November 15, 2011

የመ/ር ዘመድኩን በቀለ መዝሙር ቤት እና መኖሪያ ቤት ብርበራ ተካሄደበት


  • ዛሬ የመከላከያ መልሱንና ክርክሩን ያቀርባል
  • ጠቅ/ቤተ ክህነት ክሱ ተቋርጦ መዝገቡ እንዲመለስ ፍትሕ ሚ/ርን ጠይቋል
  • እነበጋሻው መ/ር ዘመድኩንን በተጨማሪ ክስ ለማስቀጣት፣ “እኛን አጥፍቶ እርሱ አይቀመጥም” በሚልም ከሀገር እንዲወጣ የተለያዩ የማሸማቀቂያ ዘመቻዎችን እያካሄዱ ነው
  • “የምትለውን ሕግ አብረን እናየዋለን፤ መቃብርህን ቆፍረሃል፤ 12 ሆነን ንብታችንን ሸጠንም ቢሆን አንተን ጉድጓድ እንከታሃለን፤ ከምትገባበት ጉድጓድ ማን እንደሚያወጣህ እናያለን፤”  (የፊደል ሬስቶራንት ባለቤት መ/ር ዘመድኩንን ያስፈራሩበት የዛቻ ቃል ድምፅ)፤
(ደጀ ሰላም፤ ኅዳር 5/2004 ዓ.ም፤ ኖቬምበር 15/2011/ READ IN PDF)፦ ከአርማጌዶን ቪሲዲ ጋር በተያያዘ “እኛን አጥፍቶ እርሱ አይቀመጥም” እያሉ በመ/ር ዘመድኩን በቀለ ላይ በመፎከር ላይ ከሚገኙት ጥራዝ ነጠቅ የተሐድሶ ኑፋቄ አቀንቃኞች አንዱ የሆነው ታሪኩ አበራ እና ተባባሪዎቹ ሊመሥርቱ ካሰቡት ተጨማሪ ክስ ጋር በተያያዘ የመ/ር ዘመድኩን ጌልጌላ መዝሙር ቤት እና መኖሪያ ቤት ጥቅምት 30 ቀን 2004 ዓ.ም ቀትር ላይ በፖሊስ ብርበራ እንደተካሄደበት ተገለጸ፡፡


በዕለቱ በተካሄደው ብርበራ ፖሊስ 430 የቁጥር አንድ አርማጌዶን ካሴት ጭኖ መውሰዱ ታውቋል፡፡ በብርበራው ሂደት ታሪኩ የመዝሙር ቤቱ የማባዣ ማሽንም እንዲወሰድ ፖሊሶችን በመወትወትና የመዝሙር ቤቱን ሌሎች ንብረቶች በጩኸት በመገለባበጥ ያደረገው ጥረት አልተሳካለትም፡፡ በተመሳሳይ ቀን ፖሊስ ወደ መ/ር ዘመድኩን መኖሪያ ቤት በማምራት ብርበራ ያካሄደ ሲሆን ከተመደበበት ደብረ ናዝሬት ቅዱስ ዮሴፍ ቤተ ክርስቲያን ሰባኬ ወንጌልነት የተባረረው ታሪኩ በተመሳሳይ አኳኋን የመ/ር ዘመድኩንን የሰባት እና የዘጠኝ ዓመት ሕፃናት በማስፈራራት ጭምር ቤቱን ለማተራመስ ያደረገው ሙከራ በፖሊስ በተሰጠው ማስጠንቀቂያ ዳግመኛ ሳይሳካለት ቀርቷል - በስልክና በሌሎች የተለያዩ መንገዶች የሚሰነዘርበትን ዛቻና ማስፈራሪያ ከባለቤቱ ጋር በጽንዓት ተቋቁሞ ተጋድሎውን የቀጠለው መ/ር ዘመድኩን ብርበራው በሚካሄድበት ሰዓት በመኖሪያ ቤቱ እንዳልነበር ተገልጧል፡፡

የፖሊስ ብርበራ እነ ታሪኩ፣ በጋሻው፣ ትዝታው፣ ሀብታሙ ሽብሩ ከአርማጌዶን ቪሲዲ ጋር በተያያዘ በመ/ር ዘመድኩን ላይ ለመመሥረት ላሰቡት ተጨማሪ ክስ ማስረጃ ለማሰባሰብ ያለመ እንደ ሆነ ተዘግቧል፡፡ በጥቅምት ቅዱስ ሲኖዶስ ምልአተ ጉባኤ በሕገ ወጥነታቸውና በፕሮቴስታንታዊ ተሐድሶ ኑፋቄ አቀንቃኝነታቸው የእግድ ውሳኔ የተላለፈባቸው እነበጋሻው ሰሞኑን በተጓዙበት ዱባይ ከፍተኛ ተቃውሞ እንደገጠማቸው የተገለጸ ሲሆን የተባበሩት ዐረብ ኤምሬቶች ሊቀ ጳጳስ ብፁዕ አቡነ ድሜጥሮስም ሕገ ወጦቹ (20 ግለሰቦች) ከኢትዮጵያ ወደ ሀ/ስብከታቸው ለማለፍ ፈቃድ እንዳይሰጣቸው ለኢሚግሬሽንና ዜግነት ጉዳይ መምሪያ ደብዳቤ ጽፈው እንደ ነበር ተዘግቧል፡፡

ይሁንና እነበጋሻው ወ/ሮ እጅጋየሁ በየነንና ከእርሳቸው ጋር በዝምድና እና በጥቅም የተቋጠሩ አንዳንድ ደካማ እና ጥቅመኛ የመንግሥት ባለሥልጣናትን በመያዝ ባደረጉት ጥረት የብፁዕ አቡነ ድሜጥሮስ ጥያቄ ተፈጻሚነት ሳያገኝ እንደ ቀረ ተገልጧል፡፡ እነበጋሻው በመ/ር ዘመድኩን ላይ ለመመሥረት ያሰቡት ተጨማሪ ክስም ከእነዚህ ባለሥልጣናት እገዛ እና በፍትሕ አካላቱም (ዐቃቤ ሕግ) ላይ ግፊት የሚደረግበት እንደ ሆነ ተመልክቷል፡፡

ከዚህም ባሻገር ከሕገ ወጦቹ ጋር ቁጥር አንድ የጥቅም ተካፋይ በመሆን በአጋርነት የተሰለፉት የፊደል ሬስቶራንቱ ኤፍሬም ኤርምያስ ወደ መ/ር ዘመድኩን ስልክ በመደወል፣ “የምትለውን ሕግ አብረን እናየዋለን፤ መቃብርህን ቆፍረሃል፤ 12 ሆነን ንብታችንን ሸጠንም ቢሆን አንተን ጉድጓድ እንከታሃለን፤ ከምትገባበት ጉድጓድ ማን እንደሚያወጣህ እናያለን፤” በማለት የዛቻ እና የማስፈራሪያ ቃል ሲናገሩ ተደምጠዋል፡፡ እኚህ ግለሰብ “የሰባኪው ሕጸጽ” የሚል መጽሐፍ በመጻፋቸው ከመ/ር ዘመድኩን ጋር በስም ማጥፋት ወንጀል በበጋሻው ደሳለኝ በተከሰሱት በዲያቆን ደስታ ጌታሁን ላይ ጥቅምት 20 ቀን 2004 ዓ.ም በዋለው ችሎት ሦስተኛ የዐቃቤ ሕግ ምስክር ሆነው ቀርበው የነበሩ ናቸው፡፡

ቀደም ሲል የመ/ፓ/ጠ/ቤ/ክ የስብከተ ወንጌልና ሐዋርያዊ ተልእኮ መምሪያ ጸሐፊ አሁን  የገዳማት አስተዳደር መምሪያ ጸሐፊ ሆነው በመሥራት ላይ የሚገኙት ዲያቆን ደስታ ጌታሁን ሦስተኛው የከሳሽ ምስክር አቶ ኤፍሬም ኤርምያስ፣ እነበጋሻው በሚሌኒየም አዳራሽ አዘጋጅተውት በነበረው ‹ጉባኤ› ያጋበሱትንና ሪፖርት እንዲያደርጉ ይፈለግባቸው የነበረውን ብር 940,000 ይዘው የተሰወሩ፣ በዚህም ሳቢያ በእርሳቸው ጸሐፊነት የስብከተ ንጌልና ሐዋርያዊ ልዕኮ መምሪያ ተደጋጋሚ ደብዳቤ ሲጽፍባቸውና በሚዲያ ጥሪ ቢደረግላቸውም ያልቀረቡ በመሆኑ ለምስክርነት እንደማይበቁ የተናገሩባቸው ናቸው፡፡

በዕለቱ (ጥቅምት 20 ቀን 2004 ዓ.ም) ለራሱ ክስ የዐቃቤ ሕግ የመጀመሪያ ምስክር ሆኖ የቀረበው በጋሻው ስለሥራው ሲጠይቅ “ወንጌላዊ ነኝ” ብሎ መመለሱ ተዘግቧል፡፡ ቤተ ክርስቲያን እንዲህ ያለ ስመ ማዕርግ ይሁን የሥራ መደብ የሌላት በመሆኑ በጋሻው በትክክል የየትኛው ቤተ ክርስቲያን ሰባኪ እንደሆነ በዲያቆን ደስታ ተጠይቆ ነበር፡፡ ነገር ግን በዐቃቤ ሕግ ጣልቃ ገብነት በጋሻው ጥያቄውን ሳይመልስ ራሱን በመስቀለኛ ጥያቄ ከማጋለጥ ተርፏል፡፡ ቀደም ሲል ክሱ በዕርቅና ይቅርታ እንዲነሣላቸው ከእነ በጋሻው ጋር ስለ መደራደራቸው የቀረበባቸው ዘገባ ከእውነት የራቀ በመሆኑ መታረም እንደሚገባው ዲያቆን ደስታ መግለጻቸው ተመልክቷል፡፡

በዚሁ ቀን ከሰዓት በኋላ በጋሻው ደሳለኝ በስም ማጥፋት ወንጀል በመሠረተውና በቢሮ በታየው የመ/ር ዘመድኩን በቀለ መዝገብ ዐቃቤ ሕግ መ/ር ዘመድኩን ለማራኪ መጽሔት የሰጠውን ቃለ ምልልስ በማስረጃነት አቅርቧል፡፡ ራሱ በጋሻው ደሳለኝም የዐቃቤ ሕግ ምስክር ሆኖ ቀርቦ ነበር፡፡ በመጽሔቱ በተስተናገደው ቃለ ምልልስ ላይ፣ “መ/ር ዘመድኩን ደንቆሮ ብሎ ሰድቦኛል” ያለው በጋሻው የተናገረው ቃል ከየት እንዳገኘው /በርግጥም በቃለ ምልልሱ ውስጥ ስለመኖሩ/ በማሳየት እንዲያረጋግጥ በመ/ር ዘመድኩን ጠበቃ ጌትነት የሻነህ ሲጠይቅ፣ “አይ፣ መጽሔቱ ላይ አይደለም፤ ሌላ ቦታ ነው፤ ፍ/ቤቱ ይህን ቃሌን ይሰርዝልኝ” በማለት ቀላምዷል፡፡

ዳኛውም በጋሻው የተሳሳተ ምስክርነት በመስጠት ፍ/ቤቱን ከማሳሳት እንዲጠነቀቅ አሳስበውታል፡፡ ከዚህ በመቀጠል መ/ር ዘመድኩን፣ “አንተ የት ነው የተማርኸው? የማስተማር ፈቃድ የሰጠህ ማነው?” የሚል ጥያቄ ለበጋሻው ቀርቦለታል፡፡ በጋሻውም ሲመልስ “መንፈሳዊ ኮሌጅ ተምሬ በግል ምክንያት ወጥቻለሁ፡፡ ከዚያ በኋላ ወደ ካህናት ማሠልጠኛ ገብቼ ሰርቲፊኬት አለኝ” በማለት በአቡነ ፋኑኤል የተፈረመበት ‹ምስክር ወረቀት› ማሳየቱ ተመልክቷል፡፡

ሁለቱም ተከሳሾች /መር ዘመድኩን በቀለ እና ዲያቆን ደስታ ጌታሁን/ ዛሬ ጠዋት የመከላከያ ምስክሮቻቸውንና መልሶቻቸውን እንዲያቀርቡ ፍ/ቤቱ ቀጠሮ ይዞ ነበር፡፡ ሆኖም ጠቅላይ ቤተ ክህነት ባለፈው ሳምንት ዓርብ ለፍትሕ ሚኒስቴር በጻፈው ደብዳቤ “ዲያቆን በጋሻው በተባለው ግለሰብ” የተመሠረተው ክስ፣ 1). የክሱ ፍሬ ነገር ሃይማኖታዊ በመሆኑ (ሃይማኖታዊ ይዘት ስላለው)፤ 2). ከሳሹ ግለሰብና ግብረ አበሮቹ በሕገ ወጥነትና በተሳሳተ እምነት አራማጅነታቸው በቀረበባቸው ማስረጃ በቅዱስ ሲኖዶስ ምልአተ ጉባኤ ጉዳያቸው እንዲመረመር ውሳኔ የተላለፈባቸው በመሆኑ ክሱ ተቋርጦ፣ መዝገቡ ተዘግቶ ወደ ሚ/ሩ ተመላሽ እንዲሆን የጠየቀ በመሆኑ በሚ/ሩ በኩል የጠቅላይ ቤተ ክህነቱ ጥያቄ ተቀባይነት እንደሚያገኝ እየተጠበቀ ይገኛል፡፡

Post a Comment

Blog Archive

የአቡነ ጳውሎስ "ሐውልተ ስምዕ"

ነጻ ፓትርያርክ ምርጫ ቢሆን ኖሮ ማንን ይመርጡ ነበር? እንበልና ሁሉም ነገር ሥርዓቱን ጠብቆ የተከናወነ የእጩዎች ምርጫ ቢሆን ኖሮ፣ አሁን የምናነሣቸው ጉድለቶች ባይኖሩ ኖሮ፣ 6ኛው ፓትርያርክ እንዲሆን የምትመርጡት ማንን ነበር? (ማሳሰቢያ፦ አሁን ያለው ክፍፍል እና የመንግሥት ተጽዕኖ ባይኖር ኖሮ ተብሎ የሚመለስ ጥያቄ ነው። የምን “ባይኖር ኖሮ ነው” የሚል አስተያየት ካለዎትም እናከብራለን።)