February 3, 2012

የስብከተ ወንጌል እና ሐዋርያዊ ተልእኮ መምሪያ የእነ በጋሻውን “የገቢ ማሰባሰቢያ መርሐ ግብር” አገደ

  • READ IN PDF & Read the Letter.
  •  በእግዱ ደብዳቤ ላይ “መምሪያው ከሚመድባቸው መምህራን ውጭ የሆኑ ግለሰቦች” የተባሉት እነበጋሻው በየጊዜው ፖስተር በመለጠፍ የሚያካሂዱት ቅስቀሳ ሕገ ወጥ መሆኑ ተመልክቷል
  •  የአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት ሥራ አስኪያጅ የሕገ ወጥ ሰባክያንንና ዘማርያንን ስምሪት በመፍቀድ የቅዱስ ሲኖዶስ መመሪያንና ውሳኔን እየጣሱ ነው
  • አብዛኞቹ የአህጉረ ስብከት ጽ/ቤቶችና ብፁዓን ሊቃነ ጳጳሳት ለመመሪያው ተፈጻሚነት እየሠሩ ሲሆን ተግባራዊ የማድረግ ድክመት የታየባቸውም አሉ
  • የመንበረ ፓትርያርክ ጠቅላይ ቤተ ክህነት ጽ/ቤት ፈቃድ የሌላቸውን ሕገ ወጥ ሰባክያንና ዘማርያን ነን ባዮች እንዲሁም ሕዝቡን የሚያደናግሩባቸውን የኅትመት ውጤቶቻቸውን ለመቆጣጠር የወጣውን የቅዱስ ሲኖዶስ መምሪያና ውሳኔ ለማስፈጸም የመንግሥትን እገዛ ጠይቋል
  • "ከመንበረ ፓትርያርክ ጠቅላይ ጽ/ቤት ዕውቅና እና ፈቃድ ውጪ የቤተ ክርስቲያኒቱን ሥርዐት እና መዋቅር በመጣስ በሚንቀሳቀሱ ግለሰቦች ላይ ጥብቅ ቁጥጥር እንዲደረግ እና ሕጋዊ ርምጃ እንዲወሰድ እናሳስባለን”/የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ ጽ/ቤት በመ/ፓ/ጠ/ቤ/ክ ጥያቄ ለአስተዳደሩ ፍትሕ ቢሮ እና የአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን የጻፈው ደብዳቤ/

(ደጀ ሰላም፣ ጥር 24/2004 ዓ.ም፤ Feb 2/2012)፦ እነ በጋሻው ደሳለኝ እና ሌሎች 13 ግለሰቦች ጥር 20 ቀን 2004 ዓ.ም “የርዳታ ማሰባሰቢያ መርሐ ግብር” በሚል በጠቅላይ ቤተ ክህነት ስብከተ ወንጌል አዳራሽ ሊያካሂዱት የነበረው ጉባኤ ሕገ ወጥ በመሆኑ መታገዱን በመ/ፓ/ጠ/ቤ/ክ የስብከተ ወንጌል እና ሐዋርያዊ ተልእኮ መምሪያ አስታወቀ፡፡
የመንበረ ፓትርያርኩ ምንጮች ለደጀ ሰላም እንደተናገሩት÷ እገዳው የተላለፈው በቅርቡ የስብከተ ወንጌል እና ሐዋርያዊ ተልእኮ መምሪያ ዋና ሓላፊ ሆነው የተሾሙት መጋቤ ብሉይ አእመረ አሸብር ወደ ብፁዕ ዋና ሥራ አስኪያጁ አቡነ ፊልጶስ ቢሮ ተጠርተው የ”ርዳታ ማሰባሰቢያ” መርሐ ግብሩ በጥቅምቱ ቅዱስ ሲኖዶስ ምልአተ ጉባኤ ሃይማኖታቸው እንዲመረመር ውሳኔ በተላለፈባቸውና በሌሎች ሕገ ወጥ ግለሰቦች የሚመራ በመሆኑ ዳግም የተቀሰቀሰው የምእመኑ ቁጣ ወዳልተፈለገ ደረጃ ከመድረሱ በፊት መምሪያው የራሱን ርምጃ እንዲወስድ መመሪያ ከተሰጣቸው በኋላ ነው፡፡
በብፁዕ ዋና ሥራ አስኪያጁ መመሪያ መሠረት መምሪያው መርሐ ግብሩን ማገዱን የሚገልጽ ደብዳቤ አውጥቶ በግልባጭ ለጠቅላይ ቤተ ክህነቱ የጥበቃ ክፍል ሓላፊ ያስታወቀ ቢሆንም ደብዳቤው ተፈርሞ የወጣው ግን በመምሪያው ምክትል ሓላፊ ቀሲስ ሳሙኤል እሸቱ በኩል ነው፡፡ ይህም በጥቅምቱ ቅዱስ ሲኖዶስ ምልአተ ጉባኤ ወቅት የምልአተ ጉባኤው አባላት በሃይማኖታቸው ርቱዕነት ላይ ጥያቄ ያነሡባቸውና በጊዜው የሊቃውንት ጉባኤ ምክትል ሰብሳቢ የነበሩት መጋቤ ብሉይ አእመረ አሸብር ለሕገ ወጦቹ ግለሰቦች ልዩ አስተያየት (ልዩ ግንኙነት?) እንዳላቸው የሚሰጠውን መረጃ እንደሚያጠናክረው እየተነገረ ይገኛል፡፡
የመምሪያው ምክትል ሓላፊበቁጥር ስወ/289/2004 በቀን 18/05/2004 ዓ.ም በአድራሻ የገቢ ማሰባሰቢያ መርሐ ግብሩ ይደረግላቸዋል ለተባሉት የልብ ሕመምተኛ አቶ እንዳለ ገብሬ÷ በግልባጭ ደግሞ ለቅዱስ ሲኖዶስ ጽ/ቤት፣ ለጠቅላይ ቤተ ክህነት ጽ/ቤት፣ ለፌዴራል ፖሊስ ኮሚሽንና ለአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን በጻፉት ደብዳቤ እንዳስታወቁት በገቢ ማሰባሰቢያው መርሐ ግብር ላይ የሚያስተምሩ መምህራንን መድቦ ነበር፡፡ ይሁንና ስለ ርዳታ ማሰባሰቢያው ፕሮግራም በተሰራጩት ፖስተሮች ላይ ግና ትምህርቱ በመምሪያው በተመደቡት መምህራን ሳይሆን በፖስተሮቹ ላይ በተዘረዘሩት ግለሰቦች እንደሚሰጥ ቅስቀሳ በመካሄዱ የጠቅላይ ቤተ ክህነቱ የሥራ ሓላፊዎች እና መምሪያው ባደረጉት ውይይት ጉዳዩ ሕገ ወጥ መሆኑ እንደታመነበት ደብዳቤው አስረድቷል፡፡
በመሆኑም አቶ እንዳለ ገብሬ ለልብ ሕመማቸው በውጭ ሀገር ሕክምና ለማግኘት ባለፈው ሳምንት እሑድ፣ ጥር 20 ቀን 2004 ዓ.ም በ7፡00 በሕገ ወጥ ግለሰቦች አስተባባሪነት በጠቅላይ ቤተ ክህነት ሊያካሂዱት የነበረው የርዳታ ማሰባሰቢያ መርሐ ግብር መታገዱን መምሪያው አስታውቋል፡፡
በደብዳቤው ላይ መምሪያው ከሚመድባቸው መምህራን ውጭ ለመሆናቸው ዳግመኛ የተረጋገጠባቸውን “ግለሰቦች” በሚል የተመለከቱት ሕገ ወጦች ሕዝቡን ከሚያደናግሩበት ፖስተሩ ጋር በማገናዘብ ስንዘረዝራቸው፡- በጋሻው ደሳለኝ፣ ተረፈ አበራ፣ አሰግድ ሣህሉ፣ ጥራዝ ነጠቁ ታሪኩ አበራ፤ ከዘማርያን ደግሞ አሸናፊ ገብረ ማርያም፣ ዕዝራ ኃይለ ሚካኤል፣ የትምወርቅ ሙላት፣ ዘርፌ ከበደ እና ምርትነሽ ጥላሁን ይገኙባቸዋል
የጥቅምቱ ቅዱስ ሲኖዶስ ምልአተ ጉባኤ ቀደም ሲል የተላለፉ መመሪያዎችን በማጽናት ጥቅምት 20 ቀን 2004 ዓ.ም ልዩነት በሌለው ድምፅ በወሰነው መሠረት÷ ከጠቅላይ ቤተ ክህነትም ሆነ ከየአህጉረ ስብከቱ ጋር ምንም ግንኙነት ሳይኖራቸው ከአንዳንድ ግለሰቦች ጋር በመመሳጠር በርካታ ችግሮችን እየፈጠሩ የሚገኙ ሕገ ወጥ ሰባክያንና ሕዝቡን የሚያደናግሩባቸው የኅትመት ሸቀጦቻቸው (ቪሲዲዎቻቸውመጽሐፎቻቸው) ቁጥጥር እንዲደረግባቸው አዝዟል፡፡በአንዳንድ አህጉረ ስብከት የቀደመው መመሪያ አፈጻጸም በቂ ሆኖ እንዳላገኘው የገመገመው ምልአተ ጉባኤው ለተሟላ ተግባራዊነቱ የመንግሥት ድጋፍ ሊጠየቅበት እንደሚገባ ከስምምነት ላይ ደርሶ እንደነበር ይታወሳል፡፡
በዚህም መሠረት የመ/ፓ/ጠ/ቤ/ክ ጽ/ቤት በቁጥር 8307/2789/2004 በቀን 23/4/2004 ዓ.ም ለአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ ጽ/ቤት በጻፈው ደብዳቤ÷ ከቤተ ክርስቲያኒቷ ምንም ፈቃድና ድጋፍ ሳይኖራቸው በስብከተ ወንጌል አገልግሎት የተሰማሩ “ሃይማኖተኞች ነን ባይ ሰባክያን” ሕግን ባለማክበር፣ የቤተ ክርስቲያኒቱን ሥርዐት እና መዋቅር በመጣስ ላይ ስለሆኑ በመንግሥት አካል በኩል ጥብቅ ክትትልና ሕጋዊ ርምጃ በመውሰድ ወደ ትክክለኛ አቅጣጫ እንዲመለሱ ይደረግ ዘንድ ጠይቋል፡፡
ጥያቄው የቀረበለት የከንቲባው ጽ/ቤትም የጠቅላይ ቤተ ክህነቱን ደብዳቤ መሠረት በማድረግ ለአስተዳደሩ ፍትሕ ቢሮ እና ለአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን እንዳስታወቀው ከመንበረ ፓትርያርክ ጠቅላይ ጽ/ቤት ዕውቅና እና ፈቃድ ውጭ የቤተ ክርስቲያኒቱን መዋቅር በመጣስ በሚንቀሳቀሱ ግለሰቦች ላይ ሕጋዊ ርምጃ እና ጥብቅ ቁጥጥር እንዲደረግ አሳስቧል፤የጥቅምቱ ቅዱስ ሲኖዶስ ምልአተ ጉባኤ ያስተላለፈውን ውሳኔ ስምንት ገጽ በአባሪነት አያይዟል፡፡
ይህም ሆኖ በጥቅምቱ ቅዱስ ሲኖዶስ ምልአተ ጉባኤ ፍጻሜ የአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት ሥራ አስኪያጅ ሆነው በፓትርያርኩ የተሾሙት ንቡረ እድ ኤልያስ ኣብርሃ፣ የምዕራብ ሐረርጌ ሀገረ ስብከት ጸሐፊ ሊቀ ኅሩያን ደረጀ ብርሃኑ የመሳሰሉ ባለሥልጣናት ለምልአተ ጉባኤው ውሳኔ የሚገዙ ሆነው አልተገም፡፡
ለአብነት ያህል ንቡረ እድ ኤልያስ ኣብርሃ በአንዳንድ የሀገረ ስብከቱ አጥቢያ አብያተ ክርስቲያን (በሽሮ ሜዳ መንበረ ስብሐት ቅድስት ሥላሴ፣ በኮተቤ ደብረ ልዑል ቅዱስ ገብርኤል፣ ገዳመ ኢየሱስ እና በፉሪ ጽርሐ ንግሥት ሐና ማርያም አብያተ ክርስቲያን) ሕገ ወጥ ሰባክያንና ዘማርያን ከግለሰቦች ጋር በመመሳጠር ራሳቸውን ማሰማራታቸውን በቸልታ ተመልክተዋል፤ ይህን አስመልክቶ የአጥቢያ አብያተ ክርስቲያኑ ስብከተ ወንጌል ክፍሎች፣ የሰንበት ት/ቤት ወጣቶች እና ምእመናን ያቀረቡላቸውን አቤቱታ በማጣጣል አሸማቀዋቸዋል፡፡ በዚህም ንቡረ እዱ የሀገረ ስብከቱ ሥራ አስኪያጅ ሆነው ከተሾሙበት ቀን ጀምሮ የቀደመውን የሀገረ ስብከቱን የመልካም አስተዳደር ውጥኖች ብቻ ሳይሆን ሕገ ወጥ ሰባክያንንና ዘማርያንን በመከላከል ረገድ የተመዘገቡ ውጤቶችን ወደ ኋላ እንደሚመልሱ ለተናፈሰው ስጋት ማረጋገጫ ሰጥተዋል፡፡
ንቡረ እዱ ከሀገረ ስብከቱ ሥራ አስኪያጅነታቸው ጋር በጠቅላይ ቤተ ክህነት ምክትል ሥራ አስኪያጅነት እና በቅድስት ሥላሴ መንፈሳዊ ኮሌጅ የአስተዳደር ዲንነት ደራርበው ይዘዋቸው ከነበሩት ሓላፊነቶች ተነሥተዋል፤ በቅርቡ “የሥራ ጉብኝት” ፕሮግራሞችን በማውጣት በየአጥቢያ ቤተ ክርስቲያኑ በመዞር ላይ ናቸው፤ የሥራ ጉብኝት ለማካሄድ ማሰቡ በራሱ መልካም ቢሆንም ንቡረ እዱ በደረሱባቸው አጥቢያዎች የነዳጅ እና ምሳ አበል” በሚል እስከ ብር 10,000 የተቀበሉባቸው አጥቢያዎችም እንዳሉ ተጠቁሟል፡፡ በአንፃሩ ጥቂት በማይባሉ አጥቢያዎች ከየአለቆቻቸው ጋር በተፈጠሩ የአስተዳደር ችግሮች የተነሣ የራስ አገዝ የልማት እንቅስቃሴዎቻቸው እየተጓተተ ይገኛል፤ በሂደትም ውዝግቦቹ የማያባራ የእርስ በርስ ሁከት መንሥኤ እንዳይሆኑ በመስጋት ከወዲሁ መፍትሔ ሊፈለግላቸው እንደሚገባ ተመክሯል፡፡
ለአብነት ያህል የደብረ መዊዕ ቅዱስ ሚካኤል ካቴድራል ከኅዳር ወር መባቻ አንሥቶ ያለ አስተዳዳሪ ይገኛል፡፡ የዚህም መንሥኤ ለሁለት ዓመታት የካቴድራሉን ገንዘብ እና ንብረት ሲመዝብሩ የቆዩት፣ ለክህነታቸው የማይገባ ከፍተኛ ሥነ ምግባራዊ ግድፈት ታይቶባቸዋል የተባሉት አለቃው ሊቀ ሊቃውንት ዕዝራ ተክለ ጊዮርጊስ በ12,000 የአጥቢያው ምእመናን ፊርማ ከሓላፊነታቸው እንዲነሡ በቀረበው ጥያቄ ነው፡፡ በማስረጃ የተደገፈ የአጥቢያው ምእመናን አቤቱታ የቀረበላቸው የፓትርያርኩ ልዩ ጽ/ቤት እና የሀገረ ስብከቱ ጽ/ቤት ሊቀ ሊቃውንት ዕዝራ ጋር ባላቸው ግንኙነት ምክንያት ምእመናኑና ማኅበረ ካህናቱ የመረጠውን ሰበካ ጉባኤ አላጸደቁም፤ ትክክለኛ አስተዳዳሪ አልተመደበም፤ በዚህም ምክንያት ምእመኑ ለዕለታዊ ሕዝባዊ አገልግሎት ከሚያስፈልገው ሥራ ማስኬጃ ውጭ የካቴድራሉ ቼኮች እንዳይንቀሳቀሱ አግዷል፤ በሂደትም ጉዳዩን ወደ ፍትሕ አካልና ወደ ሚዲያ በመሰድ ማስረጃዎችን ይፋ የማድረግ ሥራ እንደሚሠራ አስጠንቅቋል፡፡
በተያያዘ ዜና የምዕራብ ሐረርጌ ሀገረ ስብከት የቅዱስ ሲኖዶስ ምልአተ ጉባኤ በሕገ ወጥ ሰባክያንና ዘማርያን ላይ የተላለፈውን ውሳኔ ተግባራዊ በማድረግ ረገድ ክፍተት የታየበት ሌላው ሀገረ ስብከት ነው፡፡ በሀገረ ስብከቱ የተመደቡት ሊቀ ጳጳስ በቦታው አለመገኘታቸውን በመጠቀም ሕገ ወጦቹ በአሰበ ተፈሪ ለደብረ ጽዮን ልደታ ለማርያም ቤተ ክርስቲያን ሕንፃ ቤተ ክርስቲያን ማሠሪያ የተዘጋጀውን ጉባኤ በመጥለፍ ጉባኤውን በኢቢኤስ ቴሌቪዥን ለሚያስተላልፉት ፕሮግራማቸው ማስተዋወቂያነት ተጠቅመውበታል፡፡
የደብሩ አስተዳደርና የሀገረ ስብከቱ ሥራ አስኪያጅ ሊቀ ብርሃናት ከሃሊ በቃሉ የአጉራ ዘለሎቹን በጉባኤው ላይ መገኘት የተቃወሙ ሲሆን የሀገረ ስብከቱ ጸሐፊ ሊቀ ኅሩያን ደረጀ ብርሃኑና በሀገረ ስብከቱ ጽ/ቤት ላይ ተጽዕኖ በመፍጠር በቁጥጥር ሥር ያዋሉትሁለት ማኅበራት (ማኅበረ ናታኒም እና ማኅበረ ጽዮን) የሕገ ወጦቹን ስምሪት በማስተናበር ግንባር ቀደም ሚና መጫወታቸው ተመልክቷል፡፡
በማኅበራቱ ውስጥ የሀገረ ስብከቱን ጸሐፊና የከተማውን ሙሰኛ ባለሀብቶች በዚህ ዐይነቱ ሕገ ወጥ የጥቅም ግንኙነት የማስተሳሰር ልምድ ያላቸው ግለሰቦች የአመራርነት ሚና እንደሚጫወቱ የተጠቆመ ሲሆን ከእኒህም መካከል ይርጋዓለም ቸኮል የተባለው በተሐድሶ ኑፋቄ አራማጅነቱ በቅዱስ ሲኖዶስ ተወግዞ የተባረረው የሃይማኖተ አበው ማኅበር አባል የነበረ ግለሰብ ይገኝበታል፡፡ ዛሬ ማኅበረ ናታኒም በተሰኘ ሌላ የማኅበር ካባ የሚንቀሳቀሰው ይኸው ግለሰብ ከተወሰኑ ዓመታት በፊት “ሙት አሥነሳለሁ” በሚል በሞተ ሰው አስከሬን ላይ በፕሮቴስታንታዊ ዘይቤ ሲጨፍር ተደርሶበት በወቅቱ የሀገረ ስብከቱ ሊቀ ጳጳስ ብፁዕ አቡነ ኤዎስጣቴዎስ ቀኖናዊ ቅጣት የተሰጠው አጉራ ዘለል እንደ ነበር ተነግሯል፤ ባለበት የእጅ አመል የተነሣ ከብዙ የሥራ ተቋማት የተባረረው ግለሰቡ ከማዕከል ወደ ሀገረ ስብከቱ በሚላኩ ኦርቶዶክሳውያን መምህራን እና ሰባክያን ላይ ነውጥ በማሥነሳትም ይታወቃል፡፡ ይርጋለም በዓላማና ጥቅም ከሚያስተባብራቸው የከተማው ሙሰኛ እና ሱሰኛ ‹ባለሀብቶች› መካከል በጭሮ(አሰበ ተፈሪ) ዞን ፋይናንስ ጽ/ቤት የጫት ቀረጥ ሠራተኛ እና በኋላም በጭሮ እርሻ ቴክኒክ እና ሞያ ማሠልጠኛ ኮሌጅ የሒሳብ ባለሞያ ሆኖ ሲሠራ በሙስና(ስርቆት) ተገምግሞ እንደተባረረ የተነገረለት ታረቀኝ የተባለ ግለሰብ ዛሬ በከተማው የአንድ ሆቴል ባለቤት እንደ ሆነ ተነግሯል፡፡
የፀረ-ፕሮቴስታንታዊ ተሐድሶ እንቅስቃሴ ዒላማ አፅራረ ቤተ ክርስቲያን በአስተምህሮ ቅሰጣ የሚያደርጉትን ዘመቻ ብቻ ሳይሆን እንዲህ ዐይነቱ የጥቅመኞች ግንኙነት ለፕሮቴስታንታዊ ተሐድሶ ሤራ የሚፈጥረውን ምቹ መረብ በመበጣጠስ ላይም አተኩሮ መሥራት እንደሚገባው የሚመክሩ አስተያየት ሰጪዎች፣ የምዕራብ ሐረርጌ ሀገረ ስብከት በተመደበለት ሊቀ ጳጳስ አመራር ሰጪነት ጽ/ቤቱን አጥርቶ እና አጠናክሮ በሕገ ወጦች ላይ አፋጣኝ የእርምት ርምጃ እንዲወስድ ጠይቀዋል፤ አፅራረ ቅዱሳን ተቆጣጣሪ የሌለው ነጻ መድረክ ያገኙ በሚመስሉበት በጋምቤላ ሀገረ ስብከትም ከሥራ አስኪያጁ የማንአለብኝ ድርጊት ጀምሮ ተመሳሳይ የእርምት አካሄድ መኖር እንደሚገባው ተጠቁሟል፡፡
በሌላ በኩል በሀገር ውስጥ - እንደ ወላይታ ሶዶ፣ ጉራጌ እና ደቡብ ወሎ/ደሴ/ አህጉረ ስብከት ከውጭ - የሊባኖስና የተባበሩት ዐረብ ኤምሬቶች እና አካባቢው አህጉረ ስብከት በሕገ ወጥ ሰባክያንና ዘማርያን ላይ የወሰዷቸው ርምጃዎች ለሌሎችም አህጉረ ስብከት በአርኣያነት የሚጠቀሱ ናቸው፡፡ ጥር 18 ቀን 2004 ዓ.ም በአርማጌዶን ቪሲዲ የተነሣ ለተከሰሰው መ/ር ዘመድኩን አንደኛ የመከላከያ ምስክር ሆነው የቀረቡት የወላይታ ሶዶ ሀገረ ስብከት ሥራ አስኪያጅ አባ ኀይለ ጊዮርጊስ ተረፈ የግል ተበዳይ የተባለው በጋሻው ደሳለኝ “ከተቋም ተምሮ ያልወጣ፣ በመዋቅር ያልታቀፈ፣ በደብዳቤ ያልተላከ” በመሆኑ የማስተማር ችሎታ እና ሥልጣን ከሌላቸው ሕገ ወጦችና ሁከት ቀስቃሾች አንዱ መሆኑን ለችሎቱ አስረድተዋል፡፡ ሕገ ወጥ ሰባክያንንና ዘማርያንን የመቆጣጠር ሓላፊነት ከአጥቢያ አብያተ ክርስቲያን ጀምሮ መካሄድ እንደሚገባው ከቅዱስ ሲኖዶስ የተላለፈው ውሳኔ እንደሚያዝዝ ያብራሩት ሥራ አስኪያጁ አባ ኀይለ ጊዮርጊስ በሀገረ ስብከታቸው ይህንኑ ውሳኔ በማስፈጸም ላይ እንደሚገኙ ለችሎቱ አረጋግጠዋል፡፡ሕገ ወጦቹ በቅርቡ በዳውሮእና በወላይታ ሶዶ ጉባኤ ለማካሄድ ሙከራ ያደረጉት ጥያቄም በመምሪያው መሠረት ውድቅ መደረጉ ታውቋል፡፡
በተመሳሳይ መልኩ የሊባኖስና የተባበሩት ዐረብ ኤምሬቶች እና አካባቢው አህጉረ ስብከትሊቀ ጳጳስ ብፁዕ አቡነ ድሜጥሮስ ጥቅምት 22 ቀን 2004 ዓ.ም ለፌዴራል ጉዳዮች ሚኒስቴር እና ለብሔራዊ ደኅንነት እና መረጃ አገልግሎት በጻፉት ደብዳቤ ከሊቀ ጳጳሱ ዕውቅና እና ከሀገረ ስብከቱ ፈቃድ ውጭ ከመ/ፓ/ጠ/ቤ/ክ ጽ/ቤት ሳይላኩ ወደ አህጉረ ስብከታቸው የሚመጡ ሕገ ወጥ ሰባክያንና ዘማርያን(በደብዳቤው ላይ የ18ቱ ስም ዝርዝር ተመልክቷል) የጉዞ ትብብር እንዳይደረግላቸው ጠይቀዋል፡፡
የስብከተ ወንጌል እና ሐዋርያዊ ተልእኮ መምሪያ እነ በጋሻው በርዳታ ማሰባሰብ ስም ጥር 18 ቀን 2004 ዓ.ም ሊያካሂዱት የነበረውን ሕገ ወጥ ጉባኤ ማገዱ፣ እነበጋሻውና በፖስተሩ ላይ የተመለከቱት 13 ግለሰቦች መምሪያው ከሚመድባቸው መምህራን ውጭ መሆናቸውን ማረጋገጡ ለቅዱስ ሲኖዶስ ውሳኔ መከበር የራሱ አስተዋፅኦ እንዳለው እናምናለን፤ “ሕገ ወጥ ከሚል ጅምላ ፍረጃ ውጭ በስም ተለይተን የተጠቀስንበት ውሳኔ የለም” የሚለውን የአጉራ ዘለሎቹን የማምለጫ እና መከራከሪያ መንገድም(ዐቃቤ ሕግ መ/ር ዘመድኩንን በስም ማጥፋት ወንጀል በከሰሰበት ክስ አንዱ መከራከሪያው የሲኖዶሱ ውሳኔ በጥቅል እንጂ በስም የማይዘረዝር ነው የሚል ነበር) በተጨባጭ የዘጋ/ያቆመ ጉልሕ ርምጃ ነው
በሌላ በኩል “በውጭ አገር የሕክምና ርዳታ ያሻዋል” ለተባለው ወንድም አስፈላጊው ትብብር ለማድረግ ደጀ ሰላም ያላትን ዝግጁነት እየገለጸች ሰብአዊ ርኅራኄ/ርዳታ የሕገ ወጥነት፣ መናፍቅነት እና አጉራ ዘለልነት ጭንብል ሊሆን እንደማይገባው መልእክቷን ታስተላልፋለች፡፡ 

TO GET ALL LETTERS AND DOCUMENTS, CLICK HERE.

5 comments:

Anonymous said...

አሁንስ ያ የሰማይ ዝናባዊ እሳት ለፍርድ ይምጣ የተረፈው ሰላም እንዲያገኝ

Anonymous said...

it is good to our church leded by Egybtian bishops.b/c our fathers c't undrstand what Holy synod is.act15-29
from arat killo

Anonymous said...

Megabe Biluy Aemere Sire'at biyizu melkam newu. ' Yejib chikul qend yineksal' yihe bewetatinet lemebeltseg yeteyayazut menged ayawatam. Yaderebot Kifu ygenzeb fikir bewusto nufaqe eyewelede newu. If you continue this way you gonna reach no where. You are not working with the grace of God. You are to mechanical and you love money too much and that is why you are compromising....

Anonymous said...

ወገኖች!እባካችሁ ለራሳችን ሕይወት እንጠንቀቅ!!!

ምንም እንኳ ለብዞዎቻችሁ የእግዚአብሔር ቃል ድግምት ሆኖ ቢቀልባችሁም ለምታስተውሉ ውድ ወገኖቼ ግን የአምላካችን ሕያው ቃል ለስድብ ፈውስ እንደሚከተለው ይመክረናልና እንጠቀምበት:-

'ከእነዚህ ሰዎች ተለዩ ተውአቸውም ይህ አሳብ ወይም ይህ ሥራ ከሰው እንደ ሆነ ይጠፋልና ከእግዚአብሔር እንደ ሆነ ግን ታጠፉአቸው ዘንድ አይቻላችሁም በእርግጥ ከእግዚአብሔር ስትጣሉ ምናልባት እንዳትገኙ'
(ሐዋ/ሥራ 5:38-39)

ማስተዋልን ይስጠን!!! አሜን:: ደግሞም ለመንግሥቱ ሥራ ከራሱ ከእግዚአብሔር የበለጠ ያገባናል እንዳንል እፈራለሁና ሁላችንም እንደ ቃሉ ብንመላልስ ከመንፋሳዊ ክስረት ቢያንስ እራሳችንን እናስመልጣለን::

ሰላም ሁኑልኝ

እህታችሁ

ሰላም ነኝ

Anonymous said...

yes indeed keep your apologistic servies...this is what is expected of you as EOTC memeber.

Blog Archive

የአቡነ ጳውሎስ "ሐውልተ ስምዕ"

ነጻ ፓትርያርክ ምርጫ ቢሆን ኖሮ ማንን ይመርጡ ነበር? እንበልና ሁሉም ነገር ሥርዓቱን ጠብቆ የተከናወነ የእጩዎች ምርጫ ቢሆን ኖሮ፣ አሁን የምናነሣቸው ጉድለቶች ባይኖሩ ኖሮ፣ 6ኛው ፓትርያርክ እንዲሆን የምትመርጡት ማንን ነበር? (ማሳሰቢያ፦ አሁን ያለው ክፍፍል እና የመንግሥት ተጽዕኖ ባይኖር ኖሮ ተብሎ የሚመለስ ጥያቄ ነው። የምን “ባይኖር ኖሮ ነው” የሚል አስተያየት ካለዎትም እናከብራለን።)