December 28, 2011

የድሬዳዋ ቅዱስ ገብርኤል ቤተ ክርስቲያን መዝባሪዎች እጃቸውን ከደብሩ እና ከሀገረ ስብከቱ ላይ እንዲያነሡ ተጠየቀ


  • የደብሩ አስተዳዳሪ የአጥቢያውን ልማት የመምራት አቅም የላቸውም::
  • ፖሊስ ሁለት የሰንበት ት/ቤት ወጣቶችንና አንድ ምእመን ይዞ አስሯል::
  • ተዋንያኑ ፋንቱ ማንዶዬ እና ችሮታው ከልካይ በቁሉቢ ለአኵስም ጽዮን ሙዚዬም ግንባታ የገቢ ማሰባሰቢያ መርሐ ግብር ያካሂዳሉ::
 (ደጀ ሰላም፣ ታኅሣሥ 18/2004 ዓ.ም፤ ዲሴምበር 28/2011. READ IN PDF)፦ በድሬዳዋ ሀገረ ስብከት የሚገኙ የስምንት አጥቢያ አብያተ ክርስቲያን ሰንበት ት/ቤቶች ወጣቶች እናምእመናን በሳባ ደብረ ኀይል ቅዱስ ገብርኤል ሕንፃ ቤተ ክርስቲያን ግንባታ የተፈጸመው ሙስና ተጣርቶ በሙሰኞቹ ላይ ሕጋዊ ርምጃ እንዲወሰድ፣የደብሩን አስተዳደር በመምራት ረገድ የከፋ የአቅም ማነስታይቶባቸዋል፤በሰበካ መንፈሳዊ ጉባኤው የተተለሙ የልማት ዕቅዶች ተፈጻሚ እንዳይሆኑ ዕንቅፋት ፈጥረዋልየተባሉት የደብሩ አስተዳዳሪ መልአከ ኀይል ቆሞስ አባ ገብረ እግዚአብሔር ቸኮል ከሓላፊነታቸው እንዲወገዱ በተቃውሞ ትዕይንት ጠየቁ፡፡

የተቃውሞ ተሰላፊዎቹ “ደካማ እና ነውረኛ” በማለት ለገለጧቸው የደብሩ አስተዳዳሪ እና ለሙሰኞቹ የሕንፃ አሠሪ ኮሚቴ አመራሮች ሽፋን በመስጠት ዝርፊያውን አጠናክረዋል፤ ምእመኑ በየደረጃው ላቀረባቸው አቤቱታዎች በአድርብዬ ጠባይ ተመጣጣኝ ርምጃ አልወሰዱም ያሏቸውን የሀገረ ስብከቱን ሥራ አስኪያጅም ነቅፈዋል፡፡ የከተማው ፖሊስ ኮሚሽን የተቃውሞ ትዕይንቱን ቀስቅሰዋል፤በዋናነትም አስተባብረዋል ያላቸውን ሁለት የሳባ ደ/ኀ/ቅ/ ገብርኤል ቤተ ክርስቲያን ሰንበት ት/ቤት ወጣቶች እና አንድ ምእመን ይዞ ማሰሩም ተመልክቷል፡፡ ሁለቱ ወጣቶች እና ምእመኑ በድሬዳዋ የፌዴራል መጀመሪያ ደረጃ ፍ/ቤት ቀርበው ምርመራዬን አልጨረስኩም ባለው ፖሊስ የ14 ቀናት ጊዜ ቀጠሮ የተጠየቀባቸው ቢሆንም ፍ/ቤቱ ከአራት ቀናት በኋላ እንዲያቀርባቸው ትእዛዝ ሰጥቷል፡፡
የሰንበት ት/ቤት ወጣቶቹ እና ምእመናኑ ጥያቄዎቻቸውን በተቃውሞ ትዕይንት ያቀረቡት በየዓመቱ ታኅሣሥ 19 ቀን በርእሰ አድባራት ቁሉቢ ደብረ ፀሐይ ቅዱስ ገብርኤል ቤተ ክርስቲያን ከሚከበረው የቅዱስ ገብርኤል ክብረ በዓል አስቀድሞ ዛሬ ረፋድ ላይ ወደ ድሬዳዋ ላመሩት ብፁዕ ወቅዱስ ፓትርያርክ አቡነ ጳውሎስ የተለመደው አቀባበል በሚደረግበት በደብረ ምሕረት ቅዱስ ሚካኤል ካቴድራል በመገኘት ነው፡፡ ወጣቶቹ እና ምእመናኑ ጥያቄያቸውን ለፓትርያርኩ ለማቅረብ በካቴድራሉ ተሰልፈው በሚጠባበቁበት ወቅት በመፈክር መልክ ከያዟቸው ኀይለ ቃሎች ውስጥ፡- “የሳ/ደ/ኀ/ቅ/ ገብርኤል ቤተ ክርስቲያን አስተዳዳሪ ብቃት ስለሚያንሣቸው ከሓላፊነታቸው ይነሡ”፤ “እነ ኢንጅነር ሰሎሞን ካሳዬ ከሀገረ ስብከታችን ላይ እጃቸውን ያንሡ”፤ “የብፁዓን አባቶቻችንን ውሳኔ እናከብራለን” የሚሉ ይገኙበታል፡፡
ፓትርያርኩ ቀትር ላይ ድሬዳዋ አየር ማረፊያ ሲደርሱም ሆነ በካቴድራሉ ከተገኙ በኋላ ለወትሮው አቀባበሉን የሚያደምቁት የሀገረ ስብከቱ ስምንት አጥቢያ አብያተ ክርስቲያን አስተዳዳሪዎች፣ የሰበካ መንፈሳዊ ጉባኤያቱ ሊቃነ መናብርት፣ የሰንበት ት/ቤት ወጣቶች እና ምእመናን እንደ ወትሮው አለመገኘታቸው ታውቋል፡፡ ለፓትርያርኩ አቀባበል መቀዝቀዝ የወዲያው ምክንያቱ ፖሊስ በሰላማዊ መንገድ ጥያቄያቸውን ለማቅረብ ከተዘጋጁት ወጣቶች መካከል ሁለቱን፣ ከምእመናኑም አንዱን ለይቶ በመውሰዱ ሰልፈኞቹ ወደታሰሩበት ፖሊስ ጣቢያ በመሄዳቸው ነው ተብሏል፡፡ ዓይነተኛው ምክንያት ደግሞ በሳባ ደብረ ኀይል ቅዱስ ገብርኤል ቤተ ክርስቲያን ሕንፃ ሥራ ጋራ በተያያዘ የተፈጸመው ሙስና እና በተሐድሶ ኑፋቄ አራማጅነታቸው የተነሣ ውሳኔ የተላለፈባቸውን ሦስት ግለሰቦች ቀኖናዊ ቅጣት አፈጻጸም ቸል በማለት የሀገረ ስብከቱ ሥራ አስኪያጅ እና ሊቀ ጳጳስ ወደ ቀድሞ ቦታቸው እንዲመለሱና በእግዳቸው ወቅት ‹የቆያቸው› ውዝፍ ደመወዛቸው እንዲከፈላቸው ትእዛዝ ማስተላለፋቸው፣ ይህን ውሳኔያቸውን እንዲያጤኑ ለቀረበው ጥያቄም ምላሽ አለመስጠታቸው በአገልጋዩ እና ምእመኑ ዘንድ የፈጠረው ቁጣና ሐዘን መሆኑ ተዘግቧል፡፡
ለእስር ከተዳረጉት ሁለት ወጣቶች መካከል አንዱ (ኢንጅነር ወንድወሰን ብርሃኑ) ለሕንፃ ቤተ ክርስቲያኑ ሥራ በአማካሪ መሐንዲስነት ያገለገለ እና በዋናነት በኮሚቴው ሰብሳቢ ብርሃኔ መሐሪ የሚፈጸመውን ሙስና ሲቃወም የቆየ ነው፤ የእስሩ ዓላማ የጠቅላይ ቤተ ክህነቱ ምሕንድስና ዘርፍ ሓላፊ አቶ ሰሎሞን ካሳዬ ታኅሣሥ 19 ቀን በደብሩ ሕንፃ አሠሪ ኮሚቴ የተፈጸመውንና እርሳቸውም ከጥቅሙ ተጋሪ የሆኑበትን የጠቅላይ ቤተ ክህነቱን የኦዲት ሪፖርት የሚያስተባብል የማስተባባያ ሪፖርት ያለ ተቃዋሚ ለምእመኑ ለማቅረብ ለማስፈራራት የታቀደ ሳይሆን እንደማይቀር ለጉዳዩ ቅርበት ያላቸው አካላት ተናግረዋል፡፡ ቀደም ሲል አቶ ሰሎሞን በተመሳሳይ መንገድ ያደረጉት የተሳሳተ የማስተባባያ ሪፖርት የማቅረብ ሐሳብ በምእመኑ ማስጠንቀቂያ የከሸፈ በመሆኑ ለነገው ክብረ በዓል የተዘጋጁበት ሙከራም እንደማይሳካላቸው ምእመናኑ እየተናገሩ ይገኛሉ፡፡
የጠቅላይ ቤተ ክህነት ቁጥጥር አገልግሎት ኦዲተሮች ከሳባ ደብረ ኀይል ቅዱስ ገብርኤል ቤተ ክርስቲያን ሕንፃ አሠሪ ኮሚቴ አመራሮች እስከ መንበረ ፓትርያርኩ በተዘረጋው የጥቅም ሰንሰለት ስለተፈጸመው ሙስና አጣርተው ባቀረቡት ሪፖርት መሠረት ከፕሮጀክት አማካሪ መሐንዲስ ይሁንታ ሳይገኝ፣ ምንም ዓይነት የቅድመ ክፍያ ዋስትና ሳይቀርብ አላግባብ ለሕንፃ ሥራ ተቋራጩ ከፍተኛ ገንዘብ ተከፍሏል፡፡
በቃል ትእዛዝ እና ያለዋስትና በብድር መልክ ለሕንፃ ሥራ ተቋራጩ በየጊዜው የተፈጸመው ይኸው ያልተገባ ክፍያ በውለታ ጊዜው ውስጥ ለሕንፃው አጠቃላይ የግንባታ ፕሮጀክት ሊከፈል ከነበረው ወጪ ከግማሽ በላይ ነው፡፡ ሆኖም የሕንፃ ሥራው ከውል ጊዜው አራት ዓመት በላይ ዘግይቶም ከ65 በመቶ በላይ ባለመጠናቀቁ፣ ይህም በየጊዜው በሚንረው የግንባታ ማቴሪያሎች ወጪ የተነሣ ሕንፃው መጀመሪያ ከተገመተው 2.9 ሚሊዮን ብር ጠቅላላ ወጭ ወደ 4.8 ሚሊዮን ብር በማሻቀቡ ደብሩን ለከፍተኛ ወጪ እየዳረገው እንደሚገኝ ተመልክቷል፡፡ ከዚህም ባሻገር ከሕንፃው ዲዛየን ጋራ የማይጣጣሙ በግንባታው ገጽታ ላይ የሚስተዋሉ የኢንጂነሪንግ ችግሮች መኖራቸውም ነው የሚነገረው፡፡
የጠቅላይ ቤተ ክህነቱ የቁጥጥር አገልግሎት ኦዲተሮች በምርመራ ስላረጋገጡት የ1.8 ሚሊዮን ብር ጉድለት መተማመን ተፈጥሮ የደብሩ ሰበካ አስተዳደር ጉባኤ በጉድለቱ ሳቢያ በሕንፃ ሥራ ተቋራጩ ቀጣይነት እንዲሁም በተጓተተው ግንባታ ዕጣ ፈንታ ላይ ያነሣቸው ጥያቄዎች መፍትሔ ሳይበጅላቸው የጠቅላይ ቤተ ክህነቱ ምሕንድስና ዘርፍ ኢንጅነር ሰሎሞን ካሳዬ ከፓትርያርኩ ልዩ ጸሐፊ እና ከሕንፃ አሠሪው ኮሚቴ ሰብሳቢ ብርሃኔ መሐሪ ጋራ በመተባበር የኦዲተሮችን አቋም የሚያስቀይር እና የቀደመውን ኦዲት ሪፖርት ግኝቶች የሚያስተባብል የቅሰጣ ሪፖርት በጓሮ በር አዘጋጅተዋል፡፡ በዚህም ሳያበቁ ከምእመኑ እና ከመንግሥት ተጠያቂነት በመሸሽ ከሀገር ጠፍቶ ለሰነበተው የሕንፃ ሥራ ተቋራጭ ከውል ጊዜው ውጭ ለሆነና በ1994 ዓ.ም የቋሚ ኮንስትራክሽን መተዳደሪያ ደንብ አንቀጽ 70 መሠረት ዝርዝሩ ተለይቶ ላልታወቀ የግሽበት/የግንባታዋጋ መናር በሚል የተጨማሪ ብር 900,000 ክፍያ እንዲፈጸም አጸድቀዋል፤ እንደ ምንጮቹ ጥቆማም ከዚህ ሕገ ወጥ ክፍያ እንደ የደረጃቸው ጥቅም ተጋርተዋል፡፡
የኤጲስ ቆጶስ ሹመት ተስፈኛው የሆኑት የሀገረ ስብከቱ ሥራ አስኪያጅ ቆሞስ አባ አረጋዊ ነቦምሳ እና የሀገረ ስብከቱ ሊቀ ጳጳስ ብፁዕ አቡነ ገሪማ ለዚህ ሁሉ በደል ቸልተኝነት በማሳየት የተፈጸመውን ሙስና እና የአስተዳደር በደል ለመረጠው ምእመን በሪፖርት አጋልጦ የተተኪ ሰበካ መንፈሳዊ ጉባኤ አባላትን ለማስመረጥ የተዘጋጀውን ሰበካ ጉባኤ አስተዳደር አባላት ከቃለ ዐዋዲው ውጪ ከሓላፊነታቸው እንዲለቁ ከፓትርያርኩ ልዩ ጽ/ቤት በተጻፈ ደብዳቤ መመሪያ እንዲወርድ አድርገዋል፡፡
ይሁንና ጉዳዩን በቅርበት የሚከታተለው የአጥቢያው ምእመን ከትላንት በስቲያ እሑድ በተካሄደው አዲስ የሰበካ መንፈሳዊ ጉባኤ አባላት ምርጫ ንቁ ተሳትፎ በማድረግ በሐቅ የሚያገለግሉትን የቤተ ክርስቲያን ልጆች መርጧል፡፡በአንጻሩ ብርሃኔ መሐሪ የተባሉ የሕንፃ አሠሪ ኮሚቴው ሰብሳቢ ግን ከሌሎች የጥቅም ተጋሪዎቻቸው ጋራ አሁንም በሓላፊነታቸው ላይ እንደተቀመጡ ይገኛሉ፡፡ዛሬ የከተማው ምእመናን እና የሰንበት ት/ቤት ወጣቶች ጥያቄያቸውን በሰላማዊ መንገድ ለማቅረብ በተዘጋጁበት ሁኔታ ለሁለት ወጣቶች እና አንድ ምእመን መታሰር የእኚህ ግለሰብ ግፊት እንዳለበት ተጠቁሟል፡፡ግለሰቡ በስመ ታጋይ የሚነግዱ፣ የድሬዳዋ እግር ኳስ ፌዴሬሽን ዐቃቤ ነዋይ በነበሩበት ወቅት የፌዴሬሽኑን ካዝና በማራቆት የተባረሩ፣ ከደብሩ ሕንፃ ግንባታ ፕሮጀክት በሚጋሩት ሕገ ወጥ ጥቅም ሽንሌ በተባለ የከተማዋ ክፍል የግል ኢንቨስትመታቸውን እያካሄዱ የሚገኙ ሙሰኛ እና ጀብደኛ ግለሰብ መሆናቸው ይነገርባቸዋል፡፡
ብፁዕ አቡነ ገሪማ የፌዴራዊ መንግሥት ሁለተኛ ከተማ የሆነችው ድሬዳዋ ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ ይሁኑ እንጂ በመንበረ ጵጵስናቸው አሉ ለማለት እንደማያስደፍር የሀገረ ስብከቱ ምንጮች ይናገራሉ፡፡ “የሀገረ ስብከቱ ጽ/ቤት ሠራተኞች ደመወዝ የሚከፈለው የሒሳብና በጀት ክፍል ሠራተኛው በየወሩ አበል እየታሰበለት ደመወዝ መክፈያ ቅጽ እየያዘ አዲስ አበባ ጽርሐ መንበረ ፓትርያርክ ድረስ እየተመላለሰ ብፁዕነታቸውን በማስፈርም ነው፤” ይላሉ በሊቀ ጳጳሱ ግራ የተጋቡ አስተያየት ሰጪዎች፡፡ ይሁንና አስተያየት ሰጪዎቹ እንደሚናገሩት እንኳን አሁንና ቀድሞም አቡነ ጳውሎስ በዓመት ሁለት ጊዜ፣ ታኅሣሥ 19 እና ሐምሌ 19፣ ለቅዱስ ገብርኤል ክብረ በዓልወደ ድሬዳዋ በወረዱ ቁጥር ሊቀ ጳጳሱ አይለዩዋቸውም፡፡ ዛሬም ፓትርያርኩ ወደ ድሬዳዋ ሲያመሩ ከብፁዕ አቡነ ሕዝቅኤል፣ ብፁዕ አቡነ ፊልጶስ እና ብፁዕ አቡነ ያሬድ ጋራ ብፁዕ አቡነ ገሪማም አብረዋቸው ነበሩ፡፡ በእነዚህ የፓትርያርኩ ምልልሶች ወቅት የሀገረ ስብከቱ አጥቢያ አብያተ ክርስቲያን ተራ ገብተው ለእያንዳንዱ አቀባበል በፉክክር መልክ ለመስተንግዶ በሚያወጡት በርካታ ሺሕ ብሮች(በትንሹ ከ20,000 ብር ያላነሰ) ግብር ያስገባሉ፡፡
ዛሬ ማምሻውን ፓትርያርኩ በ1.5 ሚሊዮን ብር ያሠሩት ማረፊያቸው በሚገኝበት በደብረ ምሕረት ቅዱስ ሚካኤል ካቴድራል ከወትሮው ያነሰ ቁጥር ያለው ምእመን በተገኘበት የሠርክ መርሐ ግብር ተካሂዷል፤ አቡነ ጳውሎስም ነገ ታኅሣሥ 18 እና 19 ቀን በቁሉቢ ደ/ፀ/ቅ/ገብርኤል ቤተ ክርስቲያን በመገኘት ለአኵስም ጽዮን ቤተ መጻሕፍት ወመዘክር(ሙዚዬም) ማሠሪያ የገቢ ማሰባሰቢያ ቅስቀሳ ያካሂዳሉ ያሏቸውን ተዋንያን ፋንቱ ማንዶዬንና ችሮታው ከልካይን አስተዋውቀዋል፡፡ከእነርሱም ጋራ የካህናት አስተዳደር መምሪያ ሓላፊ(መጋቤ ካህናቱ) ሊቀ ማእምራን ኀይለ ሥላሴ ዘማርያም፣ ጌታቸው ዶኒ እና ሌሎችም ግለሰቦች መኖራቸው ተዘግቧል፡፡
በቀደመው ዜና ዘገባችን እንደገለጽነው የርእሰ አድባራት ቁሉቢ ደብረ ፀሐይ ቅዱስ ገብርኤል ቤተ ክርስቲያን በክብረ በዓል በሚያስገኘው በብዙ ሚሊዮን የሚቆጠር ገንዘብ፣በስእለት እና መባዕ በሚገቡት ስፍር ቁጥር የሌላቸው ንዋያተ ቅድሳት አማካይነት በተቋቋመው “የቁሉቢ ንዋያተ ቅድሳት ማደራጃ”ለአህጉረ ስብከት፣ ተቋማት እና መንፈሳዊ ኮሌጆች ድጎማ በሚል ሀብቱ በየጊዜው ወደ መንበረ ፓትርያርኩ ቢጋዝም ደብሩ እና አካባቢው ግን ከአንድ መለስተኛ ት/ቤት በቀር የተሠሩለት የልማት ተግባራት የሉትም፡፡

Post a Comment

Blog Archive

የአቡነ ጳውሎስ "ሐውልተ ስምዕ"

ነጻ ፓትርያርክ ምርጫ ቢሆን ኖሮ ማንን ይመርጡ ነበር? እንበልና ሁሉም ነገር ሥርዓቱን ጠብቆ የተከናወነ የእጩዎች ምርጫ ቢሆን ኖሮ፣ አሁን የምናነሣቸው ጉድለቶች ባይኖሩ ኖሮ፣ 6ኛው ፓትርያርክ እንዲሆን የምትመርጡት ማንን ነበር? (ማሳሰቢያ፦ አሁን ያለው ክፍፍል እና የመንግሥት ተጽዕኖ ባይኖር ኖሮ ተብሎ የሚመለስ ጥያቄ ነው። የምን “ባይኖር ኖሮ ነው” የሚል አስተያየት ካለዎትም እናከብራለን።)