October 8, 2011

“የቤተ ክርስቲያን ፈተናዎች” መጽሐፍ ጸሐፊ በወንጀል ተጠየቁ


  • “በአዲስ አበባ ገዳማት እና አድባራት ከፍተኛ የገንዘብ ብክነት ተንሰራፍቶ ይገኛል”
  • “እየተፈጸመ ላለው አስተተዳደራዊ ብልሽት ሁሉ ቅዱስ ፓትርያሪኩ ተጠያቂ ናቸው”
(አዲስ አድማስ፣ ቅጽ 10 ቁጥር 612፣ ቅዳሜ መስከረም 27 ቀን 2004 ዓ.ም):- “የቤተ ክርስቲያን ፈተናዎች” በሚል ርእስ በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን የፋይናንስ እና የሰው ኀይል አስተዳደር ችግሮች እና የገንዘብ ምዝበራ ላይ ያተኮረ መጽሐፍ የጻፉት አቶ ምሐባው ከበደ ዓለሙ፣ “ሕዝብን በማነሣሣት ከባድ ወንጀል” በሚል መስከረም 16 ቀን 2004 ዓ.ም መጽሐፉን ከሚያስተዋውቁበትና ከሚያሰራጩበት መስቀል አደባባይ በፖሊስ ተይዘው ለአራት ቀናት ከታሰሩ በኋላ መስከረም 19 ቀን 2004 ዓ.ም መለቀቃቸው ተገለጸ፡፡ በዕለቱ ካዛንቺስ ወደሚገኘው ስድስተኛ ፖሊስ ጣቢያ የተወሰዱት ጸሐፊው፣ መጽሐፉን ለምን እንደጻፉና ማን መረጃ እንደሰጣቸው መጠየቃቸውን ለአዲስ አድማስ ገልጸዋል፡፡


አቶ ምሐባው መስከረም 18 ቀን 2004 ዓ.ም ሜክሲኮ በሚገኘው የአዲስ አበባ የመጀመሪያ ደረጃ ከተማ ነክ ፍ/ቤት የቀረቡ ሲሆን “ሕዝብን በሕዝብ ላይ የሚያነሣሣ መጽሐፍ በመጻፍ ከባድ ወንጀል” በመፈጸማቸው በቁጥጥር ሥር መዋላቸውን የገለጸው ፖሊስ ምርመራውን ለማጠናቀቅ ተጨማሪ ጊዜ ጠይቆባቸው ነበር፡፡ የተጠርጣሪው ጠበቃም ፖሊስ ተጨማሪ ጊዜ የጠየቀበትን ምክንያት እንዲያስረዳ የጠየቁ ቢሆንም ፖሊስ “የማጣራው ነገር ስላለኝ” በማለቱ ፍ/ቤቶ ለሰኞ መስከረም 22 ቀን 2004 ዓ.ም ቀጠሮ ሰጥቶ ነበር፡፡ ይሁንና ጸሐፊው በቀጠሮው ቀን ፍ/ቤት ሳይቀርቡ መስከረም 19 ቀን 2004 ዓ.ም ጠዋት ተጠርተው በዋስ ከእስር መለቀቃቸው ታውቋል፡፡ አቶ ምሐባው “ስንፈልግህ እንጠራሃለን” በመባላቸው ፍ/ቤት አለመቅረባቸውን ለአዲስ አድማስ ተናግረዋል፡፡

በቤተ ከርስቲያኒቱ ውስጥ የሚፈጠሩ አስተዳደራዊ ችግሮችን በዝምታ በማለፋችን በቤተ ክርስቲያን የአስተዳደር ሰዎች ዘንድ ብልሹ አመራር እንደ ትውፊት እንዲቆጠር መደረጉን በመጽሐፋቸው መግቢያ ላይ ያሰፈሩት ጸሐፊው፣ የመጽሐፋቸው ዓላማ አስተዳደራዊ ችግሮችን በግልጽ ማሳየትና ለመፍትሔው ሁሉም የሚጠበቅበትን እንዲያደርግ ከእያንዳንዱ ባለድርሻ አካል የሚጠበቀውን ማሳየት እንደሆነ አመልክተዋል፡፡

በፋይናንስ አስተዳደር ረገድ ከፍተኛ ብክነት መኖሩን በማስረጃ ያሳዩት ጸሐፊው፣ በተለይም በአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት አድባራት እና ገዳማት ብክነቱ ከጫፍ እስከ ጫፍ ተንሰራፍቶ እንደሚገኝ “በዳሰሳ ጥናት ለማረጋገጥ ተሞክሯል” ብለዋል፡፡ እንዲያውም አንዳንድ የደብር አለቆች በመኖሪያ ቤታቸው ሙዳዬ ምጽዋቶችን እንደሚቆጥሩ መረጋገጡን ለማጋለጥ ይሞክራሉ፡፡ “በፋይናንስ አስተዳደር ረገድ የኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያንን ያህል ችግር ያለበት ሌላ ምንም ተቋም ሊኖር አይችልም” በሚል ርግጠኛነት የጻፉት አቶ ምሐባው፣ እርሳቸው በሰበካ ጉባኤ አባልነት ባገለገሉባት የማኅደረ ስብሐት ቅድስት ልደታ ለማርያም ቤተ ክርስቲያን የሁሉም የገቢ መሥመሮች ትክክለኛ የገቢ መጠን እንደማይታወቅ ይጠቁማሉ፡፡ በዚህም ሳቢያ ከወጭ ገቢ በልዩነት እስከ ብር 3,168,227 ድረስ የት እንደገባ እንደማይታወቅ ከሐምሌ 1 ቀን 2002 ዓ.ም እስከ ነሐሴ 30 ቀን 2003 ዓ.ም የቀረበውን የሂሳብ ሪፖርት በመጥቀስ ያስረዳሉ፡፡

በቤተ ክርስቲያን ታሪክ የቤተ ክርስቲያን አስተዳደር “እናዳሁኑ ዘመን ተበላሽቶ አያውቅም” የሚሉት አቶ ምሐባው፣ “በማንኛውም መንገድ እየሆነ ላለው አስተዳደራዊ ብልሽት ሁሉ ቀዳሚ ተጠያቂ የሚሆኑት ቅዱስ ፓትርያሪኩ ናቸው፤” ብለዋል፡፡ ምክንያቱንም ሲያብራሩ፣ “ከማንኛውም ብልሹ ሥራ ጀርባ የፓትርያሪኩ እጅ እንዳለበት፣ የእረሳቸው እጅ ሳይኖርበት የተፈጠረ ብልሽት ካለም ወቅቱን በጠበቀና ሃይማኖታዊ በሆነ መንገድ የመፍታትና የማረም ሓላፊነትና ግዴታ ስላለባቸው ከተጠያቂነት ነጻ እንደማይሆኑ አስረድተዋል፡፡

ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ጳውሎስ ከተከበቡበት የሥጋ ዝምድና ወጥተው በመንፈሳዊ ዝምድና የሁሉም አባት መሆናቸውን ተገንዝበው፣ በየዘርፉ የሚያማክሩ ባለሞያ ሰዎችን የቅርብ ረዳቶች እንዲያደርጉ የመከሩት ጸሐፊው፣ “የሌቦች መደበቂያ በመሆን ባያገለግሉ መልካም ነው፤” ሲሉ ተችተዋል፡፡

የቤተ ክርስቲያኒቱ የመጨረሻው የበላይ አካል የሆነው ቅዱስ ሲኖዶስ በሚጠበቅበት መጠን እየሠራ ባለመሆኑ የወቀሱት አቶ ሙሐባው፣ ሲኖዶሱ ውሳኔውን ማስፈጸም አለመቻሉን ይጠቁማሉ፡፡ የአጥቢያ ቤተ ክርስቲያን ዕድገት እና ውድቀት በመወሰን ረገድ ወሳኝ የሆኑት የሰበካ መንፈሳዊ ጉባኤ አባላት ፍርሃትንና ጥቅመኛነትን አስወግደው፣ አላስፈላጊ ጣልቃ ገብነትን ተቋቁመው ዐቅዶ መሠውራትንና በዕቅዱ መሠረት ዝርዝር የአፈጻጸም ሪፖርት ለመረጣቸው አካል በማቅረብ ቤተ ክርስቲያን በልማት ጎዳና እንድትገሠግሥ፣ አገልጋዮቿም የተሻለ ሕይወት እንዲኖራቸው መጣር እንደሚገባቸው አሳስበዋል፡፡ ምእመናንም በብልሹ አሠራር የተጠመዱ አገልጋዮችን በማጋለጥ ወደ ሕግ እንዲያቀርቡ፣ የሰበካ ጉባኤ አባላት በየሦስት ወሩ ሪፖርት እንዲያቀርቡላቸው በመጠየቅ የቤተ ክርስቲያኒቱን አጠቃላይ እንቅስቃሴ በትኩረት መከታተል እንዳለባቸው መክረዋል፡፡

*አቶ ምሐባው ዓለሙ ከበደ በቅድስት ማርያም ዩኒቨርስቲ ኮሌጅ መምህርና የማኅደረ ስብሐት ልደታ ለማርያም እና ደብረ መድኃኒት መድኃኔዓለም ቤተ ክርስቲያን ሰንበት ት/ቤት ሰብሳቢ ናቸው፡፡
Post a Comment

Blog Archive

የአቡነ ጳውሎስ "ሐውልተ ስምዕ"

ነጻ ፓትርያርክ ምርጫ ቢሆን ኖሮ ማንን ይመርጡ ነበር? እንበልና ሁሉም ነገር ሥርዓቱን ጠብቆ የተከናወነ የእጩዎች ምርጫ ቢሆን ኖሮ፣ አሁን የምናነሣቸው ጉድለቶች ባይኖሩ ኖሮ፣ 6ኛው ፓትርያርክ እንዲሆን የምትመርጡት ማንን ነበር? (ማሳሰቢያ፦ አሁን ያለው ክፍፍል እና የመንግሥት ተጽዕኖ ባይኖር ኖሮ ተብሎ የሚመለስ ጥያቄ ነው። የምን “ባይኖር ኖሮ ነው” የሚል አስተያየት ካለዎትም እናከብራለን።)