March 4, 2012

ብፁዕ አቡነ አብሳዲ (1912 - 2004 ዓ.ም) ሲታወሱ

  • 30 ዓመታት በመጋቢነት፤ 18 ዓመታት በረዳት ሊቀ ጳጳስነት!
  •  የቀብር ሥርዐቱ በዚያው በኢየሩሳሌም ይፈጸማል ተብሏል
  •   ፓትርያኩ በቀብር ሥርዐቱ ላይ ይገኛሉ ተብሎ ይጠበቃል
  •   በፓትርያኩ ከተሾሙት 49 ብፁዓን ሊቃነ ጳጳሳት ያረፉት 13 ደርሰዋል
(ደጀ ሰላም፣ የካቲት 14/2004 ዓ.ም፤ ፌብሩዋሪ 22/2012/ READ THIS ARTICLE IN PDF)፦ አረጋዊው አባት ብፁዕ አቡነ አብሳዲ ማረፋቸውን መዘገባችን ይታወሳል። ላለፉት 60 ዓመታት በኢየሩሳሌም ገዳማት የኖሩትና በእግራቸው ከኢትዮጵያ ወደ ቅድስት አገር የመጓዙትን ጥንታዊ ትውፊት ከፈፀሙት አበው መካከል የነበሩት ብፁዕነታቸው በሕመም እና በእርግና ምክንያት ከዚህ ዓለም ድካም በሰላም እንዳረፉ ምንጮቻችን ገልጸዋል። ዝርዝር ዜናውን እንደደረሰልን እናቀርባለን ባልነው መሠረት ያዘጋጀነውን ቅንብር እነሆ።

 በቅድስት ሀገር ኢየሩሳሌም የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ገዳማትን በመጋቢነት እና በረዳት ሊቀ ጳጳስነት ያገለገሉትና የካቲት 10 ቀን 11 አጥቢያ 2004 ዓ.ም በተወለዱ በ92 ዓመታቸው ያረፉት የብፁዕ አቡነ አብሳዲ ቀብር ሥነ ሥርዐት ነገ፣ የካቲት 15 ቀን 2004 ዓ.ም በዚያው በኢየሩሳሌም ይፈጸማል ተብሎ ይጠበቃል፡፡ ለዚህም ብፁዕ ወቅዱስ ፓትርያሪኩ ዛሬ፣ የካቲት 14 ቀን ማምሻውን ወደዚያው ማምራታቸው ተሰምቷል፡፡
የቀብር ሥርዐቱ የዘገየው የብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ጳውሎስን መድረስ በመጠበቅ መሆኑን ያመለከቱት ምንጮቹ፣ ፓትርያሪኩ ከ11 ያላነሱ አባቶችን አስከትለው በተገኙበት በአልዓዛር ጻድቁ አቡነ ተክለ ሃይማኖት ገዳም እንደሚፈጸም ተናግረዋል፡፡ በቅድስት ሀገር ኢየሩሳሌም ካሉን የታሪክ እና ቅድስና ይዞታዎች ከብሉይ ኢየሩሳሌም ከተማ ሦስት ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ በሚገኘው ቢታንያ - አልዓዛር በጻድቁ አቡነ ተክለ ሃይማኖት ስም የተሠራው ቤተ ክርስቲያን ለማኅበረ መነኮሳቱ እና ምእመናኑ መካነ መቃብር ሆኖ እንደሚያገለግል ይታወቃል፡፡
በኢየሩሳሌም የኢትዮጵያ ገዳማትየመጀመሪያው ሊቀ ጳጳስ የነበሩት ብፁዕ አቡነ ፊልጶስ በ1944 ዓ.ም ተሾመው ከመሄዳቸው አንድ ዓመት ቀደም ብሎ ኢየሩሳሌም የደረሱት ብፁዕነታቸው፣ከ1947 ዓ.ም ጀምሮ ከ30 ዓመታት በላይ በማኅበረ መነኮሳቱ ምርጫ እና ተማኅፅኖ በኢየሩሳሌም የኢትዮጵያ ገዳማትን በመጋቢነት ሲያገለግሉ ቆይተዋል፡፡ጥር 30 ቀን 1985 ዓ.ም እርሳቸውን ጨምሮ አራት አባቶች (ብፁዕ አቡነ ዮሐንስ በሎንዶን፣ ብፁዕ አቡነ ታዴዎስ በካሪቢያን፣ ብፁዕ አቡነ ሕርያቆስ በአፍሪካ) በብፁዕ ወቅዱስፓትርያሪክ አቡነ ጳውሎስ አንብሮተ እድ ኤጲስ ቆጶስነት በተሾሙት ወቅት ብፁዕ አቡነ አብሳዲምበኢየሩሳሌም የኢትዮጵያ ገዳማት የሊቀ ጳጳሱ ረዳትበመሆን አገልግለዋል፡፡
ቀደም ሲል በዮርዳኖስ መንግሥት በኋላም በእስራኤል መንግሥት ፍርድ ቤቶች ከገዳሙ ማኅበር አባላት ጋራ በመተባበር በነበራቸው የዕብራይስጥ እና ዐረብኛ ቋንቋዎች ችሎታለዴር ሡልጣን የታሪክ እና ቅድስና ይዞታችን መከበር ብርቱ ትግል ያደረጉት ብፁዕነታቸው÷ ማዕርገ ጵጵስና ከተቀበሉበት ጥር 1985 ዓ.ም ጀምሮ በዕርግና እና መዘንጋት ጋራ በተያያዘ በጭንቅላታቸው ላይ ቀዶ ሕክምና እስከተደረገላቸው እስካለፈው ዓመት ድረስ በኢየሩሳሌም የኢትዮጵያ ገዳማት ሊቀ ጳጳስ ረዳት ጳጳስ በመሆን በትጋት አገልግለዋል፤ የማኅበረ መነኮሳቱን አንድነት በማጠናከር፣ ምእመናንን በመምከር እና በማስተማር አባታዊ ሓላፊነታቸውን ተወጥተዋል፡፡
በኢየሩሳሌምየኢትዮጵያ ገዳማት አሁን በመንበረ ጵጵስናው ያሉትን ብፁዕ አቡነ ማቲያስን ጨምሮ 11 ያህል ብፁዓን ሊቃነ ጳጳሳት ተመድበው አገልግለዋል፡፡ ቀደም ሲል ከነበሩት ከፊሉን ለማስታወስ - ብፁዕ አቡነ ፊልጶስ፣ ብፁዕ አቡነ ዮሴፍ፣ ብፁዕ አቡነ ማቴዎስ፣ ብፁዕ አቡነ በርናባስ፣ ብፁዕ አቡነ ሰላማ፣ ብፁዕ አቡነ አትናቴዎስ፣ ብፁዕ አቡነ ገብርኤል፣ ብፁዕ አቡነ ቀውስጦስ፣ ብፁዕ አቡነ ሕርያቆስ ይገኙበታል፡፡እንግዲህ በቅድስት ሀገር የሚገኙ የኢትዮጵያ ገዳማትን ታሪክ በተመለከተ ተጠያቂ አባት እንደነበሩ ብዙዎች የሚመሰክሩላቸው ብፁዕ አቡነ አብሳዲ ረዳት ሊቀ ጳጳስ የነበሩት ለእኒህ 11 ብፁዓን ሊቃነ ጳጳሳትን ነበር ማለት ነው፡፡
ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ጳውሎስ ፓትርያሪክ ሆነው ከተሾሙበት ከሐምሌ ወር 1984 ዓ.ም ወዲህ ዐረፍተ ሞት የገታቸው ብፁዓን ሊቃነ ጳጳሳት በአጠቃላይ 35 ያህል ናቸው፡፡ በአቡነ ጳውሎስ አንብሮተ እድ በተለያዩ ጊዜያት ማዕርገ ጵጵስና የተሾሙት ጳጳሳት ብዛት 49 ያህል ሲሆኑ ከእኒህም ውስጥ ብፁዕ አቡነ አብሳዲን ጨምሮ በሞተ ሥጋ የተለዩን ብፁዓን አባቶች ቁጥር 13 ደርሷል፡፡ የብፁዓን አባቶቻችን በረከታቸው ይደርብን፤ የቅዱሳን አምላክ የአባቶቻችንን ነፍስ ከማኅበረ ቅዱሳን፣ ከማኅበረ መላእክት ይደምርልን፡፡
ለመጀመሪያ ጊዜ ግብጽ-ካይሮ ላይ ግንቦት 18 ቀን 1921 ዓ.ም ከተሾሙት አምስት ኢትዮጵያውያን ጳጳሳት አንዱ በነበሩት ብፁዕ አቡነ ይሥሓቅ ማዕርገ ዲቁናን፣ ከኤርትራው ጳጳስ ብፁዕ አቡነ ማርቆስ ማዕርገ ቅስናን የተቀበሉት ብፁዕ አቡነ አብሳዲ ከትውልድ ስፍራቸው ትግራይ - ሽሬ ወጥተው፣ በርሓውን አቆራርጠው ወደ ኤርትራ ደብረ ማርያም ገዳምያመሩት በ1926 ዓ.ም ነበር፡፡
በፋሽስት ጣልያን ቅኝ ሥር በነበረችው ኤርትራ ደብረ ማርያም ገዳም ለዐሥር ዓመታት ተቀምጠው በርካታ አገልጋዮችን አስተምረው ለማዕርገ ቅስና፣ ለማዕርገ ዲቁና በማብቃት በከፍተኛ ችግር ላይ የነበሩትን የኤርትራ ክርስቲያኖች በትጋት ያገለገሉት ብፁዕነታቸው÷ ከነጻነት በኋላ ኤርትራ በፌዴሬሽን ከኢትዮጵያ ጋራ ስትዋሐድ ደጃዝማች ኣብርሃ በሚባሉ የአገሩ ገዥ ተባባሪነት በሱዳን በኩል ከአገር ወጥተው ወደ ግብጽ ተጉዘው በገዳመ አስቄጥስ/ዴር ሶርያ/ለሁለት ዓመታት ተቀምጠዋል፡፡
በገዳሙ ለሁለት ዓመት ተኵል ያህል ከአንድ ረድእ/ባልንጀራቸው/ ጋራ የዐረብኛንና ዕብራይስጥ ቋንቋዎችን ያጠኑት ብፁዕነታቸው፣በግብጽ የቅዱስ ማርቆስ ቤተ ክርስቲያን ፈርሶ ዳግመኛ ከታነፀ በኋላ ቅዳሴ ቤቱ በ1943 ዓ.ም ሲከበር በሥነ ሥርዐቱ ላይ ለመገኘት በስፍራው ከግርማዊ ቀዳማዊ ዐፄ ኀይለ ሥላሴ ጋራ በክብር እንግድነት ከተገኙት ብፁዕ አቡነ ባስልዮስና ብፁዕ አቡነ ቴዎፍሎስፈቃድና ትብብር ጠይቀው ወደ ኢየሩሳሌም ተሻግረዋል፡፡
የኤርትራ ደብረ ማርያም ገዳም አበምኔት እንዲሆኑ በሊቀ ጳጳሱ ብፁዕ አቡነ ማርቆስ ሲጠየቁ÷ ኤርትራ ከእናት ሀገሯ ኢትዮጵያ ጋራ በፌዴሬሽን በመዋሐዷ ከተሰማቸው ከፍተኛ ደስታ የተነሣ፣ ‹‹ኢየሩሳሌምን ስሜ ልምጣ›› ብለው ለአንድ ዓመት በቅድስት ሀገር ተቀምጠው ለመመለስ የወጡት ብፁዕ አቡነ አብሳዲበኢየሩሳሌም የኢትዮጵያ ገዳማት ማኅበር ተማኅፅኖና ጥያቄ በዚያው ለመቆየት ተገደዋል፡፡ለአንድ መንፈቅ የተቀበሉት የመጋቢነት ሓላፊነት‹‹እንኳን ውኃ ደም ያስለቅሳል›› በሚሉት የቆብጦች የይዞታ ሙግት እና ግፈኝነት ምክንያት ተራዝሞ ቀሪ ዘመናቸውን በዚያው እንዲያሳልፉ አድርጓቸዋል፡፡
ብፁዕነታቸው ከ10 ዓመት በፊትበኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ምእመናን መታሰቢያ ድርጅት ለኢየሩሳሌምተባባሪነት የቅድስት ሀገር ተሳላሚዎችን ተከትለው ወደ ኢየሩሳሌም ለወረዱት የሐመር መጽሔት እናስምዐ ጽድቅ ጋዜጣ ዘጋቢዎች በሰጡት ቃለ ምልልስ የሚከተለውን ቃል ተናግረው ነበር፡-
‹‹. . .እኔ በእውነት ወንድሞቼ ያለኝ የሀገር ፍቅር ለእናት ለአባቶቼ እንኳን የለኝም፡፡ ታድያ እዚያ ደርሼ ተሳልሜ አልመጣም ወይበሚል ነው እንጂ ይህ ሁሉ አገኛለሁ ብዬ አላሰብኹትም ነበር፤ ግን ቅናት ያዘኝ፡፡ ኋላማ በጣም የሚገርማችሁ ነገር ግብጾች፣ ሶርያዎች እና ግሪኮች የእኛን ይዞታ እንዴት እንደ ወሰዱት ሳውቀው በጣም ቃጠሎ አሳደረብኝ፡፡ እንግዲህ እግዜር አለ፤ እንግዲህ ለፈጣሪ ወይ ግደለኝ ወይ እንደ ጣና ያሉ ደሴቶች አብያተ ክርስቲያን አሉ፤ በዚያ ሄጄ ጭቅጭቅ የሌለበት…ምንኩስናውም ቢሆን እንዲያው በእውነት ቢያዩት አያስፈልግም፤ እንዲሁ ነው እኮ፤ ምንኩስናው ያለው መሬት ይዞ÷ ነገሥታቱም ተሳስተው ነው እንጂ መሬት አለመስጠት ነበረ፡፡
አንዳንድ ነገር ሊሰጧት አርሰው÷ ቆፍረው እንዲበሉ፣ ዳባ እንዲለብሱ ነበር እንጂ ሄዱ ነገሥታት አድርገዋቸው ቁጭ አሉ፤ ይፈርዱ ይሰቅሉ ጀመሩ፡፡ ላዩ ቆብ ነው፤ ሥራው የዓለም ነው፤ የባሰ ነገር መጥቶ አዋረደው እንጂ ትክክል አልነበረም እንዴ፡፡ መነኩሴ ማለት ከዋልድባ እንዳይወጣ፣ ከማኅበረ ሥላሴ እንዳይወጣ እዚያ ቁጭ ብሎ ለነፍስ መለመን ነበር እንጂ፡፡
እግዜር ያሳይዎት÷ ጉድ ነው÷ ትክክል አልነበረም፡፡ አርሶ አያርስ ወይ በገዳም አይቀመጥ፣ ብቻ እየተነሣ ወደ ከተማ፡፡ ታዲያ እንግዲህ ምንድን ነው? ትክክል አይደለም ብንመለከተው፤ ምንኩስና ከሆነ ከገዳሙ ሳይወጣ ድኻ ምስኪን መሆን፣ ሰውነቱን አድክሞ ፍቅርና ሰላም ይዞ ስለ ሀገር ምሕላ ማድረግ ነበር፤ ሥራችን ይሄ ነበር፡፡ ካህናት የግድ በዓለም ነው ያሉ፡፡ በእውነት እንግዲህ እነርሱም ቢሆኑ በዓለም ላይ ትዳራቸውን ይዘው በእውነት ቢያቃኑ ቢሠሩና ቢቀመጡ ይህ ሁሉ አይጠፋም ነበር፡፡ በእውነቱ የምንኩስና ሥራ ከገዳም አለመውጣት ከሁከት ከጭቅጭቅ አለመግባት፣ ማስታረቅ፣ መጸለይ ነበር፡፡››
የአባቶቻችን አምላክ ልዑል እግዚአብሔር የብፁዕ አባታችንን ነፍስ ያሳርፍልን፡፡ቸር ወሬ ያሰማን፡፡አሜን፡፡

ሐመር መጽሔት ሐምሌ/ነሐሴ 1995 ዓ.ም 11 ዓመት ቁጥር 3 እና 4 እትም ላይ ከብፁዕነታቸው የንግግር ላኅይ ጋራ ለንባብ የበቃውን ቃለ ምልልስ ለትውስታ ያህል አቅርበንላችኋል፡፡መልካም ንባብ፡፡
ሐመር፡- ከካይሮ እዚህ/ኢየሩሳሌም/ በምን መጡ?
ብፁዕ አቡነ አብሳዲ፡- በአውሮፕላን መጣኹ፡፡ እዚህም እንደ መጣኹ ዴር ሡልጣን ማኅበር ገባሁ፡፡ ከዚያ ደረስኹ፤ እንግዲህ ዓመት ተቀመጥሁ፡፡ ልመናዬ ዓመት ኢየሩሳሌም ተቀምጬ ልመለስ የሚል ነበር፡፡ አሁን ልሄድ ብዬ ሳስብ አቡነ ፊልጶስ የሚባሉ ጳጳስ በአቡነ ባስልዮስ እና በጃንሆይ ፈቃድ በ1944 ዓ.ም ተሾመው መጡ፡፡ እኔ አንድ ዓመት ነው የምቀድማቸው፡፡ ገዳማቱ ሁሉ ተቀበላቸው፡፡ ትንሽ ብትረዳኝ ብትደግፈኝ፣ ይህ ገዳም ገና ነው፡፡ ሁለቱ ቁልፍ ያለ በግብጾች እጅ ነው፡፡ የቅዱስ ሚካኤልና የአርባዕቱ እንስሳን መግቢያ የትልቁንም በር ቁልፍ ግብጾች ናቸው የያዙ፡፡ ብቻ ይቺ በምሥራቅ ያለች በዐፄ ምኒልክ በ1906 ዓ.ም የተከፈተችው እርሷ ናት እንጂ ሌላው ዝግ ነው ብለው አማጠኑኝ፡፡
ለመሄድ ስነሣ አንድ የግብጽ ጳጳስ፣ ‹‹እንዴ እኛ አገራችሁን ስንገዛ ነበረ፡፡ አሁን ደግሞ ጳጳስ ብላችሁ እዚህ ትሰዳላችሁን? እንግዲህ እናንተን በእንግድነት የተቀበልናችሁ ናችሁና ውጡልን›› ብሎ ወደ ዳኛ ይከሰናል፡፡
ሐመር፡-የኢትዮጵያን መነኰሳት?
ብፁዕ አቡነ አብሳዲ፡- አዎ! አቀረበ፣ እኔ ልሄድ ስል፡፡ መነኰሳቱም ‹‹አይ ምነው፣ እንዲህ ባለ ክፉ ጊዜ ጥለኽን ትሄዳለህ? ዐረብኛ ቋንቋም ደኅና ትናገራለህና እባክህ ርዳን ልጃችን፤›› አሉኝ፡፡ ተሰብስበው ብዙ ሽማግሌዎች ነበሩ፡፡ ከ30 እስከ 60 ዓመት የተቀመጡ ብዙዎች ናቸው፡፡ ሁለት ሽማግሌዎች ነበሩ፡፡ ጥሩ አድርገው በብሩህ ገጽ ተቀብለውኝ ነበር፡፡ እነርሱ ናቸው ሰዉን ሁሉ ሰብስበው፣ ‹‹እንሹመው ገና ሳይሄድ፣ እንዲረዳን፤ ጠበቃም እናቆማለን፤ ውጡ ብለውናልና እንሟገታለን›› ብለው ተሰብስበው [እዚህ አባታችን ግቢ ማለት በአሮጌው የኢየሩሳሌም ክልል የሚገኝ፣ መምህር ወልደ ሰማዕት ቦታውን የገዙት ግቢ ነው] ስንመጣ፣ ‹‹ልጃችን ርዳን ደግፈን›› ብለው ለመኑኝ፡፡ እኔ ደግሞ አይ፣ አይሆንም አባቶቼ፤ እኔ ካገሬ ስወጣ ያረፍኹት ከግብጾች ነው፡፡ ሁለት ዓመት ተኩል በእንግድነት ተቀምጩ፣ እዚያ ቋንቋ አጥንቼ፣ በእጃቸው በልቼ አሁን እንዴት መልሼ እነርሱን እሟገታለሁ? ተመልሼ አገሬ እሄዳለሁ፤ ተዉኝ እባካችሁ አልኹ፡፡
አባ አብርሃም የሚባሉ ብሉይ የሚያውቁ ሊቅ ነበሩ፡፡ ሙሴ ያደረገውን አላወቅህም እንዴ ልጄ? አሉኝ፡፡ ሙሴ እዚያ ተወለደ፤ አደገ፤ ታዲያ ግብፃዊ እና ዕብራዊ ሲጣሉ ለማን ነው የረዳ? ለአንተ ከሙሴ በላይ ግብፆች ምን አድርገውልሃል አሉኝ፡፡ ሁሉም የግድ ያዙኝ፡፡ እንግዲህ እሺ አልኋቸው፡፡ እንግዲህ ከአዲስ አበባ ሰው እስክታመጡ ድረስ መንፈቅ ልቀመጥላችሁ፤ እኔ ጭቅጭቅ አልወድም፤ ለዚያ ላስተማርኹበት ገዳም አበምኔት ልሆን አቡነ ማርቆስ ተሾም ብለውኝ እምቢ ብዬ ነው የመጣኹ፡፡ እኔ ምንም አልፈልግም፡፡ እኔ ከመነኮስኹ ወዲያ ጭቅጭቅ ምን ያደርግልኛል ብዬ ነው የመጣኹት፡፡ አሁን ደግሞ እዚህ መጋቢነት የምትሉኝ ምንድን ነው? ብዬ ብዙ ተከራከርኋቸው፡፡ አይሆንም አሉኝ፡፡ እሺ፣ ለአንድ መንፈቅ ተቀመጥልን በኋላ ሰው ከአዲስ አበባ እናመጣለን አሉኝ፡፡
በኋላ መጋቢነቱን ተቀበልኹ፡፡ ከአቡነ ፊልጶስ ጋራ ተማከርንና ከሰስን፡፡ መነኮሳቱን ማስረጃ ስጡን ብለን ጠየቅን፡፡ ‹‹አይ፣ እኛ አንድ ነገር ስንጣላ አዲስ አበባ ነው የምንደውለው እንጂ እዚህ ይኑር አይኑር አናውቅም፤ ችግር ነው፤›› አሉን፡፡ ኑ! ክፈቱ ብለን ከዕቃ ቤት ገብተን ብንፈልግ፣ ብንል ብንል አንድ ትንሽ ነገር አገኘን እንጂ ምንም የለም፡፡ ‹‹በዐረቦች ፍ/ቤት ማስረጃው አለ፤›› አሉን፡፡
አንድ ዐረብ ተባበረንና ያን ማስረጃ አገኘን፡፡ እስራኤሎች መቼም እንደምታውቋቸው እንኳን የራሳቸውን የሌላ ዓለም የሚያውቁ ሰዎች ናቸው፡፡ አንድ ዶክተር ማንዲስ የሚባል አቡነ ፊልጶስን፣ አንተ አላቸው÷ አቤት÷ ‹‹ደጃዝማች መሸሻ እንግዲህ እርሳቸው መጥተው፣ ከዚህ አገር አስመስክረው የናንተ ነው አሰኝተው ሄደው ነበሩ፡፡ የሳቸው ማስረጃ የላችሁም፤›› አላቸው፡፡ ያችን ይሰሙና አቡነ ፊልጶስ ቀጥታ ወደ ጃንሆይ ሄዱ፡፡ ማስረጃው ተገኘ፡፡ ፎቶ አሥነስተው ሰጧቸው፡፡ እኔ ደግሞ ተቀብዬ ሐቢብ የተባለ ሳንጆርጅ የተማረ ትልቅ ዐዋቂ ጠበቃ ነው፡፡ እንካ ተርጉምልን ወደ ዐረቢኛ እና እንግሊዝኛ ብለነው እሱ ደግሞ ተርጉሞ ግማሹ በዐረቢኛ ነበረ፤ ግማሹ በቱርክ ነበረ፤ ግማሹ በፈረንሳይኛ ነበረ፤ ይህን ጥሩ አድርጎ ተረጎመልን፡፡
ይሄ አለን ብለን ወደ ዳኛ አቀረብን፡፡ ‹‹እንግዲህ ይሄ እያላችሁ ነው እንግዶች ናችሁ የሚሏችሁ; ይሄ ነው ነገሩ፡፡ ይሄማ የቆየ ነው ጠባችሁ፡፡ መቼ አዲስ ሆነና፡፡ ታዲያ ምንድን ነው እንግዶች ናችሁ ውጡ የሚሏችሁ›› ብሎ ዳኛው ተገረመ፡፡
·ረ ጌታዬ፣ ዝም ብለው ዋሽተው ነው እንጂ ያሉበት ገዳም የኛ ነው! በ1838 ዓ.ም ቁልፉን ሰርቀው ወስደውት እንጂ የኛ ነው፡፡ ያስጠጋነው ሰው ነው የወረሰን፡፡ የሃይማኖት ወገናችሁ ነኝ ብሎ ገብቶ የጠማረ ሰው ነው፤ ቱርክም ያውቃል፡፡ እርሱ ነው የወረሰን፡፡ እርሱ ወደ እኛ ከተጠጋ በኋላ ቀይ ባሕር ተዘጋ፡፡ ከዚህ የኛ ሰዎች እንዳይመጡ ባገራችን ዘመነ መሳፍንት ነው፡፡ ወዲያም መንገዱ ሁሉ ችግር ነው፡፡ ከዚህ ያሉትም ሞተው አለቁ፡፡ ያን ጊዜ ይህ ግብጻዊ ደብዳቤ ጽፎ ክፍት ቦታ አለ ብሎ ለእስክንድርያ ጳጳስ ሰደደለት፡፡
በየዓመቱ ስመው ከመመለስ በቀር ግብጾች በዚህ በጎልጎታ ቦታ የላቸውም ነበር፡፡ በኋላ ብዙ ግብጾች ተሰብስበው መጡና ቱርክን እጅ አድርገው የኛን መነኮሳት አባረሯቸው፡፡ አምስት ቀርተው ነበር፡፡ ቤቱን እናጽዳ ብለው ማስረጃውን ሁሉ አቃጠሉት፡፡ የኛን ገዳም አፍርሰው እንዴት ያለ ትልቅ ሳሎን ቤት አሠሩ፡፡ እኒያን አምስት መነኮሳት አስወጥተው በአንድ ቦታ አስቀምጠዋቸው ነበር፡፡ እንደገና አሁን ትንሽ ቆየት ብሎ፣ ኑ ውጡ! ከዚህ ውረዱ ብለው አባረሯቸው፡፡ ወጥተው ቢቸግራቸው የት እንገባለን ብለው እዚያው አፈር ቆፍረው እንደምንም ብለው ትንንሽ ጎጆ አበጅተው ከወዲያም ሰው መጥቶ ረዳቸው፡፡ እንዲያ አድርገው ሠርተው ቁጭ አሉ፡፡ አሁን ያለንበትን እንዲህ አድርገው ነው የወረሱት፡፡
እኛ ምስክር ስናቀርብ እነርሱ ይሸሹ ጀመር፡፡ ነገ ተነገ ወዲያ ይሉ ጀመር፡፡ እንደምታውቁት ግርግር ነበር፡፡ እንዲያ እንዲያ እያለ ዐሥር ዓመት ተሟገትን፡፡ ዐሥር ዓመት ጠበቃ አቆምን፡፡ የነሱ ጠበቃ በቀጠሮ በአንድ ሁከት በአንድ ነገር እያመካኘ በመጨረሻ ለኛ ‹‹ገዳሙ የነርሱ ነው›› የሚል ፍርድ አገኘን፡፡ ቁልፋቸውን እንዲያገኙ የተዘጋ ቤተ ክርስቲያናቸውን እንዲወስዱ መነኩሴውም ወጥቶ እንዲሄድ ብሎ የጆርዳን መንግሥት ፈረደልን፡፡
በዚህ ደስ ብሎን እልል ተቀብለን ስናበቃ እንደገና ናስር መጥቶ፣ ‹‹ለምን እንደዚህ ታደርጋለህ፤ ለኔ ከግዛቴ በታች አይደለምን; ሰዎቼን ለምን ታሳዝናቸዋለህ; የኛን ማስረጃ ሰብስበን እስክናመጣ ድረስ እንዳለ ይቆይ›› ብሎት ዝም ብሎ ቆይቶ ነበር፡፡ በኋላ ጆርዳን ለቆ እስራኤል አገሩን ያዘው፡፡ እስራኤሎች ደግሞ ቀጥለው፣ ‹‹አይ፣ እንግዲህ እንዲህ አርጋ የጆርዳን መንግሥት ከሰጠቻችሁ እኛ ደግሞ በፖሊቲካ እንጠቀማለን፤›› ብለው ከውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ሰው ልከው ወደ አዲስ አበባ ሄዱ፡፡ ከጃንሆይም ከቤተ ክህነትም ተገናኝተው፣ ‹‹እኛ በፍርድ እንስጣችሁና እናንተ አምባሳደር እዚህ ንግሥት ቤት ኢየሩሳሌም አቁሙልን፤›› አሉ፡፡
የኛ ቤተ መንግሥትም መክረው፣ ‹‹አይ፣ ደሞ ከዐረብ መንግሥታት እንጣላለን፤ መንገድም ይከለክለናል›› በሚል ለጊዜው ‹‹አምባሳደር አናቆምም ባይሆን ከቤተ ክህነት ተወካይ እናቆማለን›› አሏቸው፡፡ እግዚአብሔር ያላለው አይሆንም እንጂ ነገሩ እንኳ ምንም አልነበረም፡፡ ቤተ ክህነት እና ቤተ መንግሥት ምን ልዩነት አለው; እነዚህማ ከሄዱ መንግሥት ተቀበለ አይደለም! ቁልፉን እዚያ ያሉት ኤጲስ ቆጶስ ይቀበሉት እንጂ የቤተ ክህነት ወኪል አይሂድ ብለው አስቀሯቸው፡፡ እስራኤላውያንም እነዚህ ሰዎች ለካ የሚጠቅሙ አይደሉም ብለው ይሄ ከሆነስ እንግዲህ እናንተ በገዛ ራሳችሁ ውሰዱና እኛ ነን የወሰድን በሉ፡፡ እኛ ደግሞ ዝም ብለን እናያችኋለን አሉን፡፡
ይሆናል አይሆንም ተጣላን፤ ሁላችን አልተስማማንም፤ እንቀበል እንቀበል የሚል በዛ፤ እንግዲህ ከኢየሩሳሌም ድርጅት እነ አቶ መኮንን ዘውዴ ነበሩ፡፡ የንቡረ እድ ድሜጥሮስ ልጅ እዚህ ጄኔራል ቆንሲል ነበረ መጣ፡፡ ተቀበሉ ተብላችኋልና ዝም ብላችሁ ተቀበሉ ተባለ፡፡ ግብጾቹ እንግዲህ ከፍተው ወደዚያ ሲሄዱ እስራኤሎቹ ቁልፉን ለውጠው ሰጡን፡፡ እነሱ ሆ ብለው ተነሡ፡፡ ያልደረሱበት የለም፡፡ የእስላም ወገን ወደሆነ ዐረብ ሁሉ፣ ‹‹·ረ ባካችሁ ረዳት አድርጉልን›› ብለው ጮኹ፡፡ ከአዲስ አበባ አምስት የሚሆኑ ሰዎች ክቡር ዘበኞች የነበሩ ሲቪል አድርገው ሰደውልን ከኛ ጋራ አብረው ቦታውን እየጠበቁ በመጠኑ ነገሩ እየረጋ ሄደ፡፡ በኋላ ተመልሰው መጥተው ከእስራኤል ከሰሱን፡፡ ከታላቁ ፍ/ቤት ሄደው መዝጊያችንን ሰብረው ሰርቀው በጉልበት በእናንተ ዘመን በእናንተ መንግሥት ተጠቅተናል ሲሏቸው መንግሥት እንግዲህ ስለኛም ስለነሱም ጠበቃ አቆመ፡፡ ብዙ ተሟግተዋል፡፡
እንግዲህ ከፍተኛው ፍ/ቤት ምን አሉ፤ የእስራኤል መንግሥት ነገሩን አጣርቶ ያምጣ፡፡ እስከዚያው ድረስ ግን ኢትዮጵያውያን ቁልፉን እንደያዙት ይቆይ፡፡ አርባ ቀን ለመንግሥት ሰጥተነዋል ብለው ሰጡት፡፡ በአርባ ቀኑ ተሰብስበው፣ ‹‹ብዙ የቆየ ነገር ነው፤ እኛ ላሁኑ ልንጨርሰው ስላልቻልን ለጊዜው ቀጠሮ እናድርግለት ብለው ሌላ ቀጠሮ ይዘው በዚህ ዐይነት ሰነበተ፡፡ ነገ ተነገ ወዲያ እያልን ቆየን፡፡ በዚህ ዐይነት ሠላሳ ሦስት ዓመት ተቀምጠናል፡፡ በዚህ ላይ እስከ አሁን ድረስ የማይሠሩት የማያደርጉት ነገር የለም፡፡
ሐመር፡- እርስዎ ለመንፈቅ ብለው ነበርኮ ቃል የገቡት፤ ሙግቱ ደግሞ ብዙ ዘመን ፈጀ፡፡
ብፁዕ አቡነ አባሳዲ፡- እኔማ ነገ ስል ነገ ስል ይኸውልህ ኻያ ዓመት ተቀመጥኹ፡፡ እዚህ መጀመሪያ የነበሩ ጳጳስ አዲስ አበባ ከተመለሱ በኋላ ተጠርቼ ነበር፡፡ አምባሳደሩ ጠሩኝና የመጣውን ወረቀት አሳዩኝ፡፡ ይምጡና ሓላፊ ይኹኑ የሚል ነው፡፡ አይ! እዚህ ባለሁበት ሓላፊነቴ ነፍሴ ልትወጣ ነው፡፡ በዚህ ቦታ ብዙ ደከምን፤ እና አሁን ብዙ ደክሞኛል ሌላ ይምጣ እንጂ እኔ አልችልም አልኹ፡፡ ‹‹ተዉ እንዳያዝኑ በደከሙበት ቦታ›› አሉኝ፡፡ ·ረ ዐሥር ሰው ይምጣ ግዴለም አልኹ፡፡ ይሄ እንደ ትንቢት ነው፡፡ እኚህ አባታችን/ቃለ ምልልሱ በተደረገበት ወቅት የነበሩት ሊቀ ጳጳስ ብፁዕ አቡነ ቀውስጦስ/ ዘጠነኛ ናቸው፡፡

ሐመር፡- እና በቃ እዚሁ ቀሩ ማለት ነው
ብፁዕ አቡነ አብሳዲ፡- እንዴ! ገባሁበታ፤ ተያያዝን፤ አዘንኹ፤ እንዲያው ሥራውን ግብሩን ጠበቃው ሲነግረን እንኳን ውኃ ደም ያስለቅሳል - ግብራቸው፡፡ ራሳቸው የጻፉትን ነው የምልህ፡፡ እንዴት አድርገው እንደ መጡ፣ እንዴት አድርገው መነኮሳቱን እንዳወጧቸው ራሳቸው ጽፈውታል፡፡ በራሳቸው መጽሐፍ፡፡
ሐመር፡- አሁን ያ መጽሐፍ አለን
ብፁዕ አቡነ አብሳዲ፡- አዎ! ዕቃ ቤት አለ፡፡ አንድ ወዳጅ ነበረንና ሰጠን፡፡ ይኸው እንደዚህ አድርገው በዐረብኛ፣ በፈረንሳይኛ ቋንቋዎች ነው የጻፉት፡፡ እኔም ልቤ ሁሉን ነገር ረሳው፡፡ ተውኹትና እዚሁ ተጠመድኹ፡፡ ምን ·ረ ነፍሴን ላጣ ነበር ስንት ጭንቅና ችግር ነበረ፡፡
ሐመር፡- እስኪ ይንገሩኝ ምን ችግር ነበር
ብፁዕ አቡነ አብሳዲ፡- ·ረ እመቤቴ! አንደኛ እነርሱ ቋንቋቸው ንግግራቸው ዐረብኛ ነበር፡፡ ዐረቦች ደግሞ ለእነርሱ ያደላሉ፡፡ የጆርዳን መንግሥት እና ሕዝቡ እኛን ይወዱ ነበር፡፡ የኢትዮጵያን መንግሥት ይወዱን ነበረ፡፡ ደኅና ናቸው፡፡ የዚህ የፓለስታየን ሰዎች ግን ተንኮለኞች ናቸው፡፡ እዚህ ሀገር ግዛት ይሾሙ የነበሩ ርጉማን ናቸው፡፡
እንዴ! አንድ ጊዜማ ትልቅ ሀብታም ሰው ነው፤ ጳጳስ እሆናለሁ ብሎ የመነኮሰ ግብፃዊ ነው፡፡ እዚህ መጥቶ ከጳጳስ በታች ሆኖ ያገለግላል፡፡ ይሄ ቦታ/ዴር ሡልጣንን ማለታቸው ነው/ እንደምታውቁት አሳደስነው እንጂ አንድ መቶ ዓመት የተቀመጠ የመቃብር ቦታ ነበር የሚመስል፡፡ ለጤና ጥበቃ ሄደን አቤት ብለን ጮኸን ሓላፊው መጥቶ አይቶ ወሰነልን፡፡ ያ ግብፃዊ እንዴት ይታደሳል ብሎ ሞገተን፡፡ ያን ቦታኮ ባይታደስ ኑሮ ሰው ሲያልፍ አፍንጫውን ይዞ ነበር የሚያልፍ፡፡ ያን ሁሉ ብዙ ደክመን ብዙ አስጠርገን አጸዳነው፡፡ በዚህ በጣም ተናደደ፡፡
ሐመር፡- ድሮ ውኃም አልነበረ ይባላል
ብፁዕ አቡነ አብሳዲ፡- አዎ፣ ውኃም አልነበረ፤ እንደ እግዜር ፈቃድ ውኃም ጮኸን ነው ያስገባነው፡፡ እምቢ ተብሎ ተከልክሎ፡፡ ያ ጠበቃችን የነበረ አምባሳደር ሆኖ ተሾሞ ነበረ፡፡ ከምስር ተነሥቶ መጣ፡፡ ጠራኝና ዛሬ ውኃና መብራት ላስገባላችሁ ነው ቶሎ ጻፍ አለኝ፡፡ ሌላ ጠበቃ ነበር የሚጽፍልን፡፡ እንዲህ እንዲህ አድርገህ ጻፍ አልኹት፤ ጻፈ፡፡ በግድ መብራት አገኘን፡፡ መብራት እንዳይገባልን ለውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር እና ለጠቅላይ ሚኒስቴር ግብጾች ክስ ያቀረቡበትን ደብዳቤ አሳየኝ፡፡
ከዚህ በኋላ ከመንግሥት ከፍተኛ ፍ/ቤት ሄደው መብራት እና ውኃ አስገቡ ብለው ከሰሱን፡፡ በአሁኑ ጊዜ መብራት እና ውኃ ይከለከላል እንዴ! ያ አምባሳደር የሆነው የቀድሞ ጠበቃችን ጥሩ ጠበቃ ተክቶልን ነበር፡፡ አሁን ይሙት ይኑር አላውቅም፡፡ ዐረብ ስለሆነ እስራኤል ከያዙት አልቀመጥም ብሎ ወደ ኦማን ሄደ፡፡ ‹‹መብራት እና ውኃ አይከለከልም›› ብሎ ዳኛው ፈረደልን፡፡
ይሄ መብራት ሰንካላ ነው፡፡ ለውጡልን ኤንጂን እንኳ አድርጉልን ብንላቸው እስራኤላውያን ዛሬ ሌላ ጥቅም ፈልገው እምቢ አሉን፡፡ አንድ አገር ግዛት የነበረ ትልቅ ሰው የንጉሥ ሑሴን ዘመድ ነው፡፡ ከመካ መጥቶ እዚህ ተሾመ፡፡ ሦስት አራት ጊዜ ተመላልሼ ሄጄ ውኃ የለንም አስገባልን ብዬ ነገርኹት፡፡ እንግዲያስ ከውጭ ወስዳችሁ እዚያች እበር ላይ ይተከልላቸው ብሎ ፈቀደልን፡፡ ወጥቶ ከገዳሙ በር ተተከለ፡፡ ከዚያ እያዋልን እያደርን እየሳብን ወደ ውስጥ አስገባነው፡፡ እንዲህ እንዲህ አድርገን እየዋለ እያደረ እንዲህ ገዳም ያለ ሰው እንመስላለን እንጂ ‹‹ምንድን ናቸው እኒህ አራዊተ ገዳም፤ ጉድጓድ ውስጥ ተቀምጠው›› ይሉን ነበር፡፡
ሐመር፡- ከብፁዕ አቡነ ፊልጶስ ጋራ ብዙ ዓመት አብረው ሠርተዋል፤ የማይረሳዎት ጠባያቸው ምንድን ነው
ብፁዕ አቡነ አብሳዲ፡- መድኃኔዓለም! ኀይለኛ ነበሩ፡፡ ልነግርህ ነኝ፡፡ የፓለስታየን ሰዎች እርሳቸውን ሲያዩ፣ ‹‹ይሄ ግብጽ ነውን›› ይሉኛል፡፡ የለም ሐበሻ ነው እላቸዋለኹ፤ ሐበሻ እንደዚህ ያለ አለ እንዴ ይሉኛል፡፡ እንዴ! ከዚህ የበለጠ አለ አይደለም እንዴ! ስላቸው ይሥቃሉ፡፡ አቡነ ፊልጶስ ኀይለኛ ብርቱ ጎበዝ ነበሩ፤ እንዲያውም ቆይተው ቢሆን ብዙ ነገር የምንሠራው ነበር፡፡ ብዙ እንሠራ ነበር፡፡ አባ ማቴዎስም ጥሩ ጎበዝ ነበሩ፡፡ ከእርሳቸው ጋራ አምስት ዓመት ሠርቻለሁ፡፡ ሠላሳ ዓመት ነው መጋቤ ከሆንኩ ይኸውልህ፡፡ ተመልሰው ሄዱ፡፡ ሁለተኛም መጡ ያኔም መጋቢ ነበርኩ፡፡ ጎበዝ ናቸው፤ መንገድ ያውቃሉ፤ ስልት ያውቃሉ፤ ትዕግሥትም አላቸው፡፡ በኋላ ብዙ ሳይሠሩ ከዚህ ሄዱ፡፡
ሐመር፡- ግብጾች ግን ትንሣኤ በዓል ስታከብሩ ድንጋይ ይወረውሩ ነበር ይባላል
ብፁዕ አቡነ አብሳዲ፡- አዎ÷ ይወረውሩ ነበር፡፡ በዘመኔ ግን ከዘንድሮ በቀር ተመተን አናውቅም ነበር፡፡ ዘንድሮ ተመታን፡፡ እንሞታለን እንጂ ተመትተን አናውቅም ነበር፡፡ እነርሱ ክፉዎች ጨካኞች ናቸው፡፡ የፈርዖን ዘር የፈርዖን ደም ነው እንዲህ ያደረጋቸው፡፡
አንድ ትልቅ ሰው ነበረ፤ ብዙ ዓመት ኢየሩሳሌም የተቀመጠ፤ ከድሮ ጀምሮ ታሪክ የሚያውቅ ነው፡፡ ዕድሜው ዘጠና ይሆናል፡፡ ራይስ/በኢየሩሳሌም የገዳማት አለቆች መጠርያ/ ይሾማል፤ ይሻራል፡፡ አባ ሐና ይሉታል፡፡ ከግብጾች ጋራ በተጣላን ቀን አንድ የሙስሊሞች መምህር መጣ፡፡ አቡዲስ ይባላል፡፡ ልጁ እዚህ የግብጾች ገዳም ይማር ነበርና፣ ሰይዳ ለምንድር ነው ከሐበሻ የምትጣሉት፤ አለው፡፡ አንድ ሃይማኖት ነው የምትባሉት እና ይህ ነገር ለምንድን ነው፤ ምንስ ያጣላችኋል አለው፡፡
ሰማህ! አለው ያ ሽማግሌ ግብጻዊ ‹‹እኔ እንግዲህ መቃብሬ የተማሰ ልጤ የተራሰ ሰው ነኝ፡፡ እውነት ልንገርህ አይደለ፡፡ የነርሱን ቦታ ፈልገን እንዳይመስልህ፤ ዝም ካልናቸው ኀይል አግኝተው ከዚህ ካለንበት እንዳይመጡብን ነው የምንደክመው፡፡ ከዚያ ካሉ ልንመልሳቸው እንጂ እዚያ ጤና ካገኙ እዚህ ደግሞ ሊያነሡብን ነው አይሆንም ብለን ነው እንጂ መሬታቸው ነው፡፡ ግን ይዘነዋል፡፡ አርባ ዓመት አለፈ፡፡ ከያዝነው በኋላ ዛሬ የት እንሄዳለን ብለህ ነው አለኝ ብሎ ያ አስተማሪ ነገረኝ፡፡ አንተ ለካ እውነቱን ነው፡፡ እናንተ ደግሞ ጥቋቁሮች ስለሆናችሁ መደባደብና ድንጋይ መወርወር ትችላላችሁ እየተባለ በእናንተ ላይ ነበር የምንፈርደው፡፡ ለካስ ተጠቅታችሁ ነበረ ብሎ አለኝ፡፡ ራሱ አቡነ ሐና ራይስ ነገረኝ፡፡ ለካስ እውነታችሁ ነው፣ ለካ ይሄ ቦታ የራሳችሁ ነው ብሎ አጫወተኝ፡፡
ሐመር፡- ሌሎቹ ምን ይላሉ፤ ለምሳሌ ግሪኮቹ፣ አርመኖቹ…
ብፁዕ አቡነ አብሳዲ፡- ቱርኮቹ አገሩን እንደያዙ ያ ሰውዬ በ1840 ዓ.ም መጣ፡፡ ኢብራሂም ጀውሃሪ የሚባል ነው፡፡ የተማረ ሰው ነው፡፡ ቱርክ ያውቃል፡፡ አንድ አራት አምስት ሠራተኞች አሉት፡፡ ኢየሩሳሌምን ዙሮ ዙሮ ቦታ አጣ፡፡ ወደኛ መጣና እባካችሁ የሃይማኖት ዘመዳችሁ ነኝ አላቸው፡፡ ደሞ እኛ አንድ ነገር ልንገርህ፤ እኔ ትርጉሙ አይገባኝም እንጂ ፈረንጅ እንወዳለን፡፡ ወንድማችንን አንወድም እንጂ ፈረንጅ ያየን እንደሆነ እንዲያውም ከቶ ጽሕሙን እንደ አባቴ ገብረ መንፈስ ቅዱስ አስመስሎ እንደዚህ ብቅ ያለ እንደሆነ እንዴ ምን እነግርሃለኹ፤ የመንግሥተ ሰማያት መክፈቻ የያዘ ነው የምናደርገው፡፡ እና ታዲያ ያን ግብጻዊ አስገቡት፡፡ ይሄ ሰውዬ ቆየና ሰው አጣ፡፡ የሚተካ ሰው በዚያ ሲጠፋ ግብጾችን እንዲህ ያለ ቦታ አግኝቻለሁ ጳጳስ ስደዱ ብሏቸው ጳጳስ አምጥቶ ነው ያስረከባቸው፡፡
እንግዲህ ጎልጎታ ውስጥ የነበረ ግሪክ በሞላው ከዚህ ከስቅለት ቦታ የነበረ ከጌታ መቃብር ከዚህ መብራት ከሚወጣበት የነበረንን ንዋያተ ቅድሳት እርሱን ሙልጭ አድርገው ሞሰበ ወርቅ፣ ወርቅ፣ ከበሮ፣ ጸናጽል፣ የጥንት ዘውድም አክሊል ያን ሁሉ መጻሕፍት ግልብጥብጥ አድርገው ማርሻ የሚባል ገደል አለ ወደዚህ ወደ ሎጥ መንገድ፤ በሰሌን ጠቅልለው ገዳም ደበቁት፡፡
ከግሪኮች የጠረፈውን ደግሞ አርመን ወሰደ፡፡ እንዴት ቀንቷቸው መስሎሃል፡፡ አርመኖች የቱርክ ቅኝ ስለነበሩ እዚህ ወታደር ሆነው መጥተዋል፡፡ ኢየሩሳሌምን ቱርክ ሲይዛት የቱርክ ወታደር ሆነው ዐረቡን ሌላውንም ሰው እየገረፉ እያስወጡ ሂድ ውጣ እያሉ እነዚያ ሰዎቻቸውን አምጥተው ግጥም አድርገው ሞሏቸው፡፡ ብዙ ቦታ በኀይል ነጥቀው ወሰዱ፡፡ ግብፅም የቱርክ ቅኝ ስለነበሩ ብዙ ግብጻውያን የቱርክ ወታደር ሆነው መጥተዋል፡፡ እነርሱ እኒህን ሁለት አብያተ ክርስቲያን ከቅዱስ ሚካኤልና ከአርባዕቱ እንስሳ ጀምሮ እስከዚያ ያለውን ወሰዱ፡፡
አንድ ጊዜ አንዱ አርመን ሁለቱ ቤተ መቅደሶች ሲፈረዱልን እንኳን ደስ አለህ አትለኝም አልኹት፡፡ እንዴት እንኳን ደስ አለህ አትለኝም አልኹት፡፡ እንዴት እንኳን ደስ አለህ እልሃለሁ፤ ነገ ጠዋት ወደኔ ልትመጣ አይደለህምን አለኝ፡፡
ጎልዳማየር የምትባል የእስራኤል ጠቅላይ ሚኒስቴር እዚህ መጥታ ሳለች ሦስት ሊቃነ ጳጳሳት ከርሷ ሄደው ለግብጽ ነው የደገፉት፡፡ እኛ ወደ እነርሱ እንዳንደርስ ነው ፍራቻው፡፡ እንግዲህ ስለዚህ የደረሰው ቢደርስ ለግብጽ ነው የሚደግፉት፡፡
ሐመር፡- በዚያ ጊዜ ስታትስኮ የሚባል አልነበረም እንዴ
ብፁዕ አቡነ አብሳዲ፡- ወዴት ነበር ያኔ
ሐመር፡- ቆይ መቼ ነው እርሱ ሕግ የወጣው
ብፁዕ አቡነ አብሳዲ፡- ስታትስኮማ እንደዚህ ነው፡፡ ፈረንጆች በቅድስት ሀገር ርስት አልነበራቸውም፡፡ የያዙትን ቱርክ አስለቅቋቸው ነበር፡፡ ጣሊኖች መጡና ገንዘብ እየሰጡ ተ/ቤት ከፈቱ፡፡ በብላሽ ትምህርት እንሰጣለን አሉ፡፡ ቤትም እየገዙ መስጠት ጀመሩ፡፡ በዚህ ብዙ ሕዝብ አገኙ፡፡ ብዙ ሕዝብ አገኙና ጎልጎታ ውስጥ ገቡ፡፡ መሬት ውስጥ ለውስጥ ሕንጻ እየሠሩ እዚህ ላይ ጌታ የተሰቀለበት ቦታ ላይ አይታችሁ እንደሆነ የእመቤታችን ሥዕል አለች፡፡ በዚህ በኩል ወደ ላይ ሊወጡ ሲሉ ግሪክና አርመን አትወጡም አናስወጣም አሏቸው፡፡ ሲደባደቡ አንድ ትልቅ ሰው ከጀርመን አንድ ትልቅ ሰው ከፈረንሳይ መጥተው ያያሉ፡፡ ጣልያኑን አንተ ምንድን ነው የምትደባደቡ፤ ቢሉት ‹‹ደግሞ ምዕራባውያን ደግሞ ከዚህ ምን አላችሁ፤ ከዚህ ጎልጎታ የኛ ነው እንጂ እናንተ ርስት የላችሁም ብለውናል›› አላቸው፡፡ እናንተን ከዚህ ለማስወጣት ነውን፤ አዎን፤ በሉ ቆዩ፤ አይዟችሁ በርቱ በቅርብ ጊዜ እንረዳችኋለን አሏቸው፡፡ ይሄዱና ፓሪስ ላይ ስብሰባ ያደርጋሉ፡፡
ሐመር፡- መቼ
ብፁዕ አቡነ አብሳዲ፡- በ1856፡፡ ምን እናድርግ፤ ሕግ እናውጣ፤ ሕግ እናርቅቅ ይባባላሉ፡፡ ሕግ አውጥው አርቅቀው በርሊን ይሄዱና በ1878 ደግሞ ያጸድቁታል፡፡ ሁሉም የያዘውን እንደያዘ ይኑር የሚባል ሕግ አውጥው ይስማማሉ፡፡ ለቱርክ ወስደው ይህን ቅዱስ ቦታ በዚህ አስተዳድሩ ብለው ይሰጧቸዋል፡፡ አብ አልሐሚድ የሚባል ንጉሥ ተቀብሎ ‹‹በያላችሁበት ቁሙ፤ አንዱ ወደ አንዱ እንዳይመጣ›› ብሎ ያውጃል፡፡ ወደፊት የዓለም መንግሥታት ዳኛ አቁመን መርምረን አንድ ነገር እስከምናይ ድረስ አንድ ነገር እንዳይሠራ፤ አንድ ነገር እንዳይፈርስ አንድ ነገር ካለበት እንዳይነሣ፤ በዚህ ተጠባቂ ሆኖ ስታትስኮ ብለው አስቀመጡብን፡፡
                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                               
9 comments:

Anonymous said...

egiziabehere nefesachewen yemare

ማህበረ፡ክርስቲያን said...

አባታችን፡ለአገሮና፡ለሃይማኖቶ፡የለፉትን፡አምላክ፡ ይክፈሎት፡፡
እነዚህ፡ናቸው፡ታዲያ፡እህት፡ቤተ፡ክርስትያን፡የሚባሉት፡ምናችን፡ተገናኝቶ፡፡ለመሆኑ፡የሀገሬ፡መምህራን፡ሁላችሁም፡ባትሆኑ፡ብዙዎች፡እነኚህን፡ነው፡በምሳሌነት፡እየጠቀሳችሁ፡የምታስተምሩት፡፡እነሱ፡እኮ፡አሁንም፡አላቆሙም፡ እየወጉን፡ነው፡፡ኢየሩሳሌም፡ስራቸውን፡እየሰሩ፡አውሮፓና፡አሜሪካ፡ወዳጅ፡ለመምሰል፡ይሞክራሉ፡፡በጣም፡የሚያናድደው፡ደሞ፡ከእስላሞች፡ጋራ፡እየተባበሩ፡እኛን፡ማጥቃታቸው፡፡የኢትዮጵያ፡አምላክ፡ይፍረድ፡ሌላ፡ምን፡ይባላል፡፡

Anonymous said...

cheru medhniyalem nefsotn begnat yanurew.wedfit manyukerakeryuhon endsachew?

asbet dngl said...

በቅድሜያ “ነፍስ ይማር” ለኛ ለልጆቻቸው ታሪክ ለማቆየት ሲሉ ለደከሙልን : ለወጡልን : ለወረዱልን : አባታችን::
ከዚህ ቀጥየ ለማሳሰብ የምወደው ግን ይህ ቀደም ሲል የተነበበው ታሪክ በኢየሩሳሊም ደብረ ሶልጣን ሊከሰት የቻለው እኛ ኢትዩጵያን በእምነት ጠንካሮች ስንሆን በትምህርት ግን ወደሃላ በመጓተታችን ምክንያት የራሳችን ችግር የፈጠረብን ነው በየ አምናለሁ:: እንኳንስ የእህተ በተክርስቲያን የተባሉት ይቅርና በሰው ሰውኛው ቢታይ ወንድም እህትህን እንኳን እደረሱበት እግር በግር ካልደረስክ ነጥቀውህ ለመሂድ ወደ ሃላ አይሉም:: በኒ አመለካከት የእህትበተክርስትያንን መኩነኑ እንዳለ ሁኖ : እንደማህበረ ቅዱሳን ያለ ምእመን በተክርስቴያናችን በብዛትና በጥራት እንድታፈራ ማበረታታትና : እኛም ምእመናን “ሕዝቢ ባለማወቅ ጠፋ” እንዳይሆን እራሳችንን ለወንጌሉ በማስገዛት በተጨማሪም ግዚው የሰጠንን ትምህርት እንደየችሎታች ካጐለመስን መሪቱም: ቤቱም: ታሪኩም: አሁንም እጃችን ጋ ነው ያለ:: የኢትዩጵያ ላእላዊነት የገባቸውና ታሪኩዋን ጠንቅቀው ያሚያውቁ አባቶች ሙተው ሳያልቁ ይልቅስ የታሪክ ተረካቢ የነገ ባላደራ መሆናችንን በመገንዘብ በተለይ እየሩሳሊም ኖዋሪ ኢትዩጵያውያን ለዚሁ ጉዳይ ያገባኛል በማለት ከአባቶች ጉን በመሰለፍ ከሚታገሉት ካሉት በማተብና በአገር መሰል ወንድም እህቶቻችን ጋር የሚያገናኝ መሥመር (Network) ቢዘረጋ ጉዳዩ ከፍጻሚ ለማድረስ ከአሁን የተሻለ ጊዜ የለም:: ሰለዚህ እባካችሁ ያለፈውን እንደ ታሪክ እንዘግበውና አሁን ያለነው ትውልድ ማየት ማመን ነውና አቅማችን የቻለ ቅድስት እየሩሳሊም ድረስ በመሂድ : ያልቻለ ሊላ ነገር ለማየት ከሚያሳልፈው ግዚውን ቀነስ በማድረግ በኢንተርኔት በመመልከት : አልያም በፀለት በመትጋት ታሪካዌ ገዳማችንን ሙሉ ለሙሉ እናስመልስ:: አሜን

Anonymous said...

May the holy father's spirit rest, today was the day (yekatit kidanemeret) they baptized me in Jerusalem Kidane Meret Gedam. May their holiness come to us.

መላኩ said...

ያሳዝናል፣ ያስደስታልም፡ ቸሩ እግዚአብሔር የሚቀጥለው ጎዳናቸውን ከመላዕክት ጋር ሆነው እንዲጓዙ ያድርግላቸው።

በዚህች ምድል ላይ ይህን ያህል ኃብታም የሆነ የኑሮ ልምድ መጎናጸፋቸው ምን ያህል ባለፀጋ ቢሆኑ ነው፡ በጣም ያስደስታል። ከዚህ ልምድ መማሩ አሁን የኛ ፈንታ ነው።

ከቃለምልልሱ እንደምንረዳው ላለፉት 40፣ 50 ዓመታት አገራችን ኢትዮጵያ ምን ያህል መሃል ሠፋሪነት የተሞላበት ፖለቲካ ትከተል እንደነበረ ነው። ጠላቶች የሆኑትን አረቦች እና ቱርኮች ለማስደሰት ሲባል በእስራኤል ኢምባሲ መክፈት አልተፈለገም፡ ምን አተረፍን? ቀዳማዊ ኃ/ሥላሴ በጭካኔ መልክ ከሥልጣን ተወገዱ፡ ኤርትራውያን ከእናት አገራቸው ራቁ እህቶቻችንም ለርጉም አረብ ነፍሳቸውን እንዲሸጡ ተደረጉ። እነዚህን ጨካኞች የሚያገለግልና ለነሱ ወገኑን አሳልፎ የሚሰጥ የኚህ መሰሉ አባቶች እርግማን ይደርሰዋል፡ ለዚህ እርግጠኛ እንሁን።

Anonymous said...

ነፍሳቸዉን ከቀደሙት ቅዱሳን አባቶች ጋር ያኑርልን።

Anonymous said...

ያባቶቻችን አምላክ ነፍሳቸውን ይማርልን።ግን ግራ የሚገባኝ በሃይማኖታችን ብዙ ምእመናንና ምእመናት በፀበልና በተጨምራት እየተፈወሱ ምነው ብፁአን የሚባሉቱ የሆስፒታል ደንበኞች ሆኑሳ የሚነግረኝ ባገኘሁ? ደግሞም እኮ አይድኑም ።

Anonymous said...

Please, I am just interested in knowing more about "der sultan" ..... can anybody suggest something to read

Blog Archive

የአቡነ ጳውሎስ "ሐውልተ ስምዕ"

ነጻ ፓትርያርክ ምርጫ ቢሆን ኖሮ ማንን ይመርጡ ነበር? እንበልና ሁሉም ነገር ሥርዓቱን ጠብቆ የተከናወነ የእጩዎች ምርጫ ቢሆን ኖሮ፣ አሁን የምናነሣቸው ጉድለቶች ባይኖሩ ኖሮ፣ 6ኛው ፓትርያርክ እንዲሆን የምትመርጡት ማንን ነበር? (ማሳሰቢያ፦ አሁን ያለው ክፍፍል እና የመንግሥት ተጽዕኖ ባይኖር ኖሮ ተብሎ የሚመለስ ጥያቄ ነው። የምን “ባይኖር ኖሮ ነው” የሚል አስተያየት ካለዎትም እናከብራለን።)