January 30, 2012

የመ/ር ዘመድኩን የመከላከያ ምስክሮች ተሰሙ


  ·    የተከሳሽ ጠበቃ እና ዐቃቤ ሕግ የክርክር ማቆሚያ ንግግር አድርገዋል::
  ·     ውሳኔው ለየካቲት 27 ቀን 2004 ዓ.ም ተቀጥሯል::
  ·   የአርማጌዶን ቪሲዲ እውነትን መሠረት አድርጎ ከፍ ላለ ሞራላዊ ዓላማ የተሠራ ዝግጅት እንጂ የስም ማጥፋት ተግባር አይደለም፤ አዘጋጁም ሥራውን የመሥራት ችሎታ እና ሥልጣን አላቸው፡፡ የዐቃቤ ሕግ ምስክሮች የግል ተበዳይ [ከሳሽ በጋሻው ደሳለኝ] አጉራ ዘለል መሆኑን በበቂ አላስተባበሉም፤ የማስተማር ችሎታ እና ሥልጣን እንዳለው ያቀረቡት አሳማኝ ማስረጃ የለም” (የተከሳሽ ጠበቃ)::
(ደጀ ሰላም፣ ጥር 20/2004 ዓ.ም፤ January 29/2012/ READ THIS ARTICLE IN PDF)፦ አርማጌዶን ቪሲዲ የተነሣ የስም ማጥፋት ወንጀል ክስ የቀረበበት መ/ር ዘመድኩን በቀለ የመከላከያ ምስክሮቹን ለፌዴራሉ የመጀመሪያ ደረጃ ፍ/ቤት አራዳ ምድብ ችሎት አቅርቦ አሰምቷል፡፡ ተከሳሹ ከቆጠራቸው አምስት የመከላከያ ምስክሮች መካከል በችሎቱ የተሰማው የሦስቱ የምስክርነት ቃል ሲሆን ቀሪዎቹ ሁለቱ ምስክሮች ከሦስቱ የተለየ የማያስረዱ በመሆኑ ከምስጋና ጋራ ተሰናብተዋል፡፡ የግራ ቀኙ ክርክር የተጠቃለለ ሲሆን ዐቃቤ ሕግ እና የተከሳሽ ጠበቃ የክርክር ማቆሚያ ንግግራቸውን ለችሎቱ አቅርበዋል፡፡ መዝገቡን መርምሮ የፍርድ ውሳኔ ለመስጠት ለየካቲት 27 ቀን 2004 ዓ.ም ከቀትር በኋላ በ8፡00 ሰዓት ቀጠሮ ተይዟል፡፡

ጥር 18 ቀን 2004 ዓ.ም ከቀትር በኋላ በ8፡00 በአራዳ ምድብ ችሎት ስድስተኛ ወንጀል ችሎት በመዝገብ ቁጥር 96/25 ከተደመጠው የመከላከያ ምስክሮች ቃል በዋናነት ለመረዳት እንደተቻለው ቅዱስ ሲኖዶስ÷ ከአብነት ት/ቤት ወይም ከሦስቱ የቤተ ክርስቲያኒቱ ከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ገብተው ሳይማሩ እናስተምራለን፣ ሳይላኩ እና ፈቃድ ሳይኖራቸው ተልከናል በሚል ራሳቸውን የሚያሰማሩ ሰባክያን ነን ባዮች ላይ ቁጥጥር እንዲደረግባቸው የሚጠይቅ መመሪያ አውጥቷል፡፡ በመመሪያው ላይ ፈቃድ የሌላቸው ሕገ ወጥ ሰባክያን “አጉራ ዘለል” በሚል መገለጻቸውን ምስክሮቹ አስታውሰዋል፡፡ ሐምሌ 25 ቀን 2003 ዓ.ም በፓትርያኩ ፊርማ የወጣው ደብዳቤ የአርማጌዶን ቪሲዲን ዓላማ ትክክለኛነት የሚያረጋግጥ እንጂ የሚቃወም እንዳልሆነም አስገንዝበዋል፡፡
ቅዱስ ሲኖዶስ ስለ ሕገ ወጥ ሰባክያንና ዘማርያን ካስተላለፈው መመሪያ በመነሣት የግል ተበዳይ የተባለው ከሳሽ በጋሻው ደሳለኝ ከየትኛውም ተቋም ትምህርቱን ያላጠናቀቀ፣ ከሚመለከተው አካል የማስተማር ፈቃድ ሳይሰጣቸው ራሳቸውን በራሳቸው ከሚያሰማሩ አጉራ ዘለሎች አንዱ እንደሆነ አስረድተዋል፡፡ ሐምሌ 25 ቀን 2004 ዓ.ም በፓትርያርኩ ፊርማ በተላለፈው መመሪያ፣ “ምእመናንና ምእመናት በተሳሳቱ ግለሰቦች አድራጎት እንዳይማረኩ በመምህራንና በንስሐ አባቶች ጥብቅ ክትትልና ጥበቃ ሲደረግ ኖሯል፤” በሚለው መሠረት ቤተ ክርስቲያን አስተምራና መርቃ ያሰማራችው ተከሳሽ መምህር እንደሆነና ትክክለኛውን የማስተማር፣ ስሕተቱን የማረምና የመቃወም ግዴታ አለበት፡፡ አርማጌዶን ቪሲዲ ከዚህ አንጻር የተዘጋጀ ነው፤ በይዘቱም ምእመኑ ከስሕተት ትምህርት እንዲጠበቅ፣ የሚመለከተውም አካል እንደ በጋሻው ባሉ ሕገ ወጦች (አጉራ ዘለሎች) ላይ ተገቢው ርምጃ እንዲወስድ ከመጠየቅ በቀር የውግዘት ቃል አልተላለፈበትም ወይም እንደ ዐቤ ሕግ አነጋገር “የግል ተበዳይን መልካም ስም ለማጥፋት እና ከኦርቶዶክስ እምነት ተከታዮች ጋራ ለማጋጨት በማሰብ” የተዘጋጀ ነው ብለው እንደማያምኑ ለችሎቱ ተናግረዋል፡፡
በዕለቱ በተከሳሽ ጠበቃ ጌትነት የሻነህ ዋና ጥያቄ እና የድጋሚ ጥያቄ፣ በዐቃቤ ሕግ መስቀለኛ ጥያቄ እና በዳኛ ሙሉ ክንፈ የማጣሪያ ጥያቄዎች በተደጋጋሚ ከተነሡት ጥያቄዎች መካከል፣ “ትምህርት ማስተማር የሚችለው ማን ነው? አጉራ ዘለል ሰባክያንን የመቆጣጠር ሓላፊነት የማን ነው? በቤተ ክርስቲያን የስሕተት ትምህርትና የተሳሳተ መምህር የሚታረመው እንዴት ነው? ሥልጣኑስ የማን ነው? ተከሳሽ ያለውን ማስረጃ ይፋ የማውጣት ሥልጣን አለው ወይ? ካለውስ በተሻለ መንገድ /በቅንነት ለማቅረብ አይቻልም ነበር ወይ? ሐምሌ 25 ቀን 2003 ዓ.ም በፓትርያርኩ ተፈርሞ ከወጣው ደብዳቤ አኳያስ እንዴት ይታያል?” የሚሉቱ ይገኙባቸዋል፡፡
ለጥያቄው ምላሽ ከሰጡት የተከሳሽ መከላከያ ምስክሮች መካከል ሁለተኛው ምስክር ዲያቆን ዳንኤል ክብረት እንዳስረዱት÷ በቤተ ክርስቲያን ለሚፈጠር የስሕተት ትምህርት በአፍ በመጽሐፍ መልስ የመስጠት ድርሻ በዋናነት የመምህራን ሲሆን ምእመናንን ከኀጢአትና በደል የመጠበቅ ተግባር ደግሞ የንስሐ አባቶች ሓላፊነት ነው፡፡ ምእመናንን ከዕውቀት መጣመም የሚጠብቁ ሊቃውንት፣ መምህራን ከትውፊታዊው የአብነት ት/ቤት በአንዱ ጉባኤ/ሞያ አስመስክረው የወጡ አልያም ከቅድስት ሥላሴ መንፈሳዊ ኮሌጅ፣ ከሰዋስወ ብርሃን ቅዱስ ጳውሎስ መንፈሳዊ ኮሌጅ፣ ከቅዱስ ፍሬምናጦስ አባ ሰላማ ከሣቴ ብርሃን ኮሌጅ የተመረቁ መሆን ይገባቸዋል፡፡
ከዚህ አኳያ በጋሻው ደሳለኝ የአንድ ዓመት የኮሌጅ ቆይታ ያለው ብቻ በመሆኑ መምህር ሊባል፣ መምህር ሊሆን አይችልም፤ ተከሳሹ መ/ር ዘመድኩን በአንፃሩ ከቅድስት ሥላሴ መንፈሳዊ ኮሌጅ በተቀበለው ዲፕሎማ ላይ “ሂዱና አስተምሩ” ከተባሉት የኮሌጁ ደቀ መዛሙርት አንዱ በመሆኑ ትክክለኛውን የማስተማር፣ የተለየውን የማረምና የመቃወም ግዴታ አለበት፡፡ ይህንኑ ቃላቸውንም የተከሳሽ ሦስተኛ የመከላከያ ምስክር የሆኑት የቅድስት ሥላሴ መንፈሳዊ ኮሌጅ የሐዲስ ኪዳን መምህር ደጉ ዓለም ካሳ አጠናክረውታል፡፡
“አጉራ ዘለል ሰባክያን” የሚለው አገላለጽ በአርማጌዶን ቪሲዲ ላይ ከመሰማቱ በፊት የቤተ ክርስቲያኒቱ ልሳን በሆነው ዜና ቤተ ክርስቲያን ጋዜጣ ላይ መመልከታቸውን፣ በትርጉሙም ሳይማሩ ተምረናል፣ ሳይላኩ ተልከናል በማለት ራሳቸውን የሚያሰማሩ ግለሰቦችን እንደሚመለከት ዲያቆን ዳንኤል ለችሎቱ አስረድተዋል፡፡ ከዚህ አኳያ የቤተ ክርስቲያን እምነትና ትምህርት መሠረት የሆነውን አሚነ ሥላሴን በመፃረር፤ ሐዋርያትን፣ ሰማዕታትን፣ ሊቃውንትን፣ ጻድቃንን የምትወልደውን ቤተ ክርስቲያንን በ‹አሮጊቷ› ሣራ በመወከል በአደባባይ ለተነገረው የስሕተት ትምህርት በአደባባይ ምላሽ መሰጠቱ፣ መገሠጹ፣ ማስጠንቀቁ አግባብነት እንዳለው፤ እንዲያውም ከስሕተቱ አስከፊነት አንጻር የተሰጠው ምላሽ በቅንነት ብቻ ሳይሆን በርኅራኄ ጭምር የቀረበና የግል ተበዳይን ክብር እንደማይነካ ምስክሩ ገልጸዋል፡፡
አርማጌዶን ቪሲዲ ግለሰቦችን የሚያወግዝ /የውግዘት ቃል/ አለመስማታቸውን የገለጹት ዲያቆን ዳንኤል ውግዘት በክህነት ደረጃ የሚተላለፍ፤ ቄስ፣ ጳጳስ መሆንን የሚጠይቅ፣ በውጤቱም ካህኑን ከመናዘዝ፣ ቀድሶ ከማቍረብ፤ መምህሩን ከማስተማር፣ ምእመኑን ምስጢራተ ቤተ ክርስቲያንን ከመሳተፍ፣ ከምእመናን አንድነት የሚለይ፣ የሚከለክል እንደሆነ፣ የራሱ ደረጃና አፈጻጸም እንዳለው በማስረዳት አንድን ሰው ማውገዝና ስሕተቱን ገልጾ መናገር፣ ማጋለጥ የተለያዩ ጉዳዮች መሆናቸውን አስገንዝበዋል፡፡
“በቤተ ክርስቲያን ታሪክና ሥርዐት ስሕተት ሲያጋጥም በመጀመሪያ በቦታው መህራን መልስ እንደሚሰጥ፣ በካህናቱም ምክር ይሰጣል” ያሉት ዲያቆን ዳንኤል በምላሹና ምክሩ የተሳሳተው ግለሰብና ስሕተቱ የማይታረም ሲሆን በሊቃውንተ ቤተ ክርስቲያንና በቅዱስ ሲኖዶስ ደረጃ ታይቶ እንደሚወሰን፣ ለአብነት ያህል የአርዮስ ጉዳይ በዋናነት በሁለት ደረጃ (በእስክንድርያ ቤተ ክርስቲያን እና በኒቂያ ጉባኤ) ታይቶ ውሳኔ እንደተላለፈበት ለችሎቱ አስታውሰዋል፡፡
ከዚህ አኳያ ሐምሌ 25 ቀን 2003 ዓ.ም “አንዳንድ የሃይማኖት ሕጸጽ ያለባቸው ሰዎች ከሃይማኖታችን የተለየ ትምህርት ይሰጣሉ በማለት ስም በመጥቀስ ልዩ ልዩ ጽሑፎችን የሚበትኑ ግለሰቦችና ድርጅቶችን አስመልክቶ መመሪያ ስለመስጠት” በሚል በፓትርያርኩ ተፈርሞ የተላለፈው ደብዳቤ፣ “መምህራን ምእመናን እና ምእመናት በተሳሳቱ ግለሰቦች አድራጎት እንዳይማረኩ ጥብቅ ክትትል የማድረግ ሓላፊነት እንዳለባቸው” በማመልከት ግዴታቸውን የሚገልጽ እንጂ የአርማጌዶን ቪሲዲን መሠራት አይከለክልም - መ/ር ዘመድኩን በቤተ ክርስቲያኒቱ የተላከ መምህር ነውና ብለዋል፡፡ የአርማጌዶን ቪሲዲ ዝግጅት በምስል ወድምፅ የተቀናበረ ከመሆኑ በቀር ንጽጽራዊ አቀራረቡ እንደ መልአከ ብርሃን አድማሱ ጀምበሬ ኵኩሐ ሃይማኖት ወይም እንደ አለቃ አያሌው ታምሩ መች ተለመደና ከተኩላ ዝምድና ያህል እንደሚቆጥሩት የተናገሩት ዲያቆን ዳንኤል፣ “የቀደሙ አባቶች የተጠቀሙበት ነባር አቀራረብ ነው፤ ለጊዜው የተሻለውም አቀራረብ ይኸው ነው” ብለዋል፡፡
ዐቃቤ ሕግ ለዲያቆን ዳንኤል መስቀለኛ ጥያቄ ባቀረበበት ወቅት “ተከሳሽ ካለው ዲፕሎማ በላይ የትምህርት ደረጃ ያላቸው ሊቃውንት፣ ምሁራን አሉ፤ ይህ ሆኖ እያለ ቪሲዲው የተከሳሽን የበላይነት ለማሳየት የተዘጋጀ ነው” ለሚለው አነጋገር የተከሳሽ ጠበቃ ቪሲዲው የቀረበው የበላይነትንና የበታችነትን ለማሳየት ሳይሆን ሓላፊነትን ከመወጣት አኳያ መሆኑን፣ በምትኩ አነጋገሩ ዐቃቤ ሕግ በደንበኛቸው ላይ ያላቸውን መጥፎ አመለካከት የሚያሳይ ነው በማለት ተቃውመዋል፡፡ በዚህ ስሜታዊ አነጋገር የቀረበው የዐቃቤ ሕግ ጥያቄም በተከሳሽ ጠበቃ ተቃውሞ በዳኛ ብይን ውድቅ ተደርጓል፡፡
የግራ ቀኙን ክርክር ሲያዳምጥ የቆየው ችሎቱ ዐቃቤ ሕግ እና የተከሳሽ ጠበቃ የክርክር ማቆሚያ ንግግር እንዲያደርጉ ባዘዘው መሠረት፣ ዐቃቤ ሕግ ተከሳሹ አርማጌዶን ቪሲዲን ያዘጋጀው ሐምሌ 25 ቀን 2003 ዓ.ም በፓትርያርኩ ተፈርሞ የወጣውን መመሪያ በመጣስ መሆኑን፤ ያዘጋጀበት ዓላማም በተለይ ምስክሩ ታሪኩ አበራ ለችሎት ከተናገረው በመነሣት “የግል ተበዳይን መልካም ስም ለማጥፋት፣ በሕይወቱ ላይም አደጋ እንዲደርስ ለማነሣሣት በማሰብ” መሆኑን፤ የምስክሮች ቃል እርስ በርስ እንደሚጋጭ በተከሳሽ ጠበቃ በኩል የቀረቡት ማስረጃዎች ይህን እንደማያስተባብሉ ተናግሯል፡፡
ይኸው የዐቃቤ ሕግ ክስ “ከማውራት ባለፈ በማስረጃ ያልተረጋገጠ ነው” ያሉት የተከሳሽ ጠበቃ በበኩላቸው፣ የግል ተበዳይ ፈቃድ ሳይኖረውና ሳይማር እሰብካለሁ የሚል አጉራ ዘለል ለመሆኑ የሰው እና የሰነድ ማስረጃዎች መቅረባቸውን፤ ከዚህ ቀደም ተወግዘው ከተባረሩት ‹መነኮሳት› ጋራ በንግግር የሚመሳሰሉበት ሁኔታ በንጽጽር ከመቅረቡ በቀር የውግዘት ቃል አለመኖሩን፤ ይህንንም የዐቃቤ ሕግ ምስክሮች ያመኑበት ስለመሆኑ፤ ከየትኛውም ተቋም ተምሮ የወጣበትን ማስረጃ አለማቅረቡን፤ ከቪሲዲው የተነሣ የግል ሰብእናው ለመነካቱ የሚያስረዱ ተናጠላዊ ማስረጃዎች ተለይተው አለመቅረባቸውን፣ 386 የኦዲዮ እና 114 የደንበኛቸው ሲዲ ለኤግዚቢት ከሚያስፈልገው በላይ ከየሱቁ መሰብሰባቸውን፣ የዐቃቤ ሕግ ምስክር ታሪኩ አበራ ተከሳሹ ነገረኝ ያሉት ዛቻና የመግደል ሙከራ ከክሱ ጭብጥ እና ማስረጃው ጋራ የማይገናኝ መሆኑን፣ ስለሆነም ክሱ በተመሠረተበት አንቀጽ 613/3 እንደተጠቀሰው አርማጌዶን ቪሲዲ የስም ማጥፋት ወንጀል አለመሆኑን ይልቁንም በአንቀጽ 614/2 መሠረት ሕዝቡ በስሕተት ስብከት እንዳይወሰድ ታስቦ ከሞራልም ከፍ ላለ ሃይማኖታዊ ጥቅም መዘጋጀቱን፣ ይህም በወንጀል እንደማያስጠይቅ ተናግረዋል፡፡
በአጠቃላይ ዐቃቤ ሕግ ከምክንያታዊ ጥርጣሬ ውጭ (50+1 እንኳ) ያስረዱ ባለመሆኑ ደንበኛቸው አያስጠይቃቸውም ተብሎ በነጻ እንዲሰናበቱ ፍ/ቤቱን ጠይቀዋል፡፡
ችሎቱ የግራ ቀኙ ያቀረቡትን ክርክር (መዝገብ) መርምሮ በጉዳዩ ላይ የፍርድ ውሳኔ ለመስጠት ለየካቲት 27 ቀን 2004 ዓ.ም ከቀትር በኋላ በ8፡00 ቀጠሮ በመስጠት ተነሥቷል፡፡

Post a Comment

Blog Archive

የአቡነ ጳውሎስ "ሐውልተ ስምዕ"

ነጻ ፓትርያርክ ምርጫ ቢሆን ኖሮ ማንን ይመርጡ ነበር? እንበልና ሁሉም ነገር ሥርዓቱን ጠብቆ የተከናወነ የእጩዎች ምርጫ ቢሆን ኖሮ፣ አሁን የምናነሣቸው ጉድለቶች ባይኖሩ ኖሮ፣ 6ኛው ፓትርያርክ እንዲሆን የምትመርጡት ማንን ነበር? (ማሳሰቢያ፦ አሁን ያለው ክፍፍል እና የመንግሥት ተጽዕኖ ባይኖር ኖሮ ተብሎ የሚመለስ ጥያቄ ነው። የምን “ባይኖር ኖሮ ነው” የሚል አስተያየት ካለዎትም እናከብራለን።)