March 21, 2012

የዝቋላን ቃጠሎ ለመከላከል ዓለም አቀፍ ድጋፍ ተጀምሯል


·         በሰሜን አሜሪካ እና በአውሮፓ የሚኖሩ ኦርቶዶክሳውያን የገንዘብ አስተዋፅኦ እያደረጉ ነው
·         ሌሊቱን የእሳቱ መዛመት መሻሻል ቢታይበትም የፍሕሙ መብዛትና የአየሩ ሁኔታ አሁንም ያሰጋል
 (ደጀ ሰላም፤ መጋቢት 12/2004 ዓ.ም፤ ማርች 21/2012 PDF)፦ በዝቋላ ገዳምና አካባቢው የተቀሰቀሰው ቃጠሎ ዛሬ፣ መጋቢት 13 ቀን 2004 . አምስተኛ ቀኑን አስቆጥሯል፡፡ ንት ሌሊቱንና ቀትር ላይ በአደገኛ ሁኔታ እንደ አዲስ ተቀስቅሶ የነበረው የቃጠሎው መዛመት ዛሬ ሌሊቱን መሻሻል እንደታየበት የገዳሙ መነኰሳት ገልጸዋል፡፡
ይሁንና በየገመገሙ (በየጋራው) ሥር የተከማቸው ፍሕም መጥፋቱ በሚገባ ካልተረጋገጠ ከሌሊቱ ነፋስና ከቀኑ ዋዕይ የተነሣ ዳግመኛ እሳት ሊቀሰቀስ እንደሚችል መነኰሳቱ ያላቸውን ስጋት ተናግረዋል፡፡ እስከ አሁን በተደረገው የመከላከል ጥረት በገዳሙ መዳረሻዎች ሁሉ የእሳቱን መስፋፋት የሚያግዱ መከላከያዎች ተሠርተዋል፤ ለቃጠሎው አናዳጅ/ አቀጣጣይ የሆኑ ነገሮች እንዲመነጠሩ ተደርዋል፡፡
በሌላ በኩል በቀደሙ ዘገባዎቻችን እንዳመለከትነው ፖሊስ ወደ ዝቋላ እያመሩ ያሉ መኪኖችን ከመንገድ ማገዱን ቀጥሏል፡፡ ንት ከአዲስ አበባ በርካታ ምእመናንን ጭነው ምሽቱን ደብረ ዘይት ከገቡት አምስት መኪኖች አንዱ ብቻ ለማለፍ ሲፈቀድለት ሌሎቹ በዚያው በደብረ ዘይት እንዲያድሩ ተደርገዋል፡፡ እንዲያልፍ የተፈቀደለት አንድ መኪና በዝቋላ ቃጠሎውን ለማጥፋት በመረባረብ ላይ ለሚገኙ ወገኖች ስንቅ የያዘ መሆኑ ተገልጧል፡፡
ቃጠሎውን ለመከላከል ከየአቅጣጫው ከተነቃነቁት በርካታ ምእመናን መካከል ከጋዜጠኛ ጋራ በተፈጠረ አለመግባባት በሦስት የአዳማ ዩኒቨርስቲ ተማሪዎች ላይ የደረሰው የመቁሰል አደጋ ያሳሰባቸው የምሥራቅ ሸዋ ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ ብፁዕ አቡነ ጎርጎርዮ አዳራቸውን በዚያው በገዳሙ ማድረጋቸው ተነግሮናል፡፡
በሌላ በኩል በገዳማት ህልውና ላይ የተጋረጠው አደጋ ኦርቶዶክሳውያንን በዓለም አቀፍ ደረጃ አገናኝቶ እያነጋገረ ነው፡፡ ትናንት ቀንም ማታም በሰሜን አሜሪካ የሚኖሩ ምእመናን ባካሄዱት ቴሌ ኮንፍረንስ በገዳማት አጠቃላይ ህልውና ላይ የተደቀነው አደጋ ከፍተኛ ቁጣ መቀስቀሱን ተረድተናል፡፡ መንግሥት ከሚወተውተው የልማት አጀንዳ ባሻገር የቤተ ክርስቲያንንም ድምፅ መስማት እንደሚገባው ምእመናኑ አሳስበዋል፡፡ ወቅቱ የሚጠይቀው ሰማዕትነትም የቤተ ክርስቲያንን መብት የሚጋፉ የማንኛውም አካል ርምጃዎችን በጋራ መከላከል፣ መግራትና ማስወገድ መሆኑን በድርቡ ተሰምሮበታል፡፡
በሰሜን አሜሪካ የማኅበረ ቅዱሳን የአሜሪካ ማእከል፣ በሰንበት /ቤቶች አንድነት ጉባኤ እና በማኅበረ በዓለ ወልድ አስተባባሪነት ‹‹በዝቋላ ገዳም እና አካባቢው ደን ላይ የተነሣውን እሳት ለማጥፋት ለሚደረገው ጥረት የግል ልገሳዎን ይስጡ›› በሚል ርእሰ ጉዳይ በተካሄደው የኦርቶዶክሳውያኑ የስልክ ጉባኤ አስቸኳይ የገንዘብ አስተዋፅኦ የማሰባሰብ ሥራ እንዲሠራ ስምምነት ላይ ተደርሷል፡፡ ዓላማውም፡- ‹‹በአሁኑ ወቅት እሳቱን ለማጥፋት ከየአካባቢው በነቂስ ለወጣው ኢትዮጵያዊ ወገናችን ጉሮሮውን ማርጠቢያ ውኃ፣ ጉልበቱን መደገፊያ ዳቦ ማቅረቢያ እንዲሆን የታሰበ ነው። በባዶ እጁ፣ በቅጠል እና በአፈር ቋያ እሳት ለማጥፋት እየታገለ ላለው ወገን አለኝታነታችንን ለመግለጽ›› መሆኑ ተገልጧል፡፡
በመሆኑም ለጥረቱ በጎ ፈቃድ ያላቸው የቤተ ክርስቲን ልጆች ሁሉ በተከታዩ አድራሻ በመግባት ልገሳ እንዲደርጉ ጥሪ ተላልፏል - http://zekuala.mahiberekidusan.org/ or http://www.eotc-nassu.org/

ቸር ወሬ ያሰማን

አሜን

Post a Comment

Blog Archive

የአቡነ ጳውሎስ "ሐውልተ ስምዕ"

ነጻ ፓትርያርክ ምርጫ ቢሆን ኖሮ ማንን ይመርጡ ነበር? እንበልና ሁሉም ነገር ሥርዓቱን ጠብቆ የተከናወነ የእጩዎች ምርጫ ቢሆን ኖሮ፣ አሁን የምናነሣቸው ጉድለቶች ባይኖሩ ኖሮ፣ 6ኛው ፓትርያርክ እንዲሆን የምትመርጡት ማንን ነበር? (ማሳሰቢያ፦ አሁን ያለው ክፍፍል እና የመንግሥት ተጽዕኖ ባይኖር ኖሮ ተብሎ የሚመለስ ጥያቄ ነው። የምን “ባይኖር ኖሮ ነው” የሚል አስተያየት ካለዎትም እናከብራለን።)