣቸው ሰው ላይማ ይብሱ ነበር፡፡ በዚህ አኳኋን በቦክስ፣ በርግጫ እና በብትር የተመቱ ብዙዎች ናቸው፡፡ በተለይ ፖሊሶቹ ጫማቸውን ለምን እንደማያወልቁ የጠየቀ አንድ ልጅ ዐይኑ ላይ በቦክስ መትተውት ፊቱ አብጦ ነበር

ወገኖቼ ቀጣዩን የወንጌል ክፍል እያነበብን እናስተውል

'እንግዲህ በነቢዩ በዳንኤል የተባለውን የጥፋትን ርኩሰት በተቀደሰችው ስፍራ ቆሞ ስታዩ፥ አንባቢው ያስተውል' ማቴዎስ 24:15

Anonymous said...

በዉኑ እግዚአብሔር በዋልድባ አንድ ኤልያስ የለዉምን???

Blog Archive

የአቡነ ጳውሎስ "ሐውልተ ስምዕ"

ነጻ ፓትርያርክ ምርጫ ቢሆን ኖሮ ማንን ይመርጡ ነበር? እንበልና ሁሉም ነገር ሥርዓቱን ጠብቆ የተከናወነ የእጩዎች ምርጫ ቢሆን ኖሮ፣ አሁን የምናነሣቸው ጉድለቶች ባይኖሩ ኖሮ፣ 6ኛው ፓትርያርክ እንዲሆን የምትመርጡት ማንን ነበር? (ማሳሰቢያ፦ አሁን ያለው ክፍፍል እና የመንግሥት ተጽዕኖ ባይኖር ኖሮ ተብሎ የሚመለስ ጥያቄ ነው። የምን “ባይኖር ኖሮ ነው” የሚል አስተያየት ካለዎትም እናከብራለን።)