October 17, 2011

በሃይማኖት አክራሪነት እና ጽንፈኝነት ዙሪያ የተጀመረው ውይይት ቀጥሏል

  • “ሂቃብ”ን የሚከለክል መመሪያ ሊወጣ ነው::
(Addiss Admas):- ልማት ዴሞክራሲ እና የሃይማኖት አክራሪነት” በሚል ሰነድ ላይ በመመሥረት የፌዴራል ጉዳዮች ሚኒስቴር መስከረም 25 ቀን 2004 ዓ.ም በፌዴራል ፖሊስ ዋና መሥሪያ ቤት ከመገናኛ ብዙሃን አካላት እና ባለሞያዎች ጋር የጀመረውን ውይይት በመቀጠል ከዘጠኝ የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ተማሪዎች እና ድጋፍ ሰጪ ሠራተኞች ጋር ውይይት በማካሄድ ላይ ነው፡፡


ውይይቱ በቀጣይ 12 ዩኒቨርስቲዎች የሚካሄድ ሲሆን ባለፈው ሳምንት አጋማሽ የተጀመረው ውይይት ዘጠኝ ዩኒቨርስቲዎችን ያካተተ መሆኑ ተገልጿል፡፡ ውይይቱ “ሰላማዊ የመማር ማስተማር ሂደት በከፍተኛ ትምህርት ተቋማት”፣ “የ2003 ዓ.ም የትምህርት ዕቅድ አፈጻጸም”፣ “ኅብረ ብሔራዊ ፌዴራሊዝም”፣ “ልማት፣ ዴሞክራሲ እና የሃይማኖት አክራሪነት” እና “በከፍተኛ ትምህርት ተቋማት የአምልኮ፣ የአለባበስ እና የአመጋገብ ሥርዓቱ ምን መሆን አለበት?” በሚሉ ርእሶች ዙሪያ እንደሚያተኩር ተጠቁሟል፡፡ በዚህ ርእስ ስር በተደረገው ውይይት “ሂቃብ” (ሙስሊሞች ፊታቸውን ለመሸፈን የሚያደርጉት ጥቁር ሽፋን) የሚከለክል መመሪያ እንደሚወጣ ተጠቁሟል፡፡ የፌዴራል ጉዳዮች ሚኒስቴር ሚኒስትር ዶ/ር ሽፈራው ተክለማርያም፣ የሃይማኖትና እምነት ጉዳዮች ዳይሬክተር ጀነራል አቶ መረሳ ረዳ እና ሌሎችም የሚኒስትሩ ሓላፊዎች ከዩኒቨርስቲዎች ፕሬዚዳንቶች እና ቦርድ አባላት ጋር በመሆን ውይይቶቹን በመምራት ላይ ይገኛሉ፡፡
ከመገናኛ ብዙኅን አካላት እና ባለሞያዎች ጋር ተካሂዶ በነበረው የአንድ ቀን ውይይት “ልማት፣ ዴሞክራሲ እና የሃይማኖት አክራሪነት” በሚል ርእስ የተዘጋጀውና በአቶ መረሳ ረደ በቀረበው ሰነድ ላይ በአብዛኛው በሙስሊሙ ሃይማኖት አስተምህሮ ላይ ተመስርተው ከሚዘጋጁ የኅትመት መገናኛ ብዙኅን ከመጡ ተሳታፊዎች ጠንካራ ጥያቄዎች እና አስተያየቶች ቀርበዋል፡፡
“በኢፌዲሪ ሕገመንግሥት ላይ መንግስትና ሃይማኖት የተለያዩ ናቸው፤ መንግሥት በሃይማኖት ጉዳይ ጣልቃ አይገባም ሃይማኖትም በመንግሥት ጉዳይ ጣልቃ አይገባም” የሚለው የአቶ መረሳ ሰነድ፤ በሃይማኖት ሽፋን ልማትን የሚያደናቅፍ ማንኛውም አካል ከሕገመንግስቱ አንፃር “አክራሪ” እንደሚባል ይተነትናል፡፡ አንድን ሃይማኖት ነባር ሌላውን ጠላት አድርጐ ማቅረብ፣ ሃገሪቱን የአንድ ሃይማኖት ተከታይ ሃገር ብቻ አድርጐ ማቅረብ፣ መንግሥትን ከሃይማኖት ገለልተኛ አድርጐ አለማቅረብ፣ የአንድ ሃይማኖት ተከታዮች የሌላውን ሃይማኖት ተከታዮች ጠላት አድርጐ ማቅረብ ሕገመንግስቱን የሚፃረር እና ከአክራሪነት የሚያስፈርድ ተግባር ነው፤ ተብሏል፡፡
የአቶ መረሳን ትንተናን መሠረት አድርገው አስተያየት የሰጡት “የሙስሊሞች ጉዳይ” መጽሔት አዘጋጆች “መንግሥት አብዛኛው የሙስሊም ማኅበረሰብ የማይቀበለውን አሕባሽ የተባለውን አስተምህሮ በግልጽ በመደገፍ፣ ወሃቢይን በመቃወምና በአክራሪነት በመፈረጅ አንዱን አክራሪ አንዱን እንደ ቅዱስ መንገድ በማቅረብ የሙስሊም ሊቃውንት መስጠት የሚገባቸውን ብያኔ እየሰጠ ጣልቃ ገብቷል፡፡ በሙስሊሙ ማኅበረሰብ የመንግስት ጣልቃ ገብነት ጐልቶ ነው የሚታየው፡፡” በማለት ሚኒስቴሩ በሃይማኖት ጉዳይ ላይ የሚያደርገውን ውይይት ተችተዋል፡፡ መንግሥት በሕገ መንግሥቱ ከተደነገገው በተፃራሪ በተጠቀሰው መልኩ የሚያደርገውን እንቅስቃሴ በጣልቃ ገብነት በመኮነን በሚጽፉበት ወቅት በአክራሪነት መፈረጃቸው አግባብ አለመሆኑንም አዘጋጆቹ አስረድተዋል፡፡
አያይዘውም የእስልምና ጉዳዮች ም/ቤት “በሕዝበ ሙስሊሙ ያልተመረጠ መጅሊስ” መሆኑን በማመልከት መንግሥት ከመጅሊሱ ጋር አብሮ መሥራቱ ጣልቃ ገብነትና ሕዝብ ሙስሊሙን ያሳዘነ መሆኑን ገልፀዋል፡፡
በማኅበረ ቅዱሳን የሚታተመው የስምዐ ጽድቅ ጋዜጣ ዋና አዘጋጅ የሆኑት አቶ ዐሥራት ከበደ፣ ሃይማኖታዊ መገናኛ ብዙኅን ለቆሙለት እምነት ጥብቅና የሚቆምና የሚከራከር (Apologetic) ዘገባ ማውጣታቸው በአክራሪነት ሊያስፈርጃቸው ይችል እንደሆነ ጥያቄ አቅርበዋል፡፡ ከዚሁ ጋዜጣ ተወክለው የመጡት ዲያቆን ታደሰ ወርቁ በበኩላቸው፤ “የሃይማኖት ተቋማትን የሚወክለው ከፍተኛ አካል በተዳከመ ቁጥር ተቋማዊ አሠራሩም ይዳከማል፤ ይህም ከተቋሙ ውስጥ የሚወጡና ምእመኑን በተሳሳተ አቅጣጫ የሚመሩ ተስፈንጣሪ ግለሰቦች ጐልተው እንዲታዩ ምክንያት ይሆናል፡፡ አንዱ ሃይማኖት የሌላውን ሃይማኖት አስተምህሮ መረዳት ይኖርበታል፡፡ ለምሳሌ ያህል በመጽሐፍ ቅዱሳችን አንድ ሃይማኖት፣ አንድ ጌታ፣ አንዲት ጥምቀት እንዳለች የሚናገረው ጥቅስ የክርስትና ሃይማኖት መሠረታዊ አስተምህሮ እንጂ ሌሎች ሃይማኖቶች የሉም ወይም አይኖሩም ማለት እንዳልሆነ መገንዘብ ያስፈልጋል፡፡ ይህም በሃይማኖቶች መካከል ለኖረው መከባበር እና መጠበቅ አስተዋጽኦ እንዳለው በአንፃራዊ ትምህርተ መለኮት የምንረዳው ነው፡፡ ከዚህ አኳያ በአገራችን በየትኛውም ዘመንና አካባቢ በታሪክ አጋጣሚ የተፈፀሙ ስሕተቶች አሉ ከተባለ የጋራ ታሪክ አድርጐ መቀበል እንጂ አንዱ ሌላውን ለማጥቃትና ለመወንጀል መነሻ ማድረግ አይገባውም፡፡ እንዲያውም መንግሥት ሕገ መንግስቱን መሠረት አድርጐ ስህተት የተባለው ነገር እንዳይደገም ጥረት ማድረግ ይኖርበታል” በማለት ሰፊ አስተያየት ሰጥተዋል፡፡
ከተሳታፊዎች ለተነሱት ጥያቄዎች እና አስተያየቶች ዶ/ር ሽፈራው ተክለማርያም እና አቶ መረሳ ረዳ በየተራ ምላሽ ሰጥተዋል፡፡ ሚኒስትሩ ዶ/ር ሽፈራው “መንግሥት በሙስሊሙ ሃይማኖት ጣልቃ ስለመግባቱ” እንደ አስረጅ በቀረቡት ጥያቄዎችና አስተያየቶች ላይ በሰጡት ምላሽ፤ የእስልምና ጉዳዮች ም/ቤት ሕዝብ ሙስሊሙ በየደረጃ በመረጣቸው ተወካዮች የተቋቋመውና መንግሥትም ከም/ቤቱ ጋራ በመሥራት ላይ መሆኑን በማረጋገጥ፣ የቀረበው ሐሳብ አቅራቢው የተወከለበትን የሚዲያ ተቋም ብቻ የሚወክል መሆኑን ገልፀዋል፡፡ “መንግሥት አሕባሽን በመደገፍ ወሃቢይን እንደ አክራሪ ይመለከታል” ለሚለው መንግሥት ወሃቢይን በአክራሪነት የፈረጀው ሕገመንግሥቱን በተፃረረ መልኩ የእምነት ነፃነትን እና የሃይማኖት እኩልነትን በተግባር ስለሚቃወም፣ የሕዝብን ሰላም ልማትና ደህንነትን የሚያተራምስ ሥራ ስለሚሠራ፣ የእምነት ነፃነትን በመደፍጠጥ እስላማዊ መንግሥት ካልተቋቋመ በስተቀር ሌላ መንግሥት የለም በማለት በግልጽ ለጥፋት ስለሚንቀሳቀስ ነው” በሚል ዶ/ር ሽፈራው ምላሽ ሰጥተዋል፡፡
የወሃቢይን አስተምህሮ የሚከተሉ ግለሰቦች በድብቅ ቅስቀሳ በማድረግ፣ ለግጭት የሚዳርጉ መልዕክት ያላቸውን በራሪ ወረቀቶች እንደሚበትኑ ዶ/ር ሽፈራው ገልፀው በጅማ፣ በወለጋ፣ በኢሊባቡር፣ በምስራቅ ሐረርጌ እና በባሌ ለተከሰቱ የሃይማኖት ግጭቶች እና ጭፍጨፋዎች በዋናነት የወሃቢይ አስተምህሮ ተከታዮች እጅ እንዳለበት ጠቁመዋል፡፡ በሙስሊም ሃይማኖት አስተምህሮ ላይ ተመስርተው ለሚዘጋጁ የህትመት ውጤቶች የሚሠሩ አዘጋጆች በበኩላቸው፤ መንግስት በግልጽ እየደገፈው ያለው የአሕባሽ አስተምህሮ ሙስሊሞችን ከክርስቲያን ወንድሞቻቸው ጋራ የሚያጣላ ተቀባይነት የሌለው ነው ሲሉ አጣጥለውታል፡፡
የኢትዮጵያ ሙስሊም ነፃ ጋዜጠኞች ኅብረትን ወክለው የተገኙት ጊዜያዊ ሊቀመንበር፣ የሙስሊም ሕትመቶች አዘጋጆችን ሐሳብ በመቃወም የመንግስትን አቋም ደግፈው አስተያየት ሰጥተዋል፡
መንግሥት የራሱን የፖለቲካ አጀንዳ ለማራመድ ሲፈልግ ጣልቃ ይገባል፣ የፖለቲካ ፓርቲዎች በሃይማኖት ሽፋን ሕዝብን የማተራመስ ሥራ ይሠራሉ፣ መንግሥት በሃይማኖት፣ ሃይማኖትም በመንግሥት ጣልቃ አይገባም ትላላችሁ፤ በበዓላት ቀን የሃይማኖት አባቶች የሚያስተላልፉት መልዕክት ግን የመንግሥት አጀንዳ ነው፤” በሚል ከሪፖርተር ጥያቄ ቀርቦ ነበር፡፡
የሃይማኖት አባቶች የሚያስተላልፉትን መልዕክት በተመለከተ የተነሳው ነጥብ ትክክል መሆኑን የተቀበሉት አቶ መረሳ፤ የሃይማኖት መሪዎች ለተከታዮቻቸው የሚያስተላልፉት መልዕክትም ሆነ ሰበካ ሃይማኖቱን የተመለከተ ብቻ ሊሆን እንደሚገባው ተናግረዋል፡፡ መንግሥት የራሱን የፖለቲካ አጀንዳ ለማራመድ ሲፈልግ ጣልቃ ይገባል ለተባለው ምላሽ ሳይሰጡ አልፈውታል፡፡

3 comments:

Anonymous said...

ሸጋ ጅማሬ ነው

Anonymous said...

ጥንቱን ነበር እንጂ መጥኖ መደቆስ አሁን ምን ያደርጋል …… አይ ወያኔ! ስንመክር ስንዘክር አልሰማ ብለህ

ርብቃ ከጀርመን said...

ሰላም ደጀሰላሞች እንደምን ከረማችሁ ጥሩ ዜናነው ያስነበባችሁን ምክንያቱም ከገሙ አይቀር ጥምብትነው የሚል አካሄድ መሄድያለብን አይመስለኝም መንግስትም ይሄን ነገር ለማስተዋል ቢዘገይም አሁንም ከልብ ከተነሳና ከልብ ከተሰራ እድሉ አለው ነገሮችን ለማስተካከል በኔበኩል ይበልያስብላል ጅማሬው !

Blog Archive

የአቡነ ጳውሎስ "ሐውልተ ስምዕ"

ነጻ ፓትርያርክ ምርጫ ቢሆን ኖሮ ማንን ይመርጡ ነበር? እንበልና ሁሉም ነገር ሥርዓቱን ጠብቆ የተከናወነ የእጩዎች ምርጫ ቢሆን ኖሮ፣ አሁን የምናነሣቸው ጉድለቶች ባይኖሩ ኖሮ፣ 6ኛው ፓትርያርክ እንዲሆን የምትመርጡት ማንን ነበር? (ማሳሰቢያ፦ አሁን ያለው ክፍፍል እና የመንግሥት ተጽዕኖ ባይኖር ኖሮ ተብሎ የሚመለስ ጥያቄ ነው። የምን “ባይኖር ኖሮ ነው” የሚል አስተያየት ካለዎትም እናከብራለን።)