December 3, 2011

የግብረ ሰዶማውያኑ ስብሰባ በተ.መ.ድ የስብሰባ አዳራሽ እየተካሄደ ነው

READ IN PDF.
  • ከ40 - 45 የሚደርሱ ግብረ ሰዶማውያን ከደቡብ አፍሪካ የመጡ ናቸው፤ ያረፉበት ቦታ በምሥጢር ተይዟል::
  • የጁፒተር ዓለም አቀፍ ሆቴሎች አስተዳደር የግብረ ሰዶማውያኑ ስብሰባ በሆቴሉ እንደሚካሄድ የተሰራጨው መረጃ ሐሰት መሆኑን ደንበኞቹ እና አጠቃላይ ሕዝቡ እንዲገነዘቡለት አስታውቋል::
  • የባህል እና ቱሪዝም ሚኒስቴር ሠራተኞች በኢትዮጵያ ሕግ ወንጀል በሆነው ግብረ ሰዶማዊነት ላይ ለሚሰበሰቡ ግለሰቦች ፈቃድ መሰጠቱ ግራ እንዳጋባቸው ገልጸዋል፤ ሚኒስቴር መሥ/ቤቱ ምን እየሠራ እንደ ሆነ በቁጣ ላቀረቡት ጥያቄ ‹‹መፍትሔ መስጠት የሚችሉት የበላይ የመንግሥት አካላት ብቻ እንደሆኑ›› ተገልጦላቸዋል::
  •  መንግሥት በ‹ዝምታ ዲፕሎማሲ› የግብረ ሰዶማውያኑን የቅድመ (ICASA) ስብሰባ ከመከላከል ሲቆጠብ የስብሰባው የኮሚዩኒኬሽን ሓላፊዎች በበኩላቸው በተ.መ.ድ የስብሰባ አዳራሽ እየተካሄደ ስለሚገኘው ‹ሥልጠና› እና ልምድ ልውውጥ የተካተተበት የግብረ ሰዶማውያኑ ቅድመ ጉባኤ የማነቃቂያ ስብሰባ የሚያውቁት ነገር እንደሌለ በመናገር እያደናገሩ ይገኛሉ::
 
(ደጀ ሰላም፤ ኅዳር 23/2004 ዓ.ም፤ ዲሴምበር 3/2011):- አምሸር - AMSHeR/The African Men for Sexual Health and Rights/ የተባለ መቀመጫውን ደቡብ አፍሪካ ያደረገ ድርጅት ከ16“ዓለም አቀፍ የኤች.አይ.ቪ/ኤድስ እና አባላዘር በሽታዎች በአፍሪካ” ቀደም ብሎ “Claim, Scale-up and Sustain” (የራስ ማድረግ፣ ማሳደግ እና ቀጣይነት) በሚል መሪ ቃል ያቀደው የ”MSM and HIV(Men who have sex with Men)” ስብሰባ በተባበሩት መንግሥታት የስብሰባ አዳራሽ እየተካሄደ መሆኑ ተገለጸ፡፡ ነገ ቅዳሜ፣ ኅዳር 23 ቀን 2004 ዓ.ም 200 ያህል ተሳታፊዎች በተገኙበት ይደረጋል የተባለው ስብሰባም ከጠዋቱ 2፡30 ጀምሮ በውሎ እንደሚካሄድ ተጠቁሟል፡፡

ቡድኑ ለዚሁ ስብሰባ ከጥቅምት ወር መጀመሪያ አንሥቶ ግብረ ሰዶማዊ ተሳታፊዎችን ሲያፈላልግ የቆየ ሲሆን በአዲስ አበባም በመጀመሪያ ከ40 - 45 ለሚሆኑ ሰዎች፣ በቀጣይም እስከ 180 ለሚደርሱ እንግዶች መኝታ፣ መስተንግዶ እና መሰብሰቢያ አዳራሽ የሚሆኑ ሆቴሎችን ሲያጠያይቅ መቆየቱ ታውቋል፡፡ በመጨረሻም ድርጅቱ ከኖቨምበር መጨረሻ እስከ ዲሴምበር ሁለት ድረስ ከ40 - 45 ተሳታፊዎች፣ ዲሴምበር 3(ነገ ኅዳር 23 ቀን 2004 ዓ.ም) ደግሞ ከ25 አገሮች የተውጣጡ 200 ግብረ ሰዶማዊ ተሳታፊዎች እንዲሁም በጤና እና ሰብአዊ መብት ላይ ጥናት የሚያቀርቡ ከ15 አገሮች የተውጣጡ ባለሞያዎች(Experts on the health and human rights sexual minorities) የሚገኙበት የቅድመ (ICASA) ስብሰባ ቦሌ ሚሌኒየም አዳራሽ አቅራቢያ በሚገኘው ጁፒተር ዓለም አቀፍ ሆቴል እንደሚካሄድ በድረ ገጹ አስታውቆ ነበር፡፡

በካዛንቺስ አፍሪካ ኢኮኖሚክ ኮሚሽን - ተ.መ.ድ የስብሰባ አዳራሽ አጠገብ እና በቦሌ ሚሌኒየም አዳራሽ አቅራቢያ ዓለም አቀፍ እና ደረጃውን የጠበቀ አገልግሎት የሚሰጡ ሆቴሎች እንዳሉት የገለጸው የጁፒተር ዓለም አቀፍ ሆቴሎች አስተዳደር በበኩሉ ኅዳር 21 ቀን 2004 ዓ.ም ለብዙኀን መገናኛ ባሰራጨው መግለጫ፣ በሆቴሉ የተጠቀሰው ስብሰባ የማይካሄድ ከመሆኑም ባሻገር በተጠቀሰው ቀን የስብሰባ አዳራሾች በሙሉ በሌሎች ተሰብሳቢዎች የተያዘ መሆኑን ገልጧል፤ በተለያዩ የመገናኛ መንገዶች እየተሰራጩ ያሉትን መረጃዎች ደንበኞቹ እና አጠቃላይ ሕዝቡ ሐሰት መሆኑን እንዲገነዘቡለትም በሆቴሉ የሰው ሀብት እና አስተዳደር መምሪያ ሓላፊ አቶ ኢሳይያስ ወልዱ ፊርማ የወጣው ደብዳቤ አሳስቧል፡፡

የዜናው ምንጮች እንደሚያስረዱት፣ ጁፒተር ዓለም አቀፍ ሆቴል፣ ሀገራችን ከኅዳር 24 - 28 ቀን 2004 ዓ.ም ለምታስተናግደው የ(ICASA) ስብሰባ እየመጡ ያሉ እንግዶችን እያስተናገደ ነው፤ መስተንግዶውም በሚስተናገደው ግለሰብ/አካል ሕጋዊነት ላይ እንጂ በመጣበት አጀንዳ ላይ የሚመሠረት እንዳልሆነ፣ በዚህም መሠረት በኦክቶበር ወር አምሸር ለሆቴሉ ጥያቄ ማቅረቡን፣ ይሁንና የጠየቀው ቦታ የተያዘ መሆኑ ሲገለጽለት ዓላማው የሚታወቅ እንዳልነበር፣ ነገር ግን ለግብረ ሰዶማዊ አጀንዳ መሆኑ ቢታወቅ ግን ጉዳዩ በሀገሪቱ ሕግ ወንጀል በመሆኑ ስብሰባው ከተጀመረም በኋላ ቢሆን የመሰረዝ ዕጣ ይገጥመው እንደነበር የሆቴሉ ሓላፊዎች አስረድተዋል ተብሏል፤ አምሸር ከሆቴሉ የጠየቀውን ቦታ ባላገኘበት ሁኔታ ስብሰባው እንደሚካሄድበት በድረ ገጹ ማስታወቁ አግባብ አለመሆኑም ተመልክቷል፡፡

በተያያዘ ዜና የግብረ ሰዶማውያኑ ቅድመ ኮንፈረንስ ስብሰባ እንደሚካሄድ በብዙኀን መገናኛ ከተገለጸ በኋላ ከተለያዩ የኅብረተሰብ ክፍሎች የሚሰነዘረው የተቃውሞ ድምፅ እየበረታ መጥቷል፡፡ ነጋድራስ ጋዜጣ በኅዳር 22 ቀን 2004 ዓ.ም እትሙ እንደዘገበው የባህል እና ቱሪዝም ሚኒስቴር ሠራተኞች የግብረ ሰዶማውያኑን ስብሰባ አጥብቀው እንደሚቃወሙት ገልጸዋል፡፡ የዓለም ኤድስ ቀንን ምክንያት በማድረግ ባለፈው ረቡዕ በብሔራዊ ቴአር አዳራሽ በተዘጋጀው የፓናል ውይይት ላይ የሚኒስቴሩ ሠራተኞች ከዕለቱ የውይይት ርእስ ይልቅ የግብረ ሰዶማውያኑ ጉባኤ በአዲስ አበባ መደረግ እንዳሳሰባቸውና ጉዳዩ የሚመለከተው የባህልና ቱሪዝም ሚኒስቴር በመሆኑ “ምን እየሠራ እንደሆነ እንዲነግረን እንፈልጋለን” ሲሉ ቁጣ በተሞላበት ሁኔታ ጠይቀዋል፡፡

ስለ ኤች.አይ ቪ/ኤድስ የውይይት መነሻ ሓሳብ ለመስጠት መድረክ ላይ የወጡት ከሲቪል ሰርቪስ ዩኒቨርቲ የተወከሉ ግለሰብ በሠራተኞቹ ቁጣ አዘል ጥያቄ ግራ ተጋብተው የተስተዋሉ ሲሆን በጉዳዩ ላይ ደፍሮ ምላሽ ለመስጠት የፈቀደ ሰው ጠፍቶ ነበር፡፡ ቆይቶም ማንነታቸውንና የሥራ ሓላፊነታቸውን ያልገለ ተሳታፊ በመረጃ ደረጃ ሚኒስቴሩ ስለጉዳዩ እንደሚያውቅ ይሁንና ነገሩን የበላይ የመንግሥት አካላት ብቻ እንደሚፈቱት ገልጸዋል፡፡ “ግብረ ሰዶማዊነት በሀገራችን ወንጀል ነው፤ በወንጀል ዙሪያ ለሚሰበሰቡ ፈቃድ መስጠት ግራ ያጋባል፤” ብለዋል ሠራተኞቹ፡፡

ስለ ጉዳዩ በተለያዩ ብዙኀን መገናኛዎች የወጡት የ(ICASA) ስብሰባ ኮሚዩኒኬሽን ሓላፊዎች ምላሽ እንደሚያስረዳው፣ በአንድ በኩል ስለ ስብሰባው ሂደት እንጂ ለስብሰባው የሚመጡት ሰዎች ማንነት እንደማያስጨንቃቸው እየገለጹ በሌላ በኩል ደግሞ በ(ICASA) ስብሰባ ስም ወደ አገሪቱ የገቡ ግለሰቦች በግብረ ሰዶማዊ አጀንዳ ዙሪያ በጠራራ ፀይ/በግላጭ ስለሚያካሂዱት ስብሰባ የሚያውቁት ነገር እንደሌለ በመናገር ሕዝቡን እያምታቱ ይገኛሉ፡፡ ቀደም ሲል መሰል ስብሰባዎች የተካሄዱባቸው አገሮች ከሕዝባቸው ባህል እና እሴት እንዲሁም ከብሔራዊ ሕጎቻቸው ጋራ የማይጣጣሙ ድርጊቶች ፈጽመው በመሄዳቸው በእንግዳ ልማዶች ዘላቂ ጉዳት እንዳገኛቸው እየተዘገበ ይገኛል፡፡
በአፍሪካ ኢትዮጵያን ጨምሮ 37፣ በዓለም በአጠቃላይ 80 ያህል አገሮች ግብረ ሰዶማዊነትን በሕጎቻቸው በወንጀል ድርጊትነት ፈርጀው የደነገጉ ቢሆንም ከድርጊቱ ጋራ በተያያዘ እንደ ብሪታኒያ ያሉ ለጋሽ አገሮች የርዳታቸው ቅድመ ሁኔታ በማድረግ ግብረ ሰዶማዊነትን ከግለሰብ ሰብአዊ መብት ጋራ በማያያዝ ጫና በመፍጠር ላይ ናቸው፡፡Post a Comment

Blog Archive

የአቡነ ጳውሎስ "ሐውልተ ስምዕ"

ነጻ ፓትርያርክ ምርጫ ቢሆን ኖሮ ማንን ይመርጡ ነበር? እንበልና ሁሉም ነገር ሥርዓቱን ጠብቆ የተከናወነ የእጩዎች ምርጫ ቢሆን ኖሮ፣ አሁን የምናነሣቸው ጉድለቶች ባይኖሩ ኖሮ፣ 6ኛው ፓትርያርክ እንዲሆን የምትመርጡት ማንን ነበር? (ማሳሰቢያ፦ አሁን ያለው ክፍፍል እና የመንግሥት ተጽዕኖ ባይኖር ኖሮ ተብሎ የሚመለስ ጥያቄ ነው። የምን “ባይኖር ኖሮ ነው” የሚል አስተያየት ካለዎትም እናከብራለን።)