September 9, 2011

መ/ር ዘመድኩን በቀለ ለጥቅምት ሦስት ተቀጠረ

  • አርማጌዴን ቁጥር 2 ቪሲዲ በቅርብ ቀን ገበያ ላይ ይውላል::
  • ሁለቱ ተከሳሾች ጉዳያቸውን በዕርቅ ለመጨረስ ከበጋሻው ጋራ እየተደራደሩ ነው
  • ‹‹እርሱ የመሠረተብኝ ክስ ወኅኒ ብቻ ሳይሆን ሲዖል የሚያወርደኝ ቢሆን እንኳ ሲዖል እገባለሁ እንጅ በሃይማኖቴ አልደራደርም፤ የምፈጽመውም ዕርቅ የለኝም፤ ሕጉ ነጻ ያወጣኛል፤››(መ/ር ዘመድኩን በቀለ)
(ደጀ ሰላም፤ ሰፕቴምበር 9/2011):- የፌዴራሉ የመጀመሪያ ደረጃ ፍ/ቤት ቦሌ ምድብ ችሎት በሕገ ወጡ እና ጥቅመኛው በጋሻው ደሳለኝ የስም ማጥፋት ወንጀል ክስ የቀረበበት መ/ር ዘመድኩን በቀለ ከሕግ ባለሞያ ጋራ ተማክሮ በክሱ ላይ ያለውን የእምነት-ክሕደት ሐሳብ እንዲያቀርብ ለጥቅምት ሦስት ቀን 2004 ዓ.ም ትዝዛዝ ሰጠ፡፡ፍ/ቤቱ መ/ር ዘመድኩን በቀረበበት ክስ ላይ ያለውን አቋም እንዲያሳውቅ ለዛሬ ጳጉሜ አራት ቀን 2003 ዓ.ም አዝዞ የነበረ ቢሆንም በቀጠሮ ሰዓት መዛባት ምክንያት ተከሳሹ በሰዓቱ በችሎቱ አልቀረበም ነበር፤ ዳኛውም በጠዋቱ የችሎቱ ውሎ መ/ር ዘመድኩን በፖሊስ ታስሮ እንዲቀርብ ትዝዛዝ ሰጥተው ነበር፡፡ ከቀትር በኋላ ከጠበቃው አቶ ጌትነት የሻነህ ጋራ ወደ ችሎቱ ያመራው መ/ር ዘመድኩን ጠዋት ያልቀረበበት ምክንያት ጊዜ ቀጠሮው ለከሰዓት በኋላ አድርጎ በማሰቡ እንደሆነ በጠበቃው አማካይነት አስረድቷል፡፡

ዐቃቤ ሕግ በመ/ር ዘመድኩን ላይ ያቀረበው የክስ ቻርጅ እንደሚያሳየው ተከሳሽ በግል ተበዳይ በጋሻው ደሳለኝ መልካም ስም ላይ ከባድ ጉዳት ለማድረስ በማሰብ ማራኪ በተባለ መጽሔት ቅጽ 1 ቁጥር 6 ላይ፣ ‹‹ግልጽ ባለ አማርኛ ለመናገር በጋሻው መሃይም ነው፤ ያለመማሩ የፈጠረበት ችግር ነው፤ ሕገ ወጥ ሰባክያን ከሚባሉት ውስጥ በጋሻው ይካተታል…የሚያስተምረው የማያውቀውንና ያልተማረውን ትምህርት ነው፤…መጋቤ ሐዲስ በሚለው ማዕርግ መጠራቱ ሊያስፈራው ይገባል፤›› በማለት በሰጠው ቃለ ምልልስ መሆኑን ያስረዳል፡፡ ለዚህም ክስ ራሱ በጋሻው የሰው ምስክር ጨምሮ መ/ር ዘምድኩን በድምፅ ለመጽሔቱ ቃለ ምልልስ የሰጠበት ካሴት፣ ማራኪ የተባለው መጽሔት ቅጽ 1 ቁጥር 6 እትም እንዲሁም መጽሔቱ ታትሞ ለገበያ ከዋለ በኋላ በፓትርያሪክ አቡነ ጳውሎስ ፊርማ በቁጥር ለ/ፅ/598/03 በቀን 25/11/2003 ዓ.ም ተፈርሞ የወጣውና ፕሮቴስታንታዊ-የተሐድሶ ኑፋቄን በይፋ ስለመቃወም የሚከለክለው መምሪያ በማስረጃ ዝርዝር ውስጥ ተካትተው ቀርበዋል፡፡

ፍ/ቤቱ ቀደም ሲል በሰጠው ቀጠሮ መሠረት በጠዋቱ ችሎት በተለያየ መዝገብ የቀረቡት ሁለቱ ተከሳሾች ዲያቆን ደስታ ጌታሁን እና መ/ር ሣህሉ አድማሱ ክሱን እንደማይከላከሉ በመግለጻቸው ከበጋሻው ደሳለኝ ጋራ ያላቸውን ልዩነት በዕርቅ እንዲጨርሱ በዳኛው የቀረበላቸውን ሐሳብ መቀበላቸው ተገልጧል፡፡ ከችሎቱ በኋላ ዐቃቤ ሕግ ሁለቱን ተከሳሾች ከበጋሻው ጋራ ለማስታረቅ ‹‹እያደራደረ›› መሆኑ የተመለከተ ሲሆን ይህ ዜና በሚጠናቀርበት ሰዓትም በ‹መታራረቁ› ሂደት ወ/ሮ እጅጋየሁ በየነ ተጨምረውበት ተደራዳሪዎቹ በእራት ግብዣ ላይ እንደሚገኙ ተጠቁሟል፡፡
ዛሬ ከቀትር በኋላ በተመሳሳይ አኳኋን ጉዳዩን ከከሳሹ በጋሻው በ‹መተራረቅ› የመጨረስ ሐሳብ በዳኛው የቀረበለት መ/ር ዘመድኩን በቀለ ግን፣ ‹‹እኔ ከበጋሻው ጋራ የግል ጠብ የለኝም፡፡ ልዩነቴ የሃይማኖት ነው፡፡ እርሱ የመሠረተብኝ ክስ ወኅኒ ብቻ ሳይሆን ሲዖል የሚያወርደኝ ቢሆን እንኳ ሲዖል እገባለሁ እንጅ በሃይማኖቴ አልደራደርም፤ የምፈጽመውም ዕርቅ የለኝም፤ ሕጉ ነጻ ያወጣኛል፤›› በማለት በአቋሙ መጽናቱ ተሰምቷል፡፡ መ/ር ዘመድኩን ስለ በጋሻው የክሕደት ትምህርቶች ያዘጋጀውን ‹‹አርማጌዴን ቁጥር 2 ቪሲዲ›› በቅርብ ቀናት ውስጥ ለገበያ እንደሚያውል ተያይዞ የደረሰን ዘገባ ያመለክታል፡፡
Post a Comment

Blog Archive

የአቡነ ጳውሎስ "ሐውልተ ስምዕ"

ነጻ ፓትርያርክ ምርጫ ቢሆን ኖሮ ማንን ይመርጡ ነበር? እንበልና ሁሉም ነገር ሥርዓቱን ጠብቆ የተከናወነ የእጩዎች ምርጫ ቢሆን ኖሮ፣ አሁን የምናነሣቸው ጉድለቶች ባይኖሩ ኖሮ፣ 6ኛው ፓትርያርክ እንዲሆን የምትመርጡት ማንን ነበር? (ማሳሰቢያ፦ አሁን ያለው ክፍፍል እና የመንግሥት ተጽዕኖ ባይኖር ኖሮ ተብሎ የሚመለስ ጥያቄ ነው። የምን “ባይኖር ኖሮ ነው” የሚል አስተያየት ካለዎትም እናከብራለን።)