December 27, 2011

የእነ መ/ር ዘመድኩን የፍርድ ቤት ውሎ


  • READ IN PDF.
  • “የስብከተ ወንጌል ሓላፊ ነኝ” ያሉት የበጋሻው ምስክር ስለ ሕገ ወጥ ሰባክያን የወጣውን መመሪያ “አላውቀውም፤ አልደረሰኝም” አሉ፤
  • በጋሻው በ”አርማጌዶን” ቪሲዲ “አሮጊቷ ሣራ” በሚለው ንግግር “በኑፋቄያቸው ተወግዘው ከወጡት ጋራ መነጻጸሬ አግባብ አይደለም” ቢልም ምስክሩ ታሪኩ አበራ ደግሞ “አነጋገሩ ቤተ ክርስቲያንን የማክበር እንጂ የማዋረድ አይደለም” ሲል መስክሯል፤
  • “አጉራ ዘለል ሰባክያን” ማለት “ፈቃድ የሌላቸውና ሳይማሩ የሚያስተምሩ ግለሰቦች” ማለት እንደ ሆነ ያስረዳው ታሪኩ አጉራ ዘለልነት በጋሻውን እንደማይመለከትና “መጋቤ ሐዲስ መባሉም ትክክለኛ ነው” ብሏል፤
  • ዲ/ን ደስታ ጌታሁን ያቀረቧቸው የመከላከያ ምስክሮች ተከሳሹ ያሳተሙት “የሰባኪው ሕጸጽ” መጽሐፍ “ሳይማሩ ተምረናል ሳይላኩ ተልከናል በማለት ያለፈቃድ እንሰብካለን እናስተምራለን የሚሉ ሕገ ወጥ ግለሰቦችን መቆጣጠር” በሚለው የቃለ ዐዋዲው መመሪያ መሠረት መጻፉን መስክረዋል፤
  •  “ባልማርም በአደባባይ የሐዲስ ኪዳን መጋቢ ተብዬአለሁ”/በጋሻው ደሳለኝ/፤
 (ደጀ ሰላም፣ ታኅሣሥ 16/2004 ዓ.ም፤ ዲሴምበር 26/2011.)፦ አርማጌዶን ቪሲዲ የተነሣ የስም ማጥፋት ወንጀል ክስ በተመሠረተበት መ/ር ዘመድኩን ላይ የዐቃቤ ሕግ ምስክሮች ተሰሙ፡፡ “ጉዳዩ ሃይማኖታዊ በመሆኑ ፍ/ቤቱ ክሱን የማየት ሥልጣን እንደሌለው” በተከሳሽ ጠበቃ የቀረበው መቃወሚያ በፍሬ ነገር ክርክር ወቅት የሚታይ መሆኑን የገለጸው የፌዴራሉ የመጀመሪያ ደረጃ ፍ/ቤት አራዳ ምድብ ችሎት ሦስት የዐቃቤ ሕግ ምስክሮችን ቃል ካደመጠ በኋላ ብይን ለመስጠት ለሐምሌ 19 ቀን 2004 ዓ.ም ቀጠሮ ሰጥቷል፡፡ ዲያቆን ደስታ ጌታሁን “የሰባኪው ሕጸጽ” በሚል ርእስ ባሳተሙት መጽሐፍ በተመሳሳይ አንቀጽ በቦሌ ምድብ ችሎት ለተመሠረተባቸው የስም ማጥፋት ወንጀል ክስ የመከላከያ ምስክሮቻቸውን አሰምተዋል፤ ታኅሣሥ 13 ቀን 2004 ዓ.ም ደግሞ 90 ገጽ የሰነድ ማስረጃዎቻቸውን አቅርበዋል፡፡
ታኅሣሥ 10 ቀን 2004 ዓ.ም ጠዋት በዋለው ችሎት ዲያቆን ደስታ ስለ መከላከያ ምስክሮቻቸው ቃል አስቀድመው ለፍ/ቤቱ ባስያዙት ጭብጥ፡- እርሳቸው የመ/ፓ/ጠ/ቤ/ክ ሠራተኛ መሆናቸውን፣ በጋሻው ከስብከተ ወንጌል እና ሐዋርያዊ ተልእኮ መምሪያ ፈቃድ ያልተሰጠው መሆኑን፣ ከዐውደ ምሕረት የታገደውና ከምእመኑ እንዲርቅ የተደረገውም በሕገ ወጥነቱ፣ በተሳሳተና የቤተ ክርስቲያንን አስተምህሮ በማይጠነቅቀው ስብከቱ የተነሣ “የሰባኪው ሕጸጽ” መጽሐፍ በዲ/ን ደስታ ከመታተሙ በፊት ስለመሆኑ፤ የመጽሐፉ መታተም ዓላማም ቅዱስ ሲኖዶስ፣ ጠቅላይ ቤተ ክህነት እና አህጉረ ስብከት በሕገ ወጥ ሰባክያን ዙሪያ ያሰራጯቸውን ማስረጃዎች በአንድነት በማሰባሰብ ምእመኑ ከሕገ ወጡ ሰባኪ ሕጸጾች ለመጠበቅ የሚችልበትን ዝግጅት ለማቅረብ እንጂ በክሱ ጽሕፈት ላይ እንደ ተመለከተው ሆነ ብሎ የግል ተበዳይን ሰብእና ለማጉደፍ ወይም ስሙን ለማጥፋት አለ መሆኑን እንደሚያስረዱላቸው ገልጸዋል፡፡
የዲያቆን ደስታ የመከላከያ ምስክር የሆኑት የፀረ-ተሐድሶ ሰባክያን ፅምረት ሰብሳቢ መ/ር ዳንኤል ግርማ እና የደብረ መዊዕ ቅዱስ ሚካኤል ካቴድራል ስብከተ ወንጌል ሓላፊ መ/ር መኰንን ደስታ “የሰባኪው ሕጸጽ” መጽሐፍ አሳታሚ በወቅቱ በመ/ፓ/ጠ/ቤ/ክ የስብከተ ወንጌል እና ሐዋርያዊ ተልእኮ መመሪያ ጸሐፊ እንደ ነበሩ፣ መምሪያው በአዲስ አበባ እና በሌሎችም አህጉረ ስብከት ፈቃድ ሳይኖራቸው እናስተምራለን፣ እንሰብካለን በሚሉ ሕገ ወጦች ላይ ቁጥጥር እንዲደረግ ቅዱስ ሲኖዶስ የካቲት 12 ቀን 2001 ዓ.ም መመሪያ ማውጣቱን፣ ይህን መመሪያም ለማስፈጸም መምሪያው ያደረገውን እንቅስቃሴ አስታውሰዋል፤ ዲያቆን ደስታ ጌታሁን የመምሪያው ጸሐፊ/የጠቅላይ ቤተ ክህነት ሠራተኛ እንደመሆናቸው መመሪያውን የማስፈጸም ግዴታ እንደነበረባቸው አስረድተዋል፡፡
በቃለ ዐዋዲው አንቀጽ 18 ንኡስ አንቀጽ 6 - 7 ስለ ስብከተ ወንጌል ክፍል ሥራና ሓላፊነት የተዘረዘረውን መሠረት በማድረግም አንድ አገልጋይ ለማስተማር በካህናት ማሠልጠኛ፣ አብነት ት/ቤት ወይም በኮሌጅ ትምህርቱን መከታተል እንዳለበት፤ ሕገ ወጦችን መቆጣጠር ግን የጠቅላይ ቤተ ክህነት ሠራተኛ ሁሉ ሓላፊነት መሆኑን፤ በጋሻው ከቅድስት ሥላሴ መንፈሳዊ ኮሌጅ ባጠፋው ጥፋት መባረሩን እንደሚያውቁ፤ ዲያቆን ደስታ ከኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ሃይማኖት ውጭ የሆኑ መጻሕፍትና ልዩ ልዩ እትሞች ለምእመናን እንዳይሰራጩ የመቆጣጠር፤ ሳይማሩ ተምረናል፣ ሳይላኩ ተልከናል በማለት ያለፈቃድ እንሰብካለን፤ እናስተምራለን የሚሉትን ሕገ ወጥ ግለሰቦችን እንደ ተቋም ይሁን እንደ አገልጋይ የመቆጣጠር ሓላፊነት እንዳለባቸው፣ መጽሐፉም በዚህ መንፈስ የተዘጋጀ ስለመሆኑ ከኅትመቱ አስቀድሞ አሳታሚው እንደነገሯቸው መስክረዋል፡፡
ዐቃቤ ሕግ ለመጀመሪያው የመከላከያ ምስክር ተከሳሹ ዲያቆን ደስታ፣ “የት ነው የተማረው?” የሚል ጥያቄ ቀርቦላቸዋል፤ ምስክሩም ዲያቆን ደስታ በደብረ መዊዕ ቅዱስ ሚካኤል ካቴድራል ለበርካታ ዓመታት ማገልገላቸውን ተናግረዋል፡፡ “ክሱን ያውቁታል ወይ? እንዴትስ ያዩታል?” በሚል ለቀረበላቸው ጥያቄም ክሱን እንደሚያውቁት፣ ይዘቱም “የሰባኪው ሕጸጽ መጽሐፍ ስሜን አጥፍቷል፤ ከሰው ልብ አርቆኛል” በሚል የቀረበ እንደ ሆነ፤ እርሳቸው ግን በጋሻው ስሙ የጠፋውና ከሰው ልብ የራቀው በመጽሐፉ ምክንያት ሳይሆን በየጊዜው በሚናገራቸው የተሳሳቱ ትምህርቶቹ፣ በካህናት አባቶች ላይ ከሚናገረው የስድብ ቃል የተነሣ መሆኑን መስክረዋል፡፡
“10 + ምላስ” በሚል በመጽሐፉ ስለተጠቀሰው ያላቸውን አስተያየት ሲጠየቁም አባባሉ ስድብ ሳይሆን በጋሻው ያልተማረ መሆኑንና የዕውቀቱን ደረጃ ለማሳየት መሆኑን፣ ይህም በሊቀ ጵጵስና ደረጃ የሚገኙ አባቶች በተለያዩ መጽሔቶች እንደመሰከሩት አጉራ ዘለል በሚል ከገለጹት ጋራ ተመሳሳይ መሆኑን አስረድተዋል፡፡ በመቀጠል ዳኛው ለመጀመሪያው ምስክር መ/ር ዳንኤል ባቀረቡላቸው የማጣሪያ ጥያቄ “ማንኛውም ሰው ሌላውን ‹ተሐድሶ› ማለት ይችላል ወይ?” ሲሉ ጠይቀዋቸዋል፤ መ/ር ዳንኤልም ማንም ከሜዳ ተነሥቶ ሌላውን ‹ተሐድሶ ነህ› ማለት እንደማይችል፣ ነገር ግን የጠቅላይ ቤተ ክህነቱ አገልጋዮች ከንግግሩ እና ከግብሩ የተነሣ በተሐድሶ መናፍቅነት የተጠረጠረን ሰው መቆጣጠር እንደሚችሉ እና እንደሚገባቸው፣ ውሳኔው ግን የቅዱስ ሲኖዶስ መሆኑን አስረድተዋል፡፡
ዳኛው ጉዳዩ “በዕርቅ ሊያልቅ እንደሚችል” ምክር ሰጥተዋል የተባለ ሲሆን የመከላከያ ምስክሮችን ቃልና ሰነዱን መርምሮ ብይን ለመስጠት ለጥር 21 ቀን 2004 ዓ.ም ተቀጥሯል፡፡ በዚሁ ችሎት በሌላ መዝገብ ማራኪ ለተሰኘ መጽሔት በሰጡት ቃለ ምልልስ ክስ የቀረበባቸው መ/ር ዘመድኩንም ለጥር 23 ቀን 2004 ዓ.ም በ8፡00 ሰዓት የመከላከያ ምስክሮቻቸውንና የሰነድ ማስረጃዎችን እንዲያቀርቡ ፍ/ቤቱ ትእዛዝ ሰጥቷል፡፡
ከቦሌው ምድብ ችሎት ውሎ አንድ ቀን ቀደም ብሎ፣ ታኅሣሥ 9 ቀን 2004 ዓ.ም፣ ከቀትር በኋላ በአራዳ ምድብ ችሎት ዐቃቤ ሕግ ከአርማጌዶን ቪሲዲ ጋራ በተያያዘ በመ/ር ዘመድኩን ላይ የመሠረተውን የስም ማጥፋት ወንጀል ክስ ያስረዱልኛል ያላቸውን ሦስት የሰው ምስክሮች አቅርቦ አሰምቷል፡፡ ዐቃቤ ሕግ ለችሎቱ ባስያዘው የምስክሮች ቃል ጭብጥ ተከሳሽ የግል ተበዳይን በአርማጌዶን ቁጥር አንድ ካሴት ከሕዝብ ልብ እንዳስወጣው፣ በአርማጌዶን ቪሲዲ ደግሞ “ሕዝቡ የግል ተበዳይን ቀጥቅጦ እንዲገድለው እንደሚሻ” መናገሩን፣ በዚህም ሳቢያ የግል ተበዳይ መልካም ሰብእና ጠፍቶ ደኅንነቱ አደጋ ላይ ስለ መውደቁ፣ ይህም በአርማጌዶን ቪሲዲ የተነሣ መሆኑን እንደሚያስረዱለት ገልጧል፡፡
የመጀመሪያው የዐቃቤ ሕግ ምስክር ራሱ በጋሻው ነበር፡፡ በችሎቱ ስለ ሥራው የተጠየቀው በጋሻው እንደተለመደው “ወንጌላዊ ነኝ” ብሏል፡፡ ከተከሳሽ ጋራም ጠብ ይሁን ዝምድና እንደሌላቸውም ተናግሯል፡፡ በቪሲዲው የተነሣም ስለደረሰበት በደል ሲያስረዳም “ከኅብረተሰቡ ተገልያለሁ፤ መልካም ሰብእናዬ ጠፍቷል፤ ተወግዘው ከተለዩ ግለሰቦች ጋራ አንድ አድርጎኛል፤ ክብሬ ተነክቷል” ብሏል፡፡ በዐቃቤ ሕግ ተጨማሪ ጥያቄም አርማጌዶን ቪሲዲ ከተሰራጨ ጀምሮ በከተማው በየትኛውም ቦታ በነጻነት መንቀሳቀስ እንዳልቻለ፣ የመኪናው መስተዋት በየጊዜው በግለሰቦች እንደሚሰበርበት፣ በአጠቃላይ ሕይወቱ በአስጊ ሁኔታ ላይ እንደሚገኝ መስክሯል፡፡
የተከሳሽ ጠበቃ ጌትነት የሻነህም “በቪሲዲው አንተ ቃል በቃል ተሐድሶ የተባልክበት ክፍል አለ ወይ? አጉራ ዘለል ማለት ሰባኪ ምን ማለት ነው? ይህስ አገላለጽ አንተን ይመለከትሃል ወይ? ሕጋዊ ከሆንክስ የት ነው የተማርከው?” የሚሉ መስቀለኛ ጥያቄዎችን አቅርበዋል፡፡ በጋሻውም በቪሲዲው እርሱ ተሐድሶ እንደሆነ ቃል በቃል የሚናገር ክፍል ባይኖርም የሚመሳሰል ነገር እንዳለ፤ ይህም ተወግዘው ከወጡ ግለሰቦች ጋራ መነጻጸሩ መሆኑን፣ አጉራ ዘለልነት እንደማይመለከተው፣ መምህርነቱ ቀርቶ ዲቁናውን ከብፁዕ አቡነ በርቶሎሜዎስ መቀበሉን፣ አቡነ ፋኑኤልም በአደባባይ ‹መጋቤ ሐዲስ› የሚል ማዕርግ እንደሰጡት መልሷል፡፡
በመቀጠል የራሳቸውን ጥያቄ እንዲያቀርቡ በዳኛው የታዘዙት መ/ር ዘመድኩን ለፍ/ቤቱ በሰጡት ማስገንዘቢያ በጋሻው “ጠብ የለንም” ሲል የመሰከረው ስሕተት መሆኑን፣ ጠቡ በግል ጉዳይ የተነሣ ባይሆንም ከ2002 ዓ.ም ጀምሮ በመጽሔት በሚሰጣቸው ቃለ ምልልሶች፣ በሚያሳትማቸው መጽሐፎች፣ በሚያወጣቸው ቪሲዲዎች ውስጥ በሚያዩዋቸው ስሕተቶች የተነሣ በአደባባይ እንደሚቃወሙት፤ በአጠቃላይ ተከሳሽ ከሕገ ቤተ ክርስቲያን ውጭ በሚፈጽማቸው ዶግማዊ እና ቀኖናዊ ግድፈቶች ሳቢያ ግልጽ ልዩነት እንዳላቸው ተናግረዋል፡፡ ተወግዘው ከወጡት ጋራ ስለመመሳሰሉ ላቀረበው ክስ “አሮጊቷ ሣራ እኔን ወለደች፤ እገሌን ወለደች” የሚል እንቶ ፈንቶው የተሐድሶ መናፍቃን በነበሩት በእነ ‹አባ› ዮናስ መነገሩን በተመሳሳይ መንገዲም በራሱ መደገሙን በመ/ር ዘመድኩን የተነገረው በጋሻው “እንደርሱ ብያለሁ፤ ግን እነርሱ ከገለጹበት መንገድ ጋራ ተመሳሳይ አይደለም” ብሏል፡፡
መ/ር ዘመድኩን በመቀጠል በጋሻው አጉራ ዘለልነት እንደማይመለከተው የሰጠውን ምላሽ በማስታወስ ከየትኛው ት/ቤት እንደወጣ ጠይቀውታል፡፡ ከቅድስት ሥላሴ መንፈሳዊ ኮሌጅ ተባርሮ ሳይሆን በግል ጉዳዩ ምክንያት መውጣቱን የተናገረው በጋሻው የማስተማር ሥልጣኑን ያገኘው ከካህናት ማሠልጠኛ በወሰደው ትምህርት መሆኑን፣ በጥንቱ ሥርዐተ ትምህርት መሠረት ባይማርም “የሐዲስ ኪዳን መጋቢ የሚል ማዕርግ በአደባባይ እንደተሰጠው”፣ ቤተ ክርስቲያን በደብዳቤ እንዳላባረረችው፣ በካህናት አባቶች ላይ የስድብ ቃል እንዳልተናገረ በየመልኩ ለቀረቡለት ጥያቄዎች መልስ ሰጥቷል፡፡
ዳኛው ለበጋሻው ባቀረቡለት የማጣሪያ ጥያቄ፣ አርማጌዶን ቪሲዲ መውጣቱን እንዴትና ከማን እንደሰማ፣ ከየትና በምን ያህል ዋጋ እንደገዛው ጠይቀውታል፡፡ በጋሻውም አርማጌዶን ቪሲዲ መውጣቱን እርሱ የማያውቃቸው ሰዎች ከግሸን ደብረ ከርቤ ማርያም ደውለው እንደነገሩት፣ ቪሲዲውን ከጌልጌላ መዝሙር ቤት ሰው ልኮ እንደገዛው፣ የገዛበትም ዋጋ ኻያ አምስት ብር/25.00/ መሆኑን ተናግሯል፡፡ “ከተከሳሽ ጋራ ጠብ ወይም ዝምድና አለህ ወይ? ተብለህ ስትጠየቅ የለኝም ብለሃል፤ ተከሳሽ ደግሞ በሃይማኖት ጉዳይ ጠብ አለን እያሉ ነው፤ ይህ እንዴት ነው?” በሚል ለተጠየቀው “በአርማጌዶን ካሴት ነክቶኛል፤ ትቸው ነበር” ሲል መልሷል፤ በድጋሚ “ታዲያ እንዴት ጠብ የለንም አልክ?” ሲባልም “አይ፣ ትቼው ነው” ብሏል እርሱም በድጋሚ፡፡
በመቀጠል የዐቃቤ ሕግ ሁለተኛ ምስክር ሆኖ የቀረበው በደብረ ናዝሬት ቅዱስ ዮሴፍ ቤተ ክርስቲያን የስብከተ ወንጌል ሓላፊ በመሆን ከአንድ ዓመት ላልበለጠ ጊዜ የሠራው፣ ከሕገ ወጥ ቡድኑ ጋራ በመሠረተው ግብራዊ ትብብርና መደበኛ ሥራውን ትቶ ዱባይ ድረስ ተጉዞ ሀ/ስብከቱ በማያውቀው ተልእኮ ላይ በመሰንበቱ በደብሩ አስተዳደርና በአዲስ አበባ ሀ/ስብከት በየደረጃው በተወሰደበት ርምጃ ከሓላፊነቱ የተወገደው ታሪኩ አበራ ነው፡፡ ግለሰቡ በሰጠው ምስክርነት መ/ር ዘመድኩን እርሱን ሰሜን ሆቴል ቀጥሮት “በጋሻውን በአርማጌዶን ካሴት ከሕዝብ ልብ አውጥቸዋለሁ፤ በአርማጌዶን ቪሲዲ ደግሞ ሕዝቡ ቀጥቅጦ እንዲገድለው አደርጋለሁ፤ አንተም ‹ተሐድሶ የለም› እያልክ መናገርህን ተው” እንዳሏቸው እርሱም ይህን ጉዳይ አራዳ ፖሊስ ጣቢያ ቀርቦ ማስመዝገቡን፤ ከዚህም በተጨማሪ የስብከተ ወንጌል ሓላፊ ሆኖ በሠራበት አጥቢያ በጋሻው የሚመጣ ከሆነ ወጣቶች ደሙን እንደሚያፈሱት ሲዝቱ መስማቱን፣ ይህም በአርማጌዶን ቪሲዲ የተነሣ መሆኑን ለነፋስ ስልክ ላፍቶ ክፍለ ከተማ ፖሊስ ጣቢያ ቀርቦ ማስመዝገቡን፤ በጋሻውን ቤተ ክርስቲያን እስከ አሁን ያላወገዘችው በመሆኑ አሁንም ሰባኪ፣ መምህር እንደሚለው መስክሯል፡፡
ለታሪኩ አበራ መስቀለኛ ጥያቄ ያቀረቡት ጠበቃ ጌትነት ቤተ ክርስቲያን ምስክሩ የሚሉትን የበጋሻውን መምህርነት ታውቀው እንደሆነ፣ ካወቀችውም ከየትኛው ት/ቤት እንደተመረቀ ጥያቄ አቅርበውለታል፤ ታሪኩም በጋሻው የቅድስት ሥላሴ መንፈሳዊ ኮሌጅ ደቀ መዝሙር እንደነበር፣ አቡነ ፋኑኤልም መጋቤ ሓዲስ እንዳሉት እንደሚያውቅ በመጥቀስ መልሷል፡፡ “መጋቤ ሐዲስ በሚል የተሰጠውን ማዕርግ አሰጣጥ ትክክል ነው ብለህ ታምናለህ ወይ?” በሚል ለቀረበለት ጥያቄም “በእኔ አረዳድ ትክክል ነው” ብሏል፡፡
“አጉራ ዘለል ሰባክያን” ማለት ምን ማለት እንደሆነ እንዲያብራራ በመ/ር ዘመድኩን ለቀረበለት ጥያቄም “ፈቃድ የሌላቸው፣ ሳይማሩ የሚያስተምሩ ሰባክያን” ማለት እንደሆነ መልሷል፡፡ “ይህ ነገር በጋሻውን ይመለከተዋልን?” ለተባለውም “እስከ አሁን ሲኖዶሱ ስላልወሰነበት አይመለከተውም” ብሏል፡፡ “አንድ ሰው ሳይማር ማስተማር ይችላል ወይ?” ለተባለውም “ቅዱስ ፓትርያሪኩ አንዳንዴ የተሰጠውን ማዕርግ ጠቅሰው ስለሚጽፉለት ይችላል” ሲል ምላሽ ሰጥቷል፡፡ “ዐውደ ምሕረት ላይ ካህናትን፣ መነኮሳትን፣ ጳጳሳትን መሳደብ ማስተማር ነውን?” በሚል ለቀረበለት ጥያቄም “አንድ መምህር [ዲያቆንም ቢሆን የበላዮቹን] መገሠጽ ስለሚገባው ይችላል” በማለት መልሷል፡፡ የአጥቢያ ቤተ ክርስቲያን ስብከተ ወንጌል ክፍል ሓላፊ የነበረ እንደመሆኑ መጠን ቅዱስ ሲኖዶስ ያወጣውንና አዲስ አበባ ሀገረ ስብከት በሰርኩላር ያስተላለፈውን ሕገ ወጥ ሰባክያንን ስለ መቆጣጠር የተመለከተውን መመሪያ ያውቀው እንደሆነ ሲጠየቅም “ወደ ደብሩ አልደረሰም፤ እንዲህ ዐይነት መምሪያ ከቤተ ክርስቲያኒቱ ስለመውጣቱም አላውቅም” ብሏል፡፡ “ቤተ ክርስቲያንን አሮጊቷ ሣራ ብሎ መጥራት ተገቢ ነው ወይ?” በሚል ለቀረበለት ጥያቄም “መጽሐፍ ይላል” ቢልም መጽሐፍ የሚለው “የጨዋዪቱ የሣራ ልጆች ነው፤ የአሮጊቷ ማለቱ አግባብ ነው ወይ?” በሚል በድጋሚ ለቀረበለት ጥያቄ “መጽሐፍ ቅዱስ ባይልም የአሮጊቷ ማለት የማክበር እንጂ የማዋረድ አይደለም” ብሏል፡፡
ጠበቃ ጌትነት የሻነህ አንድ መምህር መገሠጽ እንደሚችል ታሪኩ ለመ/ር ዘመድኩን ጥያቄ የሰጠውን ምላሽ መሠረት በማድረግ “ዘመድኩን መምህር ነው ወይስ አይደለም?”  የሚል ተጨማሪ መስቀለኛ ጥያቄ አቅርበዋል፡፡ ታሪኩም “አዎ፣ ዘመድኩን መምህር ነው” ብሎ መልሷል፡፡ ከዚህም አያይዘው “መገሠጽስ ይችላልን?” ሲሉ ጥያቄ አቅርበዋል፡፡ ታሪኩም “አይ፣ የእርሱ ተግሣጽ ሳይሆን ሰዎች በጋሻውን እንዲገድሉት የሚያነሣሣ ስድብ ነው፤” ብሏል፡፡
በዕለቱ የዐቃቤ ሕግ ሦስተኛና የመጨረሻ ምስክር ሆኖ የቀረበው ካሴት እያዞረ በመሸጥ ሥራ የሚተዳደረው ዕድሜው 18 ዓመት እንደሆነው የተናገረው ያሬድ በቀለ የተባለ ግለሰብ ነው፡፡ ምስክሩ ቪሲዲውን ስሙን ከማያውቀው መዝሙር ቤት መግዛቱን፣ የገዛበትን ዋጋ ግን እንደማያውቀው ተናግሯል፡፡ ከበጋሻው አጉራ ዘለል ስብከት ጋራ በማያያዝ “ቤተ ክርስቲያን ኢየሱስ ክርስቶስን ጉደኛ በማለት ትገልጸዋለች ወይ?” በሚል ለቀረበለት ጥያቄ “አዎ! በሕፃንነቱ ድንቅ ተኣምራትን ይሠራ ስለነበር” በማለት መልሷል፡፡ “ክርስቶስ እና ዲያብሎስ በጎልጎታ ጨበጣ ገቡ” የሚለው የበጋሻው ዲስኩርም አባባል እና ከተገቢነት አኳያም ትክክል እንደሆነ አክሎበታል - ምስክሩ፡፡ በመቀጠልም “ጥቅምት 11 ቀን 2004 ዓ.ም በቅድስተ ቅዱሳን ማርያም ገዳም በተደረገው የተቃውሞ ትዕይንት መ/ር ዘመድኩን ኮፍያ አድርጎ የድብደባ ጉዳት አድርሰዋል ለተባሉ ሁለት ወጣቶች ብር ሲሰጥ አይቻለሁ፤” ብሏል ምስክሩ፡፡
በማጣሪያ ጥያቄ ላይ መ/ር ዘመድኩን ብሩን በስንት ሰዓት ለወጣቶቹ ሲሰጥ እንደ ተመለከተ በዳኛው ለቀረበለት ጥያቄም በ12፡00 ሰዓት ብሏል፡፡ በዚህ ወቅት መ/ር ዘመድኩን ምስክሩ በጠቀሰው የተቃውሞ ሰልፍ ላይ በአካል እንዳልተገኘ፣ በምትኩ በዕለቱ በተባለው ሰዓት የነገረ መለኮት ምሩቃን ማኅበር ሥራ አመራር ጉባኤ አባል እንደመሆኑ ማኅበሩ በአዲስ አበባ ሀ/ስብከት አዳራሽ እያካሄደ በነበረው ዓመታዊ ስብሰባ ላይ እንደነበር ተናግሯል፤ በመቀጠልም ምስክሩ ደብዳቢዎቹን ያውቃቸው እንደሆነ፣ ስንት ብር እንደተሰጣቸው ሲጠየቅም ደብዳቢዎቹን እንደማያውቃቸው፣ መ/ር ዘመድኩን ብሩን ጭብጥ አድርጎ፣ አመቻችቶ ስለሰጣቸው ስንት ብር እንደ ሆነ እንደማያውቅ ቢናገርም ቆይቶ በድጋሚ ሲጠየቅ የ100 ብር ኖቶች እንደ ሆኑ፣ ስንት የመቶ ብር ኖቶች ናቸው ሲባልም ብዙ የመቶ ብር ኖቶች ናቸው ሲል መልሷል፡፡
በክሱ ጽሕፈት ላይ የተመለከቱት ናትናኤል ታምራት እና አሰግድ ሣህሉ ከእኒህ የተለየ እንደማያስረዱለትና እንደማይፈልጋቸው ዐቃቤ ሕግ በመናገሩ በመስቀለኛ ጥያቄ ከመፈተንና ራሳቸውን ከማጋለጥ አምልጠዋል፡፡ ፍ/ቤቱ የዐቃቤ ሕግ ምስክሮችን ቃል መርምሮ ብይን ለመስጠት ለሐምሌ 19 ቀን 2004 ዓ.ም ቀጥሯል፡፡
እንደተጠበቀው በሁለቱም ቀናት ችሎቶቹ በውሏቸው በበርካታ የፀረ - ፕሮቴስታንታዊ ተሐድሶ ቤተሰቦች(ሰባክያነ ወንጌል፣ ዘማርያን፣ የጥምቀት ተመላሽ ወጣቶች) ተሞልተው ዘግይተው የመጡ ተመልካቾችም በመቀመጫ ዕጦት ምክንያት ሲመለሱ ተስተውሏል፡፡
የፕሮቴስታንታዊ ተሐድሶ አቀንቃኞችና ሕገ ወጦች የተሰባሰቡበት ቡድን ወደ ሽምግልናና ተማኅፅኖ በገባበት በአሁኑ ወቅት ምእመኑ ፀረ - ተሐድሶውን ትግል ወደፊት በመግፋት በተሐድሶነት የተጠረጠሩት ሕገ ወጥ ግለሰቦች መናፍቃን መሆናቸውን የገለጸበት ሁኔታ የሚጠቀስ ነው፡፡ ይህም ጉዳዩን የተመለከቱ ችሎቶችን በመከታተል ብቻ የተወሰነ ሳይሆን ለአብነት ያህል በኅዳር ጽዮን በዓል አከባበር ወቅት በከተማ አኵስም የሕገ ወጦቹን ኅትመት ውጤቶች ሲያሰራጩ የነበሩ አሳታሚ እና አከፋፋዮችን(አብ እና አንጾኪያ) በማገድ የፀረ - ተሐድሶ ቪሲዲ ሥራዎች “መናፍቃንን የሚያጋልጥ” በሚል ማስተዋወቂያ(ቅስቀሳ) እንዲሸጡ ማድረጉ ነው፡፡
ቸር ወሬ ያሰማን፤
አሜን፡፡   

[ቅዱስ ሲኖዶስ ስለ ሕገ ወጥ ሰባክያን እና ዘማርያን ያወጣውን መምሪያ፣ ጠቅላይ ቤተ ክህነት መምሪያው በሁሉም አህጉረ ስብከት እና አጥቢያዎች ተፈጻሚ እንዲሆን የጻፈውን መሸኛ፣ የደብረ ናዝሬት ቅዱስ ዮሴፍ ቤተ ክርስቲያን አስተዳደር እና ሰንበት ት/ቤት መምሪያውን በማጣቀስ በወቅቱ ታሪኩ አበራ ለነበረበት ስብከተ ወንጌል ክፍል የጻፏቸውን ዶኩመንቶች ቀጥለው ይመልከቱ]

8 comments:

Anonymous said...

lewere yetefetrachu nachu!
esti balfew ye kidst arsema betekerstyane mekatelu post adregachu nebere minale esun betastebaberu endih ye buna were kemetaweru!

firde bet wale kerebe tekesese tealalachu ahun le egna yeh were aydelem yemiasflgen. beka neku gedamaten betekertayn yelelebeten lemetekel endih sewen anekaku astebabaru.
enanate aljeziraaaaaa nachu lefelefachu yemetetefu
yezemenu seytan
lebetkerstyan yasebachu meslo yemetgodu nachu
ketekemachusaaaa ayenachu wede wedmut betekerstyan azuru
lemenafekanu demo hulum yeyerasun debere yetebek zend wetatun yetebabaer

yesu said...

He has to get his price YOU TOO. !!!!!!!!!!!!!!!!!!!!!!!!!!!!!!!

Anonymous said...

Hello dejeselam, sometimes you do forget we are spritual and we should look thing with spritual eyes. You guys are so swift for gossip. why don't you post for us some good news. Critisizing is the sprit for devil. You guys need to read more about being humble and detail looking. Now it is the time for fasting but you guys disribuiting gossip. Please stay focused!!!!!!!!!

Anonymous said...

አቤት ደጀ ሰላም ለምን ውሸት ነገር ሪፖርት ታደርጋላችሁ ለእናንተ እንደሚመች እድርጋችሁ ካቀረባችሁት እኮ ማንም አንባቢም ሆነ
ተከታታይ አይኖራችሁም። እውነቱን እንደወረደ ማስተላለፍ ነው ያለባችሁ። መቼም ስህተታችሁን የሚነግራችሁ ሰው አትወዱምና በዚህ
ምክንያት ይህንን አስተያየት ባታወጡት አይገርመኝም። የተለመደ ሥራችሁ ስለሆነ። ለማንኛውም በደጀ ብርሃን ብሎግ ይህ ጉዳይ
ዲሰምበር 22\11 እንደወረደ በእለቱ ዕለት እውነተኛ ሪፖርት አስነብቦናል። ውድ አንባቢያን ትክክለኛውን ሪፖርት ማንበብ ከፈለጋችሁ
በዚህ ብሎግ ተመልከቱ Dejebirhan.blogstpot.com

አመሰግናለሁ

Anonymous said...

This is for the person who commented at first Anonymous BY SAYING "LEWERE YETEFETRSCHU" first of all you should have some knowledge what is the MEDIA and then give your comment. i understand where you are coming from and about your feeling by just looking at your comment. if you are christian don't ever start your voice with HATE instead give your advise to whom it concern. as fare as i know about DEJE SELAM i have learned many things. do i agree with everything they write or say? the answer is NO but i agree with the most article they post it. i hope you do same other wise you shouldn't be on their Web. lastly MEDIA is place where you read many different kind of articles which is not everybody to agree with. If you really care about the Kidist Arisema church burn what have you done about it in personally? DEJE SELAM has done its part to let you know. it is your and our part to find solution not accusing one another. MY GOD bless you and all TEWAHEDO KIDIST AMEN!!!

Anonymous said...

what a hell are you guys doing? I think you are missing your mission. If you realy are men of God, you will forgive each other. Let God make you do that. Amen.

Woldegiorgis said...

Egziabher Amilake Yihchin Betekirstiyan Yitebke. Yitawokal Sytal Yeyazew Tor Eskiyalekibet Dires Mewagatu Yemayiker new. Leza new Begashaw enda Deke Mezamurutu yemiyasibuten merz hulu be eye akitachaw eyeworeweru yalu.Tiyitachewum yalikal, betkirstianim ayinnekatim, enersum mecreshachew yitawokal. Anede bemtsehet, lyla gize be EBS, lely gize... bicha amarachichen hulu eyemokeru new neger gin betekirstiyan Semayawit silehonech ayagegnuatim, ayinorubatim esk ahunim norewubat ayawukum. Enant ayin eyalachihu yematayu bechifin sewun kemamileki yimelsachihu

Anonymous said...

Sytan torun Yemecheresu Milikit Eyetaye new::

Blog Archive

የአቡነ ጳውሎስ "ሐውልተ ስምዕ"

ነጻ ፓትርያርክ ምርጫ ቢሆን ኖሮ ማንን ይመርጡ ነበር? እንበልና ሁሉም ነገር ሥርዓቱን ጠብቆ የተከናወነ የእጩዎች ምርጫ ቢሆን ኖሮ፣ አሁን የምናነሣቸው ጉድለቶች ባይኖሩ ኖሮ፣ 6ኛው ፓትርያርክ እንዲሆን የምትመርጡት ማንን ነበር? (ማሳሰቢያ፦ አሁን ያለው ክፍፍል እና የመንግሥት ተጽዕኖ ባይኖር ኖሮ ተብሎ የሚመለስ ጥያቄ ነው። የምን “ባይኖር ኖሮ ነው” የሚል አስተያየት ካለዎትም እናከብራለን።)