November 13, 2011

አባ ሰረቀ የተፈጸመባቸው “ከፍተኛ የስም ማጥፋት ውንጀላ” በሥራቸው ለመቀጠል እንደማያስችላቸው ገለጹ


  • READ IN PDF. UPDATED!!!!
  • የመንፈሳዊ ዘርፍ ም/ዋና ሥራ አስኪያጅ ሆነው በፓትርያኩ በመሾማቸው ተቃውሞ ያቀረቡት አካላት፣ “እንከን የሌለበትን ንጹሕ እምነታቸውን ጥላሸት የቀቡ ከሳሾቻቸው” ማንነት እና የክሱ ዝርዝር እንዲሰጣቸው ጠይቀዋል
  • ‹ውንጀላው› እስከሚጣራ ድረስ “እጅግ መራራ ተጋድሎ በከፈሉበትና ውጤት ባሳዩበት” የቀድሞ ቦታቸው እንዲቆዩ አልያም የዕረፍት ጊዜ እንዲሰጣቸው አመልክተዋል
  • “እውነትንና ፍትሕን” ከቤተ ክርስቲያን እንደሚሹ “እውነትና ፍትሕ” ከቤተ ክርስቲያን ከጠፋ ግን “ሕገ መንግሥቱን ተጠቅመው” መብታቸውን በማስከበር ከሳሾቻቸውን ለመበቀል ዝተዋል
  • ከአዲሱ የሰንበት ት/ቤቶች ማ/መምሪያ ሓላፊ ጋራ ዛሬ ርክክብ ያደርጋሉ
(ደጀ ሰላም፤ ኅዳር 2/2004 ዓ.ም፤ ኖቬምበር 12/2011)፦ ከሰንበት ት/ቤቶች ማደራጃ መመሪያ ዋና ሓላፊነታቸው ተነሥተው የትምህርት እና ሥልጠና መምሪያ ሓላፊ የተደረጉት አባ ሰረቀ ብርሃን ወ/ሳሙኤል የቀረበባቸው ከባድ “የስም ማጥፋት ወንጀል” ሳይጣራ በሥራቸው ለመቀጠል የማይቻላቸው በመሆኑ ከሥራ ጓደኞቻቸው ጋራ በመሆን “እጅግ መራራ ተጋድሎ ከፍዬበታለሁ፤ መልካም ውጤትም አሳይቼበታለሁ” በሚሉበት በሰንበት ት/ቤቶች ማደራጃ መምሪያ ዋና ሓላፊነታቸው እንዲቆዩ አልያም የዕረፍት ጊዜ እንዲሰጣቸው ጠየቁ፤ ለአዲሱ የማደራጃ መምሪያው ዋና ሓላፊ አባ ኅሩይ መሸሻ የመምሪያው ሠራተኞች አቀባበል ያደረጉላቸው ሲሆን በትንትናው ዕለት ደግሞ ከቆሞስ አባ ሰረቀ ብርሃን ወ/ሳሙኤል ጋራ ርክክብ እንደሚካሄድ እየተጠበቀ ነበር፡፡


አባ ሰረቀ “በንጹሕ እምነቴ ላይ እየደረሰብኝ [ላ]ለው ከባድ የስም ማጥፋት ወንጀል አፋጣኝ መልስ እንዲሰጥልኝ ስለመጠየቅ” በሚል ጥቅምት 27 ቀን 2004 ዓ.ም ለፓትርያክ አቡነ ጳውሎስ በጻፉት ሁለት ገጽ ደብዳቤ፣ “በቤተ ክርስቲያኒቱ ስም በመደበቅ በቤተ ክርስቲያኒቱ እና በሀገሪቱ ላይ ከፍተኛ ማኅበራዊ፣ ሃይማኖታዊ እና ኢኮኖሚያዊ ጫና ፈጥሯል” ያሉት ማኅበረ ቅዱሳን እርሳቸውና “የሥራ ባልደረቦቻቸው” ባደረጉት መራራ ተጋድሎ “የተደበቀ ሥራው በሁሉም ወገን እየተገለጠ” በመምጣቱ ከዛቻና ማስፈራራት ባሻገር “በማንነታቸው እና በንጹሕ እምነታቸው” ላይ ጥላሸት እየቀባ ከፍተኛ ዘመቻ እንደከፈተባቸው አስታውቀዋል፡፡

ጥቅምት 25 ቀን 2004 ዓ.ም የተጠናቀቀው የቅዱስ ሲኖዶስ ምልአተ ጉባኤ “የማ/መምሪያው እና የማኅበረ ቅዱሳን የሥራ አለመግባባት” በሚል በተመለከተው አጀንዳ ተራ ቁጥር 4፡- የሰንበት ት/ቤት ወጣቶችን፣ ሕፃናትንና ማኅበረ ቅዱሳንን ጭምር አስተባብሮ በመምራት ረገድ በከፍተኛ ድክመት የገመገማቸው እና አለባቸው የተባለውን የእምነት ሕጸጽ ከሊቃውንት ጉባኤ አባላት ጋራ በመሆን በማስረጃ መርምሮ የሚያቀርብ ሰባት ብፁዓን ሊቃነ ጳጳሳት ያሉበት ኮሚቴ ያቋቋመባቸው አባ ሰረቀ “የተፈጸመባቸው ከባድ የስም ማጥፋት ወንጀል” በማኅበራዊ እና ሃይማኖታዊ እንቅስቃሴያቸው ላይ ከባድ ችግር የሚደቅንና “በማንነታቸው ላይ የተፈጸመ ግድያ(Character assassination)” አድርገው የሚቆጥሩት በመሆኑ ጉዳዩ ጊዜ ሳይሰጠው በአስቸኳይ እንዲጣራ ተማፅነዋል፡፡

ፓትርያርክ አቡነ ጳውሎስ ጥቅምት 27 ቀን 2004 ዓ.ም በራሳቸው ማኅተም በጻፉት ደብዳቤ የጠቅላይ ቤተ ክህነት የመንፈሳዊ ዘርፍ ምክትል ሥራ አስኪያጅ አድርገው “በመልካም ፈቃዳቸው” በመደቧቸው ቦታ ላይ እንዳይሠሩ የተቃወሟቸው አካላት እና “ንጹሕ እምነታቸውን ጥላሸት የቀቡ” ከሳሾቻቸው ማንነት እንዲነገራቸው፣ ለክሳቸውም መልስ መስጠት ይቻላቸው ዘንድ የክሱ ጽሕፈት በዝርዝር እንዲሰጣቸውም ጠይቀዋል፡፡

ፓትርያርኩ ለአባ ሰረቀ የሰጧቸው ሕገ ወጥ ሹመት ደጀ ሰላምን ጨምሮ በየደረጃው በገጠመው ከባድ ተቃውሞ የተነሣ ጥቅምት 29 ቀን 2004 ዓ.ም በብፁዕ አቡነ ገሪማ በተጻፈ ደብዳቤ የመንፈሳዊ ዘርፍ ም/ሥራ አስኪያጅ መሆናቸው እንደተሻረና ብፁዕ ዋና ሥራ አስኪያጁ በሚመድቧቸው ቦታ እንዲሠሩ ከብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ጳውሎስ እንደታዘዘ የሚገልጽ ደብዳቤ ለአባ ሰረቀ እንዲደርሳቸው ተደርጓል፡፡ በዚህም መሠረት አባ ሰረቀ ከሕፃናት፣ ወጣቶች እና ማኅበረ ቅዱሳን ንክኪ ርቀው “ወደሚሠሩበት” የትምህርት እና ማሠልጠኛ መምሪያ መመደባቸው ተገልጧል፡፡


ይሁንና ማኅበረ ቅዱሳንን “ሰንሰለቱን ባልጠበቀ ማመልከቻ አቀራረብ” የሚከሱት ግብዙ አባ ሰረቀ የቅርብ አለቃቸው የሆኑትን ብፁዕ አቡነ ፊልጶስን ተሻግረው ለብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ጳውሎስ ባቀረቡት አቤቱታ “የሐሰት ውንጀላ” ነው ያሉት ክስ በተሰጣቸው የሥራ መደብ ሓላፊነታቸውን ለመወጣት የማያስችላቸው በመሆኑ እስኪጣራ ድረስ ቀድሞ በነበሩበት ቦታ እንዲቆዩ አልያም የዕረፍት ጊዜ እንዲሰጣቸው ጠይቀዋል፡፡ የቀረበባቸው “ውንጀላ” ተጣርቶ እውነትንና ፍትሕን ከቤተ ክርስቲያን የማያገኙ ከሆነ ደግሞ ሕገ መንግሥቱን ተጠቅመው መብታቸውን በማስከበር ‹ከሳሾቻቸውን› እንደሚበቀሉ ዝተዋል፡፡

ይገርማል! አባ ሰረቀ “የእውነት እና ፍትሕ ምንጭ ናት” እንደሆነች በአቤቱታቸው ከጠቀሷት ቤተ ክርስቲያን በላይ እና በፊት ትምክህታቸው በሌላ ኖሯል! እንደ ምንኩስናቸው ቢሆን ኖሮ ይህ ዐይነቱ አቋም ከአባ ሰረቀ አይጠበቅም ነበር፡፡ ስለዚህም ይሆን ማኅበረ ቅዱሳን “ፖሊቲካ እና ሃይማኖትን እያጣቀሰ ስለ መሄዱ” የመንግሥት ባለሥልጣናት የተገኙበትን የመስከረም 12 ቀን 2002 ዓ.ም ስብሰባ አዘውትረው በጀብደኛነት የሚተርኩት? የአባ ሰረቀ ግብዝነት(hypocrisy) ማኅበረ ቅዱሳንን በሚከሱበት “ሰንሰለቱ ያልጠበቀ የደብዳቤ አቀራረብ” ብቻ ሳይሆን እርሳቸው ራሳቸው በአሜሪካ ሳሉ በራሳቸው አነጋገር “ማጣቀስ” ብቻ ሳይሆን ሲያደበላልቁት በቆዩትና መንግሥት በሚገባ በሚያውቀው ፖሊቲካዊ አሰላለፋቸውም ጭምር የሚገለጽ ነው/ዝርዝሩን በቆይታ እንመለስበታለን/፡፡

ከአባ ሰረቀ ከሰንበት ት/ቤቶች ማደራጃ መምሪያ ዋና ሓላፊነታቸው እንደሚነሡ ከታወቀበት ጊዜ ጀምሮ እስከ አሁን ድረስ እየተስተዋሉ የሚገኙት ውሳኔውን ለማዳፈን የሚጥሩ ርብርቦች - አባ ሰረቀ የፕሮቴስታንታዊ-ተሐድሶ ፕሮጀክት ሕንብርት (መቋጠሪያ ነጥብ ወይም ውል)፣ የሰንበት ት/ቤቶች ማደራጃ መምሪያ ደግሞ የፕሮጀክቱ ገዥ መሬት ለማድረግ የነበረውን የአራረ ቤተ ክርስቲያን ስትራቴጂ እንደሚያመለክት እየተገለጸ ነው፡፡

ጥቅምት 13 ቀን 2004 ዓ.ም ምልአተ ጉባኤው አባ ሰረቀ ከማደራጃ መምሪያው ተነሥተው ደመወዛቸውን እንደያዙ ወደ ሌላ መምሪያ እንዲዛወሩ፣ ሃይማኖታዊ ሕጸጻቸውም እንዲመረመር በሙሉ ድምፅ ያለ ልዩነት የተላለፈው ውሳኔ በአማን ታሪካዊ ብቻ ሳይሆን ኦርቶዶክሳዊት ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያናችንን ከውስጥ እና ከውጭ በማጠራቀቅ ለመከፋፈል አልያም ባለችበት አዳክሞ ማንነቷን ወደ ፕሮቴስታንታዊነት ለመለወጥ ለተሸረበው የኑፋቄ ፕሮጀክት ከባድ ምት ነው ለማለት እንደፍራለን!!

ደጀ ሰላማውያን፣ በቀጣይ ቅዱስ ሲኖዶሳችን በሙሉ ድም ለወሰነው ውሳኔ ተፈጻሚነት በንዓት እንደምንሠራ እየገለጽን ደስታችሁ ፍጹም እንዲሆን፣ ለታሪክም መዘክር ይሆን ዘንድ የጥቅምቱ ቅዱስ ሲኖዶስ ምልአተ ጉባኤ ጥቅምት 13 ቀን 2004 ዓ.ም በአባ ሰረቀ ላይ፣ ጥቅምት 20 ቀን 2004 ዓ.ም በስምንት የፕሮቴስታንታዊ-ተሐድሶ-ኑፋቁ አራማጅ ማኅበራት እና በሕገ ወጥ ሰባክያን ላይ ውሳኔ ያስተላለፈበትን ቃለ ጉባኤ እና ሌሎች ተከታይ ደብዳቤዎችን እንድትመለከቱ (ፒ.ዲ.ኤፉን ይክፈቱት) እንጋብዛለን፡፡

ቸር ወሬ ያሰማን፣
አሜን፡፡


Post a Comment

Blog Archive

የአቡነ ጳውሎስ "ሐውልተ ስምዕ"

ነጻ ፓትርያርክ ምርጫ ቢሆን ኖሮ ማንን ይመርጡ ነበር? እንበልና ሁሉም ነገር ሥርዓቱን ጠብቆ የተከናወነ የእጩዎች ምርጫ ቢሆን ኖሮ፣ አሁን የምናነሣቸው ጉድለቶች ባይኖሩ ኖሮ፣ 6ኛው ፓትርያርክ እንዲሆን የምትመርጡት ማንን ነበር? (ማሳሰቢያ፦ አሁን ያለው ክፍፍል እና የመንግሥት ተጽዕኖ ባይኖር ኖሮ ተብሎ የሚመለስ ጥያቄ ነው። የምን “ባይኖር ኖሮ ነው” የሚል አስተያየት ካለዎትም እናከብራለን።)