October 28, 2011

(ሰበር ዜና) ፕሮቴስታንታዊ ተሐድሶን በመቃወም ከተደረገው ትዕይንት ጋራ በተያያዘ የታሰሩት ወጣቶች ተፈቱ


(ደጀ ሰላም፤ ጥቅምት 16/2004 ዓ.ም፤ ኦክቶበር 27/2011/ PDF)፦ በቤተ ክርስቲያን ላይ ከውስጥና ከውጭ እየተካሄደ የሚገኘውን የፕሮቴስታንታዊ ተሐድሶ እንቅስቃሴ በመቃወም እና ቅዱስ ሲኖዶስ በእንቅስቃሴው አራማጆች ላይ የቀረቡ ማስረጃዎችን መርምሮ አስቸኳይ ውሳኔ እንዲያሳልፍ ለመጠየቅ ከተጠራው የተቃውሞ ትዕይንት ጋራ በተያያዘ ከጥቅምት 11 ቀን 2004 ዓ.ም ማታ ጀምሮ ለአምስት ቀናት ከታሰሩት ወጣቶች መካከል በተባባሪነት የተከሰሱት ስድስቱ ዛሬ ማምሻውን ተፈተዋል፤ በብር 800 ዋስ እንዲወጡ የተወሰነላቸውና ‹ዋነኛ› የተባሉት ሁለቱ ወጣቶችም በነገው ዕለት እንደሚለቀቁ ይጠበቃል፡፡


ይህንንም ተከትሎ ሕገ ወጡን ቡድን በመደገፍ ከሐዋሳ መጡ የተባሉ ወጣቶችም በዋስ የሚወጡ ሲሆን ሂደቱን ያቀላጠፉላቸው የሕገ ወጥ ቡድን አስተባባሪዎች (በጋሻው ደሳለኝ፣ አሰግድ ሣህሉ፣ በሪሁን ወንደወሰን . . .) ናቸው፡፡ በድብደባ ጉዳት ደርሶበታል የተባለው ትዝታው ሳሙኤል በወረዳ 2፣ 9 እና በማእከላዊ ወንጀል ምርመራ ለአምስት ቀናት በእስር ከቆዩት ወጣቶች መካከል የደበደቡትን በመልክ ይለያቸው እንደሆን በፖሊስ ተጠይቆ ከእነርሱ መካከል እንደሌሉበት መመስከሩ ተገልጧል፡፡

የአዲስ አበባ አስተዳደር የመጀመሪያ ደረጃ ፍ/ቤት አራዳ ምድብ ችሎት ስድስቱ ወጣቶች በብር 600 ዋስ አስይዘው እንዲወጡ ከወሰነ በኋላ ‹ትፈለጋላችሁ› በሚል ወደ ማእከላዊ ወንጀል ምርመራ ተወስደዋል፤ ወጣቶቹ ጥቅምት 14 ቀን 2004 ዓ.ም ወደ ፌደራሉ የመጀመሪያ ፍ/ቤት ቀርበው የነበረ ሲሆን “ከፍተኛውን የተቃውሞ አስተባባሪ ለመያዝ” በማለት ፖሊስ በጠየቀው ተጨማሪ ጊዜ ቀጠሮ መሠረት ፍ/ቤቱ ለጥቅምት 20 ቀን 2004 ዓ.ም እንዲቀርቡ አዝዞ እንደነበር መዘገቡ ይታወሳል፡፡ ቀደም ሲል በብር 600 ዋስ እና በብር 800 ዋስ እንዲወጡ በፍ/ቤት የተወሰነላቸው ወጣቶቹ ከእስር ነጻ የወጡት/የሚወጡት የቤት ካርታ እና የመኪና ሊብሬ በዋስትና አስይዘው ነው፡፡ ይህም ዋስትናውን ከፍ/ቤቱ ትእዛዝ በላይ በማክበድ ወጣቶቹን በእስር ለማሰንበት ያለውን ፍላጎት ያሳየ ነው ብለዋል - ታዛቢዎች

“ቤተ ክርስቲያኗን በመበጥበጥ፣ ሁከት በመቀስቀስ እና በድብደባ ጉዳት በማድረስ” የሚሉ ክሶች የቀረቡባቸው ወጣቶቹ፣ በእስር ቆይታቸው ወቅት በተካሄደባቸው ምርመራ የማኅበረ ቅዱሳን አባል ስለመሆናቸው/ስላለመሆናቸው ያተኮሩ ጥያቄዎች እንደቀረቡላቸውና በምርመራው ሂደትም “ተፈጥሯል/ለመፍጠር ታቅዷል” የተባለውን ሁከት እና ብጥብጥ ከማኅበረ ቅዱሳን ጋራ በሆነ መንገድ ለማያያዝ ብርቱ ሙከራ ሲደረግ መታዘባቸው ተመልክቷል፡፡

ወጣቶቹ በበኩላቸው የተባለው ችግር የተፈጠረው በአንዲት ቤተ ክርስቲያን ውስጥ መሆኑን፣ በአንዲት ቤተ ክርስቲያን ውስጥ ደግሞ የተለያየ ሃይማኖት ሊኖር እንደማይገባው፣ ከዚህም አኳያ ‹በሃይማኖት መቻቻል› የሚባል ነገር ሊነሣ እንደማይችል፤ ለሃይማኖታቸው ባዳ እስካልሆኑ ድረስ ስለ ሃይማኖታቸው ለመመስከር የግድ በሆነ ማኅበር ውስጥ መታቀፍ/መደገፍ እንደማያስፈልጋቸው፣ የማኅበረ ቅዱሳንም አባል እንዳልሆኑ መናገራቸው ተገልጧል፡፡ ይህም አንዳንድ መፍቀሬ - ፕሮቴስታንታዊ - ተሐድሶ የሆኑ ብሎጎች የማኅበሩን አባላት በሁከት ፈጣሪነት በመክሰስ የታሰሩት የማኅበሩ አባላት መሆናቸውን የዘገቡት የጅብ ችኩል … ይሉት ክስ በተግባር የሚያስተባብል ነው፡፡

Post a Comment

Blog Archive

የአቡነ ጳውሎስ "ሐውልተ ስምዕ"

ነጻ ፓትርያርክ ምርጫ ቢሆን ኖሮ ማንን ይመርጡ ነበር? እንበልና ሁሉም ነገር ሥርዓቱን ጠብቆ የተከናወነ የእጩዎች ምርጫ ቢሆን ኖሮ፣ አሁን የምናነሣቸው ጉድለቶች ባይኖሩ ኖሮ፣ 6ኛው ፓትርያርክ እንዲሆን የምትመርጡት ማንን ነበር? (ማሳሰቢያ፦ አሁን ያለው ክፍፍል እና የመንግሥት ተጽዕኖ ባይኖር ኖሮ ተብሎ የሚመለስ ጥያቄ ነው። የምን “ባይኖር ኖሮ ነው” የሚል አስተያየት ካለዎትም እናከብራለን።)