November 5, 2011

ሁለት ሱባኤ የቆየው የቅዱስ ሲኖዶስ ምልአተ ጉባኤ ‹በሹም ሽር ውዝግብ› መካከል ተጠናቀቀ


 (ደጀ ሰላም፤ ጥቅምት 25/2004 ዓ.ም፤ ኖቬምበር 5/2011/ READ IN PDF)፦
 • ፓትርያርኩ ትናንት ሕገ ቤተ ክርስቲያንን በመተላለፍ ያለ ቅዱስ ሲኖዶስ ዕውቅና የፈጸሙት የመ/ፓ/ጠ/ጽ/ቤት ምክትል ዋና ሥራ አስኪያጅ ሹም ሽር ላይ የምልአተ ጉባኤው አባላት ተቃውሟቸውን አሰምተዋል፤ በመምሪያ ደረጃ በተደረገው ዝውውር የተሾሙት ሓላፊዎችም ለተመደቡበት ቦታ አይመጥኑም” የምልአተ ጉባኤው አባላት ቅሬታቸውን ገልጸዋል - ፓትርያርኩ እና የጠ/ጽ/ቤቱ ዋና ሥራ አስኪያጅ እርስ በርስ አሻግረው እየተያዩ ለተቃውሞው እና ለቅሬታው የአርምሞ ምላሽ ሰጥተዋል
 • ፁዕ አቡነ ቀውስጦስ ሊያቀርቡት ነበር የተባለው መልቀቂያ ስኬታማውን ሥራ አስኪያጅ ንቡረ እድ አባ ገብረ ማርያም ገ/ሥላሴን ከሥራ አስኪያጅነታቸው ለማስነሣት በፓትርያርኩ እና በሀ/ስብከቱ ውስጥ የጥቅም ኔትወርክ በፈጠሩ ግለሰቦች የተዘየደ መላ እንደነበር የሚያመለክቱ መረጃዎች እየወጡ ነው - “አይ፣ እርስዎ አይለቁም፤ መልቀቅ ያለበት ሰውዬው ነው፤ እንደሚያስቸግርዎት ዐውቃለሁ” (አቡነ ጳውሎስ ለአቡነ ቀውስጦስ ከተናገሩት)
 • የአዲስ አበባ ሀ/ስብከት ሥራ አስኪያጅ ንቡረ እድ አባ ገብረ ማርያም ገብረ ሥላሴ ወደ ጠቅላይ ቤተ ክህነቱ የመዘዋወራቸው ደብዳቤ ፈጥኖ የደረሳቸው ሲሆን የሌሎቹ እንዲዘገይ መደረጉ ተነግሯል፤ ሹመቱ እና ዝውውሩ ከገጠመው ተቃውሞ እና ከቀረበበት ቅሬታ አኳያ ማሻሻያ ሳይደረግበት እንደማይቀር ተመልክቷል
 • የሀ/ስብከቱ ሥራ አስኪያጅ ሆነው የተሾሙት ንቡረ እድ ኤልያስ ኣብርሃ ከፓትርያርኩ ጋራ ካላቸው ጥብቅ ግንኙነት አኳያ የመልቀቂያ ጥያቄያቸውን ካነሡት ሊቀ ጳጳሱ ብፁዕ አቡነ ቀውስጦስ ጋራ ተግባብተው የመሥራታቸው ሁኔታ አጠራጣሪ እንደሆነ ተዘግቧል፤ በተጨማሪም የአዲስ አበባ ሰንበት ት/ቤቶች አንድነት የንቡረ እድ ኤልያስ መሾም በኅብረቱ ቀጣይነት ላይ ስጋት እንደሚፈጥር አባላቱ በመግለጽ ላይ ናቸው
 • የተደረገው ሹመት እና ዝውውር ፓትርያርኩ ለቅዱስ ሲኖዶስ አባላት እና ለሕገ ቤተ ክርስቲያን ያላቸውን አመለካከት [ንቀት?] እና እልከኝነት የሚያሳይ በመሆኑ እርምት ይሰጥበት ዘንድ ግፊት ማድረግ እንደሚያስፈልግ ተጠቁሟል
 • የምልአተ ጉባኤውን መጠናቀቅ በማስመልከት ፓትርያርኩ ጋዜጣዊ መግለጫ ሰጥተዋል፤ ከመግለጫው ዋና ዋና ነጥቦች መካከል፡-
 • ቤተ ክርስቲያን ዕውቅና ያልሰጠቻቸው ሰባክያንና ዘማርያን ነን ባዮች ከሚያደርጉት ኢ-ሕጋዊ እንቅስቃሴ እንዲቆጠቡ ምልአተ ጉባኤው ውሳኔ ሰጥቷል
 • በአሜሪካ በስደት ከሚገኙት ከቀድሞ ፓትርያርክ እና አብረዋቸው ካሉት አባቶች ጋር ተጀምሮ የነበረው የዕርቀ ሰላም ድርድር ጉዳይ በአሜሪካ አሪዞና ግዛት ፊኒክስ ከተማ ይቀጥላል
 • ከሀገር ውጭ በሚገኙ አህጉረ ስብከት ተመድበው ከሚሠሩት መካከል የተወሰኑ ሊቃነ ጳጳሳት በሀገር ውስጥ ተመድበው እንዲሠሩ፣ በሀገር ውስጥ ካሉትም መካከል የሥራ ዝውውር እንዲደረግላቸው ጥያቄ ያቀረቡ ሊቃነ ጳጳሳት ተዛወረው ይሠሩ ዘንድ ዝውውሩ ተፈቅዶላቸዋል
 • በሰንበት ት/ቤቶች ማደራጃ መምሪያ እና በማኅበረ ቅዱሳን መካከል የተፈጠረው የሥራ አለመግባባት እና ቀኖና ቤተ ክርስቲያንን በተመለከተ አለ የተባለው ችግር ከቅዱስ ሲኖዶስ አባላት የተመረጡ ሊቃነ ጳጳሳት በሚገኙበት ስብሰባ በሊቃውንት ጉባኤው ተጣርቶ ይቀርብ ዘንድ መመሪያ ተሰጥቷል
 • በ1991 ዓ.ም የተሻሻለውና እየተሠራበት የሚገኘው ቃለ ዐዋዲ ለሦስተኛ ጊዜ ተሻሽሎ እንዲቀርብ ምልአተ ጉባኤው ተስማምቷል
 • የቤተ ክርስቲያኒቱ የዜማ መጻሕፍት፣ የሕንጻዎች፣ የቋንቋ በአጠቃላይ ብሔራዊው የአእምሮ ንብረት ባለቤትነት መብቷ በሕግ ይከበር ዘንድ በቅርስ ጥበቃ እና ምዝገባ የቤተ መጻሕፍት ወመዘክር መምሪያ ጉዳዩ ለሚመለከተው የፍትሕ አካል ቀርቦ ውሳኔ እንዲያገኝ ይደረጋል
 • ለአብነት ት/ቤቶች እና ካህናት ማሠልጠኛዎች፣ በታሪክ መዘከርነታቸው ዕውቅና ላላቸው ገዳማት፣ ዕጓለ ማውታ ሕፃናት እየተማሩ ለሚያድጉባቸውና ሴቶች መነኮሳይያት በምናኔ ለሚኖሩባቸው ገዳማት ማጠናከሪያ የሚውል በጀት በበቤተ ክርስቲያኒቱ ማእከላዊ የበጀት አስተዳደር ተጠንቶ ይቀርባል
 • መንፈሳዊ ፍርድ ቤቶችን በአዲስ መልክ ለማቋቋም የተዘጋጀው ረቂቅ ለሕዝብ ተወካዮች ም/ቤት ቀርቦ እንዲጸድቅ ምልአተ ጉባኤው ተስማምቷል
 • ለታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ የሚደረገው የቦንድ ግዥ ከመንበረ ፓትርያርክ እስከ አጥቢያ አብያተ ክርስቲያናት ድረስ ተጠናክሮ እንዲቀጥል መመሪያ ተሰጥቷል
 • የጠቅላይ ቤተ ክህነቱን አስተዳደር በሚመለከት የቀረበው ጥናት በሕግ ባለሞያዎች ከታየ በኋላ ለግንቦቱ የርክበ ካህናት ቅዱስ ሲኖዶስ ምልአተ ጉባኤ እንዲቀርብ መመሪያ ተሰጥቷል፤ … የሚሉት ይገኙባቸዋል፡፡
ጥቅምት 11 ቀን 2004 ዓ.ም በተደረገው የመክፈቻ ጸሎት ሥነ ሥርት መላው የአዲስ አበባ ሰንበት ት/ቤቶች ባሳዩት የተቃውሞ ትዕይንት እና ባወጡት የአቋም መግለጫ አቀባበል የተደረገለት የጥቅምቱ ቅዱስ ሲኖዶስ ዓመታዊ ምልአተ ጉባኤ ስብሰባ ሁላችንም ለሁለት ሱባኤያት (14 ቀናት) ስንከታተል እንደቆየነው በመካከል ከአራት ኪሎ ጽርሐ መንበረ ፓትርያርክ እስከ ዋሽንግተን ዲሲ መንበረ ጵጵስና የተከሠቱ ውዝግቦች ሳይለዩት ዛሬ፣ ጥቅምት 25 ቀን 2004 ዓ.ም ከሰዓት በኋላ ላይ በመንበረ ፓትርያርክ ቤተ መጻሕፍት ወመዘክር ርእሰ መንበር ብፁዕ ወቅዱስ ፓትርያርክ አቡነ ጳውሎስ እና ብፁዓን ሊቃነ ጳጳሳት ከመገናኛ ብዙኀን አባላት ጋ በተገናኙበት በንባብ ብቻ ተሰምቶ በተዘጋ ጋዜጣዊ መግለጫ (CLICK HERE)ተጠናቋል፡፡

ይህን ያህል ቀናት የወሰደ የቅዱስ ሲኖዶስ ስብሰባ በዘመናዊው ታሪክ ስለመኖሩ ለቤተ ክርስቲያን የቅርብ ዘመን አጥኚዎች ትተን በታዘብነው መጠን የስብሰባው ሂደት ከወሰደው ረጅም ቀናት እና በርእሰ መንበሩ አመራር ላይ ከተስተዋለው የጋራ ውሳኔ የተላለፈባቸውን አጀንዳዎች መላልሶ የማንሣት ‹ስልት› በተለይም በዕድሜ የገፉ ብፁዓን ሊቃነ ጳጳሳትን በስብሰባው የመቀጠል ትዕግሥት የተፈታተነ (ያዳከመ) እንደነበር ተገልጧል፤ አንዳንድ አባቶችም ስብሰባው ይቆያል ከተባለበት ጊዜ በላይ በመዘግየቱ ቀደም ብለው ፕሮግራም ወዳደረጉባቸው መንፈሳዊ አገልግሎታቸው አቋርጠው መሄዳቸው (ጥቅምት 20 ቀን ብፁዕ አቡነ ገብርኤል ወደ አሜሪካ ማቅናታቸው፣ ሌሎች ሁለት ብፁዓን ሊቃነ ጳጳሳት ወደየሀገረ ስብከታቸው ጎራ ብለው መመለሳቸው) ተነግሯል፡፡

ይህም ትኩረት በሚሹ አንዳንድ አንገብጋቢ አጀንዳዎች ላይ በአቋም የመላላት ሁኔታ እንዳይፈጥር ኦርቶዶክሳውያን ቤተሰቦችን አስግቶ  ነበር፡፡ ሆኖም ክብር እና ምስጋና ርቱዐን አባቶቻችንን በጠብቆቱ አጽንቶ ለመራ መንፈስ ቅዱስ ይሁንና ከአዘቦቱ በተለየና የቅዱስ ሲኖዶሱን ስብሰባ ለዓመታት በመከታተል ልምድ ያላቸውን አገልጋዮች እና ምእመናን ባስደመመ አኳኋን የምልአተ ጉባኤው አባላት ኁባሬ (Integrity, Intact) የሚመሰገን ነበር፡፡

ይኸው ከወትሮው የተጠናከረው የምልአተ ጉባኤው አባላት ኁባሬ ለሚዲያ ዘጋቢዎች እና ተንታኝ አካላት (Media pundits) በቂ ዕለታዊ መረጃ ለማግኘት ፈታኝ እንደነበር ለመሸሸግ አይቻለንም፡፡ እንደ ብዙዎች አመለካከት ነገርዬው የማይገቡ መረጃዎች ወደ ውጭ እየወጡ “በሚዲያ ዘገባዎች ከ‹መዋከብ› ታድጎ በተረጋጋ መንፈስ ለመወያየት ዕድል ይሰጣል” የሚል እምነት ቢኖርም ቤተ ክርስቲያን ካለችበት መስቀለኛ መንገድ አንጻር የሃይማኖቱ ጉዳይ ለሚገደው አገልጋይ እና ምእመን ደግሞ ሊታሰብለት እንደሚገባ ይሰማናል፡፡

በአጠቃላይ የምልአተ ጉባኤው ስብሰባ ሂደት እና ፍጻሜ ቤተ ክርስቲያናችን ከመቼውም ጊዜ በበለጠ በተለይም በተሰሉ የውስጥ ተግዳሮቶችና የከፍተኛ አስተዳደሯ የአመራር ቀውስ የተነሣ በፈታኝ ሁኔታ ላይ እንደምትገኝ በተጨባጭ አሳይቶናል፡፡

በመሆኑም መላው አገልጋይ እና ምእመን እንዲሁም ደጀ ሰላማውያን የሰላምንና የመከባበርን መንገድ አጽንተን በደረሱን መረጃዎች ላይ ተመሥርተን ጥልቅ እና መፍትሔ ከሣች ውይይት በማካሄድ በመንፈስ፣ በቃል እና በተግባር የምናደርገውን የተባበረ ሰማያዊ ተጋድሎ አጠናክረን እንድንቀጥል ደጀ ሰላም ታሳስባለች፡፡

በዚሁ አጋጣሚ ስለ ስብሰባው እና ተያያዥ ጉዳዮች በጥቅል ይሁን በዝርዝር ስናወጣቸው የሰነበትናቸውን ዘገባዎች በተለያየ መንገድ በማሰራጨት ጥረታችንን ለተራዳችሁን በሙሉ ልባዊ ምስጋናችንንና አክብሮታችንን ልንገልጽላችሁ እንወዳለን፡፡

ቸር ወሬ ያሰማን፣
አሜን

7 comments:

Anonymous said...

ደጀሰላሞች! እንደት ሰነበታችሁ?
እናንተ እንዳስነበባችሁን፤ የዘንድሮው የቅዱስ ሲኖዶስ ስብሰባ ከባለፈው ጋር ሲወዳደር የተሻለ ሰላማዊ ነበር ማለት ይቻላል። ነገር ግን አባ ሠረቀ የሃይማኖት ችግር ካለባቸው እንዴት ነው የትምህርት እና ማሰልተኛ መምሪያ ኃላፊ ሆነው ሊሾሙ የቻሉት ? በእኔ ግምት የሃይማኖት ችግር ቢኖርባቸው ኑሮ የቅዱስ ሲኖዶስ አባላት ምደባውን በጽናት መቃወም ነበረባቸው። ምክንያቱም ጉዳዩ የሃዝማኖት ጉዳይ ስለሆነ ነው።
በሌላ በኩል አሁን የሰንበት ት.ቤቶች ማዳራጃ ኃላፊ ሁነው የተመደቡት ኣባ ህሩይ ምን አይነት ሰው ናቸው?
የተሻለ መሥራት ይችላሉ ወይ?

Anonymous said...

I am satisfied by results of the meeting..90% of the time. Thank God and St Mary. Hope the coming time is not going to be..despite the holy sinode decision, this and that has been done..

Anonymous said...

menaw yaABUNA FANUALE WARE TAFA?

Anonymous said...

Temesgen, silehulum egziabher yetemesegene yihun, ersu afetsatsemun yasamrilin, ye "aba" sereke neger asdestognal, temesgen amlake sirak dink new, ayalkibih.

Anonymous said...

Dear Dejeselamawiyan,I would like to say smthg about ur website,if u are really concerned for our holly church,please please make sure to post the truth"Egziabher Yayal" it might take time but the tuth is always truth.I dont see where this website give us hope or strength.it is really frustrating,any way May the Almighty show you the truth!!!!

Anonymous said...

Dear Dejeselam's
Thanks for the info. and keep the good work up!

Anonymous said...

Thank you Dejeselam owners. I realy appriciate your at most assistans in the past few weeks Synodos meeting information. Was very vital to as day and night follow up. Weather it is good or bad news, you did your part. I don't know who you are and from where you conduct your web. Any way keep up the good job. The conclusion I came up with is that the meeting is over for now resulting with the sacrifice of the DC and Surrounding Area Membere Pipisena being thrown into the hands of the haynas(Jiboch). Imagine how the process is going to happen. This is not the end,but the begining of disaster or sunami in DC area.

Blog Archive

የአቡነ ጳውሎስ "ሐውልተ ስምዕ"

ነጻ ፓትርያርክ ምርጫ ቢሆን ኖሮ ማንን ይመርጡ ነበር? እንበልና ሁሉም ነገር ሥርዓቱን ጠብቆ የተከናወነ የእጩዎች ምርጫ ቢሆን ኖሮ፣ አሁን የምናነሣቸው ጉድለቶች ባይኖሩ ኖሮ፣ 6ኛው ፓትርያርክ እንዲሆን የምትመርጡት ማንን ነበር? (ማሳሰቢያ፦ አሁን ያለው ክፍፍል እና የመንግሥት ተጽዕኖ ባይኖር ኖሮ ተብሎ የሚመለስ ጥያቄ ነው። የምን “ባይኖር ኖሮ ነው” የሚል አስተያየት ካለዎትም እናከብራለን።)