January 19, 2012

የጥምቀት ልጆች ለበዓሉ ድምቀት በሥራ ላይ ናቸው:: Timket Preparation 2004 EC


 . ለአየካባቢያቸው ጸጥታ ሓላፊነት እንዲወስዱ ተደርገዋል::
. ጥምቀት - አንቀጸ ሃይማኖት(የድኅነት መግቢያ በር)::
(ደጀ ሰላም፣ ጥር 9/2004 ዓ.ም፤ January 18/2012/ READ THIS ARTICLE IN PDF.)፦ በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ልደት እና ጥምቀት በየዓመቱ በፍጹም መንፈሳዊ አስተሳሰብና በደማቅ ሥነ ሥርዐት ከሚከበሩት የጌታችን ዐበይት በዓላት መካከል ዋነኞቹ ናቸው፡፡
የበዓላቱ አከባበር በሚታይና በሚዳሰስ ዝግጅት፣ በመብልና በመጠጥ፣ በልብስና በጌጣጌጥ ላይ ብቻ የሚያተኩርና በዚሁ ግርግር የሚታለፍ አይደለም፡፡ ይቅርታው እና ቸርነቱ ብዙ የሆነው የዓለም ፈጣሪ በስሕተት ጎዳና የተጓዘውን ዓለም(ሰውን) ለመፈለግ፣ ወደ እውነትና የሕይወት መሥመር ለመመለስና በኃጢአት በር ወደ ዓለም የገባውን ሞት በሞቱ ደምስሶ የሰውን ዘር ሁሉ ነጻ ለማድረግ ሰው የሆነበትና ሥጋን የተዋሐደበት ምሥጢር በልብ ይታሰባል፤ በትምህርት ይገለጣል፤ በተግባራዊ እንቅስቃሴ መንፈሳዊ ሥዕሉ በጉልሕ ይታያል፡፡ የሥነ በዓላቱ ጥልቀት እና ድምቀት የሚመሠረተው በዚህ ላይ ነው፡፡
የጌታችን የመድኃኒታችን የኢየሱስ ክርስቶስ ልደት የአዲስ ሕይወት (ሐዲስ ተፈጥሮ) መሠረት የተጣለበት የመላው ዓለም ልደት ነው፤ የጌታ ጥምቀትም ሰው ሁሉ ከኀጢአት እድፍ የሚነጻበትና በጥምቀት ተወልዶ የጸጋ ልጅነትን በማግኘት የሥጋና የነፍስ ድኅነት ባለቤት የሚሆንበት የአዲስ ሕይወት ቀን ነው፡፡ ሰው ሁሉ ወደ ክርስቶስ ቤተሰብነትና የክርስቲያን ማኅበር አንድነት ብሎም ወደ ዘለዓለም ሕይወት የሚተላለፍበት በር ጥምቀት ነው፡፡ ‹‹ከውኃና ከመንፈስ ቅዱስ ያልተወለደ ወደ እግዚአብሔር መንግሥት ሊገባ አይችልም፤” ተብሏል(ዮሐ. 3÷5)
የጥንተ ክርስትናውን መሠረት ሳትለቅ ከቀደምት አበው በተላለፈው እምነት እና ሥርዐት የምትጓዘው ጥንታዊት፣ ብሔራዊት እና ሐዋርያዊት የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ለሰው ሁሉ ደኅንነት ወደ ዓለም የመጣውን የመድኃኔዓለም ኢየሱስ ክርስቶስን ቤዛነት የእግዚአብሔርን የቃል ኪዳን ጽላት(ታቦተ እግዚአብሔርን) አክብራ በአደባባይ ስትመሰክር ትታያለች፡፡ የብሉያት እና ሐዲሳት መጻሕፍት በአንድ ጥራዝ እንደሚገኙ ሁሉ ሥርዐቱንም ባህሉንም አስተባብራ ይዛ የምትገኝ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ብቻ ናት፡፡
ጌታ ከገሊላ ወደ ፈለገ ዮርዳኖስ ወርዶ የተጠመቀበትን ዕለት ከመንፈሳዊ ታሪኩ እና ምስጢሩ አንጻር በማመላከት ታቦቷን ይዛ ወደ ውኃ ምንጮች በመጓዝ በየዓመቱ በታላቅ መንፈሳዊ ሥነ ሥርዐት ስታከብር ኖራለች፤ ትኖራለች - ታቦታቱን አክብረው ወደ ባሕረ ጥምቀት የሚወርዱት ካህናተ እግዚአብሔር የጌታ፤ ባሕረ ጥምቀቱ የፈለገ ዮርዳኖስ፤ በባሕር ጥምቀቱ ዙሪያ የሚደርሰው ስብሐተ እግዚአብሔር፣ ሥርዐተ ቅዳሴ እግዚአብሔር አብ ለወልደ እግዚአብሔር ኢየሱስ ‹‹የምወደው ልጄ እርሱ ነው፤ እርሱን ስሙት” (ማቴ. 3÷16 - 17) ሲል የሰጠው ምስክርነትአንድም የዮሐንስ የንስሐ ስብከትበባሕረ ጥምቀቱ ዙሪያ ታቦታቱን ከብቦ የሚያድረው ምእመን ከመጥምቀ መለኰት ቅዱስ ዮሐንስ የንስሐ ጥምቀት ለመጠመቅ ተሰልፎ ተራውን ይጠባበቅ የነበረውን ሕዝብ በምሳሌነት የሚያዘክር ነው፡፡ ስለሆነም በልደት እና በጥምቀት በዓላት ቀናት ሕዝበ ክርስቲያኑ በብዛት እየወጣ ለአምላኩ ያለውን አክብሮት፣ ፍቅር እና ተአማኒነት በጋለ መንፈስ ይገልጻል፡፡
በአሁኑ ወቅት ይህ የጋለ መንፈስ በኦርቶዶክሳዊው ወጣት ግንባር ቀደም ተሳትፎ ቀጣይነቱ ተረጋግጦ ይገኛል፡፡ መዲናዋን አዲስ አበባን ጨምሮ በመላዋ ኢትዮጵያ የሚደካሄደው የኦርቶዶክሳውያን ወጣቶች የጥምቀተ ክርስቶስ በዓል አከባበር ተሳትፎ ከጊዜ ወደ ጊዜ እየደመቀ ቀጥሎ ዘንድሮም ለሦስተኛ ጊዜ የተለያዩ ቅድመ ዝግጅቶች እየተደረጉበት ነው፡፡
እንቅስቃሴው ከሦስት ዓመት በፊት በየቀበሌው በተደራጁ ወጣቶች ሲጀመር ቲ - ሸርት ለብሶ መዝሙር እየዘመሩ ታቦታቱን በማጀብ፣ ታቦታቱ የሚያልፉባቸውን ጎዳናዎች በማጽዳት፣ ቄጤማ በመጎዝጎዝ፣ ግራ እና ቀኝ ፊት እና ኋላ በማስተናበር ወጣቱ ለወቅቱ የአፅራረ ቤተ ክርስቲያን ትንኮሳ ዐይነታዊ ምላሽ በመስጠት የአለኝታነት መልእክት ያስተላለፈበት ነበር፡፡ በሂደት ከበጎ አድራጊ ምእመናን የሚገኘው ድጋፍ እየተጠናከረ ሲመጣ አውራ ጎዳናዎችንና አደባባዮችን በሰንደቅ ዓላማ በማሸብረቅ፣ ታቦተ እግዚአብሔርን ያከበሩ ካህናት በሚረማመዱባቸው ጎዳናዎች ምንጣፍ በማንጠፍ፣ ከበዓሉ ጋራ በተያያዘ ለነዳያን በመመገብ እንቅስቃሴው ተጠናክሮ ቀጥሏል፡፡
የሰበካው ለዚህ ወቅታዊ ተግባር የተደራጁት ወጣቶች የየራሳቸውን ሊቀ መንበር፣ ጸሐፊ እና ገንዘብ ያዥ በመምረጥ አካባቢያዊ ጥምረት በመፍጠር በከተማ ደረጃ የከተማ ማኅበራትን ኅብረት (ጥምረት) ፈጥረዋል፤ በአሁኑ ወቅት በአዲስ አበባ ከተማ 65 አካባቢያዊ ማኅበራት ሲኖሩ ማኅበራቱ ደግሞ በከተማ (በሀገረ ስብከት) ደረጃ የማኅበራት ጥምረት መመሥረታቸው ታውቋል፡፡ የማኅበራቱ ጥምረት ሰባት አባላት ባሉት ሥራ አስፈጻሚ የሚመራ ሲሆን ጠቅላይ ቤተ ክህነቱ በስብከተ ወንጌል እና ሐዋርያዊ ተልእኮ መምሪያ በመንፈሳውያን ማኅበራት ወይም በሰንበት ት/ቤቶች ማደራጃ መምሪያ ሥር የሚካተቱበት አማራጭ በመንበረ ፓትርያርኩ በኩል እየተጤነ መሆኑ ተገልጧል፡፡
ጥምቀት ልጆች በዓሉ በብሔራዊ ደረጃ በሚከበርበት በጃንሜዳ፣ ስድስት ኪሎ እና ዑራኤል አካባቢ ለተዘዋወሩ ደጀ ሰላማውያን እንደተናገሩት፣ ከነገ ጥቅምት 10 ጀምሮ ቀን ጀምሮ ለሚከበረው ለዘንድሮው የጥምቀት በዓል ቅድመ ዝግጅቱ የተጀመረው የዛሬ ሁለት ወራት ገደማ ነው፡፡ ጥምቀት ልጆች ከሁለት ወር በፊት በተመረጡ ያሬዳዊ መዝሙሮች ጥናት ጀምረዋል፤ በአንዳንዶቹ ዘንድ ቀደም ሲል ይለበሱ የነበሩ ቲ - ሸርቶች ከአገር ባህል (ሸማ) በሚሠሩ ቲ - ሸርቶች እንዲተኩ ተደርጓል፡፡ መዝሙር እየዘመሩ የታቦታቱን ዑደት የሚያስከብሩ ወጣቶች ሙሉ በሙሉ የአገር ባህል ልብስ (ቢያንስ ነጠላ) የሚለብሱ ሲሆን የሸማ ቲ-ሸርት የሚለብሱት ደግሞ አስተናባሪዎች ናቸው፡፡ ሁሉንም ወጣቶቹ በነፍስ ወከፍ በራሳቸው ወጪ የሚሸፍኑት ነው፡፡
ጥምቀት ልጆች ቀደም ሲል በአደባባይ እና ቤት ለቤት በመዞር በሰበሰቡት የምእመናን አስተዋፅኦ እስከ ብር 900 - 1950 በማውጣት 2x10 ካሬ ሜትር ቀይ ምንጣፍ ገዝተዋል፤ እንደ አስፈላጊነቱ ከመንገድ ግራ እና ቀኝ ተተክለው የሰንደቅ ዓላማ መስቀያ የሚሆኑ አጣናዎች በቀን በሦስት ብር ሒሳብ ተከራይተዋል፤ ታቦታቱ ለተወሰነ ጊዜ በሚቆሙባቸው ቦታዎች የሚያገለግሉ መድረኮች ከእነዚህ አጣናዎች ተገንብተው በቅዱሳት ሥዕላትና በሰንደቅ ዓላማ ተሸፍነዋል፤ መድረኮቹን የዲኮር አገልግሎት ከሚሰጡ ተቋማት በኪራይ ያስመጡ፣ እንዳገኙት አስተዋፅኦ መጠን ለነዳያን የበዓል ማዕድ ያዘጋጁም አሉ፡፡ በነገው የከተራ እና ጥምቀት በዓል የቀደመ የበዓል አከባበር ተሳትፎአቸውን የሚያሳይ የዶኩመንቴሽን ሥራ ለግብይት የሚያቀርቡም አሉ፤ የገቢ አቅም ለማጠናከር ሌሎቹም ሥራዎች ይሠራሉ፡፡
የጥምቀት ልጆች ይህን ሁሉ ቅድመ ዝግጅት ሲያደርጉ ከእያንዳንዱ ምእመን ሞራላዊ ማበረታቻ እና ፋይናንሳዊ አስተዋፅኦ ባሻገር የሰፈር ዕድሮች ሳይቀር የሥራ መሣሪያዎችን በማዋስ እና ሞያዊ እገዛ በመስጠት ማኅበራዊ ሚናቸውን አሳይተዋል፡፡ በሁሉም አካባቢዎች ጥምረቶቹ በሥራቸው የሚያስተባብሯቸውን የጥምቀት ልጆች በመቆጣጠር በበዓሉ ሁከት እንዳይፈጠር በጥብቅ እንዲከታተሉ ከየቀበሌው እና የክፍለ ከተማው ፖሊስ ጣቢያዎች ተደጋጋሚ መምሪያ፣ ማሳሰቢያ እንደተሰጣቸው ተዘግቧል፤ ሓላፊነት ወስደው ፊርማቸውን ያኖሩም እንዳሉ ተጠቁሟል፡፡
የ2004 ዓ.ም የጥምቀት በዓል የሚውልበት ጥር 11 ቀን ዕለቱ ዐርብ በመሆኑ ነገ ጥር 10 ቀን ገሃዱ (ጋዳው፣ ጋዱ) ኀሙስ ለውጥ ሆኖ ይጦማል፤ ጥምቀት የሚውልባቸው ዐርብ እና ረቡዕ አይጦሙምና፡፡ ገሃድ (ጋድ) ማለት ለውጥ፣ ልዋጭ ማለት ነው፡፡ ፍቹ ከዘይቤው አይገናኝም፡፡ ጥምቀት ረቡዕ እና ዐርብ በሚውልበት ጊዜ በኋላው የሚገኙት ማክሰኞ እና ኀሙስ የፍሥክ ቀንነታቸው ወደ ጾምነት ተለውጦ ይጾማሉ፡፡ በእነርሱ ለውጥ ጥምቀት የሚውልባቸው የጾም ቀኖች (ረቡዕ እና ዐርብ) የፍሥክ ቀን ሆነው ይከበራሉ፡፡
ገሃድ የረቡዕ እና የዐርብ ለውጥ ነው ብለናል፡፡ ነገር ግን ጥምቀት በሌላውም ቀን ቢውል የጥምቀት ዋዜማ ይጾማል፡፡ ጥምቀት እሑድ ቢውል ቅዳሜ ጥሉላት አይበላም፡፡ ሰኞ ቢውል እሑድ ጥሉላት አይበላም፡፡ እህል ውኃ ግን አይጦምም፡፡ ገሃድ ለጥምቀት ብቻ ነው፡፡
በዚሁ አጋጣሚ በጥምቀት ላይ የምታነሷቸውን ፎቶግራፎች ወይም የምትቀርጿቸውን ቪዲዮዎች በመላክ ትተባበሩን ዘንድ በትህትና እንጠይቃለን!!!!!!!!

ቸር ወሬ ያሰማን፤

መልካም የጥምቀት በዓል!!!!

1 comment:

Anonymous said...

Yetmket wetaoch bertu

Egziabher sew bata gize asntochwal

Gnn Ebakchihu qdusan sealn menged lay abara lay atskelu.....Eshi bertu

Blog Archive

የአቡነ ጳውሎስ "ሐውልተ ስምዕ"

ነጻ ፓትርያርክ ምርጫ ቢሆን ኖሮ ማንን ይመርጡ ነበር? እንበልና ሁሉም ነገር ሥርዓቱን ጠብቆ የተከናወነ የእጩዎች ምርጫ ቢሆን ኖሮ፣ አሁን የምናነሣቸው ጉድለቶች ባይኖሩ ኖሮ፣ 6ኛው ፓትርያርክ እንዲሆን የምትመርጡት ማንን ነበር? (ማሳሰቢያ፦ አሁን ያለው ክፍፍል እና የመንግሥት ተጽዕኖ ባይኖር ኖሮ ተብሎ የሚመለስ ጥያቄ ነው። የምን “ባይኖር ኖሮ ነው” የሚል አስተያየት ካለዎትም እናከብራለን።)