October 14, 2011

“የኢ/ኦ/ተ/ቤ ምእመናን ዓለም አቀፍ ማሕበር” ጉባዔውን አካሄደ፣ ውሳኔዎችንም አስተላለፈ

(ደጀ ሰላም፤ ጥቅምት 3/2004 ዓ.ም፤ ኦክቶበር 14/2011)፦ በአሜሪካዋ የቴክሳስ ግዛት መቀመጫውን ያደረገው እና “የኢ/ኦ/ተ/ቤ ምእመናን ዓለም አቀፍ ማሕበር” የሚል ስያሜ ይዞ የሚንቀሳቀሰው የምዕመናን እንቅስቃሴ ሁለተኛ ዓመታዊ ጉባዔውን በማካሄድ ጠቃሚ ውሳኔዎችን ማሳለፉን የተላከልን መግለጫ ያመለክታል። ማሕበሩ ከዚህ በፊት የመጀመሪያ ጉባኤውን በ1999 ዓ.ም ያካሄደ ሲሆን አሁን የተደረገው ደግሞ ለሁለተኛ ጊዜ ነው።
በዋሺንግተን ዲሲዋ የቅ/ማርያም ቤተ ክርስቲያን የተደረገው ጉባዔ የሚከተሉትን ውሳኔዎች በማስተላለፍ የተጠናቀቀ ሲሆን ሙሉውን የማሕበሩን መግለጫ ይህንን በመጫን ማንበብ የሚቻል መሆኑን እናስታውሳለን።

ውሳኔዎች
 3.1  ስለ ቤተ ክርስቲያን አንድነት በመጀመሪያ ጉባዔ ያስተላለፈውን ውሳኔ አጥንቶ የምዕመናን ጉባዔ የቤተ     ክርስቲያናችን አንድነት ጉዳይ ለድርድር የማይቀርብ፣ እስኪፈጸም የሚከታተለው መሆኑን በዚህም አጋጣሚ እስካሁን በመደረግ ላይ ያሉትን ጥረቶች አመስግኖ፣ ለወደፊቱም ቢሆን ለሰላምና ለአንድነት የሚደረገውን ጥረት ሁሉ  እንደሚደግፍ አረጋግጧል።  አስፈላጊ ሆኖ ካገኘውም የራሱን ቡድን አቋቁሞ መከታተል እንደሚገባ አስገንዝቧል።
3.2   የአብነት ትምህርት ቤቶችን በሚመለክት እስካሁን በንቡረ ዕድ ገብረ ሕይወት የተቋቋመው ድርጅት  በማሕበረ   ቅዱሳንና በሌሎች ድርጅቶች የሚደረጉትን ጥረቶች አመስግኖ  የችግሩን መባባስና መስፋፋት ተንዝቦ ችግሩን ለመቋቋም የሚሻለውን ዘዴ ባንድ ወጥ ጠቅላላ አመራር መካሄዱን ተቀብሎና አምኖ ይህን የሚወስን አመራር ለማመቻቸት  አንድ ግብረ ሀይል ለማቋቋም ተስማምቷል።

3.3    የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርሰቲያንን የቅዳሴ ሥርዓት በእንግሊዝኛ በዓለም አቀፍ ቋንቋዎች ስለ ማቅረብ በርዕሰ ደብር አብርሃም መሪነት በዲያቆን ቤዛ ቢልልኝ ረዳትነት ተዘጋጅቶ የቀረበለትን በምስጋና አዳምጦ ስለ ጥረቱ አድንቆ ስራው  የሚያጓጓ በመሆኑ በተቻለ ፍጥነት ተጠቃሎ እንዲቀርብ አዘጋጆችን ተማጥኗል።  በሚያስፈልግ እርዳታ ሁሉ የምእምናን ማሕበር አንዲተባበር ጠይቋል።

3.4    በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርሰቲያን ታሪክ ምዕመናን ከአባቶች ካህናትና መነኮሳት ጋር በቅርብ በመተባበር ለቤተ ክርስቲያናችን ደህንነትና መስፋፋት ያበረከቱት አስተዋጽኦ ግዙፍ ነው። ብርታታቸውና አይበገሬነታቸውም የሚደነቅ ነው።  ይህ ሲወርድ ሲዋረድ ሳይበርድና ሳይደክም በመካሄዱ ይኸው  በዛሬውም ጊዜ ቤተ ክርስቲያናቸው እየገጠሟት ያሉትን ችግሮች በጸሎታቸው በመማጸን፣ በጉልበታቸውም በገንዘባቸውም በጠቅላላው ባላቸው አቅም ሁሉ እያደረጉ ያሉትን አስተዋጽኦ ጉባኤው በአጽንኦት ተገንዝቧል።  ወደፊትም ቢሆን ባገራችንም ውስጥ ሆነ በዓለም አቀፍ ደረጃ የተፈነጠቀውና እየተካሄዱ ያለት እንቅስቃሴዎች በቤተ ክርስቲያናችን ላይ እያደረሱ ያሉት ተጽእኖ አስጊ ደረጃ በመድረሱ፣ ምዕመናን ከማናቸውም ጊዜ ይልቅ ነቅተው መጠባበቅ እንዳለባቸው ጉባኤው ያሳስባል። በተጨማሪም የምእመናን ጉባኤ የጊዜውን ሁኔታ በማገናዘብና መዋቅሩን በማጠናከር  ጉልበቱን ገንዘቡንና የዲፕሎማሲ ጥበቡንና ኃይሉን በማስተባበር አስተዋጽኦ አንዲቀጥል አጥብቆ ያሳስባል።


3.5    ስለ ዴር ሡልጣን ገዳም በተደረገው ውይይት ገዳሙና በገዳሙ ውስጥ የሚኖሩት መነኮሳት የሚኖሩባቸው ክፍሎችና ቤቶች ባለመታደሳቸው ለጤና ጠንቅ ደረጃ እንደደረሱ በታላቅ ኀዘን ተገንዝቧል።  ሁለተኛ ይህን ጉዳይ በቅርበት ሆኖ የሚከታተለው በእሥራኤል ውስጥ የተቋቋመው ማህበረሰብ ይህን ጉዳይ ትኩረት ሰጥቶ የሚከታተል ልዩ ኮሚቴ መዋቀር ላይ መሆኑን በደስታ ካዳመጠ በኋላ፡-

3.5.1    በእሥራኤል የተቋቋመው የኢትዮጵያ ማኅበረሰብ ተወካዮች በመካከላችን በመገኘታቸው የተሰማንን ደስታ ለአባሎቻቸው ከአክብሮት ምሥጋና ጋር እንዲያቀርቡልን፣

3.5.2    ይህ ጉባዔ ባለው አቅም ሁሉ ሕዝቡን በማስተባባር በግንዛቤና በዲፕሎማሲም ረገድ ድጋፍ ለመስጠት ስምምነት መድረሱን፣

3.5.3    በወንድማችን በዶክተር ካሣ ከበደ ስለ ዴር ሡልጣን የተዘጋጀው ጥናት ተጠናክሮ ለግንዛቤ እንዲያገለግል እንዲታተም፣
3.5.4    የዴር ሡልጣን አንገብጋቢው ጉዳይ የኢትዮጵያና የዓለም ሕዝብ በቂ ግንዛቤ እንዲያገኝ አብያተ ክርስቲያናት ልዩ ልዩ ኢትዮጵያዊ ድርጅቶች እንዲሳተፉ እንዲተባበሩ አስፈላጊውን እንቅስቃሴ ማኅበሩ እንዲያካሂድ ተወስኗል።

3.6    ከኢትዮጵያ ውጭ የሚወለዱና በሕጻንነት መጥተው ኢትዮጵያዊ ባልሆኑ ባህሎች በማደግ የባህል ግጭቶች መፈንጠቃቸው አልቀረም።  እንደዚህ ያለውን ችግር ለመቋቋም ወይም ለመቀነስ ያገራቸውን ቋንቋ በማስተማር በተጨማሪም በዓለም አቀፍ ቋንቋዎች በማስተማር ለመግባቢያ የሚጠቅሙ ለእድሜ ደረጃ የሚያገለግሉ መማሪያ መጻሕፍት እንዲያዘጋጁ በማበረታታት ያስተማማሩን ውጤትም በምርምርና በመገምገም ልንቋቋመው አንድንችል፣ እንዲሁም ለልዩ ልዩ ቋንቋንዎች ለምሳሌ በእንግሊዝኛ  በመጠቀም የቤተ ክርስቲያናችን እምነትና ትምህርት በዓለም  ደረጃ እንዲስፋፋ  ጥረት እንዲደረግ ማስፈለጉ ታምኖበታል።

3.7    በተጨማሪም ማኅበሩ  የሚመራበትን ረቂቅ የውስጥ መተዳደሪያ ደንብ፣ የማኅበሩን አወቃቀርና ገንዘብም እንዴት ማመንጨት እንደሚቻል የተጠኑ ጥናቶች ቀርበውልን በሚቀጥሉት ሁለት ሳምንታት ሀሳቦችን በጽሁፍ ለማኅበሩ እንዲቀርብ ተጠይቋል። ከምዕመናኑ  የሚቀርቡት ልዩ ልዩ ሀሳቦች ተሰባስበው ወደ ተቋቋመው የማሕበሩ አመራር ተመርቶ፤ አጣርቶ በተግባር ላይ አንዲያውልና ወደፊት ለሚያስፈልገውም መሻሻል ቢያንስ ዘዴውን ቀይሶ ለሚቀጥለው ጉባኤ በማቅረብ እንዲያጸድቅ ኃላፊነት ተሰጥቷል።
Post a Comment

Blog Archive

የአቡነ ጳውሎስ "ሐውልተ ስምዕ"

ነጻ ፓትርያርክ ምርጫ ቢሆን ኖሮ ማንን ይመርጡ ነበር? እንበልና ሁሉም ነገር ሥርዓቱን ጠብቆ የተከናወነ የእጩዎች ምርጫ ቢሆን ኖሮ፣ አሁን የምናነሣቸው ጉድለቶች ባይኖሩ ኖሮ፣ 6ኛው ፓትርያርክ እንዲሆን የምትመርጡት ማንን ነበር? (ማሳሰቢያ፦ አሁን ያለው ክፍፍል እና የመንግሥት ተጽዕኖ ባይኖር ኖሮ ተብሎ የሚመለስ ጥያቄ ነው። የምን “ባይኖር ኖሮ ነው” የሚል አስተያየት ካለዎትም እናከብራለን።)