October 22, 2011

ሕገ ወጡ ሰባክያንና ዘማርያን የፀረ ፕሮቴስታንታዊ ተሐድሶ እንቅስቃሴውን በመቃወም የተቃውሞ ትዕይንት ሊያካሂዱ ነው


  • READ IN PDF.
  • መላው የአዲስ አበባ ሰንበት ት/ቤቶች አባላት የሕገ ወጦቹን የተቃውሞ ትዕይንት በፀረ-ተቃውሞ ትዕይንት እንዲመክቱ ተጠርተዋል
  • ሕገ ወጦቹ ሰባክያንና ዘማርያን የፀረ-ተሐድሶ ሰባክያን ጥምረት አባላትንና ማኅበረ ቅዱሳንን በስም አጥፊነት ከሰዋል
  • በመ/ር ዘመድኩን በቀለ ላይ ‹የጠፋ ስማቸውን የሚያድስ› ርምጃ እንዲወስድ በፍ/ቤቱ አካባቢ ውትወታ እያካሄዱ ነው፤ የፍ/ቤት ቀጠሮው ከጥቅምት 3 ወደ ጥቅምት 28 ተዛውሯል
  • ሕገ ወጦቹ በፊደል ሬስቶራንት ተሰብስበው ሲመክሩ አምሽተዋል
  • መናፍቃን በሁሉም አህጉረ ስብከት በሚያደርጉት ስልታዊ ዘመቻ የፓትርያርኩን ድጋፍ አግኝተዋል” (የፀረ-ተሐድሶ ሰባክያን ጥምረት የአቋም መግለጫ)፤
(ደጀ ሰላም፤ ጥቅምት 9/2004 ዓ.ም፤ ኦክቶበር 20/2011)፦ በ30ው የመንበረ ፓትርያርክ አጠቃላይ ሰበካ መንፈሳዊ ጉባኤ ላይ የቀረቡት የአህጉረ ስብከት ሪፖርቶች በከፊል እንዳሳዩት፣ ቅዱስ ሲኖዶስ በየካቲት ወር 2001 ዓ.ም በሕገ ወጥ እና አጉራ ዘለል ሰባክያንና ዘማርያን (ማኅበራት) ላይ ጥብቅ ቁጥጥር እና ክትትል እየተደረገ ርምጃ እንዲወሰድ ለመላው አህጉረ ስብከት ያስተላለፈው ሰርኩላር (መመሪያ) አበረታች አፈጻጸም ታይቶበታል፡፡


በመ/ፓ/ጠ/ቤ/ክ የዋና ሥራ አስኪያጅ ጽ/ቤት፣ የስብከተ ወንጌል እና ሐዋርያዊ ተልእኮ መምሪያ ሓላፊ እና ሊቀ ጳጳስ እንዲሁም የተለያዩ አህጉረ ስብከት ጽ/ቤቶች መመሪያውን ለማስፈጸም በተለያዩ ጊዜያት በጽሑፍ ካወጧቸውና በቃል ከሰጧቸው ትእዛዛት እና ሪፖርቶች ለመረዳት እንደሚቻለው፣ በማከል ታውቀው ፈቃድ ሳይኖራቸው እንሰብካለን እያሉ ምእመናንን ግራ ከሚያጋቡና ቀኖና ቤተ ክርስቲያንን ከሚያፋልሱ ግለሰቦች እና ማኅበራት መካከል እንደ ናትናኤል፣ ምናለ እና በሪሁን ወንድወሰን ያሉትን ገባሮች ሳንቆጥር በዋናነት የሚጠቀሱት በጋሻው ደሳለኝ፣ አሰግድ ሣህሉ፣ ተረፈ አበራ እና ያሬድ አደመ ይገኙበታል፡፡ ከእነርሱም ጋራ ‹እንዘምራለን› የሚሉት እነትዝታው ሳሙኤል፣ ሀብታሙ ሽብሩ፣ ቅድስት ምትኩ፣ የትም ወርቅ ሙላት፣ ምርትነሽ ጥላሁን እና ዕዝራ ኀይለ ሚካኤል የመሳሰሉት በአድማጭነት እና ተከታይነት ተደምረው የሚታዩ ናቸው፡፡

ከእኒህም ጥቂቶቹ ዛሬ ጥቅምት 10 ቀን 2004 ዓ.ም ማምሻውን ቦሌ-ቴሌ መንገድ አትላስ ሆቴል ጀርባ ከሚገኘው ፊደል ሬስቶራንት በመሰብሰብ ሠርክ ላይ የጀመሩትን ‹ውይይት› ማታ ላይ ማጠናቀቃቸው ተዘግቧል፤ የውይይታቸው ዓላማም 30ው የመንበረ ፓትርያርክ አጠቃላይ ሰበካ መንፈሳዊ ጉባኤ በሚጠናቀቅበት ወቅት በጠቅላይ ቤተ ክህነቱ ግቢ ከቀኑ 8:00 ላይ በመገኘት፣ ስማችን ተሐድሶ በሚል ጠፍቷል፤ ቅዱስ ሲኖዶስ የጠፋውን ስማችንን የሚያድስ ውሳኔ ያስተላልፍልን፤ እኛ ተሐድሶ ተብለን ከዐውደ ምሕረት ያለ አግባብ እንደተገለልነው ሁሉ ማኅበረ ቅዱሳንና የአራት ኪሎው ቡድን (የፀረ-ተሐድሶ ሰባክያን ጥምረት አባላትን ለማለት ነው) አባላትም መገለል ይገባቸዋል፤. . .” በሚል ለማድረግ ባቀዱት የተቃውሞ ትዕይንት ላይ ለመምከር ነው ተብሏል፡፡

የሕገ ወጦቹን የተቃውሞ ትዕይንት በማድመቅ ያግዛሉ የተባሉ፣ በማወቅም ባለማወቅም በጥቅም እና በሐሰተኛ ቅስቀሳ የተደለሉ ግለሰቦች ከክብረ መንግሥት፣ ዲላ እና በአሁኑ ወቅት እንደ መላኩ ባወቀ ያሉ (ሎስ አንጀለስ አሜሪካ ነዋሪ የሆነ) ነዋሪ የፕሮቴስታንታዊ-ተሐድሶ-ኑፋቄ ተከታዮች ከተሰበሰቡበት ሐረር ከእያንዳንዳቸው ከ20 - 30 በሚሆን ቁጥር ወደ አዲስ አበባ እንዲመጡ አድርገዋል፤ እንዲሁም ከሁለት የቤተ ክርስቲያኒቱ ከፍተኛ ትምህርት ተቋማት በድብቅ የመለመሏቸውን ከ15 - 30 የሚሆኑ ግለሰቦችን ያሳትፋሉም ተብሏል፡፡

ጉዳዩን ለሚከታተሉ ታዛቢዎች አስገራሚ የሆነው ሕገ ወጦቹ ለአንዳንድ ግለሰቦችና አካላት ጥሪ ያደረጉት “እንደ ተቋም ኢትዮጵያ ውስጥ የለም፤ ካለ ቢሮውን አሳዩን” እያሉ የሚዘብቱበትን ተሐድሶን ለመቃወም በሚል ማጭበርበሪያ መሆኑ ተጠቁሟል፡፡ ለአብነትም ያህል የዜናው ምንጮች እንዳስረዱት፣ ሕገ ወጦቹ “የጥምቀት ተመላሽ ወጣቶች ማኅበር” አስተባባሪዎችንና አባላትን በተቃውሞ ትዕይንታቸው እንዲተባበሯቸው ያግባቧቸው በዚህ መልክ ነበር - ከአንዲቷ በቀር ብዙም አልተሳካላቸውም እንጂ፡፡

ሕገ ወጦቹ ከቤተ ክርስቲያኗ ከፍተኛ ትምህርት ተቋማት በአሰግድ ሣህሉ እና ናትናኤል መሪነት በድብቅ የመለመሏቸው ደቀ መዛሙርት የአገልግሎት ልብሳቸውን እንደለበሱ ወጥተው እንዲያጅቧቸው በማስታወቃቸው ለሃይማኖታቸው ቀናዒ ከሆኑ ደቀ መዛሙርት ከፍተኛ ተቃውሞ ገጥሟቸዋል፤ ት/ቤቱን ወክሎ፣ ቀሚስ ለብሶ በሕገ ወጦቹ ትዕይንት ላይ በሚሳተፍ ተማሪ ላይም ተቋማቱ ርምጃ እንዲወስዱባቸው ማሳሰባቸው ተመልክቷል፡፡


ሕገ ወጦቹ ጥቅምት 12 ቀን 2004 ዓ.ም የቅዱስ ሲኖዶስ ምልአተ ጉባኤ በጸሎት በሚከፈትበት የመንበረ ፓትርያርክ ቅድስተ ቅዱሳን ማርያም ገዳም  በብፁዓን ሊቃነ ጳጳሳ ፊት ተመሳሳይ የተቃውሞ ትዕይንት ለማድረግ ዐቅደዋል ተብሏል፡፡ የገዳሙ አስተዳደር በበኩሉ ድርጊቱ አዋኪ መሆኑን በመግለጽ በቅጽሩ አንዳችም ስብሰባ ማካሄድ እንደማይቻል የሚገልጽ ማሳሰቢያ ዛሬ ከቀትር በኋላ አውጥቷል፡፡ የአዲስ አበባ ሰንበት ት/ቤቶች አንድነት አመራርም ሕገ ወጦቹ የፀረ-ፕሮቴስታንታዊ-ተሐድሶ እንቅስቃሴን ለመቃወም ለሚያደርጉት ትዕይንት የፀረ-ተቃውሞ ትዕይንት በማካሄድ ይመክቱ ዘንድ መላው የአዲስ አበባ ሰንበት ት/ቤቶች ወጣቶች ቅዳሜ ከቀኑ 6:00 ላይ በመ/ፓ/ቅ/ቅ ማርያም አካባቢ እንዲገኙ ጥሪውን አስተላልፏል፡፡

የአዲስ አበባ ሰንበት ት/ቤቶች በሕገ ወጦቹ የተቃውሞ ትዕይንት ውስጥ ተባባሪ እንደሆኑ የሚነገርላቸውን የማደረጃ መምሪያው ዋና ሓላፊ አባ ሰረቀን ጨምሮ በፕሮቴስታንታዊ ተሐድሶ የሚጠረጠሩ በርካታ ግለሰቦች የተካተቱበት፣ ባለ አምስት ጥራዝ የሰነድ ማስረጃ እና 14 ቪሲዲዎችን ይዘታቸውን ከሚያብራራና በአምስት ምዕራፍ የተከፈለ ባለ 45 ገጽ መግለጫ ለአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት ጽ/ቤት ካስረከቡ በኋላ ጽ/ቤቱ ኮሚቴ አቋቁሞ ሰነዶቹን ካጠና በኋላ ለቅዱስ ሲኖዶስ እንዲሁም ለመ/ፓ/ጠ/ቤ/ክ የዋና ሥራ አስኪያጅ ጽ/ቤቶች እንዲደርስ መደረጉ ታውቋል፡፡

በ45 ገጾች የተጠናቀረው የማስረጃ ሰነዱ መግለጫ የመጀመሪያ ምዕራፍ፣ የሰንበት ት/ቤቶች ማደራጃ መምሪያ በቃለ ዐዋዲው እና በ1986 ዓ.ም በቅዱስ ሲኖዶስ ጸድቆ ከተሰጠው ደንብ አኳያ ሓላፊነቱን አለመወጣቱን፣ በምትኩ ከተልኮው ውጭ እየሠራ እንደ ስብከተ ወንጌልና ሐዋርያዊ ተልእኮ ባሉት መምሪያዎች ተግባራት ውስጥ ጣልቃ እንደሚገባ፣ ዋና ሓላፊው የሃይማኖት ሕጸጽ እና የሥራ አመራር አቅም ማነስ እንዳለባቸው ያትታል፡፡

ሁለተኛው የማስረጃ ሰነዱ መግለጫ፣ ቅዱስ ሲኖዶስ በተለያዩ ጊዜያት ባሳለፋቸው ውሳኔዎች በውግዘት የተለዩ እንዳሉ አመልክቷል፤ ቀኖና የተቀበሉ እንዳሉም በማስታወስ ቀኖናቸውን ሳይፈጽሙ ወይነው ወደለየለት ክሕደት በመግባት እያወኩ የሚገኙትን በስም ዘርዝሯል፡፡ አባ ሰረቀ በሕገ ወጥ ሰባክያንና ዘማርያን ላይ ቅዱስ ሲኖዶስ ያስተላለፈው መመሪያ እንዳይፈጸም ለማስተጓጎል ሙከራ እንደሚያደርጉ ገልጧል፡፡ ከዚህም በላይ የተሰጣቸውን ሓላፊነት ተገን በማድረግ በሥራቸው አጋጣሚ ያገኟቸውን ሰነዶች ለተሐድሶ መናፍቃን መሣሪያነት እንዲውል መተባበራቸውን መግለጫው አስረድቷል፡፡


ሦስተኛው የማስረጃ ሰነዱ መግለጫ በአራት ንሳን ክፍሎች የተቀመረ ነው፡፡ በመጀመሪያው ንዑስ ክፍሉ የፕሮቴስታንታዊ-ተሐድሶን አደጋ እውንነት በማስረገጥ ከ1990 ዓ.ም አንሥቶ ካለው ሂደት በመነሣት ቅዱስ ሲኖዶስ የወሰናቸውን ውሳኔዎች እና በሊቃውንት ጉባኤ የወጡ ኅትመቶችን በማጣቀስ በምንነቱ ላይ ትንተና ያቀርባል፡፡ ከሁለተኛ እስከ አራተኛ እንደ ቅደም ተከተላቸው ባሉት ንዑሳን ክፍሎች የፕሮቴስታንታዊ ተሐድሶ አራማጆችን ማንነት በፈርጅ በፈርጁ ከፋፍሎ ይዘረዝራል፤ በዚህም መሠረት፡-
  • አባ ሰረቀን ጨምሮ፣ “ድንግል ማርያም ጥንተ አብሶ አለባት” ብለው ያስተማሩቱ፤
  • የደቂቀ እስጢፋኖስን አስተምህሮ በመደገፍ ተኣምረ ማርያምን፣ በላትን ማክበርንና የመሳሰለውን ሥርት እና የተቀደሰ ክርስቲያናዊ ትውፊት በመንቀፍ ያስተማሩ፤
  • በነገረ ማርያም እና በክብረ ቅዱሳን ላይ የለየለት ፕሮቴስታንታዊ ትምህርት በማስተማር የተሐድሶ ኑፋቄን የሚያራምዱ፤
  • በዐጸደ ሥጋ ባይኖሩም ያስተማሩት ክሕደት እና የጻፏቸው መጻሕፍት ለፕሮቴስታንታዊ ተሐድሶ ኑፋቄ በማስረጃነት የተያዘባቸው ናቸው ያሏቸ
 በተሐድሶነት መናፍቅነት ተጠርጥረዋል፡፡

በምዕራፍ አራት የማስረጃ ሰነዱ መግለጫ፣ የፕሮቴስንታዊ-ተሐድሶ ኑፋቄን አስተሳሰብ በማስተጋባት የሚታወቁ የኅትመት እና ኤሌክትሮኒክስ ሚዲያዎች እንዲሁም የቴሌቪዥን ቶክሾዎች በስም ተዘርዝረዋል፡፡

በመጨረሻውና በምዕራፍ አምስት የመግለጫው ክፍል ላይ፣ ባሕታውያንና አጥማቂዎች ከሥርተ ቤተ ክርስቲያን ውጭ በየመንደሩ እና በየዐውደ ምሕረቱ በሚፈጽሙት ተግባር የሚደርሰውን ጉዳት በመዘርዘር በሲኖዶሱ መመሪያ መሠረት ርምጃ እንዲወሰድባቸው ይጠይቃል፡፡

እንግዲህ በፊደል ሬስቶራንቱ ኤፍሬም ኤርሚያስ፣ አባ ሰረቀ እና ወ/ሮ እጅጋየሁ በየነ አይዟችሁ ባይነት የሚገፋው የእነ በጋሻው ሕገ ወጥ ቡድን ነገ እና ከነገ በስቲያ ለማድረግ ያሰበው የተቃውሞ ትዕይንት፣ ማንነታቸውን ከመሠረቱ ዕርቃኑን ካወጣባቸው ማስረጃ በተነጻጻሪ ማስረጃ አልያም በንስሐ ሳይሆን በአስተዳደራዊ ውሳኔ በአቋራጭ ለመናጻት የሚያደርጉት መሯሯጥ እንደሆነ ለመረዳት አይከብድም፡፡

በሌላ በኩል የፀረ-ተሐድሶ ሰባክያን ጥምረት ከ22,173 በላይ ካህናት፣ ዲያቆናት፣ ምእመናንን፣ ምእመናትን የድጋፍ ፊርማ ባሰባሰቡበትና ለቅዱስ ሲኖዶስ ጽ/ቤት፣ ለመ/ፓ/ጠ/ቤ/ክ የዋና ሥራ አስኪያጅ ጽ/ቤት እና ለብፁዓን ሊቃነ ጳጳሳት ያሰራጩት ባለስምንት ነጥብ የአቋም መግለጫም ሕገ ወጦቹ የነገውን ዐይነት የተቃውሞ ትዕይንት ለማካሄድ እንዲገደዱ አድርጓቸው ሊሆን እንደሚችል ተገልጧል፡፡

የቤተ ክርስቲያኒቱን ልብሰ ተክህኖ በመልበስ በገዛ ዐውደ ምሕረቷ ላይ ጽርፈት እና ኑፋቄ የተቀላቀለበትን ትምህርት በማስተማር “ነጠላ የለበሰ መናፍቅ”፣ “ማዕተቡን ያልበጠሰ መናፍቅ” ለመልመል እየተንቀሳቀሱ ነው ያለው መግለጫው፣ የተሐድሶ መናፍቃን በሁሉም አህጉረ ስብከት በሚያደርጉት ስልታዊ ዘመቻ የፓትርያርኩን ድጋፍ ማግኘታቸውን አጋልጧል፡፡ አያይዞም የተሐድሶ መናፍቃኑ ቤተ ክህነቱ በአስተዳደርና በችግር አፈታት ስልት፣ በገንዘብ አጠቃቀምና መረጃ አያያዝ ያሉበትን ክፍተቶች በመጠቀም አባቶችን በመከፋፈልና በጥቅማ ጥቅም በመደለል ዓላማቸውን እያራመዱ እንደሚገኙ ገልጧል፡፡

በአቋም መግለጫው ተራ ቁጥር ሰባት ላይ በቅዱስ ሲኖዶስ ተጠንቶ ውሳኔ እስካልተሰጠበት ድረስ፣ ዲያቆን በጋሻው ደሳለኝ እና ዲያቆን አሰግድ ሣህሉ በቤተ ክርስቲያኒቱ ስም በየትኛውም የኅትመት ይሁን የኤሌክትሮኒክስ ሚዲያ ትምህርት ይሁን መግለጫ እንዳይሰጡ ጥብቅ ቁጥጥርና መመሪያ እንዲሰጥ ጥምረቱ ጠይቋል፡፡
                                                                                             

  


7 comments:

Anonymous said...

Yihiin teqawumoo yelibiyaa weyis yee gibtsi gira gebban poletika weyis haymaanot.wegen andbel goaraa leyyiteh tewaaga."Negeru iskitaara wed qiltu kaara ale sewuyyewu be hihadeg gimgema lay 1986am.
Egaa maal jennaree mana isaati jalqabe.MN Irraa.

Anonymous said...

እባካችሁ ሁላችንም ስለ ቤተክርስቲያን ሰላም እና ደህንነት እንጸልይ! እግዚአብሄርም ይረዳናል!!!!
መ.ዘ ከሽሮሜዳ

lele said...

AMELAKA GEIORGISE EREDANE

Hailegiorgis said...

መለያየት የኃጢአት ውጤት እንደሆነ ሁሉ፣ አንድነት ደግሞ የሰለም፣ የፍቅርና የስምምነት ውጤት ነው ፡፡ ኤፌ. 2፡14-15
የሰው ልጅ በተከተለው የተሳሳተ አማራጭ ከእግዚአብሔር ጋር የነበረውን ኅብረት ወይም ግንኙነት ሲያጣ ከሌሎች ፍጠረታት ጋር የነበረውን አንድነትም በተመሳሳይ አጥቶአል፤ ይልቁንም የእርስ በርስ መግባባት በመጥፋቱ የሰው ዘር በተለያየ ጎራ እየተሠለፈ በጥላቻ መተያየቱ የዘወትር ክስተት ሆነ ፡፡ የተከሰተው መለያየት በሥጋዊ ሕይወት ብቻ ሳይሆን በመንፈሳዊ ሕይወትም ጭምር ነበር፤ ጌታችን፣ አምላካችን፣ መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ወደዚህ ዓለም ከመምጣቱ በፊት ዓለማችን በመንፈሳዊ ሕይወቷ በሁለት ጎራ ተለይታ ትኖር ነበር፤ በአምልኮተ እግዚአብሔርና በአምለኮተ ጣዖት፡፡ እግዚአብሔርን ሲያመልኩ የነበሩ እሥራኤላውያን ሕዝበ እግዚአብሔር ተብለው ሲጠሩ፣ ጣዖትን ያመልኩ የነበሩትም ጣዖት አምላኪዎች ይባሉ ነበር፡፡
ሁለቱም ወገኖች የማይግባቡና በከፋ ጥላቻ ይኖሩ የነበሩ ናቸው፤ ቢሆንም ጥላቸው በእግዚአብሔር ዘንድ ተቀባይነት አልነበረውምና ይህን የሚያስወግድ የእግዚአብሔር ጥበብ በዓለም እንዲገለጥ የእግዚአብሔር አምላካዊ እቅድ ነበር፤ ይህም እቅድ በጌታችን በአምላካችንና በመድኃኒታችን በኢየሱስ ክርስቶስ ተፈጻሚ ሆነ፡፡
የሰው ጠላቶች ኃጢአትና እርሱን ተከትሎ የመጣው መለያየት ነው፤ የእግዚአብሔር ጥበባዊ አሠራርም ያነጣጠረው በኃጢአትና በውጤቶቹ ላይ ነው፡፡ በመሆኑም ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በመስቀል ላይ ተሰቅሎ ባፈሰሰው ደሙ ኃጢአትን፣ ጥላቻንና መለያየትን ገደለ፤ የግድ ነውና ኃጢአት ሲጠፋ መለያየቱም ቀረ ፡፡ የጌታችን የመድኃኒታችን የኢየሱስ ክርስቶስ ነገረ መስቀል ሰዎች የሚድኑት ክርስቶስን በማመን በሚገኝ ጽድቅና እርሱን ተከትሎ በሚፈጸም ስነ ምግባር እንጂ እስራኤል በኦሪታቸው አሕዛብ በጣዖታዊና በባህላዊ እምነታቸው አለመሆኑን አረጋገጠ፡፡
በመስቀሉ የተገኘ ሰላምና ዕርቅ ሁለቱም ወገኖች የነበራቸውን ልዩነት በመተው ሁሉም በአንዲት ቅድስት ቤተ ክርስቲያን እንዲሰበሰቡ በማስቻሉ የመስቀሉ ውጤት ሰላም፣ ዕርቅና ስምምነት ሆነ፤ ከዚህም የተነሣ በመስቀሉ ጥልን ገደለ፣ ሁለቱንም ወገኖች አስታርቆ አንድ አደረገ፣ ሰላምንም አወጀ ተብሎ ተበሰረ ፡፡ ኤፌ. 2፡14-15
የመስቀሉ ነገር ማለት የወንጌል ትምህርት ማለት ነው፤ የወንጌል ትምህርት ደግሞ እኩልነትን እንጂ መበላለጥን፣ አንድነትን እንጂ መለያየትን ሰላም፣ ፍቅር፣ ስምምነትን እንጂ ጥላቻን አያስተናግድም፤ ለዚህም ነው መስቀል ሰላማችን ነው በማለት ቅዱስ መጽሐፍ የሚያስተምረን ፡፡ የመስቀል ዕርቅ በእግዚአብሔር ዘንድ የተከናወነ መሠረታዊ እርቅ ነውና በሰዎችና በሰዎች መካከል የነበረውን ጥልና መለያየት ማስወገድ ብቻ ሳይሆን ከዚያም በላይ ነው፤ ኃጢአት ሰውን የለየው ከብዙ ነገር ነው፤ ይሁንና ጌታችን አምላካችንና መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በመስቀል ላይ ሆኖ በፈጸመው የማስታረቅ ተግባር በሰማይና በምድር ያሉትን ሁሉ አስታረቀ፡፡ ስለሆነም በመስቀል ላይ በከፈለው መሥዋዕትነትና ባፈሰሰው ደሙ በሰማይና በምድር የነበሩትን ሁሉ በማስታረቅ ሰላምን አደረገ ተብሎ የምሥራቹ ተነገረን፤ ሰው በኃጢአት ምክንያት ያጣውን ሁሉ በመስቀሉ ኃይል ማግኘትን ችሏል፡፡
ዛሬ በእግዚአብሔር ምሕረትና ይቅርታ ሀገራችን ኢትዮጵያ ከቀድሞ ጀምሮ በእግዚአብሔር ዘንድ የተመሰከረላትን የሃይማኖትና የአንድነት ጉዞ ተከትላ ወደፊት እየገሰገሰች የምትገኝበት ጊዜ ነው ፡፡ የመስቀሉ ዓላማ ልዩነትን በማስወገድ አንድነትንና ሰላምን ማረጋገጥ ነው፤ ይህ የአንድነት ሰንሰለት እስከመቼም ቢሆን መበጠስ የሌለበት ነው፡፡ ስለሆነም መለያየት የኃጢአት ውጤት እንደሆነ ሁሉ፣ አንድነት ደግሞ የሰለም፣ የፍቅርና የስምምነት ውጤት ነው ፡፡ ኤፌ. 2፡14-15 አሜን!

Anonymous said...

Hailegiorgis, God Bless you. If we are a true christian, we have to know what you are talking about, but the big problem is in our country there is no the true Wongel precher. If they see one or two V.Good Wongel Sebakiyan, they get jelose and divided, and calling names.
"Christ is the light of the world"
If the false acusiation people come to this light, every thing what they do, will show with this light. But right now they are in Dark. God open the False acusiation pepele eye, and let them stop being divided people.

I wish Others like you understant the truth.

Anonymous said...

Selam Hailegiorgis,

In the words you said you got it right but the problem is with those who came openly preaching the same words of your saying but inside to inject heretic teachings that does not belong to the Holly Church.
Just to save the church and its children from such heretics, what should we do? I mean other than praying? You understand what I am saying. Heretics come with purpose and plan; they keep throwing anything and everything in their capacity to dismantle the church. They are the dead evils who want to take everybody to their deadly devilish life. Thus what reactions should we have to abort these devilish plans? You know the church never folds her hand to embrace those who would come back to its bosom through repent and confession. But, from my experience the heretics who come with the deadly mission never repent but keep trying to execute their plans with many multifaceted methods. So our struggle is with these people? What do you suggest what we should as individuals and groups who belong to the Holly Church to defend the spiritual and physical treasures of the Church?

Anonymous said...

Thank you, Hailegorgis. our church need a person like you.

Blog Archive

የአቡነ ጳውሎስ "ሐውልተ ስምዕ"

ነጻ ፓትርያርክ ምርጫ ቢሆን ኖሮ ማንን ይመርጡ ነበር? እንበልና ሁሉም ነገር ሥርዓቱን ጠብቆ የተከናወነ የእጩዎች ምርጫ ቢሆን ኖሮ፣ አሁን የምናነሣቸው ጉድለቶች ባይኖሩ ኖሮ፣ 6ኛው ፓትርያርክ እንዲሆን የምትመርጡት ማንን ነበር? (ማሳሰቢያ፦ አሁን ያለው ክፍፍል እና የመንግሥት ተጽዕኖ ባይኖር ኖሮ ተብሎ የሚመለስ ጥያቄ ነው። የምን “ባይኖር ኖሮ ነው” የሚል አስተያየት ካለዎትም እናከብራለን።)