January 16, 2012

ኢትዮጵያ 9ኛውን የኦሪየንታል ኦርቶዶክስ እና የሮም ካቶሊክ የጋራ ኮሚሽን ስብሰባ ታስተናግዳለች


  • Read the article in PDF
  •  በቤተ ክርስቲያን ፍጹም አንድነት እና ግንኙነት(the full communion and communication) ላይ የሚያተኩረው ስብሰባ ከነገ በስቲያ ይጀመራል::
  • የስብሰባው ተሳታፊዎች በጥምቀት በዓል አከባበር ላይ ይገኛሉ፤ በሥርዐተ ቅዳሴ ይሳተፋሉ
  • ስብሰባው የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ከውጭ አብያተ ክርስቲያናት ጋራ ያላትን ግንኙነት ለማስፋፋት እና ለማጠናከር ሓላፊነት በተጣለበት ቅዱስ ሲኖዶስ ዘንድ አይታወቅም፤ ስለ ስብሰባው ልኡካን/ተልእኮ ቅዱስ ሲኖዶስ ይሁን ቋሚ ሲኖዶስ ያስተላለፈው ውሳኔ የለም::
  •  የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያንን በመወከል በመ/ፓ/ጠ/ቤ/ክ የቅርስ ጥበቃና የቤተ መጻሕፍት ወመዘክር እንዲሁም የቱሪዝም መምሪያ ሓላፊ እና በቅድስት ሥላሴ መንፈሳዊ ኮሌጅ መምህር የሆኑት ሊቀ ዲያቆን ዳንኤል ሰይፈ ሚካኤል ናቸው፡፡ በቀደሙት ጉባኤያት ቤተ ክርስቲያንን በመወከል ሲሳተፉ የቆዩት መጋቤ ብሉይ ሰይፈ ሥላሴ ዮሐንስ (ከሊቃውንት ጉባኤ) እና ሊቀ ኅሩያን ጌታቸው ጓዴ (ከውጭ ግንኙነት) ነበሩ::

 (ደጀ ሰላም፣ ጥር 6/2004 ዓ.ም፤ January 15/2012)፦ እ.አ.አ በጥር 2003 ተቋቁሞ በ2004 ግብጽ - ካይሮ ላይ የመጀመሪያውን ስብሰባ በማካሄድ የተጀመረው የኦሪየንታል ኦርቶዶክስ አብያተ ክርስቲያን እና የሮም ካቶሊክ ዓለም አቀፍ የነገረ መለኮት ውይይት የጋራ ኮሚሽን ዘጠነኛ ዙር ስብሰባ ከነገ በስቲያ፣ ጥር ስምንት ቀን 2004 ዓ.ም በጽርሐ መንበረ ፓትርያርክ የዓለም አብያተ ክርስቲያን ም/ቤት የስብሰባ አዳራሽ ይጀመራል፡፡
በስብሰባው የሚሳተፉት የአብያተ ክርስቲያኑ ተወካዮች ነገ፣ ጥር ሰባት ቀን 2004 ዓ.ም ተጠቃለው አዲስ አበባ ይገባሉ ተብሎ ይጠበቃል፡፡ ለስብሰባው በወጣው መርሐ ግብር መሠረት በመጀመሪያው ቀን ማለትም ጥር ስምንት ቀን 2004 ዓ.ም የኦሪየንታል ኦርቶዶክስ አብያተ ክርስቲያን እና የካቶሊክ ቤተ ክርስቲያን ተወካዮች ለየብቻቸው በተዘጋጀው አጀንዳ ላይ ተናጠላዊ ውይይት የሚያካሂዱ ሲሆን ጥር 9፣ 10 እና 12 ቀን ደግሞ ውይይቱ በጋራ እንደሚካሄድ ተገልጧል፡፡
ጥር 11 ቀን 2004 ዓ.ም የስብሰባው ተካፋዮች የጥምቀተ ክርስቶስ በዓል በብሔራዊ ደረጃ በሚከበርበት በጃንሜዳ ባሕረ ጥምቀት ይገኛሉ፡፡ ጥር 13 ቀን ደግሞ በሚደርሰው ጸሎተ ቅዳሴ ላይ ይሳተፋሉ ተብሏል፡፡
የቀደሙት ስምንት ዙር ስብሰባዎች በግብጽ፣ አርመን፣ ሮም (ሦስት ጊዜ)፣ ሶርያ እና ሊባኖስ የተካሄዱ ሲሆን ማክሰኞ፣ ጥር ስምንት ቀን 2004 ዓ.ም በአዲስ አበባ የሚስተናገደው ስብሰባ በብፁዕ ወቅዱስ ፓትርያርክ አቡነ ጳውሎስ በተደረገ ጥሪ የሚከናወን ነው፡፡ ለስብሰባው ተሳታፊዎች ማጓጓዣ እና መስተንግዶ በጀት ተመድቦ ቅድመ ዝግጅት የተደረገ ቢሆንም በሕገ ቤተ ክርስቲያን መሠረት የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ከውጭ አብያተ ክርስቲያናት ጋ ያላትን ግንኙነት ለማስፋፋትና ለማጠናከር ሓላፊነት በተጣለበት ቅዱስ ሲኖዶስ ዘንድ በስብሰባው ስለሚሳተፉ ልካን ይሁን ስለ ስብሰባው ተልኮ ቅዱስ ሲኖዶስ ይሁን ቋሚ ሲኖዶስ ስላስተላለፈው ውሳኔ የሚታወቅ ነገር አለመኖሩ ነው የሚነገረው፡፡
ይህም ስብሰባ በብፁዕ አቡነ ጎርጎርዮስ አገላለጽ÷ በሀብት እና በግዘፏ ተመክታ ጥንታውያን ኦርቶዶክሳውያን አብያተ ክርስቲያናትን ስትንቅ እና ስታዋርድ ከኖረችው የሮም ካቶሊክ ጋ በመሠረታዊ የአብያተ ክርስቲያን ሐዋርያዊ አገልግሎት እና ምሥጢራተ ቤተ ክርስቲያን ፍጹም አንድነት እና ወዳጅነት ጉዳይ ላይ ይይት የሚደረግበት በመሆኑ ሁኔታውን አሳሳቢ ያደርገዋል፡፡ በተለይም የሮም ካቶሊክ ቤተ ክርስቲያን እና መሰሎቿ ስለ ኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን አስበው የጻፉ መስለው ቤተ ክርስቲያኒቱ የምትዋረድበትን ማንኛውንም ነገር እንደመሰላቸው ሲያቀርቡ፣ ታሪኳንና ማንነቷን ሲሻሙ የኖሩና ያሉ መሆናቸው ስጋታችንን ያጠነክረዋል፤ ሌላው ቀርቶ የኢትዮጵያ ካቶሊካዊት ቤተ ክርስቲያን በተቋማዊ ድረ ገጿ በኢትዮጵያ ያላትን ዕድሜ የምትቆጥርበትን ዘመን ከኢትዮጵያዊው ጃንደረባ ጀምሮ ማድረጓ፣ የሌላውን ትውፊት የራስ አስመስሎ ማዳበል እንደ ብፁዕነታቸው አገላለጽ “በታሪክ እና በትውፊት ላይ ማመፅ ነው፡፡”
የጋራ ኮሚሽኑ አባላት የሆኑ የኦሪየንታል ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ አብያተ ክርስቲያን ስድስት ሲሆኑ እነርሱም የኮፕት ኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያን፣ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን፣ የመላው አርመን ሐዋርያዊት ቤተ ክርስቲያን፣ የኪልቂያ ሐዋርያዊት አርመን ቤተ ክርስቲያን፣ የሕንድ - ማላንካራ ኦርቶዶክስ ሶርያ ቤተ ክርስቲያን፣ የሶርያ ኦርቶዶክ ቤተ ክርስቲያን የኤርትራ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ናቸው፡፡
የኦሪየንታል ኦርቶዶክስ አብያተ ክርስቲያን በ451 ዓ.ም በኬልቄዶን ጉባኤ መለካውያን “ለክርስቶስ አንድ አካል ሁለት ባሕርይ ሁለት ግብር አለው” በሚል የወሰነውን በማውገዝ “ክርስቶስ አንድ አካል አንድ ባሕርይ ነው” በማለት የተለዩ ናቸው፡፡ ክርስቶስን አንድ አካል አንድ ባሕርይ ነው የምንለውም እንደ አቡሊናርዮስ ከፍለን፣ ቀንሰን፤ እንደ አውጣኪ አጣፍተን ሳይሆን እንደ ነፍስ እና ሥጋ ተዋሕዶ በባሕርይ ተዋሕዶ በዚህም ከኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያን ጋራ የታሪክና ዶግማ አንድነት አላቸው፡፡ በሌላው ክፍል የሚታወቁት በቤተሰብነት ነው፤ አብረው ይቀድሳሉ፤ አብረው ይቈርባሉ፡፡


Post a Comment

Blog Archive

የአቡነ ጳውሎስ "ሐውልተ ስምዕ"

ነጻ ፓትርያርክ ምርጫ ቢሆን ኖሮ ማንን ይመርጡ ነበር? እንበልና ሁሉም ነገር ሥርዓቱን ጠብቆ የተከናወነ የእጩዎች ምርጫ ቢሆን ኖሮ፣ አሁን የምናነሣቸው ጉድለቶች ባይኖሩ ኖሮ፣ 6ኛው ፓትርያርክ እንዲሆን የምትመርጡት ማንን ነበር? (ማሳሰቢያ፦ አሁን ያለው ክፍፍል እና የመንግሥት ተጽዕኖ ባይኖር ኖሮ ተብሎ የሚመለስ ጥያቄ ነው። የምን “ባይኖር ኖሮ ነው” የሚል አስተያየት ካለዎትም እናከብራለን።)