February 16, 2012

በጎንደር ከተማ ሁለት የአብነት ት/ቤቶች ሙሉ በሙሉ ተቃጠሉ


  • አንዱ ቤተ ጉባኤ በኢትዮጵያ ብቸኛው የመጻሕፍተ መነኮሳት ትርጓሜ ማኼጃ ነበር ተብሏል:: (READ THIS ARTICLE IN PDF)

(ደጀ ሰላ የካቲት 8/2004 ዓ.ም፤ ፌብሩዋሪ 16/2012)፦ በሰሜን ጎንደር ሀ/ስብከት ጎንደር ከተማ በሳምንት ልዩነት በሁለት አጥቢያ አብያተ ክርስቲያን በተነሡ የእሳት ቃጠሎ አደጋዎች አንድ ጥንታዊ የመጻሕፍት ትርጓሜ ቤት ሌላ የቅኔ ቤተ ጉባኤ ሙሉ በሙሉ ወደሙ፡፡ በጎንደር ከተማ የሚገኘው የሐመረ ኖኅ ሠለስቱ ምእት መጻሕፍተ መነኮሳት ትርጓሜ ት/ቤት ሙሉ በሙሉ የወደመው ከትላንት በስቲያ፣ ከየካቲት 6 ቀን 2004 ዓ.ም ከቀኑ 11፡30 ላይ መንሥኤው ባልታወቀ አኳኋን በተነሣ የእሳት ቃጠሎ መሆኑን ደቀ መዛሙርቱ ተናግረዋል፡፡ የትርጓሜ ት/ቤቱ በኢትዮጵያ ከአራቱ ጉባኤያት አንዱ የሆነውን መጻሕፍተ መነኮሳትን ብቻ የሚያሄድ ብቸኛ ቤተ ጉባኤ እንደነበር ተገልጧል፡፡

‹‹እሳት አላያያዝንም፤ ከኤሌክትሪክ መስመር ጋራ የተገናኘ ችግርም አላየንም፤›› ያሉት ደቀ መዛሙርቱ በእሳት ቃጠሎው የተማሪዎች ማደሪያዎች እና የመምህሩ መኖሪያ የነበሩ በአጠቃላይ ዘጠኝ ክፍሎች በውስጣቸው ከሚገኙ በ1714 ዓ.ም ከተጻፉ የብራና መጻሕፍተ መነኮሳት(ማር ይሥሓቅ፣ ፊልክስዩስ፣ አረጋዊ መንፈሳዊ) እና ሌሎች የኅትመት መጻሕፍት ጋራ ጨርሶ መቃጠላቸውን አስረድተዋል፡፡ እሳቱን ለማጥፋት የኢትዮጵያ አየር መንገድ የእሳት አደጋ መከላከል መኪኖች እና የከተማው ምእመናን የተረባረቡ ቢሆንም ጉዳቱን ለመቆጣጠር የተቻለው ወደ ሌሎች አካባቢዎች እንዳይዛመት በማድረግ ብቻ ነበር፡፡
የመጻሕፍተ መነኮሳት ቤተ ጉባኤው በጠቅላይ ቤተ ክህነት እና በማኅበረ ቅዱሳን በጀት የተተከለላቸው በአጠቃላይ 15 መደበኛ ደቀ መዛሙርት እና ከከተማው አድባራት እየመጡ ትምህርቱን በግላቸው የሚከታተሉ በርካታ ተማሪዎች እንደነበሩት ደቀ መዛሙርቱ ጨምረው ገልጸዋል፡፡
የአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ የክብር ዶክትሬት ዲግሪ በሰጣቸው በታወቁት የአራቱ ጉባኤያት ሊቁ አየለ ዓለሙ በ1929 ዓ.ም የተመሠረተው ት/ቤቱ በአሁኑ ጊዜ ጉባኤው ማሄድ (መቀጠል) ያልቻለ ሲሆን መምህሩ ተሾመ ታደሰ እና ደቀ መዛሙርቱ በየምእመናኑ ቤት ተጠግተው እንደሚገኙ ተመልክቷል፡፡ ቤተ ጉባኤው የሚገኝበትና በ325 ዓ.ም ለአውግዞተ አርዮስ በኒቂያ በተሰበሰቡ 318ቱ ርቱዓነ አበው ሊቃውንት ስም የተሠራው - የሠለስቱ ምእት ቤተ ክርስቲያን በ1880 እና በ1881 ዓ.ም በወራሪው ድርቡሽ ጦር ለሁለት ተከታታይ ጊዜ ከተቃጠለ በኋላ ተመልሶ አልተሠራም፡፡
የጎንደር ከተማ አድባራት በአራቱ ጉባኤያት ማእከልነት የሚታወቁ ሲሆኑ በመንበረ መንግሥት መድኃኔዓለም የመጻሕፍት ሊቃውንት ትርጓሜ፣ በመካነ ነገሥት ግምጃ ቤት ማርያም የመጻሕፍተ ሐዲሳት ትርጓሜ፣ በጻድቁ አቡነ ዐቢየ እግዚእ ቤተ ክርስቲያን የመጻሕፍተ ብሉያት ትርጓሜ፣ በተቃጠለው የሐመረ ኖኅ ሠለስቱ ምእት ቤተ ክርስቲያን ደግሞ የመጻሕፍተ መነኮሳት ትርጓሜ በመሰጠት ላይ ይገኛል፡፡
በተያያዘ ዜና በዚያው በጎንደር ከተማ የደብረ ብርሃን ሥላሴ ቤተ ክርስቲያን የሚገኘውና በዐፄ አድያም ሰገድ ኢያሱ ዘመነ መንግሥት(17ው መ.ክ.ዘ) በኖሩት የቅኔ ሊቅ መምህር ክፍለ ዮሐንስ የተመሠረተው የገለአድ የቅኔ ቤተ ጉባኤ የካቲት ሁለት ቀን 2004 ዓ.ም በደረሰበት የእሳት ቃጠሎ ሙሉ በሙሉ መውደሙ ተገልጾአል፡፡
በዕለቱ ከቀትር በኋላ ከተማሪዎች ጎጆ የተቀሰቀሰው የእሳት ቃጠሎው መንሥኤ ለጊዜው ያልታወቀ ቢሆንም ተማሪዎች ወደ መኖሪያ ቤታቸው የገባውን ጉንዳን ለማራቅ የተጠቀሙበት እሳት እንደሆነ ተገምቷል፡፡ በቃጠሎው 26 የቅኔ ደቀ መዛሙርቱ መኖሪያዎች የሆኑ ጎጆ ቤቶች በውስጣቸው ከሚገኙ የተማሪዎቹ አልባሳት፣ መጻሕፍት እና ጥሬ ብሮች ጋ መውደማቸውን የዜናው ምንጮች ተናግረዋል፡፡

 

ቸር ወሬ ያሰማን

አሜን

Post a Comment

Blog Archive

የአቡነ ጳውሎስ "ሐውልተ ስምዕ"

ነጻ ፓትርያርክ ምርጫ ቢሆን ኖሮ ማንን ይመርጡ ነበር? እንበልና ሁሉም ነገር ሥርዓቱን ጠብቆ የተከናወነ የእጩዎች ምርጫ ቢሆን ኖሮ፣ አሁን የምናነሣቸው ጉድለቶች ባይኖሩ ኖሮ፣ 6ኛው ፓትርያርክ እንዲሆን የምትመርጡት ማንን ነበር? (ማሳሰቢያ፦ አሁን ያለው ክፍፍል እና የመንግሥት ተጽዕኖ ባይኖር ኖሮ ተብሎ የሚመለስ ጥያቄ ነው። የምን “ባይኖር ኖሮ ነው” የሚል አስተያየት ካለዎትም እናከብራለን።)