October 4, 2011

"ሰሚ ጆሮ ያለው ይስማ"


(አብርሃም ሰሎሞን):- ሰው ሆኖ ለተፈጠረ ሰው እንዴት ይሳሳታል ብሎ ማሰብና መናገር ሰውዬውን ከሰው ግምት ውስጥ እንደማውጣት ይቆጠራል። የዚህ ጽሑፍ ዐቢይ መልእክት የሚሆነው የትናንቱ እንቅፋት ዛሬም እየደጋገገመ ሊመታን አይገባውም ለማለት ነው። አጋጣሚ እየጠበቁ የሚነሱ መናፍቃን ሁኔታዎች መንገድ ሲከፍቱላቸው ቢናገር ያሳምናል፤ ቢወረውር ያደርሳል፤ ቢመቱት ይመክታል፤ ቢይዙት ያመልጣል የሚሉትን ወጣት በጥቅም እየደለሉ ሀብት ያላትን ቤተ ክርስቲያንን  ሀብት እንደሌላት፤ ልጆች ያላትን ቤተ ክርስቲያንን ልጆች አልባ አድርገው ጥቅማቸውን ሲከታተሉና ኪሳቸውን ሲሞሉ ይታያሉ። የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን በየጊዜው ለተለያየ ፈተና የምትጋለጠውና በፈተናም የምትረታው የተለያዩ ችግሮች በተለያዩ አቅጣጫዎች ሲመጡባት ነው። ችግሮቹ ሁልጊዜ የሚያሸንፏትም ልጆቼ ያለቻቸው ቀላዋጭ ልጆቿ የባዕዳንን ትምህርትና ፍልስፍና ተቀብለው መልሰው ስለሚነክሱአት ነው። ምንጊዜም ቢሆን ችግሩ ሲፈጠር ታማኝ ልጆቿ ባንዳው ማን እንደሆነ ለይተው ስለሚያውቁት ተመለስ አታስጨርሰን በማለት ቃላቸውን ያሰማሉ። ትጠፋለች የተባለች ከተማ ነጋሪት ቢጎሰም አትሰማ ብለው አበው እንደመሰሉት ምሳሌ ማንነታቸውና ጥፋታቸው ቢነገራቸውም ቤታቸውን መልሰው የሚያጠቁና የሚያስጠቁ ባንዳዎች ጊዜያዊ ጥቅም ስለሚደልላቸው ከእውነት ይልቅ ውሸትን፣ ከፍቅር ይልቅ ገንዘብን፣ ከሃይማኖት ይልቅ ሥልጣንን በመውደድ የተነገራቸውን ሳይሰሙ ይቀራሉ እንጂ። አሁን መቆጨታችን ለትናንቱ ሳይሆን ዛሬም ሳንዘጋጅ የነገው መከራ እንዳይመጣብን ነው።

ላለፈው ክረምት ቤት አይሠራም የሚባለው ተረት ለሚመጣው ክረምትም ጣሪያው እንደተቀደደ ይጠብቅ አለማለት መሆኑ ለእያንዳንዳችን ግልጽ ነው። ትናንት የዝናብ ጠብታ ያስገባ የነበረ ቤት ዛሬ ጣሪያው ተነሥቶ ቤቱ መዝነቢያ ሲሆን ካየነው ለከርሞ ጎርፍ ይዞን እንዳይሄድ በበጋው መዘጋጀቱ ሰው ሆነን ለተፈጠርን ለእኛ ሊከብደን አይገባውም። ከአራዊትም፣ ሆነ ከእንስሳት እንዲሁም ከአእዋፋት መካከል መኖአቸውን በፀሐዩ ወቅት አከማችተው በዝናቡ ጊዜ የሚመገቡ ብዙ አሉና። እኛ እንደ ሰውነታችን ብንበልጥ እንጂ አናንስምና መናፍቃን ነገን ተመልክተው ዛሬ ሲያጠቁንና ሲለያዩን እያየን እኛ ነገን ሳይሆን ዛሬን እንኳን ተመልክተን በያለንበት በር ሰብሮ የመጣውን መናፍቅ ማስቆም ሲከብደን እንስተዋላለን። በእግዚአብሔር ስም የመጡ መናፍቃን አገር ሞልተዋል፤ በግል ጥቅም ታውረዋል፤ ከእኛነት ይልቅ እኔነትን ገንዘብ አድርገዋል፤ ከቤተ ክርስቲያን ክብር ይልቅ የእራሳቸውን ክብር አስቀድመዋል። ጌታችን በወንጌል ሌባው ሊሰርቅና ሊገድል ነው የሚመጣው እንዳለው ሁሉ ዛሬም ሌባው ወደ ኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን የሚመጣው ሊገላትና ሊሰርቃት ነው። ከሌሊቱ በየትኛው ሰዓት ሌባው የሚመጣበት አይታወቅምና ነቅታችሁ ጠብቁ ተብሎ እንደተጻፈ እኛም የሃይማኖት ሌቦች በየትኛው ሰዓት እንደሚመጡ ስለማናውቅ ነቅተን ልንጠባበቅ ያስፈልገናል። ወገባችን የታጠቀ መብራታችን የበራ ይሁን።

ሰልፉን ማን ይጀምር፤ ከየትስ ይጀመር?

ሰልፉን ምእመናን ከሚገለገሉበትና አገልግሎት ከሚሰጡበት ቤተ ክርስቲያን ይጀምሩት። ቅድሚያ ለግል ሕይወትና ሥራ በመስጠት የቤተ ክርስቲያንን አገልግሎት እየተከፈላቸው እንደ ሁለተኛ ሥራ አድርገው የተመለከቱና ጊዜ የፈጠረውን ይኽን አስከፊ ችግር በጸሎትም፣ በስብከትም፣ በመምራትም ሆነ በማስተባበር ሊቀርፉት ሲገባቸው ጆሮ ዳባ ልበስ በማለት የእረኝነት ኃላፊነታቸውን ዘንግተው የክህነት መታወቂያቸው ልብሳቸው ብቻ ሆኖ የሚስተዋለውን ዲያቆናትና ካህናት እንዲሁም ጳጳሳት በተለያየ ሁኔታ ትክክል አለመሆናቸውን በየተገኙበት ቦታ መንገር ያስፈልጋል። ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ የሁሉ ብልቶቻችን ሥራ ማየት ቢሆን መስማት ከየት ሊመጣ ነው? የሁሉ ብልቶቻችን ሥራ ማሽተት ቢሆን መቅመስ ከየት ሊመጣ ነው? ብሎ እንደተናገረው የምእመናኑም የካህናቱም ድርሻና ፍላጎት አንድ ዓይነት መሆን አይገባውም። ሁሉ ተመሪ ከሆነ ማን መሪ ይሁን? ሁሉ አጥፊ ከሆነ ማን አስተካካይ ይሁን? ሁሉ ዓለማዊ ከሆነ ማን መንፈሳዊ ይሁን? እዚህ ላይ ሳልጠቅሰው የማላልፈው ጉዳይ ቢኖር በጉልበት፣ በዕውቀት፣ በጊዜና በገንዘብ ቤተ ክርስቲያንን በቅንነት በማገልገል ላይ የሚገኙ ዲያቆናት፣ ካህናትና ጳጳሳት መኖራቸውን ነው። እግዚአብሔር በፈርዖን ቤተ መንግሥት ዮሴፍን ያህል የእምነት ሰው እንደነበረው ዛሬም ሀብትና ሥልጣን በተንሰራፋበትና በነገሠበት ስፍራ ለሃይማኖት ተቆርቋሪ የሆኑ ሰዎች አይኖሩም ማለት አይቻልም።
በሽታው እንዲፈወስ የበሽታው መነሻ የሆነውን ስፍራ ለማግኘት መሞከሩና ጥረት ማድረጉ አስፈላጊ ቢሆንም በሽታውን በማስተላለፍ ላይ የሚገኙትን ሕዋሳት ዝም ብሎ መመልከት ደግሞ የዋህነት ነው። ከቆሻሻ ላይ ተነሥታ የመጣችው ዝንብ ምግብ ላይ ማረፏን ካረጋገጥን ቆሻሻው ባይኖር ይቺ ዝንብ አትኖርም ነበር በማለት ዝንቧን መተው በሥራ ዓለም ብቻ ሳይሆን በፍልስፍናውም መንገድ አያስኬድም። ለእኔ ቆሻሻ ያፈራት የዝንቧ ምስኪንነት አይታየኝም። ምክንያቱም ቆሻሻው ባይኖር ዝንቧ ንብ ትሆናለች ማለት አይሞከርምም፤ አይሆንምም። በመሆኑም ተልከውም ይሁን በእራሳቸውም ውስጣዊ ስሜት ተነሣሥተው ዐውደ ምሕረትን በመድፈር የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያንን ሥርዓተ ትምህርት ቸል በማለት መሠረት የሌለውን የውጭውን ዓለም ሃይማኖት በመስበክ መውጫ ወደሌለው ወደ ገደል በሚወስድ ትምህርት ሕዝብን በማደናገር ላይ የሚገኙትን ሰባክያንም ሆነ የዚህን እኩይ ዓላማ ለማሳካት ላይ ታች የሚሉትን የሰው ዝንቦች ቃለ እግዚአብሔር ላይ ሳያርፉና በቃለ እግዚአብሔር ተወስነው የሚኖሩትን ሰዎች ሳያበላሹ ማባረር ተገቢ ነው። እርጎ የጠገበች ዝንብ መብረር ተስኗት ከእርጎው ዕቃ ውስጥ ሞታ ብትገኝም ያንን ያበላሸችውን ወተት ለመጠጣት የሚደፍር አይገኝም። ምእመናኑን እንደ እርጎው ምንፍቅና አስተማሪውን እንደ ዝንብ ብንመለከተው ምንፍቅና የተዘራባቸውን ምእመናን ለማጽዳትና መልሶ በዐውደ ምሕረቱ ላይ እንዲቆሙ ለማድረግ ረጅም ጊዜ ይወስዳል።

በተሞክሮ እንዳየነው የእነአርዮስ፣ መቅዶንዮስና ንስጥሮስ ምንፍቅና እነርሱ ተወግዘው ብቻ እንኳን ሳይሆን ሞተውም ሳለ አንዴ ያስተላለፉት ትምህርት እስከ ዛሬ ድረስ ሲያበጣብጥ ይኖራል። በመሆኑም አሁን ሕዝቡን ከቤተ ክርስቲያኑ መዐዛ እና ሥርዓት በማስወጣት አዳዲስ ሥርዓት በማስተማር እንዲኮበልል በማድረግ ላይ ያሉት እነዚህ የቤተ ክርስቲያን መስለው የቤተ ክርስቲያን ያልሆኑ መምህራን ሕዝቡ ወደ ሥርዓቱ ዳግም እንዳይመለስ አድርገው በብዙ ሁኔታ ያሰሩትን ያህል ወደፊት ደግሞ በምንፍቅና ትምህርት አስረው አንዴ ከእምነቱ ካወጡት በኋላ እናገኘዋለን ማለቱ የማይሞከር በመሆኑ የባሰ ሳይመጣ ከአሁኑ መንገድ ይፈለግላቸው እላለሁ። መዝሙረኛው በመዝሙሩ ከቀስት ያመልጡ ዘንድ ለሚፈሩህ ምልክትን ሰጠኻቸው። መዝ. ፶፱፡፬ ብሎ እንደተናገረው ቀስት ከተባለው ሞት፣ ምንፍቅና፣ መከራ፣ ችግርና የመሳሰለው ሁኔታ ለማምለጥ የተሰጠንን ምልክት ሊያጠፉብን ከተነሡ መናፍቃን ቤተ ክርስቲያናችንን መጠበቅና ማስጠበቅ የሁላችንም ኃላፊነት ነው። የጌታችን መስቀል ምልክታችን እንዳይሆንና በመስቀሉ ሥር ተገኝተን ጌታችንን እንዳናመልክ አይሁድ ለሦስት መቶ ዓመታት ቀብረው አኖሩት። የአሁኖቹ መናፍቃን ደግሞ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶን ለማጥፋት ሲያስቡ የመጀመርያ ዓላማቸውና ኢላማቸው ምልክቶቻችንን ማጥፋት ነው። ጌታ እራሱ ምልክት ይሰጣችኋል ተብሎ የተናገረውን የነብዩ ኢሳይያስን ትንቢት ቸል በማለት የተዋሕዶ ምልክት የሆነችልንን ቅድስት ድንግል ማርያምን አለመቀበል፤ ከሰው ሳይሆን ከመላእክት የተገኘውን ያሬዳዊ ዜማ እንዳለፈበትና እንዳረጀ በመቁጠር ተራ አድርጎ በመመልከት ምንም ዓይነት ቦታ አለመስጠት፤ የቤተ ክርስቲያኒቱን አንጡራ ሀብት የሆኑትን ገድላትና ድርሳናት ማስወገድ፤ ሥርዓተ ቤተ ክርስቲያንን መቃወም፤ ሰዓታቱና ማኅሌቱ ዘመን ያለፈበት አድርጎ በመቁጠር ዛሬ ተደምጦ ነገ በማይደገም አዳዲስ ዜማ ለመተካት መሰለፍ፤ በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ተጽፈው የነበሩ የቤተ ክርስቲያኒቱን ቋንቋዎች በማውጣት በሌላ ቃል መተካት፤ ገዳማቱንና አብነት ትምህርት ቤቱን የዕውቀት ማመንጫ መሆናቸውን በመካድ የሚዘጉበትን ሁኔታ በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ መንገድ ማመቻቸትና የመሳሰሉትን በማድረግ ቀድሞ ምልክቶቻችን የነበሩትን በሙሉ ከሕሊናችንና ከቤተ ክርስቲያናችን ውስጥ አውጥቶ ለመጣል ተነሥተዋል።  ከላይ ለመግለጽ የሞከርኩት ድፍን ሐሳብ ብቻ ሳይሆን መፍትሔውንም ጭምር ለመሆኑ መልእክቱን ደጋግማችሁ በማንበብ ተረዱልኝ።

ወጣት ሰባክያንና ዘማርያን።

የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን በወጣት ሰባክያን ላይ ያላት እምነት ከሌሎች አኀት አብያተ ክርስቲያን ጋር ሲነፃፀር ቢበልጥ እንጂ አያንስም። ወጣቶች በቤተ ክርስቲያን ውስጥ የሚያደርጉት ተሳትፎ እጅግ የላቀ እንደሆነም ታምናለች። ወጣት ዘማርያንና ወጣት ሰባክያን ከየገዳማቱና ከየአድባራቱ እንዲሁም ደግሞ ከየአብነት ትምህርት ቤቱ የሚወጡት ገና በወጣትነት ዕድሜያቸው ብቻ ሳይሆን በሕፃንነታቸውም ነው ለማለት ያስደፍራል። እውነታው ይኼ ሆኖ ሳለ አንዳንድ ሰዎች የመጽሐፍ ቅዱስ ትምህርት የሚያስተምራቸውና ዝማሬ የሚያቀርብላቸው ወጣት ቤተ ክርስቲያኒቷ የምትለውን ሳይሆን እነርሱ የሚወዱትን የሚነግራቸው ይሁን እንጂ የሥርዓተ ትምህርቱ መፋለስ የሚያመጣው ጉዳት አይታየቸውም። ወጣት ሰባክያኑና ዘማርያኑም ሕዝቡ ይከተላቸው እንጂ የሚያስተምሩት ትምህርትና የሚዘምሩት መዝሙር  ሥርዓተ ቤተ ክርስቲያንን አለመጠበቁ አያስከፋቸውም። ከላይ ለመግለጽ እንደሞከርኩት ቤተ ክርስቲያናችን ሥርዓተ ትምህርቷን ተከትለው የማያስተምሩትን ሰዎች ትቃወማቸዋለች እንጂ ወጣትነታቸውን አትጠላውም። እግዚአብሔርን ብለን መጥተን ወደ ውጭ ጣሉን፤ ዝማሬ ስላቀረብንና እግዚአብሔርን ስላመሰገንን ገፉን በማለት የእግዚአብሔርን ስምና መጽሐፍ ቅዱስን በር ለማስከፈቻ እና የሕዝብ ኀዘኔታን ለማግኘት ብቻ መሣሪያ አድርጎ በመጠቀም በሩ ከተከፈተ በኋላ የቤተ ክርስቲያንን ሕልውና የሚያደበዝዝና የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያንን ሥርዓተ ትምህርት የሚቃወም ትምህርታቸውን በማስገባት ተልእኮአቸውን የሚፈጽሙና የሌሎች እኩይ ምግባር ያላቸውን ሰዎች ተልእኮ የሚያሰፈጽሙ ብዙዎች ናቸው። በመሆኑም ምእመናን በቤተ መቅደስና በሥልጣነ ክህነት አገልግሎት ላይ መሳተፍ ባይችሉም ቤተ ክርስቲያንን የመጠበቅ ኃላፊነት እንዳለባቸው ልብ ሊሉት ይገባል። የሃይማኖት አባቶች ናቸው የተባሉት ካህናትና በተለይም ደግሞ ካህናትን በመሾም ሕዝብን የማስተዳደር ኃላፊነት የተሰጣቸው ጳጳሳት በተሰጣቸውና ኃላፊነትን በተሸከሙበት በቅዱስ መጽሐፍ ምእመናንን ወደ መንግሥተ ሰማያት እና አባታችን አዳም ወደወጣበት ወደ ገነት ለማስገባት ሲቻላቸው የተሰጣቸውን ሥልጣነ ክህነት ቸል በማለታቸው የተጣላ ለማስታረቅ እንኳን በማይችሉበት ደረጃ ላይ ደርሰው ስናይ አንድ ነገር እንደጎደለ ለማወቅ አያዳግትም።

ስለዚህም የሕዝብ ጥያቄ ከሁሉ የበለጠ ብርቱ ነውና ምእመናን ቤታችሁ እየፈረሰ፣ ሃይማኖታችሁ እየተከሰሰ፣ የማንነታችሁ መብት እየተጣሰ እያያችሁት በአቅራቢያችሁ ያሉትን ካህናትና መምህራን ሃይማኖታችን ወዴት እየሄደ ነው? ሥርዐታችን ወዴት እየጠፋ ነው? ብሎ መጠየቅ አደራን ከመጠበቅና የመጽሐፍ ቅዱስን ቃል ከመረዳት ያስቆጥራል እንጂ የድፍረት ተናጋሪ አያስደርግም። ስለሆነም ሰልፉን የሚሰለፍ ሌላ ሕዝብ ይመጣል ብላችሁ ሳትጠብቁ እውነትን በመናገር ብቻ ሰልፋችሁን ጀምሩ። ንጉሥ በአቅራቢያው ያሉትን መካሪዎች ካልሰማና በአገሪቱ ላይ እየደረሰ ያለውን ችግር ካላየ ወይም ደግሞ ማስተካከል በሚገባው ሰዓት ለማስተካከል ከተሳነው እንዲህ ያለ የበደል አመራር በቃኝ ለማለት መሣሪያ የማያስፈልገው ሕዝብ የኢያሪኮን ግንብ በጩኸት እንዳፈራረሰው በልዑል እግዚአብሔር አጋዥነት ያፈራርሰዋል። መሣሪያውና ብረቱ፣ ፈረሱና ሠረገላው ቢጠብቁት ኖሮ እንደ ፈርዖን የታጠቀ ባልተገኘም ነበር። ዛሬም በፈርዖን ወንበር የተቀመጠ መሪ ያለመሣሪያ በሕዝብ ጩኸት ብቻ ሲወድቅ ከጥቂት ወራት በፊት አይተናል። በቅንነት ያልተቀመጡበት ወንበር ለዕድሜ ልክ እንደማይሆን አሁን በዘመናችን ብዙዎችን አይተንማል፤ ሰምተንማል።

በአገር መሪዎች ላይ እየደረሰ ያለውን ይኼን ያልታሰበ ቀውስ እየተመለከተ ያለ የሃይማኖት መሪም እየመራው ያለውን ሕዝብ በቅንነት በመመልከት ትክክለኛ ሥራ ካልሠራ ሕዝቡ እንኳን ዝም ቢል ወንበሩ እንደ በለዓም አህያ አፍ አውጥቶ ሊናገር ይችላል። ሰሚ ጆሮ ያለው ይስማ። ስለዚህም ወጣት ሰባክያንና ዘማርያን እግዚአብሔር የሰጣቸውን ይኽን አጋጣሚ ተጠቅመው በቅድስት ቤተ ክርስቲያን ውስጥ ያገኘናቸው የቤተ ክርስቲያናችን ልጆች ናቸው በማለት የተከተላቸውን ሕዝብ የችግር መወጫ አድርገው እንዳይጠቀሙበት ሁላችን ነቅተን እንጠብቅ።  ቤተ ክርስቲያን ወጣቱን ከነሙያው ከነእውቀቱ ትቀበለዋለች፤ ምንፍቅና ይዞ ከመጣና የመናፍቃን ጉዳይ አስፈጻሚ ሆኖ ከመጣ እራሷን በታማኝ ልጆቿ ታስከብራለች።

ግልጽ መልእክት ለሃይማኖት ሽብርተኞች።

እምነታችንና ሃይማኖታችን ነው በማለት የተያያዛችሁትን የምንፍቅና መንገድ ለመከተልና የወደዳችሁትን ለማድረግ የሚከለክላችሁ የለም። እንደ ቀድሞዎቹ ፕሮቴስታንት ተቃውመናል አልተመቸንም በማለት እራሳችሁን ችላችሁ ቤተ ክርስቲያኒቷን ለቅቃችሁልን ልትወጡ ይገባችኋል። ለእኛ የማትሆኑትን ሰዎች የእኛ ናችሁ ብለን መያዝ አይኖርብንም። አውቆ የተኛን ቢቀሰቅሱት እንደማይሰማ ሁሉ ጆሮ ዳባ ልበስ ያላችሁትን ሰዎች ትምህርት ለማስተማርና ሥርዓት ለማሳወቅ መድከም አይጠበቅብንም። እንደ ልባችሁ ወደምትሆኑበትና ምንፍቅናችሁን ወደምታስተላልፉበት ሥፍራ መሄድ ሲገባችሁ ስለምን በቤታችን ተቀምጣቸሁ ታውኩናላችሁ? ቅዳሴውን ሳትቀበሉ የእናንተን ተረት እንድንቀበል ትፈልጋላችሁን? ሥርዓታችንን አፍርሳችሁ የእናንተን አዲስ ሥርዓት እንድንቀበል ትፈቅዳላችሁን? ይኽ ሞኝነት ነውና አታድርጉት እንላለን። የወፍጮ መጅ በአንገቱ ታስሮ ቢወረወር ይቀለዋል በማለት ጌታችን የተናገረው ቃል በእናንተ ሊፈጸም ግድ በመሆኑ ብዙዎችን በማሳሳት ላይ ትገኛላችሁ። ከላይ እንደተገለጸው ቤተ ክርስቲያን ወጣቱንም ሆነ አዛውንቱን፣ ወንዱንም ሆነ ሴቱን፣ ትልቁንም ሆነ ትንሹን ከነሙያው ከነእውቀቱ ትቀበለዋለች፤ ምንፍቅና ይዞ ከመጣና የመናፍቃን ጉዳይ አስፈጻሚ ሆኖ ከመጣ እራሷን በታማኝ ልጆቿ ታስከብራለች። በማለት የማያሻማ መልሳችንን እንሰጣለን።
የቤተ ክርስቲያን የበላይ አስተዳዳሪዎች ምን ማድረግ ይጠበቅባቸዋል?

ያለሥርዓት የሚሄዱትን በመገሰጽና መመሪያ በማውጣት ሰባኪ ወንጌላውያን ምን ዓይነት ትምህርት ለተከታዮቻቸው እንደሚያስተምሩ በመንገር ማሰማራት ይጠበቅባቸዋል። ወጣቱ እርሱ በእርሱ ሲጨቃጨቅና ጠላት ሆኖ ሲተያይ በአመራር ላይ የተቀመጡ ሰዎች ሰምተው እንዳልሰሙ አይተው እንዳላዩ መቀመጥ አይገባቸውም። በቤተሰብ መካከል ልጆች ቢጣሉ ማስማማትና ማስታረቅ ከዚያም አልፎ ተርፎ ሁሉም ልጆች በጋራ የሚጠቀሙበትንና ተቻችለው የሚኖሩበትን ሁኔታ ማመቻቸት የወላጆች ፋንታ ነው። የሃይማኖት መሪዎችም የተቀመጡበት ወንበር ሕግ የሚያረቁበትና ሕግ የሚያስፈጽሙበት መሆን ሲገባው በቦታው ላይ መቀመጣቸው ሥልጣናቸውን ብቻ ማንጸባረቂያ ሊሆን አይገባውም። ዕለት ከዕለት በመትጋት የወጣቱን አካሄድና የትምህርቱን አሰጣጥ መከታተል ይኖርባቸዋል። በአንድ ዐውደ ምሕረት ላይ የሚሰብኩ ሰባክያን ስለምን የተለያየ ስብከት ሲሰብኩ ዝም ተብለው ይታለፋሉ? አርም፤ አስተካክል ሊባሉ ይገባቸዋል። ሃይማኖት እየፈረሰና እየወደቀ እያየ ይሉኝታን ገንዘብ ማድረግ በአመራር ላይ ለተቀመጠ ሰው አግባብ አይደለም። ፍጹም የሆነ ፍቅር ከላይ ከጀመረ ወደታች የማያልፍበት አንዳች ነገር አይኖረውም። በመሆኑም በአመራር ላይ የተቀመጣችሁ አስተዳዳሪዎች የእግዚአብሔር እንደራሴ መሆን ይኖርባችኋላ እንጂ የሰው ጉዳይ አስፈጻሚ መሆን አይገባችሁም። ፍቅር ለኔ ብቻ ይድላኝ አያስብልምና ለእኔ ይመቸኛል የምትሉትን ሰው ብቻ ይዛችሁ ሃይማኖትን አትምሩ። ሁላችን ለእናንተ ልጆቻችሁ ነንና ዛሬ በተቀመጣችሁበት ወንበር ላይ ሆናችሁ ነገን ተመልከቱ። እኛም የእናንተን ቀና አመለካከትና መንገድ ተከትለን የአባቶቻችን ልጆች ነን እንድንል በፍቅር ወንበር ላይ የፍቅርና የአንድነትን ነገር ተነጋገሩ። ሕዝበ እስራኤል ኢያሱን አንተ ምራን እኛም እንመራልኻለን እንዳሉትና እንደተመሩለት እኛም የእናንተን ቃል ሰምተን እንድንመራ የቀደመችውን እምነት ይዛችሁ እንደ ሥርዓታችን አስተዳድሩን።

ወስብሐት ለእግዚአብሔር!
አብርሃም ሰሎሞን

5 comments:

ርብቃ ከጀርመን said...

ሰላም ደጀሰላሞች እንደምን ከረማችሁ በጣም አስተማሪና የልቤንሀሳብ ነው ደስበሚል የቤተክርስቲያን ቃል ስለጻፋችሁት አመሰግናለሁኝ በመቀጠልግን ልገልጽላችሁ የፈለኩት ነገር ከጽሁፋችሁ ጋር የተመሳሰለነገር ትናንትና እዚህ እኛ በምንኖርበት በጀርመን አገር በፍራንክፈርት ቅድስትማርያም ቤተክርስቲያን በተደረገ ስብሰባላይ ጥያቄ የነበረን ምእመናን በጀርመን ሀገር የበላይ የነበሩት አባት በነበረን ያስተዳደር ጉድለትና የቤተክርስቲያንን ስርአት ያፋለሰ ሁኔታ ስንጠይ መልሳቸው ባያረካን ይሄን ነገርእኮ ፍትሀነገስቱ እምነት ላጎደለ (ለሰረቀ) ካህንእኮ ክህነቱን ይሻራል ይላል ብለን ብንጠይቅ የተሰጠንመልስ ከበላይ አስተዳዳሪው ፍትሀነገስቱን ከተከተልንማ እናንተም ገብታችሁ አታስቀድሱም እኔም ገብቸ አልቀድስም የሚል ነበረና ሁላችንም ደነገጥን እውነትም ትክከል ቢሆን ነውእንጅ ስንትናስን መረጃና በድምጽና በመጽሀፍ የተያዘበትን ቄስና ከስድስት አመት በፊት በመናፍቃን አዳራሽ በፓስተርነት ያገለግል እንደነበረ እረሱም ያመነ መረጃም የቀረበበት ካህን ያለምንም ቀኖና ለጻፈው መጽሀፈፍ ምነምአይነት ማስተካከያናይቅርታ ሳይጠይቅ ይባስብሎም አሁንም ምእመናንን ኮርስ እየሰጠና ሲጨርሱም ወደመናፍቃን አዳራሽ እየሄዱ እየተጠመቁ ባሉበት ሁኔታ ሀግ የሚል መጥፋቱ እንዳሉትም ፍትሀነገስቱ በቅርስነት ወደሙዚየም እንደተላከና በነበርእንደቀረ የሚያስረግጥ ነገር ነው የሆነብን እና እባካችሁ ደጀሰላሞች ፍትሀነገስቱ ይሰራበታል ወይስቀርቱዋል ወይስ አገርቤት ብቻ ነው የሚሰራበት የሚመለከተውን ክፍል ጠይቃችሁ ለኛ ግራ ለገባን የጀርመን ምእመናን መልስ ስጡን! የቅዱሳን አምላክ ምእመናን ከነጣቂተኩላ የሚጠብቅ አባት ይስጠን አሜን!


Anonymous said...

Betam tiru tsihuf new. Dejeselam endezih ayinet tiru tiru negerochin eyemerete biakerb tiru new. Hulunim post madireg tegebi ayidelem. Yihe menifesawi neger bicha yemikerbibet blog new mehon yalebet. Egziabher amlak betechristianin yitebikilin. Egnam abiziten sile betechristian enitseliy. Egna keberetan hulum neger yistekakelal. Yegna yemenifes dikimet new ena yihen hulu fetena yemiametabin.

Cher yaseman

Temelkach said...

Very interesting idea. Yes it is the people(Miemenan) that can protect our church at this time. No other option. It is clear we don't have Patriarc, no papasat, no kesawst, no diakonat, and no senbet timhirt bet temari. Right now we have no one to depend for help. LET US HELP OURSELVES!!!!!!!!!!!!!!!!!!!!!!!!!!!!!!!!!!!!!!!!!!!!!

I think we better go for this idea. I will do my part financially. The question is who can organize the people? Anyone who has an idea please let us talk about it PLEASE PLEASE!!!!!!!Before it is too late.

Anonymous said...

What is all these religious warfare you are waging? Is this Christianity? You guys are fond of creating differences. We are fed up of the worldly governments that are stealing our peace, our property and the love we have for each other. Now, you are adding another dimension to it: Alkaida type of rift between Christians, specially our families who seldom go to Church to listen to sibket. Now it will be a good excuse for them to turn away from anything that is related to the words of God. I think the perpetrators of such animosity is to kill 'Wengel'. That you cannot do!! Beleive me, Medhanealem would not allow you.

mengede nitsuh said...

ሐሳቡ መልካም ነው። ነገር ግን መፍትሔው ላይ ይበልጡን ትኩረት ሊደረግበት የሚገባው ነገር አለ ባይ ነኝ። ለዚህ ሁሉ ችግር ዋናው መሻሻል/መቀየር ያለበት ቢኖር መሪና አመራር ነው። አሁን ቤተክርስቲያኗ ጠባቂ እንደሌላት ሆናለች፤ አጥር እንደሌለው ቤት ሰዳ ሆናለች፤ ማንም እንደፈለገ በስሟ እያሳተመ መዝሙር አይሉት ዘፈኑን ይሸቅጣል፣ በአውደ ምሕረቷ ላይ ያረግዳል፣ ምንፍቅናን ይወሻክታል፣ ንግዱን ይቸረችራል ወዘተ ይህ ሁሉ እንዳይሆን ሥርዓት እንዲያስከብሩ የተሾሙ አባቶች ኃላፊነታቸውን ከዘነጉ ምን ይደረጋል ተብሎ ብቻ መቀመጥ ሳይሆን እንዲህ ያሉትን እንዲታረሙ ማድረግ ካልሰሙ እምቢተኛ ከሆኑ ማስወገድና በምትካቸው ለቤተክርስቲያን የሚቆረቆሩ እንዲሾሙ ማድረግ ነው። ነገር ግን ከጥፋትም በላይ ጥፋት እያጠፉ ቤተክርስቲያንን ለመናፍቃን አሳልፈው ሰጥው ‘‘ መጠበቅን ጠብቅልን እረጅም እድሜ ስጥልን’’ እያልን በመጸለይ መከራችንን ከምናበዛና ከምናስረዝም መጀመሪያ ለእነዚህ አይነት ግዴሌሾች እውቅና አለመስጠት ስማቸውን አለመጥራት ያስፈልጋል። አንቱ ብሎ ስድብ የለም ይላል ያገሬ ሰው ወይ እንደ እስክንድር ተዋጋ ወይ የእስክንድርን ስም መልስ ተብሏል። ቤተክርስቲያን ይህ ሁሉ ደረጃ ሳትደርስ የዘመናችን የቤተክርስቲያን ችግሮች እናት የሆኑትን ሰው ሁሉም በወቅቱ በቃ ቢላቸው ኖሮ ይህ ሁሉ ባልደረሰ ነበር! አሁንም ለቤተክርስቲያን ተቆርቁረናል የምንል ሰዎች እርስ በርሱ የሚጋች ነገር ስናደርግና ስንናገር እንዳንገኝ። ሆ! ተብሎ የሚሰራ ነገር የለም። ምእመናን እነዚህን ሰርጎ ገብ መናፍቃን ማጽዳት የሚችለው ህዝብ በህዝ ላይ በመነሳትና በማስነሳት ሳይሆን ሥርዓትና ሕግ የሚያስከብር መሪ እንዲኖር ሁሉንም አማራጮች በመጠቀም ነው። ምክንያቱም የህዝብን በህዝብ ላይ መነሳትንና መከፋፈልን መናፍቃኑም ሆኑ ሌሎች ጉዳያቸው እንዲዘነጋላቸው የሚፈልጉ ክፍሎች ግር ግር እንዲፈጠር ስለሚፈልጉ ይህንንም ማስተዋል ያሻል። ለዚህም ነው በታሪክም ሆነ አሁንም በዘመናችን ለቤተክርስቲያንም ሆነ ለሀገር አያሌ ችግሮች መሪን ማስተካከል፣ መቀየር ወይም ማስወገድ መፍትሔ ተደርጎ የሚወሰደው። ለእኛም መፍትሔው ይኼው ነው።

Blog Archive

የአቡነ ጳውሎስ "ሐውልተ ስምዕ"

ነጻ ፓትርያርክ ምርጫ ቢሆን ኖሮ ማንን ይመርጡ ነበር? እንበልና ሁሉም ነገር ሥርዓቱን ጠብቆ የተከናወነ የእጩዎች ምርጫ ቢሆን ኖሮ፣ አሁን የምናነሣቸው ጉድለቶች ባይኖሩ ኖሮ፣ 6ኛው ፓትርያርክ እንዲሆን የምትመርጡት ማንን ነበር? (ማሳሰቢያ፦ አሁን ያለው ክፍፍል እና የመንግሥት ተጽዕኖ ባይኖር ኖሮ ተብሎ የሚመለስ ጥያቄ ነው። የምን “ባይኖር ኖሮ ነው” የሚል አስተያየት ካለዎትም እናከብራለን።)