March 20, 2012

ተጨማሪ መረጃዎች:- የዝቋላ ገዳም አሁን ያለበት ደረጃ

(ደጀ ሰላም፤ መጋቢት 11/2004 ዓ.ም፤ ማርች 20/2012/ READ THIS ARTICLE IN PDF)፦
Picture: Courtesy of Nigusie Girma
የዝቋላን ገዳም ቃጠሎ ለመከላከል እየተደረገ ባለው ጥረት፡-
·     ቃጠሎውን ጨርሶ ለማጥፋት የአቢሲኒያ የበረራ አገልግሎት አውሮፕላን ለመስጠት ፈቃደኛ ነው፤ ሂሊኮፕተርም ከአየር ኀይል ለማግኘት ዕድሉ አለ፤ ይሁንና የመርጫ መሣሪያ ቴክኖሎጂ በአገሪቱ የለም፤ የኬሚካሉም መወደድ ችግር ሆኗል፡፡
·      አሁን ባለው የቴክኖሎጂ አቅም በዝቅተኛ ከፍታ እየበረሩ ወደ ጥልቁ ገደልና ጫካ ውኃ ብቻ ለመርጨት ቢሞከር አደጋ መጋበዝ ይሆናል፤ በከፍታ በረራ ቢረጭ ደግሞ ውኃው አየር ላይ ነው የሚቀረው፡፡ በመሆኑም ዘልቆ ሊወርድ የሚችለውን የማጥፊያ ኬሚካል በውድ ዋጋ ለማግኘት ቢቻል እንኳ የመርጫ መሣሪያው በእጅጉ አስፈላጊ ይሆናል፡፡
·     የአደጋ መከላከልና ዝግጁነት ያሰማራው ኀይለ ግብር የተዳፈነው እሳት አሁን ካለበት የባሰ እንዳይዛመት እሳተ ከላ(Fire Break) በግንድ፣ በቅጠሉ መሥራት እንደ ተሻለ አማራጭ ውስዶ እየተረባረበ ነው፡፡ ቃጠሎውን ለመከላከል የሚመጡ ምእመናንም የዝቋላን አቀበት ተቋቁመው ወጥተው በምንጣሮ፣ በቁፋሮ፣ በሸክም ለመራዳት የሚችሉ መሆን ይገባቸዋል፡፡

Picture: Courtesy of Nigusie Girma 
·                     በየቦታው የተከማቸው የቃጠሎ ፍሕም በጣም ብዙ ነው፤ በተደጋጋሚ ቃጠሎ የመቀስቀስ ዕድሉ ከፍተኛ ነው፡፡ አሁን ባለን መረጃ ንት ሌሊት እና ዛሬ ጠዋት ዳግመኛ የተቀሰቀሰው እሳቱ በገዳሙ ከብቶች ማደሪያ በኩል ወደ ገዳሙ እያቀና ነው ተብሏል፡፡ ከጸሎቱ ባሻገር ለእሳቱ መጥፋት ዘላቂ መፍትሔ ለመስጠት እርጥበት አጠር ከሆነው አየር አኳያ ርግጠኛ ለመሆን ጉልበት ያለው የሰው ኃይል በጣም አስፈልጓል፡፡
·                     የዝቋላን ገዳም ቃጠሎ ለመከላከል የተሰማሩ ወጣቶች በጠቅላይ ቤተ ክህነት ናቸው - ተቃውሟቸውን ለመግለጽ፣ ጥያቄያቸውንም ለማቅረብ፡፡ ፖሊስ ወጣቶቹ እንዲበተኑ እያዘዘ ነው፡፡
·                     በጠቅላይ ቤተ ክህነቱ ወጣቶቹን የሚያነጋግር ሓላፊ የለም፤ ዋና ሥራ አስኪያጁ ብፁዕ አቡነ ፊልጶስ ከፓትርያሪክ አቡነ ጳውሎስ ጋራ በአሁኑ ሰዓት በቅዱስ ማርቆስ ካቴድራል እየተከናወነ በሚገኘው የብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ሲኖዳ የቀብር ሥነ ሥርዐት ላይ ለመገኘት ትላንት ማምሻውን ሄደዋል፡፡ ለጉዞው ከ44,000 ብር በላይ ወጪ ተደርጓል፡፡ ብሔራዊ የኀዘን ቀን የታወጀ ሲሆን ከሥነ ሥርዐቱ ፍጻሜ በኋላ የቅዱስነታቸው አስከሬን በወታደራዊ ሄሊኮፕተር ተወስዶ ከካይሮ 100 ኪ.ሜ ርቀት ናይል ዴልታ ዋዲ ኤል ናጥሩን የቅዱስ ቢሾይ ገዳም እንደሚያርፍ ተዘግቧል፡፡
·                     የገዳማት አስተዳደር መምሪያ ሓላፊ ንቡረ እድ አባ ገብረ ማርያም ያሉበት ኮሚቴ ቃጠሎው ከተነሣ አራት ቀናት በኋላ ዛሬ ወደ ዝቋላ አምርቷል፡፡ የምሥራቅ ሸዋ ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ ብፁዕ አቡነ ጎርጎርዮስ በገዳሙ ጸሎተ ቅዳሴ ላይ ናቸው፡፡
Picture: Courtesy of Laekemariam Dibabu
·      ከፍተኛ ቁጥር ያለው ምእመን ቃጠሎውን ለመከላከል የሚረዱ የግል መሣሪያዎችን (ጄሪካን፣ የቁፋሮ፣ መቁረጫ መሣሪያዎች) እና ደረቅ ስንቅ በመያዝ ከአዲስ አበባ፣ አዳማ እና ቢሾፍቱ ወደ ዝቋላ እየተመመ ነው፡፡
·                     በተለያዩ የብዙኀን መገናኛዎች እሳቱ ጨርሶ እንደጠፋና ለመከላከል እንደተቻለ የሚሰራጨው ዘገባ በቦታው በመሬት ላይ ከሚታየው ሐቅ ጋራ ያልተጣጣመ በመሆኑ ሳንዘናጋና ሳንሳነፍ ታሪካዊ ግዴታንን ባለን አቅም እንወጣ!!!

ቸር ወሬ ያሰማን

አሜን

Post a Comment

Blog Archive

የአቡነ ጳውሎስ "ሐውልተ ስምዕ"

ነጻ ፓትርያርክ ምርጫ ቢሆን ኖሮ ማንን ይመርጡ ነበር? እንበልና ሁሉም ነገር ሥርዓቱን ጠብቆ የተከናወነ የእጩዎች ምርጫ ቢሆን ኖሮ፣ አሁን የምናነሣቸው ጉድለቶች ባይኖሩ ኖሮ፣ 6ኛው ፓትርያርክ እንዲሆን የምትመርጡት ማንን ነበር? (ማሳሰቢያ፦ አሁን ያለው ክፍፍል እና የመንግሥት ተጽዕኖ ባይኖር ኖሮ ተብሎ የሚመለስ ጥያቄ ነው። የምን “ባይኖር ኖሮ ነው” የሚል አስተያየት ካለዎትም እናከብራለን።)