December 22, 2011

የጽላተ ጽዮን ነገር - የደጀ ሰላም ሪፖርታዥ


አቡነ ጳውሎስ ከጽላተ ጽዮን ማደሪያ እድሳት ይልቅ ለሙዚዬሙ ግንባታ ትኩረት ሰጥተዋል
 (ደጀ ሰላም፣ ታኅሣሥ 12/2004 ዓ.ም፤ ዲሴምበር 22/2011. READ IN PDF)
  •  የርእሰ ገዳማት ወአድባራት አኵስም ጽዮን ማርያም ሰበካ ጉባኤ 1.8 ሚሊዮን  ብር ወጪ የጽላተ ጽዮን ማደሪያ እድሳት ያካሂዳል፤ በሰበካ ጉባኤው ሥር የሚካሄደው እድሳት አቡነ ጳውሎስ “በተለየ ጥረትና አመራር ሰጭነት” ከሚቆጣጠሩት ሙዚዬም ግንባታ ፕሮጀክት ጋራ የሚያገናኘው ነገር የለም
  • የጽላተ ጽዮንን ማደሪያ በገንዘባቸው በማደስ ስማቸውን ለማስጠራት የመጡ ባለሀብቶች ጥያቄ ተቀባይነት አላገኘም፤ ይልቁንስ የኢትዮጵያውያን ሁሉ ጠባቂ እና መድኃኒት ለሆነችው ጽሌ-ኦሪት-ጽዮን ማደሪያ እድሳት እያንዳንዱ ምእመን የአቅሙን እገዛ እንዲያደርግ ጥሪ ተደርጓል
  •  ለተቸገሩ አብያተ ክርስቲያን የሚሰበሰበውን ርዳታ ጨምሮ የመንበረ ፓትርያርኩ የገንዘብ ምንጮች/አቅሞች በሕዳሴው ግድብ አምሳል ቅስቅሳ ወደሚደረግለት የሙዚዬም ግንባታ ፕሮጀክት እንዲዘዋወሩ ጫና በመደረጉ የጠቅላይ ቤተ ክህነቱን ሠራተኞች ኑሮ እያቃወሰው ነው፤ በአዲስ አበባ ገዳማትና አድባራት አስተዳደርና በካህናቱ መካከልም ፍጥጫ ፈጥሯል

  • የሙዚዬሙ ግንባታ ፕሮጀክት በውጭ ምንዛሬ 8.9 ሚሊዮን  ዮሮ እና 25 ሚሊዮን  ዶላር በኢትዮጵያ ገንዘብ ደግሞ ከ200 ሚሊዮን  እና ከ425 ሚሊዮን  በላይ የሚሉ የተለያዩ የወጭ መጠኖች ተነግረዋል፡፡ ይህን ወጪ መሸፈን የሁሉም ኢትዮጵያዊ “ሃይማኖታዊ እና ዜግነታዊ ግዴታ” እንደሆነ፣ “የታቦተ ጽዮን ብዜቶችና ቅጅዎች የሆኑ መላው የአብያተ ክርስቲያናት ታቦታት ዐሥራት የማውጣት ግዴታ” እንዳለባቸው ተዘግቧል
  • ·         የፕሮጀክቱ ወጪ መጠን በየጊዜው የሚቀያየረው የሙዚዬሙ ግንባታ ቅዱስ ሲኖዶስ ውሳኔ ያልሰጠበት ግለሰባዊ፣ ወቅቱን ያልጠበቀ ግብታዊ፣ በቁጥጥር አገልግሎቱ ወይም ሌላ አካል ኦዲት የማይደረግ አጠራጣሪ መሆኑ ተገልጧል
  • ፓትርያርኩ ዓለም አቀፍ የቱሪስት መዳረሻና የአርኬዎሎጂ መካን በሆነችው አኵስም ጽዮን ለሚሠራው ሙዚዬም ዓለም አቀፍ ጨረታ እንዲወጣ የቀረበላቸውን ጥያቄ ወድቅ በማድረግ ፕሮጀክቱን ለአንድ የሀገር ውስጥ ሕንፃ ሥራ ተቋራጭ ያለጨረታ በመስጠታቸው የግንባታውን ወጭ ይሸፍናል የተባለው የልዑል አክሊለ ብርሃን መኰንን ኀይለ ሥላሴ ፋውንዴሽን ድጋፍ መንፈጉን ነቅፈዋል
  • ሦስት ደርብ (ፎቅ) ያለው የሙዚዬሙ ሕንጻ ምድር ቤት አቡነ ጳውሎስ ለመካነ መቃብራቸው የሚያዘጋጁት መሆኑ እየተነገረ ነው
  • ፓትርያርኩ ሙዚዬሙን ለማሠራት ምክንያት ስለሆናቸው አጋጣሚ በኅዳር ጽዮን በዓል አከባበር ላይ የሰጡት መግለጫ በጽላተ ጽዮን ደኅንነት ላይ ጥያቄ አሥነስቷል - “. .በሌላው ክፍል ካህናት ያልሆኑ አይገቡም የሚል ሕግ ስላለ በሕግ የተሳሰረ፣ የከበረው ዕቃ ተጋርዶ እኛ ያን ያህል ለፍተን ደክመን መጥተን እዚህ እናንተ እጅ ያለውን ክብር ለምን ትሰውሩታላችሁ?. . . እዚያ ቤት የሚገቡ ቢበዛ ሁለት ሰው ነው - ገበዙ እና ገበዙን የሚረዳ ወጣት ሰው፤ ሌላ አይፈቀድለትም፡፡ ዕቃዎቹ ግን የታሪክ አሻራ ያረፈባቸው ናቸው፤ እንዳይሰረቁ ከፍተኛ እንክብካቤ ይደረግላቸዋል፡፡”
  • ባለፈው ዓመት ብቻ ፓትርያርኩ የሦስት ሙዚዬሞችን ግንባታ ዕብነ መሠረት ያስቀመጡ ሲሆን አንዱን ደግሞ መርቀዋል፡፡ በአንጻሩ የደብረ ዳሞ ገዳም ዕቃ ቤት ጠባቂ ‹በዘራፊዎች› መገደላቸውንና ቀደም ሲል የደብረ ዳሞ ይሁን የሌሎች ቅዱሳት መካናት ዕቃ ቤቶች በደረሰባቸው ‹ቃጠሎ› መጎዳታቸውን ያስታወሱ ታዛቢዎች ቅርስ ንዋያተ ቅድሳታችንን “ለጎብኚዎች እና ለተመራማሪዎች ምቹ ለማድረግ” በሚል ከያሉበት በአንድ ማእከል ተሰብስበው እንዲቀመጡ የሚደረግበት ሁኔታ በጥንቃቄ መታየት እንደሚገባው እያሳሰቡ ነው
 (ደጀ ሰላም፣ ታኅሣሥ 10/2004 ዓ.ም፤ ዲሴምበር 20/2011. READ IN PDF)፦ የርእሰ ገዳማት ወአድባራት አኵስም ጽዮን ቤተ መጻሕፍት ወመዘክር/ሙዚዬም/ን በዘመናዊ እና ዓለም አቀፍ ደረጃውን በጠበቀ መንገድ በማሠራት ከሦስት ሺሕ ዓመት የሚበልጥ ዕድሜ ያላቸውን ታሪካዊ ቅርሶች ለጉብኝት እና ምርምር ምቹ ለማድረግ በሚል የሚካሄደው እንቅስቃሴ የጠቅላይ ቤተ ክህነቱን ጽ/ቤት ካዝና እና የሠራተኞች ኑሮ፣ የአዲስ አበባ ገዳማትንና አድባራትን አቅም እየተፈታተነ መሆኑ ተገለጸ፡፡
የቤተ መጻሕፍት ወመዘክሩ ግንባታ በፓትርያርኩ ይፋ ከተደረገበት ሚያዝያ 11 ቀን 2003 ዓ.ም ጀምሮ ለፕሮጀክቱ የሚያስፈልገው ወጭ በየጊዜው እየተለዋወጠ ሲነገር ቢቆይም ጠቅላላው ገንዘብ ግን ከምእመናንና በጎ አድራጊዎች እንደሚጠየቅ ነበር የተገለጸው፡፡ ይሁንና ለግንባታው ማስጀመሪያ በሚል “ቅዱስ ሲኖዶስ እንደለገሠው” የተዘገበው 15 ሚሊዮን  ብር በፓትርያርኩ ትእዛዝ ከቁሉቢ ንዋያተ ቅድሳት ማደራጃ የባንክ ተቀማጭ በብድር የተወሰደና እስከ አሁን ተመላሽ እንዳልተደረገ ተመልክቷል፤ የቅዱስ ሲኖዶስ የጋራ ስምምነትና ውሳኔ ያላረፈበት መሆኑም ታውቋል፡፡
በየዓመቱ ታኅሣሥና ሐምሌ ወራት በርእሰ አድባራት ቁሉቢ ደ/ፀሐይ ቅዱስ ገብርኤል በሚከናወነው ክብረ በዓል በስእለትና መባዕ የሚሰጡት ንዋየ ቅድሳት በኮሚቴ ተመን ወጥቶላቸው የሚሸጡ ሲሆን በሚገኘው ገቢም ከማደራጃው በጀት ለተመደበላቸው አህጉረ ስብከት፣ ኮሌጆችና ተቋማት እንዲደርስ ይደረጋል፡፡ ሆኖም የቁሉቢ ንዋየ ቅድሳት ማደራጃ ባለፈው ዓመት ሚያዝያ ለሙዚዬሙ ግንባታ በብድር ስም ከተወሰደበት ብር 15 ሚሊዮን  በተጨማሪ ካለፈው ሳምንት ዐርብ፣ ታኅሣሥ ስምንት ቀን 2004 ዓ.ም ጀምሮ ማደራጃው ያሉት ንዋየ ቅድሳት በሙሉ በኮሚቴ እየተተመኑ ለሽያጭ መዘጋጀታቸውንና ለግንባታ ፕሮጀክቱ ተጨማሪ ገንዘብ ለማግኘት መታቀዱ ተሰምቷል፡፡
ኅዳር 13 ቀን 2004 ዓ.ም አዲስ አበባ ላይ በተቋቋመው የርእሰ ገዳማት ወአድባራት አኵስም ጽዮን ቤተ መጻሕፍት ወመዘክር የግንባታ አስተባባሪ ኮሚቴ ጽ/ቤት ስብሰባ የተጠሩት የመንበረ ፓትርያርክ ጠቅላይ ቤተ ክህነት ሠራተኞች ለሙዚዬሙ ግንባታ የአንድ ወር ደመወዛቸውን በአንድ ዓመት ከፍለው እንዲያጠናቅቁ ስምምነት ላይ ተደርሷል ቢባልም አካሄዱ “በመብታቸው ላይ ተወስኖ የመጣ እንጂ ፈቃዳቸውን ያልሰጡበት” መሆኑን በመቃወም የተናገሩ ነበሩ ተብሏል፡፡ ባለፈው ዓመት ግንቦት ወር የወር ደመወዛቸውን በዓመት ለመስጠት የጀመሩትን የታላቁ ሕዳሴ ግድብ አስተዋፅኦ በማበርከት ዜግነታዊ ግዴታቸውን በመወጣት ላይ መሆናቸውን የገለጹት ሠራተኞቹ የአኵስም ጽዮን ንብረት የሆኑ ጥንታውያን ንዋያተ ቅድሳትና ቅርሶች በአግባቡ ተጠብቀው ለትውልድ እንዲተላለፉ የሙዚዬሙ መገንባት ያለውን አስፈላጊነት ቢያምኑበትም ወቅቱን ያልጠበቀ በመሆኑ በኑሯቸው ላይ ጫናን የሚፈጥር እንደሆነ ተናግረዋል፡፡ በዕለቱ ፓትርያርኩ የስድስት ወር ደመወዛቸውን፣ አዲሱ የሰንበት ት/ቤቶች ማደራጃ መምሪያ ዋና ሓላፊ ከደመዛቸው በተጨማሪ ብር 10,000፣ በአዲሱ የሥራ ገበታቸው ለመገኘት እምቢኝ አሻፈረኝ ያሉት አባ ሰረቀም ብር 5000 እንደሚሰጡ ቃል መግባታቸው ታውቋል፡፡
በዚሁ ስብሰባ ላይ የቤተ መጻሕፍት ወመዘክሩን የሥራ ሂደት አስመልክቶ ማብራሪያ የሰጡት የግንባታው አስተባባሪ ኮሚቴ አባልና የአዲስ አበባ ሀ/ስብከት ሥራ አስኪያጅ ንቡረ እድ ኤልያስ ኣብርሃ “የተቀደሰውን ሐሳብ ጥቀርሻ ለመቀባት እንቅስቃሴ ያደርጋሉ” ያሏቸው “አንዳንድ ሰዎችና የግል ሚዲያዎች” ከድርጊታቸው እንዲታቀቡ አስጠንቅቀዋል፡፡ በጥቅምቱ ቅዱስ ሲኖዶስ ምልአተ ጉባኤ ላይ የአኵስም ቤተ መጻሕፍት ወመዘክርን ጨምሮ በአዲስ አበባ ሀ/ስብከት ያለጨረታ የሚሰጡ ግንባታዎችንና አላግባብ የሚፈጸሙ ክፍያዎችን አስመልክቶ ብፁዕ አቡነ ሳሙኤል በጉዳዩ ላይ ሊነጋገርበት እንደሚገባ የተናገሩትን በመጥቀስ የዘገቡ ጋዜጠኞችንም ንቡረእዱ “ለታሪክና ለቅርስ ደንታ ቢሶች የሆኑ፣ ሕዝቡን ለማደናገር የሚንቀሳቀሱ” በማለት ዘልፈዋቸዋል፡፡ 
የአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት ሥራ አስኪያጅነትን ከጠቅላይ ቤተ ክህነቱ ምክትል ሥራ አስኪያጅነት ጋራ ደርበው የያዙት ንቡረ እዱ እንዲህ ይበሉ እንጂ እውነቱ ግን ከአዲስ አበባ ገዳማትና አድባራት ተሰብስቦ ለተቸገሩ የገጠር አብያተ ክርስቲያን የሚከፋፈለው ገንዘብ እና ንዋያተ ቅድሳት ቢያንስ ለመጪዎቹ ስድስት ወራት ለአኵስም ሙዚዬም ግንባታ እንዲውል ሓላፊነት የጎደለው ውሳኔ መተላለፉ ነው፡፡ በ2003 ዓ.ም የበጀት ዓመት የተቸገሩ አብያተ ክርስቲያን ርዳታ አሰባሳቢ ኮሚቴው ብር 3,467,185.16 ከአዲስ አበባ አድባራትና ገዳማት የሰበሰበ ሲሆን ከዚህም ውስጥ ብር 21,000 አከፋፍሏል፤ በ48ቱም አህጉረ ስብከት ለሚገኙ የተመረጡ የገጠር አብያተ ክርስቲያን ንዋያተ ቅድሳትን ሰጥቷል፡፡
በአሁኑ ወቅት በአዲስ አበባ ሀ/ስብከት በሚገኙ ከ19 ያላነሱ አጥቢያዎች እየተደረገ በሚገኘው የአስተዳዳሪዎች ዝውውር ጋራ በተያያዘ ደርቶ በሚታየው የጥቅም አቀባይና አቀባባይ ኔትወርክ የቀደሙትን ሥራ አስኪያጅ መልካም ውጤቶች ወደ ኋላ የመመለስ አዝማሚያ የታየባቸው ንቡረ እዱ ሌሎችን በአደናጋሪነት ይክሰሱ እንጂ ሐቁ፣ ለሙዚዬሙ ግንባታ በሚል በሁሉም የሀገረ ስብከቱ አጥቢያዎች ከተቀመጠው የሙዳዬ ምጽዋት ሣጥን በተጨማሪ እያንዳንዱ አጥቢያ ካለው ልዩ ገቢ ከብር 75,000 ያላነሰ እንዲያዋጣ በተጣለው ልዩ ተመን የተነሣ ጥቂት የማይባሉት ለሠራተኞቻቸው እና ለአገልጋዮቻቸው ስለሚከፍሉት ደመወዝ ጭንቅ ጥብብ እንዳላቸው ነው፡፡
በሁሉም አጥቢያዎች ከተቀመጡት አንድ አንድ እና ከዚያም በላይ የሙዳዬ ምጽዋት ሣጥኖች ብቻ እስከ አሁን ድረስ ከግማሽ ሚሊዮን  ብር (800,000.00) በላይ መሰብሰቡ ሳይበቃ፣ እያንዳንዱ አጥቢያ በወር በዓል ቀን የሚያስገባውን ማንኛውም ገቢ ለሙዚዬሙ ግንባታ ፕሮጀክት በሚል በአስተባባሪ ኮሚቴው አባላት ተገልብጦ ይወሰድበታል፡፡ ይህን ለመፈጸም ይቸግረናል ባሉ አንዳንድ አጥቢያዎች ላይ የኮሚቴው አባላት በአለቆች እና ጸሐፊዎች ላይ በሚፈጥሩት ጫና የተነሣ አስተዳዳሪዎችና ጸሐፊዎች ከሚያስተዳድሯቸው ካህናትና ሠራተኞች ጋራ ፍጥጫ ውስጥ ገብተዋል፡፡ እንደ ደብረ አሚን ጻድቁ አቡነ ተክለ ሃይማኖት እና ደብረ ጽጌ ቅዱስ ጊዮርጊስ ያሉት አድባራትም በአንድ ጊዜ እስከ ብር 200,000 ከቋታቸው ወጪ አድርገው በመስጠት ከመዋጮ ቀንበር እንደተገላገሉ ቆጥረውታል፡፡ እውነታው ግን ይኸው ጉዳይ የቤተ መጻሕፍት ወመዘክሩ ግንባታ ፕሮጀክት እስከሚጠናቀቅበት ሁለትና ሦስት ዓመት የሚቀጥል መሆኑ ነው፡፡     
በኅዳር ወር ታትሞ የወጣው ዜና ቤተ ክርስቲያን ጋዜጣ “ለአኵስም ጽዮን ያልተዘረጉ እጆች ለማን ይዘረጋሉ?” በሚል ርእስ ባሰፈረው ርእሰ አንቀጽ፣ “በመላው ኢትዮጵያ የሚገኙት አብያተ ክርስቲያናት መሥዋዕተ ሐዲስ የሚሠዋባቸው ታቦታት ሁሉ መሥዋዕተ ኦሪት ይሠዋባት ከነበረችውና ዛሬም መሥዋዕተ ሐዲስ እየተሠዋባት ያለችው በርእሰ አድባራት ወገዳማት አኵስም ጽዮን የምትገኘው የታቦተ ጽዮን ቅጅና ብዜቶች ናቸው፡፡ ይህም ከሆነ ዘንድ የመላ ኢትዮጵያ አብያተ ክርስቲያናት ታቦታት ለታቦተ ጽዮን ዐሥራት ማውጣት ግዴታቸው ነው”  በማለት ለንቡረ እዱ ርምጃ አጽድቆት ሰጥቷል፡፡ እውነታው ግን መዋጮው ከዐሥራት ላይ መሆኑ፣ ቅደም ተከተሉን ያልጠበቀ እና በቂ የማሳመን ሥራ ያልተሠራበት መሆኑ ነው፡፡
ፕሮጀክቱ የፓትርያርኩ ልዩ ጥረት እየተደረገበት እና ቀጥተኛ አመራር እየተሰጠበት መሆኑን ያስታወቀው ርእሰ አንቀጹ፣ አኵስም ለኢትዮጵያ የእምነቷና የሥልጣኔዋ መሠረት፣ የመንፈሳዊውና የዓለማዊው ጉዳይ ሁሉ መገኛ መሆኗን አስታውሶ ጥንታውያን ቅርሶቿም የኢትዮጵያ ጥንተ ሥልጣኔ ምን ደረጃ ላይ ደርሶ እንደነበር እንደሚያመለክተን አብራርቷል፡፡ ከእነዚህ ዕፁብ ድንቅ ቅርሶች መካከል አብዛኞቹን ዩኔስኮ በዓለም ቅርስነት የመዘገባቸው ሲሆን ከመላው ዓለም ቅርሶቹን ለመጎብኘት ወደ ከተማዋ የሚጎርፈው ቱሪስትና ተመራማሪ ብዛት በእጅጉ በርካታ መሆኑን አትቷል፡፡ ከቅርሶቹ በተጨማሪ በአኵስም ከአንድ ሺሕ በላይ ልዩ ልዩ በወርቅ የተለበጡ የብራና መጻሕፍት፣ የወርቅና የብር መስቀሎች፣ ከወርቅና ብር የተሠሩ የጥንታዊ ነገሥታት ዘውዶች፣ አልባሳትና ኮርቻዎች ሌሎችም ድንቃድንቅ ቅርሶች ለደኅንነታቸው እጅግ አስጊና አሳሳቢ በሆነ ሁኔታ ተቀምጠው እንደሚገኙ ጋዜጣው ዘርዝሯል፡፡
“ስለሆነም ዘመናዊ፣ ለጎብኚዎችና ለተመራማሪዎች ምቹ የሆነ ሙዚዬም በጥንታዊቷ አኵስም ጽዮን ቤተ ክርስቲያን በመገንባት ቅርሷችን ከብልሽትና ከብክነት ከመታደግ ባሻገር ታሪክ ተመራማሪዎች፣ ጎብኚዎችና ተማሪዎች በቅርሶቹ ዙሪያ በቂ መረጃ የሚያገኙበትን መንገድ መፍጠር ይቻላል” የሚለውን ሐሳብ “በግንባር ቀደምነት፣ ፍጹም በሆነ የሓላፊነት ስሜት በመምራትና የተለየ ተግባር የሚያከናውን ጠንካራ ኮሚቴ በማዋቀር ሥራው የሚቀላጠፍበትን መንገድ ቀይሰዋል፤ የተቋቋሙት ኮሚቴዎችም በተቋቋሙበት ዘርፍ ሥራዎቻቸውን በሓላፊነት ስሜት በማከናወን ላይ ናቸው”  ብሏል፡፡
አያይዞም “ለኢትዮጵያና ለኢትዮጵያውያን ኵራት በሆነችው አኵስም ጽዮን ደረጃውን የጠበቀ ቤተ መጻሕፍት ወመዘክር መገንባት ግድ በመሆኑ ከ25 ሚሊዮን  የአሜሪካ ዶላር በላይ ወጪ የሕንፃ ሥራው በከተማዋ የተመረጠና ምቹ ሥፍራ በመጣደፍ ላይ መሆኑን፣ ሥራውም ከሁለት እስከ ሦስት ዓመታትን ይወስዳል ተብሎ እንደሚገመት” አመልክቷል፡፡ ፕሮጀክቱ የሚጠይቀው ወጪ የቤተ ክርስቲያንን አቅም በእጅጉ የሚፈታተን እንደሆነ ያልሸሸገው ርእሰ አንቀጹ ቅርሶቹ የሀገር ሀብቶች መሆናቸውን ከግምት በማስገባት፣ “ሁሉም ኢትዮጵያዊ ዜጋ ለዓባይ ግድብ መዋጮ በነፍስ ወከፍ ካደረገው ርብርብ ባልተናነሰ መልኩ ለአኵስም ጽዮን ሙዚዬም ግንባታ መዋጮም ሊረባረብ ይገባዋል፤ የዓባይ ግድብ የሥጋችን ብርሃን እንደሆነ ሁሉ ታቦተ ጽዮንም የነፍሳችን ብርሃን ናትና” ሲል ተማፅኗል፡፡
ሌሎች በጋዜጣው የተስተናገዱ ጽሑፎችም ይህንኑ ጉዳይ በተለያዩ አገላለጾች በማጎላመስ ፕሮጀክቱ ለጎብኚዎችና ተመራማሪዎች በቂ መረጃ በመስጠት ቁጥራቸውን በዕጥፍ እንደሚጨምረው፣ ይህም የሀገር ልማትንና የገጽታ ግንባታውን “እንደሚያሳልጠው” አስረድተዋል፡፡ ከዚህም የተነሣ እንቅስቃሴውን መደገፍ ሃይማኖታዊ ብቻ ሳይሆን ዜግነታዊ ግዴታም ጭምር መሆኑን፣ ስለዚህም ከባህልና ቱሪዝም ሚኒስቴር ጀምሮ መገናኛ ብዙኀን በአጠቃላይ የድርሻቸውን በመወጣት የሥልጣኔ ቁንጮ የነበረችውን አኵስምን “የዘመናዊ ቤተ መጻሕፍት ወመዘክር መገኛ እናድርጋት” በማለት አሳስበዋል፡፡
ዐፄ ፋሲል በ1627 ዓ.ም ባሠሩት ሕንፃ ቤተ ክርስቲያንና ዐፄ ኀይለ ሥላሴ በ1957 ዓ.ም ካሠሩትና በመጠኑ ሰፋ ካለው የአኵስም ጽዮን ሕንፃ ቤተ ክርስቲያን በስተጀርባ ሰሜናዊ ምሥራቅ አቅጣጫ የሚገነባው ቤተ መጻሕፍት ወመዘክር /ሙዚዬም/ በ4975 ካሬ ሜትር ስፋት ያለው ሲሆን ሦስት ደርቦች /ፎቆች/ ይኖሩታል፡፡ የሕንፃው ዐቅድ በግሪክ የሕንፃ ባለሞያዎች የተሠራ፣ ዘመኑ የሚጠይቀው የቴክኖሎጂ ግብአቶች ሁሉ የተሟሉለትና የሕንፃው የላይኛው ክፍል የአኵስም ሐውልቶች ከተጠረቡበት ድንጋይ የሚሠራ ከመሆኑም በላይ በውስጡ የሚቀመጡትን ቅርሶች በዘመናዊ መልኩ ለመጠበቅ እና ለመከባከብ የሚያገለግል የኤክትሮኒክስ መሣሪያ ይገጠምለታል ተብሏል፡፡ የዚሁ መካኒካል እና ኤሌክትሪካል መሣሪያ ወጭም የሕንፃው ግንባታ ከሚወስደው ገንዘብ በላይ እንደሆነዜና ቤተ ክርስቲያን ጋዜጣ ተዘግቧል፡፡
ኅዳር 21 ቀን 2004 ዓ.ም በተከበረው የኅዳር ጽዮን በዓል ላይ ብፁዕ ወቅዱስ ፓትርያርክ አቡነ ጳውሎስ ባስተላለፉት መልእክት፣ “ሥራውን በራሳችን አቅም እንጀምራለን ብለን አጠቃላይ ጥናቱን ጨርሰን ወደ ቁፋሮ ከገባን በኋላ ገንዘብ አጠረንና ቆምን፤ ለሥራው 200 ሚሊዮን  ብር ያስፈልጋል ተባልኩ፤. . .የአዲስ አበባ ሀገረ ስብከትና ከጠቅላይ ቤተ ክህነት ደመወዛቸውን እንዲሰጡ አድርጌያለሁ፡፡ እኔ እዚህ ስለምን በዚህ ሰዓት ደግሞ ምርጥ ምርጥ ለማኞች በአገሪቷ እየተዘዋወሩ እንዲለምኑ አድርጌ ነው የመጣሁት” በማለት የምእመናኑን አስቸኳይ ድጋፍ እንደሚሹ ተናግረዋል፡፡ ሙዚዬሙ የሚሠራበት ዓላማም “የእግዚአብሔር አገልጋዮች እንዲያገለግሉበት፣ እንዲጠቀሙበት፤ ዐዋቂዎቹ የወላጆቻቸውን አሻራ እያዩ እግዚአብሔርን እንዲያመሰግኑ፣ ወጣቱ በዕውቀት ጎዳና የመራመድ ዕድል እንዲያጋጥመው ነው”  መሆኑን አስረድተዋል፡፡
ፓትርያርኩ የፕሮጀክቱን መጀመር ይፋ ካደረጉበት ጊዜ ጀምሮ ለግንባታው የሚፈለገው ወጭ በተለያየ አኀዛዊ መጠን እየተገለጸ ነው፡፡ አቡነ ጳውሎስ በክብረ በዓል ንግግራቸው “200 ሚሊዮን  ብር ያስፈልጋል ተባልኩ” ካሉት ጋራ በሚቀራረብ አኳኋን ስለ አኵስም ጽዮን ውሏቸው የዘገበው የኢትዮጵያ ቴሌቪዥን የፕሮጀክቱ ወጪ 8.9 ሚሊዮን  ዩሮ እንደሆነ ሲዘግብ፣ ማዕርግ ካህሱ የተባሉ የፕሮጀክቱን አስተባባሪ የጠቀሰው የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት ድረ ገጽ በበኩሉ ሥራው ከ100 ሚሊዮን  ብር በላይ በሆነ ወጭ በመካሄድ ላይ እንደሆነ ዘግቧል፡፡ ዜና ቤተ ክርስቲያን ጋዜጣ በኅዳር ወር እትም ርእሰ አንቀጹ ግንባታው ከ25 ሚሊዮን  የአሜሪካ ዶላር በላይ ወጭ እንደሚጠይቅ ሲያመለክት፣ በዚሁ እትም የወጣ ሌላ ጽሑፍ ደግሞ ሙዚዬሙን ገንብቶ ለማጠናቀቅ ይፈጃል ተብሎ የተገመተው ከብር 425 ሚሊዮን  ብር በላይ መሆኑን ያሳያል፡፡
እኒህ አኀዞች የግንባታ አስተባባሪ ኮሚቴው ጽ/ቤት አባላት በየመድረኩ ከተናገሩት ወጪ ጋራ “በላይ” በሚለው ግምታዊ ቃል ይታረቁ ካልሆነ በቀር ስለ ፕሮጀክቱ ግልጽነት ጥያቄዎችን ማሥነሳቱ አልቀረም፡፡ አንዳንዶች ገንዘቡ አሁን በተጠቀሰበት መጠንና በግሽበቱ ሳቢያ እየጨመረ የሚሄደውን የግንባታ ዋጋ ንረት በማየት “ማለቂያ የሌለው ፕሮጀክት ነው” ሲሉ ሌሎችም ፓትርያርኩ የጠቅላይ ቤተ ክህነቱን ሠራተኞችና አገልጋዮች ክፉኛ በማስጨነቅ ሥራውን በራሳቸው “ልዩ ጥረትና አመራር” የሚቆጣጠሩበት ምክንያት “በግንቦቱ የርክበ ካህናት ቅዱስ ሲኖዶስ ምልአተ ጉባኤ ላይ መካነ መቃብራቸው በቤተ መጻሕፍት ወመዘክሩ (ሙዚዬሙ) ይሆን ዘንድ ለማስወሰን” እንደሆነ አስተያየታቸውን ሰጥተዋል፡፡
የአንዳንዶቹ ትችት የሚነሣው ደግሞ የቤተ መጻሕፍት ወመዘክሩ ግንባታ አሁን ሥራውን በሓላፊነት ለያዘው ተኽለ ብርሃን እምባዬ ሕንፃ ተቋራጭ ያለጨረታ ከተሰጠበት ግልጽነት የሚጎድለው አካሄድ ነው፡፡ በጠቅላይ ቤተ ክህነቱ ለሚሠሩ የግንባታ እና እድሳት ተግባራት ፈቃድ የሚሰጡ፣ ዲዛየን የሚሠሩና ግንባታ የሚያስጀምሩ የዕቅድና ልማት መምሪያ እንዲሁም የምሕንድስና ዘርፍ አገልግሎት ያሉ ሲሆን በአኵስሙ ቤተ መጻሕፍት ወመዘክር ፕሮጀክት የእነዚህ አካላት መዋቅራዊ ተሳትፎ ምን እንደሆነ ግልጽ አይደለም፡፡ ሁለት ነገሮች ግን ግልጽ ናቸው፡፡ የመጀመሪያው ባለአንድ ግለሰብ አመራር የሆነው የምሕንድስናው ዘርፍ ለፓትርያርኩ ማንኛውም ትእዛዝ ኦሆ ባይ የሆኑ፣ በሙሰኛ/ብልሹ ምግባራቸው የተነሣ በመንግሥት ሞያዊ እገዳ ተጥሎባቸው የነበሩ፣ ከሕንፃ ሥራ ተቋራጮች ጋራ እየተመሳጠሩ ሕገ ወጥ ክፍያዎችን እንዲፈጸም በማዘዝ (ባለፈው ሳምንት በድሬዳዋ ሳባ ደብረ ኀይል ቅዱስ ገብርኤል እንዳደረጉት) ጥቅም የሚካፈሉ መሆናቸው ነው፡፡
ሌላው ደግሞ የሙዚዬሙን የመሥራት ዕቅድ እንዳለ በአቡነ ጳውሎስ የተነገራቸው የዐፄ ኀይለ ሥላሴ የልጅ ልጅ ልዑል አክሊለ ብርሃን መኰንን፣ ወጪውን በፋውንዴሽናቸው በኩል በመሸፈን አያታቸውን እቴጌ መነን የሠሩትን ታላቅ ሥራ እንደሚያድሱ ከሦስት ዓመት በፊት በገቡት ቃል መሠረት ለፕሮጀክቱ ዓለም አቀፍ ጨረታ እንዲወጣ ለፓትርያርኩ ላቀረቡት ጥያቄ ተሰጥቷቸዋል የተባለው መልስ ነው ተብሏል፡፡ ፋውንዴሽናቸው ፕሮጀክቱን ሊረዳ የሚችለው ዓለም አቀፍ ጨረታ ሲወጣ እንደሆነ ልዑሉ አቅርበውት ነበር ለተባለው ጥያቄ “ስለ እርሱ ምን አግብቷቸው፤ የሚሰጡትን ይስጡ” የሚል መልስ ከምሕንድስናው ዘርፍ በመሰጠቱ የርዳታ ዕቅዱ መሰረዙ ተነግሯል፡፡
አቡነ ጳውሎስ በኅዳር ጽዮን በዓል አከባበር ላይ ስለዚህ ጉዳይ ሲያስረዱ የተናገሩት ግን “በዓለም የኢኮኖሚ ቀውስ የተነሣ የልዑሉ ፋውንዴሽን ገጥሞታል” የተባለውን ችግር የሚያጣቅስ፣ የተገባው ቃል ያለ መጠበቁን ጫናም ወደ ልዑሉ የሚያዞር ነው፤ እንዲህ ሲሉ፡-
“. . . በመሀከሉ ደግሞ ለጽዮን አገለግላለሁ ያሉ አንድ ወንድማችን መጡ፡፡ ሕዝባችን በእግዚአብሔር ስም ሲጠይቁት ዐይኑን አያሽም፡፡ እሺ ብሎ ዕድሉን ለልጃችን ሰጠ፡፡ በዚህ ዓለም ግን ሁልጊዜ ነገር እንዳስቀመጡት አይኖርም፡፡ እርሳቸው ወንድማችን ከመጡበት አገር በሌላውም አገር እንደሚገኝ ያለ ዕንቅፋት ስላጋጠማቸው ያ የተባለውን ገንዘብ ማንቀሳቀስ ስላልተቻለ ዝም ብለን ሦስት ዓመት ያህል አባከንን፤ አምነን በእግዚአብሔር ስም በጽላተ ሙሴ ስም ነው የጠየቅን፡፡ አሁንም አልካዱም፤ ጨርሶ አልሄዱም፤ ግን ያጠራቀሙት ገንዘብ ሊለቀቅላቸው ባለመቻሉ ይህን ጉዳይ በወቅቱ በጊዜው መሥራት አልቻልንም፡፡ የምንሠራው ሥራ ወላጆቻችን እንዳደረጉት የጀመሩትን ሠርተው፣ መርቀው፣ ተጠቅመውበት ለልጆቻቸውም አደራ ብለው ነው የሄዱት፡፡ እኛም ከወላጆቻችን የተለየ ጠባይ ሊኖረን አይገባም፡፡ እንሠራለን እያሉ መኖር መሥራት አይደለም፤ ማፌዝ ነው፡፡
ቤተ ክርስቲያን ውስጥ ከሚካሄዱ ግንባታዎች ጋራ ዘወትር የሚነሣው የሙስናው እና የብኩንነት ነገርም ምልክቱ መታየቱ አልቀረም፡፡ ለአብነት ያህል አቡነ ጳውሎስ የሙዚዬሙ ግንባታ አሁን ከመሠረቱ ወጥቶ ግራውንድ ቢኖች በታሠሩበት ደረጃ እስከ 35 ሚሊዮን  ብር ክፍያ ቢፈጸምም በቂ ሆኖ እንዳልተገኘ መናገራቸው ለጽዮን በዓል በስፍራው ተገኝተው ሂደቱን የታዘቡ ተመልካቾችን አላሳመነም፡፡ ታዛቢዎቹ በተጠቀሰው ወጪ መጠን ከዚያም በላይ የሆነውን የግንባታውን ክፍል ማከናወን እንደሚቻል ነው የሚናገሩት፡፡
ብኩንነትን በሚመለከት በቀላሉ ለማስረዳት ያህል ፓትርያርኩ ከብፁዓን አባቶችና ከአጃቢዎች ጋራ ለጽዮን በዓል አከባበር ወደ አኵስም ያቀኑት በአየር ሲሆን ከእርሳቸው ጉዞ ቀደም ሲል አቀባበሉን ያሣምራሉ፤ ገቢ ያሰባስባሉ የተባሉ በርከት ያሉ ልኡካን ከጠቅላይ ቤተ ክህነቱ በሰባት መኪኖች/በየብስ/ ተጓጉዘው አኵስም ገብተው ነበር፡፡ በአጠቃላይ ከእርሳቸው ጋራ ከሃያ ያላነሱ ልኡካን የነበሩ ሲሆን ነዳጅ እና አበልን ጨምሮ የስምሪቱ ወጪ ከብር 150,000 እንደማያንስ ነው የተነገረው፡፡ አሳዛኙ ነገር በበዓሉ ዋዜማና ዕለት ለሙዚዬሙ በተደረገው ቅስቀሳ የተገኘው ጠቅላላ አስተዋፅኦ ከብር 46,000 ያልበለጠ መሆኑ ነው፡፡ “እርሳቸው ሲጓጓዙ ብቻ ብሩ ያልቃል፤ ሲበላ ሲጠጣ ርኅራኄ የለም” ብለዋል የአንድ መምሪያ ባልደረባ፡፡
ከበዓሉ አምስት ቀን ቀደም ብሎ ኅዳር 16 ቀን 2004 ዓ.ም በመንበረ ፓትርያርኩ የዓለም አብያተ ክርስቲያን ም/ቤት አዳራሽ በተካሄደውና የቤተ መጻሕፍት ወመዘክሩ ግንባታ አስተባባሪ ኮሚቴ ጽ/ቤት የከተማውን ባለሀብቶች በጠራበት ስብሰባ የተገኙት ከ30 የማይበልጡ ናቸው፡፡ ከተነገሩት በርካታ ንግግሮችና ከቀረቡት ሪፖርቶች አኳያ በቃል ኪዳን የተገኘው ገንዘብ የተጠበቀውን ያህል አለመሆኑ ፓትርያርኩን ቢያሳዝንም ባለሀብቶቹ ግን በሚገባ በሚረዱት የቤተ ክህነቱ ብኩንነት የተነሣ በመዋጮ ጥያቄ መማረራቸው ተዘግቧል፡፡
ሌሎች ጥቂቶች ደግሞ የሙዚዬሙ ወጪ ከፍተኛነትና በአብዛኛው በውጭ ምንዛሬ ከመገለጹ ጋራ ተያይዞ በገንዘቡ ምንጭና በተነገረው የፕሮጀክቱ ዓላማ ሐቀኝነት ላይ ያላቸውን ጥርጣሬ ሲገልጹ ተደምጠዋል፡፡ አቡነ ጳውሎስ በጽዮን ክብረ በዓል ወቅት ለቤተ መጻሕፍት ወመዘክሩ መሠራት ምክንያት የሆናቸውን አጋጣሚ የተናገሩበት መንገድ አሻሚነትም ከጠርጣራዎቹ ጥርጣሬ ጋራ የሚመጋገብ ሆኗል፡፡ ይኸውም በአንድ በኩል በፓትርያርኩ ንግግር ውስጥ በቤተ ክርስቲያን ሦስት ጾታዎች - ካህናት፣ ወንዶች እና ሴቶች መኖራቸው፣ እንደየጾታቸውም ሥርዐት የተሠራበት ሁኔታ “በሕግ መታሰር ነው” የሚያሰኝ ድምፅ መኖሩ ነው፡፡ በ17ው መ.ክ.ዘ ዐፄ ፋሲል ባሠሩት የአኵስም ጽዮን ቤተ ክርስቲያን ወንዶች ምእመናን የሚገቡበት ለሴቶች ምእመናት ያልተፈቀደ፣ ካህናት ብቻ የሚገቡበት ለወንዶችም ለሴቶችም ምእመናን የተከለከለ ክፍል መኖሩ “ክቡሩን ዕቃ መጋረድ ተደርጎ” በመወሰዱ ነው፡፡
አቡነ ጳውሎስ ይህን ያጣቀሱት እርሳቸው ለተልእኮ ሲፋጠኑ ከውጭ አገር መጥተው ያገኟቸው ሴቶች ናቸው፤ እንዲህም ብለዋቸዋል፡-
“. . .ለተልእኮ ስፋጠን ከውጭ አገር የመጡ ሁለት ሴቶች እኅቶቻችን አገኙኝ፤ ባሕር ተሻግረን፣ አገር አቋርጠን፣ በሰማይ በርረን፣ በባሕር ተንሳፈን፣ በእግራችን ተሯሩጠን ከዚህ መጥተናል፡፡ የሚታይ የከበረ፣ የተቀደሰ፣ ከጥንት ጀምሮ የመጣ ብርቅና ድንቅ የሆኑ የተቀደሱ ሥርዐትና ቅርሶች ስላሉን ለማየት ነው የመጣን፤ እዚህ ከመጣን በኋላ አንድ፣ ሁለት፣ ሦስት፣ አራት፣ አምስት ነገሮች ብቻ አውጥተው ከሚያሳዩን ለማየት የመጣነውን ሳናይ ተመልሰን እንሄዳለን፡፡ እነዚህ ጥቂቶችም ቢሆኑ ካሉበት ቦታ ላይ ገብተን ለማየት እንዳንችል ሕገ ቤተ ክርስቲያኑ ይከለክላል፤ በሌላው ክፍል ካህናት ያልሆኑ አይገቡም የሚል ሕግ ስላለ በሕግ የተሳሰረ፣ የከበረው ዕቃ ተጋርዶ እኛ ያን ያህል ለፍተን ደክመን መጥተን እዚህ እናንተ እጅ ያለውን ክብር ለምን ትሰውሩታላችሁ?”
ይኸው የአጋጣሚ ንግግር “ክቡሩን ዕቃ ተስማምተን፣ ተከባብረን፣ ቆጥረን፣ ዐውቀን ዘመኑ የሚፈቅደውን የሚታይበትን ቦታ እንሥራ” ወደ ማለት እንዳመጣቸው፣ የብልህ ብልህ የሆኑት አባቶቻችን ታሪክ መሥራት ብቻ ሳይሆን ሠርቶ ያገለገለን ዕቃ የሚያስቀምጡበት ዕቃ ግምጃ ቤት በመላዋ ኢትዮጵያ እንደ ሠሩ ብፁዕ ወቅዱስ ፓትርያርኩ አስረድተዋል፡፡
ይህ እንዳለ ሆኖ አቡነ ጳውሎስ በማስከተል የተናገሩት ቃል ሰሞኑን መነጋገሪያ ስለሆነው የጽላተ ጽዮን ደኅንነት ስጋትን አጭሮ ነበር ከተባለው የ2001 ዓ.ም የጣልያን ጉብኝታቸው ወቅት ለኢጣልያ የዜና ወኪል ንግግራቸው ጋራ የተያያዘ ሆኗል፡፡ የዜና ወኪሉ “ዓለም የቃል ኪዳኑን ታቦት የሚያይበት ጊዜ ስለ መድረሱ አቡነ ጳውሎስ ማስታወቃቸውን” መሠረት በማድረግ የሺሕ ዘመናት ምሥጢር ሊገለጽ መሆኑን ዘግቦ ነበር፡፡ ይህ ዘገባ ሙሉ በሙሉ የተሳሳተ እንደነበር በወቅቱ ማስተባበያ የተሰጠበት ሲሆን በጽዮን በዓል ዕለት ፓትርያርኩ የሙዚዬሙን መገንባት አስፈላጊነት ካስረዱበት ሁኔታም ጋራ ተያይዞ ዳግመኛ መቀስቀሱ አልቀረም፡፡
ደጀ ሰላም የደረሰው የብፁዕ ወቅዱስ ፓትርያርኩ ንግግር የዕቃ ቤቱ ጠባቂ አንድ መሆናቸውንና ከረዳታቸው በቀር ሌላ ሰው ወደ ዕቃ ቤቱ ለመግባት ያልተፈቀደለት መሆኑን፣ በዚህም የተነሣ ታሪካዊ ቅርሶች በዕቃ ቤቱ መጥበብና በአያያዝ ጉድለት ሳቢያ መበላሸታቸውን፣ ይህም የሙዚዬሙን መሠራት የግድ እንዳደረገው ያብራሩበት ነው፡-  
“እዚያ ቤት የሚገቡ ቢበዛ ሁለት ሰው ነው፤ ገበዙ እና ገበዙን የሚረዳ ወጣት ሰው፤ ሌላ አይፈቀድለትም፤ ዕቃዎቹ ግን የታሪክ አሻራ ያረፈባቸው ናቸው፤ እንዳይሰረቁ ከፍተኛ እንክብካቤ ይደረግላቸዋል፡፡ ዕቃ ቤቱ ጨለማ ነው፤ ጠባብ ነው፤ የተገኘውን ዕቃ ወደዚያ ከመከመር በስተቀር ለዕቃው አግባብ ያለው አቀማመጥ አይቀመጥም፡፡ ይህን ሁሉ በመገንዘብ የአኵስም ሊቃውንት ታላላቅ አባቶች፣ ካህናትና የመንግሥትም አባላት ባሉበት ጉዳዩ እንዲቆጠር ተደረገ፡፡ ከዚያ በኋላ ወደ ሙዚዬሙ ነው የሚያዘነብለው ያለ፤ አስፈላጊውን ዘመኑ የሚፈቅደውን ሥራ እንዲሠራ ተወሰነ፡፡”
ይህን መሠረት አድርጎ የተቀሰቀሰው ስጋት ሙሉ በሙሉ አግባብ ነው ለማለት አይቻልም፡፡ ለዕቃ ቤቱ ገበዝ እና ረዳት እንዳላቸው ሁሉ በ1957 ዓ.ም እቴጌ መነን ባሠሩት የጽላተ ጽዮን ማደሪያ የምትገኘውን ጽላተ ጽዮንንም በገሃድ የሚጠብቁ መነኮስ አባት (አሁን ያሉት አባ ገብረ መስቀል ይባላሉ) እና በኅቡእ የሚከታተሉ የጽዮን ጠባቂዎች ማኅበር አባላት እንዳሉ ይታወቃል፡፡ ለደጀ ሰላም አስተያየታቸውን የሰጡ የከተማው ነዋሪዎች እንደገለጹት ለወሬው ሚዛን እንደማይሰጡትና ይልቁንም አሁን ያሉትን የጽላተ ጽዮን ጠባቂ ሰለባ ለማድረግ ያለመ ስለመሆኑ ጥርጣሬ እንዳላቸው ተናግረዋል፡፡ “ያም አለ ይህም አለ ወሬው ጽላተ ጽዮን ፈቅዳ በመጣችበት ኢትዮጵያ ዛሬም መኖሯን ከማረጋገጥ በቀር ያለ እግዚአብሔር ፈቃድ ለማንም በዋዛ የምትጨበጥ፣ የምትዳሰስ እንዳልሆነች ቅዱስ መጽሐፍ ያረጋግጣል”  ብለዋል አስተያየት ሰጪዎቹ፡፡
ይልቁንስ አስተያየት ሰጭዎቹን የሚያሳስባቸው ካለፈው ዓመት ክረምት መግቢያ ጀምሮ ጣሪያዋ የዝናም ውኃ በከፍተኛ ደረጃ በማፍሰሱ የተነሣ በኬንዳ (ሸራ) ስለተሸፈነው የጽላተ ጽዮን ማደሪያ በጉልሕ የተናገሩት አንቀጽ አለመኖሩ ነው - ቅዱስነታቸውን ያሳሰባቸው የሙዝዬሙ ግንባታ ፕሮጀክት ነውና፡፡ እንዲያውም ለሙዚዬሙ የተካሄደው ቁፋሮ ሥራ በጅምሩ በመጓተቱ በ1957 ዓ.ም ግርማዊ ቀዳማዊ ንጉሠ ነገሥት ዐፄ ኀይለ ሥላሴ ያሠሩት ወንዶችም ሴቶችም የሚገቡበት ሕንፃ ቤተ ክርስቲያን መሠረቱን ጎርፍ እየሸረሸረው መሆኑን በማስመልከት ለተቆፋፈረው ጉድጓድ መፍትሔ እንዲበጅለት የአኵስም ጽዮን ነዋሪዎችና የከተማው ባለሥልጣናት ተመራርጠው ወደ እርሳቸው ለአቤቱታ የመጡበትን ሁኔታ መውቀሻ አድርገውታል - ቅዱስነታቸውን ያሳሰባቸው ፕሮጀክቱን ማስፈጸሚያ ገንዘብ እንደ ልብ አለማግኘታቸው ነውና፡፡
በአሁኑ ወቅት የርእሰ ገዳማት ወአድባራት አኵስም ጽዮን ማርያም ቤተ ክርስቲያን ሰበካ ጉባኤ እና የከተማው ሕዝብ ሸራ (ኬንዳ) ለብሳ የምትገኘውን የጽላተ ጽዮን ማደሪያ ጣሪያ በ1.8 ሚሊዮን  ብር ወጪ ለማደስ እንቅስቃሴ እያደረገ መሆኑ ታውቋል፡፡ በአሁኑ ወቅትም የዋናው ማደሪያ እድሳት ከመጀመሩ በፊት ጽላተ ጽዮን ከነበረችበት ወጥታ የምትቆይበት ሌላ ማደሪያ በአቅራቢያው እየተሠራ መሆኑንና የከተማው ነዋሪም ለዚሁ ወሳኝ ተግባር ቅድሚያ በመስጠት እየተረባረበ መሆኑ ተገልጧል፡፡ አንድ የቤተ ክርስቲያኑ አገልጋይ በስም የጠቀሷቸው ሁለት ባለሀብቶች የጽላተ ጽዮን ማደሪያ እድሳትን በገንዘባቸው ጨርሰው መታሰቢያቸውን ለራሳቸው ለማድረግ ጥያቄ አቅርበው የነበረ ቢሆንም ተቀባይነት እንዳላገኙ ተናግረዋል፡፡
“የጽላተ ጽዮን ማደሪያንና የጽዮን ማርያም ቤተ ክርስቲያን ያሠሩት ደጋግ ነገሥታትና ንግሥት ስም/መታሰቢያ መጥፋት አይገባውም” የሚል አቋም የያዘው አስተዳደሩ “ጽዮን እናታችን” የሚሉ የጽዮን ወዳጆች የሆኑ ሁሉም ኢትዮጵያውያን ተጨንቀው ከሚያወጡት ከእያንዳንዳቸው አስተዋፅኦ ሥራውን መጨረስ እንደሚሻ ተመልክቷል፤ ስለሆነም ሁሉም ኢትዮጵያዊ የበኩሉን እገዛ እንዲያደርግ ተጠይቋል፡፡
ዴይሊሜይል በኅዳር ወር መጨረሻ ላይ አንድ ብሪታኒያዊ ፎቶግራፍ አንሺ ቱሪስት በሁለቱ ሕንፃ አብያተ ክርስቲያን መካከል በሚገኘው በማደሪያው አቅራቢያ የቁፋሮ ሥራ ሲካሄድ መመልከቱን፣ ይኸው የታቦተ ጽዮን ማደሪያ እድሳትም ታቦተ ጽዮን ወደ ጊዜያዊ ማደሪያዋ ስትወሰድ እርሷን የማየት ዕድል እንደሚሰጥ የተናገረውን ጠቅሶ ከዘገበው ጋራ በተያያዘ የሚነገረውም ስፍራውን የሚጎበኙ አንዳንድ ቱሪስቶች ውስወሳ እና ሽድሸዳ መሆኑ ተመልክቷል፡፡ “ጽላተ ጽዮንን በዐይናችን ካላየን” የሚሉ በርካታ ቱሪስቶች ከሥርዐቱ አኳያ የሚነገራቸውን ቢቀበሉም አልፎ አልፎ ግን ክልከላውን በአሉታ በመውሰድ ብቻ ስለ አጠቃላይ ሁኔታው የተዛባ መልእክት የሚያስተላልፉ ስለመኖራቸው ከሚያሰፍሯቸው የጉዞ ማስታወሻዎች መረዳት ይቻላል፡፡ ምናልባት ፓትርያርኩን የገጠሟቸው እንዲህ ዐይነቶቹ ይሆኑን?
ባለፈው ዓመት ብቻ ፓትርያርኩ በአዲስ አበባ የመጀመሪያው ቤተ ክርስቲያን መሆኑ ለሚነገረው ለደብረ ቀራንዮ መድኃኔዓለም እና ለርእሰ አድባራት ደብረ ፀይ ቁሉቢ ቅዱስ ገብርኤል አብያተ ክርስቲያን የቅርስ መጠበቂያና ሙዚዬሞች ግንባታ ዕብነ መሠረት ያስቀመጡ ሲሆን የደብረ ሊባኖስ ጻድቁ አቡነ ተክለ ሃይማኖት ገዳምን ሙዚዬም ደግሞ መርቀዋል፡፡ መልካም!! በአንጻሩ የደብረ ዳሞ ገዳም ዕቃ ቤት ጠባቂ ‹በዘራፊዎች› መገደላቸውንና ቀደም ሲል የደብረ ዳሞ፣ የአዲስ ዓለም ጽዮን ማርያም ቤተ ክርስቲያንና የሌሎችም ቅዱሳት መካናት ዕቃ ቤቶች በደረሰባቸው ‹ቃጠሎ› መጎዳታቸውን ያስታወሱ ታዛቢዎች ቅርስ ንዋያተ ቅድሳታችንን “ለጎብኚዎችና ተመራማሪዎች ምቹ ለማድረግ” በሚል ከያሉበት በአንድ ማእከል ተሰብስበው እንዲቀመጡ የሚደረግበት ሁኔታ በጥንቃቄ መታየት እንደሚገባው እያሳሰቡ ነው፡፡
ለ30ው የመንበረ ፓትርያርክ አጠቃላይ ሰበካ መንፈሳዊ ጉባኤ በቀረበው የብፁዕ ዋና ሥራ አስኪያጁ ሪፖርት በብዙ አካባቢዎች ቅርሶች የሚጠበቁባቸው ሙዚዬሞችና ዕቃ ቤቶች ተገንብተው፣ ታላላቅ ምሥጢራዊ ካዝናዎችና ቁም ሣጥኖች ተሠርተው ቅርሶች ለጎብኚዎች በሚያመች ሁኔታ መደራጀታቸው፤ ለቅርስ ጠባቂዎችም ሥልጠና መሰጠቱ፣ ቅርሶች በጥራት እንዲመዘገቡና በየዓመቱም ቁጥጥር እንዲደረግባቸው መመሪያ መሰጠቱ ተገልጧል፡፡ በአንጻሩ በአንዳንድ አህጉረ ስብከት ነባር ጽላትን በፎርጅድ የመለወጥ ተንኮል እንደሚሠራ፣ በአንዳንዶቹም የዘረፋ ሙከራ እንዳልቀረ ተመልክቷል፡፡ መጠነ ሰፊ የጽላት ዘረፋው ከብዙ ስርቆት ጽላተ ጽዮንን ለማግኘት የመማሰን የጥቅመኞች ብቻ ሳይሆን የውጭ የስለላ ድርጅቶችና ጀብደኞች ሤራ ሊሆን እንደሚችል የሚያመለክቱ ትንታኔዎች አሉ፡፡ አለቃ አያሌው ኢትዮጵያ ለጽላተ ጽዮን የዘላለም ማረፊያ ልትሆን መመረጧን፣ ሁለቱንም የሚለያያቸው እንደሌለ አስመልክቶ የሚከተለውን ጽፈዋል፡-
“እግዚአብሔር በደብረ ሲና በፈቀደው መልክ ተገልጦ በጨለማና በጭጋግ መካከል ሁለቱን ጽላት ለሙሴ ሰጠ፤ ግን ሁለት ጽላት ብቻ የተዘጋጀችበትን ምክንያት ያወቀ የሚያውቅም የለም፤ እስከ ዛሬም አልተገለጸም፡፡ ነገር ግን ኋላ በዘመነ ሰሎሞን ታቦተ ጽዮን ወደ ኢትዮጵያ መምጣቷን ስንመለከት ዕብራዊውን ሙሴንና ኢትዮጵያዊት ሚስቱን አንድ ያደረገ ልዑል እግዚአብሔር ቤተ እስራኤልን ኢትዮጵያ አድርጎ አስቦ ኖሯልን? የሚል አንክሮ ይገጥመናል፡፡”

ጽዮን በጽዮንነቷ ጸንታ ትኖራለች፤
ቸር ወሬ ያሰማን፤ አሜን፡፡

++++++++
ስለ ታቦተ ጽዮን ታሪካዊ ትውስታ እንዲሆን ከዚህ በታች ያሉትን ጽሑፎች እንድታነቡ እንጋብዛለን።
መልካም ንባብ!!!
አኵስም እንተ ይእቲ እሞን ለአህጉር
(ፕሮፌሰር ሥርግው ሐብለ ሥላሴ)
የአክሱም ታሪክ እንደ ምንጩ ይለያያል፡፡ የአፍ ታሪክን መሠረት ያደረግን እንደሆነ የከተማዪቱ አመሠራረት ቅድመ ልደተ ክርስቶስ ከ2000 ዓመት በፊት ይሆናል፤ መሥራቹም በስሙ ሀገሪቱን ኢትዮጵያ ያሰኘው ኢትዮጲስ ነው፤ መቃብሩም በምሥራቅ ጫፍ በጎብደራ አካባቢ እንደሚገኝ ይታመናል፡፡ ሁለተኛዪቱ የከተማዋ ቆርቋሪ ንግሥተ ሳባ በ1000 ቅድመ ልደተ ክርስቶስ እንደነበረች ይገመታል፡፡ እርሷም ወደ ኢየሩሳሌም ወርዳ ከንጉሠ እስራኤል ሰሎሞን ልጅ ፀንሳ የኦሪትን ሥርዐት ተቀብላ መመለሷን ታሪከ ነገሥት ይገልጻል፡፡ ልጇ ቀዳማዊ ምኒልክም በኋላ ጽላተ ኦሪትን አምጥቷል ይለናል፡፡ ቤተ መንግሥቱም ዛሬ ወደ ጎንደር በሚወስደው አውራ ጎዳና በደቡብ በኩል ነበር ይባላል፡፡ በዚህ ሥፍራ በተደረገው ቁፋሮ የሕንፃ ቅሪቶች ተገኝተዋል፡፡ ያልተጠረቡ የድንጋይ ሐውልቶች በብዛት ቆመው ይታያሉ፡፡ በቃል ታሪኩ መሠረት ሦስተኛ የአክሱም ከተማ ቆርቋሪዎች ከአራተኛው መቶ ክፍለ ዘመን በኋላ የኖሩት ኣብርሃ እና ኣጽብሃ ናቸው፡፡ እነርሱ የሠሩት ቤተ መንግሥት ዛሬ ታዕካ ነገሥት የሚባለው እንደሆነ ይገመታል፡፡
የተጻፉ የታሪክ ምንጮችን መሠረት ያደረግን እንደሆነ በአባ ጰንጠሌዎን ገዳም የተገኘው የግሪክኛ የደንጊያ ጽሑፍ ነው፡፡ ጽሑፉ የተፈረካከሰ ቢሆንም አክሱም የሚለው ቃል በከፊል ይነበባል፡፡ ፐሪፕሎስ በሚል ርእስ አንድ የግሪክ ነጋዴ በጻፈው መጽሐፍ የአክሱምን ዋና ከተማነት ያረጋግጣል፡፡ አክሱም እንደ መናገሻ ከተማ የገነነችው በሦስተኛው እና በአራተኛው ምእቶች ነበር፡፡
. . . በአራተኛው መቶ ክፍለ ዘመን ክርስትና በኢትዮጵያ ሥሩ ጠልቆ ሰጥሟል፡፡ ይኸውም በነገሥታቱ ኣብርሃ እና አጽብሃ ርቱዕነት፣ በቅዱስ አቡነ ፍሬምናጦስ ትጋት ነው፡፡ ኣብርሃና አጽብሃ ክርስትናን ከማስፋፋት ጋራ የሚጸናበትን በማበጀት አስተዋፅኦ አድርገዋል፡፡ በቃል በቆየን ታሪክ መሠረት የመጀመሪያውን የአክሱም ጽዮን ቤተ ክርስቲያን አሠርተዋል፡፡ ይኸውም ገበዘ አክሱም በመባል ይታወቃል፤ ገበዝ የሚለው ቃል ካቴድራል ከሚለው ጋራ ተመሳሳይነት አለው፡፡ የቤተ መቅደሱ ስፋት በጣም ታላቅ ሲሆን 12 መቅደሶች ነበሩት፡፡ እያንዳንዱ በማን ታቦት ስም ተሠይሞ እንደ ሆነ አይታወቅም፡፡
. . .በሰባተኛው ምእት ላይ የእስላም ሃይማኖት በዐረብ ሲንቀሳቀስ ለመጀመሪያዎቹ ተከታዮች ምቹ አልነበረም፡፡ መሐመድ ወገኖቹን ወደ ኢትዮጵያ እንዲሄዱ ነግሯቸው ወደ አክሱም መጥተው ተስተናግደዋል፡፡ ያን ጊዜ ንጉሡ አርማህ ነበር፡፡ የእስላምን ሃይማኖት ይቃወሙ የነበሩት ወገኖች ስደተኞችን እንዲሰጧቸው በመልእክተኞች ጠይቀው ነበር፡፡ ነገር ግን ስደተኞቹ ተላልፈው አልተሰጡም፡፡ እስላም እስኪጠናከር እዚህ ቆይተው በኋላ በመሐመድ ጥያቄ መመለስ የፈለጉቱ ወደ ዐረብ ተመልሰዋል፡፡ ወደ ኢትዮጵያ መጥተው ከነበሩት የመሐመድ ተከታዮች አንዲቱ ሃቢባ የምትባል በኋላ ወዳጁ የነበረችው ናት፡፡ የመሐመድ ሞት በተቃረበበት ወቅት የአክሱም ከተማን ሁኔታ እየተረከችለት ሕመሙን ለማስታገሥ ትሞክር ነበር፡፡ ከትረካዋም መካከል የአክሱም ጽዮን ቤተ ክርስቲያን ትልቅነት፣ በውስጡም ስለሚታዩት ሥዕሎች የተመለከቱ ይገኙበት ነበር፡፡ ትረካዋ ከእስልምና መሠረተ ትምህርት ጋራ የሚቃረን ቢሆንም ሰሚ ጆሮ አልነሣትም፡፡ እኛም ከዚህ ትረካዋ የያኔው የአክሱም ጽዮን ቤተ ክርስቲያን ሥዕል እንደነበረው እንረዳለን፡፡
ከዚህ በኋላ አክሱም የደስታ ጊዜ አላሳለፈችም፡፡ ከውስጥ ለሥልጣን የነበረው ትንቅንቅ፣ ከውጭ አገርን ለመውረር የነበረው ትግል ሰላሟን ነስቶ ብልጽግናን አጉድሎባታል፡፡ ሁኔታው እየተባባሰ ሄዶ ዐሥረኛው ምእት ላይ ሲደርስ የጉዲት መነሣት ይገጥመናል፡፡ ጊዜው አመቺ ባለመሆኑ የተጣራ ዘገባ የለንም፡፡ የእስላም እና የግብጽ ክርስቲያን ምንጮች እርስዋ ሴት እንደነበረችና በማእከላዊ መንግሥት ላይ ተነሥታ እንደነበር በሚገባ አውስተውታል፡፡ በእርስ በስ የሥልጣን ሽኩቻ ተዳክሞ የነበረውን ማእከላዊ መንግሥት አስወግዳ ሥልጣን ጨብጣለች፡፡ ምንጮቹ አጉልተው የሚያሳዩን ጥፋቷን ነው፡፡ ባለ12 ቤተ መቅደስ የነበረውን የመጀመሪያውን የአክሱም ጽዮን ቤተ ክርስቲያን አፈረሰች፡፡ መጽሐፎችንና ንዋየ ቅድሳትን ደመሰሰች፤ ሐውልቶችን ሰበረች፤ የአክሱም ጽዮን ካህናት ግን ጽላቱን ይዘው ወደ ሐይቅ ተሰደዱ፡፡
የዮዲትን የግዛት ዘመን ምንጮቹ እስከ 40 ዓመታት ያደርሱታል፡፡ ከእዚያ በኋላ አንበሳ ውድም ዮዲትን አባርሮ ሥልጣን ጨበጠ፡፡ የፈረሰውን ለማቃናት ሞክሯል፡፡ ጽላተ ሙሴ ከተሰደደችበት ተመለሰች፡፡ ሁለተኛው መለስተኛ ሕንፃ ቤተ ክርስቲያን ሰባት መቅደሶች የነበረው ተሠራ፤ ግን አሁንም ሁኔታው ተረጋጋ ማለት አይቻልም፡፡ በውጭ ተጽዕኖ በውስጥ ብጥብጥ ምክንያት በ12ው ምእት መጀመሪያ አጋማሽ ላይ አክሱም እንደ ዋና ከተማነት አበቃላት፡፡ የዛጔ መንግሥት ተቋቋመ፤ ግን አሁንም ቢሆን አክሱም የነበራት ክብር አልቀነሰም፡፡ የኋላ ዘመን የታሪክ መዝገብ “አክሱም እንተ ይዕቲ እሞን ለአህጉር፤ አክሱም የሀገሮች እናት የሆነችው ወይም አክሱም “ዳግሚት ኢየሩሳሌም፤ ሁለተኛዪቱ ኢየሩሳሌም” ይሏታል - ከጽላተ ሙሴ ጋራ በማያያዝ፡፡
. . . 16ው ምእት በጠቅላላው ለክርስቲያኑ መንግሥት ምቹ አልነበረም፡፡ አሕመድ ግራኝ ተነሥቶ ንጉሡን ልብነ ድንግልን በማባረር ላይ ነበር፡፡ ልብነ ድንግልም እያፈገፈገ አክሱም ደረሰ፡፡ ከእዚያም ደብረ ዳሞ ወጥቶ ሳለ ግራኝ አሕመድ ተከታትሎ ሄዶ የአክሱም ጽዮንን ሁለተኛ ቤተ ክርስቲያን በ1527 ዓ.ም አቃጠለው፡፡ ጽላተ ሙሴ ግን ካህናቱ ቀደም አድርገው ወደ አንድ ስውር ቦታ ይዘዋት ስለተሸሸጉ አላገኛትም፡፡
ሦስተኛውን ቤተ ክርስቲያን ለመሥራት ጊዜ ፈጅቷል - በዐፄ ፋሲል ዘመነ መንግሥት በ1627 ዓ.ም ገደማ ነበር፡፡ ይህ ቤተ ክርስቲያን ከፊተኛው በአራት ያነሰ ማለት ሦስት መቅደሶች ብቻ ያሉት ነው፡፡ ይህ እንዳለ ሆኖ በአጠገቡ ሴቶች ሊገቡበት የሚቻላቸው ሌላ ቤተ ክርስቲያን በቅርቡ ተሠርቷል፡፡ ይኸውም ዐፄ ኀይለ ሥላሴ ያሠሩት ሲሆን የእንግሊዝዋ ንግሥት ኤልሳቤጥ በተገኙበት በ1957 ዓ.ም ተመርቋል፡፡
ይህ ቤተ ክርስቲያን እንደ መጀመሪያው 13 ቤተ መቅዶሶች አሉት፡፡ ይኸውም በመካከል ታቦተ እግዝእትነ ማርያም ናት፡፡ ከእርሷ በስተቀኝ ታቦተ ሥላሴ፣ ታቦተ ሚካኤል፣ ታቦተ ዮሐንስ ወንጌላዊ፣ ታቦተ ሐዋርያት፣ ታቦተ ጊዮርጊስ፣ ታቦተ ሰላማ ይገኛሉ፤ ከታቦተ እግዝእትነ ማርያም በስተግራ ደግሞ ታቦተ ኢየሱስ፣ ታቦተ ገብርኤል፣ ታቦተ ማርቆስ ወንጌላዊ፣ ታቦተ ሠለስቱ ምእት፣ ታቦተ ኣብርሃ ወኣጽብሃ እና ታቦተ አቡነ ተክለ ሃይማኖት ናቸው፡፡ ከእኒህ ታቦታት መካከል አምስቱ ማለትም ታቦተ ሚካኤል፣ ታቦተ ዮሐንስ ወንጌላዊ፣ ታቦተ ጊዮርጊስ፣ ታቦተ ሰላማ እና ታቦተ ሠለስቱ ምእት በኣብርሃ ወአጽብሃ ዘመነ መንግሥት የነበሩ ናቸው፡፡ የቀሩት ሰባቱ ጽላት ግን የታሪኩን ስልት በመከተል በመመልከትና በመመርመር እንዲደርሱ የተደረጉ ናቸው፤ ይህም ማለት ከቅርብ ጊዜ የታሪክ ድርጊቶች ጋራ በማገናዘብ ነው፡፡
ምንጭ፡- Sergew Hable-Selasse, Ancient and Medival Ethiopian History to 1270, (Addis Abeba)
ጽዮን በጽዮንነቷ ጸንታ ትኖራለች
(አለቃ አያሌው ታምሩ)

የሰው ልጅ በባሕርዩ ክፋት የማይለየው በመሆኑ ስቶ ተሳስቶ ከመንገድ ወጥቶ እግዚአብሔርን ስለ በደለና በጣዖታት ስለ ተሰናከለ፣ ልዑል እግዝአብሔር በሚታይ በሚዳሰስ ነገር ወደ እርሱ ሊያቀርበው፣ በየቀኑም ወደ ረቂቅነት ወደ ጥልቀት ሊራመድ ይገባው የነበረው የሰው ልጅ ዕውቀት ርምጃውን እየለቀቀ ወደ ግዙፍነትና ወደ ድቁርና እየተንፏቀቀ ወደ ኋላው ስለ ሄደ፣ ትእዛዝ ባለማክበር ከእንስሳት እና ከአራዊት ከአዕዋፍም ከጥቃቅን ፍጥረቶች ሁሉ ይልቅ ስለ ተዋረደ፣ ግዙፍ አእምሮው በሚፈቅደለት መጠን ወደ አምልኮቱ ሊስበው ወዶ፣ መሥዋዕቱን ጸሎቱን ስግደቱን ፍጹም አገልግሎቱን ሊያቀርብባት ትእዛዙ የተጻፈባትን የድንጋይ ገበታ/ጽሌ/ ሰጠው፤ እርሷም ጽዮን ትባላለች፡፡
ጽሌ ማለት በግእዙ የነጠላነት፣ ጽላት የብዛት ስም ነው፤ ነገር ግን በልማድ እንደ አንድ ኾኖ ይነገራል፡፡ እንዲሁም በጽላት እና በታቦት መካከል የሁኔታና የአነጋገር ልዩነት ሲኖር ልማደኛው ሰው ‹ታቦተ ጽዮን ጽላተ ሙሴ ናት› በማለት ሲናገር ይሰማል፡፡ ጽሌ ኦሪት ጽዮን ወደ ኢትዮጵያ እንድትገባ የፈቀደ እግዚአብሔር ጽላቱ 593 ዓመት በደብተራ ኦሪት ከኖሩ በኋላ እምነ ጽዮንን በሥነ ፍጥረት ሲፈልገውና ሲናፍቀው ለነበረ ኢትዮጵያዊ ሕዝብ ሰጠ፡፡ በዚህ ጽሌ ፊት ይቀርብ የነበረው መሥዋዕት እግዚአብሔር ለሙሴ እንዳዘዘው ከተቀደሱት እንስሳት ወገን - የበሬ፣ የበግ፣ የጠቦት፣ የወይፈን፣ የጊደር ስብና እግዚአብሔር አምላክ በሙሴ አማካይነት ኪዳኑን ያጸናበት ደማቸው ነበር፡፡
ይህም በብሉይ ኪዳን የተፈጸመው ነገር ሐዲስ ኪዳን ለጸናበት ለክርስቶስ ደም መንገድ ጠራጊው ነበር፡፡ ስለዚህ ኦሪት ወደ ክርስቶስ መሪ ትሆነን ዘንድ ሕጉ የተጻፈበት ጽዮንን፣ ኪዳኑ የጸናበት መሥዋዕተ ኦሪትን ለእኛ ለኢትዮጵያውያን ሲሰጥ “እምኵሉ ተዓይኒሁ ለያዕቆብ ነኪር ነገሩ በእንቲአኪ ሀገረ እግዚአብሔር - ከያዕቆብ ከተሞች ከሴሎ፣ ከኢየሩሳሌም ይልቅ ሀገረ እግዚአብሔር ኢትዮጵያ ሆይ፣ እግዚአብሔር ስለ አንቺ የሠራው ነገሩ ልዩ ነው፤ ድንቅ ነው” ሲል ነብዩ ዳዊት የገለጸው የልቡና አድናቆትና ውዝዋዜ በጎላ ታወቀ፤ ተረዳ፡፡
ይልቁንም እግዚአብሔር ታምራቱን የገለጸባቸውን ልዩ ልዩ አገሮች ካስታወሰ በኋላ በዚያው ከተወለዱት የኢትዮጵያ ሕዝብ “ሰው ሁሉ እምነ ጽዮን ይላል” ሲል የተናገረው የአኵሱም ጽዮን ቤተ ክርስቲያን መስከረም 12 ቀን 1945 ዓ.ም ስትመሠረት የረቀቀው ጎልቷል፤ የተደበቀው ተገልጧል፡፡
አኵስም በሐውልቶችዋ ስመ ጥሩነት በቤተ ክርስቲያንዋ ጥንታዊነት የኢትዮጵያ የታሪክ ፋና ናት፡፡ ሲያያዝ በመጣው ታሪክ እንደሚገኘው በቀዳማዊ ምኒልክ ዘመን የመጣችው ቅድስት ጸዮን በጥንቱ ዘመን አንሰባ ዛሬ ደግሞ መዝበር እየተባለ የሚጠራው በዚሁ አቅራቢያ በሚገኘው ቦታ ምኵራበ ኦሪት ነበረች፡፡
የክርስትናን ሥርዐት የጀመሩት ኣብርሃና ኣጽብሃ በነገሡበት ዘመን ግን ውኃ ሰፍሮበት የነበረው ይህ ስፍራ ባሕሩ በተኣምራት ደርቆላቸው የመጀመሪያዪቱ ቤተ ክርስቲያን አሳነፁላት፡፡ በዚያን ጊዜ 12 የመቅደስ ክፍሎች እንደነበሩባት ይነገራል፡፡ ከዚህም አያይዛ በየጠቅላይ ግዛቶቿና አውራጃዎቿ አህገረ ምስካይ እና ምኩራበ ኦሪትን አደራጀች፡፡
የጥንቱ የአኵስም ጽዮን ቤተ ክርስቲያን በጉዲት ከተቃጠለ በኋላ አንበሳ ውድም ባለሰባት መቅደስ አድርጎ አሳንፆት ነበር፡፡ ከዚህም ወዲህ በ1527 ዓ.ም በግራኝ ሠራዊት ስለተመዘበረች 105 ዓመት ያህል ቆይቶ የተነሣው ዐፄ ፋሲል ይህ አሁን ያለውን ሕንፃ አሠርቶላት በየዘመኑም የነበሩት ታላላቅ ሰዎች እያደሱላት እስከዛሬ ቆይታለች፡፡ በኣብርሃ ወአጽብሃ ጊዜ የነበሩትም የቤተ መቅደስ ክፍሎች አሁንም እንዲኖሩ ምኞታችን ስለሆነ መካከሉ የእምነ ጽዮን መቅደስ ኾኖ በግራ እና በቀኝ ስድስት፣ ስድስት መቅደሶች እንዲገኙበት ሆኗል፡፡
የጥንቱ ቤተ ክርስቲያን ለሴቶች የተከለከለ ነበር፡፡ ይህ የተሠራው መቅደስ ግን ሳይከለከሉ እንደ ወንዶቹ ምእመናን ጸሎታቸውን ለማድረስ ተፈቅዶላቸዋል፡፡ የጥንቱም ሕንፃ በየዘመናቸው ላሠሩት ጥንታውያን ነገሥታት መታሰቢያነቱን እንደያዘ እንዲኖር ትተነዋል፡፡ ይህችም የሕዝብ እና የአሕዛብ ተስፋ የተመሠረተባት፣ የእግዚአብሔር ሕጉ የተጻፈባት፣ አምልኮቱ የታወቀባት፣ ኪዳኑ የጸናባት ጽሌ የሥግው ቃል እናት የእመቤታችን ምሳሌ ስለሆነች መታሰቢያነቷ ሳይለወጥ ጽዮን በጽዮንነቷ ፀንታ ትኖራለች፡፡
ምንጭ፡- አለቃ አያሌው ታምሩ፣ የኢትዮጵያ እምነት በሦስቱ ሕገጋት፣ 1953 ዓ.ም
++++++

“ሁለት ጽላት ብቻ የተዘጋጀችበትን ምክንያት ያወቀ የሚያውቅም የለም”
(አለቃ አያሌው ታምሩ)
ሕገ ኦሪት ወደ ኢትዮጵያ ከመግባቷ በፊት እምነት በኢትዮጵያ መኖሩን ለማስታወስ ክብረ ነገሥት የተባለው የታሪክ መጽሐፍ “ወሆረት እንዘ ይትዌከል ልባ በእግዚአብሔር” - “የሳባ ንግሥት ልቧ በእግዚአብሔር እምነት ጸንቶላት መንገዷን ሄደች” ይላል፡፡ ይህ ቃል ምንም እንኳን መግለጫው ቤተ መቅደስን የመሰለ ቦታ፣ መማርያ፣ ማጥንያ መጽሐፍ እንደነበረ ቢያስረዳም የእግዚአብሔር እምነት ከሕገ ኦሪት በፊት በኢትዮጵያ እንደነበረ ገልጾአል፡፡
እንግዲህ የኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያን መሠረተ እምነት የተጣለው በዘመነ አበው በእነ አብርሃም ጎን ዐምደ ሃይማኖቷ የተተከለው በእነ ያዕቆብ አንጻር መሆኑ ነው፡፡ በሁለተኛው መቶ ክፍለ ዘመን ቤተ እስራኤል ኦሪትን መሪ አድርጋ ወደ ክርስቶስ ጉዞዋን ስትጀምር እግዚአብሔር አገራችንን በረድኤቱ አልዘነጋትም፡፡ እግዚአብሔር በደብረ ሲና በፈቀደው መልክ ተገልጦ በጨለማና በጭጋግ መካከል ሁለቱን ጽላት ለሙሴ ሰጠ፤ ግን ሁለት ጽላት ብቻ የተዘጋጀችበትን ምክንያት ያወቀ የሚያውቅም የለም፤ እስከ ዛሬም አልተገለጸም፡፡ ነገር ግን ኋላ በዘመነ ሰሎሞን ታቦተ ጽዮን ወደ ኢትዮጵያ መምጣቷን ስንመለከት እብራዊውን ሙሴንና ኢትዮጵያዊት ሚስቱን አንድ ያደረገ ልዑል እግዚአብሔር ቤተ እስራኤልን ኢትዮጵያ አድርጎ አስቦ ኖሯልን? የሚል አንክሮ ይገጥመናል፡፡ ቀድሞም “ኢትዮጵያ እጆቿን ወደ እግዚአብሔር ትዘረጋለች” ብሎ ዳዊት በመንፈስ ትንቢት የተናገረው ቃል ኢትዮጵያ በእምነት ከልዑል እግዚአብሔር የተፈቀደላትን ታቦተ እግዚአብሔር ለመቀበል መዘጋጀት እንደነበረባት ያመለክታል፡፡
በዚህ መሠረት ተስፋ ጊዜውን ጨርሶ ቦታውን ለአማናዊ ሥራ በሚለቅበት ኢትዮጵያ በቀዳማዊ ምኒልክ ዘመነ መንግሥት ለሕገ ልቡና አጋዥ ሕገ መጽሐፍን፣ ለእምነቷ ምስክር ታቦተ ጽዮንን፣ ሕግን የሚያስተምሩ ካህናት ሌዋውያንን አግኝታ በቤተ መንግሥቷ ጎን ቤተ ክህነትን አቋቋመች፡፡
ዛሬ አንሰባ፣ ቀድሞ መዝበር ይባል በነበረው ቦታ ላይ ምኩራበ ኦሪትን ሠራች፡፡ ከዚህም አያይዛ በየጠቅላይ ግዛቶቿና አውራጃዎቿ አህጉረ ምስካይ እና ምኩራባተ ኦሪትን አደራጀች፡፡ በቤተ እስራኤል ተቋቁሞ የነበረው ቤተ ክህነት በልዩ ልዩ ምክንያት ሲለወጥና ሲናወጥ ቤተ መቅደስም ልዩ ልዩ ጣዖታት መቆሚያ ለመሆን ስትደርስ በኢትዮጵያ የተቋቋመው ቤተ ክህነት በምንም ምክንያት አልተናወጠም፡፡ ምኩራቦቿም በአንሰባ ከተሠራችው ምኩራበ ኦሪት ጀምሮ በየክፍሉ በሚገኙ ሌዋውያን ይጠቀሙ ስለነበር ከእግዚአብሔር ስም በቀር ስመ ጣዖት አልተጠራባቸውም፤ ከሥዕለ ኪሩብም በቀር ልዩ ልዩ የአማልክት ሥዕል አልተቀረጸባቸውም፡፡
ስለዚህ ኢትዮጵያ ሀገረ እግዚአብሔር በመባል ፀንታ ሀገረ ክርስቶስ ወደ መባል ስትደርስ በንግሥት ሕንደኬ ጃንደረባ በሃይማኖተ ኦሪት ላይ ሃይማኖተ ወንጌልን አገኘች፡፡ በግዝረት ላይ ጥምቀትን ማኅተም አደረገች፡፡. . .ይኸውም በኦሪት እየተመራች ወደ ክርስቶስ መድረሷን፣ ከሕገ ኦሪት ወደ ሕገ ወንጌል መራመዷን፣ ከመሥዋዕተ እንስሳ ለአማናዊ መሥዋዕት ለኢየሱስ ክርስቶስ ክቡር ደምና ቅዱስ ሥጋ መብቃትዋን፣ በመንፈሰ ረድኤት ላይ መንፈሰ ልደትን መታደሏን በጠቅላላውም ዕጥፍ ድርብ ሀብቷን የሚያመለክት ነው፡፡
ምንጭ፡- Liqe Tebebit Ayalew Tamiru, Proceedings of the Third International Conference of Ethiopian Studies, (የኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያን)Addis Abeba, 1966.

++++++++
የንግሥት ሳባ ከኢየሩሳሌም ወደ ኢትዮጵያ መመለስ
እና
የቀዳማዊ ምኒልክ ልደት

(መሪጌታ መልአኩ ፈለቀ እንደተረኩት ድምፀ ተዋሕዶ ጋዜጣ ተከታታይ እትሞች የተቀነጨበ)

ንግሥት አዜብ ከንጉሥ ሰሎሞን ለርሷም ሆነ ለወገኖቹዋ የሚጠቅመውን ሥጋዊና መንፈሳዊ ጥበብ በመስማትና በማጥናት በኢየሩሳሌ ከቆየች በኋላ ወደ ሀገሯ ኢትዮጵያ ለመመለስ ያላትን ፈቃድ ገልጻ ለንጉሥ ሰሎሞን ላከችበት፡፡ እርሱም ይህ መልእክት በደረሰው ጊዜ፣ “አገራችን ድረስ መጥተሽ ሥርዐተ መንግሥት ሳናሳይሽ ልትሄጂ አይገባም” ብሎ መለሰላት ይባላል፡፡
. . .በተሰነውም ቀን አስፈላጊው ሁሉ እንደ ሕጉና ሥርዐቱ ተዘጋጀና ንግሥት ማክዳ በክብር ተጠርታ እርሷ ሁሉን ከምታይበት ሰገነት ላይ ሆና ሥርዐተ መንግሥቱ ሲደረግ አየች፡፡ ለመሳፍንቱና ለመኳንንቱ በጠቅላላውም ለሠራዊቱ የተደረገውን የግብዣውን አቀራረብ አደነቀች፡፡ በዚሁም ወቅት ቀዳማዊ ምኒልክ ተፀነሰ፡፡
. . .ንጉሥ ሰሎሞንም በብዙ ሠራዊትና መኳንንት ታጅቦ ሲሸኛት የወርቅ ቀለበቱን ከትንሽ ጣቱ አውልቆ፣ “ይህ ማስታወሻ ይሁንሽ፤ ምናልባትም አምላከ እስራኤል ፈቃዱ ሆኖ ከአንቺ ልጅ ቢሰጠኝ ይህን ምልክት ይዞ ወደኔ ሊመጣ ይችላል፡፡ በዚያች ሌሊት ብዙ ራእይ አይቻለሁ፤ ከራእዩም አንዱ ይህ ነው፡- ፀሓይ አስቀድሞ በእስራኤል ላይ ወጥቶ ከታየ በኋላ ወደ ኢትዮጵያ ሄዶ ሲያበራ አየሁ፡፡ ሀገርሽ በአንቺ ምክንያት በረከትን ታገኝ ይሆናል፡፡ አምላከ እስራኤል ያውቃል፡፡ አንቺ ግን እግዚአብሔርን በፍጹም ልብሽ ውደጅው፡፡ የነገርኩሽን ሁሉ አስታውሽው፡፡ እግዚአብሔር ከአንቺ ጋራ ይሁን፤ መንገድሽም የቀና ያድርገው” ብሏት ወደ ቤተ መንግሥቱ ተመለሰ፡፡
ንግሥት ማክዳም መንገዷን ቀጠለችና የመን ደረሰች፡፡ ከዚያም ባሕረ ኤርትራን ተሻግራ በሐማሴን በኩል ማይበላ በተባለው ከተማ ደረሰች፡፡ ከዚያም ሳለች ወንድ ልጅ ወለደችና ስሙን ዕብነ ሐኪም ብላ ጠራችው፡፡ ከዚሁ ቦታ ተነሥታ ወደ ዋና ከተማዋ በዚያን ጊዜ ሳባ ዛሬ ግን አኵስም ወደሚባለው በገባችበት ጊዜ የኢትዮጵያ መኳንንትና መሳፍንት በጠቅላላውም ሠራዊቱ ሁሉ በክብር ተቀብለዋታል፡፡. . .ኋላም የሕፃኑ ስም ምኒልክ ተባለ፡፡ 12 ዓመት በሆነውም ጊዜ ሞግዚቶቹን አባቴ ማነው እያለ ይጠይቅ ጀመር፤ እነርሱም እውነተኛውን መልስ አይመልሱለትም ነበር፡፡. . .ከዕለታት በአንድ ቀን ከሹማምንቱ ልጆች ጋራ ሲጫወት ከተጫዋቾቹ አንዱ፣ “እናትህ ንግሥት ነች፤ አባትህ ማነው?” ብሎ ጠየቀው፡፡ ከዚህ በኋላ እናቱን እየተመላለሰ ቢጠይቃት ንግሥት ማክዳ፣ “ሀገሩ ሩቅ መንገዱ ጭንቅ ነውና ልጄ ሆይ አታስቸግረኝ” ብላ የንጉሥ ሰሎሞንን ስም ጠቅሳ ነገረችው፡፡ ከሞግዚቶቹና ከሌሎችም ባልንጀሮቹ ሲሰማው የነበረውን ቃል በእናቱ አንደበት ስለተገለጸለት በጣም ተደሰተና 22 ዓመት ሲሆነው፣ “የእግዚአብሔር ፈቃዱ ቢሆንልኝ አባቴን አይቼ ለመመለስ አስቤያለሁና ፈቀድሽ ይሁንልኝ” ብሎ እጅ ነሥቶ አመለከተ፡፡

የቀዳማዊ ምኒልክ ኢየሩሳሌም መድረስ
. . .ቀዳማዊ ምኒልክ ከታወቀው ነጋዴና የንግሥት ሕንደኬ መልእክተኛ ከሆነው ታምሪን፣ የአባቱንና የእርሱንም መኳንንትና ሠራዊት አስከትሎ በኢየሩሳሌም ጋዛ ወደምትባለው አገር ደረሱ፡፡ ይህችውም አገር ንጉሥ ሰሎሞን ለንግሥት ሳባ ማረፊያ ይሁንሽ ብሎ የሰጣት አገር ናት፡፡ ያችም አገር በዘመነ ብሉይ ኢትዮጵያውያን በምናኔም ይሁን በሌላም ነገር በሚሄዱበት ጊዜ ማረፊያቸው ነበረች፡፡ ከክርስቶስ ልደት በኋላም የኢትዮጵያ ሕንደኬ ጃንደረባ በኢየሩሳሌም በዓለ ፋሲካን አክብሮ እጅ ነስቶ ሲመለስ ማረፊያ ቦታው ጋዛ ነበር፡፡
 ቀዳማዊ ምኒልክ ጉዞውን ቀጥሎ ከአባቱ ከተማ ኢየሩሳሌም ገባ፡፡. . .የጦር አዛዡ ብንያስም ልጁን ወደ ንጉሥ እልፍኝ ይዞት ገባ፡፡ ንጉሥ ሰሎሞንም ገና በሩቅ ሲያየው ደንግጦ ተነሥቶ አንገቱን አቅፎ እየሳመ “እነሆ አባቴ ዳዊት ከሙታን ተለይቶ ከመቃብር ተነሣ” እያለ ሲናገር በዙሪያው የተሰለፉ መኳንንት ይሰሙት ነበር፡፡ ከዚያ በኋላ ወደ ግምጃ ቤት ገብቶ ሙሉ ሽልማት እንዲደረግለት ትእዛዝ ሰጠ፤ ከዙፋኑ ፊት ለፊት በመንበር እንዲያስቀምጡትም አደረገ፡፡ መኳንንቱና መሳፍንቱም ስለ ቀዳማዊ ምኒልክ እና ስለ እናቱ ሰፊ ቃለ በረከት አቀረቡ፡፡ ወዲያውም ልጁ ቀዳማዊ ምኒልክ አባቱ ለእናቱ መታሰቢያ ሊሆናት ለብቻዋ በቆይታ ሰጥቷት የነበረውን የወርቅ ቀለበት፣ “ከእናቴ ከንግሥት ጋራ የተነጋገርከውን አስብ” ብሎ ለአባቱ ሰጠው፡፡ እርሱም፣ “የተፈጥሮ መልኬን በአንተ ላይ አይቼ ልጄ እንደሆንክ ተረድቼ ተቀብዬሃለሁ፡፡ የምልክት ቀለበት ስለምን ትሰጠኛለህ?” ብሎ መልስ ሰጠው፡፡
. . .ቀዳማዊ ምኒልክ ከአባቱ ጋራ በኢየሩሳሌም ሦስት ዓመት ሲቆይ በመጻሕፍት በኩል መጻሕፍተ ሙሴን፣ ሕገ መንግሥትንና ሥርዐተ ክህነትን፣ የዕብራይስጥ ቋንቋን ከሊቀ ካህናቱ ከሳዶቅ ተምሯል - ወዲያው እንደ ደረሰ አባቱ ሰሎሞን ከሳዶቅ ጋራ ተነጋግሮ የነገሥታቱ ልጆች ከሚማሩበት ት/ቤት አግብቶት ነበርና፡፡ የ22 ዓመት ወጣት ነበርና ትምህርቱን በሦስት ዓመት አከናውኗል፡፡ ከዚህ በኋላ እናቱ በየጊዜው ስለምትልክበት ወደ ኢትዮጵያ ለመመለስ አሳቡን ቆረጠ፡፡

የቀዳማዊ ምኒልክ ወደ ኢትዮጵያ መመለስ እና የታቦተ ጽዮን መምጣት
ቀዳማዊ ምኒልክ ወደ አገሩ ለመመለስ ሲሰናዳ ንጉሥ ሰሎሞን ሕዝቡን ሰብስቦ፣ “ይህ ልጄ ወደ እናቱ አገር ወደ ኢትዮጵያ ሊሄድ ነውና የበኵር የበኵር ልጆቻችሁንና ከካህናቱም ወገን የተማሩት አብረውት እንዲሄዱ” ብሎ አዘዛቸው፤ ነገሩንም በምክር አስረዳቸው፡፡ ከዚህ በኋላ ከሕዝቡ ወገን 12,000 ሰዎች እንደተመረጡ፣ ከካህናቱም ስምንት ሌዋውያን ተመርጠዋል፡፡ በዚህ ጊዜ ኢየሩሳሌም የነበሩት የወንድ መኳንንትና የሴት ወይዛዝርት በጠቅላላው ሕዝቡ ከፍ ያለ ሐዘን ተሰማቸውና አለቀሱ፤ የበኵር ልጆቻቸውን ሰጥተዋልና፡፡
ከዚህም አያይዞ ንጉሥ ሰሎሞን ሊቀ ካህናቱ ሳዶቅን ጠርቶ፣ “በቶሎ ሂድና በታቦተ ጽዮን ላይ የሚገኘውን መጎናጸፊያ አምጣ፡፡ እኔ የሰጠኹህን ልብስ ወስደህ በሁለቱ መጎናጸፊያዎች ላይ አድርገው፡፡ የልጄ እናት ንግሥት ማክዳ በታምሪን ቃል በላከችው መልእክቷ፣ ‹እኔና በመንግሥቴ ውስጥ ያሉት ሁሉ ታቦተ ጽዮንን እናስባት ዘንድ ለበረከት የሚሆን ነገር ላክልኝ› ብላ ልካብኛለች፡፡ ልጄም አሳስቦኝ ነበርና ለበረከት የሚሆነውን ስጠው፤ ስትሰጠውም የእናቱን ቃል አስረዳው፤ ሕገ ኦሪትን እንዲጠብቅ አስጠንቅቀው፤ በምትሠራው ሥራ ሁሉ ታቦተ ጽዮን መሪ ትሁንህ፤ መሥዋዕትም በምትሠዋበት ጊዜ በኢየሩሳሌምና በታቦተ ጽዮን አንጻር ሁንና ሠዋ፤ ስትጸልይም በኢየሩሳሌም አንጻር ሁነህ ጸልይ ብለህ ንገረው”  አለው፡፡ ሊቀ ካህናቱ ሳዶቅም ከንጉሡ የታዘዘውን ሁሉ ለቀዳማዊ ምኒልክ ነገረው፤ ቀዳማዊ ምኒልክም ፈጽሞ ደስ አለው፡፡

የታቦተ ጽዮን ከቤተ መቅደስ መውጣት እና ወደ ኢትዮጵያ መምጣት
የሊቀ ካህናት የሳዶቅ ልጅ አዛርያስ ሊቀ ካህናት ሆኖ ወደ ኢትዮጵያ እንዲመጣ ከንጉሥ ሰሎሞን ትእዛዝ ደረሰው፤ ትእዛዙም እንደደረሰው ወደ እግዚአብሔር ቢያመለክት መልአከ እግዚአብሔር ተገልጦ፣ በፊቱ ዓምደ እሳት ተተክሎ ቤተ መቅደሱም በብርሃን ተከቦ አየ፡፡ ወዲያውም ፈጥኖ ሄዶ የመንፈስ ጓደኛውን ኤልማስን ከእንቅልፉ አነቃው፡፡ ኤልማስም ፈጥኖ ሄዶ የመንፈስ ጓደኛውን አቢሳን ከእንቅልፉ ቀሰቀሰውና ሁሉም ተያይዘው ታቦተ ጽዮን ወዳለችበት ቤተ መቅደስ ገብተው ከመንበሩ እግር አጠገብ ቆሙ፡፡
በዚያም ጊዜ በቤተ መቅደሱና በዙሪያው ይታይ የነበረው ብርሃን ታቦተ ጽዮን ካለችበት አንሥቶ እንደ ኮከብ ተወርውሮ ወደ ኢትዮጵያ ሲያርፍ እንደ አዩ ይነገራል፡፡ አዛርያስም፣ “እግዚአብሔር ታቦተ ጽዮንን ይዛችሁ ሂዱ ሲለን ነው”  ብሎ፣ “ታቦተ ጽዮንን ንጉሡ በሰጠን መጎናጸፊያ ሸፍናችሁ ተነሡ”  አላቸው፡፡ ኤልማስ እና አቢሳም ታቦተ ጽዮንን ይዘው ሲወጡ ከአዛርያስ በቀር ያወቀ የለም፡፡ እነርሱም ከቀዳማዊ ምኒልክ ጋራ ወደ ኢትዮጵያ ለመምጣት ጉዟቸውን ጀመሩ፡፡
ጉዟቸውም በመልአከ እግዚአብሔር መሪነት በእግዚአብሔር ቸርነት ስለተቃናላቸው በቅርብ ቀን ውስጥ ጋዛ ከምትባለው ክፍለ ሀገር ደረሱ፡፡ ከዚያም ቃዴስ በርኔ ከምትባለው በርሓ አደሩ፡፡ ከዚያም ተጉዘው ደብረ ሲናን ወደ ቀኝ አይተው በቅርብ ቀን ጉዞ በኤርትራ የብስ ሰፈሩ፡፡ ከዚያም የኢትዮጵያ ጠረፍ ከሆነችው ቤሌንቶስ ደረሱ፡፡
ይህ ሁሉ ቀንና ሌሊት ሲያልፍ በኢየሩሳሌም ንጉሥ ሰሎሞን እንዲሁም ሊቀ ካህናቱና በጠቅላላውም ሕዝቡ የታቦተ ጽዮንን ወደ ኢትዮጵያ መምጣት አላወቁም፤ ምክንያቱም የበኵር ልጆቻቸው ስለተለዩዋቸው ልቡናቸው በሐዘን ተነክቶ ነበርና ነገሩን ሊያነሣሣው ባለመቻሉ ነው፡፡
ሊቀ ካህናቱ ሳዶቅ የተለመደውን ጸሎቱን አድርሶ ከቅድስተ ቅዱሳን ውስጥ ገብቶ ቢመለከት ታቦተ ጽዮንን ከቦታዋ አጣትና አዘነ፤ ደነገጠ፤ ሌዋውያን ካህናትም ሰምተው ደነገጡ፤ በከተማውም ሽብር ሆነ፡፡ ወዲያውም ንጉሥ ሰሎሞን ነገሩን ሰማና ሳዶቅን አስጠርቶ ጠየቀው፡፡ አንዳንድ ታሪክ ጸሐፊዎች ቀዳማዊ ምኒልክ ከአባቱ ከሰሎሞን ተሰናብቶ ከሄደ በኋላ ወዲያው የታቦተ ጽዮንን መውጣት ሰምቶ ስለነበር “ባሕሩን ተሻግረው እንደሆን ተዋቸው፤ አለበለዚያ ግን መልሳችሁ አምጧት” ብሎ መልእክተኞችን ሰዶ ነበር ይላሉ፡፡
ከዚህ በኋላ ሌዋውያን ካህናት ለቀዳማዊ ምኒልክ፣ “ከሙሴ ጀምሮ እስከ እሴይ የልጅ ልጅ እስከ ሰሎሞን ድረስ ለአዳም ልጆች መድኃኒት የሆነቻቸው ታቦተ ጽዮን እነሆ አሁን ለአንተ ተሰጠች፡፡ ይኸውም ሊሆን የቻለው በፈቃደ እግዚአብሔር ነው እንጂ በእኛ ኀይል አይደለም፡፡ እኛ አሰብን፤ እግዚአብሔር ፈጸመው፡፡ እንዲህም የሆነው የእግዚአብሔር የሕጉ ታቦት ለአንተና ለልጅ ልጆችህ መሪ ትሆን ዘንድ እግዚአብሔር አንተንና ወገኖችህን ኢትዮጵያውያንን ስለመረጠ ነው፡፡ ነገር ግን ሕገ እግዚአብሔርን ባትጠብቅ ኖሮ ታቦተ ጽዮንን ለማግኘት አትችልም ነበር፤ የእግዚአብሔር ፈቃድ ባይሆን ኖሮ ታቦተ ጽዮን ካለችበት ቦታ አትነሣም ነበር፡፡ ስለዚህ ከዛሬ ጀምሮ ታቦተ ጽዮን ክብርና ድኅነት የምታሰጠን መሆንዋን አስብ”  ብለው የታቦተ ጽዮንን ወደ ኢትዮጵያ መምጣት ነገሩት፡፡
ሊቀ ካህናት አዛርያስም ኤልማስን ጠርቶ፣ “የንጉሣችን ልጅ ቀዳማዊ ምኒልክ የታቦተ ጽዮንን ከእኛ ጋራ መሆን እንዲረዳና ፈጽሞ ደስ እንዲለው መጎናጸፊውን ገልጠህ አሳየውና መልሰህ እንደነበረው አድርገህ አጎናጽፋት”  አለው፡፡ ቀዳማዊ ምኒልክ የታቦተ ጽዮን ወደ ኢትዮጵያ መምጣት በትክክል ስለተረዳ የደስታው ብዛት ድንጋይ ሆነበት፤ “አቤቱ ፈጣሪዬ ሆይ፣ የሕግህ ማደሪያ የሆነችው ታቦተ ጽዮንን ለማየት አበቃኸኝ፡፡ ክብርና ምስጋና ይግባህ” እያለ መላልሶ ለእግዚአብሔር ምስጋና አቀረበ፤ በታቦተ ጽዮን ፊት በገና እየደረደረ እግዚአብሔርንም አመስግኗል፡፡ በሰዓት በሰዓት በታቦተ ጽዮን ፊት አስተብርኮ /ስግደት/ እያደረገ፣ “ጥበብን አሳድሪብን፤ በዘመኑ ሁሉ ስምሽ በእኛ ላይ በእኛ ላይ እንዲገለጥ መንፈሳዊ ኀይል ስጭን፤ በረድኤት ተነሽ፤ ድል አድራጊነትን ለብሰሽ፤ ጠላቶችሽን አሳፍሪያቸው፤ የሚወዱሽን ደስ አሰኚአቸው፤ አንቺን የሚከተሉትን ሁሉ በረድኤት ጠብቂያቸው” ጸሎቱን ያደርስ ነበር፡፡ የታቦተ ጽዮን መምጣት በግልጽ በተነገረም ጊዜ በተከተሉት ሠራዊት መካከል የተደረገው ደስታ በጣም ከፍ ያለ ነበር፡፡
ከዚህ በኋላ ሌዋውያን ካህናት ታቦተ ጽዮንን በመጎናጸፊያ አጎናጽፈው ባማረና በተጌጠ ሠረገላ አድርገው በፊቷና በኋላ ሆነው እየዘመሩ ጉዟቸውን በመቀጠል ወደ ኢትዮጵያ ገብተዋል፡፡
በኢየሩሳሌም ሊቀ ካህናቱ ሳዶቅ ንጉሥ ሰሎሞን ወዳለበት እልፍኝ ሲገባ አዝኖ ተክዞ አገኘው፡፡ ሳዶቅም ንጉሥ ሆይ፣ ምነው አዝነሃል?” ብሎ ጠየቀው፡፡ ንጉሡም ያዘነበት ምክንያት ንግሥት አዜብ ወደ ኢየሩሳሌም ሄዳ በነበረ ጊዜ በፀሓይ አምሳል ያየውን ራእይ በማሰብ ራእዩ ትክክል ስለሆነ ነው፡፡ ይህንኑም ራእይ በመዘርዘር አስረዳው፡፡ ሳዶቅም፣ “ይህ ራእይ የታቦተ ጽዮን ወደ ኢትዮጵያ መሄድ የሚያመለክት ይመስለኛል”  አለው፡፡ ንጉሡም ሊቀ ካህናቱን ይዞ ከመኳንንቱና መሳፍንቱ ጋራ ከተማከረ በኋላ ሕዝቡን በዐዋጅ ሰብስቦ፣ “ይህ ነገር እንዳይሰማ፤ ታቦተ ጽዮን ወደ ኢትዮጵያ ብትሄድ አብረው የሄዱት ልጆቻችን ናቸውና በእኛና በእነርሱ ልዩነት የለም፤ ነገር ግን ከአምልኮተ እግዚአብሔር ውጭ የሆኑ አሕዛብ ሰምተው እንዳይዘብቱብን ተጠንቀቁ፤ ታቦተ ጽዮን በሄደችበት በኢትዮጵያም ቢሆን የእኛ ጠባቂ መሆኗን አንጠራጠርም”  ብሏቸዋል፡፡ እነርሱም ይህን ቃል ተቀብለውታል፡፡ ይኸውም በክብረ ነገሥት ተጽፏል፡፡
የቀዳማዊ ምኒልክና የታቦተ ጽዮን መምጣት እንደተሰማ ነጋሪት ተመታ፤ መለከት ተነፋ፤ ንግሥት ማክዳ ራሷ ሠራዊቷን አሰልፋ በጥቂት ቀን ጉዞ ከልጇ ጋራ ተገናኘች፤ ታቦተ ጽዮንንም እጅ ነስታ እግዚአብሔርን አመሰገነች፡፡ የተገናኙበትም ቦታ መደባይ ወለል ይባላል፡፡ የታቦተ ጽዮን ወደ ኢትዮጵያ መምጣት ለንግሥቲቱና ለሠራዊቷ ብቻ ሳይሆን ለጠቅላላው ሕዝብም በተነገረ ጊዜ ከፍ ያለ ደስታና እልልታ ይሰማ ነበር፡፡ ቀዳማዊ ምኒልክ ከእናቱ ንግሥት አዜብ ጋራ ሆኖ በዚያን ጊዜ ሳባ በኋላ አኵስም ተብላ ወደምትጠራው ዋና ከተማ ገባ፡፡
ንግሥት አዜብ ከምኒልክ ጋራ አብረው ከሄዱት ይልቅ አብረው የመጡትን በይበልጥ አመሰገነች፡፡ ካህናቱን ድርጎ አውጥታ ማረፊያ ሰጥታ ሁሉንም ልጇ እንደነገራት በየደረጃቸው አስቀመጠቻቸው፡፡ ታቦተ ጽዮንንም ለጊዜው በድንኳን አሳርፈው ቆይተው ግን በኢትዮጲስ መቃብር ላይ መቃኞ አሠርተው በክብር አስቀምጠዋታል፡፡ በኋላም እናቱ ንግሥት አዜብ ሳባ በሚባለው ከተማዋ ላይ ቤተ መቅደስ አሠርታ ታቦተ ጽዮን እንድትገባ አድርጋለች፡፡ ከኢየሩሳሌም ከመጡት ከነገደ እስራኤል እና ከኢትዮጵያውያን ወገን ሰዎች አስመርጣ ታቦተ ጽዮንን በትጋት እንዲጠብቁ ሥርዐት ሠርታለች፡፡
ሁሉን ከአከናወነች በኋላ መንግሥቱን በሙሉ ለልጇ ለቀዳማዊ ምኒልክ አስረከበች፡፡. . .ንግሥት ሳባ ኢትዮጵያንና ሌሎችንም አገሮች በመንፈሳዊና በሥጋዊ ጥበብ ስታስተዳድር ከኖረችና መንግሥቷን በሕይወቷ ለልጇ ካስተላለፈች በኋላ በነገሠች በ74 ዘመንዋ ከዚህ ዓለም በሞት ተለየች፡፡ የቀብሯም ሥርዐት በቤተ መንግሥቷ አጠገብ ባሠራችው መቅደስ ተፈጸመ፡፡ ያም ቦታ የንግሥት ሳባ መቃብር እየተባለ ይጠራል፡፡ በዘመንዋ በኢትዮጵያውያን ዘንድ የነበረው ሥልጣኔ በጣም ከፍ ያለ ስለነበር እነሆ ዛሬ ብዙዎች ጥንታውያን ቅርሶች በመናገሻ ከተማዋ ይገኛሉ፡፡
ንግሥቷ በቅጽል ስሟ ንግሥት ማክዳ፣ ጐሎ ማክዳ ትባላለች፤ በሀገርም ዘርፍ ሲጠሯት ንግሥተ ሳባ፣ ንግሥተ አዜብ ይሏታል፡፡ በዘመንዋ ዝናዋ በዓለም የተስፋፋ ገናና ንግሥት እንደነበረች ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በሚያስተምርበት ጊዜ የእምነቷን ታላቅነት በመጥቀስ፣ “ከምድር ዳርቻ የመጣችው ንግሥት አዜብ ትፋረዳችኋለች”  (ማቴ.12÷42) በማለት ጸሐፍት ፈሪሳውያንን አስጠንቅቋቸዋል፡፡

በአጠቃላይ ታቦተ ጽዮን ወደ ኢትዮጵያ የመጣችው በፈቃደ እግዚአብሔር ለመሆኑ የሚቀጥሉት ማስረጃዎች አሉ፡-
ሀ)በብሥራተ መልአክ በፈቃደ እግዚአብሔር እንጂ በሰው ፈቃድ ባለመሆኑ፤
ለ)ወደ ኢትዮጵያ ለመምጣት ጉዞ ከመጀመሩ በፊት ለእግዚአብሔር መሥዋዕት ማቅረብ ተፈላጊ መሆኑ ሊቀ ካህናቱ አዛርያስ ከመልአከ እግዚአብሔር መስማቱ፤
ሐ)ለታቦተ ጽዮን ወደ ኢትዮጵያ ለመምጣቷ ምክንያት የሆኑት ራሳቸው ነገደ እስራኤል እንጂ ኢትዮጵያውያን ባለመሆናቸው፤
መ)ታቦተ ጽዮን ወደ ቤተ መቅደስ ስትወጣና ከወጣችም በኋላ ይህን ባደረጉት ሰዎች ላይ አንዳችም ዐይነት መቅሰፍት ከእግዚአብሔር ባለመታዘዙ፤
ሠ)ነገደ እስራኤል ታቦተ ጽዮንን ይዘው ቀዳማዊ ምኒልክን አጅበው ሲመጡ በመልአከ እግዚአብሔር መሪነት በመሆኑ የሚሉት ናቸው፡፡9 comments:

Anonymous said...

በ“ሁሉም ኢትዮጵያዊ ዜጋ ለዓባይ ግድብ መዋጮ በነፍስ ወከፍ ካደረገው ርብርብ ባልተናነሰ መልኩ ለአኵስም ጽዮን ሙዚዬም ግንባታ መዋጮም ሊረባረብ ይገባዋል፤ የዓባይ ግድብ የሥጋችን ብርሃን እንደሆነ ሁሉ ታቦተ ጽዮንም የነፍሳችን ብርሃን ናትና”
የመለስና የአባ ጳውሎስ ከስልጣን ስንብት አስቀድሞ የመጫረሻው የብር መዝረፊያ ፕሮጀክት ምስባክ
እኛስ ኢትዮጵያውያን ለጽላተ ጽዮን የምናደርገው ጥበቃ ምን መሆን አለበት እንደ ሉሲ እያየን ዝም እንል ይሆን? ፈረንጎቹስ ከአባ ጳውሎስ ጋር ምን እየመከሩ ይሆን?

Anonymous said...

ሰላም ደጀ ሰላማውያን
ፈረንጆች ኢትዮጵያን የሰዶም ቤት አድርገው የማንነታችን መገለጫወቻችንንና ቅርሶቻችን ላይ ካተኮሩ ዘመናት አስቆጥረዋል አሁን ደግሞ ወሬው ከኛ ሳይደረስ ስለ ጽላተ ጽዮን ማደሪያ እድሳትን አስታከው እንዴት ሊነጥቁን እንደሚችሉ በመወያየት ላይ ናቸው ለዚሀም ማን እንደሚያመቻችላቸው መገመት አያቅተንም
ወገኖቸ ጽላተ ጽዮን ጠንክረን መጠበቅ ያለብን ዛሬ ነው በተለይ ኢትዮጵያ የሚኖሩ በቻ ሳይሆን በውጭ የምንኖርም ማድረግ የምንችለው ነገር ካለ መነጋገር አለብን ዝምታችን በዛ ሌቦቹም ተመቻቸው


http://www.dailymail.co.uk/news/article-2069765/Ark-Covenant-revealed-leaking-roof-Ethiopian-chapel.html

Will this be the first time the world sees the Ark of Covenant? Leaking roof in Ethiopian chapel 'will lead to relic being revealed'Posted on Monday, December 05, 2011 12:23:24 PM by marshmallow


*Leaking roof in Ethiopian chapel 'will lead to relic being revealed'


*Ark contains Ten Commandments God 'gave' to Moses on Mount Sinai

*One holy monk is the only person allowed to see the holy box...

* ...but he'll need a hand carrying metre long wooden structure to new home

A very British problem of a leaky church roof could be about to give the world the chance to glimpse the legendary Ark of the Covenant.

That's because the claimed home of the iconic relic - a small chapel in Ethiopia - has sprung a leak and so the Ark could now be on the move.

The Ark - which The Bible says holds God's Ten Commandments given to Moses on Mount Sinai - is said to have been kept in Aksum, in the Chapel of the Tablet, adjacent to St Mary of Zion Church, since the 1960s.

According to the Old Testament, it was first kept in the Temple of Solomon in Jerusalem for centuries until a Babylonian invasion in the 6th century BC.

Since then it's been the goal of many adventurers and archaeologists to find it. Most-famously, but also fictitiously, Indiana Jones was shown in the 1981 Steven Spielberg film Raiders of the Lost Ark.

There has also been a long-running claim from the Orthodox Christians of Ethiopia that they have had the Ark for centuries, and since the 1960s it has apparently been kept in the chapel.

This small and curiously-styled building is surrounded by spiked iron railings, and situated between two churches, the old and new, of St Mary of Zion in central Aksum.

No one has been allowed to see the holy object, described in scripture as being made from acacia wood, plated with gold and topped with two golden angels, except one solitary elderly monk...........


(Excerpt) Read more at dailymail.co.uk ...

Anonymous said...

ሰላም ደጀ ሰላማውያን
ፈረንጆች ኢትዮጵያን የሰዶም ቤት አድርገው የማንነታችን መገለጫወቻችንንና ቅርሶቻችን ላይ ካተኮሩ ዘመናት አስቆጥረዋል አሁን ደግሞ ወሬው ከኛ ሳይደረስ ስለ ጽላተ ጽዮን ማደሪያ እድሳትን አስታከው እንዴት ሊነጥቁን እንደሚችሉ በመወያየት ላይ ናቸው ለዚሀም ማን እንደሚያመቻችላቸው መገመት አያቅተንም
ወገኖቸ ጽላተ ጽዮን ጠንክረን መጠበቅ ያለብን ዛሬ ነው በተለይ ኢትዮጵያ የሚኖሩ በቻ ሳይሆን በውጭ የምንኖርም ማድረግ የምንችለው ነገር ካለ መነጋገር አለብን ዝምታችን በዛ ሌቦቹም ተመቻቸው


http://www.dailymail.co.uk/news/article-2069765/Ark-Covenant-revealed-leaking-roof-Ethiopian-chapel.html

Will this be the first time the world sees the Ark of Covenant? Leaking roof in Ethiopian chapel 'will lead to relic being revealed'Posted on Monday, December 05, 2011 12:23:24 PM by marshmallow


*Leaking roof in Ethiopian chapel 'will lead to relic being revealed'


*Ark contains Ten Commandments God 'gave' to Moses on Mount Sinai

*One holy monk is the only person allowed to see the holy box...

* ...but he'll need a hand carrying metre long wooden structure to new home

A very British problem of a leaky church roof could be about to give the world the chance to glimpse the legendary Ark of the Covenant.

That's because the claimed home of the iconic relic - a small chapel in Ethiopia - has sprung a leak and so the Ark could now be on the move.

The Ark - which The Bible says holds God's Ten Commandments given to Moses on Mount Sinai - is said to have been kept in Aksum, in the Chapel of the Tablet, adjacent to St Mary of Zion Church, since the 1960s.

According to the Old Testament, it was first kept in the Temple of Solomon in Jerusalem for centuries until a Babylonian invasion in the 6th century BC.

Since then it's been the goal of many adventurers and archaeologists to find it. Most-famously, but also fictitiously, Indiana Jones was shown in the 1981 Steven Spielberg film Raiders of the Lost Ark.

There has also been a long-running claim from the Orthodox Christians of Ethiopia that they have had the Ark for centuries, and since the 1960s it has apparently been kept in the chapel.

This small and curiously-styled building is surrounded by spiked iron railings, and situated between two churches, the old and new, of St Mary of Zion in central Aksum.

No one has been allowed to see the holy object, described in scripture as being made from acacia wood, plated with gold and topped with two golden angels, except one solitary elderly monk...........


(Excerpt) Read more at dailymail.co.uk ...

Anonymous said...

ውድ ደጀ ሰላሞች እጅግ የሚማርክ መረጃ ነው እድሜ ይስጣችሁ እግዚአብሔር አምላክ አገልግሎታችሁን ይባርክ በአክሱም ያላችሁ ውድ ክርስቲያኖች የእናታችን የታቦተ ጽዮንን ነገር አደራ አደራ አደራ።

Anonymous said...

ገንዘብና አባ ጳውሎስ ምላስና ጥርስ ናቸው።

Anonymous said...

His holiness abba paulos is «ጌታዋን የተማመነች በግ፣ ላቷን ደጅ ታሳድራለች»
http://www.youtube.com/watch?v=1lqsEEvS6no&feature=related

Anonymous said...

is tabot tsion in Ethiopia ? i DO NOT THINK SO THAT IS WHY ABUNE PAUL REFUSE TO RENEW IT.

Anonymous said...

WELADIET AMLEAKE Ebakshen, Tslatuen Kemitbkeu Lela, Wed Tslateu Kerbewm Minem Endayayeu, Endaynkeu, Btshem Tesrteo Eskiyalike Deries TSLATE TSYONEN Sewribachew, Bedfirte Yemigbutinem, Bealem Eskismea, Kichachew Adrashen, Tinte Yenbreu, Abtoche, Berabe, Bebirde, Besinte Cegier, Mererin Bekan Sayleu, EGZIABHER Befikdew, Kezieche Mider Eskiyalfeu Derse, TSLATE TSYONIEN, Mela Betkirstyanien, Kirsochwean Sitbkeu, Selnoreu, Ena Silalfeu Abatoche Belshe! Zime Atbey, Lijshenme Alkshbet Ebakeshe, Asrateshe Leay Ena Betkirstyan Leay Yemidrgwen Gife Zime Aybel Fituen Yimleslien Zinde, ASASBIEN DENGIEL HOY ASASBIEN!

Anonymous said...

I am happy about Abune paulos, because he is doing well but all of you are YE WETET ZINB; please be clam and live your life. Who are you who blame him? He is head of our church and he became father of our church over the world by willing of GOD.

Blog Archive

የአቡነ ጳውሎስ "ሐውልተ ስምዕ"

ነጻ ፓትርያርክ ምርጫ ቢሆን ኖሮ ማንን ይመርጡ ነበር? እንበልና ሁሉም ነገር ሥርዓቱን ጠብቆ የተከናወነ የእጩዎች ምርጫ ቢሆን ኖሮ፣ አሁን የምናነሣቸው ጉድለቶች ባይኖሩ ኖሮ፣ 6ኛው ፓትርያርክ እንዲሆን የምትመርጡት ማንን ነበር? (ማሳሰቢያ፦ አሁን ያለው ክፍፍል እና የመንግሥት ተጽዕኖ ባይኖር ኖሮ ተብሎ የሚመለስ ጥያቄ ነው። የምን “ባይኖር ኖሮ ነው” የሚል አስተያየት ካለዎትም እናከብራለን።)