February 9, 2012

የዋሺንግተን ዲሲና አካባቢው ሀ/ስብከት የብፁዕ አቡነ ፋኑኤልን እንቅስቃሴ አስመልክቶ መግለጫ አወጣ


·         የመግለጫውን ሙሉ ቃል ይዘናል። 
(ደጀ ሰላም፤ ጥር 30/2004 ዓ.ም፤ ፌብሩዋሪ 8/2012/ READ THIS ARTICLE IN PDF)፦ የዋሺንግተን ዲሲና አካባቢው ሀ/ስብከት አስቸኳይ አጠቃላይ ጉባዔውን በኖርዝ ካሮላይና ሻርለት ባካሔደ ማግስት ሀ/ስብከቱ ባለበት አጠቃላይ ሁኔታ ዙሪያ መግለጫ አውጥቷል። መግለጫው እንደሚያትተው “የዋሽንግተን ዲሲና አካባቢው ሀገረ ስብከት ሥራ አስፈጻሚ ጉባኤ ይህንን መግለጫ ለመስጠት ያነሳሳው ዋና ምክንያት በቅርቡ ጥር 12 ቀን 2004 ዓ.ም ብፁዕ አቡነ ፋኑኤል ከአሜሪካ ድምጽ የአማርኛ አገልግሎት ጋር ባደረጉት ቃለ መጠይቅ ሕዝበ ክርስቲያኑን የሚያንጽ በአባትነት ደረጃ አስተማሪ የሆነ ነገር መናገር ሲጠበቅባቸው ሕዝበ ክርስቲያኑን እና አብያተ ክርስቲያኑትን ያሳዘነ ሀሳብ ሰጥተዋል። በሰጡትም ቃለ መጠይቅ ላይ የዋሽንግተን ዲሲና አካባቢው ሀገረ ስብከት እንደሌለ፤ በሀገረ ስብከቱ መዋቅር ሥር  ያሉ አብያተ ክርስቲያናት ቃለ ዐዋዲ ጠብቀው እንደማይንቀሳቀሱ በመናገር የቤተ ክርስቲያንን የበላይነት ጥያቄ ውስጥ የሚያስገባ እና  ሕዝበ ክርስቲያኑንም ወደ አልተፈለገ አለመግባባት የሚመራ ገለጻ መሆኑን በሀገረ ስብከቱ ሥር የሚገኙ አብያተ ክርስቲያናት ተገንዝበዋል” ብሏል።

አክሎም “የተሰጠው መግለጫ የሀገረ ስብከትን መዋቅር ለማጠናከር፤ የቤተ ክርስቲያን ሥርዓት ለመጠበቅና ለማስጠበቅ ከፍተኛ መስዋዕትነት የከፈሉትን ካህናት፣ ምእመናንና የሰንበት ት/ቤት ወጣቶች ያሳዘነና የአባትና የልጅ ግንኙነትን የበለጠ የሚያሻክር፤ ከዚህ ቀደም ሀገረ ስብከቱን ለማጠናከር የደከሙ ብፁዓን አባቶች ድካም በዝቅተኛ ግምት እንዲታይ የሚያደርግ እንደሆነ ጠቁሞ “የዋሽንግተን ዲሲና አካባቢው ሀገረ ስብከት በቅዱስ ሲኖዶስ ፈቃድ የተመሰረተና እስካሁንም  ቅዱስ ሲኖዶስ  የመደባቸው ሊቃነ ጳጳሳት  አገልግሎት ሲያከናውኑ የቆዩበትና  አሁንም መንፈሳዊ ኃላፊነቱን በመፈጸም ላይ የሚገኝ” መሆኑን አረጋግጧል
ሀገረ ስብከቱ የቤተ ክርስቲያኒቱን ቃለ ዐዋዲ መሠረት ባደረገ መልኩ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያንን ሕጋዊ ውክልና ያለው፤ በየትኛውም ደረጃ የቤተ ክርስቲያንን መብት በማስከበር ደረጃ ሙሉ ሕጋዊ ሰውነት ያለው ነው። በሥሩ ለሚገኙ አብያተ ክርስቲያናት ለሚፈጠርባቸው ቸግር እና ለሚፈልጉት ማንኛውም ድጋፍ ከሦስተኛ አካል ጋር በሙሉ ውክልና መነጋገር የሚችል ነው። ይህ ሀገረ ስብከት የራሱ የሆነ ጽ/ቤትና መንበረ ጵጵስና ያለው ነው።  የሀገረ ስብከቱን አጠቃላይ እንቅስቃሴ የሚመራ የሀገረ ስብከቱ መንፈሳዊ አስተዳደር ጉባኤ ያለውና  በሀገረ ስብከቱም ጽ/ቤት ሥር የተለያዩ ክፍሎች ተቋቁመው ዘርፈ ብዙ አግልግሎት በማከናወን ላይ የሚገኝ ነው። ሀገረ ስብከቱ ቋሚ አድራሻ ያለው ሕጋዊ የሆነ እንቅስቃሴውን የሚያሳውቅበት ድረ ገጽ ያለውና  በተሰጠው የሀገረ ስብከት ክልል ውስጥ መንፈሳዊ እንቅስቃሴ በማድረግ ላይ የሚገኝ ነው” ሲል ሕጋዊነቱን አጽንዖት ሰጥቶ አስረድቷል። 
መግለጫው በብፁዕ አቡነ አብርሃም ስለተፈጸመው የሀገረ ስብከት መንበረ ጵጵስና ግዥ ሲያብራራም ዝርዝር ማስረጃው ለቅዱስ ሲኖዶስ እንደቀረበ ጠቅሶ አንዳንዶች ለመናገር እንደሚፈልጉት በድብቅ የተፈጸመ ነገር የለውም ብሏልከዚህ በፊት የሰላም ልዑካን በመሆን ወደ አሜሪካ መጥተው የነበሩ የቅዱስ ሲኖዶስ አባላትና ሊቃውንተ ቤተ ክርስቲያን በዚሁ በተገዛው መንበረ ጵጵስና ተገኝተው አድናቆታቸውን የገለጹበት የሀገረ ስብከቱ ሊቀ ጳጳስ የነበሩት  ብፁዕ አቡነ አብርሃምም በወቅቱ በግልጽ ለቅዱስ ሲኖዶስ አባላት ያስረዱ በመሆኑ ጉዳዩ ለቅዱስ ሲኖዶስ አባላት ዘንድ የታወቀ መሆኑን ያመለክታል። ከሁሉ በላይ የሚደንቀው ደግሞ ሀገረ ስብከቱ መኖሩን አላውቅም ያሉን ብፁዕ አቡነ ፋኑኤል ቢናገሩም ከዚህ በፊት ብፁዕ አቡነ አብርሃም ባደረጉላቸው ጥሪ መሠረት ብፁዕ አቡነ ፋኑኤል የሀገረ ስብከቱን ጽ/ቤትና መንበረ ጵጵስና የጎበኙና በምሥራቀ ጸሐይ ቅዱስ ተክለ ሃይማኖት ቤተ ክርስቲያን ተገኝተው ጸሎተ ኪዳን አድርሰው መሄዳቸው ዘንግተውት አላውቀውም ማለታቸው ሌሎች ጉዳዮችንም ወደፊት እያነሣን ልናስታውሳቸው እንደሚገባን አመላክቶናል። የሀገረ ስብከቱ ሥራ አስፈጻሚ ጉባኤ እና በሀገረ ስብከቱ ሥር የሚገኙ አብያተ ክርስቲያናት ከብፁዕ አቡነ ፋኑኤል ጋር ያላቸው አለመግባባት የቤተ ክርስቲያንን መዋቅር በመጠቅና ባለመጠበቅ ላይ ሆኖ  እያለ ሁሉም የሚያውቀውን እውነታ በተለይም ቃለ መጠይቁን ያደረጉላቸው ባለሙያ ሳይቀሩ ሀገረ ስብከት ጽ/ቤት እንዳለ ሲናገሩ የቅዱስ ሲኖዶስ አባል የሆኑት ሊቀ ጳጳስ ይህንን ለመመስከር ሳይችሉ መቅረታቸው ወደፊትም ከብፁዕ አቡነ ፋኑኤል ምን መልካም ነገር መጠበቅ እንዳለብን አጠያያቂ ሆኖ አግኝተነዋል። ይህ የሰጡትም ቃለ መጠይቅ ለታሪክም ለመፈራረጃም እንዲሆን ይቀመጣል ።  በአሁኑ ዘመን ሕዝበ ክርስቲያኑን መምራት የሚቻለው እውነትን በመናገር ብቻ ነው ፤ በማደናገር ለመምራት መሞከር በሰውም ሆነ በእግዚአብሔር ዘንድ ክብርን ያሳጣል” ሲል መግለጫው አብራርቷል።
አያይዞም ብፁዕ አቡነ ፋኑኤል በቅዱስ ሲኖዶስ ፊት ቀርበው የዋሽንግተን ዲሲው ደብረ ምሕረት ቅዱስ ሚካኤል ቤተ ክርስቲያንን ወደ ቤተ ክርስቲያን መዋቅር መግባቱን አበስራለሁ ብለው በተቀደሰው ጉባኤ ፊት የተናገሩትን ቃል በተግባር ፈጽመው ቢያሳዩን አስተማሪነቱ ታላቅ ይሆን ነበር፤ ቃልና ተግባር ተስማምቶ ሲገኝ በእግዚአብሔር ዘንድ ልዩ ክብር ያስገኛልና” ካለ በኋላ “በሀገረ ስብከቱ መዋቅር ሥር የተሰባሰቡ አብያተ ክርስቲያናት ቃለ ዐዋዲውን የጠበቁ ስለመሆናቸው  የጉዳዩ ባለቤት የሆኑት በተግባር የፈጸሙት በመዋቅር ሥር የሚገኙ አብያተ ክርስቲያናት ሊናገሩ ሲገባቸው ብፁዕ አቡነ ፋኑኤል ቃለ ዐዋዲውን የሚጠብቅ ቤተ ክርስቲያን የለም ማለታቸው መረጃን ያላገናዘበ ገለጻ መስጠት ሁልጊዜም በሰው ዘንድ  እንደሚያስገምት ትምህርት የሚሰጥ ነው” እንዲሁም በሀገረ ስብከቱ ሥር ከሚገኙ አብያተ ክርስቲያናት  መካከል  ከቅዱስ ሲኖዶስ  ጽ/ቤት የተላከውን ቃለ ዐዋዲ የእንግሊዘኛ ትርጉም  በቀጥታ  መተዳደሪያ ደንባቸው አድርገው ያስገቡ እንዳሉ ግን ማስገንዘብ እንወዳለን” ብሏል መግለጫው።
ከዚህም ባሻገር “ብፁዕ አቡነ ፋኑኤል ጥር 14 ቀን  2004 ዓ. ም በጻፉት ደብዳቤም  በሀገረ ስብከቱ በሕጋዊ መንገድ ተመርጦ የቤተ ክርስቲያንን ኃላፊነት በመወጣት ላይ የሚገኘውን የመንፈሳዊ አስተዳደር ጉባኤ (ሥራ አስፈጻሚ ጉባኤ) የግል ጥቅም የተነካባቸው እና በሕገ ወጥ መንገድ ማኅተም አስቀርጸው ይንቀሳቀሳሉ በማለት ከእውነት በራቀ መልኩ የጻፉት ደብዳቤ በቀላል የማይታይና ለመወንጀልም የተሞከረው በሀገረ ስብከቱ ሥር የሚገኙ አብያተ ክርስቲያናትን፤ በሀገረ ስብከቱ አጠቃላይ ጉባኤ የተመረጠውን መንፈሳዊ አስተዳደር ጉባኤ እና በወቅቱ የነበሩትን ሊቀ ጳጳስ ብፁዕ አቡነ አብርሃምንም ስለሆነ በቅዱስ ሲኖዶስ ፊት ማስረጃ ማብራሪያ ፍርድ መጠየቅ እንደሚገባን አምነንበታል” ብሏል።
ሀገረ ስብከቱ የሚጠቀምበትን  ማኅተም ከዚህ በፊት በሕጋዊ መንገድ ተሠርቶ ይጠቀምበት የነበረ እንጂ ብፁዕ አቡነ ፋኑኤል  እንደጻፉት በሕገ ወጥ መንገድ የተሠራ” እንዳልሆነ ያስቀመጠው መግለጫው ማን ለግል ጥቅም  እንደቆመ የቅዱሳን አምላክ እግዚአብሔር ፍርድ ይስጥ ከማለት የበለጠ የምንለው ነገር የለም፤ ማንም ከእርሱ የሚያመልጥ የለምና የሶስና አምላክ ፍርድ ይስጠን እንላለን” ሲል አትቷል።
በመጨረሻም “በሀገረ ስብከቱ ሥር የሚገኙ አብያተ ክርስቲያናት የሚፈልጉት ክርክርን ሳይሆን ለቤተ ክርስቲያን የሚጠቅም ሥራን ነው፤ በስሜታዊነት የሚናገር አባት ሳይሆን በመንፈሳዊነት የሚመራ አባት ነው፤ የተዘበራረቀ አካሄድ ሳይሆን ግልጽ የሆነ አቋምና አመራር ነው። ብፁዕ አቡነ ፋኑኤል የሀገረ ስብከቱን መዋቅር ተቀብለው አቋማቸውን ግልጽ አድርገው ለመሄድ ዝግጁ እስከሆኑ ድረስ በሀገረ ስብከቱ ሥር ያሉ አብያተ ክርስቲያናት አብረዋቸው ለመሥራት ዝግጁ ናቸው። ሀገረ ስብከቱ መመራት ያለበት በግል አመለካከት እና ስሜት ሳይሆን ቤተ ክርስቲያኒቱ ባስቀመጠችው መመሪያ መሆን አለበት ብለን እናምላለን። ይህ አቋም መንፈሳዊና ሃይማኖታዊ አቋም ነው፤ ሰውን ደስ ይበለው ብለን እግዚአብሔርን አናሳዝንም የሀገረ ስብከት መዋቅር የጸና  ሃይማኖታዊ መሠረት አለው” ሲል አጠቃሏል።  

የመግለጫውን ሙሉ ቃል ለማንበብ ይህንን ይጫኑ።

 

ቸር ወሬ ያሰማን

አሜን

Post a Comment

Blog Archive

የአቡነ ጳውሎስ "ሐውልተ ስምዕ"

ነጻ ፓትርያርክ ምርጫ ቢሆን ኖሮ ማንን ይመርጡ ነበር? እንበልና ሁሉም ነገር ሥርዓቱን ጠብቆ የተከናወነ የእጩዎች ምርጫ ቢሆን ኖሮ፣ አሁን የምናነሣቸው ጉድለቶች ባይኖሩ ኖሮ፣ 6ኛው ፓትርያርክ እንዲሆን የምትመርጡት ማንን ነበር? (ማሳሰቢያ፦ አሁን ያለው ክፍፍል እና የመንግሥት ተጽዕኖ ባይኖር ኖሮ ተብሎ የሚመለስ ጥያቄ ነው። የምን “ባይኖር ኖሮ ነው” የሚል አስተያየት ካለዎትም እናከብራለን።)