January 3, 2012

በእስላማዊ አክራሪዎች ቅስቅሳ የተቃጠለችው የጋሮሬ ቅድስት አርሴማ ቤተ ክርስቲያን ይዞታን የማስከበር ሂደት በሽምግልና ስም እየተጓተተ ነው

  • READ THIS ARTICLE IN PDF.
  • የከተራ - ጥምቀት በዓል የቅድስት አርሴማ ቤተ ክርስቲያን በተቃጠለችበት እና የቤተ ክርስቲያናችን ይዞታ በሆነው ስፍራ ላይ ይከበራል::
  • በፌዴራል ጉዳዮች ሚኒስቴር የሃይማኖትና እምነት ጉዳዮች ዳይሬክቶሬት “ጉዳዩ አስቸጋሪ ቢሆንም ባለው መረጃ ላይ እየሠራሁ ነው” ብሏል፤  ዳይሬክቶሬቱ በቅድስት አርሴማ ቤተ ክርስቲያን መቃጠል ያዘኑ ምእመናንን ለማጽናናት ከአጎራባች ዞኖችና ወረዳዎች ወደ ስልጢ ከተማ/ቅበት/ እየተደረገ ያለውን ሐዋርያዊ ጉዞ “ችግሩን ማራገብ ነው” በሚል ተችቷል::
  • የስልጢ ደብረ ስብሐት ቅድስት ማርያም ቤተ ክርስቲያን ሰበካ ጉባኤ አባላት ወደ ክልል እና ፌዴራል አካላት በመመላለስ ለእንግልትና አላስፈላጊ ወጪ መዳረጋቸውን ገልጸዋል፤ በሥራ ገበታቸው ማስጠንቀቂያ የተሰጣቸው ክርስቲያን የመንግሥት ሠራተኞች መኖራቸውን በመጥቀስ በኑሯቸው የደኅንነትና የሥራ ዋስትና ስጋት እንዳለባቸውም አመልክተዋል::

  • “ምንም እንዳትሰጉ፤ ከክልል እስከ ፌዴራል ድረስ መደወል ያለብን አካላት ጋር ሁሉ ደውለን ጨርሰናል፤ እጃችን ረጅም ነው፤ የፈለጉበት ሊሄዱ ይችላሉ” (የስልጢ ወረዳ ፖሊስ አዛዥ ዋና ሳጅን ሐሰን ሾሞሎ የሰበሰቧቸው የወረዳው ፖሊስ አባላት ርምጃ እንዲወስዱ ለማደፋፈር ከተናገሩት)::
  • የጅማውን ጭፍጨፋ የፈጸሙ እንደሆኑ የተነገረላቸው እስላማዊ አክራሪዎች በወራቤ ደብረ ኀይል ቅዱስ ሩፋኤል ቤተ ክርስቲያን ላይ ሌላ የማቃጠል ሙከራና በዞን ደረጃም ቅስቀሳ በማካሄድ የምእመኑን ትዕግሥት እየተፈታተኑ ነው፡፡ በሽምግልናው እየተሳተፉ ያሉ አዛውንት ሙስሊሞች በበኩላቸው በቅድስት አርሴማ ቤተ ክርስቲያን ላይ የተፈጸመው ጥፋት የማይገባ መሆኑን በመግለጽ “አሁንም ቢሆን ቤተ ክርስቲያኗ በነበረችበት መልኩ ተሠርታ ልንክሳቸው ይገባል” ማለታቸው ተዘግቧል::
  • “ቤት ስለፈረሰባችሁ ነው የምታለቅሱት፤ ገና የእያንዳንድሽ አንገት ይታረዳል” (ኮንስታብል ሺፋቃ አብዶ የተባለች የስልጢ ወረዳ ፖሊስ የቅድስት አርሴማ ቤተ ክርስቲያን መቃጠል በዕለት ሁኔታ መዝገብ እንዲሰፍር ለጠየቁ ምእመናን ከተናገረችው)::
  • የቅድስት አርሴማን ቤተ ክርስቲያን በማቃጠል የተግባር ተሳትፎ ከነበራቸው አንዱ በድንገተኛ አደጋ ሲቀሠፍ ሌላዋ ደግሞ ራሷን አጥፍታለች::
  • “እግዚአብሔር ዐመፀኞችን ይቀጣል፤ እኛ የዐመፅ ሳይሆን የፍትሕ ሰዎች ነን፤ ምን አጠፋን? ምናችሁንስ ነካን? ፍቅርን በሰበክን፣ ሕዝባችንን በመከርን ምን አደረግን? መዋቅርን ጠብቃችሁ ሕግን ማስከበር ሲገባችሁ ተማሪዎችን አነሣስታችሁ ቤተ ክርስቲያንን ማቃጠል ተገቢ ነው ወይ? እውነት ፍትሕ አለ? ሕግ አለ? ፍርዱን እግዚአብሔር እንዲሰጥ እንጸልያለን፤ ከእናንተ በላይ ለሆነውም አካል አቤቱታችንን እናቀርባለን” (የሀ/ስብከቱ ሊቀ ጳጳስ ብፁዕ አቡነ ቀሌምንጦስ የተቃጠለው ቤተ ክርስቲያን እንዳልሆነ ለማስተባበል ለሞከሩት የስልጢ ወረዳ አስተዳደር ባለሥልጣናት ከተናገሩት)::
  • “የኢትዮጵያ ሃይማኖቶች ተቋማት ጉባኤ” በማንኛውም መንገድ የሌላውን እምነት በመፃረር እና ለጠብ የሚያነሣሣ ቅስቀሳ በማድረግ ስብከት ማካሄድ ሰባክያንን በእስር እና በገንዘብ የሚያስቀጣ፣ ፈቃዳቸውንም የሚያስነጥቅ ስምምነት ላይ መድረሳቸው ተዘገበ::

(ደጀ ሰላም፣ ታኅሣሥ 23/2004 ዓ.ም፤ January 2/2012)፦ እነሆ በስልጤ ሃዲያ ከንባታ እና ጉራጌ አህጉረ ስብከት ስልጤ ዞን ስልጢ ወረዳ ቅበት ከተማ ቆቶ ባሎሶ ቀበሌ ቆቶ መንደር የምትገኘው የጋሮሬ ቅድስት አርሴማ ቤተ ክርስቲያን እስላማዊ አክራሪዎች በቀሰቀሱት የግፍ ድርጊት ከተቃጠለች ታኅሣሥ 19 ቀን 2004 ዓ.ም አንድ ወር አልፏታል፡፡
እስላማዊ አክራሪዎች፣ ጎጠኛ የመንግሥት ባለሥልጣናት እና የስም ኢንቨስተሮች በሸረቡት ሤራ የተቃጠለችውን የቤተ ክርስቲያኗን ይዞታ በፍትሕ አካል በሕግ አግባብ ለማስከበር የአጥቢያው አስተዳደር የሚያደርገውን ጥረት “በቅድሚያ በሽምግልና የተጀመረው ሂደት መፈታት አለበት” የሚል አቋም በያዙት የክልሉ ባለሥልጣናት ሳቢያ መጓተቱን የከተማው ምእመናን እና አገልጋዮች ገለጹ፡፡
የተቃጠለችውን የቅድስት አርሴማ ቤተ ክርስቲያንን አስተዳደር በበላይነት የሚመራው የቅበት ደብረ ስብሐት ቅድስት ማርያም ሰበካ ጉባኤ ሁለት አባላት እና አስተዳዳሪው መልአከ ስብሐት አፈወርቅ ከበደ÷ የስልጤ ዞን እና ስልጢ ወረዳ ባለሥልጣናት ስለ ጉዳዩ ለክልል እና ፌዴራል አካላት በሚሰጧቸው የተሳሳቱ መረጃዎች እንዲሁም በሽምግልናው ሂደት ቅልጥፍና ማነስ የተነሣ ችግሩን ለክልሉ የጸጥታና አስተዳደር ቢሮ እንዲሁም ለፌዴራል ጉዳዮች ሚኒስቴር ሓላፊዎች እየተመላለሱ ለማስረዳት ተገደዋል፡፡ ይህም ለከፍተኛ እንግልት እና አላስፈላጊ ወጪ እንደዳረጋቸው በመግለጽ አማርረዋል፡፡
የደብሩ አስተዳደር ለፌዴራል ጉዳዮች ሚኒስቴር የሃይማኖቶችና እምነት ጉዳዮች ዳይሬክቶሬት በሰጡት አስረጅ የወረዳው፣ የዞኑና የክልሉ የፍትሕ እና አስተዳደር አካላት ከ2000 ዓ.ም ጀምሮ ለስድስት ጊዜያት የቤተ ክርስቲያኒቱን ይዞታ ያረጋገጡባቸውን ሰነዶች፣ የቤተ ክርስቲያኒቱን መቃጠል የሚያሳየውንና በእስላማዊ አክራሪዎቹ በራሳቸው የተቀረጸውን ቪዲዮ ፊልም አቅርበዋል፤ አፋጣኝ መፍትሔም እንዲሰጣቸው ጠይቀዋል፡፡ “ችግሩ በቅድሚያ በክልልና በወረዳ ደረጃ በተቋቋመው የሽምግልና ኮሚቴ መፈታት አለበት፤ ዳግመኛ በማይፈጠርበት አኳኋንም ለሰላም እና መረጋጋት ቅድሚያ እንሰጣለን” ካሉት የክልሉ ባለሥልጣናት ጋር በጉዳዩ ላይ እየተነጋገረበት መሆኑን ያስታወቁት የዳይሬክቶሬቱ ሓላፊዎችም “የተወሳሰበ ቢሆንም ባለው መረጃ ላይ እየሠራን ነው፤” ማለታቸው ተዘግቧል፡፡
ቤተ ክርስቲያኒቱ በተቃጠለችበት ዕለት ከሀገረ ስብከቱ ሊቀ ጳጳስ ጋር በስፍራው በተገኙት የደቡብ ክልላዊ መንግሥት ባለሥልጣናት መመሪያ ሰጭነት “ወንጀለኞችን አጣርቶ ለፍርድ ለማቅረብ” በሚል የወረዳ አስተዳደሩ ጽ/ቤት አባላት፣ ከክርስቲያኑ እና ከሙስሊሙ የተውጣጡ ስድስት ስድስት የአገር ሽማግሌዎች የሚገኙበት የጋር ኮሚቴ መቋቋሙን የዜናው ምንጮች አስታውቀዋል፡፡
ስለ ጋር ኮሚቴው መቋቋም አስተያየታቸው የሰጡት ምንጮቹ፣ “ኮሚቴው በሚቋቋምበት ወቅት ጉዳዩን በሚገባ የሚያውቁና የሚያስረዱ አገልጋዮችን እና ምእመናንን እንዳንመርጥ ‹እገሌ መጤና ችግር ፈጣሪ የመንግሥት ሠራተኛ ነው - ይቅር፣ እገሌ ይጨመር› በሚሉት የወረዳው አስተዳደር ባለሥልጣናት ሳቢያ ጫና ተፈጥሮብናል፤ ሙስሊሞቹ ከመረጧቸው የጋር ኮሚቴው አባላት መካከል ቤተ ክርስቲያኒቱን በማቃጠል ቀጥተኛ ተሳትፎ የነበራቸው ግለሰቦች አሉበት፤ ኮሚቴው ተቋቁሞ ንግግር በተጀመረበት ሁኔታ የወረዳው ፖሊስ ‹በቃጠሎው እጃቸው አለበት› ብሎ ካሰራቸው ሁለት ሙስሊም ወጣቶች ጋር ሁለት ክርስቲያን ወጣቶችንም በማሰር አላግጦብናል፤ ታሳሪዎቹ እያንዳንዳቸው በብር 5000 ዋስ ጠርተው ዕለቱኑ ቢፈቱም ሁለቱ ክርስቲያን ወጣቶች በዕለቱ በቤተ ክርስቲያናችን መቃጠል ምክንያት በደብረ ስብሐት ቅድስት ማርያም ቤተ ክርስቲያን ተሰብስበው ያዝኑ ከነበሩት ምእመናን መካከል የነበሩ ከመሆናቸውም በላይ በወጣቶቹ እስር ምክንያት የንግግሩ ሂደት ተስተጓጉሎ እንደነበር፤” አስረድተዋል፡፡
የቅድስት አርሴማን መቃጠል የሚያሳየውን ፊልም በተንቀሳቃሽ ስልኮቻቸው ላይ የጫኑና በእስላማዊ አክራሪዎቹ የሚመከሩ ሙስሊም ተማሪዎች በት/ቤት ሳይቀር ፊልሙን ለክርስቲያን ተማሪዎች በግልጽ እያሳዩ “ገና ጅሃድ ነው የምናውጅባችሁ፤ የትም ብትሄዱ ምንም ልታመጡ አትችሉም” እያሉ ልጆቻቸውን እንደሚያሸማቅቁባቸው ምእመናንኑ ተናግረዋል፤ ይዞታ ለማስከበር ከተንቀሳቀሱት ክርስቲያን የመንግሥት ሠራተኞች መካከል “መጤ እና ችግር ፈጣሪ ናችሁ” በሚል ማስጠንቀቂያ የተሰጣቸውና ከሥራቸው የታገዱም መኖራቸውን አጋልጠዋል፡፡
እስላማዊ አክራሪዎቹ በተቃጠለችው የቅድስት አርሴማ ቤተ ክርስቲያን ደቡባዊ ማእዝን ያለውን የሼሕ ቃሲም መቃብር እንደ ቅዱስ ስፍራ (Shrine) አድርጎ ቀድሞ ያልነበረ አዲስ ታሪክ በመፍጠር በዓል እናከብርበታለን፤ እንሰግድበታለን በሚል ሰፊው ሕዝበ ሙስሊም ያልጠየቀውን ጥያቄ ለመቆስቀስ ተንቀሳቅሰውም እንደነበር ተዘግቧል፡፡ ለዚህም የወረዳው መሬት አስተዳደር ጽ/ቤት ከአምስት ዓመት በፊት በይዞታ ሰነድ ቅጽ 01 ቦታው የኦርቶዶክስ እምነት ተከታዮች ጥምቀት በዓል ማክበሪያ ቦታ እንደሆነ የሰጠውን ማስረጃ በመሻር÷ የወረዳው መጀመሪያ ደረጃ ፍ/ቤት በይግባኝ ወደ ሆሳዕና ከፍተኛ ፍ/ቤት አምርቶ የመስክ ሥራ በመሥራት ይዞታው የቤተ ክርስቲያን እንደሆነ ተረጋግጦ የተወሰነውን ውሳኔ በማጽናት መዝገቡን መዝጋቱን በመከልስ “ቦታው የክርስቲያኑም የሙስሊሙም የወል ይዞታ ነው” በሚል አዲስ ውሳኔ መወሰኑ ለአክራሪዎቹ ጅሃዳዊ ቅስቀሳ እገዛ ማድረጉ ተመልክቷል፡፡
ለውዝግቡ መቀስቀስ ዋነኛ ምክንያት የሆነው የስልጤ ዞን ኢንቨስትመንት ጽ/ቤት የቤተ ክርስቲያንን የባሕረ ጥምቀት ቦታ አል-ኢስታዝ አውቶሞቶቭ ኢንዱስትሪያል ግሩፕ ለተባለ ኢንቨስተር አላግባብ መስጠቱ መሆኑን ምንጮቹ አስታውሰዋል፤ የቆቶ ባሎሶ ቀበሌ ጽ/ቤት በወረዳው አስተዳደር ጽ/ቤት በቀረበለት ጥያቄ መሠረት ከግለሰብና ተቋም ይዞታ ነጻ የሆነና ለኢንቨስተሩ አዘጋጅቶት የነበረው ሦስት ሄክታር መሬት ከቤተ ክርስቲያኒቱ ይዞታ ከሁለት ኪ.ሜ በላይ ርቀት እንደነበረው ውሳኔው የሰፈረበትን ቃለ ጉባኤ በመጥቀስም አስረድተዋል፡፡ በአሁኑ ወቅት ባለሀብት ነኝ ባዩና ተወካዮቹ የቤተ ክርስቲያኒቱን ይዞታ ለመንጠቅ የእርሱ ንብረት የሆነው ተሽከርካሪ ለመንግሥታዊ ሥራ የሚጠቀመውን የወረዳውን አስተዳደር ጽ/ቤትና ሌሎች መንገዶችን በመጠቀም በከተማይቱ የተለያዩ ማግባቢያዎችን እያካሄደ እንደሚገኝ ለማወቅ ተችሏል፡፡
በአንጻሩ በጋር ኮሚቴው ውስጥ ከሚገኙና ከሙስሊሙ ወገን ከተወከሉ ስድስት የኮሚቴው አባላት መካከል ሁለት ሽማግሌዎች በአክራሪዎቹ የተፈጸመው ጥፋት መደረግ የማይገባው መሆኑን በመግለጽ “የተቃጠለችው ቤተ ክርስቲያን ዳግመኛ በነበረችበት መልኩ ተሠርታ ልንክሳቸው ይገባል” የሚል አቋም መያዛቸው ተሰምቷል፡፡ በመጪው ጥር 10 እና 11 ቀን የሚከበረው የከተራ - ጥምቀት በዓልም የባሕረ ጥምቀት ይዞታችን በነበረው በዚሁ ስፍራ እንዲከበርም ስምምነታቸውን ገልጸዋል ተብሏል፡፡
በክልልና ፌዴራል ደረጃ ያሉ አንዳንድ ባለሥልጣናት ችግሩን እንደማራገብ አድርገው ቢቆጥሩትም÷ የቅድስት አርሴማ ቤተ ክርስቲያን ከተቃጠለችበት ሳምንት መጨረሻ (ኅዳር 24 ቀን 2004 ዓ.ም ጀምሮ) የስልጤ ዞን አጎራባች ከሆኑ ወረዳዎች (ሆሳዕና፣ ቡታጅራ፣ ቡኢ፣ ወላይታ) ምእመናን ወደ ስልጢ ወረዳ ቅበት ደብረ ስብሐት ቅድስት ማርያም ቤተ ክርስቲያን በበርካታ አውቶቡሶች በመመላለስ ላዘነው የከተማው ምእመን የስብከተ ወንጌልና መዝሙር አገልግሎት በማቅረብ አጽናንተዋል፤ አገልግሎቱ የሚጠናከርበት፣ የተቃጠለው ተመልሶ የሚሠራበት የገንዘብ ድጋፍ በማድረግም አለኝታነታቸውን ገልጸዋል፡፡
 በዚህ ዐይነቱ የምእመናን አጋርነት የተበሳጩ የሚመስሉት የከተማው እስላማዊ አክራሪዎች የደብረ ስብሐት ቅድስት ማርያም ቤተ ክርስቲያንንም ለማቃጠል በየመስጂዶቻቸው በሚያሰሙት ድንፋታ እየዛቱ ይገኛሉ፡፡ የስልጤ ዞን ዋና ከተማ በሆነችው ወራቤ የሚገኘውንና የከተማዋ ምእመናን ከአምስት ዓመት በፊት እስከ ክልል ድረስ ተመላልሰው በማስፈቀድ በብዙ መከራ ያሠሩትን የደብረ ኀይል ቅዱስ ሩፋኤል ቤተ ክርስቲያን ለማቃጠል ሙከራ ማድረጋቸው ታውቋል፡፡ ሙከራው የተደረገው ታኅሣሥ 16 ቀን መንፈቀ ሌሊት ላይ ነው፡፡
በዕለቱ የከተማው መብራት ጠፍቶ የስልክ ግንኙነትም አስቸጋሪ እንደነበር የተመለከተ ሲሆን በተጠቀሰው ሰዓተ ሌሊት በርካታ ሰዎች ጨለማን ተገን በማድረግ ወደ ቅጽሩ ዘልቀው ታጭዶ የተከመረውን የግቢውን ሣር ወደ ሕንፃ ቤተ ክርስቲያኑ ዙሪያ እያስጠጉ ነበር፡፡ ይሁንና የብዙ ሰዎችን ውርውር ማለት የተመለከተው የቤተ ክርስቲያኑ ጥበቃ የማስጠንቀቂያ ተኩስ በመተኮሱ ወራሪዎቹ በቅጽሩ እየዘለሉ በመውጣት አምልጠዋል፡፡ የተኩሱን ድምፅ ሰምተው በፍጥነት ከደረሱ ሦስት ምእመናን ጋር በመሆን በዙሪያው በተካሄደ አሠሣ “የአእምሮ ሕሙም ነው” የተባለ ግለሰብ ለማቃጣጠል ከተዘጋጀው ሣር አጠገብ ክብሪት ይዞ መገኘቱ ተገልጧል፡፡ ምእመናኑ ግለሰቡን ለከተማው ዙሪያ ወረዳ ፖሊስ ማዘዣ ጣቢያ በማስረከብ የሆነውን ነገር ማስታወቃቸው ተዘግቧል፡፡
ከሁለት ሳምንት በፊት፣ ታኅሣሥ 8 ቀን 2004 ዓ.ም፣ ከቡኢ የመጡ ሰባክያንና ዘማርያን በቅበት ቅድስት ማርያም አገልግሎት ሰጥተው መመለሳቸውን የሰማ አብዱልከሪም (በቅጽል ስሙ ጨክን) የተባለ ጽንፈኛ በተመሳሳይ ቀን “ምን ሊያደርጉ ነው የሚመላለሱት፤ እንዲህ ከሆነ ማርያምን እናፈርሳለን” ብሎ ከተናገረ አራት ቀናት በኋላ በመኖሪያ ቤቱ በኤሌክትሪክ ገመድ ተይዞ ‹ተቃጠልኩ› እያለ እንደጮኸ ከግንድ ተጣብቆ መሞቱ ተዘግቧል፡፡ የተበጠሰ የኤሌክትሪክ ገመድ ለመቀጠል እየሞከረ የነበረው ይኸው ጽንፈኛ በግብርና ሥራ የሚተዳደር፣ ባለትዳርና የልጆች አባት ሲሆን በቅድስት አርሴማ ቤተ ክርስቲያን ቃጠሎ ቀጥተኛ ተሳትፎ እንደነበረው ተገልጧል፡፡
ባለፈው ሳምንት ከተከናወነው የጽንፈኛው የቀብር ሥነ ሥርዐት በኋላ ጅሃዲስቱ ጀማል ሽኩሪ በግሉ በሚቆጣጠረው መስጂዱ፣ “ወንድማችን አብዱልከሪም ይመራን፣ ያደራጀን፣ ያስተምረን የነበረ ስለሆነ በቀጥታ ጀነት ነው የሚገባው” ሲል መናገሩ ተዘግቧል፡፡ ሌላዋ የጥፋት ድርጊቱ ተሳታፊም ባልታወቀ ምክንያት መርዝ ጠጥታ አእምሮዋን አጥታ መሞቷ ታውቋል፡፡ የዞኑና የወረዳው ባለሥልጣናት ጽንፈኝነትን መጠለያ አድርጎ የሚራመደውን የጎሳ ፖሊቲካና የግል ጥቅም ተከላክለው የክርስቲያኑን መብት ማስጠበቅ ባልቻሉበት ሁኔታ የከተማው ምእመናን እንዲህ መቅሠፍታዊ አደጋዎች አምላካዊ የቅጣት ብትር እንደሆኑ እየቆጠሩት ይገኛሉ፡፡
በርግጥም የሀገረ ስብከቱ ሊቀ ጳጳስ ብፁዕ አቡነ ቀሌምንጦስ ከጠዋት እስከ ማታ በቅበት ደብረ ስብሐት ቅድስት ማርያም ቤተ ክርስቲያን ጠብቆ በልቅሶ የተቀበላቸውን ምእመን ባጽናኑበት በዚያ የመከራቸው ቀን፡- “ልጆቼ፣ ሃይማኖት ፍቅርን፣ አንድነትን፣ መከባበርን ነው የሚሰብከው፤ እንደበደባለን እንጂ አንደበድብም፤ እንሰደዳለን እንጂ አናሰደድም፤ እንመታለን እንጂ አንመታም፡፡ ሕዝብን ከሕዝብ የሚያጋ ወንጀለኞች አሉ፤ እግዚአብሔር እነርሱን እንዲያጋልጥ ጸልዩ፤” ብለው ነበር፡፡ ብፁዕነታቸው ለምእመኑ ከሰጡት የማፅናኛ ቃል አስቀድሞ የተቃጠለችው ቤተ ክርስቲያን ፍሕም በሚንቀለቀልበት በዓመዱ ላይም ሕፃናት ከሚሯሯጡበት ስፍራ ደርሰው የሆነውን ተመልክተዋል፡፡ ሃያቱ ሙክታር የተባለው የወረዳው አስተዳዳሪ ዐይኑን በጨው ታጥቦ “የሚወራው ነገር በሙሉ አሉባልታ ነው፤ ከውጭ ሆናችሁ የምትሰሙትና መሬት ላይ ያለው የተለያየ ነው፤ የተቃጠለው ቤተ ክርስቲያን አይደለም” ሲል በዐይን ስለሚታየው እውነት ሊቀ ጳጳሱን ለመገዳደር አላፈረም፤ ሌላው የወረዳ ምክር ቤቱ ሹምም “ስሜታዊ አይሁኑ” በማለት ምክር ለመስጠት ቃጥቶታል፡፡
“ዛሬኮ መሞት ነበረብኝ” ያሉት ብፁዕነታቸውም ምእመኑ አባቶቹን አክባሪ በመሆኑ የሚሰጠውን መመሪያ ተቀብሎ አጸፋ ከመስጠት መታገሡን አስረድተዋል፡፡ “ምን አጠፋን? ምናችሁንስ ነካን? ፍቅርን በሰበክን፣ ሕዝባችንን በመከርን ምን አደረግን? መዋቅርን ጠብቃችሁ ሕግን ማስከበር ሲገባችሁ ተማሪዎችን አነሣስታችሁ ቤተ ክርስቲያንን ማቃጠል ተገቢ ነው ወይ? እውነት ፍትሕ አለ? ሕግ አለ? ፍርዱን እግዚአብሔር እንዲሰጥ እንጸልያለን፤ ከእናንተ በላይ ለሆነውም አካል አቤቱታችንን እናቀርባለን፤” በማለትም የግፍ ድርጊቱን በሕጋዊ መንገድ እንደሚፋረዱት አስታውቀዋቸዋል፡፡
ከብፁዕነታቸው ጋር በቅጽሩ ተገኝተው ምእመናኑን ያጽናኑት የደቡብ ክልላዊ መንግሥት የጸጥታ አስተዳደር ቢሮ ምክትል ሓላፊ አቶ ኢዮብ አንበሳ በተቃራኒው ምእመናኑ ስለ ነበራቸው ርጋታ አመስግነው፣ “ፖሊስ ኀፍረት ስለተሰማው የእናንተን ፊት ማየት አይችልም፤ አይደለም ቤተ ክርስቲያን ጭራሮ እንኳን ባለቤት አለው፤ ወንጀለኞችን አጣርተን ለሕግ እናቀርባለን፤” ብለው ነበር፡፡
ነሐሴ 21 ቀን 2003 ዓ.ም የሃዲያ እና ስልጤ አገረ ስብከት ሥራ አስኪያጅ፣ የስልጢ ወረዳ ቤተ ክህነት ሓላፊ፣ የቆቶ ባሎሶ ቀበሌ ሊቀ መንበርና የአካባቢው ምእመናን በተገኙበት ሥራዋ የተጀመረው የቅድስት አርሴማ ቤተ ክርስቲያን ግንባታ በወር ጊዜ ውስጥ ተጠናቅቆ መስከረም 29 ቀን 2004 ዓ.ም ቅዳሴ ቤቱን ለማክበር በዝግጅት ላይ ነበረች፡፡
በተያያዘ ዜና በጻድቁ አቡነ አረጋዊ መታሰቢያነት የተቋቋመ ማኅበር ሰሞኑን “ለመላው የሀገራችን የኢትዮጵያ ሕዝቦች” በሚል ርእስ ባሰራጨው ዘለግ ያለ ጽሑፍ ከቅርብ ዓመታት ወዲህ “የኢትዮጵያ ሕገ መንግሥት የፈለግነውን እምነት የማራመድ ነጻነት ሰጥቶናል” በሚል ሽፋን ሕዝብን ከሕዝብ፣ መንግሥትን ከሕዝብ እርስ በርስ ለማጋጨት፣ ሀገራችንን ኢትዮጵያን የደም መሬት ለማድረግ እየተንቀሳቀሱ ያሉ ‹ሽብርተኞች› ቁጥራቸው እየተበራከተ መምጣቱን ገልጧል፡፡
ሽብርተኞቹ ትልቅ ስትራቴጂ ተነድፎላቸውና ብዙ በጀት ተመድቦላቸው ሌት ተቀን የተለያዩ የውስጥ ባንዳዎችን ለማሠልጠን ጥረት እንደሚያደርጉ ያመለከተው ጽሑፉ በተለይም ጽንፈኛ ሙስሊሞች የውስጥ ባንዳዎችን በማብዛት ቤተ ክርስቲያኒቱን ለማጥቃት ያለሙበትን ስልት ያብራራል፤ ለእንቅስቃሴያቸውም ዐይነታዊ እና ተመጣጣኝ ምላሽ መስጠት እንደሚያስፈልግ በማተት የበኩሉን አስፍሯል
በሌላ በኩል የኢትዮጵያ የሃይማኖት ተቋማት ጉባኤ ታኅሣሥ 12 እና 13 ቀን 2004 ዓ.ም በባሕር ዳር ከተማ ባካሄደው ስብሰባ÷ በአንዱ ቤተ እምነት መድረክ ወይም በሌላ ማንኛውም መንገድ (የኅትመት እና ኤሌክትሮኒክስ) የሌላውን እምነት የሚነቅፍ ስብከት ማካሄድ እና ሌሎችን ለጠብ የሚያነሣሣ ቅስቀሳ ማድረግ በእስር እና በገንዘብ (ከብር 500 - 5000) ያስቀጣ ዘንድ በአብያተ እምነቱ መካከል ስምምነት ላይ መደረሱ ተዘግቧል፡፡ በተለይም ከፕሮቴስታንት እና ሙስሊም አብያተ እምነት ለአንዳንዶቹ በውጭ ከሚገኙ አካላት ከፍተኛ ፈንድ እንደሚላክላቸውና ገንዘቡ ግን ለምን ተግባር እንደሚውል በግልጽ እንደማይታወቅ መገለጹ ተዘግቧል፡፡ በስብሰባው በእያንዳንዱ ቤተ እምነት ለሚሰማሩ መምህራን ፈቃድ የመስጠት አስፈላጊነትና ያለ መስጠት ጉዳት የተመለከተ ጥናት የቀረበ ሲሆን ከየተቋማቸው ፈቃድ ሳይኖራቸው የሚሰማሩ ሰባክያን ሓላፊነት በሚወስዱበትና ተጠያቂ በሚሆኑበት አሠራር ላይ መክሯል ተብሏል፡፡
ስብሰባው የደረሰባቸውን ስምምነቶች ለማስፈጸም የአብያተ እምነቱ ተቋማት ያላቸውን አቅም የሚጠራጠሩ አስተያየት ሰጪዎች በበኩላቸው በመንጋ ቅሰጣ የተቸገሩቱ የራሳቸውን እምነት ለመከላከልና መንጋውን ለመጠበቅ በመደበኛ እና ተነጻጻሪ መንገድ የሚሰጡት ትምህርት ከስምምነቱ አኳያ ያለው ግንኙነት ግልጽ አለመሆኑን ተናግረዋል - እንደ አብነትም አንድ ወር ያህል ያስቆጠረውና በአዲስ አበባ ደብረ መዊዕ ቅዱስ ሚካኤል ካቴድራል በየሳምንቱ ረቡዕ፣ በማኅደረ ስብሐት ልደታ ለማርያም ቤተ ክርስቲያን በየሳምንቱ ሰኞ እና ዐርብ “ኦርቶዶክስ መልስ አላት” በሚል መርሕ በፀረ ተሐድሶ ሰባክያን ጥምረት አባላት በቀጥታ ክዋኔ የተጀመረው የጥያቄ እና መልስ መርሐ ግብር ሊጠቀስ ይችላል፡፡
በሌላም በኩል በጅማው ጭፍጨፋ ጭምር የሚጠረጠሩ፣ “የውሻ እና የክርስቲያን ድምፅ መስማት አንፈልግም” የሚሉ ጽንፈኞች ከቃል አልፈው ወደ ተግባር በተሸጋገሩበትና አስተዳደራዊ ድጋፍ ባላጡበት በእነ ጀማል ሽኩሪ ዐይነቱ መስጂድ ስምምነቱ ከወረቀት እንደማያልፍ ያላቸውን ስጋት መግለጻቸው አልቀረም፡፡
                                       


Post a Comment

Blog Archive

የአቡነ ጳውሎስ "ሐውልተ ስምዕ"

ነጻ ፓትርያርክ ምርጫ ቢሆን ኖሮ ማንን ይመርጡ ነበር? እንበልና ሁሉም ነገር ሥርዓቱን ጠብቆ የተከናወነ የእጩዎች ምርጫ ቢሆን ኖሮ፣ አሁን የምናነሣቸው ጉድለቶች ባይኖሩ ኖሮ፣ 6ኛው ፓትርያርክ እንዲሆን የምትመርጡት ማንን ነበር? (ማሳሰቢያ፦ አሁን ያለው ክፍፍል እና የመንግሥት ተጽዕኖ ባይኖር ኖሮ ተብሎ የሚመለስ ጥያቄ ነው። የምን “ባይኖር ኖሮ ነው” የሚል አስተያየት ካለዎትም እናከብራለን።)