January 6, 2012

የአራዳው ፍ/ቤት መ/ር ዘመድኩን እንዲከላከል አዘዘ


  • READ THIS ARTICLE IN PDF.
  • በእናቱ ሞት በደረሰበት ኀዘን እና በቁሉቢ ጉዞ በአራዳው ምድብ ችሎት በቀጠሮ ያልተገኘው መ/ር ዘመድኩን “የመደመጥ መብቴ ተነፍጓል፤ ከውሳኔ አስቀድሞ አቋም ተይዞብኛል” በማለት በዳኛው ላይ ምሬቱን ገልጧል::
  • “እናቱ ለመሞታቸው የሕክምና ማስረጃው ተተርጉሞ ይቅረብ፤ ከገብርኤል እና ከፍ/ቤት ማን ይበልጣል?” (ዳኛው)::
  • “ሊጠፋብን ስለሚችል ማረፊያ ቤት እንዲቆይ ይታዘዝልን”(ዐቃቤ ሕግ)::
  • በቦሌው ምድብ ችሎት መ/ር ዘመድኩን የመከላከያ ምስክሮቹን አሰምቷል፤ ሊቀ ጠበብት ዘሪሁን መከላከያ ምስክር ሆነው ቀርበዋል::
  • ማይምን” “መጋቤ ሐዲስ” የሚሉት ማብራሪያ ተሰጥቶባቸዋል::
(ደጀ ሰላም፣ ታኅሣሥ 26/2004 ዓ.ም፤ January 5/2012)፦ በአርማጌዶን ቪሲዲ የስም ማጥፋት ወንጀል ክስ የተመሠረተበት መ/ር ዘመድኩን በቀለ ክሱን እንዲከላከል የፌዴራሉ የመጀመሪያ ደረጃ ፍ/ቤት አራዳ ምድብ ችሎት አዘዘ፡፡
መ/ር ዘመድኩን እንዲከላከል የታዘዘው የዐቃቤ ሕግ ሁለተኛ ምስክር ታሪኩ አበራ፣ “መ/ር ዘመድኩን ሰሜን ሆቴል ቀጥሮ አግኝቶኝ የግል ተበዳይን በጋሻው ደሳለኝን በአርማጌዶን ካሴት ከሕዝብ ልብ አስወጥቸዋለሁ፤ በአርማጌዶን ቪሲዲ ደግሞ ሕዝቡ ቀጥቅጦ እንዲገድለው ነው የማስደርገው ብሎኛል” በማለት የተናገረውን የምስክርነት ቃል እንዲሁም አቡነ ጳውሎስ በቁጥር ል/ጽ/598/1634/03 በቀን 24/11/2003 ዓ.ም “አንዳንድ የሃይማኖት ሕጸጽ ያለባቸው ሰዎች ከሃይማኖታችን የተለየ ትምህርት ይሰጣሉ በማለት ስም በመጥቀስ ልዩ ልዩ ጽሑፎችን የሚበትኑ ግለሰቦችንና ድርጅቶችን አስመልክቶ የሰጡትን መምሪያ” የተመለከተውን ሰነድ ነው፡፡ መ/ር ዘመድኩን ጥር 8 ቀን 2004 ዓ.ም ከቀትር በኋላ በ8፡00 የመከላከያ ምስክሮችን እንዲያቀርብ ፍርድ ቤቱ ትእዛዝ ሰጥቷል፡፡
ዛሬ፣ ታኅሣሥ 26 ቀን 2004 ዓ.ም ረፋድ ላይ የነበረው የፍ/ቤቱ ውሎ ተከሳሹ መ/ር ዘመድኩንና ጠበቃው ጌትነት የሻነህ ከዳኛው ጋር አተካራ የገጠሙበትን፣ ኀይለ ቃል የተለዋወጡበትን በዚህም ስሜቱ የተጎዳው መ/ር ዘመድኩን ያነባበትን ትዕይንት ያስተናገደ ነበር፡፡ በአተካራውና የኀይለ ቃለ ልውውጡ ተከሳሹ መ/ር ዘመድኩን በጠበቃው ይሁን በራሱ በኩል ለማስረዳት በፈለገው ጉዳይ በችሎት የመደመጥ መብቱ እንደተነገፈ፣ ከሚዛናዊ ፍትሕ አሰጣጥ አኳያም ተከሳሽ ክሱን እንዲከላለከል ዳኛው ትዛዙን ያነበቡበት መግለጫ ከብይን በፊት እርሱን በጥፋተኝነት በመፈረጅ አቋም የተያዘበት እንደሆነ ገልጧል፡፡ በዳኛው በኩል ደግሞ መ/ር ዘመድኩን ያቀረበው ምክንያት ምንም ይሁን በዛሬው ችሎት ተከሳሹ ታስሮ መቅረብ እንደነበረበት፣ በራሳቸው ቃልም “ያስያዘው ዋስትና ለመንግሥት ገቢ ተደርጎ፣ ወደ እስር ቤት ተወርውሮ፣ ከእስር ቤት ሆኖ ጉዳዩን እንዲከታተል” በእጅጉ እንደሚፈልጉ ያሳዩበት ያልተጠበቀና አስጊ አዝማሚያ ሆኗል፡፡ ይ ህንንም ሁኔታ የተከሳሹ መ/ር ዘመድኩን ወላጅ እናት ሞተ ዕረፍት በንግግሩ ሂደት መገለጽ ከፈጠረው ኀዘን ጋር ተያይዞ ከችሎቱ ተከታታዮች ይሰማ የነበረው የታፈነ ሳግ /የልቅሶ ድምፅ/ ግልጽ አድርጎታል፡፡
የሁሉም መንሥኤ ግን ተከሳሹ መ/ር ዘመድኩን የዛሬውን ትእዛዝ ለመስጠት ችሎቱ አስቀድሞ ቀጠሮ ሰጥቶበት በነበረው ታኅሣሥ 19 ቀን 2004 ዓ.ም በችሎት አለመቅረቡ፤ ይህን ተከትሎም በዛሬው ችሎት መጀመሪያ ላይ ዳኛው ተከሳሹ ለምን ለ24 ሰዓት ታስሮ እንዳልቀረበ ያቀረቡት ጥያቄና ከጥያቄው ቀጥሎ የተካሄደው መካረር የታየበት የቃላት ምልልስ ነው፡፡ የፖሊሱ ተወካይ “ተከሳሹ ታስሮ ይቅረብ” የሚለውን ትእዛዝ ለማስፈጸም በሚገኝበት አድራሻ መሄዳቸውን፣ ይሁንና በእናቱ ሞት ምክንያት በኀዘን ላይ እንደነበረ በመረዳታቸው አስረው ለማቅረብ መቸገራቸውን፣ በዛሬው ተለዋጭ ቀጠሮ ግን እንዲገኝ ማድረጋቸውን አስረድተዋል፡፡
መ/ር ዘመድኩን ታኅሣሥ 19 ቀን የቆየ ሕመም የጠናባቸውን ወላጅ እናቱን ለመጠየቅ ወደ ምዕራብ ሐረርጌ ቆሬ አምርቶ የነበረ ሲሆን ወዲያውም የቅዱስ ገብርኤልን ክብረ በዓል በቁሉቢ ለመዋል ሐሳብ ነበረው፡፡ ሆኖም ለሕክምና ደደር ሆስፒታል የገቡት ወላጅ እናቱ እዚያው በማረፋቸው በኀዘን ላይ ነበር፡፡ በቀጠሮው (ታኅሣሥ 19 ቀን) ተከሳሽ በችሎቱ ለመገኘት ያልቻለበትን ይህንኑ ምክንያት ጠበቃው በዕለቱ ቀርበው ለማስረዳት ቢሞክሩም ዳኛው “አልቀበልም፤ እስር ቤት ነው የምወረውረው፤ ዋስትናውንም ለመንግሥት ገቢ አድርጌ እርሱ ከእስር ቤት ሆኖ ይከራከር” ብለው እንደመለሱላቸው ተገልጧል፡፡
ዳኛው ታኅሣሥ 19 ቀን በነበረው ቀጠሮ ጠበቃው ያስረዱትን እንደማይቀበሉ ይናገሩ እንጂ በዛሬው ውሎ ተከሳሹ ስለ ቁሉቢ ጉዞው ታኅሣሥ 9 በነበረው ችሎት አስቀድሞ ማስታወቅ እንደነበረበት፣ ከዚያም በኋላ ስለገጠመው ኀዘንም ከዚህ ችሎት በፊት አቤቱታ ማቅረብ እንደነበረበት ተናግረዋል፡፡ የዐቃቤ ሕግ ምስክሮች ቀርበው በተሰሙበት ታኅሣሥ 9 ቀን የቁሉቢ ጉዟቸውን ሳያስታውቁ የቀሩት በተራዘመው የምስክርነት ሂደት ምክንያት በመዘንጋታቸው መሆኑን ያስረዱት መ/ር ዘመድኩን፣ ጠበቃቸው በቀጠሮው ቀን ለችሎቱ ያስረዱት ምክንያት ተቀባይነት አለማግኘቱን ባስታወቋቸው መሠረት ከኀዘን ላይ ተነሥተው ታኅሣሥ 20 ቀን አዲስ አበባ ደርሰው የገጠማቸውን እክል ለዳኛው በቢሮ ለማስረዳት ቢሞክሩም ዳኛው በማመናጨቅ ሊሰሟቸው እንዳልፈለጉ አስታውቀዋል፡፡
“ጠበቃ ያቆምሁት እኔን እንዲወክል፣ በሕግ ፊት ስለእኔ እንዲያስረዳ ነው” ያለው መ/ር ዘመድኩን በተመሳሳይ ጉዳይ በሌላ ችሎት የተከሰሰ ቢሆንም የዚህኛው ችሎት አካሄድ የተለየ እንደሆነበት፣ በጠበቃው በኩልም ይሁን በራሱ ቀርቦ በችሎት የመደመጥ መብቱ ከተነፈገ ጠበቃውን ከዛሬ ጀምሮ ለማሰናበት እንደሚገደድ፣ ራሱን ችሎ እንደሚከራከርም በተማረረ ስሜት ገልጧል፤ ስለ እናቱ ሞት በሚያስረዳበት ወቅትም ዳኛው፣ “በቂ ምክንያት አይደለም፤ ስለ እርሱ ምን አገባኝ፤ የተለየ ፍ/ቤት የለም፤ አለቃዬ ስላለ ክሰሰኝ በማለታቸው በእጅጉ የተሰማው መ/ር ዘመድኩን፣ “እናቴን አልቀበርኩም፤ ፍ/ቤቱን አክብሬም አልተከበርኩም፤ እናቴንና እርስዎን አልረሳችሁም፤ ክሱን አልፈራም፤ እንዴት ግን ሰብአዊነት አይሰማዎትም?” ብሎ አንብቷል፡፡
ከዚህ በኋላ ዳኛው መለሳለስ የታየባቸው ቢሆንም የቃላት ምልልሱ በቀጠሮ ቀን አወሳሰን ላይም ተሰምቷል፡፡ የሆነው ሆኖ በመጨረሻ ችሎቱ ተከሳሽ መ/ር ዘመድኩን በቀለ የመከላከያ ምስክሮቹን እና የሰነድ ማስረጃዎቹን፣ የእናቱን ሞት ከሚያስረዳና በአማርኛ ከተተረጎመው የሕክምና ማስረጃን ጨምሮ ለጥር 8 ቀን 2004 ዓ.ም፣ ከቀትር በኋላ በ8፡00 እንዲያቀርብ አዝዟል፡፡
ታኅሣሥ 19 ቀን 2004 ዓ.ም በደደር ሆስፒታል ሕይወታቸው ያለፈው የመ/ር ዘመድኩን ወላጅ እናት ትንት፣ ታኅሣሥ 25 ቀን 2004 ዓ.ም ልጆቻቸውን ወልደው ባሳደጉበት ምዕራብ ሐረርጌ ሀገረ ስብከት ልዩ ስሙ ቆሬ በተባለ ቦታ በሚገኘው የቅዱስ ገብርኤል ቤተ ክርስቲያን ቀብራቸው ተፈጽሟል፡፡ ደጀ ሰላም ለመ/ር ዘመድኩንና መላው ቤተሰቡ መጽናናትን ትመኛለች፡፡
በሌላ በኩል ዐቃቤ ሕግ በፌዴራሉ የመጀመሪያ ደረጃ ፍ/ቤት ቦሌ ምድብ ችሎት የስም ማጥፋት ወንጀል ክስ የመሠረተበት መ/ር ዘመድኩን በቀለ የመከላከያ ምስክሮቹንና የሰነድ ማስረጃዎቹን አቅርቧል፡፡ ተከሳሹ በሐምሌ ወር 2003 ዓ.ም ታትሞ ከወጣው ማራኪ መጽሔት ጋር ከአካሄደው ቃለ ምልልስ ጋር በተያያዘ የተመሠረተበትን ክስ ለመከላከል ሦስት የሰው ምስክሮችን አሰምቷል፤ ባለ16 ገጽ የሰነድ ማስረጃም አያይዞ አቅርቧል፡፡ የግራ ቀኙን ክርክር ያዳመጠው ፍ/ቤቱ የምስክሮችን ቃል እና ሰነዶችን መርምሮ ብይን ለመስጠት ለጥር 24 ቀን 2004 ዓ.ም ቀጠሮ ሰጥቷል፡፡
በመ/ር ዘመድኩን ጠበቃ ጌትነት የሻነህ የተቆጠሩት የመከላከያ ምስክሮች በአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ ፊሎሎጂ ትምህርት ክፍል ባልደረባ የሆኑት መ/ር ደሴ ቀለብ፣ በዚሁ ትምህርት ክፍል የድኅረ ምረቃ ትምህርታቸውን በመከታተል ላይ የሚገኙት ሊቀ ጠበብት ዘሪሁን ሙላቱ ግዛው እና የማራኪ መጽሔት ዋና አዘጋጅ አቶ ሚዮን ሹሩቤ ናቸው፡፡ መ/ር ደሴ ቀለብ ከሥራ ሁኔታ ጋር በተያያዘ ያልተገኙ ሲሆን በችሎቱ ቀርበው ምስክርነታቸውን የሰጡት ሊቀ ጠበብት ዘሪሁን ሙላቱ እና አቶ ሚዮን ሹሩቤ ናቸው፡፡
ታኅሣሥ 23 ቀን 2004 ዓ.ም ጠዋት በቦሌ ምድብ ችሎት በነበረው የፍ/ቤቱ ውሎ የተከሳሽ ጠበቃ ባስያዙት ጭብጥ፡- ሊቀ ጠበብት ዘሪሁን ሙላቱ በክሱ ጽሕፈት ላይ እንደ ስም ማጥፋት ተደርገው ስለቀረቡት ጉዳዮች በተለይም ማይምን/መሀይምን እና ሕገ ወጥ ስለተባሉ ቃላት ሓሳብ እንደሚያስረዱ፤ አቶ ሚሊዮን ሹሩቤም በዋና አዘጋጅነት በሚሠሩበት ጋዜጣ ላይ መ/ር ዘመድኩን የሰጡት ቃለ ምልልስ ስም አጥፊ ላለመሆኑ እንደሚያስረዱ ገልጸዋል፡፡
ከተከሳሽ እና ‹የግል ተበዳይ› ጋር ስላላቸው ትውውቅ በዳኛው የተጠየቁት ሊቀ ጠበብት ዘሪሁን ሙላቱ÷ መ/ር ዘመድኩንን እና በጋሻው ደሳለኝን በቅድስት ሥላሴ መንፈሳዊ ኮሌጅ በሚማሩበት ወቅት እንደሚያውቋቸው አስታውሰው መ/ር ዘመድኩንና እርሳቸው ትምህርታቸውን ጨርሰው ሲወጡ የግል ተበዳይ የተባለው ግን ትምህርቱን ማቋረጡን አስረድተዋል፡፡ ዐቃቤ ሕግ ተከሳሽ ማራኪ ከተባለው መጽሔት ጋር ባካሄዱት ቃለ ምልልስ “አንዳችም የስም ማጥፋት ንግግር የለምን?” ሲሉ ለሊቀ ጠበብት ዘሪሁን ሲጠይቋቸው ምስክሩ “የለም” ሲሉ መልሰዋል፤ ዐቃቤ ሕጉም “መሀይም[ን] ማለት ምን ማለት ነው?” በማለት ጠይቀዋቸዋል፡፡ ሊቀ ጠበብት ዘሪሁንም “መሀይም[ን] ማለት ያለ ምንም ፍልስፍና፣ ትንታኔና ሳይንሳዊ ማስረጃ ፈጣሬ ዓለማት እግዚአብሔር አለ ብሎ የሚያምን አማኝ፣ ምእመን ማለት ነው፤” ብለው መልሰዋል፡፡
“አማኝ እንጂ አስተማሪ መሆን አይችልም?” በማለት ለቀረበላቸው ጥያቄ “አማኝ መስካሪ እንጂ አስተማሪ መሆን አይችልም፤ መ/ር ዘመድኩን የግል ተበዳይን መሀይም ማለታቸው እግዚአብሔርን ያለዕውቀት/ግንዛቤ የሚያምን በተሰጠው ቃለ ምልልስ ደረጃ ስድብ አይደለም፤ ምናልባት በቋንቋ ትምህርት semantic change የሚባል ነገር አለ፤ ይኸውም በአንድ ወቅት መልካም ትርጉም የነበረው ቃል በሌላ ወቅት መጥፎ ትርጉም ሊይዝ ይችላል፡፡ በመጽሔቱ ቃለ ምልልስ ውስጥ መሀይም[ን] የሚለው ቃል በሃይማኖት ትምህርት የዕውቀት እጥረትን፣ ምንም አለማወቅን የሚያሳይ ነው፤” ብለዋል፡፡
ምስክሩ በመቀጠል የቀረበላቸው የዐቃቤ ሕግ ጥያቄ፣ “እንዲህ ዐይነቱን ትርጉም የምትሰጥበት ትምህርትህ፣ ማረጋገጫህ ምንድን ነው?” የሚል ነበር፡፡ ፍ/ቤቱ እስከዚህ ደቂቃ ድረስ የትምህርት እና የሥራ ደረጃቸውን ባለመጠየቁ “አዝናለሁ” ያሉት መ/ር ዘሪሁን የተማሩትን ትምህርት ወደ መዘርዘር ገብተዋል፡፡
ከቅድስት ሥላሴ መንፈሳዊ ኮሌጅ በሥነ መለኮት የመጀመሪያ ዲግሪ (B.TH)፣ ከአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ በፊሎሎጂ ትምህርት ሁለተኛ ዲግሪ፣ በአሁኑ ወቅት ደግሞ በዚሁ የፊሎሎጂ ትምህርት የፒኤች.ዲ መርሐ ግብር ቋንቋ እና ፍልስፍና ላይ ከፍተኛ ትምህርታቸውን በማጠናቀቅ ላይ የሚገኙ መሆናቸውን፤ በቤተ ክርስቲያንም ማዕርጋቸው ሊቀ ጠበብት እንደሚባል፣ ግእዝን የሚያውቁ ባለቅኔና በትምህርታቸውም ፊሎሎጂን በከፍተኛ ደረጃ ያጠኑ በመሆናቸው የቋንቋን ፍቺ/ሐሳብ ብቻ ሳይሆን የሆሄያቱን እና ፊደሎቹን ዕድሜ ጭምር ተንትነው ማስረዳት የሚችሉ ባለሞያ መሆናቸው በፍጹም ርጠኝነት ለችሎቱ ተናግረዋል፡፡
ከዚህ የምስክሩ ንግግር በኋላ በአለባበሳቸው እንደነገሩ ሆነው ስለቀረቡት ሊቀ ጠበብት ዘሪሁን ችሎቱ በፍጹም መደመም ተሞልቶ ታይቷል፤ የዐቃቤ ሕጉና የዳኛው አንተታም ወደ አንቱታ ሲለወጥ ለመታዘብ ተችሏል፡፡ ጥያቄ እና መልሱም ቀጥሎ ዐቃቤ ሕግ “አስተማሪ ወይም መምህር መሆን የሚችለው ማን ነው?” የሚል ጥያቄ አቅርቧል፡፡ ምስክሩም በቤተ ክርስቲያን መምህር መሆን የሚችሉት በጥንታዊ ሥርዐተ ትምህርት ከትውፊታዊው የአብነት ት/ቤት የወጡ አልያም ከሦስቱ የቤተ ክርስቲያን ኮሌጆች [ቅድስት ሥላሴ፣ ቅዱስ ፍሬምናጦስ አባ ሰላማ ከሣቴ ብርሃን፣ ሰዋስወ ብርሃን ቅዱስ ጳውሎስ] ትምህርታቸውን ጨርሰው የወጡ መሆናቸውን አስረድተዋል፡፡ “እሺ፣ ከካህናት ማሠልጠኛ የወጣስ?” ለተባሉትም ማሠልጠኛ ማለት ሠልጣኙ ለተወሰነ ጊዜ በሠለጠነበት ጉዳይ እንጂ ሙሉ መምህር ሊሆን፣ መምር ሊባል እንደማይችል ገልጸዋል፡፡
አስከትሎም “መጋቤ ሐዲስ የሚባለው ማዕርግስ እንዴት ነው የሚሰጠው?” በሚል ጠየቀ ዐቃቤ ሕግ፤ ሊቀ ጠበብት ዘሪሁንም “በቤተ ክርስቲያን ጥንታዊ ሥርዐተ ትምህርት መሠረት የግእዝ ቋንቋን ዐውቀው፣ ቅኔን ተምረው፣ የሐዲስ ኪዳን መጻሕፍትን ንባብ፣ ትርጓሜና ምስጢር ዐውቀው ከመምሮቻቸው ማኅተም ሲቀበሉ፤ ፓትርያሪኩ ባሉበት የምስክር ወረቀት ሲሰጣቸው” መሆኑን አብራርተዋል፡፡ ከዚህ አኳያ እርሳቸው በጋሻው ‹መጋቤ ሐዲስ› የተባለበትን የምስክር ወረቀት ይሁን ደብዳቤ ያላዩ/ ያልደረሳቸው መሆኑን ተናግረዋል፡፡
በመቀጠል ዐቃቤ ሕግ “የት ነው የሚሠሩት?” የሚል ጥያቄ አቅርቧል፡፡ ሊቀ ጠበብት ዘሪሁንም አሁን ትምህርታቸውን በመከታተል ላይ መሆናቸውን ቀደም ሲል ግና በቦሌ ደብረ ሳሌም መድኃኔዓለም ካቴድራል ሕዝብ ግንኙነት ሓላፊ እንደነበሩ ተናግረዋል፡፡ ይህን ምላሻቸውን ተከትሎ ዐቃቤ ሕግ “ከዚህ በፊት ተከሰው ነበር?” ሲል ጠይቋል፡፡ የተከሳሽ ጠበቃ ጌትነት የሻነህ ይህን የዐቃቤ ሕግ ጥያቄ በመቃወም ጥያቄው ምስክሩ ሊመሰክሩበት ከመጡበት ጉዳይ ጋር የማይገናኝ በመሆኑ ውድቅ እንዲደረግ አመልክተዋል፡፡ ዳኛውም የጠበቃውን ማሳሰቢያ በመቀበላቸው የዐቃቤ ሕግ ጥያቄ ውድቅ ተደርጎ ወደ ሌላ ጥያቄ መሸጋገር ተደርጓል፡፡
ቀጣዩ የዐቃቤ ሕግ ጥያቄ ሊቀ ጠበብት ዘሪሁን በማራኪ መጽሔት ላይ የወጣውን የመ/ር ዘመድኩን ቃለ መጠይቅ አንብበውት እንደሆነ የሚመለከት ነው፤ ምስክሩም “አዎን፣ አንብቤዋለሁ” አሉ፡፡ “ማንም ሰው እጅ የሚገባና ሕዝብ የሚያነበው ነው፤” - ቀጠለ ዐቃቤ ሕግ፡፡ “አዎ፣ መጽሔቱ ቃለ ምልልስ የሚያስተናግድበት ቋሚ ዓምድ አለው፤ የሚያነቡ ሰዎች መርጠው ሊያነቡ ይችላሉ፤ በመ/ር ዘመድኩንና በግል ተበዳይ መካከል የተፈጠረው ችግር ግን መጽሔቱ ከመጀመሩ በፊት የነበረና የሚታወቅ ነው፤ መሀይም የሚለው ቃል ጥልቅ ዕውቀት/ግንዛቤ የሌለው ማለት ነው፡፡” ዐቃቤ ሕግ በመቀጠልም “ይህን በምን መለካት ይቻላል?” ሲል ላቀረበው ጥያቄ ምስክሩ አንድ አነስተኛ ማሳያ ጠቅሰዋል - “የግል ተበዳይ የጋግራን እሪታ በሚል ርእስ ጽፎ ያሳተመውን መጽሐፍ ለምን አታዩትም፤ በዚህ መጽሐፍ ላይ የግል ተበዳይ ለአጋንንቱ ሁሉ ምስጋናዬን አቀርባለሁ ብሏል፡፡”
የግል ተበዳይ ሕገ ወጥ ስለመባሉ ምስክሩ እንዲያስረዱ ዐቃቤ ሕግ ላቀረበው ጥያቄ ምስክሩ÷ በጋሻው የምርጫ 97ን መነሣሣት ተጠቅሞ “የመስቀሉ ሥር ቁማርተኞች” መጽሐፍ በማሳተም አባቶችን መሳደቡን፣ በሃይማኖት አባቶች እና ታቦት ላይ ድንጋይ ማስወርወሩን፣ እርሳቸውም ከፓትርያኩ በብዳቤ ታዝዘው “የስድብ አፍ” በሚል ርእስ ምላሽ መጻፋቸውን፤ ከግርግሩ በኋላ ከቅድስት ሥላሴ መንፈሳዊ ኮሌጅ ታግደው ከነበሩት 11 ደቀ መዛሙርት ዘጠኙ ተመልሰው ገብተው ትምህርታቸውን ሲያጠናቅቁ በጋሻው ግን በትምህርቱ ሳይዘልቅ እንደወጣ መቅረቱን፣ መታወቂያውም ተሳዳቢነት፣ ብጥብጥ እና ሁከት ፈጣሪነት መሆኑን በማስረዳት ምስክርነታቸውን አጠናቀዋል፡፡
ማራኪ መጽሔት ዋና አዘጋጅ አቶ ሚሊዮን ሹሩቤ ከመ/ር ዘመድኩን ጋር ቃለ ምልልስ ያደረጉት የበጋሻውን አስተሳሰቦችና ተግባራት በመደገፍ (ወገናዊ ሆነው) ተጠያቂውን በመሞገት እንደነበር ለችሎቱ አስረድተዋል፤ በቃለ ምልልሱ ላይም በተደረገው አርትዖትም ባለባቸው ሓላፊነት አስፈላጊው የእርማት ሥራ መሥራታቸውን፣ በዚህም ለአንባቢው ከበድ የሚሉ አገላለጾች እንዲቀሩ ተደርገው ማንንም በማይጎዳ መልኩ መስተናገዱን አስረድተዋል፡፡ ሁለቱን የምስክሮች ቃል ያዳመጠው ችሎቱ ከቀረቡት የሰነድ ማስረጃዎች ጋር በመመርመር በክሱ ላይ ብይን ለመስጠት ለጥር 24 ቀን 2004 ዓ.ም ቀጠሮ ሰጥቷል፡፡
በወቅቱ በምስክርነት ስለቀረቡት ሊቀ ጠበብት ዘሪሁን ሙላቱ የተደበላለቁ ስሜቶች ተስተውለዋል፡፡ ምስክሩ በተለያዩ የብዕር ስሞች ተጽፈው በታተሙ ጽሑፎች ተጠርጥረው ከፍተኛ ተቃውሞ ደርሶባቸዋል፡፡ የወቅቱን ዘገባዎች ያስተላለፈችው ደጀ ሰላም “Ghost Writer” (እውነተኛ ስማቸው ሳይታወቅ እየተከፈላቸው የሚጽፉ) በማለት ሰይማቸው እንደነበር ይታወሳል፡፡
አሁን ሊቀ ጠበብት በሚል የማዕርግ ስም የሚጠሩት የቀድሞው ሊቀ ትጉሃን ዘሪሁን ሙላቱ በመ/ፓ/ጠ/ቤ/ክ የዕሥራ ምእት በዓል አከባበር ጽ/ቤት ሓላፊ ሆነው ሠርተዋል፡፡ ከበዓል አከባበሩ ፍጻሜ በኋላም በቦሌ ደብረ ሳሌም መድኃኔዓለም መጥምቁ ዮሐንስ ወአቡነ አረጋዊ ካቴድራል ሕዝብ ግንኙነት ሓላፊ ነበሩ፡፡ በነሐሴ ወር 2002 ዓ.ም ፈታሔ በጽድቅ በሚል የብዕር ስም በሊቀ ማእምራን ፋንታሁን ሙጬ፣ ወ/ሮ እጅጋየሁ በየነ፣ በጋሻው ደሳለኝ እና ያሬድ አደመ ላይ ያተኮረ “የሐውልቱ ሥር ቁማርተኞች” የተሰኘ መጽሐፍ አዘጋጅተው አሳትመዋል ተብለው በሊቀ ማእምራን ፋንታሁን፣ ወ/ሮ እጅጋየሁ እና በጋሻው የስም ማጥፋት ወንጀል ክስ ተመሥርቶባቸው ነበር፡፡
በክሱ የዋስ መብታቸው ተጠብቆ እንዲወጡ የአዲስ አበባ የመጀመሪያ ደረጃ ፍ/ቤት አራዳ ምድብ ችሎት ወስኖ የነበረ ቢሆንም ባልታወቀ ምክንያት ውሳኔውን ያስገለበጡት እነወ/ሮ እጅጋየሁ በፌዴራሉ መጀመሪያ ደረጃ ፍ/ቤት አራዳ ምድብ ችሎት ክሳቸውን ቀጥለው በተጠርጣሪው ላይ አንድ ዓመት ከስምንት ወር እስራት አስፈርድውባቸው ነበር፡፡ ለአምስት ወራት በቃሊቲ ማረሚያ ቤት የቆዩት ተጠርጣሪው “የመከላከያ ማስረጃዎቼ ውድቅ የተደረጉት በአግባቡ ሳይታዩልኝ ነው፤” በሚል ለከፍተኛ ፍ/ቤት ይግባኝ ጠይቀዋል፡፡ በዚህም ከሳሾቻቸው የመጽሐፉ ጸሐፊ እርሳቸው ለመሆናቸው ከጥርጣሬ በላይ ማስረዳት ሳይችሉ እንዳስፈሩዱባቸው ባቀረቧቸው ማስረጃዎች በማሳመናቸው በታኅሣሥ ወር 2003 ዓ.ም ከእስር ነጻ ይወጡ ዘንድ እንደተወሰነላቸው ተነግሯል፡፡
ሊቀ ጠበብት ዘሪሁን ሙላቱ ግዛው “የማርያም መንገድ” በሚል ርእስ ስለ ነገረ ማርያም የጻፉትን ባለ 300 ገጽ መጽሐፍ ለማሳተም በዝግጅት ላይ የሚገኙ ሲሆን በአሁኑ ወቅት በመሠረታዊ ጉዳዮች ላይ ከፀረ - ተሐድሶ ሰባክያን ምረት ጋር በመተባበር እያገለገሉ ይገኛሉ፡፡ ለዚህም “ኦርቶዶክስ መልስ አላት” በሚል መርሕ በደብረ መዊዕ ቅዱስ ሚካኤል ካቴድራል በየሳምንቱ ረቡዕ፤ በማኅደረ ስብሐት ልደታ ለማርያም ቤተ ክርስቲያን በየሳምንቱ ሰኞ እና ዐርብ ከ12፡00 ሰዓት ጀምሮ የሚካሄዱትና በርካታ ምእመናን እየተሳተፉበት የሚገኙት የቀጥታ ክዋኔ የጥያቄና መልስ መርሐ ግብሮች ላይ በግንባር ቀደምነት መሳተፋቸው ተጠቃሽ ነው፡፡
ከሁለቱ የቀጥታ ክዋኔ መርሐ ግብሮች መካከል በማኅደረ ስብሐት ልደታ ለማርያም ቤተ ክርስቲያን በሳምንት ሁለት ጊዜ የሚካሄደው የጥያቄ እና መልስ ጉባኤ በደብሩ አስተዳዳሪ አባ ተክለ ማርያም አምኜ ትእዛዝ መከልከሉ ተገልጧል፡፡ በዚህ ሳምንት ሰኞ ሊካሄድ የነበረው መርሐ ግብር በሚከታተለው ምእመናንና የአስተዳዳሪውን ትእዛዝ እናስፈጽማለን ባሉ የደብሩ ሠራተኞች መካከል በተፈጠረ ውዝግብ ተስተጓጉሏል፡፡ ይሁንና የጉዳዩ ተከታታዮች እንደሚያስረዱት ከሳምንት ወደ ሳምንት የተከታታዮቹ ቁጥር እየጨመረና የሌላ እምነት አማኒዎችን ትኩረት ሳይቀር እየሳበ የሚገኘው የቀጥታ ጥያቄና መልስ መርሐ ግብር እንዲቆም እጃቸው ረዥም የሆኑ ግለሰቦች ግፊት ሳያደርጉ አልቀረም፡፡ ጣቶች ሁሉ ወደ ቀድሞዎቹ የሊቀ ጠበብት ዘሪሁን ከሳሾች ይጠቁማሉ፡፡ (ዝርዝሩን በቆይታ እንመለስበታለን)
  
ቸር ወሬ ያሰማን፣
አሜን

15 comments:

Anonymous said...

beanid eiras hulet milas betam tasazinalachihu kenanite yemayitebek new befit zerihun mulatun enidayisheteinidayilewet adirigachihu simun sitatfu nebere zare min tegenenanew mawedes yejemerachihut? yasazinal manin mamen yichalal? zerihunim hone begashawe yawu nachew genizeb ketekefelachew letaot yisewalu silezih eibakachihu adirbayi atihunu

Anonymous said...

mehere zmdekune egezixbeHyre beretatune YeseTehe. Yledetaw
gubaYa wdlyla debere teqYero makahade bicale Teru nwe::
egezixbehare betekeresetiYanacenn yetbeke

Anonymous said...

Ere le zemedikunin yemayimesekir sew ale endie, ager hulu tesebisibo limesekirilet yichilal, degimom lik new tikikilegna melis new yesetew, hizibu be 1 lay tenesito mechoh alebet, yebetekirisitiyan abatochim metebaber alebachew, esikemeche dires endih honen eninoralen

Anonymous said...

እግዚአብሔር ያፅናህ:: የእናትህን ነፍስ ይማር::

Anonymous said...

Deje Selam enkan lebrhane lidetu beselam aderesachihu beldetu sewna egziabher -sena melaekt semayna midir tarkrwal enantem tareku Keldetu behala dehina zena akirbu astemru yesewn sim atatsifu -yeswni gebena atmezikibi ekuy filstsa yibekal lememezgeb ahun beka yibelen wongail astemrubet- tarik tenagerube aba ekele wetsa werde atbelu lemanim altsekememi betkirstiyann lemenafikan asalfo setse engi

Anonymous said...

ዘመድኩን በጣም ተሰምቶናል አዝነናል እግዚአብሔር የእናትህን ነፍስ በሰማይ ያንተንም ነፍስ በምድር ይማርልን።
ከወዳጆችህ ካሴት አዙዋሪዎች

Zola said...

ግዚአብሔር ያፅናህ:: የእናትህን ነፍስ ይማር:: LE ZEMEDIKUN

AYZOH IT IS A MATTER OF TIME YOU WILL BE FREE OF CHARGE

DO NOT BE AFRAID

GOD IS WITH YOU

GOD BLESS YOU

Anonymous said...

Zemedikun Birtatun Yistih .Yeenatihin Nefis Yimarlin. Please, let everyone be with him. You paid for Tewahedo and you will get it from your God.

መሰሲ said...

ወንድማችን መጽናናቱን ይስጥህ፤ የናታችንንም ነፍስ ይማር፡፡

መሲ said...

ወንድማችን ላንተ መጽናናቱን ይስጥህ፤ የእናታችንንም ነፍስ ይማር፡፡

መሲ said...

ወንድማችን ላንተ መጽናናቱን ይስጥህ፤ የእናታችንንም ነፍስ ይማር፡፡

Anonymous said...

egziabher yatsinah egziabhern yeyaze ayferam ewnet netsa tawetalech.ewnet kealem aydelechimna hulem tigefalech.hawariatm tegeftew enji yihich elem temechitachew aydelem yalefut.EGZIABHER YATSINAH

Anonymous said...

i am very proud with leke tebebt and memeher zeriun.this is what we need this days.Be strong and keep stand up for the truth like abune peterose.i also want to say for maheber kidusan woladete amelake kenatega thune.I JUST relized know how much you guys means to the church. you have enemy from in side and out side.but no one defet you.because there is a spirit of abune gorgoriose with you and all those kidusans and memherans tselote kenatega new(is with you).i was not a member of mahebere kidusan but now i will be a member for the seek of my religIon.GOD BLESS ETHIOPIA AND ORTHODOX TEWAHEDO RELIGION.D/N SOLOMON MESKEL

Anonymous said...

i am very proud with leke tebebt and memeher zeriun.this is what we need this days.Be strong and keep stand up for the truth like abune peterose.i also want to say for maheber kidusan woladete amelake kenatega thune.I JUST relized know how much you guys means to the church. you have enemy from in side and out side.but no one defet you.because there is a spirit of abune gorgoriose with you and all those kidusans and memherans tselote kenatega new(is with you).i was not a member of mahebere kidusan but now i will be a member for the seek of my religIon.GOD BLESS ETHIOPIA AND ORTHODOX TEWAHEDO RELIGION.D/N SOLOMON MESKEL

Anonymous said...

bemejemeria zemedikun ye enatihin nefis yemar antenim ke nemelaw betesebih gar metsinanatin yesitih... begashaw ena groupochu gin ewnet le geta qal kehone yehen yahil lifatu enkuan sim matifat lelam derese tebilo alemawi fird bet ayikedim le wendemu... be abatoch masimeker kalonem le egziabiher metew neberebet.....le zawim patriarik tebiyewin sitimolich kerimeh ahun kesu achawach gar tebabireh lelan sew mekises???? be fit ekerakerilachu neber ahun gin ande ande negerachun say orthodoxawinet ayetayebetim ewnet ena nigat eyader yeteral.... ERIS BE ERSACHIN SANISIMAMA GETAN MAGELIGEL WAGA BIS YADERGAL
.... ke huletachum side groupy honachihu le geta fiqad sayhon le groupachihu muach eyehonachihu yemesilegnal....egnanim hone egziabiherin win lemadreg ye miwaguachihun be elih sayhon be fiqir ashenifu sile ewnet eyetegadele kale gin pls tesifa atikuretu egna banawikilachihum fetari wagachihun ayasatachihum manin endeminamin gira gebiton new. lelaw fetena alibeqam bilon enante endezi sititalu mayet asazinon new. emebirihan tirdan. Amen!!!

Blog Archive

የአቡነ ጳውሎስ "ሐውልተ ስምዕ"

ነጻ ፓትርያርክ ምርጫ ቢሆን ኖሮ ማንን ይመርጡ ነበር? እንበልና ሁሉም ነገር ሥርዓቱን ጠብቆ የተከናወነ የእጩዎች ምርጫ ቢሆን ኖሮ፣ አሁን የምናነሣቸው ጉድለቶች ባይኖሩ ኖሮ፣ 6ኛው ፓትርያርክ እንዲሆን የምትመርጡት ማንን ነበር? (ማሳሰቢያ፦ አሁን ያለው ክፍፍል እና የመንግሥት ተጽዕኖ ባይኖር ኖሮ ተብሎ የሚመለስ ጥያቄ ነው። የምን “ባይኖር ኖሮ ነው” የሚል አስተያየት ካለዎትም እናከብራለን።)