January 24, 2012

የዘርዐ ያዕቆብ አደባባይ የአደባባይነት ቅርስነቱ አበቃ?

  • አቡነ ጳውሎስ በተገኙበት በዐፄ ዘርዐ ያዕቆብ አደባባይ የነፈሰው ማዕበል መሰል ውቅንብል ነፋስ የባሕረ ጥምቀቱን ሥነ ሥርዐት ለሩብ ሰዓት አስተጓጐለ::
  • ማዕበል መሰሉ ነፋስ “መልአከ እግዚአብሔር ወርዶ እየባረከ ነው” የሚል ትርጉም ቢሰጠውም በምእመኑ ዘንድ ግን የአስከፊ ድርጊት ንግር ተደርጎ ተወስዷል::
  • የሰሜን ሸዋ ሀገረ ስብከት በዘርዐ ያዕቆብ አደባባይ ላይ አገልግሎት ሰጪ ሕንፃ ሊያስገነባ ነው፤ ታሪካዊው አደባባይ የደብረ ብርሃን ከተማ አብያተ ክርስቲያን ባሕረ ጥምቀት እና መስቀል ደመራ የሚያከብሩበት ነው::
(ደጀ ሰላም፣ ጥር 15/2004 ዓ.ም፤ January 24/2012/ READ THIS ARTICLE IN PDF)፦ ምድር መሠረት፣ የሰማይ ዐምድ የሆነው ረቂቁ ነፋስ በእግዚአብሔር ትእዛዝ እንደሚነሣ፣ እንደ ዐውሎ (ጥቅል) ሆኖ ሲነፍስም ድንገቴ ነውና የእግዚአብሔር ፍርድ ምሳሌ እንደሆነ ይታመናል (መዝ.106(107)÷25፤ ምሳ. 10÷25፤ ኢሳ. 17÷13፤ ናሆም 1÷3)፡፡ ጥር 13 ቀን 2004 ዓ.ም በደብረ ብርሃን ከተማ በታሪካዊው ዘርዐ ያዕቆብ አደባባይ እና አካባቢው የታየው ይህንኑ የሚያጠይቅ ነው ተብሏል፡፡

በዕለቱ የጠባሴ ቅዱስ እግዚአብሔር አብ፣ በደብረ ጽባሕ ቅዱስ ጊዮርጊስ እና በቅዱስ ሩፋኤል አብያተ ክርስቲያን ድርብ ከሆኑ ሌሎች ሁለት የእግዚአብሔር አብ ታቦታት ጋር ማደሪያቸውን በዚያው አድርገው በጥምቀት ክብረ በዓል ላይ ነበሩ፤ በክብረ በዓሉ ላይም በዕለቱ ከአዲስ አበባ ጠዋት በ3፡00 ተነሥተው ቀትር ላይ በስፍራው የደረሱት ብፁዕ ወቅዱስ ፓትርያክ አቡነ ጳውሎስ የተገኙ ሲሆን ብፁዕ አቡነ ገሪማ እና ብፁዕ አቡነ ሳዊሮስ ተከትለዋቸዋል፡፡ ቀደም ብሎ ፓትርያኩ ከደብረ ብርሃን 20 ኪ.ሜ ርቀት ላይ ከሚገኘው አሣግርት ወረዳ ጫጫ ከተማ ሲደርሱ በካህናት እና ፈረሰኛ ምእመናን ደማቅ አቀባበል ተደርጎላቸዋል፡፡
የአቡነ ጳውሎስ የሰንበት መንገድ ከጥምቀት በዓል ጋር ይገናኝ እንጂ ዋናው የጉዞው መርሐ ግብር ግን የዐፄ ዘርዐ ያዕቆብ (1434 - 1460 ዓ.ም) ፍርድ መስጫ በነበረው ታሪካዊ አደባባይ ላይ የኪራይ ገቢ ለማስገኘት ታስቦ ለሚገነባው የአገልግሎት ሕንፃ ዕብነ መሠረት ለማስቀመጥ ነው፡፡ በየመንገዱ የተደረገላቸው አቀባበል ለመዘግየታቸው ምክንያት እንደሆነ በመጥቀስ በአደባባዩ የተገኘውን አገልጋይና ምእመን ይቅርታ የጠየቁት ፓትርያኩ የመሠረት ድንጋዩን ካስቀመጡ በኋላ ቅኔዎች እየተበረከቱ ማዕበል መሰሉ ነፋስ በድንገት የተነሣው፡፡ አዋራውን ከምድር ላይ እየጠራረገ ወደ ቀኝና ግራ እየተራጨ በምላት እና በኀይል ያጋፋ የነበረው ነፋሱ ጥቅል የአዙሪት መልክ እንደነበረው ለክብረ በዓሉ የተገኙ የዐይን እማኞች ተናግረዋል፡፡
በከሣቴ ብርሃን ተሰማ የአማርኛ መዝገበ ቃላት አገላለጽ ውቅንብል ነፋስ ሊባል የሚችለው ይኸው ማዕበላዊ ነፋስ ሲነፍስ በአደባባዩ የነበሩ ምእመናን አብዛኞቹ በማጎንበስ እና ከመሬት ላይ በመተኛት ያሳለፉት ሲሆን ካህናቱና ሌሎቹም የያዙትን ጥላ ወደ ጎን በመወደር ለመጋረድ ሲታገሉ ታይተዋል፡፡ በዚህም ሁኔታ ክሥተቱ ከሩብ ሰዓት ላለነሰ መቆየቱ ተዘግቧል፤ መርሐ ግብሩን ይመሩ የነበሩት የሀገረ ስብከቱ ሥራ አስኪያጅ መጋቤ ሐዲስ ይልማ ቸርነት “መልአከ እግዚአብሔር ወርዶ ሲባርክ ነው” በሚል ለማረጋጋት መሞከራቸው ተሰምቷል፡፡
ነፋስ የአየር እንቅስቃሴ ነው፡፡ በመጽሐፈ ኄኖክ (ምዕ. 25) እንደተመለከተው፣ በቤተ ክርስቲያናችን የሥነ ፍጥረት ትምህርትም እንደሚነገረው ነፋስ የምድር መሠረት የሰማይ ዐምድ ነው፡፡ ከአራቱ አሥራወ ፍጥረታት (ባሕርያት) አንዱ የሆነው ነፋስ ረቂቅ፣ ርጉዕ፣ ህውክ ነው፡፡ ይኸውም ከሰማይ በታች በአራቱ ማእዝናት የመላ፣ በገዛ ኀይሉ የሚታወክና የሚናወጥ ሌላውንም ሁሉ የሚያናውጥ፣ የሚያገዝፍ፣ የሚያስረዝም፣ የሚያሳድግ የፍጥረት ሁሉ ሕይወት አንቀሳቃሽ ማለት ነው፡፡
ነፋስ እንደ አቅጣጫው የበረከት ወይም የመቅሰፍት ሊሆን ይችላል፡፡ ጻድቅ ነቢይ ኄኖክ እንደነገረን በአጽናፈ ምድር (በአራት ማእዝናት በእያንዳንዳቸው ሦስት፣ ሦስት) ነፋሳት የሚወጡባቸው እና የሚገቡባቸው 12 መስኮቶች አሉ - አንድም ለመዐት፣ ጥፋት እና መቅሰፍት፤ አንድም ለምሕረት፣ ፍቅር፣ ድኅነት እና በረከት፡፡
አራት የምሕረት፣ ስምንት የጥፋት ነፋሳት አሉ፡፡ ነፋሳት የመቅሰፍት ሲሆኑ ከእነርሱ ድርቅ፣ ዋዕይ፣ ዋግ፣ ቀቅ፣ የረጋ የተበተነ ውርጭ፣ ክፉ ጠል፣ ክፉ ዝናም፣ ኩብኵባም ይወጣል፡፡ ነፋሳት የምሕረት ሲሆኑ ከእነርሱ በጎ ዝናም፣ በጎ ፍሬ፣ በጎ ጠል፣ በጎ ሽቱ ይወጣል፡፡ ነፋስ የጽልመት (መጨለም እና መጥቆር)፣ የይብሰት (ድርቅ፣ ሙቀት)፣ ቍረት (ብርድ፣ ቅዝቃዜ) ባሕርይ ያለው ሲሆን ህልውናው የሚገለጠው ነገሮችን ከማወዛወዝ፣ ገፍቶ ከማስነሣት፣ ወስዶ ከመመለስ፣ አንሥቶ ከመጣል ከመሆኑ ጋር ተያይዞ የተለያዩ አገራዊ ስያሜዎች አሉት፡፡

ዋና ዋናዎቹን ለማንሣት ያህል፡-
ለምለም ነፋስ ቀላል ሆኖ ሣርን፣ ቅጠልን በትንሹ የሚያንቀሳቅስ፣ ለሕይወትም ጤናን የሚሰጥ ነው፡፡
መንጠሌ ነፋስ ክረምት ሲወጣ የሚነፍስና ውኃ ያላላውን ምድር የሚያጠነክር ነው፡፡
ልክስክስ ነፋስ በትንሹ ሆኖ እንደ ዐውሎ ነፋስ ሳይበረታ እየተዘዋወረ ትቢያውን እያነፈሰ በትኖት መልሶ በዚያው በቦታው የሚጥለው የሚልከሰከሰው ልክስክስ ነፋስ ይባላል፡፡
ማዕበል ነፋስ ከወደ ምሥራቅም ሆነ ከወደ ምዕራብ ነፍሶ በምላት፣ በኀይል እያጋፋ ነፍሶ ዛፍንም ከወዲያ ወዲህ እያማታ፣ የወራውን ቅጠል እና ፍራፍሬ የሚያራግፍ፣ ትቢያውን ከምድር ላይ እየጠራረገ የሚበትን ነው፡፡
ኀብላይ ነፋስ ቤትን የሚገለባብጥ፣ ዛፍን የሚነቃቅል፣ በምድር ላይ ያለውን ቁስ ሁሉ ከቦታው የሚያፈልስ ነው፤ ምድርን የሚገለባብጥ ናደት ነፋስ የሚባልም አለ፡፡
ዐውሎ ነፋስ/ኵርፊት ነፋስ በበርሓ ቦታ ከመሬት ላይ አዋራውን፣ አሸዋውን እንደ ጋር እያስመሰለ የሚጠርግና ወደ ሕዋ እያወጣ የሚበትን ጥቅል ነፋስ፣ ተጠቅሎ፣ ቀና ብሎ፣ ዐምድን መስሎ ወደ ዐየር የሚወጣ፣ ሰውን ከብትን እየዋጠ የሚያስቀር ነው፡፡ ጠሮ ነፋስ ወይም ጥቅል ነፋስ ከወደ ሰማይ ዘንድ መስሎ፣ በረዶውን ቋጥሮ ተዥሞልሙሎና ተያይዞ እንደ አዙዋሪት የእንዝርት ራስ እየተንሸረሸረ ወደ ምድር ሲወርድና ዝቅ ሲል እየተስፋፋ ወርዶ ቤትን፣ ዛፍን የሚገለባብጥ ነው፡፡
ወዠብ ነፋስ፡- ነፋስና የዝናም ወጨፎ በአንድነት እየነፈሰና እየወዠበ የሚዘንብ፣ ሰውንም ከብትንም በወጨፎ የሚወዥብ ነው፡፡
ውቅንብል ነፋስ በቀኝ እና በግራ እየተራጨ የሚያማታ፣ ትቢያውን ግብስብሱን እየጠረገ የሚረጭ ነፋስ ነው፡፡

ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ጳውሎስ ስለ ውቅንብል ነፋሱ ያሉት ቀጥተኛ ነገር ባይታወቅም የሕንፃውን ዕብነ መሠረት ያስቀመጡት ግን የቀድሞዎቹ ደጋግ አባቶች ባቆዩት ይዞታ ላይ በመሆኑ እርሳቸው ያስቀመጡት የመሠረት ድንጋይ አዲስ እንዳልሆነ ተናግረዋል ተብሏል፡፡ ዘጠኝ ሰዓት ላይ የአደባባዩ ባሕረ ጥምቀት መርሐ ግብር ተጠናቅቆ ሦስቱ ታቦታቱ ወደ መንበረ ክብራቸው ተመልሰዋል፡፡
በኢትዮጵያ ከሚታወቁት አብሕርተ ምጥማቃት - የአኵስሙ ማይ ሹም፣ የጎንደሩ የፋሲል ግንብ፣ በላስታ የንጉሥ ላሊበላ መዋኛ፣ የሸንኮራ ሜዳው ራቡቴ ወንዝ እና የአዲስ አበባው ጃንሆይ ሜዳ (ጃንሜዳ) - አንዱ የሆነው የዐፄ ዘርዐ ያዕቆብ ፍርድ መስጫ አደባባይ በደብረ ብርሃን ከተማ የሚገኙ ዘጠኝ ታቦታት (የቅድስት ሥላሴ፣ ቅድስት ማርያም፣ ኪዳነ ምሕረት፣ ቅዱስ ዑራኤል፣ ቅዱስ ቂርቆስ፣ ቅዱስ ጊዮርጊስ፣ ጻድቁ አቡነ ገብረ መንፈስ ቅዱስ፣ ቅዱስ ሩፋኤል፣ ልደታ ለማርያም) የሚያድሩበት የጥምቀተ ክርስቶስ እና የመስቀል ደመራ፤ የቃና ዘገሊላ እና ብርሃን የወረደበት መጋቢት 10 ቀን በዓላትም ማክበርያ ቦታ ነው፡፡
አደባባዩ 24,883 ካሬ ሜትር ስፋት ያለው ሲሆን እንደ ሊቀ ትጉሃን ኀይለ ጊዮርጊስ ዳኜ (አሁን የዕቅድና ልማት መምሪያ ም/ሓላፊ) ለእስራት ከተዳረጉ፣ አቶ ሳሙኤል ቤተ ማርያም፣ ወ/ሪት መሶበ ወርቅ ቅጣው፣ መጋቤ አእላፍ ማሙዬ ሸዋፈራሁ፣ ዲ/ን ኢንጅነር ጌታሁን ታደሰ እና መ/ር ማንያዘዋል አበበ ያሉቱ አገልጋዮችና ምእመናን ካደረጉት እልህ አስጨራሽ ውጣ ውረድ በኋላ ለአንድ የግል ባለሀብት ተላልፎ ከመሰጠት ተርፎ ጳጉሜ 2 ቀን 1999 ዓ.ም የከተማው ማዘጋጃ ቤት ይዞታው የደብረ ብርሃን አብያተ ክርስቲያን መሆኑን በማረጋገጥ ለሰሜን ሸዋ ሀገረ ስብከት የባለቤትነት ካርታ ሰጥቷል፡፡
አሁን በአገልግሎት የኪራይ ገቢ ለማስገኘት በሚል የታሰበውን ሕንፃ የሰሜን ሸዋ ሀገረ ስብከት፣ የሸንኮራ ደብረ መንክራት ቅዱስ ዮሐንስ፣ የጻድቃኔ ማርያም እና ደብረ ምጥማቅ አብያተ ክርስቲያን በጋር በመሆን ነው፡፡ ግንባታው የአደባባዩን አንድ ጠርዝ ተከትሎ በልዩ ሁኔታ እንደሚሠራ ተገልጧል፡፡ ሆኖም የቦታው ቅርሳዊ ዋጋ ከአደባባይነቱ ጋር መያያዙን፣ እንዲሁም በዐበይት በዓላት በአደባባዩ የሚገኘውንና በየጊዜው እየጨመረ የሚሄደውን የምእመናን ቁጥር ከግምት በማስገባት የሕንፃው መገንባት የቦታውን የ”አደባባይ ቅርስነት” እንደሚያጠፋው፣ እንደሚያደበዝዘው በማመልከት አጥብቀው የሚቃወሙ አካላት አሉ፡፡ የግንባታው መፈቀድ/መካሄድ በቤተ ክርስቲያን ስም “ከውጭ ተቀናቃኝ ወደ ውስጥ ጥቅመኞች የተላለፈበት ስልት” መሆኑን የሚያስረዱት ተቃዋሚዎቹ አደባባዩን ለማልማት ሌሎች አማራጮች መፈተሽ እንዳለባቸው አስተያየት ይሰጣሉ፡፡
ተቺዎቹ ከአደባባዩ ወዲያ በመካከል ያለውን አውራ ጎዳና ተሻግሮ በሚገኘው የደብረ ብርሃን ቅድስት ሥላሴ ቤተ ክርስቲያን ቅጽር ውስጥ የነበሩትን ዕድሜ ጠገብ እና አገር በቀል የደብሩን ዐጸደች በመቁረጥ አገልገሎት የሚሰጥ ሕንፃ ቀደም ሲል መገንባቱን ያስታውሳሉ፡፡ ይህም ለቅድስት ቤተ ክርስቲያን ክብር እና ቅድስና መጠበቅ አሉታዊ አስተዋፅኦ ያለው በመሆኑ በደብረ ብርሃን ቅድስት ሥላሴ ብቻ ሳይሆን በአዲስ አበባና ሌሎች ከተሞችም ከቤተ ክርስቲያን ጋር ተያይዘው፣ ኩታ ገጠም ተደርገው የሚሠሩ ሕንፃዎች አገልግሎት ሊታሰብበት እንደሚገባ ይመክራሉ፡፡
የደብረ ብርሃን ቅድስት ሥላሴ ቤተ ክርስቲያን በ1904 የተመሠረተ ሲሆን በያዝነው ዓመት 100ዓመቱን ይይዛል፡፡

9 comments:

Anonymous said...

ልብ ያለው ልብ ይበል!!!

lele said...

AMELAKA KEDOSANE BATA KERESETANEN YETABEKALE

Anonymous said...

Neseha enegeba;;;;;;;

Anonymous said...

batsalote enebareta gana bezo tamer enayalane edema kasatane.

123--- said...

Kirs lematfat yalachew Tigat!!! Timketin metages akate???

Anonymous said...

DEBREBIRHAN SILLASSIE KETEMESERETE 100 AMET? SLEYETGNAW BETEKRSTIAN NEW YEMTAWERUT?

Anonymous said...

DEBRE BIRHAN SLASSIE KETEMESERETE SINT AMETU NEW?

Anonymous said...

Amleke ethiopia firdun yisten

Anonymous said...

kidus amanuel ethiopian kene kibirua kene ayimanota yitebik. amen

Blog Archive

የአቡነ ጳውሎስ "ሐውልተ ስምዕ"

ነጻ ፓትርያርክ ምርጫ ቢሆን ኖሮ ማንን ይመርጡ ነበር? እንበልና ሁሉም ነገር ሥርዓቱን ጠብቆ የተከናወነ የእጩዎች ምርጫ ቢሆን ኖሮ፣ አሁን የምናነሣቸው ጉድለቶች ባይኖሩ ኖሮ፣ 6ኛው ፓትርያርክ እንዲሆን የምትመርጡት ማንን ነበር? (ማሳሰቢያ፦ አሁን ያለው ክፍፍል እና የመንግሥት ተጽዕኖ ባይኖር ኖሮ ተብሎ የሚመለስ ጥያቄ ነው። የምን “ባይኖር ኖሮ ነው” የሚል አስተያየት ካለዎትም እናከብራለን።)