October 10, 2011

የደብረ ሊባኖስ አቡነ ተክለ ሃይማኖት አንድነት ገዳም መጽሐፍ ትርጓሜ ቤት ከሚያዝያ/ 2003 ዓ.ም ጀምሮ እንደተዘጋ ነው


·        መምህራኑ እና ለምረቃ የደረሱ የመጽሐፍ፣ የአቋቋም እና የዜማ ደቀ መዛሙርት ከጉባኤ ታጕለው፣ ድርጓቸውን አጥተው በአዲስ አበባ ይገኛሉ::
·        የጉባኤ ቤቱን በጀት “ከማኅበረ ቅዱሳን ለማስጣል” በሚል ወደ ገዳሙ እንዲዛወር ተደርጓል
·        “ገድለ ተክለ ሃይማኖት እንደገና መጻፍ አለበት” የሚሉ በተሐድሶ መናፍቅነት የሚጠረጠሩ አንዳንድ ‹መነኮሳት› ከፍተኛ ተቃውሞ ገጥሟቸዋል::
 (ደጀ ሰላም፤ መስከረም 28/2004 .ም፤ ኦክቶበር 9/2011)በብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ባስልዮስ ዘመነ ፕትርክና ከተቋቋመበት ከ1952 ዓ.ም ጀምሮ በሥራ ላይ የሚገኘውና ደጋግ አበው ሊቃውንትና ካህናት የወጡበት የደብረ ሊባኖስ ጻድቁ አቡነ ተክለ ሃይማኖት አንድነት ገዳም መጽሐፍ ትርጓሜ ቤት ከሚያዝያ ወር 2003 ዓ.ም ጀምሮ እንደተዘጋ ነው፡፡ ጽፈው፣ አመልክተው በማስመስከር ለመመረቅ የደረሱ በርካታ የትርጓሜ ጻሕፍት፣ የዜማ እና የአቋቋም ደቀ መዛሙርት ከመምህሮቻቸው ጋ ከጉባኤው ታጕለው እና ድርጓቸውን አጥተው ለይግባኝ/አቤቱታ በመጡበት አዲስ አበባ እንደሚገኙ ተገልጧል፤ በመምህራኑና በደቀ መዛሙርቶቻቸው መፈናቀል ምክንያት ገድለ አቡነ ተክለ ሃይማኖት እየተተረጎመ ለገዳሙ አጥቢያ ምእመናን እና ለጠበልተኞች በየዕለቱ ይሰጥ የነበረው የስብከተ ወንጌል አገልግሎት መቋረጡም ተመልክቷል፡፡


ውዝግቡ የተቀሰቀሰው፣ “ት/ቤቱ ለገዳሙ የሚጠቅመው ነገር የለም፤ ተማሪውም በርሻ ሥራው አልረዳንም፤ ይልቁንስ የጉባኤ ቤቱ በጀት ወደ ገዳሙ መዞር አለበት፤” የሚል አቋም በያዙት የገዳሙ ዋና አስተዳዳሪ ጸባቴ አባ ኀይለ መስቀል ውቤ ርምጃ ምክንያት ነው ተብሏል፡፡ ከተቋቋመበት ጊዜ ጀምሮ በቀጥታ ከመ/ፓ/ጠ/ቤህነት በሚመደብለት በጀት ይመራ የነበረው የመጽሐፍ ትርጓሜው ቤተ ጉባኤ በቀድሞው ዘመን ለመምህራኑና ለእያንዳንዱ ደቀ መዝሙር በነፍስ ወከፍ በድርጎ ይሰጥ ከነበረው ብር ስምንት አሁን እስከደረሰበት ብር 120 ድረስ ያከፋፍል ነበር፡፡ በጀቱን ከጠቅላይ ቤተ ክህነቱ ተረክበው ለመምህራኑና ለደቀ መዛሙርቱ የሚገባቸውን እየሰጡ በማከፋፈሉ ሥልጣን የነበራቸውም የት/ቤቱ ሊቀ ጉባኤ ናቸው፡፡ ቁጥራቸው ከ100 በላይ የሚሆኑ የዜማ እና የአቋቋም ተማሪዎችም መሬቱ ጾም በማያድረው ደብረ ሊባኖስ ገዳም ጸሎተ ፍትሐት እያደረሱ ለአገልግሎቱ የሚከፈለው ገንዘብ እየተጠራቀመ በወር በወር ይከፋፈሉታል፤ ለእያንዳንዳቸውም በወር በአማካይ ከብር 40 - 50 ይደርሳቸዋል፤ በፍትሐት አገልግሎት የዕለት ጉርሳቸውን ችለው የሚማሩ በመሆኑም “የፍትሐት ትክለኛ” ይባላሉ፡፡

እንግዲህ ጸባቴው ይህ አሠራር ተለውጦ ጠቅላይ ቤተ ክህነቱ በሊቀ ጉባኤው በኩል ለቤተ ጉባኤው የሚያከፋፍለው በጀት እና በፍትሐት አገልግሎት የሚገኘው ገቢ በቀጥታ ወደ ገዳሙ ገቢ እንዲደረግ ማዘዛቸው በመምህራኑና በደቀ መዛሙርቱ ዘንድ ከፍተኛ ተቃውሞ አሥነስቷል - መምህራኑ እና ደቀ መዛሙርቱ “ጸባቴው እና አንዳንድ መነኮሳት ጉባኤ ቤቱ እንዲኖር አይፈልጉም፤ በሂደትም ያጠፉታል” በሚለው ጥርጣሬያቸው ሳቢያ በጀቱ ከጠቅላይ ቤተ ክህነቱ በቀጥታ ለጉባኤ ቤቱ ሲላክ በነበረበት መልኩ እንዲቀጥል ነው ፍላጎታቸው፡፡

ውዝግቡ ከፍተኛ ደረጃ ደርሶ በነበረበት ወቅት በሊቀ ማእምራን ፋንታሁን ሙጬ የሚመራ አጣሪ ቡድን ወደ ገዳሙ ተልኮ ነበር፡፡ ለጠቅላይ ቤተ ክህነቱ ዋና ሥራ አስኪያጅ ጽ/ቤት የቀረበው የአጣሪ ኮሚቴው ሪፖርት ግን ሊቀ ጉባኤው የትምህርት ቤቱን ማኅተም እና ሰነድ ለገዳሙ እንዲያስረክቡና በጀቱም ወደ ገዳሙ እንደሚዞር የሚገልጽ ነበር፤ ሪፖርቱን መነሻ ያደረገው የብፁዕ አቡነ ፊልጶስ ደብዳቤም በጀቱ በቀጥታ ለገዳሙ እንደሚላክ፣ በፍትሐት አገልግሎት የሚገኘው ገቢም በቀጥታ ለገዳሙ ገቢ እንደረግ የሚያዝዝ ነበር፡፡ እንደ ገዳሙ ምንጮች ምልከታ የአጣሪ ኮሚቴው ሰብሳቢ ከገዳሙ አስተዳደር ለ”ጉዳይ ማስፈጸሚያ” ከተመደበው ብር 190,000 ተጠቃሚ ሳይሆኑ አልቀረም፡፡

በሪፖርቱ እና ውሳኔው ላይ ይግባኝ ለማለት ወደ አዲስ አበባ የመጡት መምህራኑ እና ተማሪዎቹ ወደ ብፁዕ ወቅዱስ ፓትርያኩ ለመቅረብ ብዙ ጥረት አድርገው ቢሳካላቸውም በገዳሙ ጸባቴ እና በሌሎች አጋዦቻቸው፣ “ት/ቤቱን የሚመራው ማኅበረ ቅዱሳን ነው” የሚል ወቀሳ የደረሳቸው ፓትርያኩም በጀቱን ከማኅበረ ቅዱሳን ለማስጣል በሚል መንፈስ የአጣሪ ኮሚቴውን ሪፖርት ማጽናታቸው ተገልጧል፡፡ ከዚህ በኋላ በገዳሙ ተምረው ለከፍተኛ ደረጃ ከበቁ ብፁዓን አባቶች አንዱ የሆኑትና አሁን የቅዱስ ሲኖዶስ ዋና ጸሐፊ የሆኑት ብፁዕ አቡነ ሕዝቅኤል እንዲሁም የደብረ ሊባኖስ ገዳም አካባቢ አረጋውያን ሽምግልና ቢገቡም ውሳኔውን ለማሻሻል እንዳልተቻላቸው የጉዳዩ ተከታታዮች አስረድተዋል፡፡ መምህራኑና ተማሪዎቹ ት/ቤቱን ጥለው ለመሰደድ እንደሚገደዱ ቢናገሩም ጸባቴው “ይሂዱ! ሌላ ተማሪ እናስገባለን” በሚል ወይ ፍንክች ብለዋል፡፡ እንዲያውም ለገዳሙ በተመደበው ሚኒባስ ወደ አዲስ አበባ እየተመላለሱ፣ ማደሪያ እና ቀለብ በገዳሙ ወጭ እየተደረገ በግላቸው መሬት መግዛታቸውን፣ የገዳሙን አቅም ለመደጎም በከተማው ቤት ለመሥራት የታቀደው ሐሳብ ግን መረሳቱን ምንጮቹ ጠቁመዋል፡፡

ለበርካታ ታዛቢዎች አነጋጋሪ የሆነው ጸባቴው በአንድ በኩል “በገዳማችን ጉዳይ ላይ ለመተጋገዝ እና በጸሎት ለመረዳዳት” በሚል ለማኅበረ ቅዱሳን ጽ/ቤት ተደጋጋሚ የእንወያይ ደብዳቤ እያበረሩ፣ በሌላ በኩል ደግሞ ማኅበሩን በፓትርያኩ ፊት መክሰሳቸው ግርምት ፈጥሯል፡፡

በተያያዘ ዜና ከላይ በተገለጸው ጉዳይ አቋማቸውን ከጸባቴው ጋራ እያስተባበሩ ውስጥ ለውስጥ በሚያራምዱት ሐሳብ ከመጽሐፍ ቤቱ በተለይም ከብሉያት መምህሩ ግልጽ ተቃውሞ የገጠማቸው አምስት መነኮሳት “ገድለ ተክለ ሃይማኖትን የቀድሞውን ዳግመኛ አርትተን፣ ሌሎች አዳዲሶችንም ጨማምረን በአዲስ መልክ እንጽፈዋለን” በማለት ተነሣስተዋል ተብሏል፡፡ ከእኒሀም ጥቂቶቹ በጉባኤ ቤቱ ተማሪዎች እንደነበሩ ተዘግቧል፡፡

ከአራት ዐሥርት ዓመታት በላይ ከዘለቀው ከደብረ ሊባኖስ ጻድቁ አቡነ ተክለ ሃይማኖት አንድነት ገዳም የመጽሐፍ ትርጓሜ ት/ቤት አሁን የደቡብ ኦሞ/ ጂንካ/ ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ ብፁዕ አቡነ ዕንባቆም (ሊቀ ጉባኤ ነበሩ)፤ የሰሜን ምዕራብ - ሸዋ ሰላሌ ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ ብፁዕ አቡነ ቀውስጦስ፣ የቅዱስ ሲኖዶስ ዋና ጸሐፊ ብፁዕ አቡነ ሕዝቅኤል ወጥተውበታል፤ ከቀድሞዎቹም እንደ ብፁዕ አቡነ ጎርጎርዮስ ካልዕ ያሉት ይገኙበታል፡፡

6 comments:

Anonymous said...

AONA TAKELA HAYEMANOTE amaledone.laabatochachen lebe yesete.ewenattaga abata yesetane

Anonymous said...

Please correct the following; "በብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ባስልዮስ ዘመነ ፕትርክና ከተቋቋመበት ከ1952 ዓ.ም ጀምሮ በሥራ ላይ የሚገኘውና ደጋግ አበው ሊቃውንትና ካህናት የወጡበት የደብረ ሊባኖስ ጻድቁ አቡነ ተክለ ሃይማኖት አንድነት ገዳም ከሚያዝያ ወር 2003 ዓ.ም ጀምሮ እንደተዘጋ ነው"

The Monastery was established in the 13 century.

I understand you mean "መጽሐፍ ትርጓሜ ቤት". But, readers would be mislead.

Gebre Z Cape said...

Yigermal. Yahunu yibas, beyegizewu ferge bizu complaints eyekerebu yigegnal.

Amilak ante eridan.

ደጀ ሰላም said...

Thank you.

ርብቃ ከጀርመን said...

ዋ የነዛ በፋሽስት ጣልያንወረራ ግዜ ህንጻ ቤተክርስትያኑ ሲቃጠል አይናችን አያይም እያሉ የነደደእሳትውስጥ እራሳቸውን እየጣሉ ያለቁ ሰማእታት አባቶች አጽም ዛሬ ቢያየን እንኩዋን ለህንጻ ቤተክርስትያኑ በአምሳሉ ለተፈጠርነው ውስጣችን ላለው ቤተመቅደስነት ለኛነታችን ሳያስቡልን መሪየሆኑት አባቶች በምንፍቅና በሙስና በክህደትነና እንዲሁም በዝሙት ፈርሰው እያፈረሱት ተቃጥለው እያቃጠሉት እንደሆነ ለመንጋው የማጨንቃችው ሆዳቸው አምላካቸው የሆኑ መሪዎች(አባቶች) እንደተነሱብን ባያችሁልን ባጸደነፍስ ያላችሁ ቅዱሳን አባቶቻችን በደማችሁ የጸናችሁትን ተዋህዶን ዛሬብታዩት ምንትሉን ይሆን አጽማችሁ እውነትን ይፍረድ ቤተክርስቲያን በሉተራውያን ተናውጻለች ምላጃችሁን ከመቸውም ይበልጥ ትሻለች! የሰማእታት አምላከ ቤተክርስቲያንን ይጠብቅልን አሜን!

Anonymous said...

Egziyow berctachew aylyen betame yaseznall!!!!!!!!!!

Blog Archive

የአቡነ ጳውሎስ "ሐውልተ ስምዕ"

ነጻ ፓትርያርክ ምርጫ ቢሆን ኖሮ ማንን ይመርጡ ነበር? እንበልና ሁሉም ነገር ሥርዓቱን ጠብቆ የተከናወነ የእጩዎች ምርጫ ቢሆን ኖሮ፣ አሁን የምናነሣቸው ጉድለቶች ባይኖሩ ኖሮ፣ 6ኛው ፓትርያርክ እንዲሆን የምትመርጡት ማንን ነበር? (ማሳሰቢያ፦ አሁን ያለው ክፍፍል እና የመንግሥት ተጽዕኖ ባይኖር ኖሮ ተብሎ የሚመለስ ጥያቄ ነው። የምን “ባይኖር ኖሮ ነው” የሚል አስተያየት ካለዎትም እናከብራለን።)