March 15, 2012

“ምሁራን ለቤተ ክርስቲያን ቤተ ክርስቲያን ለምሁራን” (የውይይት መርሐ ግብር በማኅበረ ቅዱሳን)

·  በቤተ ክርስቲያን ለጥናት እና ምርምር ተግባር አመቺ ምኅዳር የመፍጠር ሥራ መጠናከር እንዳለበት ተጠቁሟል
·   የጥናትና ምርምር ቋንቋና አድማስ፣ የቤተ ክርስቲያን ሥርዐተ ትምህርት መሻሻል፣ የቅርስ ምንነትና በጥናትና ምርምር ስም የሚወጡ ቅርሶች ደኅንነት አወያይቷል
·    በቤተ ክርስቲያን ውስጥ የሚካሄዱ ጥናቶች ከሁለተኛ ደረጃ መረጃዎች ይልቅ ቅርሶቹና ነዋያተ ቅድሳቱ በቀጥታ የሚታዩባቸው፣ ሊቃውንቱ በባለቤትነት የሚሳተፉባቸው መስክ ተኮር ምርምሮች ሊሆኑ እንደሚገባ ተመክሯል
·   “የማኅበረ ቅዱሳን ጥናት እና ምርምር ማእከል ከፍ ያሉ እሴቶችን መሠረት ያደረጉ የለውጥ ሐሳቦች እና ለዘመኑ ተግዳሮቶች ምላሽ የሚሰጡ የፖሊሲ አማራጮች ምንጭ መሆን ይጠበቅበታል” ተብሏል
·     ዶ/ር አንኬ ዋንገር “ዳግሚት ጎርጎርዮስ” በሚል ተሞካሽተዋል

(ደጀ ሰላ መጋቢት 6/2004 ዓ.ም፤ ማርች 15/2012)፦ በተለያየ የሞያ መስኮች የተሰማሩ ምሁራን በጥናትና ምርምር ሥራ የቤተ ክርስቲያንን አገልግሎት እንዲያግዙ ማኅበረ ቅዱሳን ጥሪ አደረገ፡፡ ጥሪው የተደረገው የማኅበሩ ጥናትና ምርምር ማእከል “ምሁራን ለቤተ ክርስቲያን ቤተ ክርስቲያን ለምሁራን” በሚል ርእስ የካቲት 23 ቀን 2004 ዓ.ም በአዲስ አበባ ኢንተርኮንቲነታል ሆቴል ባካሄደው የግማሽ ቀን ውይይት ላይ ነው፡፡
ውይይቱን በንግግር የከፈቱት የማኅበረ ቅዱሳን ሰብሳቢ ቀሲስ ዶ/ር ሙሉጌታ ሥዩም÷ የጥናትና ምርምር ሥራ የቤተ ክርስቲያንን ወቅታዊ ፈተናዎች ለመቋቋም፣ መንፈሳዊ እሴቶቻችንን በአግባቡ ለመጠበቅ፣ የወደፊቱ የቤተ ክርስቲያን አገልግሎት ዘመኑን የዋጀ፣ በስልትና ጥናት ላይ የተመሠረተ ለማድረግ የሚያዘጋጀን በመሆኑ ታላቅ ጠቀሜታ ያለው መሆኑን ገልጸዋል፡፡ ከዚህ አኳያ ጥናትና ምርምር ለቤተ ክርስቲያን አገልግሎት የሚሰጠውን ይህንኑ ፋይዳ የሚገነዘቡ ምሁራን ሁሉ የድርሻቸውን ይወጡ ዘንድ በወሳኝ ወቅት ላይ እንደሚገኙ ቀሲስ ዶ/ር ሙሉጌታ አሳስበዋል፡፡
ለአገራችን ልዩ የጥበብ ድባብ በመኾን ዓለምን የሚያስደንቁት የሥነ ጽሑፍ፣ የሥነ ዜማ፣ የሥነ ጥበብ፣ የኪነ ሕንጻ፣ የሕግና አስተዳደር፣ የዘመን አቆጣጠር፣ የሥርዐተ ቤተ ክርስቲያንና ማኅበራዊ ሕይወት እሴቶቻችን ቀደምት የቤተ ክርስቲያን ሊቃውንትና መምህራን የተጠበቡባቸው የምርምር ውጤቶች በመሆናቸው ለኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ሊቃውንት የጥናትና ምርምር ሥራ እንግዳ ነገር አለመሆኑን እንደሚመሰክሩ የማኅበሩ ሰብሳቢ ተናግረዋል፡፡ የአገራዊ ማንነት እና ሥልጣኔ ምንጭ፣ የበርካታ ድንቅ ቅርሶች ቤተ መዘክር የኾነችው ጥንታዊቷ የኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያን በምርምር ሥራ ያልተዳሰሰና በየሞያ መስኩ የአጥኚዎችን ቀልብ ሊስብ የሚችል እምቅ ሀብት ያላት በመኾኑ “ለራሳችን ታሪክ፣ ለራሳችን ጥበብ፣ ለራሳችን ማንነትና መገለጫ ቦታ ልንሰጠው ይገባል፤” ብለዋል ሰብሳቢው፡፡
ማኅበረ ቅዱሳን ከቤተ ክርስቲያን ጋራ በተያያዙ ማኅበራዊ፣ ምጣኔ ሀብታዊ፣ ባህላዊና በመሳሰሉት ጉዳዮች ላይ ጥናትና ምርምር የማድረግ፣ ቤተ ክርስቲያናችንም በውጤቱ ተጠቃሚ እንድትኾን የማስቻል ዓላማ እንዳለው የተናገሩት ቀሲስ ዶ/ር ሙሉጌታ÷ “የምሁራን ጥናትና ምርምር ሥራ የማንነትና የታሪክ ባለቤት የኾነችው የኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያን ለአገር ያበረከተችውን አስተዋፅኦ ለትውልዱ ለማስተዋወቅ፣ የነገዪቱ ኢትዮጵያም ይህንኑ አስተዋፅኦ ጠብቃና አዳብራ ለትውልድ የማስተላለፍ ሓላፊነቷን እንድትወጣ የሚያደርግ ታላቅ ተግባር” እንደኾነ ለተወያዮቹ አስገንዝበዋል፡፡
በዚህ መንፈስ በዕለቱ “በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ለምርምር እና ምሁራዊ አስተዋፅኦ ያሉ ምቹ ኹኔታዎች/ዕድሎች - Opportunities for Research and Scholarly Work in the Ethiopian Orthodox Tewahedo Church” በሚል ርእስ የሚካሄደው ውይይት÷ በተለያየ ሞያ የተሰማሩ የዘመኑ ምሁራን በጥናትና ምርምር ሥራ የቤተ ክርስቲያንን አገልግሎት እንዲያግዙ ሁኔታዎችን ለማመቻቸት፤ በዘርፉ አገልግሎት በመስጠት ላይ ያሉትን ሊቃውንት ለማበረታታት፤ ለእርስ በርስ ልምድ ልውውጥ እና በቤተ ክርስቲያን ዙሪያ ለሚደረጉ ጥናቶች ያሉትን ምቹ ሁኔታዎች ለማመላከት ታስቦ መዘጋጀቱን አመልክተዋል፤ ለስምረቱም የምሁራኑን ውጤታማ ምክክር እና ትብብር ጠይቀዋል፡፡
በነገረ መለኰት ከፍተኛ ትምህርታቸውን በመከታተል ላይ በሚገኙት ጀርመናዊቷ የሕክምና ባለሞያ ዶ/ር አንኬ ዋንገር (ወለተ ማርያም) የቀረበው ሐሳብ÷ በኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያን ያሉትን አማራጭ የጥናትና ምርምር ርእሰ ጉዳዮች በደምሳሳው የቃኘና ጥናት አቅራቢዋ የጥናቱንና ምርምሩን ተግባር አስቸጋሪ አድርገውታል ያሏቸውን ውስንነቶች ያመላከተ ነበር፡፡
መንፈሳዊ ሀብታት በተፈጥሯዊ ገጽታቸው የሞሉባቸው ታሪካዊ የቱሪስት መዳረሻዎች (አኵስም፣ ላሊበላ፣ ጎንደር…) ገና በቅጡ ያልታወቁ የምርምር እና ምሁራዊ ሥራዎች መገኛዎች መሆናቸውን የገለጹት ዶ/ር አንኬ በማሳያነት በጠቀሱት በሥነ ዜማ ዘርፍ ያሬዳዊ ዜማን የምናጠናበት የምልክት ሥርዐት በሌላው ዓለም በስፋትና በቀላሉ አለመታወቁ፣ ከያሬዳዊ ዜማ ውጭ ሌሎችም የዜማ ሀብቶች መኖር አለመኖራቸው፤ በላሊበላና ይምርሐነ ክርስቶስ የሚታዩት የሥነ ሥዕል፣ የኪነ ሕንጻ ጥበባት ንድፍ፣ አሠራርና ትእምርታዊነት፤ የጥንታዊው ትምህርት ባሕርይ፤ የሕግ እና አስተዳደር ሥርዐቱ ለኅብረተሰቡ የሰጠው አገልግሎት የመሳሰሉት ነጥቦች በማኅበራዊና የተፈጥሮ ሳይንሶች መስኮች እንደ አገባቡ የጥናትና ምርምር ጉዳይ የመሆን አቅም እንዳላቸው ዘርዝረዋል፡፡
ጥናቶችና ምርምሮች በስልታቸው፣ በይዘታቸው ከአኀት አብያተ ክርስቲያን ጋራ ያሉንና የሌሉንን ጉዳዮች በንጽጽር የሚዳስሱ÷ ኅብረተሰቡና ቤተ ክርስቲያን በሁለትዮሽ አንዱ በሌላው ላይ ስላለው ተጽዕኖ የሚቃኙ÷ ዘመናዊውን የጥናትና ምርምር ሥነ ዘዴ በማረቅ ለቤተ ክርስቲያን ጥናት አስተዋፅኦ የሚያደርግበትን ሁኔታ ማመቻቸቱ በሁሉም ጥናታዊ ክንውኖች ውስጥ ተሸጋጋሪ እና ተተኳሪ ነጥቦች ሊሆኑ እንደሚገባ ዶ/ር አንኬ መክረዋል፡፡ በቤተ ክርስቲያን ጥናትና ምርምር የማካሄድን ስለምንነት ሲያብራሩም የኢትዮጵያን ቤተ ክርስቲያን ለማወቅ በእጅጉ ለሚናፍቀው ዓለም አቀፍ ኅብረተሰብ ጉጉት ምላሽ ይሰጣል፤ ቀደም ሲል በተጠቀሱት መስኮች ተዘጋጅተው ለኅትመት የበቁ ተጠቃሽ የጥናትና ምርምር ሥራዎች አለመኖራቸው፤ የቤተ ክርስቲያን ጥናትና ምርምር የሚያስገኘው ዕውቀት በዓለምአቀፍና በአካባቢ ማኅበረሰብ ላይ በጎ ተጽዕኖ ስለሚያሳርፍ፤ ከታወቁ ዩኒቨርስቲዎች ጋራ የወል ጥናትና ምርምር መርሐ ግብሮችን የመዘርጋት ዕድል ስለሚፈጥር በማለት አብራርተዋል፡፡
አባ ጎርጎርዮስ 
የቤተ ክርስቲያን ሀብታት ለዓለም አቀፍ ምሁራን ያላቸውን ተደራሽነት በተመለከተ በተለይም ብዙዎቹ የጽሑፍ ምንጮች በመገኛቸው የግእዝ ቋንቋ ያሉ መሆናቸው የቋንቋ እግዳት ቢፈጥርም “ግእዝ ተምሮ የትርጉም ሥራዎችን መሥራት ያን ያህል አዳጋች ተግባር አይደለም፤” ብለዋል፡፡ እንደ ዶ/ር አንኬ ምልከታ በውጭ እና በሀገር ውስጥ ምሁራን በርካታ ጥናቶችና ምርምሮች ቢሠሩም ከዩኒቨርስቲዎች /መካነ ጥናቶች/ ወጥተው፣ ለኅትመት በቅተው ለተጠቃሚው ወገን የደረሱቱ በቂ ናቸው ሊባሉ አይችሉም፡፡
የዶ/ር አንኬን የመነሻ ሐሳብ ተከትሎ በርካታ አስተያየቶችና ጥያቄዎች ተሰጥተዋል፡፡ ጥናትና ምርምር የቤተ ክርስቲያንን ሀብት ለማበልጸግ፣ መንግሥትና የቤተ ክህነት አካላት ለሚሰጡት ውሳኔ አጋዥ እንደሚኾን የገለጹ አንድ ተሳታፊ፣ “ይሁንና ያለንን የማይገለጽ ሀብት ለማስተላለፍ የሚደረገው ጥረት አነስተኛ ነው፤ መድረኩ ሰፊና በየሞያ መስኩ አያሌ ኀልዮት (ቴዎሪ) ሊመነጭበት የሚችል በመሆኑ በቦታው ተገኝቶ በውስጡ ገብቶ ማጥናት” እንደሚያስፈልግ መክረዋል፡፡
ለዚህም ግእዝንና ዜማን ጨምሮ በቅድስት ሥላሴ መንፈሳዊ ኮሌጅ ለከፍተኛ ዲፕሎማ የሚያበቃቸውን ትምህርት ያጠኑት፣ በአሁኑ ወቅትም በኦሪየንታል ኦርቶዶክስ ነገረ መለኰት የድኅረ ምረቃ ትምህርታቸውን እየተከታተሉ የሚገኙት የዶ/ር አንኬ አርኣያነት ከአገር ውጭ ያሬዳዊ ዜማን አጥንተው ሲያበቁ በአውሮፓ ኖታ ለመተካት ከሞከሩ ጥቂት ምሁራን ይልቅ የሚጠቀስ መኾኑን አስረድተዋል - “ዳግማዊ/ት ጎርጎርዮስ” ሲሉም አሞካሽተዋቸዋል፡፡ አባ ጎርጎርዮስ በ17ው መ/ክ/ዘ ከኢትዮጵያ ቤተ አምሐራ ወደ አውሮፓ በመሄድ ከኢትዮጵያ ጥናት ሊቁ (German Ethiopianist/Orientalist) ሂዮብ ሉዶልፍ (እ.አ.አ 1624 - 1704) ጋራ በመገናኘት የአማርኛንና የግእዝን ቋንቋ ያስጠና መነኮስ ነው፡፡ በዚህ ጥናት የታገዘው ኢዮብ ሉዶልፍ በአውሮፓ ለኢትዮጵያ ጥናት መጀመር መሠረት የኾኑ የአማርኛ - ላቲን፣ የግእዝ - ላቲን ሰዋስዎችን፣ የኢትዮጵያ ታሪክ መጻሕፍትንና ሌሎችንም ሁነኛ ሥራዎች አበርክቷል፡፡
የአገር ውስጥ የቤተ ክርስቲያን ጥናትና ምርምር አቅም ገና በሚገባ አለመደራጀቱን ያመለከቱ የአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ መምህር ጥናቶቻችን በሁለተኛ ደረጃ የመረጃ ምንጮች ላይ ከመጠመድ ይልቅ ቅርሶቹ እና ነዋያተ ቅድሳቱ ባሉበት ስፍራ በሚመረመሩበት፣ ሊቃውንቱ በባለቤትነት በሚሳተፉበት የመስክ ስምሪት ላይ ማተኰር ይኖርባቸዋል ብለዋል፡፡ ይህ በመጀመሪያ ደረጃ መረጃዎች ላይ የተመሠረተ መስክ ተኰር የጥናትና ምርምር አካሄድ የሁሉም ዐይነት ቅርሶች (የሚዳሰሱና የማይዳሰሱ፣ የሚንቀሳቀሱና የማይንቀሳቀሱ ቅርሶች) ባለቤት የሆነችው ቤተ ክርስቲያን ሀብቶች በምን ያህል አስደንጋጭና አሳሳቢ ሁኔታ ላይ እንደሚገኙ በተጨባጭ ለመረዳት፤ የጥናቱና ምርምሩም አቅጣጫ መፍትሔ ሰጪ፣ ችግር ፈቺ ለማድረግ እንደሚጠቅም አስረድተዋል፡፡ በጥናትና ምርምር ስም በውጭ አገር ዜጎችና በአንዳንድ ኢትዮጵያውያን ተባባሪዎቻቸው ለሕገ ወጥ ጥቅምና ዝውውር እየተጋለጡ ያሉት ቅርሶችና የባለቤትነት መብት ጉዳይም ጥያቄ ሊነሣበት እንደሚገባ ጠቁመዋል፡፡
በጥንቱ ሥርዐት የቤተ ክርስቲያንን ነባር ትምህርት ከተማሩ በኋላ ዘመናዊውን ትምህርት ዘልቆ ወደ ጥናትና ምርምር ለመግባት በርካታ ዓመታትን (ከኀምሳ ዓመት ያላነሰ) እንደሚወስድና ይህም ጥናትና ምርምር በሚጠይቀው ተነሣሽነትና አእምሯዊ ብቃት ላይ የራሱ ተጽዕኖ እንደሚያሳርፍ በአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ መምህር የሆኑት ዶ/ር ሥርግው ገላው ተናግረዋል፡፡ መምህሩ ብዙዎቹ የዘመኑ ምሁራን የቤተ ክርስቲያን ትምህርት የተማሩ ያለመሆናቸውን፣ የቤተ ክርስቲያን ትምህርት የተማሩትም በጥናትና ምርምር ላይ ያለማተኰራቸውን መተላለፍ እንደ ዐቢይ ችግር ጠቅሰዋል፤ መፍትሔውም በአለቃ ኪዳነ ወልድ አነጋገር “ጥፈትና ትምህርት እየቅል” የሆኑበትን የቤተ ክርስቲያን ሥርዐተ ትምህርት መከለስ መሆኑን አመልክተዋል፡፡
“ጥናትና ምርምር አካዳሚያዊ ነጻነትንና ምሁራዊ አቅምን ይጠይቃል” ያሉት ዶ/ር ሥርግው በቤተ ክርስቲያናችን አካዳሚያዊ አስተያየትን ሃይማኖታዊ ነቅ አድርጎ የመወሰድ ዝንባሌ በመኖሩ ልዩ ሐሳብ ያላቸውን ፊት መንሳቱና ማሸማቀቁ ቆሞ ለጥናትና ምርምር ተግባር አመቺ የኾነ ምኅዳር የመፍጠር ሥራ መጠናከር እንዳለበት መክረዋል፤ ምዕራባውያኑ በቤተ ክርስቲያን ጥናትና ምርምር ላይ ያላቸው ፍላጎት እየቀዘቀዘ በመጣበት ሁኔታ ችግሩ ዘላቂ ምላሽ የሚያገኘው በሥርዐተ ትምህርት ማሻሻያው ውስጥ እንደኾነም አጽንዖት ሰጥውበታል፡፡
በቅርስ ጥናትና ጥበቃ ባለሥልጣን ከፍተኛ ተመራማሪ የኾኑት አቶ መንክር ቢተው በበኩላቸው “ቤተ ክርስቲያኒቱ ለጥናትና ምርምር የተዘጋጀች ናት ወይ? ማጥናትስ ይቻላል ወይ?” ሲሉ ጠይቀዋል፡፡ ጥያቄውን ለማንሣት ያስገደዳቸው ቱሪስቶችን ይዘው በየቤተ መዘክሩ ሲሄዱ “ቅርስ ነው፤ አይወጣም” በሚል የተጠየቀውን ለማግኘት ‹የሚገጥማቸው ውጣ ውረድ› ነው፡፡ ጥናትና ምርምር ችግር ፈቺ፣ መፍትሔ አምጪ በመሆኑ እንደሚያምኑበት የገለጹት አቶ መንክር፣ ከሁሉ አስቀድሞ በቤተ ክርስቲያን ጥናትና ምርምር የሚያስፈልጋቸው ጉዳዮች ተቆጥረውና ተሰፍረው መለየት (Inventory and Standardization) እንደሚያስፈልግ፤ ከዚህም ጋራ አጥቢያ አብያተ ክርስቲያን በጋራ ወይም በተናጠል ባለድርሻ በሚሆኑበትና የተጠናከረ ጥበቃ በሚያደርጉበት አኳኋን ቤተ መዘክር ማቋቋም ይኖርባቸዋል ብለው እንደሚያምኑ አመልክተዋል፡፡ ከፍተኛ ተመራማሪው “በመቆም ላይ ናቸው፤ በቀጣይነታቸው ላይ ጥናት ያስፈልጋቸዋል” ካሏቸው የቤተ ክርስቲያን ጥንታዊ ሥራዎች ውስጥ የሥነ ሥዕል፣ የቁም ጽሕፈት፣ የብራና እና ብርዕ ዝግጅት ሞያዎች ይገኙባቸዋል፡፡
በ17ው መቶ ክፍለ ዘመን በአውሮፓ በኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያን ሥነ ድርሳንና ቋንቋ፣ ሥነ ጥበብ፣ ታሪክና ነገረ መለኰት ላይ በማተኰር ለተጀመረው የኢትዮጵያ ጥናት ምክንያት የሆኑትን ኢትዮጵያዊውን መነኮስ አባ ጎርጎርዮስን በመጥቀስ ለጥናትና ምርምር ብዙም ትኩረት እንዳልተሰጠ ተደርጎ መነገሩን የነቀፉት በአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ የፊሎሎጂ መምህርና የማኅበረ ቅዱሳን ሚዲያና ሕዝብ ግንኙነት ዋና ክፍል ሓላፊ ዲያቆን ዶ/ር መርሻ አለኽኝ ናቸው፡፡ በዲያቆን ዶ/ር መርሻ አባባል ራሳችንን ለጥናትና ምርምር ድንግል አድርገን የምናቀርብበት ሁኔታ በኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያን ዙሪያ በውጭ ይኹን በአገር ውስጥ ምሁራን የተሠሩ የጥናት መዘርዝሮችን (Indices) ብዛት በጥሞና ያልተመለከተ መከራከሪያ ነው፡፡
ዲያቆን ዶ/ር መርሻ 
በእርሳቸው እምነት ዋነኛው ትኩረት ጥናቶቹን የማቃናት፣ የማስተካከል ጉዳይ ነው፡፡ ለዚህም ምዕራባዊውን የጥናትና ምርምር ሥነ ዘዴ በሚያርቅ፣ ለሊቃውንተ ቤተ ክርስቲያን ቀጥተኛ መድረክ በሚሰጥ አኳኋን ለማካሄድ ጥረት ሊደረግ ይገባል ብለዋል፡፡ ከግእዝ ወደ ውጭ ቋንቋዎች የመመለስ ሥራ ከፍተኛ የጥናትና ምርምር ሥራ እንዳልሆነ በዶ/ር አንኬ የተነገረው አባባል “ለመቀበል አዳጋች ነው” ያሉት ዲያቆን ዶ/ር መርሻ እውነታው “ግእዝ በስፋት ያልተተረጎመ ደረቅ ቋንቋ” እንደሚባል በማስታወስ የምለሳ ሥራው ጥንቃቄ የተመላበት ጥናትና ምርምር የሚሻ ጥልቅ ተግባር መሆኑን አሳስበዋል፡፡ የማኅበሩ ሰብሳቢ ቀሲስ ዶ/ር ሙሉጌታም ይህንኑ ሐሳብ በማጠናከር÷ በአሁኑ ወቅት በአገር ውስጥ ጨምሮ ከአፍሪካ(ደቡብ አፍሪካ፣ ደቡብ ሱዳን) እና ከሌሎች ክፍላተ ዓለም በኦርቶዶክስ ተዋሕዶ እምነት የሚጠመቁ፣ ትምህርቱን ሥርዐቱን ማወቅ የሚሹ የልዩ ልዩ ቋንቋ ተናጋሮች፣ ባህል ባለቤቶች ጥያቄ እያቀረቡ በመሆኑ በቋንቋዎች ላይ የሚሠሩ ጥናቶችና ምርምሮች ከፍተኛ ቦታ የሚሰጣቸው ናቸው ብለዋል፡፡
ከቋንቋ ጋራ በተያያዘ በውይይቱ አጽንዖት የተሰጠው ሌላው ሐሳብ ጥናትና ምርምር የሚካሄድበት ቋንቋ ነው፡፡ በፊደላችንና በቋንቋችን የተካበተውን ሀብት አሟጠን እንዳልደረስንበት ያመለከተው የተሳታፊዎቹ አስተያየት፣ ጥናትና ምርምር ከባዕድ ቋንቋ ይልቅ በራሳችን ቋንቋ እየተሠራ ወዲያውም ቋንቋችን ከዘመኑ አስተሳሰብ አኳያ እንዲዳብርና ሚናውን እንዲጫወት መደረግ እንዳለበት ተወትውቷል፡፡ በአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ የታሪክ ትምህርት ክፍል ሓላፊና የማኅበረ ቅዱሳን ጥናትና ምርምር ማእከል ቦርድ ሰብሳቢ ዶ/ር ውዱ ጣፈጠ በውጭ ምሁራን የተሠሩ በርካታ ጥናቶች ውስንነት ምንጭ የቋንቋ ችግር መሆኑን በመጥቀስ በአገርኛ ቋንቋዎች የሚሠሩ ጥናቶችና ምርምሮች መበረታታት እንዳለባቸው፣ ካህናትና ሊቃውንተ ቤተ ክርስቲያን ጥናትና ምርምር እንዲሠሩ፣ በየሞያቸው በት/ቤቶች እንዲያስተምሩ መሠልጠን እንዳለባቸው ተናግረዋል፡፡ የማእከሉ ዳይሬክተር ዲያቆን መንግሥቱ ጎበዜ በበኩላቸው መምህራን ከራሳቸው በተጨማሪ ተማሪዎቻቸው የጥናት ርእሰ ጉዳዮቻቸውን በቤተ ክርስቲያን ዙሪያ እንዲደርጉ በማበረታታት፣ በማማከር፣ መረጃዎችንና ዶኩመንቶችን ለማእከሉ በመስጠት እንዲያግዙ ጠይቀዋል፡፡
በጥናቱ መግቢያ ከተጠቆሙት የጥናት ርእሰ ጉዳዮች (thematic areas) እንደተጠበቁ ሆነው፣ የማኅበሩ ጥናትና ምርምር ማእከል በግብረ ገብ/ሞራል/ እና በታሪክ የቤተ ክርስቲያን ተጽዕኖ ጎልቶ በሚታይበት የኢትዮጵያ ፖሊቲካ ጉዳዮችም ሊጤን እንደሚገባው አስተያየት የሰጡት ተወያዮቹ÷ ጥናትና ምርምር ለዘመኑ ጥያቄዎች ቤተ ክርስቲያን ወጥ ምላሽ እንድትሰጥ በማድረግ አገልጋዩና ምእመኑን ከጉራማይሌ አካሄድ እንደሚጠብቅ ገልጸዋል፤ እንደ አብነትም ዘመኑ በደረሰበት የሕክምና ጥበብ፣ በመድኃኒት አወሳሰድና በጠበል ዙሪያ ያሉ መደናገሮችንና የተሰጡ መፍትሔዎችን ጠቅሰዋል፡፡ ከዚህ ጋራ በተያያዘ የማኅበረ ቅዱሳን ጥናትና ምርምር ማእከል ከፍ ያሉ መንፈሳዊ እሴቶችን መሠረት ያደረጉ የለውጥ ሐሳቦችና ለዘመኑ ተግዳሮቶች ምላሽ የሚሰጡ የፖሊሲ አማራጮች ምንጭ ሊሆን እንደሚገባ አሳስበዋል፡፡ “ጥናትና ምርምር በአዲስ ፕሮጀክቶች ላይ የሚሠራ ሥራ ነው” ያሉት ሌላው ተሳታፊ የማኅበረ ቅዱሳን ጥናትና ምርምር ማእከል ከዚህ ቀደም ተሠርተው በመደርደሪያ ላይ የቀሩ ጥናቶች እየተመዘኑና በመጽሐፍ መልክ እየወጡ የኅትመት ብርሃን በሚያዩበት ሁኔታ ላይም እንዲሠራ ጠይቀዋል፡፡
“የቅዱሳት መጻሕፍት ጥናትና ምርምር ማእከል” በሚል በ1998 ዓ.ም የተቋቋመው የማኅበረ ቅዱሳን ጥናትና ምርምር ማእከል በ2000 ዓ.ም የምርምር ክፍል፣ የቤተ መጻሕፍትና ዶኩመንቴሽን ክፍል፣ የኅትመትና መርሐ ግብር ማስተባበሪያ ክፍል በሚሉ ሦስት ክፍሎች ዳግመኛ የተዋቀረ ሲሆን በሊቀ ጳጳስ ብፁዕ አቡነ ሉቃስ የሚመራ፣ የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ምሁራን በአባልነት የሚገኙበት የአማካሪ ቦርድ አለው፡፡ ማእከሉ በጥናትና ምርምር ሥራዎች ላይ ከመሳተፍና ከማስተባበር ባሻገር መጻሕፍትንና ሰነዶችን ያሰባስባል፤ በቤተ ክርስቲያን ላይ አተኩረው ለሚካሄዱ ምርምሮች የሞያ፣ ገንዘብ እና ቁሳቁስ ድጋፍ እንደሚሰጥም ተዘግቧል፡፡

ቸር ወሬ ያሰማን

አሜን

Post a Comment

Blog Archive

የአቡነ ጳውሎስ "ሐውልተ ስምዕ"

ነጻ ፓትርያርክ ምርጫ ቢሆን ኖሮ ማንን ይመርጡ ነበር? እንበልና ሁሉም ነገር ሥርዓቱን ጠብቆ የተከናወነ የእጩዎች ምርጫ ቢሆን ኖሮ፣ አሁን የምናነሣቸው ጉድለቶች ባይኖሩ ኖሮ፣ 6ኛው ፓትርያርክ እንዲሆን የምትመርጡት ማንን ነበር? (ማሳሰቢያ፦ አሁን ያለው ክፍፍል እና የመንግሥት ተጽዕኖ ባይኖር ኖሮ ተብሎ የሚመለስ ጥያቄ ነው። የምን “ባይኖር ኖሮ ነው” የሚል አስተያየት ካለዎትም እናከብራለን።)