December 14, 2011

በጋሻው በመ/ር ዘመድኩን ላይ የመሠረተው ክስ የፀረ-ፕሮቴስታንታዊ-ተሐድሶውን ጥምረት እያጠናከረው ነው


  • “የአዲስ አበባ ጥምቀት ተመላሽ ወጣቶች ኅብረት”፣ ኦርቶዶክሳውያን ፖሊሶች እና የችሎት ተከታታዮች ለመ/ር ዘመድኩን ያላቸውን አጋርነት ገልጸዋል::
  • በድብደባ ሙከራ ወንጀል ክስ እንዲመሠረትበት የተወሰነበት መናፍቁ አሰግድ ሣህሉ መ/ር ዘመድኩን ከሕገ ወጡ ቡድን ጋራ ዕርቅ እንዲያወርድ ተማፀነ::
  • በጠቅላይ ቤተ ክህነቱ ጥያቄ የተቋረጠው የክስ መዝገብ እንዲቀጥል ተደርጓል::
(ደጀ ሰላም፣ ታኅሣሥ 4/2004 ዓ.ም፤ ዲሴምበር 14/2011/ READ IN PDF)፦ በጋሻው ደሳለኝ በመ/ር ዘመድኩን በቀለ እና ዲያቆን ደስታ ጌታሁን ላይ በስም ማጥፋት ወንጀል መሥርቶት የነበረውና በጠቅላይ ቤተ ክህነት ዋና ሥራ አስኪያጅ ብፁዕ አቡነ ፊልጶስ ጥያቄ ተቋርጦ የነበረው የክስ መዝገብ ዳግመኛ ተከፍቶ እንዲንቀሳቀስ በፍትሕ ሚኒስቴር ዴኤታ አቶ ብርሃኑ ጸጋዬ መመሪያ ከተሰጠ በኋላ ሁለቱ ተከሳሾች ዛሬ፣ ታኅሣሥ አት ቀን 2004 ዓ.ም ጠዋት በፌዴራሉ የመጀመሪያ ደረጃ ፍ/ቤት ቦሌ ምድብ ችሎት ቀርበዋል፡፡

የክሱ ፋይል መ/ር ዘመድኩን ለማራኪ መጽሔት ከሰጡት ቃለ ምልልስ፣ ዲያቆን ደስታ ጌታሁን ደግሞ “የሰባኪው ሕጸጽ” በሚል ርእስ ካሳተሙት መጽሐፍ ጋራ በተያያዘ ቀደም ሲል ተቋቁሞ የነበረው ክስ መሆኑን ለችሎቱ የተናገሩት ዳኛ ሁለቱ ተከሳሾች ያለጠበቆቻቸው የቀረቡ በመሆኑ፣ እያንዳንዳቸው እንደ ቀድሞው የብር 5000 ዋስ በማስያዝ ታኅሣሥ 10 ቀን 2004 ዓ.ም ጠበቆቻቸውንና የመከላከያ ማስረጃዎቻቸው ይዘው እንዲቀርቡ ትእዛዝ ሰጥተዋል፡፡
ከትእዛዙ በፊት ዐቃቤ ሕግ ሙሉ ግደይ በዋስትናው ጉዳይ ላይ የተለየ አስተያየት ይኖራቸው እንደሆነ ከዳኛው ለቀረበላቸው ጥያቄ የቀድሞው የዋስትና መጠን በቂ በመሆኑ ላይ ተቃውሞና ልዩነት እንደሌላቸው ተናግረዋል፡፡ የመ/ር ዘመድኩን ጠበቃ የሆኑት አቶ ጌትነት የሻነው ከትእዛዙ በኋላ በችሎት ቀርበው በቀጣ ቀጠሮ የመከላከያ ምስክሮችን ከማቅረባቸው በፊት በክሱ ላይ ማሳሰቢያ እንዳላቸው ቢያስታውቁም ማሳሰቢያቸውን በቀጣዩ ቀጠሮ እንዲያቀርቡ በዳኛው ተነግሯቸዋል፡፡
“የሰባኪው ሕጸጽ” መጽሐፍ ያሳተሙትና የክሱ መቋረጥ ውሳኔ በተነገረበት በቀደመው የችሎቱ ውሎ ማብቂያ ላይ በአሰግድ ሣህሉ የድብደባ ሙከራ ወንጀል የተቃጣባቸው ዲያቆን ደስታ ጌታሁን በዛሬው ችሎት አቤቱታ አቅርበዋል፡፡ ለካራማራ ፖሊስ ምስክሮቻቸውን ይዘው ቀርበው ቃላቸውን በማስመዝገብ መጥሪያ ካወጡ በኋላ ከዐቃብያነ ሕግና ከጽ/ቤቱ ሓላፊ ጋራ መነጋገራቸውን ያስረዱት ዲያቆን ደስታ ዐቃቤ ሕግ ግን ክሱን ለመመሥረት ፈቃደኛ አለመሆኑን አስታውቀዋል፡፡ አቤቱታውን ያዳመጡት ዳኛው ዲያቆን ደስታ ጉዳዩን ወደ ፍትሕ ሚኒስቴር ዴኤታው አቶ ብርሃኑ ጸጋዬ ቀርበው እንዲነጋገሩበትና ውጤቱን ለችሎቱ እንዲያሳውቁ ትእዛዝ ሰጥተዋቸዋል፡፡ አንዳንድ አስተያየት ሰጪዎች የዲያቆን ደስታ አቤቱታ በዚህ ውስን አጋጣሚ የፍትሕ ሥርዐቱ የሚፈተሽበት አንድ ማሳያ መሆኑን ተናግረዋል፡፡
በዛሬው የችሎቱ ውሎ የደብረ ጽጌ ቅዱስ ዑራኤል ቤተ ክርስቲያንና አካባቢው የጥምቀት ተመላሽ ወጣቶች ከችሎቱ ጅማሬ እስከ ፍጻሜው በቁጥር በርከት ብለው በመገኘት ድባቡን አስገርመዋል፡፡ በአርማጌዶን ካሴት እና በአርማጌዶን ቪሲዲ መ/ር ዘመድኩንን የሚያውቁ ኦርቶዶክሳውያን የችሎቱ ተከታታዮች፣ የጸጥታ አስከባሪዎችና በተለያዩ የክስ መዝገቦች የቀረቡ ጥቂት የማይባሉ ባለጉዳዮች ሳይቀሩ በአስፈላጊው መንገድ ከጎናቸው በመቆም ድጋፋቸውን እንደሚሰጧቸው ሲገልጹ ተሰምተዋል፡፡
ንት መ/ር ዘመድኩን ከአርማጌዶን ቁጥር አንድ ቪሲዲ ጋ በተያያዘ በበጋሻው ተከሰው በፌዴራሉ የመጀመሪያ ደረጃ ፍ/ቤት አራዳ ምድብ ችሎት በቀረቡበት ወቅት እንዲያሲዙት የተጠየቀውን የብር 3000 ዋስ እርሳቸው የማያውቋቸውና ችሎቱን ለመከታተል የተገኙ ምእመናን መሸፈናቸው ተመልክቷል፡፡ በዛሬው ችሎት ሁለቱ ተከሳሾች እያንዳንዳቸው የተጠየቁትን የብር 5000 ዋስትናም መ/ር ዘመድኩን በራሳቸው ከጨመሩት ብር 1000 ውጭ/ በተመሳሳይ መንገድ መሸፈኑ ተገልጧል፡፡
ከፍርድ ቤቱ ውሎ መጠናቀቅ በኋላ በችሎቱ ሥነ ሥርዐትና በፀረ - ተሐድሶው ጎራ የታየው መተባበር ያስደነገጣቸውም ያበሳጫቸውም ከሚመስሉት አንዱ የሆነው አሰግድ ሣህሉ ከደብረ ጽጌ ቅዱስ ዑራኤል “ጥምቀት ተመላሽ ወጣቶች” ተወካይ ጋ መነጋገሩ ተዘግቧል፤ በንግግሩም አሰግድ ሣህሉ “ምናለ ይህ ጉዳይ በዕርቅ ቢያልቅና ይቅር ብንባባል?” የሚል ጥያቄ ያቀረበ ሲሆን ጉዳዩ የግል ጠብ ሳይሆን እርሱን ጨምሮ ሕገ ወጡ ቡድን በቤተ ክርስቲያን ላይ እያደረሰ ያለውን በደል በቀኖናዊ፣ ሕጋዊና አስተዳደራዊ መንገድ የሚፈታበት አካሄድ አካል እንደሆነ በተወካዩ አማካይነት እንደተነገረው፤ ይቅርታ/ዕርቅ የሚያስፈለገውም ለመ/ር ዘመድኩን ሳይሆን ለሕገ ወጡ ቡድን በመሆኑ ከበደሏት ቤተ ክርስቲያን ይቅርታ እንዲጠይቁም ተመክረዋል፡፡ ይሁንና አሰግድ በእርሱ በኩል በጋሻውን እንደሚያግባባ፣ ወጣቶቹም መ/ር ዘመድኩንን እንዲያሳምኑለት በመማፀን ሽምግልና በመጠየቁ መቀጠሉ ነው የተነገረው፡፡
በአጠቃላይ በትንቱ ይሁን በዛሬው የችሎቶቹ ውሎዎች የታዩት ተጨባጭ መተባበሮች የፀረ - ፕሮቴስታንታዊ ተሐድሶ ንቅናቄው ሰፊ መሠረት መያዙንና ምእመኑ መንፈሳዊውን ተጋድሎ የራሱ ጉዳይ ለማድረጉ፣ በቤተ ክርስቲያናችን የፕሮቴስታንታዊ ተሐድሶ ሤራና ራስ በቀል አጉራ ዘለልነትም በአስተማማኝ ሁኔታ እንደሚሸነፍ ይኸው የተጠናከረ አጋርነት የማያወላዳ ምስክር ሆኖ ተወስዷል፡፡

Post a Comment

Blog Archive

የአቡነ ጳውሎስ "ሐውልተ ስምዕ"

ነጻ ፓትርያርክ ምርጫ ቢሆን ኖሮ ማንን ይመርጡ ነበር? እንበልና ሁሉም ነገር ሥርዓቱን ጠብቆ የተከናወነ የእጩዎች ምርጫ ቢሆን ኖሮ፣ አሁን የምናነሣቸው ጉድለቶች ባይኖሩ ኖሮ፣ 6ኛው ፓትርያርክ እንዲሆን የምትመርጡት ማንን ነበር? (ማሳሰቢያ፦ አሁን ያለው ክፍፍል እና የመንግሥት ተጽዕኖ ባይኖር ኖሮ ተብሎ የሚመለስ ጥያቄ ነው። የምን “ባይኖር ኖሮ ነው” የሚል አስተያየት ካለዎትም እናከብራለን።)