December 4, 2011

የግብረ ሰዶማውያኑን ስብሰባ የተቃወሙ ኦርቶዶክሳውያን ወጣቶች ታስረው ተለቀቁ

  • ወጣቶቹ ከካዛንቺስ እና አካባቢው የተሰባሰቡ ናቸው ተብሏል
  • ተቃዋሚዎቹ በመፈክር መልክ ከያዟቸው ኀይለ ቃሎች መካከል “ግብረ ሰዶም ኀጢአት ነው!”፤ “ግብረ ሰዶም የዘር ማጥፋት ወንጀል ነው!”፤ “ቅድስት ሀገር ኢትዮጵያ በግብረ ሰዶማውያን አትረክስም!”፤ “[የወንጀል ሕጉ] አንቀጽ 629 ይከበር!” የሚሉ ይገኙበታል
  • ግብረ ሰዶማዊነት ለረጅም ጊዜ ከአእምሮ በሽታ ዝርዝር ተደምሮ የቆየ ነው
(ደጀ ሰላም፤ ኅዳር 23/2004 ዓ.ም፤ ዲሴምበር 3/2011):- የዓለም ኤድስ ቀንን ምክንያት በማድረግ በኤች.አይ.ቪ/ኤድስ እና አባላዘር በሽታዎች ላይ አተኩሮ ከሚካሄደውና ኢትዮጵያ ከነገ ኅዳር 24 - 28 ቀን 2004 ዓ.ም ድረስ ከምታስታናግደው 16ው ዓለም አቀፍ ስብሰባ ቀደም ብሎ ዛሬ ኅዳር 23 ቀን 2004 ዓ.ም የተካሄደውን የግብረ ሰዶማውያኑን ስብሰባ የተቃወሙ ወጣቶች ለአንድ ሰዓት ያህል ታስረው መለቀቃቸው ተሰማ፡፡

200 ተሳታፊዎች እንደተገኙበት የተገለጸውና ቅዳሜ በአፍሪካ ኢኮኖሚክ ኮሚሽን - የተባበሩት መንግሥታት የስብሰባ አዳራሽ ሲካሄድ የዋለው ይኸው ስብሰባ አምሸር - AMSHeR (The African Men for Sexual Health and Rights) የተባለ ከ13 የአፍሪካ አገሮች በተውጣጡና ግብረ ሰዶምን በግለሰብ ሰብአዊ መብት ላይ የተመሠረተ በጎ ምግባር አድርገው በሚወስዱ 15 ድርጅቶች የተቋቋመ ቡድን የተዘጋጀ ነው፡፡ የዛሬው ስብሰባ 200 ያህል ግብረ ሰዶማውያን በጋራ የተሳተፉበትና ለሦስተኛ ቀን የተካሄደ የማሳረጊያ ስብሰባ ሲሆን ኅዳር 21 እና 22 ቀን 2004 ዓ.ም በተለያየ ደረጃ ተመሳሳይ ስብሰባዎች በዚያው የኢ.ሲ.ኤ - ተ.መ.ድ የስብሰባ አዳራሽ ሲካሄዱ መቆየታቸው ታውቋል፡፡ 
“ለግብረ ሰዶማውያኑ አዲስ ትብብር ለመፍጠር እና ለማቀናጀት፣ ልምድን ለማዳበር፣ ምርጥ ተሞክሮዎችን ለማስፋፋት እና ለሚቀጥለው ትውልድ ይህንኑ ዘይቤ ለማስተላለፍ” የሚል ዓላማ የያዘውን ይህን ስብሰባ ዛሬ የተቃወሙት ወጣቶች ቁጥራቸው 15 ያህል እንደሚደርስ ተገልጧል፡፡ ተቃዋሚዎቹ ዛሬ ጠዋት 2፡00 ላይ በመጀመሪያ ያመሩት ቀደም ሲል ስብሰባው ይካሄድበታል ወደተባለውና ቅርንጫፉ ካዛንቺስ ወደሚገኘው ጁፒተር ዓለም አቀፍ ሆቴል ነበር፡፡ ይሁንና የሆቴሉ አስተዳደር የተጠቀሰው ስብሰባ በሆቴሉ እንደማይካሄድ ለአንዳንድ የሚዲያ አካላት በመግለጹ ይህንኑ ዘግይተው የተረዱት ተቃዋሚዎቹ በአቅራቢያው ወዳለው ኢ.ሲ.ኤ - ተ.መ.ድ አቅንተዋል፡፡
ወጣቶቹ በኀይለ ቃል ያሰሟቸው ከነበሩት መፈክሮች ውስጥ “ግብረ ሰዶም ኀጢአት ነው!”፤ “ግብረ ሰዶም የዘር ማጥፋት ወንጀል ነው!”፤ “ቅድስት ሀገር ኢትዮጵያ በግብረ ሰዶማውያን አትረክስም!”፤ “[የወንጀል ሕጉ] አንቀጽ 629 ይከበር!” የሚሉ ይገኙበታል፡፡ ይሁንና ከቀኑ 5፡30 ላይ ከ15 ተቃዋሚዎች መካከል “በዋናነት አስተባረዋል” የተባሉ ሰባት ወጣቶች ሲቪል በለበሱ የጸጥታ ኀይሎች ተለይተው ካዛንቺስ ቶታል አካባቢ ወደሚገኘው ፖሊስ ጣቢያ ከተወሰዱ በኋላ 7፡50 ላይ መለቀቃቸው ታውቋል፡፡ ወጣቶቹ በጣቢያ ቆይታቸው ያለፈቃድ የተቃውሞ ሰልፉን ለምን እንዳደረጉ፣ ስለ ስብሰባው መረጃውን ከየት እንዳገኙ መጠየቃቸው ተዘግቧል፡፡
ስለ ስብሰባው በሚዲያ መስማታቸውንና ተሳታፊዎቹ ባሉበት ወይም በሚሰሙበት አኳኋን ተቃውሟቸውን ማሰማት እንደሚሹ ወጣቶቹ ላቀረቡት ጥያቄም “ከጀርባ ሌላ ዓላማ ከሌላችሁ በቀር ፈቃድ አውጥታችሁ መቃወም ትችላላችሁ፤ ይሁንና ይህን ስብሰባ እንኳን እናንተ እኛም እንድናውቀው አልተፈቀደም” የሚል ምላሽ እንደተሰጣቸው አመልክተዋል፡፡ በዘመነ መሳፍንት እስራኤላውያን ግብረ ሰዶማዊነትንና ግብረ ሰዶማውያንን ለመከላከል ባሳዩት ቁርጠኝነትና በከፈሉት መሥዋዕት ችግሩን ከኅብረተሰቡ ማጥራታቸው ይታወሳል/መሳ.19፣ 22 - 28፤ 1ኛነገሥ. 14፣ 22 - 24፣ 46፤ 15፣10/፡፡
በሌላ በኩል በዓለም አቀፍ የበሽታዎች ዝርዝር መግለጫ /International Classification of Diseases 1 - 9/ICD ላይ ግብረ ሰዶማዊነት እንደ በሽታ ተቆጥሮ ለብዙ ዓመታት ሰፍሮ እንደ ኖረ ዩናይትድ ፎር ላይፍ ኢትዮጵያ “ግብረ ሰዶማዊነት - ተፈጥሮ? የምኞት ሸለቆ? መብት? የዝሙት ከፍታ ጫፍ?” በሚል ርእስ ያሳተመው መጽሐፍ ገልጧል፡፡ መጽሐፉ ጨምሮ እንዳተተው በአሜሪካ በአእምሮ ሕክምና ማኅበር “ግብረ ሰዶማዊነት ከአእምሮ መዛባት የተነሣ የሚፈጠር በሽታ ነው” ተብሎ ስለሚቆጠር በአእምሮ በሽታዎች ዝርዝር ውስጥ ተመዝግቦ እንደነበር አመልክቷል፡፡ ነገር ግን ከቅርብ ዓመታት ወዲህ ከሁለቱም ስፍራዎች ከበሽታዎች ዝርዝር ውስጥ እንዲሰረዝ መደረጉን፣ ይህም በመስኩ የበርካታ ሊቃውንትን ተቃውሞ ቀስቅሶ እንደነበር አትቷል፡፡ ግብረ ሰዶማዊነት ከአእምሮ በሽታ ዝርዝር ውስጥ ሲሰረዝ የቀረበው ምክንያት፡- “አንድ ሰው ግብረ ሰዶማዊ መሆን ወይም አለመሆን የራሱ መብት ነው” በሚል “Right Based Approach” እንደነበር ጨምሮ ጠቅሷል፡፡
ለግብረ ሰዶማዊነት ጥብቅና የቆሙ ወገኖች “እንደዚህ ተወልደናል” (Born that way) የሚለውን የግብረ ሰዶማውያን ኀልዮት በመጥቀስ ግብረ ሰዶማዊነትን ጄኔቲካዊ ውርስ ለማድረግ ቢጥሩም በርካታ ሳይንሳዊ ጥናቶች በአእምሮ ጤና መዛባት እና በግብረ ሰዶማውያን መካከል ጠንካራ ግንኙነት እንዳለ አረጋግጠዋል፡፡  (Neil Whitehead, Ph.D. & Briar Whitehead) የተባሉ ተመራማሪዎች በጻፉት My Genes Made Me Do It! - A Scientific Look At Sexual Orientation በተሰኘ መጽሐፋቸው እንደገለጹት ራስን ማጥፋት፣ ግራ የመጋባት፣ የጠባይዕ ተለዋዋጭነት፣ የአደንዛዥ ዕፆች እና የአልኮል ሱሰኝነት፣ ማኅበራዊ ሕይወትን መፃረር እና ከፍተኛ ወንጀሎችን በተደጋጋሚ መፈጸም የመሳሰሉት ብዙ ችግሮች በግብረ ሰዶማውያን ላይ ጎልተው የሚታዩ ችግሮች ናቸው፡፡ ሳይንሱ ይህን ቢልም ገና ጥንት በቅዱስ መጽሐፍ ግብረ ሰዶማዊነት በተፈጥሯዊ እውነት ላይ የማመፅ ተግባር መሆኑንና ውጤቱም ሰዎች እርስ በርስ በፍትወት ለሚቃጠሉበት ለማይረባ እእምሮ ተላልፎ መሰጠት መሆኑ ተገልጧል፡፡/ሮሜ 1፣18፤ ዘሌዋ 20፣13፤ 18፣ 22-23፤ 24 - 28/።

 

በግብረ ሰዶማውያኑ ስብሰባ ላይ የሚሰነዘረው ተቃውሞ እየተጠናከረ የመጣ ሲሆን ዛሬ ታትመው የወጡት ፍትሕ እና አዲስ አድማስ ጋዜጦች የአገሪቱን ሕግ በማጣቀስ፡- ግብረ ሰዶም በኢትዮጵያ መቼም ሕጋዊ እንደማይሆን፣ የሃይማኖት ተቋማት ብዙ ሥራ እንደሚጠበቅባቸው መንግሥትም የሕዝቡን ሞራላዊ ክብር የማስጠበቅ ሕገ መንግሥታዊ ግዴታ እንዳለበት የሚያሳስቡ ጽሑፎችን ይዘው ወጥተዋል፡፡
                       
የግብረ ሰዶማዊነት ነገር
(አዲስ አድማስ፤ ኅዳር 23 ቀን 2004 ዓ.ም)
/አበባየሁ ለገሠ/
ግብረ ሰዶማዊነት ኢትዮጵያ ውስጥ መቼም ቢሆን ሕጋዊ አይሆንም፡፡ በዚህ ድርጊት ውስጥ ያሉ ማረፊያ ስለሚፈልጉ ቢስፋፋላቸው ይወዳሉ፡፡ አንድ ሰው ጤናው ሲጓደል ከሕመሙ ለመፈወስ ጥረት ያደርጋል እንጂ ለሌሎቹም ይዳረስ አይባልም፡፡ ለዚህም የአገሪቱን መንግሥታዊ የጸጥታ እና የፍትሕ ተቋማት እንዲሁም ሀብት ጥቅም ላይ አያውልም፡፡
ባለፈው ማክሰኞ ይህን ድርጊት በመቃወም መግለጫ ለመስጠት የተሰባሰቡ የሃይማኖት ተቋማት የጤና ጥበቃ ሚኒስትሩን መገኘት ምክንያት አድርጎ በተፈጸመ ውይይት መግለጫው ለሌላ ጊዜ መተላለፉን ከግል ሚዲያዎች ዜና ለመረዳት ተችሏል፡፡ ዋናው ጉዳይ የሃይማኖት ተቋማቱም ሆኑ ሌሎች የሚመለከታቸው ሁሉ ድርጊቱን ተቃውመው አቋም እንዲይዙ ነው የሚጠበቀው፡፡
የግብረ ሰዶማዊነትን ነገር ከጤና ክፍተት ጋራ መመልከቱ የተሻለ ነው፡፡ ከመብት አንጻር የሚጠየቀው የሌሎችን ጤናማ መብት ለመጣስ የሚመች በመሆኑ ነው፡፡ ከፍተኛ የሆነ የጠባይዕ ለውጥ የሚያስከትል ስለመሆኑ በርካታ ጥናቶች ያረጋገጡ ሲሆን መብት ይሁን ቢባል ተዘርዝረው የማያልቁ ቀውሶች እንደሚከሠቱ ላፍታም መጠራጠር አያስፈልግም፡፡ ግብረ ሰዶማዊነትን የማስፋፋት አካሄድ በገንዘብ እና የፖሊቲካ ሥልጣንን በሽፋንነት በመጠቀም፣ እንዲሁም የድርጊቱን ተቃዋሚዎች ደግሞ በማዋከብ እና የሰላማዊ ኑሮ ዋስትና በማሳጣት በተግባር የሚደገፍ ስለመሆኑ እየታወቀ መጥቷል፡፡
ከውጭ የሚመጡ የተወሰኑ ትውልደ ኢትዮጵያውያን እና የሌሎች አገሮች ዜጎች በዚህ ችግር ውስጥ ነው ያሉት፡፡ ገንዘብ ይዘው የሚንቀሳቀሱት በተለይ በየጎዳናው ካሉ ኢትዮጵያውያን የተወሰኑትን ማግኘት ስለሚችሉ ነው፡፡ ሀብቷን መጠቀም ያልቻለች ሀገር ለባሕር ማዶ ርዳታ እና ፖሊቲካዊ ግንኙነት ሲባል ዜጎቿ እንዲቸበቸቡ መፍቀድ የለባትም፡፡ “ሳይቃጠል በቅጠል”ን መተረት እንጂ ለተወሰኑ ተጽዕኖ ፈጣሪዎች እጇን ለመስጠት እየከጀለች ከሆነ፣ እንዲስፋፋ ምክንያት የሆኑት ምግባረ ብልሹ ዜጎች፣ ተቋማት እንዲሁም ሌሎች አካላት ሊያስቡበት ግድ ይላል፡፡
የኢትዮጵያ ሕገ መንግሥት ይህን ድርጊት አይቀበለውም፡፡ ሕገ መንግሥቱ የበላይ ሕግ ነው፡፡ ማንኛውም የመንግሥት ባለሥልጣን ይሁን አካል፣ ልማዳዊ አሠራር ከዚህ ሕገ መንግሥት ጋራ የሚቃረን ከሆነ ተፈጻሚነት እንደሌለው በአንቀጽ 9(1) ላይ ተመልክቷል፡፡ ይህ ግን አልተፈጸመም፡፡ “ማንኛውም ዜጋ፣ የመንግሥት አካል፣ የፖሊቲካ ድርጅቶች፣ ሌሎች ማኅበራት እንዲሁም ባለሥልጣኖቻቸው ሕገ መንግሥቱን የማስከበርና ለዚሁ ሰነድ ተገዢ መሆን አለበት፤” ይላል በአንቀጽ 9(2)፡፡ እውነታው ይህ ነው?
. . . ግብረ ሰዶማዊነትን መቃወም የኅብረተሰቡን ጤንነት መጠበቅ ነው፡፡ ደኅንነት ነው፡፡ በሕገ መንግሥቱ አንቀጽ 91(1) መሠረት መሠረታዊ መብቶችንና ሰብአዊ ክብርን፣ ዴሞክራሲንና ሕገ መንግሥቱን የማይቃረኑ ባህሎችና ልማዶች በእኩልነት እንዲጎለብቱና እንዲያድጉ የመርዳት ሓላፊነቱ የመንግሥት ነው፡፡
የጋብቻ ሥርዐትም ቢሆን በኢትዮጵያ ሕገ መንግሥት አንቀጽ 34(1 መሠረት በወንዶች እና በሴቶች መካከል የሚፈጸም ነው እንጂ በተመሳሳይ ጾታ መካከል አይደለም፡፡ ቤተሰብ መመሥረት የሚቻለው በወንድ እና በሴት መካከል ካለው ግንኙነት መነሻነት በመሆኑ በሕገ መንግሥቱ አንቀጽ 34(3) መሠረት ከኅብረተሰቡና ከመንግሥት ጥበቃ የማግኘት መብት አለው፡፡
በ1992 ዓ.ም የፌዴራል የተሻሻለው የቤተሰብ ሕግም ቢሆን ከአንቀጽ 1 - 4 ድረስ የብሔራዊ፣ የሃይማኖት እና የባህል ሥርዐትን መሠረት ያደረጉ ጋብቻዎች በአንድ ወንድ እና በአንድ ሴት መካከል የሚፈጸሙ ናቸው፡፡ የተፈጸመው ጋብቻ ከኢትዮጵያ ውጭ ቢሆን እንኳ የሕዝብን ሞራል የሚቃረን ከሆነ በዚህ ዐዋጅ ቁጥር 213/92 ዓ.ም አንቀጽ 5 መሠረት ተቀባይነት የለውም፡፡ ግብረ ሰዶማዊነትን መሠረት ያደረገ ጋብቻ ደግሞ በኢትዮጵያ የቤተሰብ ሕግ ውስጥ ቦታ የለውም፡፡
ግብረ ሰዶማውያን(ሁሉም ባይሆኑም) የተወሰኑት ድርጊቱን ለማቀበል በመልካም አስተሳሰብ የላቸውም፡፡ ይህንንም በተለያዩ መንገዶች ለመግለጽ ጥረት ሲያደርጉ ቆይተዋል፡፡ መልካም መንገዶችን ለመግፋት ሞክረዋል፡፡ ከሕገ መንግስቱ በተጨማሪ ግብረ ሰዶማዊነት በግልጽ በኢትዮጵያ የተከለከለ መሆኑን ተሻሽሎ እንዲደነገግ ማድረግ፣ የወንጀል ሕጉ በቂ ሆኖ ካልተገኘ ራሱን የቻለ ዐዋጅ ማዘጋጀት፣ ይህን ጥፋት ለማስፋፋት የሚሞክር ማንኛውም የባለሥልጣን ሓላፊነቱን እንዲያስረክብ፣ ማንኛውም ተቋም በዚህ ድርጊት ውስጥ ከተገኘ እንዲዘጋ ማድረግ ያስፈልጋል፡፡ የሃይማኖት ተቋማትም ብዙ ሥራ መሥራት ይጠብቃቸዋል፡፡

        ሕገ መንግሥቱ ይከበር፤ ሞራላችንም ይጠበቅ
/ፍትሕ፣ ኅዳር 22 ቀን 2004 ዓ.ም/
(አንተነህ ደረሰ)

ከተለያዩ የመገናኛ ብዙኀን ለመረዳት እንደቻልነው ኢትዮጵያ በኡች.አይ.ቪ/ኤድስ ላይ የሚካሄደውን 16ው ዓለም አቀፍ ኮንፈረንስ ለማስተናገድ ዝግጅቷን አጠናቃለች፡፡ ከዚህ ኮንፈረንስ ቀደም ብሎ ግን ወንድ ግብረ ሰዶማውያን በአፍሪካ ሕጋዊ ዕውቅናና ከለላ እንዲያገኝ የሚሠሩ ግለሰቦችና ዓለም አቀፍ ተቋማት በመጪው ቅዳሜ(ዛሬ፣ ኅዳር 23 ቀን) በመዲናችን አዲስ አበባ ጉባኤያቸውን ለማካሄድ ዝግጅታቸውን አጠናቀዋል፡፡
ጉባኤው ከአገሪቱ ሕግ አንጻር እንዴት ይታያል? ግብረ ሰዶማዊነት ለእኛ ለኢትዮጵያውያን ምን ማለት ነው? ጉባኤው በሀገራችን መካሄዱ ምን አንድምታ አለው? የሚሉ ጥያቄዎችን ማንሣታችን አይቀርም፡፡ የመጨረሻውን ጥያቄ ለአንባብያን ልተውና የቀሩት ላይ ጥቂት ልበል፡፡
የኢ.ፌ.ዴ.ሪ ሕገ መንግሥት አንቀጽ 27 ንዑስ አንቀጽ 5 ላይ በግልጽ እንደተመለከተው ምንም እንኳን ማንኛውም ሰው የአመለካከት ነጻነት ቢኖረውም የያዘው አመለካከት ለሕዝብ የሞራል ሁኔታ ተፃራሪ ከሆነ አመለካከቱን ከመግለጽ በሕግ ሊገደብ እንደሚችል ደንግጓል፡፡ በሕገ መንግሥቱ መሠረት የወጣው የወንጀል ሕግም በአንቀጽ 643 በግልፅ እንዳስቀመጠው ከግብረ ገብ/ሞራል/ ውጭ የሆኑ ነገሮችን፣ ምርቶችንና ሥራዎችን ሕዝብ በተሰበሰበበት ቦታ ማቅረብ ወይም መግለጽ ወንጀል መሆኑን ይደነግጋል፡፡
መቼም ጉባኤው በግል የሚካሄድ አለመሆኑ ግልጽ ነው፡፡ በጉባኤው ላይም ወንድ ግብረ ሰዶማዊነትን የሚመለከቱ ንግግሮች፣ ጥናታዊ ጽሑፎች፣ በራሪ ወረቀቶችና የመሳሰሉት ሥራዎች መቅረባቸው አይቀርም፡፡ የወንጀል ሕጉ ግብረ ሰዶማዊነት ከሞራል ውጭ መሆኑን፣ በአንቀጽ 629 - 631 ባሉ ድንጋጌዎች የሕዝብን ሞራል በመፃረር የሚፈጸሙ ወንጅሎች በተዘረዘሩበት ምዕራፍ ሥር አስፍሮትና ቅጣትም ጥሎበት ይገኛል፡፡ ሕገ መንግሥቱ ይሁን የወንጀል ሕጉ በጋራ ኢትዮጵያ ውስጥ ግብረ ሰዶምን መፈጸም ብቻ ሳይሆን ግብረ ሰዶምን የሚያበረታቱ አመለካከቶችን ሕዝብ በተሰበሰበበት ቦታ መግለጽ በሕግ የተከለከለ ሆኖ እንገኘዋለን፡፡
ሕጉ ይህን ቢልም ሕግ አስፈጻሚው ወዶና ፈቅዶ የወንድ ግብረ ሰዶማዊነት የሕግ ከለላ ያገኝ ዘንድ የሚታገሉ አካላት ጉባኤያቸውን አመለካከታቸውን መግለጽ ኢ-ሕገ መንግሥታዊ በሆነበት አገራችን ሊያካሂዱ ነው፡፡
ግብረ ሰዶማዊነት በባህላችንም በሃይማኖታችንም የተወገዘ ተግባር ነው፡፡ የትኛውም የኢትዮጵያ ባህል ወይም ሃይማኖት ግብረ ሰዶማዊነትን ይጠየፋል፡፡ ይህን የማይጠየፍ ባህል ወይም ሃይማኖት አለን የሚል አካል ቢኖር እንኳን ከላይ የተጠቀሰውን የሕግ ድንጋጌ ስለሚፃረር ከተጠያቂነት የሚድን አይሆንም፡፡
በጉዳዩ ላይ ከማንም በፊት ድምፃቸውን ያሰሙ ዘንድ የሃይማኖት አባቶች ተጠቃሾች ናቸው፡፡ የሃይማኖት አባቶች ማክሰኞ፣ ኅዳር 19 ቀን 2004 ዓ.ም መግለጫ ለመስጠት የተገናኙ ቢሆንም የጤና ጥበቃ ሚ/ሩ ዶ/ር ቴዎድሮስ አድሓኖም በቦታው በመገኘት የሃይማኖት አባቶችን በማነጋገር መግለጫው ለሌላ ጊዜ እንዲተላለፍ በማድረጋቸው የሃይማኖት አባቶች በጉዳዩ ላይ አንድም ቃል ሳይናገሩ ወደ መጡበት ተመልሰዋል፡፡
ይህ ብዙ ጥያቄዎችን የሚያጭር ተግባር ነው፡፡ የሃይማኖት አባቶች ምን ነካቸው? ለሃይማኖታዊው አስተምህሮ፣ ለነፍሳቸው ያደሩ አይደሉምን? መንግሥት ሌላ ሃይማኖት ሌላ፡፡ ሃይማኖታችን ግብረ ሰዶማዊነትን አይፈቅድም ብለው ጉባኤውን ቢያወግዙ ምናለበት? ዶ/ሩስ ምን ነክቷቸዋል፡፡ ማድረግ ያለባቸው ሕገ መንግሥቱን ማክበርና ማስከበር፣ የሕዝብን ሞራል መጠበቅና ጉባኤው እንዳይካሄድ ማድረግ ነው ወይስ የሃይማኖት አባቶች ጉባኤውን እንዳያወግዙ ማድረግ?...መንግሥት ጉባኤውን ከፈቀደ፣ የሃይማኖት አባቶችም መንግሥትን ፈርተው ዝም ካሉ የሕዝቡን መብት ማን ያስከብር? ድምፁንስ ማን ያሰማለት? ሞራሉንስ ማን ይጠበቅለት?
በመጨረሻ ይህ እላለሁ - ይህ ጉባኤ በአገራችን እንዲካሄድ የፈቀደ አካል አንድ ቀን በሕግ ተጠያቂ፣ በታሪክም ተወቃሽ መሆኑ አይቀርም፡፡ መንግሥት ደጋግሞ እንደሚለው እኔም መንግሥትን እላለሁ፡- “ሕገ መንግሥቱ ይከበር፤ ሞራላችንም ይጠበቅ” ፈጣሪ ኢትዮጵያን ይባርክ፡፡


Post a Comment

Blog Archive

የአቡነ ጳውሎስ "ሐውልተ ስምዕ"

ነጻ ፓትርያርክ ምርጫ ቢሆን ኖሮ ማንን ይመርጡ ነበር? እንበልና ሁሉም ነገር ሥርዓቱን ጠብቆ የተከናወነ የእጩዎች ምርጫ ቢሆን ኖሮ፣ አሁን የምናነሣቸው ጉድለቶች ባይኖሩ ኖሮ፣ 6ኛው ፓትርያርክ እንዲሆን የምትመርጡት ማንን ነበር? (ማሳሰቢያ፦ አሁን ያለው ክፍፍል እና የመንግሥት ተጽዕኖ ባይኖር ኖሮ ተብሎ የሚመለስ ጥያቄ ነው። የምን “ባይኖር ኖሮ ነው” የሚል አስተያየት ካለዎትም እናከብራለን።)