March 8, 2012

ዝክረ ዐድዋ - በኦርቶዶክሳዊት ቤተ ክርስቲያን


·        ኢትዮጵያውያን በዐድዋ ጦርነት በጠላት ላይ ለነበራቸው የሞራል የበላይነት ምንጩ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን መሆኗ ተገልጧል
·        የሀገር ትርጉም፣ የሀገር እና የቤተ ክርስቲያን ሉዓላዊነት ምንነት ተሳታፊዎችን አከራክሯል
·        የታሪክ ልሂቃን በዘመነኛው የዐድዋ ድል ሐቲት ላይ የሚታይባቸው ዝምታ አሳስቧል
·        ፋሽስት ኢጣልያና ቫቲካን ተባብረው በኢትዮጵያ ላይ ለፈጸሙት ግፍ ኢትዮጵያንና የኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያንን “ይቅርታ ይጠይቁ” ተብሏል
·     “ኦርቶዶክሳዊ ማንነት እንደ ኢትዮጵያዊ ብሔራዊ መለዮ መራመድ ይገባዋልን?” የሚል ጥያቄም ተነሥቷል
(ደጀ ሰላም፣ የካቲት 29/2004 ዓ.ም፤ March 8/2012/)፦ ወርኀ የካቲት በግብርናው መስክ አርሶ አደሩ መከሩን አጭዶ፣ ከምሮና ወቅቶ ከውድማ የሚከትበት እንደ ሆነ ሁሉ በዐውደ ውጊያውም መላው ኢትዮጵያውያን በምሥራቅ አፍሪቃ ቀንድ የተወጠነውን የቀጥተኛ ቅኝ አገዛዝ ማዕበል በመግታት ዓለም አቀፋዊ ድል ያስመዘገቡበት ታሪካዊ ወር ነው፡፡

 ታላቅ የአገር ፍቅር ስሜት ሰንቆ፣ በስልት እና ቅንጅት ከጠላት ልቆ የተገኘው የተባበረው የኢትዮጵያ ጦር የካቲት 23 ቀን 1888 ዓ.ም ዕለተ ሰንበት በዐድዋ - እምባ ሶሎዳ፣ ማርያም ሸዊቶ፣ ዓዲ ተቡንና በመሳሰሉት ዋነኛ የጦር ግንባሮች በሰነዘረው የጎሕ ማጥቃት (Dawn Attack) እ.አ.አ በ1870 ግዛታዊ አንድነቱን (Nation State) አረጋግጦ በአዲስ ፖሊቲካዊ፣ ዲፕሎማሲያዊ፣ ወታደራዊ ጉልበት በመጣው የኢጣልያ ጦር ላይ የማያወላውል ድል ተቀዳጅቷል፡፡
የተባበረው የኢትዮጵያ ጦር ከ116 ዓመት በፊት ጥቁሮች በነጮች ላይ የተጎናጸፉትን ዐቢይ ወታደራዊ ድል ሲጎናጸፍ የኢጣልያ ቅኝ አገዛዝ ሕልም በዐድዋ ሜዳ ተቀበረ፤ ኢትዮጵያም በነጻነት መኖሯ ተረጋገጠ፡፡ የዐድዋ አብነት በዚህ ብቻ ሳይወሰን የነጮች የበላይነት ከአስከፊ የዘር መድልዎ ፖሊሲ ጋር በተቆራኘባቸው ደቡባዊ አፍሪቃ እና አሜሪካ የላቀ መንፈሳዊ ውጤት አስገኝቷል፡፡ በእኒህ አገሮች ለሚገኙት ጥቁሮች የዐድዋ ባለድል የኾነችው ኢትዮጵያ የነጻነትና የክብር ቀንዲል ለመኾን በቅታለች፡፡
ቀደም ሲል በቅዱስ መጽሐፍ በስፋት የምትወሳው ኢትዮጵያ “ኢትዮጵያኒዝም”  እየተባለ ለሚጠራ ከነጮች ተጽዕኖ ነጻ የኾነ የጥቁሮች የሃይማኖት እንቅስቃሴ መንሥኤ ነበረች፡፡ አሁን ደግሞ ለዐድዋ ድል መገኘት ዋነኛ ሚና ለተጫወተው የኢትዮጵያውያን የሞራል የበላይነት ማእከሉ የኾነችውን የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያንን በመክበብ በአምሳሏ አብያተ ክርስቲያናትን አቋቁመዋል፡፡ “አቢሲኒያን”፣ “ኢትዮጵያን” እና “ኮፕቲክ” በሚል ቅጽል የሚጠሩ አያሌ አብያተ ክርስቲያናት እና የሃይማኖት ንቅናቄዎች በተለይ በአሜሪካ አህጉር መቋቋማቸው የትስስሩ አንድ ገጽታ ነው፡፡ የአስተምህሯቸው መነሻም “ኢትዮጵያ እጆቿን የምትዘረጋለት አምላክ እርሱ የተገፉት፣ የተጨቆኑት ሕዝቦች አምላክ ነው፤” የሚል ነው፡፡ በዚህ ረገድ የዐድዋ ድል ፋና እስከ ኤስያ አህጉርም ዘልቆ ከዐሥር ዓመት በኋላ የነጩን ዓለም ዳግመኛ ለማናወጥ የበቃው ጃፓን በሩስያ ላይ ያገኘችው ድል መቅድም ኾኗል፡፡
የጥቁር ሕዝቦች ከኢትዮጵያ ጋር መተሳሰር በደስታ ጊዜ ብቻ ሳይኾን በመከራዋም ጊዜ የተፈተነ ነበር፡፡ ከዐድዋ ድል አርባ ዓመታት በኋላ ኢትዮጵያን የኢጣልያ ፋሽስታዊ ፅልመት ሲጋርዳት የዓለም ጥቁሮች በሙሉ ከኢትዮጵያ ጎን በመሰለፍ ተንቀሳቅሰዋል፡፡ ይኸው አሰላለፍ የተገለጸበት ፖሊቲካዊ መልክ የኢጣልያን ፋሽስታዊ ወረራ በመቃወም በዓለም መድረክ ይሟገቱ ከነበሩት ውስጥ እንደነ ጆሞ ኬንያታ እና ክዋሜ ንክሩማህ ያሉትን ወጣት አፍሪቃዊ መሪዎች መጥቀስ ይቻላል፡፡ በእኒህ መሪዎች አማካይነት መላውን ጥቁሮች ለማስተባበር በአሜሪካውያን ጥቁሮች አስቀድሞ የተነሣሣው የ”ፓን አፍሪካኒዝም” እንቅስቃሴ ወደ አፍሪቃ አህጉር ለመሸጋገር በቅቷል፡፡ ይህ በከፊል በዐድዋ ድል ብሥራት የተጀመረው እንቅስቃሴ ቆይቶ በ1955 ዓ.ም ድሉ በተገኘበትና የዐድዋን ድል ተከትሎ ዋና መዲናነቷ በጸደቀላት አዲስ አበባ የአፍሪቃ አንድነት ድርጅት ሲመሠረት አንድ ታሪካዊ ፍጻሜ ላይ ደርሷል ለማለት እንደሚቻል የታሪክ ምሁራን ያስረዳሉ፡፡
ታሪክ ጸሐፊው ጆርጅ በርክሌይ “በአፍሪቃ ታላቅ የተወላጆች ኀይል መነሣቱን ያበሠረና ጨለማዪቱ አህጉር ሥልጣኗን ባንሰራፋችባት በአውሮጳ ላይ የምታደርገው ዐመፅ የመጀመሪያ ምዕራፍ” ሲል የገለጸው የዐድዋ ድል ለመጀመሪያ ጊዜ በብሔራዊ ክብረ በዓል ደረጃ የተዘከረው በሰባተኛ ዓመቱ በ1895 ዓ.ም ነበር፡፡ በዓሉ ወደ ዐድዋ ከዘመቱት ታቦታት አንዱ በነበረው የገነተ ጽጌ ቅዱስ ጊዮርጊስ ቤተ ክርስቲያን በሚገኝበት በእምዬ ምኒልክ አደባባይ ሲከበር በስፍራው ከነበሩት ብዙ ሺሕ ፈረሰኞች የተነሣ “ፀሐይ በአዋራ መጋረዷን” ጳውሎስ ኞኞ “የኢትዮጵያ እና ኢጣልያ ጦርነት” በተሰኘው መጽሐፉ ገልጧል፡፡
በዓሉ ዘንድሮም ለ116 ጊዜ በብሔራዊ ደረጃ ሲከበር በአዲስ አበባ ኮተቤ ደብረ ጽባሕ ቅዱስ ሚካኤል ቤተ ክርስቲያን ሰንበት ት/ቤት እና በማኅበረ ቅዱሳን በተዘጋጁ መድረኮች ዐድዋን ከቤተ ክርስቲያን ጋር በሚያዛምዱ ርእሰ ጉዳዮች ላይ ጽሑፎች ቀርበዋል፤ ውይይቶችም ተካሂደዋል፡፡ የማኅበረ ቅዱሳን ጥናትና ምርምር ማእከል የካቲት 24 ቀን 2004 ዓ.ም ያዘጋጀው ውይይት “የኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያን፣ ሀገር እና የሀገር ሉዓላዊነት” በሚል ርእስ የተካሄደ ነበር፡፡ ባለፈው ዓመት የተጀመረውና ከዐድዋ ድል በዓል አከባበር ጋር በተያያዘ በየዓመቱ ቀጣይነት እንደሚኖረው የተገለጸው ይኸው ውይይት በብሔራዊ ሙዝየም አዳራሽ የተካሄደ ሲሆን ከ120 ያላነሱ ተሳታፊዎች ተካፍለውበታል፡፡ በተጠቀሰው ርእሰ ጉዳይ የመነሻ ጽሑፍ ያቀረቡት በቅርስ ጥናትና ጥበቃ ባለሥልጣን የቅርስ ጥናትና ምርምር ዳይሬክቶሬት ተመራማሪ የኾኑት አቶ ተስፋዬ አራጌ ሲኾኑ ውይይቱን ለአጭር ጊዜ የመሩት ደግሞ ብርጋዴር ጄኔራል ዋስይሁን ንጋቱ ናቸው፡፡
የንጉሠ ነገሥት ዐፄ ዮሐንስን የመተማ ጦርነት ዐዋጅ መነሻ በማድረግ የአገርን ትርጉም ያብራሩት ጽሑፍ አቅራቢው አቶ ተስፋዬ፣”አገር ማለት በጊዜ ልደት እትብት የሚቀበርባት - መካነ እትብት፤ በጊዜ ሞት ተከፍቶ የሚጠብቅ መካነ ዕረፍት፤ በመዋዕለ ሕይወት በነጻነት የሚኖሩባት - ማንነት፣ ነጻነት፣ ሕይወት፣ ታሪክ፣ ሃይማኖት፣ መንግሥተ ሰማያት /በምድር በሠራነው በሰማይ ዋጋ እናገኛለንና/” ማለት መሆኑን አብራርተዋል፡፡ በቅዱስ መጽሐፍ “የጥበብ መጀመሪያ እግዚአብሔርን መፍራት ነው” እንደተባለ ሁሉ “የፍቅር መጀመሪያ አገርን ማፍቀር/መውደድ ነው፤” ብለዋል፡፡
የቅድመ ጦርነቱን ታሪካዊ ሂደት በሰፊው ያብራሩት አቶ ተስፋዬ ÷ ከሩስያ በቀር በ13 የአውሮጳ መንግሥታት ስምምነት የተገኘበት፣ በተለይም በእንግሊዝ አደፋፋሪነት የተገፋውና በውጫሌ ውል ገሃድ የወጣው የኢጣልያ የቅኝ አገዛዝ ፍላጎት በኢትዮጵያውያን ለባዕድ አልገዛም ባይነት በመጨናገፉ ማሳረጊያው የዐድዋ ጦርነት የኾነው ግጭት መጀመሩን አውስተዋል፡፡ በውጭ ግንኙነት ረገድ ኢትዮጵያን የኢጣልያ ጥገኛ የሚያደርገው የውጫሌ ውል በየካቲት ወር 1885 ዓ.ም በዐፄ ምኒልክ በይፋ ከተሻረ በኋላ፣ ኢጣልያ በሰሜን በኩል የትግራይን መሳፍንት በማሸፈት የዐፄ ምኒልክ ባላንጣ የማድረግ ፖሊሲ ራስ መንገሻ ዮሐንስ ከዐፄ ምኒልክ ጋር ዕርቅ ሲፈጽሙ፣ የራስ መንገሻን አርኣያ ተከትለው እነ ራስ ስብሐት አረጋዊ እነ ደጃች ሓጎስ ተፈሪ “አገራችንን አሳልፈን አንሰጥም” በማለት በዐድዋ ዘመቻ ወቅት ከዐፄ ምኒልክ ጎን ሲቆሙ ዕርቃኑን መቅረቱን አውስተዋል፡፡
በዐድዋ ጦርነት የተባበረው የኢትዮጵያ ጦር ለተቀዳጀው ድል የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያንን ሚና የዘረዘሩት አቶ ተስፋዬ፣ ራስ መንገሻ ከዐፄ ምኒልክ ጋር በፈጸሙትና በሥጋ ወደሙ በቃለ መሐላ በጸናው ዕርቅ ሥዕለ ማርያምን ይዘው የተማፀኑት አበው ካህናት ከፍተኛ ሚና መጫወታቸውን አስረድተዋል፡፡ በዐፄ ምኒልክ የክተት ዐዋጅ ውስጥም ንጉሠ ነገሥቱ ጠላት አጥፍቶ፣ ድንበር አስፍቶ ያኖራቸው እግዚአብሔር መኾኑን፣ እግዚአብሔር እንደማያሳፍራቸውና አሳፍሯቸውም እንደማያውቅ፣ ድንበር አልፎ የመጣው የኢጣልያ ጦር የሃይማኖትም ጠላት መኾኑን በመግለጽ በእግዚአብሔር ረዳትነት ድል እንደሚያደርጉት ማመናቸው፣ ጉልበት ያለው ሁሉ ለሃይማኖቱ ሲል እንዲረዳቸው መማጠናቸው፣ ወስልቶ የቀረውን ሁሉ ግን በአገር ጉዳይ አማላጅ የለምና እንደሚቀጡት በእመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ስም ማስጠንቀቃቸው መሪዎቹ የነበራቸውን ክርስቲያናዊ ባህልና ትምህርት የሚያረጋግጥ ነው፡፡
በዐድዋ ዘመቻ ኅዳር 29 ቀን 1888 ዓ.ም ዐምባ አላጌ ላይ በተካሄደው የመጀመሪያው ጦርነት የግንባር ቀደሙ ጦር መሪ ፊታውራሪ ገበየሁ ጦራቸውን ሊታመን በማይችል ድፍረትና ወኔ እየመሩ ውጊያ የገቡትና ድል ያደረጉት በአምሳለ መስቀል ካማተቡና ጸሎት ካደረሱ በኋላ ነበር፡፡ ቀጥሎ በተደረገው የመቐለ ከበባ ብልሃታቸውን ያሳዩት እቴጌ ጣዪቱ በሰልፋቸው እግዚአብሔር እንዲገባበት ጸልየዋል፤ “አሳፍረኸኝ አታውቅምና” ሲሉም ሥዕለት ተስለዋል፡፡ ከዚህ በኋላ ዐፄ ምኒልክ ጦራቸውን ወደ ዐድዋ መርተው ጣልያኖች ከዓዲ ግራትና እንጢቾ ምሽጋቸው ወጥተው ውጊያ የሚገቡበትን ቀን በናፍቆት እየጠበቁ ለማይቀረው ጦርነት ሲዘጋጁ በዐድዋ እንዳባገሪማ ገዳም የሳምንት ሱባኤ ገብተው ነበር፡፡
“ክፉ ቀን” በሚል ስያሜ በሚታወቀው ችጋር ኢትዮጵያና ምሥራቅ አፍሪካ በረሃብ በተመቱበት ወቅት በገዛ ስንቁ በእግሩ ተጓጉዞ ዘምቶ ለግዳጅ የተሰማራን ሠራዊት የውጊያ ወኔና ዝግጁነት ጠብቆ ማቆየት አዳጋች ነውና የሰራዊቱ ስንቅ ይዞታ አሳሳቢ አድርጎታል፡፡ ከአርበኛው ጋር ግንባር ቀደም ኾነው ÷ ረዳኤ ምንዱባን ቅዱስ ሚካኤል ለርእሰ መነኰሳት አባ እንጦንስ ባመለከተው አምሳል የሰሌን ቆብ ደፍተው አብረው የዘመቱት መነኰሳት፣ ባሕታውያንና መስቀል የጨበጡ ካህናት በሠራዊቱ መካከል በመገኘት ውጊያው እስኪጀመር ድረስ እያበረታቱ የአገር ፍቅር ስሜቱን በመጠበቅ ሚናቸውን አሳይተዋል፡፡
የሠለጠነው የኢጣልያ ጦር እነባሻይ ኣውዓሎም ሓረጎትን በመሳሰሉ ኢትዮጵያውያን የስለላ ሰዎች ብልሃት ርምጃዎቹን ማቀነጃጀት እንዲሳነው ኾኖ ወደ ጦርነቱ እንዲገባ በማድረግ ኢትዮጵያ በወታደራዊ መረጃም የበላይነት እንዲኖራት አስችለዋል፡፡ የዘማቹን አርበኛ ወኔ እየጠበቁ ያቆዩት መነኰሳትና ካህናት በውጊያውም ወቅት ራሳቸው በሕይወታቸው ዋጋ እየከፈሉ ጀግናውን እየናዘዙ፣ ፈሪውን እያወገዙ ለሀገር መሞት ክቡር መሥዋዕት መኾኑን እያስገነዘቡና ከሞት በኋላ ያለውን ተስፋ መንግሥተ ሰማያት እየሰበኩ፣ በጀግንነት ለወደቁትም ጸሎተ ፍትሐት እያደረጉ አባታዊ ሓላፊነታቸውን ተወጥተዋል፡፡
በዘመናዊው የኢትዮጵያ ታሪክ የ19ኛው ምእት የጦርነቶች ማሳረጊያ የተባለው የዐድዋ ጦርነት ግብጻዊው ጳጳስ አቡነ ማቴዎስ በዐድዋ ቅዱስ ገብርኤል ከመሩት ጸሎተ ቅዳሴ በኋላ ተጀምሮ ባለ ድሉ የገበሬ ሠራዊት እንዳማርያም ላይ ተሰብስቦ በካህናቱ መሪነት ባደረሰው ስብሐተ እግዚአብሔር ነበር የተጠናቀቀው፡፡
አቶ ተስፋዬ የታሪክ ምንጮችን በማገናዘብ እንዳስረዱት በተለያዩ ዘመናት በኢትዮጵያ ላይ የተቃጡትን የባዕዳን ጥቃቶችን በመከላከል አበው ጳጳሳትና ሊቃውንተ ቤተ ክርስቲያን ሳይቀሩ ቀጥተኛ ተሳትፎ ነበራቸው፡፡ የዐድዋን ሽንፈት ለመበቀል ከአርባ ዓመት በኋላ ወረራ የፈፀመውን የኢጣልያን ፋሽስት ለመጋፈጥ ካህናቱ ወደ ጦርነት እንዲሄዱ አለቃ መርሻ ዘውእቱ የተባሉ የቅኔ ሊቅ በሚከተለው መንገድ ቀስቅሰዋል፡-

                        ግቢ ትምህርት ቤት ተመለሽ ቅኔ፤
                        ወንዶች ከዋሉበት እውላለሁ እኔ።

ሌላውም ሊቅ በሚከተለው ስንኝ ተናግረዋል፤
                        ደኅና ኹኝ እማማ በደኅና ቆይን፣
                        ዕድል ለአገራችን ምንም አይጎድለን፣
                        ወንዛችን ብዙ ነው ውኃም አይጠማን፣
                    ዱሯችን ብዙ ነው አያሻንም ጉድባ፣
                    ምድራችን ነፋሻ አያስፈራም ወባ፣
                        ጋራችን ትልቅ ነው መነጥር አያሻ፣
                        ድንኳንም አንተክል አለን ብዙ ዋሻ፣
                    ሥጋም እንዳያምረን ዱር ሁሉ እንስሳ ነው፣
                    ጠጅም እንዳያምረን ጫካው ሁሉ ማር ነው፣
                          ይራባሉ ብለሽ እንዳትጨነቂ፣
                          እጅሽን ዘርግተሽ ከአምላክ ፊት ውደቂ፡፡

የዚሁ የፋሽስት ኢጣልያ ወረራ ሰለባ በነበረችው የኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያን አድባራትና ገዳማት ብዙ ባሕታውያንና መነኰሳት ካህናት ለአገራቸውና ለሃይማኖታቸው መሥዋዕት ሲኾኑ ከጳጳሳቱም ታሪካቸው ለኢትዮጵያውያን መመኪያ የኾኑት ሰማዕተ ጽድቅ አቡነ ጴጥሮስ ጳጳስ ዘምሥራቀ ኢትዮጵያ እና አቡነ ሚካኤል ጳጳስ ዘጐሬ በግፈኛው ፋሽስት መገደላቸው ተመልክቷል፡፡
በጽሑፍ አቅራቢው የተወሱት ሌላው ሊቅ በዐፄ ሠርጸ ድንግል (1555 - 1589 ዓ.ም) ዘመነ መንግሥት የነበሩትና በጀግንነታቸው ንጉሡ የራስነት ማዕርግ የሰጧቸው የድጓው ሊቅ ዮናኤል ናቸው፡፡ በቱርኮች ላይ ንጉሡ ባስተላለፉት የክተት ዐዋጅ ወደ ሰሜን ሲዘምቱ አብረው የዘመቱት ሊቁ ዮናኤል በታኅሣሥ ወር 1578 ዓ.ም ድባርዋ ዓዲቆር ላይ በተደረገው ውጊያ የጠላትን መሪ ባሻ ሐሰንን በጦር ወግተው ለንጉሡ ግዳይ ጥለዋል፡፡ ንጉሡ ዮናኤል ባሳዩት ጀግንነት ራስ አሰኝቶ ምን እንደሚፈልጉ ይጠይቃቸዋል፡፡ ዮናኤልም “ስሜ ለዘላለም እየተጠራ እንዲኖርልኝ በድጓ ዜማ ይመልከትልኝ” አሉት፡፡ ንጉሡም ይኹንልህ ብለው ሊቃውንቱን ጠርተው ራስ ዮናኤል የፈጸመውን ጀግንነት አስረድተው “በድጓ ዜማ ይመልከትለት” ብለው አዘዙ፤ ሊቃውንቱም ትእዛዙን ተቀብለው፡-
በሰማዕት ነስኡ ዕሴቶሙ፤
ወረከቡ ተስፋሆሙ ዜማ፤
ዮናኤል ሎሌ ባሻይን ቆረጠው በሾተል፣
የመለክ ሰገድ ሎሌ ዮናኤል፣
ባሻይን አረደው በሾተል”
ብለው በአራራይ ዜማ አዚመው በድጓው መድበል ስላመለከቱለት በዜማ እየታወሰ ይኖራል፡፡ መ/ር ወልደሚካኤል የተባሉ ሌላ የመጻሕፍት መምህር የደርቡሽ ጦር ጎንደርን በወረረበት ወቅት፣ “ከእናንተ መካከል የፈራ ቢኖር ይሂድ፤ እኔ ግን ለሃይማኖቴ እሞታለሁ፤” ሲሉ መሥዋዕትነትን ተቀብለዋል፡፡
በአጠቃላይ እንደ ጽሑፍ አቅራቢው አቶ ተስፋዬ አባባል የኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያን የሀገርን ምንነት በዜጎች ኅሊና በመቅረጽ እና የሀገርን ሉዓላዊነት በማስጠበቅ ረገድ “የራስዋን ታሪክ የሠራች፣ መንግሥት እና ሕዝብ የሠራውን ታሪክም ያስጠበቀች” የትውልድ ባለውለታ መኾኗን፣ ይህም አገልግሎቷ ዛሬም በየጠረፉ ድንበር በሚጠብቀው ሠራዊት ዘንድ ቀጥሎ እንደሚገኝ አስረድተዋል፤ እንደ አብነትም በምሥራቅ ኢትዮጵያ ጠረፍ ክልል ሶማሌ በቀብሪደሃር ቅድስት ማርያም፣ ሃርቲሼክ አቡነ አረጋዊ፣ ጭናክሰን ቅዱስ ገብርኤል፣ ጉዳ ቅዱስ ገብርኤል እና ደገሃቡር ቅዱስ ጊዮርጊስ አብያተ ክርስቲያናት በመከላከያ ሠራዊት መካከል ኾነው የሚያገለግሉትን ካህናት አስታውሰዋቸዋል፡፡
ውይይቱን የመሩት ብርጋዴር ጀነራል ዋስይሁን ንጋቱም አንድ ሌላ ከፍተኛ መኰንን በአንድ ወቅት የተናገሩትን በመጥቀስ ሲናገሩ፣ “መድፍም ታንክም ጄትም ቢደረደር ወኔ፣ የአገር ፍቅር ስሜት ከሌለ ሁሉም ሸምበቆ ነው፤” ብለዋል፡፡”የአገር ጉዳይ የመከላከያ (ብሔራዊ) ጦር ሓላፊነት ብቻ አይደለም” ያሉት ጀነራል መኰንኑ በሠራዊቱ ክፍሎች ውስጥ ሞራላዊ ብርታቱ እንዲጠበቅ የኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያን ከፍተኛ ቦታ እንዳላት አውስተዋል፡፡ በዚህ ረገድ በምሥራቅ ይኹን በሰሜን የጦር ግንባሮች በየሻለቃው ከግዳጅ በፊት ሞራላዊ ብርታት የሚሰጡ ካህናት አባቶች እንደነበሩ አውስተዋል፡፡ ይህም ኾኖ የቤተ ክርስቲያን ቀዳሚ ሓላፊነት የአገርና የዓለም ሰላም እንዲጠበቅ መጸለይና ሌሎችንም ሰላማዊ ጥረቶች ማድረግ መኾኑን እንደሚገነዘቡ አመልክተዋል፡፡
ከውይይቱ ተሳታፊዎችም በርካታ ሐሳቦች ተነሥተዋል፤ ጥያቄዎችም ቀርበዋል፡፡ በጽሑፉ በጥቂቱ የቀረበው የቤተ ክርስቲያን ሚና በግልጽ የሚታወቅ ኾኖ ሳለ ዛሬ በአንዳንድ ክፍሎች ቤተ ክርስቲያን እንደ ችግር የምትጠቀስበት ኹኔታ መኖሩ እንደሚያሳዝናቸው የገለጹ አንድ ተሳታፊ ዛሬም “አገራችን በሰማይ ነው”  እያሉ አለቦታው በመጥቀስ የሚያጭበርብሩ በሃይማኖት ስም የሚንቀሳቀሱ መናፍቃን ትውልድና ቤተ ክርስቲያን የከፈሉትን ዋጋ የሚያራክሱ በመኾናቸው ልናውቅባቸው እንደሚገባ መክረዋል፡፡
“ሀገር ማለት ሕዝብ ነው፤ ወንዙ፣ ሜዳው፣ ተራራው አይደለም” በማለት አንዳንድ ፖሊቲከኞች የሚሰጡትን ፍችም እንደማይቀበሉት አስታውቀዋል፡፡ ይህን ሐሳብ የሚጋሩ ሌላው የአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ ተማሪም በዓለም አቀፍ ሕግ አገር ሲባል ሕዝብን፣ ዓለም አቀፍ ዕውቅና ያለው ግዛትን፣ ድንበርን፣ መንግሥትን እና ሉዓላዊነትን እንደሚያካትት በመግለጽ “አገር ማለት ሕዝብ ነው” የሚለው ፍች ጉድለት ያለበት መኾኑን አስረድተዋል፡፡
በአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ መምህር የሆኑና ከታሪክ ጥናት አንጻር የጽሑፉን አቀራረብ (ወገንተኛነት) የተቹ ሌላ ተሳታፊ፣ “በቀደሙት ሁለቱ አስተያየቶች ስለ አገር ምንነት የተሰጡት ማብራሪያዎች በመጀመሪያ ደረጃ የሚቀርቡና በቂ ያልሆኑ መግለጫዎች ናቸው፤ አገር በአንድ መንገድ ለመግለጽ የሚያዳግት ነገር (abstract entity) ነው፤” ብለዋል፡፡ ሉዓላዊነት የውስጥ እና የውጭ ተብሎ እንደሚከፈል በማስረዳትም÷ ግብጻውያን ጳጳሳት ለብዙ ሺሕ ዓመታት ከግብጽ እየተሾሙ ይመጡ የነበረበት ሁኔታ፤ ቤተ መንግሥቱ እና ቤተ ክህነቱ እርስበርስ ለኀይል ሲቀናነቀኑ የኖሩበት ታሪክ ከአገር እና ከቤተ ክርስቲያን ሉዓላዊነት አንጻር እንዴት እንደሚታይም ጠይቀዋል፡፡ ሌላው ተሳታፊም “የአገር ሉዓላዊነት ተከበረ የሚባለው የውጭ ጠላት ስለተመከተ ብቻ ነው ወይ?” የሚል ጥያቄ አቅርበዋል፡፡
ለጥያቄዎቹ ከመድረኩም ከተሳታፊዎችም የተሰጡ ሐሳቦች በአገር እና በአገር ሉዓላዊነት ዙሪያ በደረቁ የሚሰጡ ሳይንሳዊ ብያኔዎች በኢትዮጵያ እና በኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያን ተጨባጭ ሁኔታ ውስጥ መታየት እንደሚገባቸው የሚያሳስቡ ጥቅል ምላሾች ነበሩ፡፡ የትኛውም አገር የሕዝቦች የግጭትም የሰላምም መስተጋብር ውጤት እንጂ በእጅ ለእጅ መጨባበጥ ወይም በልመና የቀና አለመኾኑን ያመለከቱት መላሾቹ ጀርመን፣ ፈረንሳይ፣ ኢጣልያ፣ ቤልጅየም የመሳሰሉት አገሮች ዛሬ የያዙትን ግዛታዊ አቋም እንደ ምሳሌ አቅርበዋል፤ ለሦስት ሺሕና ከዚያም በላይ÷ እንደ ዶናልድ ሌቪን ባሉት ምሁራን ዘንድ ደግሞ በድንቅነሽ /ሉሲ/ ዕድሜ ሊቆጠር የሚችለው የኢትዮጵያ የመንግሥትና የነጻነት ታሪክ ጥልቅ ጥናት እንደሚያሻው መክረዋል፡፡
በብዙ አጋጣሚዎች ‹ታሪክ› እየተባለ የሚነገረው የምሁራን ሐተታ በመሠረታዊ ጠባዩ ‹ወገንተኛ› መሆኑን በመጥቀስ ከባዕዳኑ ወይም እነርሱን ከሚመስሉቱ ምሁራን (miseducated scholars) ይልቅ በተሻሉ ምንጮች ላይ ማተኮር፣ እነርሱንም ማጥራት እንደሚገባ አጽንዖት ተሰጥቷል፡፡ “ወላጆቻችን የመላእክት ሳይኾን የሰው ልጅ ሥራ ነው የሠሩት፤ ስሕተት ቢገኝበትም ባዶ ግን አይደለም፤” ብለዋል የታሪክ ባለሞያው አቶ ተስፋዬ፡፡
የአገርን ሉዓላዊነት ማስከበር ድንበር አልፎ የመጣን የውጭ ጠላት በመመለስ ብቻ ሳይሆን የባህል ወረራ ዋነኛ አጀንዳ በሆነበት በዛሬው የግሎባላይዜሽን ዘመን ማንነትን ጠብቆና ተነጻጻሪ አቅም ይዞ በመገኘት እንደሚገለጽ ሌላው የመድረኩ አወያይ የማኅበረ ቅዱሳን ጥናትና ምርምር ዳይሬክተርና በአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ የአርኬዎሎጂ መምህር መንግሥቱ ጎበዜ አስረድተዋል፡፡ አህጉሪቱን እንደ ማዕበል እያጥለቀለቀ በነበረው የአውሮጳ ቅኝ አገዛዝ ዘመን የኢትዮጵያን የወደፊት ዕድልና የዕድገት አቅጣጫ ከተቀረው የአፍሪካ አህጉር የለየው የዐድዋ አብነት በተከታታይ ትውልዶች ዘንድ ብሔራዊ ኩራትንና ነጻነትን ያጎናጸፈ ነው፡፡ የዘመኑ ትውልድም ባሉበት ወቅታዊ ማኅበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊ እና ፖሊቲካዊ ተግዳሮቶች ፊት ዐድዋን የመንፈስ ልዕልናው ስንቅ ሊያደርገው እንደሚገባ መምህሩ ተናግረዋል፡፡
ከቤተ ክርስቲያን ሉዓላዊነት ጋር በተያያዘ ለተነሣው ጥያቄ በውይይቱ ትኩረት የተሰጠው ኢትዮጵያ ጳጳሳትን ከግብጽ ስታስመጣ መቆየቷ ነው፡፡ ጽሑፍ አቅራቢው አቶ ተስፋዬ የግብጻውያን ጳጳሳት እየተሾሙ መምጣት ኢትዮጵያውያን “በማመን እንጂ በመበለጥ ያደረጉት አይደለም” ሲሉ መምህር መንግሥቱ ጎበዜ ደግሞ ቅዱስ ፍሬምናጦስ ወደ ግብጽ ሄዶ የክርስትና ሃይማኖት ቀድሞም የነበረ መሆኑን አብሥሯል፡፡ በጵጵስና ተሾሞ ያመጣልንም ሥርዓ ተ ቤተ ክርስቲያንን እንጂ ሃይማኖትን አይደለም፡፡ ከአኵስም ቤተ መንግሥት ወደ እስክንድርያ ሲላክ በትውልዱ ሶርያዊ ይሁን እንጂ በዜግነቱ ኢትዮጵያዊ ኾኖ ነበር፡፡
ከቅዱስ ፍሬምናጦስ በኋላ ግብጻውያን ጳጳሳት እየኾኑ መላካቸው ቅብጦቹ በፍትሐ ነገሥቱ በሥርዋጽ ባስገቡት ዲቃላ ሕግ የተነሣ በመኾኑ፣ በሂደትም ችግር በማስከተሉ ከዛጔው ንጉሥ ቅዱስ ሐርቤ ጀምሮ ለዘመናት ጥያቄ ሲነሣበት ቆይቶ በ1951 ዓ.ም የኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያን በመንበረ ፕትርክና ራሷን የቻለች (Autocephalous and Independent Church) ለመኾን ስትበቃ ምላሽ ማግኘቱን አብራርተዋል፡፡
መ/ር ያረጋል አበጋዝ በበኩላቸው በተፃራሪው ቅዱስ ፍሬምናጦስ (አባ ሰላማ ከሣቴ ብርሃን) የመጀመሪያው የኢትዮጵያ ጳጳስ እንደኾነ የሚነገረው የቅዱስ ፍሬምናጦስ ዘመድ ሜሮጵዬስ ለቤተ ክርስቲያን ታሪክ ጸሐፊዎቹ ሩፊኖስ፣ ሶዞሚኖስ እና ቴዎዶር የነገራቸው ተይዞ በመኾኑ ተጨማሪ ፍተሻ ሊደረግበት እንደሚገባ ጠቁመዋል፡፡ ቀደም ሲል በተሰጠው አስተያየት እንደተጠቀሰው ክርስትና ወደ ኢትዮጵያ የገባው ከሐዋርያት ዘመን ጀምሮ (34 ዓ.ም) በኢትዮጵያዊው ጃንደረባ በመሆኑ፣ ከእርሱም ጋር ቅዱስ ማቴዎስና ሌሎችም ሐዋርያት በኢትዮጵያ የተለያዩ ክፍሎች ማስተማራቸውና የቅዱስ ማቴዎስ ገድል መኖሩ፣ እኒህ ሐዋርያት ባስተማሩበት ኹኔታ ኢትዮጵያውያንን ከዲቁና እስከ ጵጵስና አልሾሙም ለማለት እንደማይቻል፣ በኋላም ነገሥታቱ ኣብርሃና ኣፅብሃ ቅዱስ ፍሬምናጦስን ሥርዓተ ቤተ ክርስቲያንን ከግብጽ እንዲያመጣ የመላካቸው መነሻ የነበረ ነገር ግን በተለያየ ምክንያት አፈጻጸሙና ይዞታው የተዳከመ ትውፊት ሊኾን እንደሚችል አስተያየታቸውን ሰጥተዋል፡፡
ውይይቱ የዐድዋን ድልና ተጽዕኖውን በማዘከር ላይ ማተኰር ይገባው እንደነበር የተናገሩት መ/ር ያረጋል÷ “የዐድዋ ድል የሚያጎናጽፈውን የመንፈስ የበላይነት ለማጣጣም በባዕዳኑ መካከል እንደ መገኘት ጥሩ አጋጣሚ የለም፤” ብለዋል፡፡ ለትምህርት በፈረንሳይ አገር በነበሩበት ወቅት የዐድዋን ድል በማሰብ “እኛ (ኢትዮጵያውያን) ነጻ ሕዝቦች ነን፤” ብሎ መናገር ከሚያሳድርባቸው የመንፈስ ርካታ የተነሣ “የአባቶቻችንን ነፍስ ይማር፤ አጥንታቸውን ያለምልም” ይሉ እንደ ነበር ገልጸዋል፤ ከተሳታፊውም ከፍተኛ ድጋፍ ተችሯቸዋል፡፡
መምህሩ የዐድዋን ታሪክ በነባራዊ ይዘቱ ከመቀበል ይልቅ ራሳቸውን ዳኛም ምስክርም አድርገው አጉል ትችት የሚያራግቡ አካላትን በመተው፣ የታሪኩን ጠባቂነት ባለቤትነትም ለኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን በመስጠት ኦርቶዶክሳዊነትን የኢትዮጵያዊነት ብሔራዊ መለዮ አድርጎ የማራመድ ሐሳብ ውይይት እንዲካሄድበትም ጠይቀዋል፡፡ ለዚህም ከጥቅምቱ የሩስያ አብዮት ጀምሮ በቦልሼቪኮች ኮሚኒስታዊ አገዛዝ ከፍተኛ በደል የተፈጸመባት የሩስያ ኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያን ቀድሞም ዛሬም ለብሔራዊ ስሜት መበልጸግ የነበራትና ያላት የማይተካ ድርሻ እንደ ምሳሌ ተጠቅሷል፡፡
በ70 ዓመታቱ የሶቭየት ዘመን ጳጳሳቷ፣ ካህናቷ እና ምእመናኗ የእንግልትና ግድያ ዒላማ÷ አብያተ ክርስቲያኗ፣ ገዳማቷ እና የትምህርት ተቋሞቿ የስልታዊ ዓለማዊ ማራከሶች (Repression and Secularisation) ሰለባ የነበረችው የሩስያ ኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያን እ.አ.አ በ1941 የናዚ ጀርመንን ጥቃት ለመመከት በተደረገው ትግል የሕዝቡ የአርበኝነት ማእከል ነበረች፡፡ 75 በመቶ ሕዝቧ የምሥራቅ ኦርቶዶክስ ክርስትና ተከታይ የኾነባት የዛሬዪቱ ድኅረ ኮሚኒስት ሩስያ እንደነ ፓትርያሪክ አሌክሲ ሁለተኛ (1990 - 2008) ባሉት መሪዎቿ ጥረት እነሆ የአገራዊ ማንነት ተቆርቋሪዎች እና ብሔረተኞች ትእምርት ኾና፣ ፕሬዝዳንቱና ጠቅላይ ሚኒስትሩም ሳይቀሩ ሲያስቀድሱባት እናያለን፡፡
እንደ ሰርቢያ ባሉት የቀድሞ የዩጎዝላቪያ ግዛቶች የቤዛንታይን/ምሥራቅ/ ኦርቶዶክስ ክርስትና ዐይነተኛ ብሔራዊ መለዮ ከመኾኑ የተነሣ “ሰርቢያዊ ኾኖ ካቶሊክ ወይም ፕሮቴስታንት አይታሰብም” እስከ መባል መደረሱን መ/ር ያረጋል ገልጸዋል፡፡ “በመጀመሪያ እኔ ጀርመናዊ ነኝ፤ ከዚያም ፕሮቴስታንት ነኝ” የሚለውን የታወቀ አባባል በማጣቀስ ከመ/ር ያረጋል ጋር የሚተባበሩ የሚመስሉት ጽሑፍ አቅራቢው አቶ ተስፋዬም የአንጋፋውን የአገር ሽማግሌ ፊታውራሪ አመዴ ለማን ብሂል አስታውሰዋል - የቤተ ክርስቲያን የውስጥ አገልግሎት የካህናቱና ምእመናኑ ቢሆንም ቅርሱና ባህሉ ግን የሁሉም ኢትዮጵያዊ ነው፡፡
የውይይቱ ተሳታፊዎች ከሰነዘሯቸው ጥያቄዎች ውስጥ ቤቱን ፈገግ ያደረገ ጥያቄ መነሣቱ አልቀረም፡፡ “ጥያቄው የጓደኞቼ ነው፤ ልመልስላቸውም አልተቻለኝም” ያለው አንድ የአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ ተማሪ ለመድረኩ ያቀረበው ጥያቄ፣ “በኢጣልያ ወረራ ቫቲካን (የሮማ ካቶሊክ) የገንዘብ ርዳታ ማሰባሰቧን÷ ወራሪውን ሠራዊት፣ ታንኩንና መድፉን መባረኳን በመጥቀስ እናወግዛታለን፡፡ የኛስ ቤተ ክርስቲያን ለአርበኞች ሞራላዊ ድጋፍ ሰጥታለች ስንል የሮም ካቶሊክ ካደረገችው እንደምን ተለይቶ ይታያል?” የሚል ነበር፡፡ ንጽጽሩ ጉዳዩን ከምንመለከትበት ‹መነጽር› /አመለካከት/ ሊነሣ እንደሚችል የተናገሩት የማኅበሩ ጥናትና ምርምር ዳይሬክተር መ/ር መንግሥቱ ጎበዜ፣ ኦርቶዶክሳዊት ቤተ ክርስቲያን በጦርነቱ የነበራትን ሚና የኢጣልያ ቅኝ አገዛዝ ኀይል ከነበረው አጠቃላይ ፍላጎትና የሮማ ካቶሊክ በዚህ ኀይል ተጠቅማ ለማሳካት ዐቅዳው ከነበረው ልዩ ፍላጎት አኳያ መገምገም እንደሚያስፈልግ መክረዋል፡፡
የኢትዮጵያ ታሪክ “የጦርነት ታሪክ ነው” መባሉን እንደማይስማሙበት የተናገሩት ዳይሬክተሩ፣ “የኢትዮጵያ ታሪክ በመከላከል ላይ የተመሠረተ የመሥዋዕትነት ታሪክ ነው ተብሎ ቢቃና ይመረጣል፤” ብለዋል፡፡ የዐድዋ ጦርነትና ቤተ ክርስቲያን በጦርነቱ የነበራት ሚና አገራችን ነጻነቷን በኀይሏ ተከላክላ ለማስከበር የተፈጸመው ተጋድሎ ትልቁ ምስክር እንጂ እንደ ቅኝ ገዥዋ ኢጣልያና የኢትዮጵያን ምእመናን ወደ ላቲንነት ጎተራ ለማስገባት ቋምጣ እንደነበረው ቫቲካን (ሮም ካቶሊክ) የሌላውን የመቀራመት ጠኔ እንዳልነበር አስገንዝበዋል፡፡ ስለሆነም ኦርቶዶክሳውያን ካህናት አገራቸውን ለሚከላከሉ አርበኞች የሰጡትን ቡራኬ ካቶሊካውያን ካርዲናሎችና ፓፓው የሌላውን አገር ግዛትና ማንነት በመውረር ካህናት መነኰሳትን ላረዱ፣ አብያተ ክርስቲያናትን ላጋዩ ፋሽስቶች ከሰጡት ቡራኬ ጋር ማነጻጸር ከባድ የአስተሳሰብ (መነጽር) ችግር መኖሩን እንደሚያሳይ የታሪክና አርኬዎሎጂ መምህሩ ዲያቆን መንግሥቱ ጎበዜ አሳስበዋል፡፡
ቫቲካን ለቅኝ ገዥው የኢጣልያ መንግሥት የገንዘብ ድጋፍ መስጠት፣ ወታደሮቹንና የጦር መሣሪያዎቻቸውን “የተቀደሰ ዘመቻ ነው” እያሉ መባረክ ብቻ ሳይሆን በሴቶች፣ ሕፃናት፣ አረጋውያን ላይ ግፍ በተፈጸመበት፣ ብዙ ገዳማት እና አድባራት በተቃጠሉበት፣ ኢትዮጵያ ከብዙ ጠላት እየተከላከለች ያቆየቻቸው ቅርሶቿ በተዘረፉበት በአምስት ዓመቱ የፋሽስት ወረራ ወቅት ከሞሶሎኒ ጎን ተሰልፈው ምክር የሚሰጡ ካህናቷ በርካታ ኦርቶዶክሳውያን ካህናትን ማስፈጀታቸው ይታወቃል፡፡ ከዚሁ ነጥብ ጋር በተያያዘ አስተያየታቸውን የሰጡ አንድ የውይይቱ ተሳታፊ “ፋሽስታዊው መንግሥትና ቫቲካን ተባብረው በኢትዮጵያ ላይ ለፈጸሙት ግፍ ኢትዮጵያንና የኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያንን ይቅርታ ሊጠይቁ ይገባል፤” ብለዋል፡፡
የየካቲት 12 የሰማዕታት ቀን 75 ዓመት የአልማዝ ኢዮቤልዩ ዝግጅት በአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ መኰንን አዳራሽ በተከናወነበት ወቅት “ዓለም አቀፍ ኅብረት ለፍትሕ በኢትዮጵያ” (Global Alliance for Justice - Ethiopian Course)የተሰኘው ድርጅት መሥራች አቶ ኪዳኔ ዓለማየሁ ባቀረቡት ጽሑፍ የፋሽስት ኢጣልያ ግፍና በደል (Facist War Crimes) ፍትሕ እና ፍርድ እንዲሰጠው በተመሳሳይ ሁኔታ ጠይቀዋል፡፡ የፍትሕ ጥያቄው ይመለከተኛል የሚል ማንኛውም ሰው በድርጅቱ ድረ ገጽ www.Globalallianceforethiopia.gov ላይ በመግባት Sign petition የሚለውን በመጫን ፊርማቸውን እንዲያኖሩ (ድምፃቸውን እንዲለግሡ) ተማፅነዋል፡፡
ከምላሾች ይልቅ በርካታ ጥያቄዎች በተነሡበት በዚሁ የግማሽ ቀን የዐድዋ ድል በዓል አከባበር ውይይት ለማእከሉ ጥናት እና ምርምር ግብአት የሚሆኑ በርካታ ሐሳቦች መገኘታቸውን በማእከሉ ዳይሬክተር ተመልክቷል፡፡ በአንጻሩ በዐድዋ ዙሪያ የሚነሡ ዘመነኛ ሐቲቶችን ጨምሮ በሌሎችም የኢትዮጵያና የቤተ ክርስቲያን ጉዳዮች ላይ ሐሳባቸውን በመድረክ ላይ ለማቅረብ የሚፈቅዱ የሚደፍሩም ምሁራን ማነሳቸው ማእከሉን እንደሚያሳስበው ዳይሬክተሩ መናገራቸው ተዘግቧል፡፡ በውይይቱ ተሳታፊዎች በተደጋጋሚ የተነሣው የታሪክ ምሁራኑ ዝምታ ማኅበረ ቅዱሳን እንደ ተቋም የምርምር ማእከሉ በተለይ ለወጣቱ ታሪኩን፣ እሴቱንና ማንነቱን በሚገባ በማሳወቅና በማሳተፍ ረገድ አበክሮ መሥራት እንደሚገባው ተወትውቷል፡፡
በውይይቱ ላይ የማኅበረ ቅዱሳን የበገና ሠልጣኞች መዝሙር አቅርበዋል፡፡ በቅርስ ጥናትና ጥበቃ ባለሥልጣን የጥናትና ምርምር ዳይሬክቶሬት ከፍተኛ ተመራማሪው አቶ መንክር ቢተው ፍርንዱስ እና መደበኛ ጉባኤ ቃና ቅኔዎችን፣ ግስ ቅኔ እና የገጸ በረከት ቅኔዎችን አቅርበዋል፡፡ ለዛሬው በአቶ መንክር የግስ እና የገጸ በረከት ቅኔዎች እንሰናበታችኋለን፡፡

እለ ትነብሩ ተንሥኡ
ወእለ ታረምሙ አውስኡ
ምኒልክሃ በቃለ ስብሐት ጸውዑ፡፡

ስምኡ ዘንተ መልእክተ ጣዪቱ ንግሥተ ሸዋ
ወለብዉ ዘልፈ ግዕዛነ ዐድዋ
ምኒልክ ለኢትዮጵያ በደሙ ዘአሠርገዋ(2)፡፡

ቸር ወሬ ያሰማን፤
አሜን፡፡9 comments:

Anonymous said...

ሞሶሎኒና ቫቲካን ይቅርታ ይበሉን ከተባለ የይቅርታ ነገር ከተነሳ ማለቴ ነው መለስና አባ ፓውሌም የኢትዮጵያን ኦርቶዶክስ ቤተክርስቲያንና የኢትዮጵያን ህዝብ ይቅርታ መጠየቅ አለባቸው::

Anonymous said...

ሞሶሎኒና ቫቲካን ይቅርታ ይበሉን ከተባለ የይቅርታ ነገር ከተነሳ ማለቴ ነው መለስና አባ ፓውሌም የኢትዮጵያን ኦርቶዶክስ ቤተክርስቲያንና የኢትዮጵያን ህዝብ ይቅርታ መጠየቅ አለባቸው::

mam said...

Egziabher yibarkachihu. Ye mahberunm agelglot yibark.

Meseret worku said...

Hi!Deje selamawyan lyu ena tdgbi,mannetun resto berasu moralawi zktet lemidekmew wotat,mhur...yemankia dewol new bye amnalew.

Anonymous said...

Why do the fashist Vatican and Italians officially appologize for what they did to Ethiopians and Our church ? while Our church leader "the Beyonce guide" has already expressed his loyality to the vatican and has started discussion bilateral issues.

symon said...

ይህ ተሳትፎ አሌ የማይባል ነው በዚያ ጊዜ አባቶቻችን ፈጣሪያቸውን ለምነው ተማፅነው ተአምራዊ ድል ተቀናጅተው ለዚህ አበቁን።አሁን ግን "ጦርነት በፀሎት አይካሄድም "ተብለን ውጤቱ እስካሁን ዋጋ አስከፋይ ብቻ ሳይሆን የሚያመረቅዝም ሆኗል ።ቀጣዩም እጅግ አስፈሪ ነው ።ሰው በማያውቀው ቢያንስ ዝም ቢል ጥሩ ነበር ።

symon said...

አንድ ወዳጄ ጣሊያን ሮማ ኗሪ ነው ቫቲካን የበደለችውን ሐገራት ሁሉ ይቅርታ ስትጠይቅ ለምን ኢትዮጵያን ተወቻት ብዬ ብጠይቀው "ሰይጣን እየሱስ ክርስቶስን ይቅርታ ጠይቋል ወይ "ብሎ አስገራሚ መልስ ሰጠኝ ።

Anonymous said...

ዝክረ አድዋው መልካም ነው። ነገር ግን መሠረታዊውን እውነት አሳንሷል። የአድዋ ድል የኢትዮጵያውያን ጀግንነት ውጤት አይደለም፣ ቤተ ክርስቲያን አስተዋጽኦ አደረገች ማለት ቦታዋን ማሳነስ ነው። አድዋን ያሸነፈው እግዚአብሔር እራሱ ነው። ኢትዮጵያ ማለት እራሷ ቤተክርስቲያን ናት። የአድዋ ድል ብቻ ሳይሆን በሁለተኛው የአለም ጦርነት ኢትዮጵያ በጣሊያን ላይ በመጨረሻ የተቀዳጀችው ድል የእግዚአብሔር ድል ነው። የኢትዮጵያ ታሪክ የጦርነት ታሪክ ነው የሚሉት ኢትዮጵያን ለመውረር የዘመቱባት ጠላቶቿ ወይም የነሱ የህሊና ተማራኪዎች ናቸው። ቴናጋሪው በትትክል እንዳቀረቡት ኢትዮጵያ ሁልጊዜ የመከላከል፡ዉጊያ፡ነው፡የምታደርገው። አረቦች ክርስትናን፡ሊያጠፉ እስልምናን በጦርነት፡ይዘው መጡ እንጂ፡ኢትዮጵያ፡ወደነሱ፡ ጦርነትት ይዛ፡አልሄደችም።
በዚህ፡መንፈሳዊነት፡ባለው፡ውይይት፡ውስጥጽ ሉሲን፡ምን፡አመጣት? ይስብሰባው፡አነሳስ፡መልካም፡ሆኖ፡ሳለ ትንታኔዎቹ፡አሁንም፡የውጭ የህሊና ዘመቻ፡ሰለባዎች፡ሆነው፡አሁንም፡ይታይኛል።

Yeshiber kehawassa said...


Kesis Z taseru? betam yigermal? mnew ethiopia tebelashechi saa ? endete ewounetegna sew tefasaa? GETA yayal!! woladite amlak tmeleketalechi ayizoh yene geta.
mnale enezan kaliti yaklutn taramiwochi behonku!!! mngna yetadelu nachew kuchi bye emar neber... mnyadergale ...yih alem lEyesus kirstosm alhon ...
Zare brihane alem Kidus powolos dagmegna maremia bet worede bizu nefsochi biza egizeabhair liadnachew yefekdachew alu meselegni ....kisis gebulachw? Egziabhair yiyilachihu mn yibalal lenezih HODAMLAkOCHI.............

Blog Archive

የአቡነ ጳውሎስ "ሐውልተ ስምዕ"

ነጻ ፓትርያርክ ምርጫ ቢሆን ኖሮ ማንን ይመርጡ ነበር? እንበልና ሁሉም ነገር ሥርዓቱን ጠብቆ የተከናወነ የእጩዎች ምርጫ ቢሆን ኖሮ፣ አሁን የምናነሣቸው ጉድለቶች ባይኖሩ ኖሮ፣ 6ኛው ፓትርያርክ እንዲሆን የምትመርጡት ማንን ነበር? (ማሳሰቢያ፦ አሁን ያለው ክፍፍል እና የመንግሥት ተጽዕኖ ባይኖር ኖሮ ተብሎ የሚመለስ ጥያቄ ነው። የምን “ባይኖር ኖሮ ነው” የሚል አስተያየት ካለዎትም እናከብራለን።)