January 19, 2012

አርዕስተ ዜና፦ የኩሪፍቱ ሪዞርት እና ስፓ የባቦ ጋያ መድኃኔዓለም ባሕረ ጥምቀት እና መስቀል ደመራ ቦታ “የይዞታ ባለመብት ነኝ” እያለ ነው

(ደጀ ሰላም፣ ጥር 10/2004 ዓ.ም፤ January 19/2012/ READ THIS ARTICLE IN PDF.
  • የኩሪፍቱ ሪዞርት እና ስፓ ሥራ አስኪያጅ የሆኑትና “ውል ተቀባይ ናቸው” የተባሉት አቶ ታዴዎስ ጌታቸው “የደብሩ የልማት ኮሚቴ ተጠሪ” ናቸው፤ ከባሕረ ጥምቀቱ እና መስቀል ደመራው አጠቃላይ 13,020 ካሬ ሜትር ይዞታ ላይ ለሪዞርቱ ማስፋፊያ በሚል በሊዝ የወሰዱትን 11,000 ካሬ ሜትር መሬት በድርጅታቸው ስም ካርታ እና ፕላን በቢሾፍቱ ማዘጋጃ ቤት አሠርተውለታል፡፡ በምትኩ በቤተ ክርስቲያኒቱ ሓላፊነት ሥር ለሚቋቋም ሙዓለ ሕፃናት፣ ክሊኒክ፣ ዳቦ ቤት፣ ወፍጮ. . . መሥሪያ ወጪ በወሰዱት የማስፋፊያ ቦታ ላይ ግንባታ አጠናቀውና በይፋ ሥራ ጀምረው ጥቅም ማግኘት ከጀመሩበት ወር አንሥቶ በየወሩ ብር 20,000 “በግል ፈቃደኛነት እና በበጎ ፈቃድ ለመስጠት ተስማምተዋል”
  • የሪዞርቱ ባለቤት ቦታውን በሊዝ ወስዶ በይዞታ ባለቤትነት እንዲጠቀምበት ውል የተዋዋሉት የደብሩ አስተዳዳሪ መልአከ ፀሐይ ቆሞስ አባ የማነ ብርሃን ታደሰ፣ ምክትል ሊቀ መንበሩ አቶ መኰንን ግሩም፣ ጸሐፊው መዘምር ገብረ ሕይወት ዋለልኝ ናቸው፤ ውሉን የሀገረ ስብከቱ ሊቀ ጳጳስ ብፁዕ አቡነ ጎርጎርዮስ አጽድቀዋል፡፡ የደብሩ ሰበካ ጉባኤ ከተመረጠ ስምንት ዓመታት ያለፉ ሲሆን የኦዲት ይሁን ሌሎች የሥራ ሪፖርቶችን አቅርቦ አያውቅም፡፡ በምእመኑ በአዲስ መልክ የመረጣቸውን የሰበካ ጉባኤ አባላት ሀገረ ስብከቱ መካተት ይገባቸዋል በሚላቸው የቀድሞው ሰበካ ጉባኤ አንዳንድ አባላት ምክንያት አላጸድቅም ብሏል፡፡ የካህናቱ ደመወዝ በምእመኑ እና በጎ አድራጊዎች ርዳታ ነው የሚሸፈነው፡፡
  • በውል ሰጪው የደብሩ ሰበካ ጉባኤ እና በውል ተቀባዩ የሪዞርት እና ስፓ ሥራ አስኪያጁ መካከል ተደረሰ የተባለውን ስምምነት ከይዞታው ቆርሶ ለቤተ ክርስቲያን መሥሪያ፣ ለመካነ መቃብር፣ ለባሕረ ጥምቀት እና መስቀል ደመራ በዓላት ማክበሪያ ከሰጠው ምእመን የተሰወረ ነው
  • ሊቀ ጳጳሱ ብፁዕ አቡነ ጎርጎርዮስ “እጃችሁን ተይዛችሁ እስር ቤት ትገባላችሁ” በሚል በካህናቱ እና ምእመናኑ በተቋቋመው የይዞታ አስመላሽ ኮሚቴ አባላት ላይ እየዛቱ ነው፤ ለሦስት ቀንም ያሳሰሯቸው የይዞታ አስመላሽ ኮሚቴ አባላትም አሉ፡፡ “ይዞታችንን አሳልፎ የሚሰጥ አባት የለንም” ያሉት ምእመናኑ በበኩላቸው የባሕረ ጥምቀት ይዞታቸው እንዲከበር፣ እስከዚያው ድረስ የዛሬውን በዓል የሚያከበሩበት ጊዜያዊ ቦታ እንዲሰጣቸው ጠይቀዋል
  • ውዝግቡ እልባት እስኪሰጠው ድረስ የደብሩ ካህናት እና ምእመናን የጥምቀት በዓልን የሚያከብሩበት እንዲመቻችላቸው ጥር 3 ቀን 2004 ዓ.ም “በስልክ ለሥራ አስኪያጁ በመደወል አሳስበዋል” ቢባልም የይዞታ አስመላሽ ኮሚቴ አባላቱ የቅዱስነታቸው አባታዊ መምሪያ እንዳልተከበረ አስታውቀዋል፤ አቡነ ጳውሎስ የኩሪፍቱ ሪዞርት እና ስፓ የክብር አባል(VIP) መሆናቸው የተዘገበ ሲሆን ከሥራ አስኪያጁ ጋራ ባደረጉት የስልክ ልውውጥ ይኸው ‹ወዳጅነታቸው› እንደ ቀጠለ መሆኑን የሚያሳብቁ ልውውጦችን አድርገዋል ተብሏል
  • በ6410 ሜትር ካሬ ስፋት ላይ የሰፈረው የኩሪፍቱ ሪዞርት እና ስፓ ከአዲስ አበባ 50 ኪ.ሜ ላይ የሚገኝ ሲሆን ዘመናዊ እና ውድ የመዝናኛ አገልግሎት ይሰጣል፡፡ በሪዞርቱ ለአንድ ቀን የመኝታ አዳር ብቻ እንደ የደረጃው በትንሹ ከ150 የአሜሪካን ዶላር ያላነሰ ይከፈልበታል፡፡ አባላት በየዓመቱ ከብር 3000 ያላነሱ የሚከፍሉ ሲሆኑ በመኝታ፣ ማሳጅ፣ ሳውና፣ ፀጉር ሥራ፣ ጃኩዚ እና ሌሎችም አገልግሎቶች ላይ የ25 በመቶ ቅናሽ ያገኛሉ፡፡
Post a Comment

Blog Archive

የአቡነ ጳውሎስ "ሐውልተ ስምዕ"

ነጻ ፓትርያርክ ምርጫ ቢሆን ኖሮ ማንን ይመርጡ ነበር? እንበልና ሁሉም ነገር ሥርዓቱን ጠብቆ የተከናወነ የእጩዎች ምርጫ ቢሆን ኖሮ፣ አሁን የምናነሣቸው ጉድለቶች ባይኖሩ ኖሮ፣ 6ኛው ፓትርያርክ እንዲሆን የምትመርጡት ማንን ነበር? (ማሳሰቢያ፦ አሁን ያለው ክፍፍል እና የመንግሥት ተጽዕኖ ባይኖር ኖሮ ተብሎ የሚመለስ ጥያቄ ነው። የምን “ባይኖር ኖሮ ነው” የሚል አስተያየት ካለዎትም እናከብራለን።)