March 7, 2012

ሰበር ዜና - ፍ/ቤቱ በመ/ር ዘመድኩን ላይ ፈረደ


·         ፍ/ቤቱ የአምስት ወራት የእስራት ቅጣት ወስኗል::
·     “የተበደልኩበትን የፍትሕ ሥርዐት ጭምር እታገላለሁ፤” ያለው መ/ር ዘመድኩን ለውሳኔው የቅጣት አስተያየት ለመስጠት ፈቃደኛ አልሆነም::
·     መ/ር ዘመድኩን አስቀድሞ የተከሰሰበት አንቀጽ የቅጣት ውሳኔን በእስራት ወይም በገንዘብ ከሚሰጠው ንኡስ አንቀጽ 613(1) አጠቃሎ ወደሚሰጠው ንኡስ አንቀጽ 613(3) እንዲለወጥ ተደርጓል::
·        የፍ/ቤቱ የውሳኔ ሐተታ በበጋሻው ደሳለኝ “ሕገ መንግሥታዊ የእምነት ነጻነት መገደብ” ላይ አጽንዖት ሰጥቷል፤ ለተከሳሽ የሚረዱ ጠቃሚ ማስረጃዎችንና የምስክሮችን ቃል ግን አልተጠቀመባቸውም ተብሏል
·        “እኔ አርማጌዶን ቪሲዲን የሠራኹት በቤተ ክርስቲያኔ ላይ ያንዣበበው አደጋ ይገፈፍ ዘንድ የድርሻዬን ለመወጣት ነው፡፡ ሥራዬ አደጋውን በመግፈፍ የራሱን አስተዋፅኦ አድርጓል፡፡ ዛሬ ወደ እስር ስሄድ አባቶቼ ስለ ቤተ ክርስቲያን በተቀበሉት ፈተና ካገኙት ጸጋ በረከት እንደምሳተፍ አምናለኹ፡፡ በዚህም ደስ ይለኛል::(መ/ር ዘመድኩን በቀለ ከውሳኔው በኋላ) 
READ THIS ARTICLE IN PDF.
(ደጀ ሰላም፣ የካቲት 27/2004 ዓ.ም፤ March 6/2012/)፦ የፌዴራሉ የመጀመሪያ ደረጃ ፍ/ቤት አራዳ ምድብ ችሎት በአርማጌዶን ቪሲዲ ዐቓቤ ሕግ የስም ማጥፋት ወንጀል ክስ በመሠረተበት መ/ር ዘመድኩን በቀለ ላይ የአምስት ወራት የእስራት ቅጣት ወሰኗል፡፡ ፖሊስ በኤግዚቢት ስም ከመ/ር ዘመድኩን መኖሪያ ቤት እና መዝሙር ቤት የሰበሰባቸው 114 አርማጌዶን ቪሲዲች “ለቤተ ክርስቲያኒቱ ከፍተኛ የእምነት መሪዎች እንዲሰጥ” 340 አርማጌዶን ካሴቶች ደግሞ ምንም ዐይነት ማስረጃ ያልቀረበባቸው በመሆኑ ለባለቤቱ ተመላሽ እንዲሆን ፍ/ቤቱ አዝዟል፡፡
ከታኅሣሥ ሦስት ቀን 2004 ዓ.ም ጀምሮ በተለያዩ ጊዜ ቀጠሮዎች የግራ ቀኙን ሙግት ሲያዳምጥ የቆየው ፍ/ቤቱ ዛሬ፣ የካቲት 27 ቀን 2004 ዓ.ም፣ ከቀትር በኋላ ባሰማው የቅጣት ሐተታ ያሠመረባቸው የውሳኔ ሐሳቦች÷ በአርማጌዶን ቪሲዲ የተነሣ “የግል ተበዳይ” ተብዬው በጋሻው ደሳለኝ “ከምእመናን ልብ እንዲወጣ” መደረጉ፣ “ቪሲዲው የተሠራው ምእመናን የግል ተበዳይን ቀጥቅጠው እንዲገድሉት ነው” በሚል በጥራዝ ነጠቁ ታሪኩ አበራ የተሰጠው የቃል ምስክርነት፣ “ሕገ መንግሥቱ ለግል ተበዳይ በሰጠው የአምልኮ መብት የመረጠውን እምነት የማራመድ ነጻነቱ መገደቡ” የሚሉ ናቸው፡፡
ዐቃቤ ሕግ ለፍ/ቤቱ ባቀረበው የቅጣት አስተያየት ተከሳሽ መ/ር ዘመድኩን “በቁጥር ሦስት ቪሲዲ እንገናኝ በሚል በጀመረው ተግባሩ ከመቀጠል ወደኋላ ስለማይል የበለጠ ጉዳት ከማድረሱ በፊት” አንቀጹ የሚፈቅደው ከባድ ቅጣት እንዲወሰንበት ጠይቆ ነበር፡፡
አርማጌዶን ቪሲዲ በስም ማጥፋት ወንጀል እንደማያስጠይቀው ፍ/ቤቱም ጉዳዩን የመከታተል ሥልጣን እንዳልነበረው ሲያሳስብ የቆየው መ/ር ዘመድኩን በበኩሉ÷ ፈጽሞ ነጻ በመሆን አልያም ቅጣት ከመቀበል ውጭ ሌላ ውሳኔ ጠብቆ እንዳልመጣ በመግለጽ በጠበቃው በኩል መቅረብ የሚገባው የቅጣት አስተያየት እንዲሰጥ ፈቃደኛ አልሆነም፡፡
የተላለፈበት የቅጣት ውሳኔም በትእዛዝ እንጂ በትክክለኛ የፍትሕ አሰጣጥ ሥነ ሥርዐት ላይ ተመሥርቷል ብሎ እንደማያምን፤ በዚህም የተበደለበትን የፍትሕ ሥርዐት ጭምር ይግባኝ በመጠየቅ እንደሚታገለው፤ በአርማጌዶን ቪሲዲ ለሕዝብ እና ለቤተ ክርስቲያን ያስተላለፈው መልእክት ተቀባይነት አግኝቶ ‹የግል ተበዳይ› የትም እንዳያስተምር በመደረጉ ቪሲዲው የተሠራበትን ዓላማ ማሳካቱን፣ ይህም ስሕተት የኾነው በፍ/ቤቱ ዐይን እንጂ ለቤተ ክርስቲያን ግን ትክክለኛ መሆኑን፣ ስለዚህም በጀመረው ተግባሩ እንደሚቀጥል በማረጋገጥ በዚህ ችሎት የሚሰጠውን ውሳኔ ከመቀበል በቀር የሚጠይቀው የቅጣት ይቀነስ አስተያየት እንደሌለ ለችሎቱ ተናግሯል፡፡ መ/ር ዘመድኩን ይህን ሐሳቡን እንዲቀይር በዳኛ ሙሉ ክንፈ በተደጋጋሚ ቢጠየቅም ፈቃደኛ አልኾነም፡፡ “እኔም ትዳርና ልጆች አሉኝ፤ ውሳኔው አያስበረግገኝም” ብሏል ለችሎቱ፡፡
የችሎቱ ምንጮች እንደተናገሩት÷ ፍ/ቤቱ በቅጣት ሐተታው አጽንዖት ከሰጠባቸው ሐሳቦች አንዱ የሆነው አርማጌዶን ቪሲዲ “ምእመኑ የግል ተበዳይን ቀጥቅጦ እንዲገድለው ለመቀስቀስ የተሠራ መሆኑንና ይህንንም ተከሳሽ ጥቅምት 11 ቀን 2004 ዓ.ም ለማስፈጸም በወቅቱ የተቃውሞ ሰልፍ ተደርጎበት በነበረው ቅድስት ማርያም ቤተ ክርስቲያን በአካል ተገኝቶ ለወጣቶች ገንዘብ ሲሰጥ እንደነበር” በዐቃቤ ሕግ ምስክሮች ታሪኩ አበራና ሌላ ግለሰብ የተሰጠውን ምስክርነት በበቂ ሊያስተባብል የሚችለው የሰነድ ማስረጃ አልታየም፤ የሰነድ ማስረጃው መ/ር ዘመድኩን በተጠቀሰው ዕለት በተባለው ስፍራ እንዳልነበር የሚያረጋግጥ ነው፡፡ በሌላ በኩል ፓትርያሪኩ ሐምሌ 25 ቀን 2003 ዓ.ም የተጻፈው ደብዳቤና በቤተ ክርስቲያን የስሕተት ትምህርቶችን አስመልክቶ ያለው የውሳኔ አሰጣጥ ከአርማጌዶን ቪሲዲ ጋራ በማነጻጸር የተሰጡ አሳማኝ የመከላከያ ምስክሮች ቃል በቅጣት ውሳኔው ሐተታ ውስጥ በቂ ማገናዘብ አልተደረገባቸውም፡፡
ከዚህም ባሻገር ዐቃቤ ሕግ ለመ/ር ዘመድኩን ሰጥቶት በነበረው የክስ ጽሕፈት ላይ እንደተመለከተው ክሱ የተመሠረተበት የወንጀለኛ መቅጫ ሕግ አንቀጽ 613 ንኡስ አንቀጽ (1) በተጠቀሰው “የስም ማጥፋት ወንጀል” ድርጊት ከስድስት ወር ባልበለጠ እስራት ወይም በገንዘብ እንዲቀጣ አማራጭ ድንጋጌዎችን የሚያስቀምጥ ነው፡፡ ዛሬ ዳኛ ሙሉ ክንፈ ባነበቡት የቅጣት ሐተታ ውስጥ ግን የመ/ር ዘመድኩን የክስ አንቀጽ ከሦስት ወራት ባላነሰ እስራትና በገንዘብም በድምር ወደሚያስቀጣው ንኡስ አንቀጽ 613(3) እንዲቀየር ተደርጓል፤ ዐቓቤ ሕግ ባቀረበው የቅጣት ማክበጃ አስተያየት ይሆን?
የሆነው ይሁን ባለፈው ቀጠሮ የመ/ር ዘመድኩን ጠበቃ በወንጀል ሕጉ አንቀጽ 614 ንኡስ አንቀጽ (1) እና (2) መሠረት አርማጌዶን ቪሲዲ የሕዝብን ከፍ ያሉ ሃይማኖታዊና ሞራላዊ ጥቅሞች (higher interest and moral aim) ለመከላከል መረጃ የተሰጠበት እንጂ የማንንም ስም ሆነ ተብሎ ለማጥፋት ብያኔ/ውሳኔ ያልተላለፈበት እንደሆነ አስረድተው ነበር፤ የመከላከያ ምስክሮችም ይህንኑ የሚያስረግጥ ማብራሪያ ሰጥተው ነበር፡፡
ማለፊያ! አንዳችም መረበሽ የማይታይበት መ/ር ዘመድኩን በቀለ ከውሳኔው በኋላ ለችሎቱ ተመልካቾች ተናግሯል፤ እንዲህም ብሏል፡- “እኔ አርማጌዶን ቪሲዲን የሠራኹት በቤተ ክርስቲያኔ ላይ ያንዣበበው አደጋ ይገፈፍ ዘንድ የድርሻዬን ለመወጣት ነው፡፡ ሥራዬ አደጋውን በመግፈፍ የራሱን አስተዋፅኦ አድርጓል፡፡ ዛሬ ወደ እስር ስሄድ አባቶቼ ስለ ቤተ ክርስቲያን በተቀበሉት ፈተና ካገኙት ጸጋ በረከት እንደምሳተፍ አምናለኹ፡፡ በዚህም ደስ ይለኛል፡፡ ሁሉም ሓላፊነቱን ይወጣ!!”፡፡
ይህ ዜና በሚጠናቀርበት ሰዓት መ/ር ዘመድኩን በዚያው በአራዳ ምድብ ችሎት የእስረኞች ማቆያ ውስጥ የነበረ ሲሆን ወደ ቃሊቲ ማረሚያ ቤት እንደሚዛወር ተዘግቧል፡፡
የመምህር ዘመድኩን እስር በኦርቶዶክሳውያን ልቡናና መድረክ ስፍራ ባጡት በሕገ ወጦች በጋሻው ደሳለኝና መሰሎቹ ላይ በየስፍራው ተፈጻሚ የሆነውን የመከላከል ርምጃ ያጠናክረው እንደሆን እንጂ አያላላውም!!
ቅዱሳን መላእክትን በአርያም፣ የወንጌል ገበሬዎቹን ሐዋርያትን በአጽናፈ ዓለም፣ ደጋጎቹን መነኮሳት በገዳም፣ ቆራጦቹን ሰማዕታት በደም ያጸና የአባቶቻችን አምላክ እግዚአብሔር ወንድማችን መ/ር ዘመድኩን በቀለን በመከራው ሁሉ እንዲያበረታው እንለምናለን፤ ሁላችንም በጸሎታችን እንድናስበውም ደጀ ሰላም ጥሪዋን ታስተላልፋለች፡፡

Post a Comment

Blog Archive

የአቡነ ጳውሎስ "ሐውልተ ስምዕ"

ነጻ ፓትርያርክ ምርጫ ቢሆን ኖሮ ማንን ይመርጡ ነበር? እንበልና ሁሉም ነገር ሥርዓቱን ጠብቆ የተከናወነ የእጩዎች ምርጫ ቢሆን ኖሮ፣ አሁን የምናነሣቸው ጉድለቶች ባይኖሩ ኖሮ፣ 6ኛው ፓትርያርክ እንዲሆን የምትመርጡት ማንን ነበር? (ማሳሰቢያ፦ አሁን ያለው ክፍፍል እና የመንግሥት ተጽዕኖ ባይኖር ኖሮ ተብሎ የሚመለስ ጥያቄ ነው። የምን “ባይኖር ኖሮ ነው” የሚል አስተያየት ካለዎትም እናከብራለን።)