January 16, 2012

በሐዲያ ዞን ምንነቱ ያልታወቀ የሰማይ እሳት ቤቶችን እየለየ በማቃጠል ላይ ነው


  • READ THE ARTICLE IN PDF.
  • እሳቱ እሳታዊነት በጩኸት ይበረታል፤ በእልልታ ይከስማል
  • እሳቱ ቤቶቹን የሚያቃጥለው “ምልክትና ማስጠንቀቂያ ከሰጠ በኋላ” ነው
  • “የእግዚአብሔር ቁጣ ነው፤ በአካባቢያችን ኑፋቄ፣ ውሸት፣ ክፉ ቅንዐት እና ንብረት መቀማማት በርክቶ ይታያል”/የአካባቢው ነዋሪ/

(ደጀ ሰላም፣ ጥር 6/2004 ዓ.ም፤ January 15/2012)፦ በቅዱስ መጽሐፍ የተወደደ መሥዋዕት/ቍርባን ለሚያቀርቡ አንዳንድ ሰዎች እግዚአብሔር በእሳት ይመልስላቸው ማለትም እሳት ከሰማይ እየወረደ መሥዋዕታቸውን ይበላ እንደ ነበር ተጽፏል፤ እግዚአብሔርም ብዙ ጊዜ ራሱን በእሳት ነበር የሚገልጠው፡፡ ይኸውም እሳት የእግዚአብሔርን ክብር፣ ሕዝበ እስራኤልንም የመጠበቁን ሁኔታ ማመልከቻ ነበር፡፡ እሳት የእግዚአብሔርን ቅድስና፣ ጽድቅ እና ቁጣ እንደሚያሳይ ተገልጧል፡፡ ሰሞኑን በደቡብ የአገራችን ክፍል የተከሠተውና ይህ ዘገባ እስከተጠናከረበት ሰዓት ድረስ ያልጠው እሳት ክሥተት/ባሕርይ በመጽሐፍ ቅዱስ እሳት የፍትሐ እግዚአብሔር ምሳሌ እንደሆነ የተገለጸውን እንደሚያረጋግጥ አስተያየት እየተሰጠበት ይገኛል፡፡

በከምባታ ሐዲያ ጉራጌ እና ስልጤ አህጉረ ስብከት በሐዲያ ዞን ሊሙ ወረዳ ናራ መድኃኔ ዓለም አጥቢያ ከአንድ ሳምንት በፊት የተከሠተው ይኸው እሳት ቤቶችን እየለየ በማቃጠል ላይ መሆኑን የሰበካው ምእመናን ተናግረዋል፡፡ ሸንቆላ በተሰኘው ተራራ አቅራቢያ በሚገኘው የናራ መድኃኔዓለም ቤተ ክርስቲያን አጥቢያ ያለማቋረጥ በሚከሠተው እሳት እስከ አሁን በሰው ሕይወት ሆነ አካል ላይ የደረሰ ጉዳት ባይኖርም 36 ቤቶች መቃጠላቸው ተዘግቧል፡፡
ቤቶቻቸው የተቃጠሉባቸው ነዋሪዎች ከድንኳን በተሠራላቸው ጊዜያዊ መጠለያ ለማቆየት ጥረት የተደረገ ቢሆንም እሳቱ ድንኳኑንም ከማቃጠል አልተመለሰም፡፡ በአሁኑ ወቅት ተፈናቃዮቹ ልዩ ባሕርይ ያለው እሳት ብቻ ሳይሆን በሌሊቱ ሰዓት ከብቦ ከሚያስፈራራቸው የጅብ መንጋ ጋም ለመፋጠጥ መገደዳቸው ተነግሯል፡፡ የደቡብ ክልላዊ መንግሥት ርእሰ መስተዳድር አቶ ሽፈራው ሽጉጤ በፍራው ተገኝተው የደረሰውን ጉዳት የተመለከቱ ሲሆን ርእሰ መስተዳድሩ ራሳቸው ባሉበት እሳቱ ሁለት ቤቶችን ሲያቃጥል መታየቱ ተመልክቷል፡፡
ከሆሳዕና ከተማ ከ40 - 50 ኪ.ሜ ወይም ከሦስት ሰዓት የእግር ጉዞ ርቆ በሚገኘው መንደር የተከሠተው እሳት ቀደም ሲል በተመሳሳይ አኳኋን በምሥራቅ ሐረርጌ ሀገረ ስብከት ከታየውና በመቶዎች የሚቆጠሩ መኖሪያ ቤቶችን አጋይቶ በርካታ ቤተሰቦችን ካፈናቀለው የሰማይ እሳት የተለየ ባሕርይ ያለው ነው ተብሏል፡፡ የዐይን ምስክሮች እንደተናገሩት፣ እሳቱ በቤቶች መካከል ቢከሠትም የእሳቱ ነበልባል ከአንዱ ወደ ሌላው ሊዛመት በሚችልበት መልኩ እየታየ ሁሉንም ቤቶች ሳይሆን እያለፈ ነው የሚያቃጥለው፡፡ የቤቶቹ ቃጠሎ የሚጀምረው ከላይ/ከክዳናቸው በመሆኑ ነዋሪዎች ራሳቸውንና ንብረታቸውን ለማዳን ዕድል ይሰጣቸዋል፤ ከዚህ የቅድመ ቃጠሎ ምልክት/ማስጠንቀቂያ በኋላም ቤቱ ሙሉ በሙሉ ይቃጠላል፡፡
እስከ አሁን በእሳቱ እየተለዩ ከነደዱት 36 ቤቶች ብዙዎቹ የፕሮቴስታንት እምነት ተከታይ የሆኑ ነዋሪዎች ንብረቶች መሆናቸውን የተናገሩት የዐይን እማኞቹ፣ እሳቱ ንብረታቸው በሚጋይባቸው ነዋሪዎች ጩኸት መጠኑ ተባብሶ እንደሚጨምር፣ እልልታ ሲያሰሙ ደግሞ መጠኑ እንደሚቀንስና እንደሚከስም ማስተዋላቸውን አስረድተዋል፡፡ በክሥተቱ መጀመሪያ ላይ አደጋው ሰው ሠራሽ ነው በሚል ፖሊስ የተወሰኑ ሰዎችን በቁጥጥር ሥር አውሎ የነበረ ቢሆንም ከሁኔታው ያልተለመደ መደጋገም ምክንያት የታሰሩት ሰዎች መለቀቃቸው ተጠቁሟል፡፡
ክሥተቱ የእግዚአብሔር ቅጣት እንደሆነ የተናገሩ አንድ ነዋሪ፣ “ውሸት ይበዛል፤ በጣም እንዋሻለን፤ ምንፍቅናውም እዚህ ነው የበረከተው፤ በአካባቢያችን በተለይም ከመሬት አጠቃቀም ጋራ በተያያዘ ቃልን አለመጠበቅ፣ መቀናናት፣ አለመደማመጥ በተደጋጋሚ ይታያል፤” ሲሉ ሳይንሳዊ ማብራሪያ ለመስጠት አዳጋች የሆነውን እሳታዊ ክሥተት መንሥኤ አስረድተዋል፡፡  
ክሥተቱ ከታወቀበት ዕለት አንሥቶ የሰበካው ኦርቶዶክሳዊ ምእመናን በናራ መድኃኔዓለም ቤተ ክርስቲያን እየተገኙ ጸሎተ ምሕላ እንደሚያካሂዱ ተዘግቧል፡፡ ግንድ አንሣው  (በቅጽረ ቤተ ክርስቲያኑ ከወደቀ የቆየ ግንዲላ ተነሥቶ በቆመበት ተኣምር) በሚል የሚታወቀው የናራ መድኃኔዓለም ታቦት በ1990 ዓ.ም ገደማ ተሰርቆ በተወሰደበት ሆሳዕና ከተማ ዘራፊው እንዳይንቀሳቀስ በማሰር በቁጥጥር ሥር ሲውል፣ ታቦቱም በታላቅ ክብር ወደ መንበሩ መመለሱ ተነግሯል፡፡
የሰሞኑን ክሥተት ደግሞ ምእመናኑ በጸሎተ ምሕላ እያዘኑበት፣ እያመለከቱበት ይገኛሉ፡፡


Post a Comment

Blog Archive

የአቡነ ጳውሎስ "ሐውልተ ስምዕ"

ነጻ ፓትርያርክ ምርጫ ቢሆን ኖሮ ማንን ይመርጡ ነበር? እንበልና ሁሉም ነገር ሥርዓቱን ጠብቆ የተከናወነ የእጩዎች ምርጫ ቢሆን ኖሮ፣ አሁን የምናነሣቸው ጉድለቶች ባይኖሩ ኖሮ፣ 6ኛው ፓትርያርክ እንዲሆን የምትመርጡት ማንን ነበር? (ማሳሰቢያ፦ አሁን ያለው ክፍፍል እና የመንግሥት ተጽዕኖ ባይኖር ኖሮ ተብሎ የሚመለስ ጥያቄ ነው። የምን “ባይኖር ኖሮ ነው” የሚል አስተያየት ካለዎትም እናከብራለን።)