October 1, 2011

የመስቀል-ደመራ በዓል አከባበር ልዩ የሕዝብ ግንኙነት ሥራ እንደሚያስፈልገው ተጠቆመ


  • በሁሉም ዘርፍ ለሀገሪቷና ለሕዝቧ ባለውለታ ለሆነችው ለጥንታዊቷ፣ ታሪካዊቷና ብሔራዊቷ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ዓመታዊ በዓላት ማስሚዲያዎች የሚሰጡት የዜና ሽፋን፣ “ተከታዮቿን አንገት የሚያስደፋና ከፍተኛ ቅሬታን የሚያሳድር” እንደሆነ ተገልጧል
  • “በአዲስ አበባ ያለውን አከባበር ብቻ ሳይሆን በአኵሱም፣ በጎንደር እና በላሊበላ ከተሞች ያለውን የመስቀል በዓል አከባበር በስፋት በማስተዋወቅ ሁኔታውን ማጉላት ጠቀሜታውን እጥፍ ያደርገዋል፤” (የ2004 ዓ.ም መስቀል መጽሔት ልዩ ዕትም)
  • “የመስቀልም ሆነ የጥምቀት በዓል በሚከበርበት ጊዜ ቤተ ክርስቲያናችን የምትፈልገው የበዓሉ ገጽታ አንዳችም ነገር ሳይቀላቀልበት በብቸኝነት እንዲታይላት ነው፡፡” (መጋቤ ምሥጢር ወልደ ሩፋኤል ፈታሒ)
(ደጀ ሰላም መስከረም 20/2004 ዓ.ም፤ ኦክቶበር 1/2011)፦ ከሃይማኖታዊ እና ባህላዊ በዓልነቱ እና የአከባበር ሥርዐቱ ባሻገር የቱሪስት መስሕብ በመሆን ለሀገር ኢኮኖሚ እና ገጽታ ግንባታ የሚያበርክተው ከፍተኛ አስተዋፅ ከዓመት ወደ ዓመት እየጨመረ ለመጣው የመስቀል ደመራ በዓል አከባበር የሕዝብ ግንኙነት ሥራ ልዩ ትኩረት ተሰጥቶት ሊሠራ እንደሚገባው ተጠቆመ፡፡
እንደ መስቀል እና ጥምቀት ያሉት የቤተ ክርስቲያኒቷ ዐበይት በዓላት በየዓመቱ በተከበሩ ቁጥር በሬዲዮ እና በቴሊቪዥን የሚሰጠው የስርጭት ሽፋን ለሌሎች የእምነት ተቋማት ከሚሰጠው የዜና እና ዝግጅት ሽፋንና በሕገ መንግሥቱ ከተደነገገው የሁሉም እምነቶች ነጻነትና እኩልነት አኳያ በቤተ ክርስቲያናችንና በተከታዮቿ ዘንድ ከፍተኛ ቅሬታን እንዳሳደረም ተገልጧል፡፡ ቤተ ክርስቲያናችን የምትፈልገው፣ የበዓላቱ ምንነትና ታላቅነትም የሚገለጸው የአከባበራቸው ገጽታ አንዳችም ነገር ሳይቀላቀልበት በብቸኝነት ሲታይ እንደሆነም ተመልክቷል፡፡

የ2004 ዓ.ም የመስቀል-ደመራ በዓል አከባበርን አስመልክቶ በመ/ፓ/ጠ/ቤ/ክ በታተመው ልዩ “የመስቀል መጽሔት” ዕትም ላይ እንደተገለጸው፣ የመስቀል በዓል አከባበርና አመጣጥን አስመልክቶ የተጻፉ ጽሑፎችን በመጠቀም፣ የቤተ ክርስቲያን ሊቃውንትንና የሚመለከታቸውን ሁሉ በመጠየቅ ራሱን የቻለ ዶክመንታሪ ፊልም ማዘጋጀት ለምእመኑ አስተማሪ ከመሆኑም በላይ የውጭ ጎብኚዎችም በቂ ዕውቀት የሚያገኙበትን ዕድል በመፍጠር ለቱሪስቶች ቁጥር መጨመር የጎላ ሚና ይኖረዋል፤ የበዓሉን አከባበር የሚያመለክት የሕዝብ ግንኙነት ሥራም በቤተ ክርስቲያኒቱ ብቻ ሳይሆን በባህል እና ቱሪዝም ሚኒስቴር እንዲሁም በኮሚዩኒኬሽን ጉዳዮች ጽ/ቤት ልዩ ትኩረት ተሰጥቶት ሊሠራ እንደሚገባው በልዩ ዕትሙ ላይ “የመስቀል በዓል አከባበር ባለፉት ሃያ ዓመታት” በሚል ርእስ በመ/ፓ/ጠ/ቤ/ክ የሕዝብ ግንኙነት መምሪያ ሓላፊ በሆኑት እስክንድር ገብረ ክርስቶስ የቀረበው ጽሑፍ ያስረዳል፡፡

መንግሥት በዓሉን በመላው ዓለም በማስተዋወቅ ረገድ በቴሊቪዥን ያልተቆራረጠ ሽፋን ለመስጠት የሚያደርገውን ጥረት በማጠናከር በአዲስ አበባ ያለውን አከባበር ብቻ ሳይሆን በአኵስም፣ በጎንደርና በላሊበላ ከተሞች ያለውን የመስቀል በዓል አከባበር በማከል ሁኔታውን ማጉላት ጠቀሜታውን እጥፍ እንደሚያደርገው ሓላፊው አመልክተዋል፡፡ የመስቀል ደመራን በዓል የምታከብር ሀገር ኢትዮጵያ እና የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ብቻ መሆኑ በገሃድ የሚታወቅበት አጋጣሚ መሆኑን የገለጹት ሓላፊው ክዋኔው ሃይማኖታዊ ይዘቱን ጠብቆ ለተከታዩ ትውልድም ይቆይ ዘንድ ቤተ ክርስቲያን ከምታደርገው ጥረት ጎን ለጎን መንግሥት እና ሌሎች አካላት የድርሻቸውን ሊወጡ ይገባቸዋል ብለዋል፡፡

በሌላ በኩል “የመስቀልን በዓል እንዴት እናክብረው?” በሚል ርእስ የመጽሔቱን መልእክት ያሰፈሩት የልዩ እትሙ ዋና አዘጋጅ መጋቤ ምስጢር ወልደ ሩፋኤል ፈታሒ፡- የብዙኀን መገናኛዎች (በተለይ ኢትዮጵያ ሬዲዮ እና ቴሌቪዥን ድርጅት) ለቤተ ክርስቲያናችን የበዓል አከባበር የሚሰጡት የዝግጅት እና የዜና ሽፋን “እንዳያማህ ጥራው እንዳይበላ ግፋው” ዓይነት የበዓሉን ከፊል ገጽታ በወለምታ ወይም በቆረጣ አሳይቶ ወይም ለአንድ ሰከንድ ያህል እንደ ትል እሳት ብልጭ አድርጎ በማሳለፍ በዓሉን ወደማይመለከት ሌላ ፕሮግራም የሚያመራ፣ ከአስደሳችነቱ ይልቅ አሳኝነቱ የሚያመዝንና ሌሎች እምነቶች ከአዲስ አበባ እስከ ክልል ከተሞች ለሚያከብሯቸው በዓላት እስከ ሦስት ቀን ድረስ ከሚሰጠው ሽፋን አኳያ አድሏዊ እንደሆነ (በእኩልነት የማያስተናግድ) በመግለጽ የድርጅቱን አሠራር ተችተዋል፡፡

ዋና አዘጋጁ “ሌላ ፕሮግራም” ያሉትን ሲያብራሩም፣ “በጥምቀት በዓል የእንስሳትን ወይም የቀንድ ከብቶችን ቀን መርሐ ግብር ከዘፈን ጋራ ቀላቅሎ ያካሂድበታል፡፡ የመስቀልን በዓል ደግሞ ሙሉ በሙሉ የብሔር ብሔረሰቦችን ዘፈን በማዘፈን ወይም በማስጨፈር ሙሉውን ቀን ዳንኪራ ሲያስረግጥበት ይውላል፡፡ በፋሲካም ሙሉ ሌሊት ሲንጸባረቅበት የሚያድረው ይህ ይነቱ ትርኢት ነው፤” ብለዋል፡፡ የቤተ ክርስቲያናችን በዓላት በሚከበሩበት ወቅት በሌሎች ላይ በማይቀርብበት አኳኋን የሌሎችንም የሃይማኖት ተቋማት በዓላት ቀላቅሎ ወይም ጣልቃ እያስገቡ በማሳየት የሁሉንም እምነቶች ተከታዮች ግራ ማጋባቱንና ማደናገሩን፣ ሌሎች የሃይማኖት ተቋማት በዓላቸውን ሲያከብሩ ግን የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ዓመታዊ በዓላት እንደማይካተቱበት መታዘባቸውን፣ ይህም “የኢ.ፌ.ዴ.ሪ መንግሥት ለሁሉም የሃይማኖት ተቋማት የሰጠውን የእኩልነትና የነጻነት ድንጋጌ መጣስ” እንደሆነ ገልጸዋል፡፡

“የድርጅቱ ጋዜጠኞች በቀጥታ ርጭት ወቅት ጣልቃ እየገቡ አንዳንድ የበዓሉን ታዳሚዎች በተለይም “የውጭ ዜጎችን አስተያየት እንጠይቃለን” እያሉ ራሳቸውንም ጨምረው የሁለት ሦስት ግለሰቦችን ምስል ብቻ በማሳየት ሊታይ የሚገባውንና ዓለሙን ሁሉ የሚያስደምመውን አጠቃላይ የበዓሉን ገጽታ ሸፍነውት ሳይታይ ይቀራል፤ ወይም የበዓሉ መርሐ ግብር ይጠናቀቃል፤ የመስቀልን ታሪክና ክብር ራሱ በዓሉ ቢናገር የተሻለ ነበር፤” ያሉት መጋቤ ምሥጢር ወልደ ሩፋኤል፣ “ጋዜጠኞቹ ከበዓሉ ተሳታፊዎች የሚሰበስቡት አስተያየት ተገቢ ነው ከተባለ የበዓሉ አጠቃላይ ገጽታ እንዳይሸፈን የጋዜጠኞቹ ጥያቄና የተጠያቂዎቹ አስተያየት ወደ ሕዝብ የሚለቀቅበት ሌላ ክፍል ለምን አይኖርም? የሃይማኖት ጉዳይ እኮ የሀገርም ጉዳይ ነው፤” ሲሉም ጠይቀዋል፡፡

ዋና አዘጋጁ አክለውም የመስቀልን በዓል እንደ ስንፍና መቁጠር ብሎም የሀገሪቱን መንፈሳዊ እሴት አዳፍኖ ማስቀረት የዐማፅያን አይሁድ ደቀ መዛሙርት መሆንና ራስን ከሚጠፉት ወገኖች ጋራ ማስቆጠር መሆኑን ጋዜጠኞች በጥልቀት ሊገነዘቡት እንደሚገባቸው መክረዋል፡፡ የበዓሉን አከባበር ሙሉ ገጽታ ቀርፆ አለማቅረብ በራሱ ደግሞ በበዓሉ ላይ ለመገኘት ከተለያዩ ክፍላተ ዓለማት ወደ ኢትዮጵያ ከሚጎርፉት ቱሪስቶች የሚገኘውን ገቢ መከላከልም እንደሆነ አሳስበዋል፡፡ “እንደ ባሕታዊ ኪራኮስ የመስቀሉን አዳኝነት አመልካች መሆንና ሳይፈሩና ሳያፍሩ ጠንክሮ ማስተማሩም የወቅቱ አባዎች ድርሻ ነው፡፡ የባሕታዊ ኪራኮስ ተወካዮች ስሕተቱ ሁሉ ሲፈጸም እያዩና እየሰሙ በወቅቱ እንዲታረም ካላደረጉና ራሳቸውንም ሆነ ስሕተት ፈጻሚውን አካል ካላዳኑ የኋላ ኋላ ፍርድ እንደሚጠብቃቸው ጥርጥር የለውም፤” በማለት አስጠንቅቀዋል፡፡

ማስታወሻ፡- መጋቤ ምሥጢር ከሰጡት ሐሳብና ምክር አንጻር በደመራው ማግስት በኢሬቴቪ “የኢትዮጵያን አይዶል የ2003 የፍጻሜ ውድድር” የቀጥታ ርጭት ጨምሮ ሲተላለፉ በዋሉት ሌሎች ዝግጅቶች አግባብነት ላይ ደጀ ሰላማውያን ሊወያዩ ይችላሉ፡፡
Post a Comment

Blog Archive

የአቡነ ጳውሎስ "ሐውልተ ስምዕ"

ነጻ ፓትርያርክ ምርጫ ቢሆን ኖሮ ማንን ይመርጡ ነበር? እንበልና ሁሉም ነገር ሥርዓቱን ጠብቆ የተከናወነ የእጩዎች ምርጫ ቢሆን ኖሮ፣ አሁን የምናነሣቸው ጉድለቶች ባይኖሩ ኖሮ፣ 6ኛው ፓትርያርክ እንዲሆን የምትመርጡት ማንን ነበር? (ማሳሰቢያ፦ አሁን ያለው ክፍፍል እና የመንግሥት ተጽዕኖ ባይኖር ኖሮ ተብሎ የሚመለስ ጥያቄ ነው። የምን “ባይኖር ኖሮ ነው” የሚል አስተያየት ካለዎትም እናከብራለን።)