September 23, 2011

ወ/ሮ እጅጋየሁ በየነ “ሐውልቱ እስከ መቼ?” የሚል መጽሐፍ አሳተሙ


  • መጽሐፉ የፕሮቴስታንታዊ-ተሐድሶ-ኑፋቄ አራማጅ ነው በሚባል ሰው የተዘጋጀ እንደሆነ ተነግሯል፤
  • በመስቀል-ደመራ በዓል ዐውደ ትርኢት የሚያቀርቡ ወጣቶች የሰንበት ት/ቤቶች ማደራጃ መምሪያ ዋና ሓላፊን ጨምሮ ወ/ሮ እጅጋየሁ በየነ እና ሕገ ወጥ ሰባክያን በበዓሉ ላይ አንዳችም ተሳትፎ እንዳይኖራቸው አስጠንቅቀዋል፤
 (ደጀ ሰላም፤ መስከረም 12/2004 ዓ.ም፤ ሰፕቴምበር 23/2011)፦ ወ/ሮ እጅጋየሁ በየነ አቡነ ጳውሎስን ሰርፕራይዝ አድርጌበታለሁ የሚሉትንና ከብር አራት መቶ ሺ በላይ ገንዘብ እንደወጣበት ተናገሩለት ሐውልተ ስምዕ በተመለከተ “ሐውልቱ እስከ መቼ?” የተሰኘ መጽሐፍ ማሳተማቸው ተሰማ፡፡ ወይዘሮዋ መጽሐፉን መስከረም 16 ቀን 2004 ዓ.ም ተከብሮ በሚውለው የመስቀል-ደመራ በዓል ላይ ለማሰራጨት እንደተዘጋጁ ተነግሯል፡፡


ወይዘሮዋ
ከ100 ያላነሱ ገጾች ያሉት ይኸው መጽሐፍ የተዘጋጀው፣ በወይዘሮዋ አቅራቢነት ከአቡነ ጳውሎስ ጋ የተዋወቀውና በፓትርያኩ ልዩ ጽ/ቤት ተቀምጦ ከኦርቶዶክሳዊ አስተሳሰብ እና ላህይ በራቀ አገላለጽ በፓትርያኩ ስም የተለያዩ የጽሑፍ መልእክቶችን ሚያሰራጨው አሸናፊ መኮንን አማካይነት እንደ ሆነ ተዘግቧል፡፡

በቤተ ዘመድ ስም በፓትርያኩ ዙሪያ ለተሰበሰቡት አንዳንድ ግለሰቦች በፕሮቴስታንቶቹ ባህል እጁን እየጫነ እስከ መጸለይ መድረሱ የሚነገርለት ይኸው ግለሰብ ባለፈው ዓመት ብቻ በሰሙነ ሕማማት፣ በቅድስት ሥላሴ መንፈሳዊ ኮሌጅ የደቀ መዛሙርት ምረቃ በዓል እና በፓትርያኩ 19 ዓመት በዓለ ሢመት ወቅት  “አባታዊ መልእክት ለመንፈስ ቅዱስ ልጆቼ” እና “አባታዊ መልእክት ለደቀ መዛሙርት” በሚል አርእስት በብፁዕ ወቅዱስ ፓትርያኩ ስም የተሰራጩት ጽሑፎች ያዘጋጀ ሲሆን ጽሑፎቹ በመሠረታዊ አስተሳሰባቸው ከኦርቶዶክሳዊ ተዋሕዶ ሃይማኖት የሚፃረሩና የእምነትን ድንበር የሚያፈልሱ እንደሆኑ ተተችዋል፡፡

በጥቅምት ወር 2003 ዓ.ም የተካሄደው የቅዱስ ሲኖዶስ ምልአተ ጉባኤ ቀኖና ቤተ ክርስቲያንንና የአበውን የተቀደሰ ትውፊት በመጣስ በቦሌ ደብረ ሳሌም መድኃኔዓለም ካቴድራል ቅጽር የተተከለው የአቡነ ጳውሎስ ሐውልተ ስምዕ ተነሥቶ በመንበረ ፓትርያኩ ቤተ መጻሕፍት ወመዘክር እንዲቀመጥ ላስተላለፈው ውሳኔ ተገዥ አለመሆናቸውን በተደጋጋሚ ያሳዩት ወ/ሮ እጅጋየሁ ባለፈው ዓመት ከ”ቁም ነገር” መጽሔት ጋራ ባደረጉት ቃለ ምልልስ “ሐውልቱ አሁንም አለ፤ ይኖራል፤ ይቀጥላል፤ የሚፈርስ ሐውልት የለም፤ ሐውልት መሥራት በቅዱስ አባታችን ጊዜ የተጀመረ አይደለም፤ ለሀገራቸው ብዙ ለሠሩትና የዓለም አብያተ ክርስቲያናት ፕሬዝዳንት እና የዓለም ሃይማኖቶች ለሰላም የክብር ፕሬዝዳንት ለሆኑ አባት ሐውልት ይበዛባቸዋልን?” ማለታቸው ይታወሳል፡፡

በመስቀል-ደመራ በዓል እንደሚሰራጭ የተነገረለት መጽሐፍም ወ/ሮ እጅጋየሁ የቅዱስ ሲኖዶስን ውሳኔ በመገዳደር በቃለ ምልልሱ እንደተናገሩት፣ “ሐውልቱ እንዳለ እና እንደነበረ እንደሚቀጥል” የሚገልጹበት፣ “በልዩ ሁኔታ ለማክበር” እያሰቡበት እንደሆነ ለሚነገረው የፓትርያኩ 20 ዓመት ሢመትም መቅድም እንደሆነ ተገልጧል፡፡

በተያያዘ ዜና ወ/ሮ እጅጋየሁ በየነን ጨምሮ የሰንበት ት/ቤቶች ማደራጃ መምሪያ ዋና ሓላፊ የሆኑት አባ ሰረቀ፣ በጋሻው ደሳለኝ እና አሰግድ ሣህሉን የመሳሰሉ ሕገ ወጥ ሰባክያን መስከረም 16 ቀን 2003 ዓ.ም በተለይም በአዲስ አበባ መስቀል አደባባይ በሚከናወነው የመስቀል-ደመራ በዓል አከባበር ወቅት በክቡር ትሪቡኑ እና በአደባባዩ ላይ አንዳችም ተሳትፎ እንዳይኖራቸው የዕለቱን ዐውደ ትርኢት ለማቅረብ በልምምድ ላይ የሚገኙት ከአምስት ክፍለ ከተሞች የተውጣጡ ቁጥራቸው 5000 የሚሆን የሰንበት ት/ቤት ወጣቶች አስጠንቅቀዋል፡፡

የማደራጃ መምሪያው ዋና ሐላፊ ስለ ፕሮቴስታንታዊ-ተሐድሶ-ኑፋቄ ባላቸው አቋም፣ ማደራጃ መምሪያው የተሰጠውን ተልእኮ በአግባቡ ባለመወጣቱ እንዲሁም ብፁዕ ወቅዱስ ፓትርያኩ የፀረ-ፕሮቴስታንታዊ-ተሐድሶ-ኑፋቄን ለመመከት ስለሚደረገው ትግል ባስተላለፉት መመሪያ ሳቢያ የዘንድሮውን የመስቀል-ደመራ በዓል ወደ አደባባይ ወጥቶ በማክበር እና ወደ አደባባይ ሳይወጡ በአጥቢያ ተወስኖ በማክበር መካከል የተለያዩ አቋሞች ሲራመዱ መቆየታቸው ተነግሯል፡፡

ጉዳዩ ያሳሰባቸው የሀገረ ስብከቱ እና የመንበረ ፓትርያክ ጠቅላይ ቤተ ክህነት ሓላፊዎች ከአድባራት እና ገዳማት አለቆች፣ ጸሐፊዎች እና የሰንበት ት/ቤቶች ተጠሪዎች ጋራ መስከረም ዘጠኝ ቀን 2004፣ የበዓል አከባበር ኮሚቴ አባላት እና የመንግሥት ተወካዮች ደግሞ ትንት መስከረም 11 ቀን 2004 ዓ.ም መወያየታቸው ተሰምቷል፡፡

በዘመን መለወጫው “የእንኳን አደረዎ” በዓል እና መስከረም 10 ቀን በቅድስት ሥላሴ ካቴድራል በተከበረው የተቀጸል ጽጌ በዓል ከወትሮው በተለየ ዝቅተኛ የተሳታፊዎች ቁጥር ያሳሰባቸው ብፁዕ ወቅዱስ ፓትርያኩ ለመስቀል-ደመራው በዓል ምእመኑ በስፋት ተቀስቅሶ ወጥቶ እንዲያከብር ተማነዋል፤ መንግሥት በበኩሉ ፓትርያኩ እና አንዳንድ ሓላፊዎች ምእመኑን የሚያስቆጡና ውዝግብ ውስጥ የከተቱ ችግሮች በአስቸኳይ መፍትሔ እንዲበጅላቸው በአጽንዖት አሳስቧል ተብሏል፡፡

በሀገረ ስብከቱ 138 አጥቢያ አብያተ ክርስቲያን የሚገኙትን ሰንበት ት/ቤቶች የሚያስተባብረው የአንድነት አመራር በበኩሉ በአባ ሰረቀ፣ በአጥማቂ ግርማ፣ በበጋሻው ደሳለኝ እና በአሰግድ ሣህሉ ላይ የተጠናቀሩ የምስል ወድምፅ እና የጽሑፍ ማስረጃዎችን በማጠናቀር ለአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት ጽ/ቤት እንዲሁም ለቋሚ ሲኖዶስ ጽ/ቤት ማስረከቡ ተመልክቷል፤ በቀረበው ማስረጃ መሠረትም የጥቅምቱ ቅዱስ ሲኖዶስ ምልአተ ጉባኤ ማስረጃዎቹን መመርምሮ ተገቢውን ውሳኔ እንዲያሳልፍ ተጠይቋል፡፡ ከዚህና ተያያዥ ጉዳዮች ጋራ ያለንን ዜና ዝርዝር እንደደረሰን እናቀርባለን፡፡  
Post a Comment

Blog Archive

የአቡነ ጳውሎስ "ሐውልተ ስምዕ"

ነጻ ፓትርያርክ ምርጫ ቢሆን ኖሮ ማንን ይመርጡ ነበር? እንበልና ሁሉም ነገር ሥርዓቱን ጠብቆ የተከናወነ የእጩዎች ምርጫ ቢሆን ኖሮ፣ አሁን የምናነሣቸው ጉድለቶች ባይኖሩ ኖሮ፣ 6ኛው ፓትርያርክ እንዲሆን የምትመርጡት ማንን ነበር? (ማሳሰቢያ፦ አሁን ያለው ክፍፍል እና የመንግሥት ተጽዕኖ ባይኖር ኖሮ ተብሎ የሚመለስ ጥያቄ ነው። የምን “ባይኖር ኖሮ ነው” የሚል አስተያየት ካለዎትም እናከብራለን።)