December 17, 2011

በስልጢ ወረዳ የቆቶ ቅድስት አርሴማ ቤተ ክርስቲያን መቃኞ ጉልላት እና ጣሪያ በወረዳው ፖሊስ ተነቅሎ ከተወሰደ በኋላ የግድግዳው ዕንጨት በሙስሊም ተማሪዎች ተቃጥሎ ተቀበረREAD IN PDF.
  • 200 የወረዳው ምእመናን ተወካዮች ወደ ሐዋሳ በማምራት ለክልሉ ርእሰ መስተዳድር ረዳት ጽ/ቤት አቤቱታቸውን አቅርበዋል፤ በሁኔታው ያነቡት የሀ/ስብከቱ ሊቀ ጳጳስ ብፁዕ አቡነ ቀሌምንጦስ በስፍራው በመገኘት ምእመናንን አጽናንተዋል፤ በጉዳዩ ላይም ከወረዳ አስተዳደር እና ፖሊስ እንዲሁም ከክልሉ የፍትሕ እና ጸጥታ ዘርፍ ሓላፊዎች ጋራ እየመከሩበት ነው
  • መቃኞው የተሠራበት ቦታ የቤተ ክርስቲያን ባሕረ ጥምቀት ይዞታ ስለ መሆኑ የደቡብ ክልላዊ መንግሥት ርእሰ መስተዳድር ጽ/ቤት፣ በክልሉ ግብርና እና ገጠር ልማት ቢሮ የተፈጥሮ ሀብትና የገጠር መሬት አስተዳደር ዘርፍ፣ የስልጢ ወረዳ አስተዳደር ጽ/ቤት እና የወረዳው ፍ/ቤት እንዲሁም የቆቶ ባሎሶ ቀበሌ አስተዳደር ጽ/ቤት በየደረጃው በሰጧቸው ውሳኔዎች አረጋግጠው ነበር
  • በውድቅት ሌሊት የተወሰደው የወረዳው ፖሊስ አፍራሽ ግብረ ኀይል ሕገ ወጥ ርምጃ የቤተ ክርስቲያኒቱ አስተዳደር በፍ/ቤት ውሳኔ ላይ ይግባኝ በጠየቀበትና የአፈጻጸም መመሪያ ባልተሰጠበት የተፈጸመ ሲሆን፣ ዛሬ ጠዋት ግድግዳውን በማፈራረስ ያቃጠሉት ሙስሊም ተማሪዎች ደግሞ በወረዳው ክርስቲያኖች ላይ ጅሃድ ባወጀው ጀማል ሽኩሪ በተባለ ጽንፈኛ የተቀሰቀሱ ናቸው
  • በቅድስት አርሴማ መቃኞ ሥራ ክርስቲያኖችን የረዱ የከተማው ሙስሊም አዛውንቶች የጀማል ሽኩሪን የጅሃድ ጥሪ ተቃውመዋል
  • በስልጤ ዞን ያሉት የሌሎች 20 አብያተ ክርስቲያን ይዞታ ዋስትና እያሰጋ ባለበት በአሁኑ ወቅት የአጎራባች ከተሞች ምእመናን ለስልጤ ወረዳ ምእመናን ያላቸውን አጋርነት በተለያዩ ድጋፎች በመግለጽ ላይ ናቸው
  • በዞኑ ዝቅተኛ ኑሮ ያላቸውን ኦርቶዶክሳውያን ክርስቲያኖችን በተለይ ሴቶችን ሆነ ብሎ በጋብቻ እያጠመዱ በማስለም የኦርቶዶክሳውያን ክርስቲያኖችን ቤተሰብ እና ቁጥር ማመንመን፣ ማዕተባቸውን እንዲበጥሱ ወይም እንዲሸፍኑ ማስገደድ፣ በሥራ ቅጥር እና በከፍተኛ ሓላፊነት አያያዝ ወቅት አድልዎ ማድረግ እና ክርስቲያን ፖሊሶችን ሳይቀር በስብሰባ ወቅት ማግለል፣ በአጠቃላይ ስልጤ እስላማዊ እንጂ ክርስቲያናዊ ማንነት ሊኖረው እንደማይችል፣ ክርስቲያን ምእመን በዞኑ በየትኛውም ደረጃ የመንግሥት ሥልጣን መያዙ ሓራም እንደሆነ ተደርጎ የሚካሄደው ተጽዕኖ እና ቅስቀሳ ከጊዜ ወደ ጊዜ እየከፋ መምጣቱ ተመልክቷል
  (ደጀ ሰላም፤ ኅዳር 19/2004 ዓ.ም፤ ኖቬምበር 29/2011):- በከምባታ ሐዲያ ጉራጌ እና ስልጤ አህጉረ ስብከት ስልጤ ዞን ስልጢ ወረዳ ቆቶ ባሎሶ ቀበሌ ቆቶ መንደር የምትገኘው የቆቶ ቅድስት አርሴማ ቤተ ክርስቲያን መቃኞ ቤት ጉልላት እና ጣሪያ በስልጢ ወረዳ(ቅበት) ፖሊስ ግብረ ኀይል ተነቅሎ መወሰዱንና የመቃኞው ግድግዳ ዕንጨት እና የቅጽሩ አጥር የአንድ ጽንፈኛ ግለሰብን የጅሃድ ጥሪ ተቀብለዋል በተባሉ ጥቂት የቦዜ አንደኛ ሳይክልና መለስተኛ ሁለተኛ ሳይክል ት/ቤት ሙስሊም ተማሪዎች ዛሬ ረፋድ ላይ ተነቃቅሎ በጉድጓድ ውስጥ ከተጣለ በኋላ እንዲቃጠል መደረጉ ተገለጸ፡፡

  ለከተማው ሴት ተማሪዎች ኒቃብ በማደል እንዲሸፋፈኑ ይቀሰቅሳል የተባለው ጀማል ሽኩሪ የተባለው አክራሪ ባለሀብት ግለሰብ እሑድ፣ ኅዳር 17 ቀን 2004 ዓ.ም ቀትር ላይ በወረዳው ክርስቲያኖች ላይ ጅሃድ እንዲደረግ ጥሪ ማስተላለፉ የተዘገበ ሲሆን 30,000 ብር የወጣበት የቆቶ ቅድስት አርሴማ መቃኞ በሚሠራበት ወቅት እገዛ ያደረጉ አዛውንት ሙስሊሞች ጥሪውን ተቃውመዋል ተብሏል፡፡ በጽንፈኛው ግለሰብና በልጁ ቅስቀሳ የተነሣሡ ጥቂት ተማሪዎች ግን ዛሬ በቦዜ ት/ቤት ዳይሬክተር እና በወረዳው ትምህርት ጽ/ቤት ሓላፊ እየተመሩ ወደ ወረዳው አስተዳደር ጽ/ቤት በመሄድ ሥራው ተጠናቆ የቅድስት አርሴማን ታቦት ለማስገባት ዝግጅት የተደረገበትን መቃኞ የውጭ አጥር እና የግድግዳ ዕንጨት ዛሬ፣ ማክሰኞ ኅዳር 19 ቀን 2004 ዓ.ም በመነቃቀል ጉድጓድ ውስጥ ከጣሉ በኋላ ማቃጠላቸው ተነግሯል፡፡

  ከተማሪዎቹ ጠብ አጫሪና ሓላፊነት የጎደለው ድርጊት ቀደም ሲል ባለፈው ሳምንት ዐርብ፣ ኅዳር 15 ቀን 2004 ዓ.ም ሌሊት፣ ‹‹ቦታው ባሕረ ጥምቀት እንጂ የቤተ ክርስቲያን መሠረት እና ጉልላት የሚጣልበት አይደለም፤ ማንኛውም ግንባታ፣ አጥር ወይም ቤት መሰል ነገር ማቆም፣ ከመንግሥት አካል ፈቃድ ሳይሰጥ መሥራት ሕገ ወጥ ነው›› በሚል የስልጤ ወረዳ ፖሊስ ጽ/ቤት ግብረ ኀይል በማሰማራት የመቃኞውን ጉልላት እና ጣሪያ ከነቃቀለ በኋላ ወደ ፖሊስ ጣቢያው መውሰዱ ተገልጧል፡፡ የፖሊስ ማሳሰቢያ/ ማስጠንቀቂያ ሁለት ጊዜ የተሰጠ ሲሆን በድጋሚ የተሰጠው ማስጠንቀቂያ ‹‹እየተገነባ ያለው ቤተ ክርስቲያን መሰልና የአጥር ግንባታ የኅብረተሰብን መተላለፊያ መንገድ በመዝጋት፣ የሕዝብ እና የመንግሥት መሬት በመውረር የተፈጸመ ነው›› በማለት የመቃኞ ሥራው ሕገ ወጥ እንደሆነ የሚገልጽ ነበር፡፡

  ይሁንና በዚሁ ጉዳይ በከሳሽ ዐቃቤ ሕግ እና በተከሳሽ ቤተ ክርስቲያን መካከል ከቆቶ ባሎሶ ቀበሌ ማኅበራዊ ፍ/ቤት ጀምሮ እስከ ሆሳዕና ከፍተኛ ፍ/ቤት በደረሰው የይዞታ ክርክር ቦታው ‹‹መንግሥታዊ ያልሆነ /የኦርቶዶክስ/የእምነት ቦታ›› የሚል ማረጋገጫ የተሰጠው መሆኑን ሰነዶች ያመለክታሉ፡፡ የቆቶ ባሎሶ ቀበሌ ማኅበራዊ ፍ/ቤት ‹‹መረጃ ስለ መስጠት›› በሚል ርእስ በቀን 5/52001 ዓ.ም ለስልጢ ወረዳ ሰበካ ጉባኤ ጽ/ቤት በጻፈው ደብዳቤ፡- በሰሜን የጋፎሬ ወንዝ፣ በደቡብ የእንዳለ ረጀቦና የሼሕ ቃሲም መቃብር፣ በምሥራቅ የባጃ ገደል፣ በምዕራብ የመኪና መንገድ የሚያዋስነው ሁለት ሄክታር መሬት የኦርቶዶክስ እምነት ተከታዮች የጥምቀተ ክርስቶስ ማክበሪያ መሆኑን ገልጧል፡፡

  ሁለት ሄክታር ስፋት ያለው ይኸው ስፍራ ከ1938 ዓ.ም ጀምሮ ዛሬ በአንድ የሰበካ መንፈሳዊ ጉባኤ አስተዳደር ሥር የሚገኙት የአገታ ቅድስት ማርያም እና ቆቶ ቅዱስ ጊዮርጊስ አጥቢያ አብያተ ክርስቲያን በዓለ ጥምቀትን የሚያከብሩበት የባሕረ ጥምቀት ቦታ እንደነበር ተዘግቧል፡፡ የውዝግቡ መነሻ የባሕረ ጥምቀት ቦታው ሸምሱ አወል ለተባሉ ኢንቨስተር ጠጠር እና ኮረት ማምረቻ እንዲሆን ሕገ ወጥ በሆነ መንገድ በዞኑ መሰጠቱ እንደሆነ የአጥቢያው ምእመናን አስረድተዋል፡፡

  የቤተ ክርስቲያን አስተዳደር የዞኑ አስተዳደር ጽ/ቤት የባሕረ ጥምቀቱን ቦታ አሉስታዝ ኢንዱስትሪያል ግሩፕ ለተባለው ድርጅት በሕገ መንገድ መስጠቱ አግባብ አለመሆኑን በመጥቀስ ለወረዳው አስተዳደር ጽ/ቤት አመልክቷል፡፡ በዚህም መሠረት በቁጥር ስወኢ /712/2000 በቀን 08/05/2000 የወረዳው አስተዳዳር ጽ/ቤት በጻፈው ደብዳቤ ቦታው የኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያን የአምልኮ ቦታ በመሆኑ በቦታው ላይ እየተካሄደ ያለው ግንባታ እንዲነሣና የተፈጠረው ስሕተት እንዲታረም ያሳስባል፤ ነገር ግን ውሳኔው ተግባራዊ ባለመሆኑ የቤተ ክርስቲያን አስተዳደር ለክልሉ የርእሰ መስተዳድር ጽ/ቤት ያመለክታል፡፡

  የርእሰ መስተዳድሩ ጽ/ቤት በቁጥር ደኢ/መንግ/542/00 በቀን 14/06/2000 ዓ.ም ለስልጤ ዞን ዋና አስተዳዳሪ ጽ/ቤት/ወራቤ/ በጻፈው ደብዳቤ፡- ‹‹ቦታውን ቤተ ክርስቲያኒቱ ለባሕረ ጥምቀት በዓል ማክበሪያነት ስትጠቀምበት የነበረ ከሆነ በምእመናኑና በኢንቨስትመንቱ መካከል አላስፈላጊ ግጭት እንዲፈጠር ምክንያት ስለሚሆን፣ መንግሥት ደግሞ ሁለቱንም ተቋማት ሕግና ደንቡ በሚፈቅደው መሠረት ሰላማዊ በሆነ መንገድ የመምራት ሓላፊነት ያለበት ስለሆነ የዞኑ አስተዳደር ለጉዳዩ ትኩረት ሰጥቶ ሕጋዊ መፍትሔ እንዲሰጥ እናሳስባለን›› የሚል ደብዳቤ ይጽፋል፤ ቆይቶም የክልሉ ግብርናና ገጠር ልማት ቢሮ የተፈጥሮ ሀብትና የገጠር መሬት አስተዳደር ዘርፍ ቀደም ሲል በቆቶ ባሎሶ ቀበሌ ማኅበራዊ ፍ/ቤት ዳኞች የተላለፈውን የባሕረ ጥምቀቱን ወሰን በመለያ ቁጥር 0045 በሰጠው ምስክር ወረቀት በማጽናት ቦታው የቤተ ክርስቲያን ይዞታ መሆኑን ያረጋግጣል፡፡

  በዚህም መሠረት በ‹ኢንቨስተሩ› እና በቤተ ክርስቲያኑ አስተዳደር መካከል በሁከት ይወገድልኝ በተመሠረተው ክስ የስልጢ ወረዳ ፍ/ቤት በመዝገብ ቁጥር 05681 በቀን 21/11/2003 ዓ.ም ‹‹ጉዳዩ እስኪጣራ ማንኛውም ነገር እንዳይሠራና አሁን ባለበት ሁኔታ እንዲቆይ›› ሲል ያስተላለፈውን የዕግድ ትእዛዝ በማንሣቱ የአጥር እና የመቃኞው ሥራ ባለፈው ዓመት መጨረሻ እንደተካሄደ ተገልጧል፡፡ ይሁንና ከላይ በተጠቀሱት አካላት የሚሰጡ ውሳኔዎችን በአፈጻጸም ሂደት ከመገልበጥ እና ከማጓተት ወደ ኋላ ያላሉት አንዳንድ የወረዳና የዞን ባለሥልጣናት ይብሱኑ አቋማቸውን ቀይረው፣ ‹‹ቦታው ክርስቲያኖች በዓመት አንድ ጊዜ ጥምቀት የሚያከብሩበት፣ ሙስሊሞች በዓመት ሁለት ጊዜ የሚሰግዱበት የወል ቦታ ነው›› በማለት ቦታው ለሁለት እኩል ተከፍሎ እንዲሰጥ ሐሳብ ያቀርባሉ፡፡

  ሙስሊሞቹ በዓመት ሁለት ጊዜ የሚሰግዱት በቦዜ ት/ቤት ግቢ ሆኖ ሳለ ይህን የፈጠራ ታሪክ ማቅረባቸው ጥንቱንም የኢንቨስተር ተብዬው ዓላማ ልማት/ኢንቨስትመንት/ እንዳልነበር የሚያሳይ ነው፡፡ ይህንንም ፈጠራ ከወረዳው አስተዳደር እና ፍ/ቤት ጀምሮ በቀና አስተሳሰብ እስከ ወረዳ ከተማው ድረስ እየተመላለሱ ይዞታው የቤተ ክርስቲያን መሆኑን ለማሳመን ሲጥሩ የቆዩትን የቆቶ ባሎሶ ቀበሌ ሊቀ መንበርንም ጭምር ለማሳመንም ችለዋል፡፡ በዚህም ሳቢያ ክሱ ዳግመኛ በመንቀሳቀሱ በወረዳው የአስተዳደርና የፍትሕ አካላት ላይ አመኔታ ያጡት አገልጋዮች እና ካህናት ማስረጃቸው ከመንግሥት አስፈጻሚ አካላት ተጽዕኖ ነጻ በሆነ ፍ/ቤት ታይቶ እንዲወሰንላቸው እስከ መጠየቅ ከመጓዛቸውም በላይ እስከ ከፍተኛ ፍ/ቤት እና ጠቅላይ ፍ/ቤት ሰበር ሰሚ ችሎት አድርሷቸው ነበር፤ በቃል በተሰጣቸው ምክርም ማስረጃዎቻቸው አስተማማኝ መሆናቸውንና ችግር ካጋጠማቸው በይግባኝ ደረጃውን ጠብቀው እንዲመጡ የሚመክር ነበር፡፡

  ስለሆነም ባለፈው ሳምንት ረቡዕ፣ ኅዳር 13 ቀን 2004 ዓ.ም፣ በወረዳው ፍ/ቤት ቀርበው የይዞታ ማረጋገጫ ማስረጃዎቻቸውን ያቀረቡ ሲሆን በአንጻሩ ዐቃቤ ሕግ ያቀረባቸው የሙስሊሞቹ ምስክሮች ከሚባለው ቦታ ጋራ ግንኙነት ስለሌለው ቦታ ምስክርነት ሲሰጡ መደመጣቸው ተዘግቧል፤ ዐርብ፣ ኅዳር 15 ቀን 2004 ዓ.ም በፍ/ቤቱ የተሰጠው ውሳኔ ግን የተሠራው መቃኞ እንዲፈርስ የሚያዝዝ ነበር፤ ውሳኔው ዕለቱኑ ይግባኝ የተጠየቀበት ቢሆንም የፍርድ ሂደቱ ባልተጠናቀቀበትና የውሳኔ አፈጻጸም ባልተሰጠበት ሁኔታ የወረዳው ፖሊስ ጣቢያ ኅዳር 15 ለ16 አጥቢያ ግብረ ኃይል በማሰማራት ማፈራረስ መጀመሩ ተመልክቷል፡፡

  በዚህ ሳምንት ሰኞ፣ ኅዳር 18 ቀን 2004 ዓ.ም የከተማው ምእመናን ተወካዮች የሆኑ ቁጥራቸው 200 የሚሆኑ ምእመናን በአምስት መኪና ወደ ሐዋሳ ማልደው በመጓዝ ከደቡብ ክልል ርእሰ መስተዳድር ፕሬዝዳንት ጽ/ቤት ረዳት/ተወካይ ጋራ መነጋገራቸው ታውቋል፡፡ ዛሬ ረፋድ ላይ በይዞታው ላይ የተፈጸመውን ሕገ ወጥ ተግባር ተከትሎ ደግሞ ምእመናን በአገታ ቅድስት ማርያም ቤተ ክርስቲያን ተሰብስበው የዋሉ ሲሆን የሀ/ስብከቱ ሊቀ ጳጳስ ብፁዕ አቡነ ቀሌምንጦስ ከአዲስ አበባ ተጉዘው ቀትር ላይ በአጥቢያ ቤተ ክርስቲያኑ በመድረስ ምእመኑን አጽናንተዋል፤ ከወረዳ አስተዳደር ጽ/ቤት እና ከፖሊስ ጣቢያ ሓላፊዎች ጋራም እየተነጋገሩ መሆናቸው ተዘግቧል፡፡

  ባለሥልጣናቱ በሃይማኖት ስም በክርስቲያኖች ላይ የሚያደርጓቸው ግልጽ እና ስልታዊ ጫናዎች በወረዳ ከተማው/ቀበት/ ሳይወሰን ከከተማዋ ውጭ ሦስት ሰዓት መንገድ ርቆ በሚገኘው ኤሎስ ቅዱስ ሚካኤል፣ ግራር፣ ዳሎቻ/ሳንኩራ መድኃኔዓለም በሚባሉ ገጠር ቀበሌዎች/ሰበካዎች/ ጠንክሮ እንደሚታይ ታዛቢዎች ተናግረዋል፡፡ በኤሎስ ቅዱስ ሚካኤል ክርስቲያን ሕፃናትን ‹‹በዓለም ላይ ኢስላም ብቻ ነው ያለው፤ እናንተ ብቻ ናችሁ ክርስቲያን ሆናችሁ የቀራችሁት›› በሚሉ ማግባቢያዎች የማስለም፣ በተመሳሳይ መንገድ በግራር እንደ ጽዋ እና ዝክር ያሉ ክርስቲያናዊ ትውፊቶችን የማስተው ጥረቶች እንደሚደረጉ ተጠቁሟል፡፡

  በሳንኩራ መድኃኔዓለም በሚገኘውና ‹‹አማራ ሰፈር›› ተብሎ በሚታወቀው አካባቢ ደግሞ በቅጥር ወቅት በክርስቲያኖች ሃይማኖታዊ መገለጫዎች (ማዕተብ) ላይ እንዳያሳዩ/እንዲበጥሱ ጫና በመፍጠር፣ በኑሮ አቅማቸው ዝቅተኛ የሆኑ (በተለይ ሴቶችን) በማግባት እምነታቸውን የማስቀየርና ቁጥራቸውን የማመንመን ስልት ጎልቶ እንደሚታይ ተነግሯል፡፡

  በዚህ አካሄዳቸው በመተማመን ይመስላል 20 ያህል አጥቢያ አብያተ ክርስቲያን ባሉበት የስልጤ ዞን አንዳንድ ባለሥልጣናት የዞኑ ነዋሪ መቶ በመቶ ሙስሊም መሆኑን ለመናገር የማያፍሩት፡፡ ለእነርሱ በዞኑ ውስጥ ክርስቲያን ምእመን የመንግሥት ባለሥልጣን መያዙ ‹ሃራም› ሲሆን የስልጤም ሃይማኖታዊ ማንነትም እስላማዊ ብቻ ከመሆን ውጭ ሌላ ሊሆን አይችልም፡፡ ይህም ፍጹም የተሳሳተ አቋማቸው አንድም ሕገ መንግሥቱ ሃይማኖትንና መንግሥትን በመለያየት ያስቀመጠውን ዐብይ ድንጋጌ የሚጥስ፣ ዳግመኛም ሰው በነጻነት የመረጠውን ሃይማኖት ለማራመድ ያለውን ነጻነት የሚደረምስ አቋም እንዲያራምዱ አድርጓቸዋል፡፡

  በጥቅሉ ግን ጥቂት የማይባሉ ጥብቅ ፕሮቴስታንታዊ እምነት አራማጆች ባሉበት በሃዲያ እና እምነትን ከጎሳዊ ማንነት ጋራ ያጣመረ እስላማዊ አክራሪነት እየጎላ በመጣበት በስልጤ የሚገኘው የብፁዕ አቡነ ቀሌምንጦስ አህጉረ ስብከት የተጠናከረ ድጋፍና እንቅስቃሴ እንደሚያሻው የተገለጠ እውነት ነው፡፡

  ቸር ወሬ ያሰማን፣
  አሜን


Post a Comment

Blog Archive

የአቡነ ጳውሎስ "ሐውልተ ስምዕ"

ነጻ ፓትርያርክ ምርጫ ቢሆን ኖሮ ማንን ይመርጡ ነበር? እንበልና ሁሉም ነገር ሥርዓቱን ጠብቆ የተከናወነ የእጩዎች ምርጫ ቢሆን ኖሮ፣ አሁን የምናነሣቸው ጉድለቶች ባይኖሩ ኖሮ፣ 6ኛው ፓትርያርክ እንዲሆን የምትመርጡት ማንን ነበር? (ማሳሰቢያ፦ አሁን ያለው ክፍፍል እና የመንግሥት ተጽዕኖ ባይኖር ኖሮ ተብሎ የሚመለስ ጥያቄ ነው። የምን “ባይኖር ኖሮ ነው” የሚል አስተያየት ካለዎትም እናከብራለን።)