March 13, 2012

የአሰቦት ገዳም ደን በ15 ቀናት ውስጥ ለሦስተኛ ጊዜ እየተቃጠለ ነው


·         እሳቱ ከአባ ሳሙኤል ገዳም 100 ሜትር ያህል ድረስ ተቃርቧል፤ የማኅበረ መነኰሳቱ የድረሱልን ጥሪ ቀጥሏል::
·         ኢሳዎቹ እሳቱን ለማጥፋት የመጣውን ሕዝብ በተኩስ ለማከላከል ሞክረዋል
·         የቃጠሎው መደጋገም በኢኮኖሚያዊ ጥቅም ያልተወሰነ የአክራሪዎች ሤራም ሊሆን እንደሚችል በሜኢሶ ወረዳ የሚታየው የጽንፈኞች ትንኮሳ ምልክት እየሰጠ ነው
·         በአሰቦት አቅራቢያ የሚገኝን ተራራ ለማልማት አንድ ሚልዮን ብር በጀት ተመድቧል

 (ደጀ ሰላም፣ መጋቢት 3/2004 ዓ.ም፤ ማርች  12/2012 READ IN PDF)፦ የካቲት 20 ቀን 2004 ዓ.ም ረፋድ፤ የአሰቦት ደብረ ወገግ ቅድስት ሥላሴ እና አቡነ ሳሙኤል ገዳም በወተት ምርትና ማድለብ ፕሮጀክት የሚተዳደርባቸውን ከ70 የማይበልጡ ከብቶች ለመዝረፍ ወደ ገዳሙ ክልል የገቡ የኢሳ ጎሳ አባላት ለመከላከል የተደረገውን ጥረት ተከትሎ በቅድስት ሥላሴ ቤተ ክርስቲያን አቅጣጫ በሚገኘው የገዳሙ ደን ላይ እሳት ተለኰሰበት፡፡ ለወትሮው በየወቅቱ በሚቀያየሩና ከማኅበረ መነኮሳቱ በተውጣጡ አራት፣ አራት መነኰሳት ዘብነት ከሚጠበቀው ገዳም ከብቶች ቢዘረፉ እንኳ እንደተለመደው በአካባቢ ሽምግልና እንዲመለሱ ይደረግ ነበር ምላሹ ሰደድ እሳት መልቀቅ ይሆናል ብሎ የጠበቀ አልነበረም፡፡

የካቲት 20 ቀን ረፋድ ላይ የተቀሰቀሰው እሳት የገዳሙ መነኰሳት፣ ከአቅራቢያውና ከአካባቢው የወረዳ ከተሞች በመጡ ምእመናን እንዲሁም በኦሮሚያ ፖሊስ ርብርብ ከሦስት ቀናት በኋላ የካቲት 22 ቀን ማምሻውን ለመግታት ተቻለ፡፡ ይሁንና “በቁጥጥር ሥር ውሏል” የተባለው እሳት ዐርብ፣ የካቲት 23 ቀን ማምሻውን በጻድቁ አቡነ ሳሙኤል ቤተ ክርስቲያን አቅጣጫ በሚገኘው ደን በኩል ዳግመኛ ተቀስቅሶ የነበረ ቢሆንም በማግሥቱ ቅዳሜ፣ የካቲት 24 ቀን ማምሻውን በቁጥጥር ሥር እንደዋለ ተነገረ፡፡ ይህን ጊዜ እንደ መንሥኤ የተጠቀሰው “በቀደመው ቃጠሎ ተዳፍኖ የቀረ ረመጥ በነፋሱ ምክንያት በመቀጣጠሉ ነው” የሚል ነበርና በቀጣዩ ቀን እሑድም የማጥፋቱ ሥራ ተጠናክሮ ቀጥሎ እንደ ነበር የዐይን እማኞች ገልጸዋል፡፡
ከመጋቢት ወር 2001 ዓ.ም ወዲህ በአንድ ሳምንት ለሁለተኛ ጊዜ የተቀሰቀሰውን ይህን ቃጠሎ በማጥፋቱ ሂደት የታየው አሳሳቢ ነገር የድርጊቱ ፈጻሚዎች ከኦሮሚያ ፖሊስ አቅም በላይ መሆናቸውን ያሳየ ነበር፡፡ ይኸውም ቃጠሎውን ለመከላከል በቻሉት ዕቃ ውኃ ሞልተው ከሜኢሶ እስከ አሰቦት ያለውን 17 ኪ.ሜ፣ አቋርጠው ከጻድቁ አቡነ ሳሙኤል ቤተ ክርስቲያን በስተምሥራቅ አቅጣጫ በሚታየው ተራራ ደን ውስጥ የሚነደውን ነበልባለ እሳት ለማጥፋት አቀበቱን በሚወጡ ምእመናን ላይ ተኩስ መከፈቱ ነው፡፡ ጾታ ሳይለይ ጫንቃቸው መሸከም የቻለውን ውኃ ተሸክመው ተራራውን በሚወጡት ምእመናን ላይ ኢሳዎቹ የከፈቱትን የማከላከል ተኩስ ለማስቆም የተቻለው ከጭሮ (አሰበ ተፈሪ) በመጣው የፌዴራል ፖሊስ አባሎች በተሰጠው አጠፌታ እንደ ሆነ ተዘግቧል፡፡
በዚህ ወቅት የምዕራብ ሐረርጌ ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ ብፁዕ አቡነ ዳንኤል፣ ከጠቅላይ ቤተ ክህነት የካህናት አስተዳደር መምሪያ ሓላፊ መጋቤ ካህናት ኀይለ ሥላሴ ዘማርያም እና የሕዝብ ግንኙነት መምሪያ ምክትል ሓላፊ ሊቀ ኅሩያን ዳዊት ታደሰ በአካባቢው እንደነበሩ የተገለጸ ቢሆንም ቀድሞም ቢሆን በወረዳው መስተዳድርና ፖሊስ ሊፈታ ያልቻለውን ችግር መፍትሔ ሊያበጅሉት እንዳልቻሉ የሚያረጋግጠው ቃጠሎ ለሦስተኛ ጊዜ እንዳይደገምና እንዳይነሣ ከማድረግ አላገዱትም፡፡
ንት መጋቢት ሁለት ቀን 2004 ዓ.ም አሁንም ታላቁ የገዳሙ ደን ይዞታ በሚገኝበት የጻድቁ አቡነ ሳሙኤል ቤተ ክርስቲያን አቅጣጫ ቃጠሎው አገርሽቷል፡፡ ከቀኑ ዐሥር ሰዓት ላይ የተቀሰቀሰው ቃጠሎው ይህ ዜና እስከተጠናቀረበት ሰዓት ድረስ በቁጥጥር ሥር ለማዋል ባለመቻሉ ከፍተኛ የብዝኀ ሕይወት ሀብት ያለውና ለመናንያኑና መነኰሳቱ የጸሎትና መንፈሳዊ ተጋድሎ መካን የሆነውን ደን እያጠፋ ወደ አባ ሳሙኤል ገዳም 100 ሜትር ያህል ርቀት መቅረቡ ተነግሯል፡፡ የወረዳውን ባለሥልጣናት ለማግኘት እየተደረጉ ያሉ ሙከራዎች ስልካቸው በመጥፋቱና በቢሮ የሉም በመባሉ የማኅበረ መነኰሳቱ የድረሱልን ጥሪ በሀገረ ስብከት እና ወረዳ ቤተ ክህነት ጽ/ቤቶች እንዲሁም ለፖሊስ ብቻ አቤቱታቸውን ለማቅረብ ተገደዋል፡፡
የአካባቢው አስተዳደር ለችግሩ ያለውን አያያዝ ምፀታዊ የሚያደርገው በአሰቦት አቅራቢያ የሚገኝን አንድ ተራራ ለማልማት እስከ አንድ ሚልዮን ብር በጀት በመመደብ የጉድጓድ ቁፋሮ እያደረገ ባለበት ሁኔታ ጥብቅ/ነዋሪ ሆኖ የቆየው የአሰቦት ገዳም በተደጋጋሚ ሰው ሠራሽ ቃጠሎ እንዲጋይ የተፈረደበት መሆኑ ነው፡፡
በየምሽቱ ሦስትና አራት ሰዓት ገደማ ወደ ገዳሙ ክልል የሚገቡ ግለሰቦች (ጠራቢዎቹ) በአንድ በኩል ጨለማውን ለማራቅ በሌላ በኩል የመጡበትን የጭፍጨፋ ተግባር ጨርሰው እስኪወጡ ድረስ ቅዝቃዜውን ለማራቅ እሳት እንደሚያቀጣጥሉ ተገልጧል፡፡ እሳቱን ማጥፋታቸው ግድ አይሰጣቸውም፡፡ የቆረጡትን ግንድ ወደ ከተማ ወስደው ሠንጥቀው፣ ጠርበው ለተለያዩ አገልግሎት የሚውሉ ጣውላዎችን ያዘጋጁባቸዋል፡፡ ደኑ ከተቃጠለ በኋላ በሚቀረው ባድማ መሬት ላይ በሚበቅለው ሣር ላይም ከብቶቻቸውን ያሰማሩበታል፡፡ ይህ ሁሉ ሲሆን ከሕገ ወጦቹ መካከል በአግባቡ ተጠይቀው ርምጃ ሲወሰድባቸው እንደማይታይ ነው የአባቢው ነዋሪዎች የሚናገሩት፡፡
“የጉዳዩ መነሻ ከዚህም ያለፈ ነው” የሚሉ ሌሎች አስተያየት ሰጪዎች በበኩላቸው፣ ከአሰቦት ከተማ 17 ኪ.ሜ ላይ በሚገኘው ሜኤሶ ወረዳ ክርስትናን የሚያጥላሉ ንግግሮች ከመስጊድ ማድመጥ አዘቦታዊ ተግባር መሆኑን በመግለጽ÷ እኒህ ‹ስብከቶች› በቪሲዲ ኅትመቶች ወደ አሰቦት ወረዳ መሠራጨታቸውን የፈጠረው የአክራሪነት ዝንባሌ በገዳሙ ላይ ለሚፈጸመው ተደጋጋሚ የጥፋት ተግባር የፈጠረውን የጠርዘኝነት አእምሯዊ ሁኔታ በመንሥኤነት ይጠቅሳሉ፡፡ የሀገረ ስብከቱ ጽ/ቤት ሁኔታውን ከዞንና የወረዳ አስተዳደር ጋራ በመነጋገር ለማርገብ ጥረት ማድረጉ የተነገረ ቢሆንም በየጊዜው ከፓኪስታን ሠልጥነው ይመጣሉ በሚባሉ ቡድኖች/ግለሰቦች ምክንያት ችግሩ ከጊዜ ወደ ጊዜ በመባባስ ላይ መሆኑ ተዘግቧል፡፡
በ13ው መ/ክ/ዘ በቀናው የአሰቦት ደብረ ወገግ ቅድስት ሥላሴ እና አቡነ ሳሙኤል ገዳም መናንያን ባሕታውያንን፣ ወንዶች መነኰሳትንና ሴቶች መነኰሳዪትን ጨምሮ 170 የገዳሙ ማኅበር አባላት ይገኛሉ፡፡ ብዙዎቹ በዕድሜ የገፉ፣ በትኅርምት የሚኖሩ ናቸው፡፡
ከቃጠሎ አደጋው ባሻገር ከይዞታ በተያያዘ ከአንድ ግለሰብ ጋራ የፍ/ቤት ሙግት ላይ የሚገኘው ገዳሙ፣ በየጊዜው በሚያጋጥመው የገቢ አቅም መዋዠቅ ምክንያት እየተቋረጠ (በችግር ጊዜ መምህራን ወደ ከተማ እየተሰደዱ በደኅናው ጊዜ ስለሚመለሱ) የሚቀጥል የጉባኤ ትምህርት ይሰጥበታል፡፡ የገዳሙ ዋነኛ የመተዳደሪያ መንገዶች ከወተት ምርት እና ከብት ማድለብ፣ በገዳሙ አቅራቢያ ከሚካሄደው የማር ምርት እንዲሁም በከተማው በማኅበረ ቅዱሳን ከተተከለው የእህል ወፍጮ አገልግሎት በሚገኘው ገቢ መሆኑ ተመልክቷል፡፡

ቸር ወሬ ያሰማን፤
አሜን፡፡Post a Comment

Blog Archive

የአቡነ ጳውሎስ "ሐውልተ ስምዕ"

ነጻ ፓትርያርክ ምርጫ ቢሆን ኖሮ ማንን ይመርጡ ነበር? እንበልና ሁሉም ነገር ሥርዓቱን ጠብቆ የተከናወነ የእጩዎች ምርጫ ቢሆን ኖሮ፣ አሁን የምናነሣቸው ጉድለቶች ባይኖሩ ኖሮ፣ 6ኛው ፓትርያርክ እንዲሆን የምትመርጡት ማንን ነበር? (ማሳሰቢያ፦ አሁን ያለው ክፍፍል እና የመንግሥት ተጽዕኖ ባይኖር ኖሮ ተብሎ የሚመለስ ጥያቄ ነው። የምን “ባይኖር ኖሮ ነው” የሚል አስተያየት ካለዎትም እናከብራለን።)