March 17, 2012

መ/ር ዘመድኩን በአስቸጋሪው የታራሚዎች ዞን ሐዋርያዊ ተልእኮውን እየፈጸመ ነው


·         የቦሌው ምድብ ችሎት በመ/ር ዘመድኩን ላይ የጥፋተኝነት ውሳኔ ሰጥቷል::
·  የሃይማኖት ሕጸጽን የመዳኘት ሥልጣን የለኝም ያለው ፍ/ቤቱ የበጋሻውን የማስተማር ፈቃድ አስመልክቶ በዐቃቤ ሕግ የቀረቡ ማስረጃዎችን ውድቅ አድርጓል::
·         ዲያቆን ደስታ ጌታሁን ይግባኝ ይጠይቃሉ::
·         የሰባክያነ ወንጌል ፀረ ፕሮቴስታንታዊ ተሐድሶ ፅምረት መግለጫ ያወጣል::
·         የፕሮቴስታንት ቤተ እምነት የሚያዘውትሩት የጠቅላይ ቤተ ክህነቱ መዝገብ ቤት ሓላፊ የሥራ ግዴታቸውን በቅንነት ባለመፈጸም ከሕገ ወጦቹ ጋራ ያላቸውን ትብብር አሳይተዋል::

(ደጀ ሰላም፣ መጋቢት 7/2004 ዓ.ም፤ March 16/2012READ THIS ARTICLE)፦ ቤተ ሞቅሕ የግዞት፣ የእስራት ቤት ማለት ነው፡፡ ቦታው ወንጀለኞች የሚቆዩበት የቅጣት ስፍራ ነው፡፡ ይኹንና ዐማፅያን አይሁድ፣ አላውያን ነገሥታት እና መናፍቃን ካህናት ለወህኒ የዳረጓቸው ቅዱሳን አበው አብዝተው በመገረፍና በመታሰር ስለ ክርስቶስ በተቀበሉት መከራ ወህኒ (ቤተ ሞቅሕ) ሐዋርያዊ ተልእኳቸውን የፈጸሙበት፣ ብዙዎችን ለድኅነት ያበቁበት ኾኗል፡፡
ቅዱስ ጳውሎስና ሲላስ ከግንድ ተጠርቀው በታሰሩበት ወኅኒ ቤት የወኅኒውን መሠረት ያናወጠውን፣ ምድርን ያንቀጠቀጠውን፣ ወህኒ አዛዡንና ቤተ ሰዎቹን ካለማመን ወደ ማመን የመለሰውን መዝሙራቸውንና ትምህርታቸውን፤ ቅዱስ ጳውሎስ በእስራቱ ዓመታት የከተባቸውን መልእክታት፤ ወንጌላዊው ቅዱስ ዮሐንስ በግዞቱ ሓላፊያትን፣ ማእከላውያንን፣ መፃዕያትን ያየበትን ራእዩን ያስታውሷል፡፡
ክርስትና የትንት ታሪክ ብቻ አይደለም፤ በጊዜውም አለጊዜውም ነቅተው ተግተው የሚኖሩት ዘላለማዊ ሕይወት ነው፤ ገድልም እንደ ዘመኑ ነው፡፡ በዚህ መንፈስ የፕሮቴስታንታዊ ተሐድሶ ኑፋቄ መውጊያዎች የኾኑት ሕገ ወጦቹ እነ በጋሻው ደሳለኝ በመሠረቱት የስም ማጥፋት ወንጀል ክስ በቃሊቲ ማረሚያ ቤት የሚገኘው መ/ር ዘመድኩን በቀለ ቀደምት አባቶች ስለ ቤተ ክርስቲያን በተቀበሉት መከራ ካገኙት በረከት የሚያሳትፈውን፣ ለወንድሞቹ የጽናት አብነት የሚኾንበትን ደማቅ ታሪክ እየጻፈ መሆኑ ተገልጧል፡፡
የፀረ ፕሮቴስታንታዊ ተሐድሶ ኑፋቄ እንቅስቃሴ አካል በሆነው አርማጌዶን ቪሲዲ በቀረበበት የስም ማጥፋት ወንጀል ክስ የፌዴራሉ የመጀመሪያ ደረጃ ፍ/ቤት አራዳ ምድብ ችሎት የካቲት 27 ቀን 2004 ዓ.ም ያለአግባብ የአምስት ወራት እስራት የፈረደበት መ/ር ዘመድኩን በቀለ÷ ወደ ቃሊቲ ማረሚያ ቤት ከገባበት ቀን አንሥቶ ለታራሚዎች በሚሰጠው አገልግሎት ከፍተኛ መነቃቃት እና ለውጥ ተፈጥሯል፡፡
መ/ር ዘመድኩን ወደ ቃሊቲ በተዛወረበት ዕለት ከማረሚያ ቤቱ ዞኖች መካከል አስቸጋሪ ወደሆነው እንዲወዱት በጠየቀው መሠረት እንዲገባ የተደረገው ከባድ ጠባይና ልምድ የሚታይባቸው ታራሚዎች ወደሚገኙበት ዞን ሁለት ነበር፡፡ የማረሚያ ቤቱ ምንጮች እንደተናገሩት÷ በዚህ ዞን የሚገኙ ብዙዎቹ ታራሚዎች ከባድ ወንጀል የፈጸሙ፣ ፖሊስ እንኳ ጠዋት ማታ እስረኞችን ለመቍጠር የሚቸገርበት÷ የሚደበደብበት፣ ሐሺሽ በጫማ ደብቀው እስከማስገባት የደረሱበት ነው ይባላል፡፡ መ/ር ዘመድኩን ወደ ዞን ሁለት ከገባ በኋላ በቋሚ መርሐ ግብር በሚሰጠው ትምህርትና በሚደረገው ምክክር የጠባይ ለውጥ እየመጣ መሆኑ ተነግሯል፡፡
ትምህርቱና ምክክሩ በፈጠረው መነቃቃት በታራሚው የቆመው ግንድ ተቆርጦ፣ የወደቀው ተፈልጦ የዞኑ ቤተ ጸሎት ተሠርቷል፡፡ በዚህች ቤተ ጸሎት ዘወትር ጠዋት ከቆጠራ መልስ ከዕለት ውዳሴ ማርያም ጀምሮ ጸሎታት ይደርሱባታል፡፡ ከጸሎቱ በኋላ ቃለ እግዚአብሔር ተሰምቶ ሁሉም ወደየሥራው ይሄዳል፡፡ ከቀትር በኋላ (ከ8፡00 - 9፡00) ጸሎት ተደርጎ የተጀመረው ተከታታይ ትምህርት ይቀጥላል፡፡ በየዕለቱ የሚፈጸመው መንፈሳዊ መርሐ ግብር በተለያዩ ወንጀሎች ተፈርዶባቸው በዞኑ የፍርድ ጊዜያቸውን በመፈጸም ላይ ለሚገኙ መነኰሳት እና ካህናት ብርታት ሰጥቶ ከፍተኛ ተሳትፎ እንዲያደርጉ አነሣስቷቸዋል፡፡
ዛሬ መጋቢት ሰባት ቀን 2004 ዓ.ም፣ በፌዴራሉ የመጀመሪያ ደረጃ ፍ/ቤት ቦሌ ምድብ ችሎት በሌላ መዝገብ ነገር ግን በተመሳሳይ ክስ ከቀረበው መ/ር ዘመድኩን፣ ከእርሱ ጋራ ከነበሩት ሌሎች ታራሚዎችና ከአቅራቢዎቹ የማረሚያ ቤቱ ፖሊሶች ለማረጋገጥ የተቻለው መ/ር ዘመድኩን በቃሊቲ የፈጸመውን ይህንኑ ሐዋርያዊ ተልእኮውን ነው፡፡
የቦሌ ምድብ ሁለተኛ ወንጀል ችሎት መዝገቡን ለዛሬ የቀጠረው መ/ር ዘመድኩን ለማራኪ መጽሔት በሰጠውና በቅጽ አንድ ቁጥር 6፣ ሐምሌ 2003 ዓ.ም ታትሞ በወጣው ቃለ ምልልሱ “በጋሻው ያልተማረ ነው፤ መሃይም ነው በሚል የግል ሰብእናውን ነክቷል፤ የእምነት ነጻነቱን ተጋፍቷል፤ ይህም በግል ተበዳይ ላይ ከፍተኛ ጉዳት አድርሷል” በሚል ዐቃቤ ሕግ በመሠረተው የስም ማጥፋት ወንጀል ክስ የግራ ቀኙን ክርክር ሲያዳምጥ የቆየው ፍ/ቤት የሚያሳልፈውን ውሳኔ ለመስማት ነው
ዐቃቤ ሕግ ያቀረባቸውን የክስ ማስረጃዎችና የተከሳሽን መከላከያዎች መመርመሩን በውሳኔው ያመለከተው ፍ/ቤቱ በመ/ር ዘመድኩን ላይ የጥፋተኝነት ብይን በማሳለፍ የቅጣት ውሳኔ ሰጥቷል፡፡ የችሎቱ የቅጣት ውሳኔ ሐተታ እንደሚያስረዳው÷ የመ/ር ዘመድኩን ሁለት የመከላከያ ምስክሮች ‹መሃይም› ስለሚለው ቃል ምንነት የሰጡት ማብራሪያ የተለያየ ነው፡፡
ይኸውም መ/ር ዘመድኩን ለማራኪ መጽሔት በሰጡትና ዐቃቤ ሕግ በማስረጃነት ባቀረበው የቃለ ምልልስ ካሴት እና መጽሔት ላይ መሃይም የሚለው ቃል የተነገረበት አገባብ በተከሳሽ አንደኛ ምስክር እንደተገለጸው ‹አማኝ› ማለትን የሚያመለክት ኾኖ አልተገኘም፡፡ የተከሳሽ ሁለተኛ ምስክር የኾኑት የማራኪ መጽሔት ዋና አዘጋጅ ደግሞ “ተከሳሽ መሃይም የሚለውን ቃል የተጠቀመው በጋሻው የዕውቀት፣ የግንዛቤ ችግር ያለበት መኾኑን ለማመልከት እንጂ ክብሩን ለመንካት፣ ስሙን ለማጥፋት አይደለም” ነበር ያሉት፡፡ በመኾኑም በቅጣት ሐተታው አገላለጽ “የሁለቱ ምስክሮች ቃል በፍ/ቤቱ ዘንድ ተቀባይነት አላገኘም፡፡”
መጽሔቱ በተለያየ የዕውቀት ደረጃ ለሚገኙ አንባብያን የሚቀርብና አገር ዓቀፍ ሽፋን ያለው መኾኑን ጨምሮ ያመለከተው የቅጣት ውሳኔው መሃይም በሚለው አነጋገር ተከሳሽ በግል ተበዳይ ላይ “ጉዳት ለማድረስ አስቦ የተናገረው መኾኑ እንደ ተረጋገጠ” ገልጧል፡፡ ስለዚህም “በወንጀል ሕጉ አንቀጽ 613(3) መሠረት ተከሳሽ ጥፋተኛ ነው ሲል ፍ/ቤቱ ውሳኔ ሰጥቷል” ተብሏል በቅጣት ውሳኔው፡፡
ዐቃቤ ሕግ ከሳሽ በጋሻው የቤተ ክርስቲያን ትምህርት እንደተማረና የማስተማር ፈቃድ እንዳለው ያቀረበው ማስረጃ ከክሱ ጭብጥ ጋራ የማይያያዝ በመሆኑ ውድቅ መደረጉ በቅጣት ውሳኔው ሐተታ ላይ ተመልክቷል፡፡
የአራዳው ምድብ ችሎት ዳኛ ሙሉ ክንፈ የመ/ር ዘመድኩን አርማጌዶን ቪሲዲ ሕገ ወጥ ነው ብለው ሳይወስኑ ቪሲዲው ወደ ጠቅላይ ቤተ ክህነቱ ከፍተኛ ሓላፊዎች ዘንድ ተወስዶ እንዲመረመር ካስተላለፉት እርስ በሱ ከሚጣረስ ውሳኔ በተፃራሪ የቦሌው ምድብ ችሎት ዳኛ ፉአድ ኪያር፣ “ፍ/ቤቱ መሃይም በሚለው ቃል አነጋገር እንጂ ሃይማኖታዊ ይዘት ባለው የክርክሩ ይዘትና ማስረጃዎች ውስጥ ገብቶ ይህ ትክክል ነው፤ ያኛው ስሕተት ነው ብሎ መመርመር ስለማይገባው” ከዚህ ጋራ የተያያዙ የዐቃቤ ሕግ ማስረጃዎችን እንዳልተቀበላቸው ነው የገለጡት፡፡
ዳኛ ፉአድ ኪያር የቅጣት ውሳኔውን በንባብ ካሰሙ በኋላ ዐቤ ሕግ ሙሉ ግደይ ባቀረቡት የቅጣት አስተያየት÷ መ/ር ዘመድኩን በሌላ ችሎት የአምስት ወራት እስራት የተፈረደበት መሆኑን፣ በዚህ ችሎት የተመሠረተው ክስ በሂደት ላይ እያለ ተከሳሹ በሌላኛው ችሎት ከተመሠረተበት ክስ የዋስትና መብቱ ተጠብቆ ከወጣ በኋላ የተፈጸመ፣ ይህም “ተከሳሹ ወንጀል መፈጸምን ልማድ አድርጎ መያዙን የሚያሳይ በመሆኑ” በወንጀል ሕጉና በቅጣት አወሳሰን ማኑዋሉ መሠረት ቅጣቱ ከብዶ እንዲወሰን ጠይቀዋል፡፡
‹መሃይም› የሚለው ቃል የግል ተበዳይ በአስተምህሮ ጥልቅ ዕውቀት የሌላቸው መሆኑን እንደሚገልጽ ለችሎቱ የተናገሩት ጠበቃ ጌትነት የሻነህ÷ በወንጀል ሕጉ ቁጥር 614 (2) መሠረት እውነትና ከፍ ያሉ ጥቅሞችን ስለ መጠበቅ በሚደነግገው አንቀጽ ሥር÷ “ተከሳሹ የተናገረው እውነት ኾኖ ወይም እውነት መኾኑን ለማወቅ በቂ ምክንያት ኖሮት ድርጊቱን በሚፈጽምበት ጊዜ፣ የሌላውን ሰው ስም ለማጥፋት ወይም ክብሩን ለመጉዳት ሐሳብ ያልነበረው መሆኑን ወይም ተገቢ ለሆነ ጠቅላላ የሕዝብ ጥቅም ወይም ከፍ ላለ ጥቅም ወይም ሞራላዊ ዓላማ መሆኑን ያስረዳ እንደ ሆነ በስም ማጥፋት ወንጀል አይቀጣም” በማለት እንደሚደነግግ ለችሎቱ ጠቅሰዋል፡፡ ከዚህ አኳያም መ/ር ዘመድኩን የሃይማኖቱን አስተምህሮ፣ ሕግና ሥርዐት ከማስጠበቅ ውጭ ሆነ ብሎ የግል ተበዳይን በግል ጉዳይ የመጉዳት ፍላጎት እንደሌለው ጠበቃው አስረድተዋል፡፡ ይሁንና ፍ/ቤቱ አነጋገሩ ወንጀል ነው ብሎ በማመኑ የቅጣት አስተያየታቸውን እንደሚያቀርቡ ገልጸዋል፡፡
ጠበቃው በቅጣት አስተያየታቸው ዐቃቤ ሕግ ተከሳሽ መ/ር ዘመድኩን “ወንጀልን መፈጸም አመሉ/ልማዱ አርጎታል” ሲሉ የገለጹትን በመቃወም በደንበኛቸው አመል/ልማድ ላይ በሌላ ፍ/ቤት የቀረበ ክስ አለመኖሩን አስታውቀዋል፡፡ “ወንጀል ሞያ/ልማድ ሆነ የሚባለው ድርጊቱ በተደጋጋሚ እየተፈጸመ እንደ መተዳደሪያ ሲያዝ፣ እውነታነቱ ተረጋግጦ በሬከርድ ሲቀመጥ ነው” ያሉት ጠበቃው ደንበኛቸው ይህ ዐይነቱ የወንጀለኛነት ጠባይዕ እና ሬከርድ እንደሌላቸው ገልጸዋል፡፡
ከዚህ አኳያ በአራዳ ምድብ ችሎት በመዝገብ ቁጥር 96/6/25 የተመሠረተው ክስ በዚሁ ችሎት ክስ በመሠረቱት የግል ተበዳይ የቀረበ፣ እንደ ክሱ አቀራረብም የአራዳው በኦዲዮ፣ የቦሌው በመጽሔት የተፈጸመ ነው በሚል የተመሠረተ ዓላማው ይዘቱ ተመሳሳይ ክስ በመሆኑ ÷ አንዱን ድርጊት በተለያዩ መዝገቦች/ቀናት ከፋፍሎ “ልማድ ሆኗል” በሚል እንደ ቅጣት ማክበጃ መቅረብ እንደማይገባው አብራርተዋል፡፡
ይልቁንስ መ/ር ዘመድኩን በኦዲዮ ቪዥዋልና ተዛማጅ መብቶች ጥበቃ ማኅበር በጸሐፊነት እንደሚሠሩ በመግለጽ የሕግ የበላይነትንና መከበርን የሚደግፉ፣ የቤተሰብ አስተዳዳሪና የልጆች አባት መሆናቸውን የገለጹት ጠበቃው ቅጣቱ ከብዶ ቢወሰን ከደንበኛቸው መልካም ጠባይዕ እና ሓላፊነት አንጻር ጉዳት ስለሚያደርስ ቅጣቱ በገደብ እንዲደረግላቸው ጠይቀዋል፡፡ መ/ር ዘመድኩንም በተለይ ሁለት ልጆች እንዳሉት፣ የትምህርት ውጤታቸውንም በቅርበት የሚከታተልላቸው እርሱ መሆኑን፣ ስለ ኮፒ ራይት መጠበቅ ከፍተኛ ትግል እያደረገ መሆኑን፣ ለተለያዩ አብያተ ክርስቲያን ያለ ክፍያ በነጻ አገልግሎት የሚሰጥ መሆኑን በመግለጽ የጠበቃውን አስተያየት የሚያጠናክር መግለጫ ሰጥቷል፡፡
የቀረቡት የቅጣት ማቅለያዎችና ማክበጃዎች በማስረጃ ተደግፈው ቀርበው ክርክር ሊካሄድባቸው እንደሚችል የተናገሩት ዳኛ ፉአድ ኪያር÷ መ/ር ዘመድኩን የቤተሰብ ሓላፊ ስለመሆኑ፣ በኮፒ ራይት ዙሪያ በሚሠራው ማኅበር በጸሐፊነት ስለማገልገሉ የሚያስረዱ ማስረጃዎችን ከቀጣዩ ቀነ ቀጠሮ በፊት እንዲያስገባ፣ መ/ር ዘመድኩን እኒህን ማስረጃዎች ለማሰባሰብ ይፈቀድለት ዘንድ ለማረሚያ ቤቱ እንዲጻፍ፣ በማረሚያ ቤት ቆይቶም መጋቢት 13 ቀን 2004 ዓ.ም እንዲቀርብ ትእዛዝ ሰጥተዋል፡፡
በተያያዘ ዜና በዚሁ ችሎት “የሰባኪው ሕጸጽ” በሚለው መጽሐፍ የተነሣ በዐቃቤ ሕግ የስም ማጥፋት ወንጀል ክስ የቀረበባቸው ዲያቆን ደስታ ጌታሁን በብር 3000 የገንዘብ ቅጣት እና በሁለት ዓመት ገደብ ከእስር ወጥተው ወደ ቤተሰባቸው ተቀላቅለዋል፡፡ የካቲት 30 ቀን 2004 ዓ.ም በዋለው ችሎት ፍ/ቤቱ የጥፋተኝነት ብይን ያስተላለፈባቸው ዲያቆን ደስታ ለቅጣት ያበቃቸው የ”ሰባኪው ሕጸጽ” በሚል ርእስ ያሳተሙት መጽሐፍ “በጋሻው 10+ምላስ ነው በሚል አገላለጽ ከሕዝብ ልቡና እንዲወጣ፣ ተጽዕኖው ከባድ ለሆነ ጉዳት እንዲዳረግ አድርጓል” በሚል ነው፡፡
በጋሻው ‹10+ምላስ› ላለመሆኑም ከቅድስት ሥላሴ መንፈሳዊ ኮሌጅ በእጅግ ደካማ ውጤት፣ በከፍተኛ የምግባር ጉድለት የቆየባቸው ሁለት ዓመታት እና እርሱ በሐዋሳ ካህናት ማሠልጠኛ ለሁለት ወራት ተከታትዬዋለኹ የሚለው ‹ሥልጠና› [የስፍራው ምንጮች ግን በጋሻው በማሠልጠኛው ተምረው ከወጡት ካህናት ዝርዝር ውስጥ እንደሌለበት ይገልጻሉ] ‹ማስረጃዎች› መቅረባቸውን ነው የፍ/ቤቱ የቅጣት ውሳኔ ሐተታ የሚያስረዳው፡፡
በመ/ር ዘመድኩን የክስ መዝገብ እንደተደረገው ሁሉ በዚህኛውም የቅጣት ውሳኔ ሐተታ ላይ ዐቃቤ ሕግ የ‹ሰባኪው ሕጸጽ› መጽሐፍ “በምቀኝነት በመነሣሣት የተደረገ የስም ማጥፋት ወንጀል ነው፤ ድርጊቱ የግል ተበዳይን የፈለገውን የማምለክ/የእምነት ነጻነት የሚጋፋ ነው” በሚል በቅጣት ማክበጃነት ያቀረባቸው ነጥቦች ማስረጃ ያልቀረበባቸውና የሕግ ይዘት የሌላቸው በመሆኑ ውድቅ ተደርገዋል፡፡
ክሱ ከተመሠረተበት ካለፈው ዓመት ነሐሴ ወር 2003 ዓ.ም ጀምሮ የቅጣት ውሳኔው እስከ ተሰጠበት የካቲት 5 ቀን 2004 ዓ.ም ድረስ ያለጠበቃ የተከራከሩት በጠቅላይ ቤተ ክህነት የገዳማት አስተዳደር መምሪያ ጸሐፊ የሆኑት መልአከ ፀሐይ ደስታ ጌታሁን ባለትዳርና የልጆች አባት መሆናቸውን፣ በአሁኑ ወቅት ባለቤታቸው ለመውለድ የተቃረቡ ነፍሰ ጡር መሆናቸውን፣ ከዚህ ቀደም ተከሰው የማያውቁና የወንጀል ሬከርድ እንደሌለባቸው ያቀረቧቸው የቅጣት ማቅለያ አስተያየቶች በፍ/ቤቱ ካሳዩት መልካም ጠባይ ጋራ ተደምሮ ዝቅተኛው የቅጣት እርከን (ብር 3000 የገንዘብ እና የሰባት ወራት እስራት በሁለት ዓመት ገደብ) ውሳኔ ተላልፎባቸዋል፡፡ ‹የሰባኪው ሕጸጽ› መጽሐፍ ድጋሚ እንዳይታተም እና ከዚህ ቀደም ታትመው በፖሊስ የተያዙ የመጽሐፉ ቅጂዎችም ‹እንዲወገዱ› ፍ/ቤቱ አዝዟል፡፡ የሁለት ዓመቱ የገደብ ጊዜ እስኪፈጸም ድረስም መልአከ ፀሐይ ደስታ ቀደም ብሎ ለዋስትና ያስያዙት ብር 5000 እንደተያዘ ይቆያል፡፡
ለስድስት ቀናት በእስር በቆዩበት የቦሌ ክፍለ ከተማ ፖስ ጣቢያ ከጸጥታ አስከባሪዎች እና እስረኞች ከፍተኛ ድጋፍ እና መልካም አቀባበል እንደተደረገላቸው የገለጹት የገዳማት አስተዳደር መምሪያ ጸሐፊው መልአከ ፀሐይ ደስታ በውሳኔው ላይ ይግባኝ እንደሚጠይቁ ተናግረዋል፡፡
በአጠቃላይ በአራዳውም ይኹን በቦሌው የፌዴራሉ የመጀመሪያ ደረጃ ፍ/ቤቶች በዐቃቤ ሕግ የተመሠረቱት ክሶች በተከሳሾች እና የግል ተበዳይ ነው በተባለው ሕገ ወጡ በጋሻው ደሳለኝ መካከል ትምህርተ ሃይማኖትን፣ ቀኖና ቤተ ክርስቲያንንና ሕገ ቤተ ክርስቲያንን በማስከበርና ባለማስከበር መካከል በመሆኑ ፍ/ቤቶቹ ጣልቃ ገብተው የማየት ሥልጣን እንደሌላቸው የክስ መቃወሚያ የቀረበው ከጅምሩ ነበር፡፡ በተለይም በቦሌው ችሎት የተመሠረተው ክስ በሃይማኖቱ ርቱዕነት ላይ ጥያቄ የቀረበበት በጋሻው ደሳለኝ ጉዳዩ በቅዱስ ሲኖዶስ ትእዛዝ በሊቃውንት ጉባኤ እየታየ ባለበት ኹኔታ የሚካሄድ በመሆኑ እንዲቋረጥ የጠቅላይ ቤተ ክህነቱ ዋና ሥራ አስኪያጅ ባቀረቡት ጥያቄ መሠረት ፍትሕ ሚኒስቴር መዝገቡ እንዲመለስ ትእዛዝ የሰጠበትና ቆይቶም ሕገ ወጦቹ የብፁዕ ዋና ሥራ አስኪያጁን ቀራቢዎች በገንዘብ ደልለው በፈጠሩት ማጭበርበር እንዲቀጥል የተደረገ ነው፡፡
ይህም ኾኖ ተፈጸመ የተባለው የስም ማጥፋት ወንጀል በብዙኀን መገናኛ (በምስል ወድምፅ፣ በመጽሔት) የተደረገ በመሆኑ በዐቃቤ ሕግ ሳይሆን በራሱ በግል ተበዳዩ መቋቋም እንደነበረበት በመገናኛ ብዙኀንና የመረጃ ነጻነት ዐዋጅ ቁጥር 590/2000 አንቀጽ 43/7 የተደነገገውን መሠረት በማድረግ ትችት የቀረበበት ነው፡፡ በሌላ አነጋገር የክስ መዝገቡ በዐቃቤ ሕግ መቅረቡ ፍጹም ከሕግ ውጭ በመሆኑ በወንጀለኛ መቅጫ ሕግ ሥነ ሥርዐት ሕግ ቁጥር 131 መሠረት መዘጋት ነበረበት፡፡
በሌላ መልኩ በብዙኀን መገናኛ በተፈጸሙ ወንጀሎች ተሳታፊ ስለመሆንና ስለ ሓላፊነት በሚመለከተው በ1996 ዓ.ም የወንጀል ሕግ አንቀጽ 43/1/ሀ እና በመገናኛ ብዙኀንና የመረጃ ነጻነት ዐዋጅ 590/2000 አንቀጽ 41/1 መሠረት የመረጃው ምንጭ ሳይሆን የፕሬሱ አዘጋጅ ሓላፊ እንደሚሆን ተደንግጓል፡፡ በዚህ መሠረት ለምሳሌ በቦሌው ችሎት በተመሠረተው ክስ የመ/ር ዘመድኩን አነጋገር ወንጀልን የማያቋቁም ስለመሆኑ የማረጋገጥ የሞያና የሕግ ግዴታ ያለበት፣ በጉዳዩ ላይ ሊከሰስና ሊጠየቅ ይገባ የነበረው የመጽሔቱ ዋና አዘጋጅ እንጂ መ/ር ዘመድኩን መሆን እንዳልነበረበት የሕግ አስተያየት ተሰጥቷል፡፡
በዳኝነት ተግባር ዳኞች በግልጽ ከታወቀው ሕግና ሥርዐቱ ባሻገር ለጉዳዩ ያላቸው ማመዛዘንና የሚመስላቸው አስተያየት (discretion) ሰፊ እንደሆነ ይታወቃል፡፡ ይኹንና የቦሌው ችሎት በሃይማኖት አስተምህሮ ግጭት ጣልቃ በመግባት ለመወሰን እንደማይቻል ሲያስቀምጥ በአራዳው ችሎት ደግሞ “አርማጌዶን ቪሲዲ የግል ተበዳዩን ሕገ መንግሥታዊ የማመልክ/የእምነት ነጻነት የሚጋፋ ነው” በሚል የመፈረጁ÷ በጠቅላይ ቤተ ክህነቱ እንዲመረመርም ውሳኔ የመተላለፉ ሰፊ ልዩነት ከፍትሕ አሰጣጥ ተጨባጭነት አኳያ የሚያወያይ ነው፡፡ የአንድን ሃይማኖት መሠረተ እምነት ባላከብርክበት ሁኔታ በዚያው ሃይማኖታዊ ሥርዐትና ተቋማዊ አሠራር ውስጥ የሚጠበቀው የማምለክ ነጻነትስ እንደምን ያለ ነው?
በተያያዘ ዜና መልአከ ፀሐይ ደስታ ጌታሁን የጠቅላይ ቤተ ክህነቱ ሠራተኛ መሆናቸውን እንዲያስረዳላቸው ከፍ/ቤቱ የታዘዙትን ማስረጃ (ደብዳቤ) በጠቅላይ ቤተ ክህነቱ ፐርሶኔል ክፍል ተጽፎ ከተፈረመበት በኋላ ለደብዳቤው ቁጥርና ቀን ተሰጥቶ እንዳይወጣ የዋናው መዝገብ ቤት ሹም ወ/ሮ ዐጸደ ግርማይ “ራሱ መጥቶ ካልወሰደ” በሚል ለማዘግየት ሞክረው እንደነበር ተዘግቧል፡፡
ባለፈው ታኅሣሥ ወር በመምሪያ ሓላፊ ደረጃ የዋናው መዝገብ ሹም ሆነው የተቀመጡት ወ/ሮ ዐጸደ ከፕሮቴስታንት ክፍልፋዮች አንዱ በሆነውና ራሱን ‹ሙሉ ወንጌል› እያለ በሚጠራው ቤተ እምነት እንደሚያዘወትሩ፣ በፓትርያኩና በልዩ ጽ/ቤታቸው ስም የሚወጡትን ጽሑፎች እንደሚያዘጋጅ በሚነገርለት የተሐድሶ ኑፋቄ አራማጁ አሸናፊ መኰንን እጅ በፕሮቴስታንታዊ ዘይቤ ‹እጅ እየተጫነ እንደሚጸለይላቸው› በሰፊው ይነገርባቸዋል፡፡ ቀደም ሲል በፓትርያኩ ልዩ ጽ/ቤት በጸሐፊነት በነበሩበት ወቅት ሓላፊነታቸውን በመጠቀም ቀናዒ ኦርቶዶክሳውያንን ሲፈታተኑ የቆዩት የወ/ሮ ዐጸደ በዚህ ቁልፍ የሰነዶች ቦታ መቀመጥ የፓትርያኩ ቀጥተኛ ይኹንታ እንዳለበት ምንጮቹ ተናግረዋል፡፡


ቸር ወሬ ያሰማን፣
አሜን

8 comments:

Anonymous said...

Amazing

Aba paulos do not care about the church, does it touch him , what these people are doing on the church.He should have been like zemedhun and be in prision

Look Orthodox people

He the so called "patriarch" is doing because he is so happy and the one who pushes the judges , he did not say anything , just calm as is he do not see or hear. we know this trick "doctor"!!!!!!!!!!!!!!


The patriarch paulos, can be protestant , it is up to him but not in orthodox church, leave the building of the church and then you can go any where to accomplish your task. please go down , God make you some miracle on you to drop down.If you like confess and return , if not leave with your supporters and join any team

Anonymous said...

God pless you Zemedikun you are our hero

Anonymous said...

በተለያዩ ወንጀሎች ተፈርዶባቸው በዞኑ የፍርድ ጊዜያቸውን በመፈጸም ላይ ለሚገኙ መነኰሳት እና ካህናት

WHAT A SHAME?

Anonymous said...

"መ/ር ዘመድኩን ለማራኪ መጽሔት በሰጠውና በቅጽ አንድ ቁጥር 6፣ ሐምሌ 2003 ዓ.ም ታትሞ በወጣው ቃለ ምልልሱ “በጋሻው ያልተማረ ነው፤ መሃይም ነው በሚል የግል ሰብእናውን ነክቷል፤ የእምነት ነጻነቱን ተጋፍቷል፤ ይህም በግል ተበዳይ ላይ ከፍተኛ ጉዳት አድርሷል”

DS why can't you be impartial? If you really stand for the church and the truth be honest. Both of them are your brothers. Don't be like GOD and judge one of them as saint the other as enemy. Our lord told us "But I say to you that everyone who is angry with his brother will be liable to judgment; whoever insults his brother will be liable to the council; and whoever says, ‘You fool!’ will be liable to the hell of fire". Matthew 5:22

PLEASE PLEASE PLEASE have fear of GOD. I know most of you are trying to protect the church but unfortunately you are putting yourself out of the holy church by doing unholy things. Be careful what you say and write.

I don't care if you post it or not. At least one you will read this and the message is for you anyway.

Anonymous said...

we will descues at DC on the demonstration

Anonymous said...

zemede be strong it is part of your life you are a winner.winner never quit.you play a signficant role so that it will be history of our church.
from seattel

EthiopiaTesfaye said...

አውንስ መስማት የሰለቸኝ ነገር ቢኖር በደልን ነው። ተነስትን በይፋ ቤተክርስቲያናችንን መታደግ ብቻ ነው መፍትዬው ፤ ወሬ ግን ሰለቸን ተነሱ አንነሳ።

EthiopiaTesfaye said...

አውንስ መስማት የሰለቸኝ ነገር ቢኖር በደልን ነው። ተነስትን በይፋ ቤተክርስቲያናችንን መታደግ ብቻ ነው መፍትዬው ፤ ወሬ ግን ሰለቸን ተነሱ አንነሳ።

Blog Archive

የአቡነ ጳውሎስ "ሐውልተ ስምዕ"

ነጻ ፓትርያርክ ምርጫ ቢሆን ኖሮ ማንን ይመርጡ ነበር? እንበልና ሁሉም ነገር ሥርዓቱን ጠብቆ የተከናወነ የእጩዎች ምርጫ ቢሆን ኖሮ፣ አሁን የምናነሣቸው ጉድለቶች ባይኖሩ ኖሮ፣ 6ኛው ፓትርያርክ እንዲሆን የምትመርጡት ማንን ነበር? (ማሳሰቢያ፦ አሁን ያለው ክፍፍል እና የመንግሥት ተጽዕኖ ባይኖር ኖሮ ተብሎ የሚመለስ ጥያቄ ነው። የምን “ባይኖር ኖሮ ነው” የሚል አስተያየት ካለዎትም እናከብራለን።)