September 13, 2011

ምን ዓይነት ለውጥ ለቤተ ክርስቲያን? (ለግልጽ ውይይት የቀረበ)


  • በትዕግስት አንብቡት፤ ሚዲያዎችን ጨምሮ ለአባቶችም ለምእመናንም በማድረስ ተባበሩን። .
(ደጀ ሰላም፤ ሰፕቴምበር 3/211 READ IN PDF)፦ ከቅርብ ዓመታት ወዲህ ጨርሶ መደበቅና ማስተባበል እንኳን ከማይቻልበት ደረጃ የደረሰው የቤተ ክርስቲያናችን ውስጣዊ ቀውስ እጅግ አሳሳቢ ሆኗል። እንደ አንድ የቤተ ክርስቲያኒቱ ተከታይ ነገሩን በተቻለን ቅርበት ስንከታተል ቆይተናል። በየሚዲያው የሚወጡትን ጽሑፎች፣ ዜናዎች እና ቃለ ምልልሶችንም ሳያመልጡን ለመረዳት ሞክረናል። ሆኖም በሚዲያ የሚቀርቡት ብዙዎቹ አስተያየቶች ችግሩን በተረዱት መጠን ወይም መልክ በማንጸባረቅ ላይ የተወሰኑ ናቸው።
ችግርን በትክክል መረዳት የመፍትሔው ግማሽ እንደመሆኑ ውይይቱ የሚወደድ ነው። የመፍትሔ አቅጣጫ ለማመላከት የሞከሩ ፀሐፊዎችና ተናጋሪዎች ቢኖሩም ቅሉ ብዙውን ጊዜ ሐሳቦቹ ቅንጭብ በመሆናቸው አጠቃላይ ውጤታቸው በግልጽ የሚታይ አይደለም። ከሁሉም በላይ የሚያሳዝነው ደግሞ ቤተ ክርስቲያኒቱ የራሷን ችግር የምትመረምርበት ተቋማዊ ዝግጅት የሌላት ሆና ትታያለች። ምእመናንና ሌሎች ተቆርቋሪ ዜጎችም ተጨባጭ ለውጥ ሊያመጣ የሚችል አስተዋጽዖ የሚያደርጉበት ዕድል ዝግ ነው ማለት ይቻላል።


እነዚህ ችግሮች ሲያብሰለስሉን ቆይተዋል። ችግሩ ከቁጥጥር ውጭ ከመሆኑ በፊት በየደረጃው በአስቸኳይ ቀጥተኛና ጥልቅ ውይይት መደረግ እንዳለበት እናምናለን። እንደ ዜጋ፣ ከዚያም በላይ እንደ አንድ የቤተ ክርስቲያኒቱ ልጅ የራሳችንን ሐሳብ ለማካፈል ቀርጠን ስንጽፍ የቆየነው ከዚህ በመነሣት መሆኑን በተደጋጋሚ መግለጻችን ይታወሳል። ይህን ሐሳባችንን ሌሎች ሚዲያዎችም እንደሚያስተናግዱት ተስፋ እናደርጋለን። ወደ ሐሳቡ ከመግባታችን በፊት ሦስት ነገሮችን በማሳሰቢያ መልክ መግለጽ እንወዳለን።

1.      አሁን የምንደብቀው፣ ብንደብቀውም የሚጠቅመን ገመና የለም። የቤተ ክርስቲያንን ችግር በግልጽ አውጥቶ መነጋገር ገመና እንደመግለጥ የሚቆጠርበት ጊዜ አልፏል። ችግሩን ለመረዳት፣ መፍትሔ ለመፈለግ እስከጠቀመን ድረስ ማናቸውንም ነገር በግልጽ መጥቀስ እንደበጎ ሊታይ ይገባዋል ብለን እናምናለን። እንደተለመደው በመሠረታዊው ችግር ላይ ሳይሆን በእንጭፍጫፊ እና ሁለተኛ ደረጃ እንከኖች ላይ ጉልበታችንን፣ ጊዜያችንን አናባክን።

2.     የቤተ ክርስቲያን አስተዳደራዊና መንፈሳዊ ችግር እኛ ሰዎች የፈጠርነው ችግር ነው። ስለዚህ ችግሩን የመፍታት ቀዳሚ ኃላፊነት ያለብን እኛው ነን። በዚህ ዓላማችን እግዚአብሔር እንዲረዳን እንማጸናዋለን፣ ያለጥርጥርም ይረዳናል። ነገር ግን ቤተ ክርስቲያን አሁን የገባችበት ቀውስ የእግዚአብሔር ፈቃድ እንደሆነና የእኛ ጥረት ለውጥ እንደማያመጣ ማሰብ በሰውም፣ በታሪክም ይሁን በፈጣሪ ፊት ከኃላፊነት የሚያድነን አይሆንም። ስለዚህ ነገሩ የግልና የጋራ ኃላፊነታችንን የመወጣት ኅሊናዊና አገራዊ ግዴታ ነው።


3.     አንዳንድ ሰዎች አሁን እየታዩ ያሉትን ችግሮች አምኖ ተቀብሎ ስለ መፍትሔ ከመነጋገር ይልቅ እጅ በመጠቋቆም ወይም  በጥንታዊቷ ቤተ ክርስቲያን የነበሩ ጠንካራ ተሞክሮዎችን ብቻ በማንሣት የራሳቸውንም የአድማጮቻቸውንም ትኩረት ሲያባክኑ ይታያል። እነዚህን ሰዎች “ታሪክ ውስጥ ከመደበቅ ወጥታችሁ እውነትን ተጋፈጡ፤ እጅ መጠቋቆሙ ለውጥ አያመጣም” ልንላቸው ይገባል። አሁን የተረት ጊዜ አልፏል። አሁን ያለችውና የምንነጋገርባት ቤተ ክርስቲያን በተቋማዊ ቅርጿ ከጥንታዊቷ የተለየች ናት። በቀደመው ዘመን የነበረ ጥሩ ነገርም ለአሁን ችግር መቅረፊያ ትምህርት እንጂ የአሁኑን መሸፈኛ ወይም ማረሳሻ ሆኖ መቅረብ የለበትም። እንዲህ ማድረግ አሁን ያለው ችግር እንዲባባስ ጊዜ መስጠት ነው።

ለውይይት እንዲረዳን በአራት ጭብጦች ላይ እናተኩራለን። የችግሩ ተቋማዊ አድራሻ፣ የችግሩ ምንጭ፣ ያለው ችግርና የሚያስከትለው አደጋ፣ ምን ዓይነት ለውጥ እንደሚያስፈልገን ማለትም አዝጋሚ ወይስ አብዮታዊ? የሚሉትን ጭብጦች እናነሣለን። በሚገባ የሚታወቁ ችግሮችን ወደመዘርዘር ሳንገባ እያጠቃለልን ለማቅረብ እንሞክራለን። በዚህ ጽሑፍ ውስጥ ሙሉ በሙሉ ያተኮርነው በውስጣዊ ችግሮች ላይ ብቻ ነው። ግምገማውን የተሟላ ለማድረግ ውጫዊ ሁኔታዎችና ተጽዕኖዎች እጅግ አስፈላጊ እንደሆኑ እንረዳለን። ሁሉንም ነገር በዚህ አጭር ጽሑፍ ማጠቃለል ግን የሚሞከር አልሆነልንም። ውስጣዊውንም ቢሆን በጨረፍታ ነው።

ውይይታችንን ለመጀመር ብዙ አማራጮች አሉን። የችግሩን መጠን፣ በማስከተል ላይ ያለውን ጉዳትና ያዘለውን አደጋ መተንተን የበለጠ ተገቢ ይመስለናል። የምንመርጠው የመፍትሔ አቅጣጫም በዚህ ላይ የተመሠረተ ይሆናል። በችግሩ ስፋት፣ ባሕርይ እና አደጋ ላይ ተቀራራቢ ግንዛቤና አቋም ካልያዝን በመፍትሔዎቹ ላይ መስማማት አንችልም። እዚህ ላይ በሁሉም ላይ ፍፁም አንድ ዓይነት መረዳትና መግባባት መፍጠር አለብን። ሙሉ በሙሉ ግን ይቻላል ማለታችን አይደለም።

የችግሩ ተቋማዊ አድራሻ

አሁን ቤተ ክርስቲያንን እንደጎርፍ ያጥለቀለቁትን ችግሮች በተቋማዊ አድራሻቸው ብንመድባቸው ስምንት ዋና ዋና ቦታዎችን እናገኛለን። እነዚህ ተቋማት እንደየደረጃቸው ቁልፍ የአመራር እና የአፈጻጸም ሚና የሚጫወቱ ናቸው። ያለእነዚህ ተቋማት የቤተ ክርስቲያኒቱን ተቋማዊ ሕይወት ማሰብ አይቻልም። የአንዱ በሽታ የሌላውም ሕመም ነው፤ የአንዱ መዳከም ለሌላው ውድቀት በር ከፋች ነው። ተቋማቱ በዓላማቸው፣ በሥራ እሴቶቻቸው እና በራዕያቸው አንድ ዓይነት እንደሆኑ ይታመናል። ወይም የአንድ ቤተ ክርስቲያን ልዩ ልዩ ብልቶች እንደመሆናቸው መጠን እንደዚያ እንዲሆኑ ይጠበቃል። አስቸኳይ ትኩረትና መሠረታዊ ለውጥ የሚፈልጉት ተቋማቱ የሚከተሉት ናቸው።

1.      ቅዱስ ሲኖዶስ፣
2.     ቅ/ ፓትርያርኩ፣
3.     ጠቅላይ ቤተ ክህነት፣
4.     አኅጉረ ስብከት፣
5.     አጥቢያ አብያተ ክርስቲያናት አስተዳደር፣
6.     ሰበካ ጉባኤ፣
7.     ማኅበረ ካህናት እና
8.     ሕግጋተ ቤተ ክርስቲያን፣

ስለ እነዚህ ተቋማት ዝርዝር ድክመት መጻፍ ሰፊ ቦታ የሚወስድ ነው። አብዛኛውም ተደጋግሞ የተነገረ ነው። ቀዳሚዎቹን ሰባት ተቋማት አስተሳስረው የሚይዙት መጠባበቂያዎች ሕግጋት ናቸው። ሕግጋት ስንል በተለይ አስተዳደርን፣ የአስተዳደር ዘይቤን የሚመለከቱትን ነው። አሁን ከሰፈነው ዝብርቅርቁ የወጣ የሚመስል፣ ጠያቂና ተጠያቂ የማይለያዩበት፣ የዕውቀትና የሥራ ጥራት መለኪያ ደብዛው የጠፋበት ሁኔታ በመነሣት የችግሮቹ አንዱ ምንጭ ከሕግጋትና ከአፈጻጸማቸው ጋር የተቆራኘ እንደሆነ አያጠራጥርም። (ሕግጋትን እንደ አንድ “ተቋም” መመልከት በማኔጅመንትም ይሁን በኅብረተሰብእ ሳይንስ የተለመደ ነው።) እዚህ ላይ በሥራ ላይ የሚገኘው ቃለ ዐዋዲም ይሁን ሌሎች መመሪያዎች/ ሕጎች ከነድክመቶቻቸውም ቢሆን በተግባር ላይ አልዋሉም። አንድ ሕግ ተግባር ላይ ሊውል ካልቻለ ሕጉ ራሱ ችግር ሊኖርበት እንደሚችል አመላካች ነው። ችግሩ “የአፈጻጸም ነው” ማለት ወደ ምን ዓይነት የስሕተት አዙሪት እንደሚከት ከኢሕአዴግ መማር ይቻላል።

የችግሩ  ምንጭ

ቀደም ሲል የጠቀስናቸው ተቋማት ከሥራና ከመፍትሔ ማዕከልነት ወደ ብክነትና ወደ ችግር መፈልፈያነት የተለወጡበት ብዙ ምክንያት ሊኖር ይችላል። ታሪካዊ፣ ግላዊ፣ ቡድናዊ፣ ተቋማዊ እና ውጫዊ ሁኔታዎች የየራሳቸውን ሚና ይጫወታሉ። ዝርዝሩን ለማወቅ ጠለቅ ያለ ጥናት ያስፈልጋል። በአጠቃላይ ግን የታዘብናቸውን ከመዘርዘራችን በፊት የቤተ ክርስቲያኒቱ ችግር ሁሉ በአሁኑ ፓትርያርክ የተፈጠረ አድርጎ መረዳት የተሳሳተ መሆኑን መግለጽ እንፈልጋለን። አሁን ተባብሶ ገነፈለ እንጂ ችግሮቹ ቀድሞም የነበሩ ናቸው። ችግሮቹን ከታሪካዊ መሠረታቸው ለመረዳት ካልሞከርን የመፍትሔ አማራጫችን ወደተሳሳተ አቅጣጫ ሊመራን ይቻላል። አቡነ ጳውሎስ ከመንበራቸው ቢነሱ ችግሮቹ በአንድ ቀን ተንነው አይጠፉም። በእርግጥ ለውጥ ለማምጣት ትልቅ ዕድል ይሰጣል። አሁን በምንታዘበው መልኩ ግን አቡነ ጳውሎስን ራሳቸውን በውድም በግድም የመፍትሔው አካል ማድረግ ይቻላል፤ ይገባልም።

1.    የተቋማዊ አሠራር ባህል አለመዳበር

በታሪካዊና በግለሰባዊ ምክንያቶች የተነሣ በቤተ ክርስቲያናችን ውስጥ የተቋማዊ አሠራር ባህል አልዳበረም። ከተጻፈ ሕግና መመሪያ ይልቅ ልማድ ወይም የአንድ መንፈሳዊ አባት/ ካህን ቃል የበለጠ ይከበራል። ይህ ከፓትርያርኩ ጀምሮ እስከ አጥቢያ አስተዳዳሪ ድረስ የሚታይ ባህል ነው። ሰዎች ይህን የሚያደርጉት በቅንነት ወይም ደግሞ የግል ፍላጎታቸውን (ጥቅማቸውን) ለማስከበር ሊሆን ይችላል። በምንም መነሻ ያድርጉት ግን ባህሉ የምናከብራቸው ካህናት ቃልና ፍላጎት ሕግን እንዲተካ መንገዱን አመቻችቷል። በዚህም ምክንያት በሕጉና በመመሪያው መሠረት ብቻ እሠራለሁ የሚለው አገልጋይ በየትኛውም የቤተ ክርስቲያናችን ተቋም ረጅም ጊዜ መቆየት አይችልም። በሰበካ ጉባኤ አባልነት እንኳን በዚህ መንገድ መሥራት ትልቅ ተጋድሎን ይጠይቃል።

በአጠቃላይ በማወቅም ይሁን ባለማወቅ በሕዝቡ ውስጥ የዳበረው አመለካከት የሚቀበላቸውን ሰዎች ቃል ከሕግ ባላይ እንዲያከብር የሚያበረታታ ነው። አንድ የምናከብረው ካህን የሃይማኖት ሕጸጽ ቢገኝበት ፈጽሞ አንታገሰውም፤ የሃይማኖት ሕጸጽ ካልተገኘበት ግን የፈለገውን ሕግ እየጣሰ ቤተ ክርስቲያንንና በዙሪያው ያሉ ምእመናንን ቢጎዳ እንኳን ቃሉን ከማክበር አንቆጠብም። አንዳንድ ጊዜ የምንሰማው ጉድ ሰውየው ሃይማኖቱን ቢክድ ከሚሰማን የበለጠ የሚያሳዝን እና የሚያሳፍር ነው። ነገር ግን ስለቤተ ክርስቲያን ሕግም ይሁን ስለ ኅሊና ብሎ ይህን መሰሉን ሰው “ተመለስ” ብሎ የሚገስጽ ሰው ከሺህ አንድ አይገኝም። ሕግ አውጪም፣ ሕግ ተርጓሚም፣ ሕግ አስፈጻሚም አንድ ሰው፣ አንድ አካል የሆነበት ተቋም ከቀውስ የሚታደገው አይኖርም።

ይህ የተሳሳተ አመለካከት፣ እምነትና ባህል በረጅም ጊዜም ቢሆን መቀየር ይኖርበታል። ይህም ለአባቶች የምንሰጠው መንፈሳዊ ክብር መነሻና ትርጉሙ ምንድን ነው? የክብራችን መጀመሪያና መጨረሻስ የት ነው? በሚሉት ጉዳዮች ላይ ዘላቂ ትምህርት እንደሚያስፈልገን ያሳያል።     

2.   የተጠያቂነት አለመኖር

በተራ ቁጥር አንድ የተገለጸው ችግር እዚያ አያቆምም። ሕግ የሚጥሱ ሰዎች ተጠያቂ የሚሆኑበት አሠራርና ባህልም የለም። ይህም ከቅዱስ ሲኖዶስ እስከ አጥቢያ የተንሰራፋ ባህል ነው። ለዚህ አራት ምክንያቶች አሉ። አንዱ ምክንያት ተጠያቂነትን አስገዳጅ የሚያደርግ የሕግና የተቋም መደላድል የለም። ሁለተኛው ምክንያት በተጠያቂነት እና በይቅርታ ጽንሰ ሐሳቦች ዙሪያ ጥርት ያለ አመለካከትና ግንዛቤ በብዙዎች ዘንድ የለም። ሦስተኛ ምክንያት በተለይ ካህናትንና አገልጋዮችን ተጠያቂ ማድረግ ለእነርሱ ያለንን ክብር እንደመካድ አልፎም ቤተ ክርስቲያንን እንደመዳፈር ይወሰዳል። ሁሉም በስሜትና በቆራጥነት “ካራውን” የሚመዘው የሃይማኖት ሕጸጽ ሲባል ነው። አራተኛው ምክንያት የመጠቃቀምና የመሸፋፈን ስትራቴጂ ነው። ሌባ ሌባን እንደማይከስ ሁሉ (ትርፉን እንካፈል ይላል እንጂ) በቤተ ክርስቲያንም “ደብቀኝ እደብቅሃለሁ” የሚለው የጥቅም ትስስር የገነነ ነው።

በፍርድ ቤትም ይሁን በአስተዳደራዊ መድረክ በተጠያቂነት መቅረባቸው አግባብ አይሆንም የምንላቸው ሰዎች ካሉ እነርሱን መጀመሪያውኑ ከአስፈጻሚነት የሥራ ምድብ ማራቅ ያስፈልጋል። ፓትርያርኩን ከዕለታዊ የሥራ አስፈጻሚነት በማራቁ ሐሳብ ጠቃሚ የሚሆንበት አንዱ ምክንያት ይህ ነው። አንድ ፓትርያርክ በብር ማባክን፣ በሠራተኛ ምደባ በትንሹም በትልቁም ስሙ ሊነሳ፣ እርሱም እዚህ ውስጥ ሊገባ ፈጽሞ አይገባውም። ለፓትርያርኩም ለቤተ ክርስቲያኒቱም አይበጅም።

3.   ሙያ፣ ባለሙያ እና ዓላማ

በታሪክ እንደምናነበው ቤተ ክርስቲያንን ከጠበቋት ጥንካሬዎች አንዱ ሙያንና ባለሙያዎቿን ማክበሯ ነው። ዛሬ ይህ በቦታው የለም። ሲጀመር አብዛኞቹ የቤተ ክርስቲያኒቱ ተቋማት ራዕያቸው፣ ግባቸው፣ ዓመታዊ ዒላማቸው ወዘተ. ምን እንደሆነ በተጨባጭ የሚታወቅ ነገር ጥቂት ነው። አንድ አጥቢያ ወይም ሀገረ ስብከት ዕቅዱ ምንድን ነው? ዕቅዱ በምን ይመዘናል? ዕቅዱን እንዴት ያስፈጽማል … ከጥቅም ጋር ካልተያያዙ የማይታሰቡ ናቸው። ቢሮ መግባት፣ ዐውደ ምሕረት ላይ ቆሞ መስበክ፣ ሕንጻ መገንባት ብቻውን የሥራው መጀመሪያም መጨረሻም የሚመስለው ይበዛል። ውድድሩ የበለጠ ገቢ መሰብሰብ እንጂ ሌላ መመዘኛ የለውም።

የዚህ አንዱ መሠረታዊ ችግር ሙያ እና ባለሙያዎች በቤተ ክርስቲያን ቦታ አለማግኘታቸው ነው። ሙያና ባለሙያ ሲባል በአብነት ትምህርት ቤቱ ዕውቀት መስክ ብቻ አይደለም። ከዚያ የባሰውና ቤተ ክርስቲያኒቱን እገደል አፋፍ ያቆማት እንዲያውም የሌላው ዕውቀት፣ ሙያና ሙያተኛ በቤተ ክርስቲያን መጥፋቱ ነው። ዛሬ በሥራ አመራር፣ በኢኮኖሚክስ፣ በሶሲዎሎጂ ወዘተ ዓለም እጅግ ተራምዶ፣ ሁሉም ዓይነት ተቋማት የዚህ በረከት ተቋዳሾች ሆነው ቤተ ክርስቲያን ግን አሁንም በጾም ላይ ትገኛለች፤ ጾሙ ከተፈታ ስንት ዘመን አልፎት። እኛ ዘንድ አሁንም ካህን መሆን ወይም የነገረ መለኮት ዕውቀት ብቻውን ለማንኛውም ሥራ እንደሚያበቃ ይቆጠራል።

የትርጓሜ መምህሩ፣ የዜማው ሊቅ፣ የብሉይና የሐዲስ አስተማሪው ሁሉ የየራሱ ሙያ አለው። እነዚህ ባለሙያዎች ዕውቀታቸውን እንዲዘሩ አልተከበሩም፣ አልረዳናቸውም። ይብሱን ደሞ ቁምስናና ጵጵስና የአስተዳደር ሙያ ባለቤትነት ማዕረግ ተደርጎ ይቆጠራል። እነዚህ ሰዎች ጥሩ አመራር ባለመስጠታቸው በእነርሱ ብቻ አይፈረድባቸውም። ከዚህ የበለጠ ሊያደርጉ የሚችሉበት ዕውቀት፣ ልምድ እና ልምድ እና “ኤክስፖዠር” የላቸውም። ምናልባት በተወሰነ መልኩ ጥሩ ሥራ የሚሠሩ ቢኖሩም እንኳን በግል ብቃታቸውና ቀናነታቸው እንጂ በባለሙያነታቸው አይደለም። እንዲህ ዓይነቱ ብሩህ ልብ ያለው ቀና ሰው ደግሞ ብዙ ጊዜ አይገኝም።

ዛሬ ችግሩን ሁሉ እንዲፈታ የምንጠብቅው ቅዱስ ሲኖዶሳችን ብዙ ዕድሜያቸውን በገዳም ሕይወት ያሳለፉ ብፁዓን አበው የሚገኙበት ነው። ለእነዚህ አባቶች ንጹሕ ሙያዊ መረጃ፣ ትንተናና አስተያየት የሚሰጡ የየዘርፉን ባለሙያዎች አልመደብንላቸውም። ቀሪዎቻችን በየትምህርት ቤቱና በየሥራ ቦታችን የምናየው የሥራ ሒደት፣ የሰው ኀይል አስተዳደር፣ የሀብት አጠቃቀም ሳይንስ ለእነርሱ የምናስበውን ያህል ቅርብና ቀላል ሊሆን አይችልም። ምንም እንኳን መንፈሳዊ አባቶቻችን ቢሆኑም ሁሉ የተገለጠላቸው ቅዱሳን እንዳልሆኑም መርሣት አይገባም ነበር። እነርሱ ራሳቸውም ቢሆኑ “ሁሉን እናውቃለን” ሳይሉ ባለሙያዎችን በዙሪያቸው መሰብሰብ ይገባቸው ነበር። ይሄ ነገር በሁሉም ደረጃ መኖር ያለበት ሆኖ ይሰማናል።    

4.   የምእመናን መገለል

የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያን ጥንታዊ የአምልኮ ሥርዓት ምእመናንን በእጅጉ የሚያሳትፍ ነው። ከቅዳሴ የበለጠ የተከበረ ሥርዓት የለንም። ቅዳሴ ግን ያለ ምእመናን የተሟላ አይሆንም። የቅዳሴ ሥርዓቱ እያንዳንዱ ሂደት ምእመናን ያሉበት ነው፤ ከአሐዱ አብ ቅዱስ እስከ አሜን። የዘመናዊቷ ቤተ ክርስቲያን (መንበረ ፕትርክና ካገኘን ወዲህ ያለው ማለታችን ነው) ተቋማዊ አስተዳደር ግን በመዋቅሩም ይሁን በይዘቱ የካህናት፣ ይልቁንም የመነኮሳት ፍጹም የበላይነት የተንሰራፋበት ነው።

ቃለ አዋዲው (የቤተ ክርስቲያኒቱ ከአጥቢያ እስከ ሲኖዶስ የምትተዳደርበት ዋናው ሕግ) ለምእመናን ቦታ መስጠቱ የሚካድ ባይሆንም በመዋቅሩ ከታች ወደላይ ስንጓዝ የምእመናን ውክልናና ተሳትፎ በከፍተኛ መጠን እየቀነሰ ሔዶ ደብዛው ይጠፋል። ከፍ ባሉት መድረኮች ለስሙ የሚወከሉት ምእመናን ይህ ነው የሚባል ዕውቀትና ልምድ ማካፈል የማይችሉ፣ ከአባቶች ቡራኬ ለመቀበል እንጂ የሐሳብ ፍጭት ለማካሔድ የማይችሉ ናቸው። ስለዚህ እንዳሉ መቁጠርም የሚቻል አይደለም። በአጥቢያ ደረጃ የሰበካ ጉባኤዎቹ አደረጃጀት ዞሮ ዞሮ በአስተዳዳሪዎቹ ፍጹም የበላይነት ሥር የሚወድቅ ነው። አስተዳዳሪዎቹ ደግሞ ቀደም ሲል በተጠቀሱት ምክንያቶች ትርጉም ያለው ኃላፊነትና ተጠያቂነት የሌለባቸው ናቸው። በሰበካ ጉባኤ ለማገልገል ገብተው ተማርረው የወጡ ባለሙያ ምእመናን ብዙ ናቸው። ዛሬ አብዛኛው ምእመን በአጥቢያው ጉዳይ መሳተፍ የሚፈልግ አይደለም። ለምን ብሎ ነገሩን መመርመር ያስፈልግ ይሆናል።

የቤተ ክርስቲያኒቱን ማዕከላዊ አንድነት ከመጠበቅ አኳያ አሁን ያለው አሠራር የሚያስተምረን ነገር እንዳለ እናምናለን። ነገር ግን ምእመናንን በስፋት ወደ አስተዳደር ማምጣት የዘላቂው መፍትሔ አካል ተደርጎ መታየት ይኖርበታል። የቤተ ክህነቱ ሰዎቹ የተማሩ፣ ሌላው ምእመን ያልተማረ (ጨዋ) የነበረበት ማኅበረሰባዊ እውነታ ተቀይሯል። ዛሬ ዕውቀትን ከነገረ መለኮት መስክ አስፍተን ብንገመግም ብዙ ዕውቀት ያለው በቤተ ክህነት ሰዎች አካባቢ ሳይሆን በጥንቱ “ጨዋ” ምእመን ዘንድ መሆኑን እንገነዘባለን። ስለዚህ የቤተ ክርስቲያናችን አስተዳደር ይህን እውነት የሚቀበልና የሚጠቀምበት መሆን አለበት። የቤተ ክርስቲያን አስተዳደር “ለጥቁር ራሶች” (ክህነት የሌላቸው የቤተ ክርስቲያን አገልጋዮችና ምእመናን በሽሙጥ የሚጠሩበት ስም ነው) በሩን እንዲከፍት ዘመኑ ያስገድደዋል።

ያለው ችግርና የሚያስከትለው አደጋ

በቤተ ክርስቲያናችን ውስጥ ያሉትን ችግሮች በጥልቀት መመርመር ራሱን የቻለ ጥናት ይጠይቃል። በዚህ ጽሑፍ ለማንሣት የሚቻለው መሠረታዊ ችግር ይታይባቸዋል የምንላቸውን አካባቢዎች (ርእሰ ጉዳዮች) በአንኳሩ መጥቀስ ነው። መጀመሪያ ችግሮቹን ከዚያ አደጋዎቹን በአጠቃሎ እንጠቅሳለን። እነዚህም፦

ሀ. የክህነትና የሥልጣነ ክህነት አሰጣጥ (ከዲቁና እስከ ጵጵስና)፤
ለ. የዘመናዊ አስተዳደር መዋቅር፣ ዕውቀት፣ ሕግና አሠራር ያልዳበረበት አመራር (ከአጥቢያ እስከ ቅ/ሲኖዶስ)፤
ሐ. ብልሹ የካህናትና የአገልጋዮች አስተዳደር (ከሙዳየ ምጽዋት ቀበኛው አንስቶ ወሲባዊ ጥቃት እስከሚፈጽፈመው ድረስ   
    ተንደላቆ የሚኖርበት አስተዳደር)፤ 
መ. ከፍተኛ የሀብት ብክነት እና ምዝበራ (ሀብት ሲባል ገንዘብ፣ ጊዜ፣ ዕውቀት፣ ጉልበት ያካትታል)፤
ሠ. ሥር የሰደደ በወንዝ፣ በብሔር፣ በገንዘብ እና በጥቅም ላይ የተመሠረተ አሠራር፤
ረ. አገሪቱ፣ ቤተ ክርስቲያኒቱ፣  እና ምእመናን የደረሱበት ዘመን የሚመጥን ሕግና አሠራር የሚፈጥር፣ የሚተገብር አካል
   በቤተ ክህነቱ አለመኖር፤
ሰ. በቤተ ክርስቲያኒቱ ውስጥ ያሉ ልዩ ልዩ ፍላጎቶችን አቻችሎ መምራት የሚችል አመራር መታጣት፤
ሸ. ቤተ ክርስቲያኒቱን በባለቤትነት (ከፈጣሪ በተሰጠው አደራ መሠረት) የሚመራ፣ ስለወደፊቱ የሚጨነቅ፣ የሚያቅድ፣
   የሚሠራ አመራር/ ትውልድ አለመፈጠሩ፤
ቀ. የመንፈሳዊነት እጦት በተለይ በአገልጋዮች ዘንድ (ይሄ ለመለካት የሚያስቸግር ነው፤ ደሞ ሁሉንም የሚመለከት አይደለም። ብዙ እውነተኛ መንፈሳዊ ሰዎች አሉ። አብዛኛው ግን በሥራው ተገልጦ ስናየው የምንታዘበው ሌላ ነው።) መኖር፤ የሚሉት ናቸው። ወጣም ወረደ፣ በዚህም አልነው በዚያ፣ ችግሮቹ ሁሉ ከእነዚህ የሚወጡ አይደሉም። ከዚህ የሰፋ፣ የችግሩን ክፋት የበለጠ የሚያሳይ ዝርዝር ሊሰጡ የሚችሉ ብዙዎች ይኖራሉ።

ለመሆኑ እነዚህ ችግሮች የደቀኑብን አደጋ ምንድን ነው? በእኛ አስተያየት፣ በአደጋዎቹ ላይ የሚኖረን አመለካከት የቤተ ክርስቲያናችንን መጻዒ ዕድል ሊወስን የሚችል ነው። እንዲሁ ለውይይት ያህል አሁንም አንኳር የምንላቸውን አደጋዎች እንዘርዝር። አንዳንዶቹ አደጋዎች ከወዲሁ መድረስ መጀመራቸውን ልብ ይሏል።

1.      የቤተ ክርስቲያኒቱ መሠረታዊ የሃይማኖት ትምህርት ሊፋለስ ይችላል፤ ይህም ለውስጣዊ የሃይማኖት አንጃ (የመናፍቃን ቡድን) መፈጠር በር ይከፍታል፣
2.     የቤተ ክርስቲያን አስተዳደራዊ ማዕከላዊነት ሊናጋ ይችላል። (አጥቢያዎች፣ ወረዳዎች እና አህጉረ ስብከቶች በማዕከሉ ማለትም በጠቅላይ ቤተ ክህነቱ አልመራም በሚሉ ቡድኖች እጅ ሊወድቁ ይችላሉ። ልዩነቱ በጳጳሳት ዘንድ መድረሱን፣ የጳውሎስ የመርቆርዮስ መባል መጀመሩን ልብ ይሏል። ሌላስ ሊከተል አይችልምን? )፤
3.     ቤተ ክርስቲያን በብሔር እና በፖለቲካ ልትከፋፈል ትችላለች (አልደረሰም ለማለት ያስደፍረናል?)፤
4.     ቤተ ክርስቲያን ጠብቃ ያቆየቻቸው ጠቃሚ ትውፊቶች፣ ቅርሶች እና ታሪኮች ያለ ባለቤት ይቀራሉ፤ የወሮበላ መነገጃ ይሆናሉ። ይህም ከተጀመረ ሰንብቷል።
5.     ልዩነቶቹ ወደ ምዕመናን ሊወርዱ ይችላሉ። ይህም አደገኛ ግራ መጋባት ይፈጥራል። ችግሩ ለአገርም ሊተርፍ ይችላል።
6.     ቤተ ክርስቲያኒቱ በአገሪቱ ውስጥ ያላት ተደማጭነት፣ አስተዋጽዖ እና ክብር ጠፍቶ ለአሸማቃቂ የሐፍረት ታሪክ መልስ ለመስጠት የምንገደድበት ሁኔታ ይመጣል። ከዚህ ከፊሉ መፈጸሙን ልብ ይሏል።
7.     ከሁሉም በላይ ደግሞ (እግዚአብሔር አይበለው እንጂ) የቤተ ክርስቲያኒቱ መንፈሳዊ ሕይወትና ክብር ይወድቃል፤

እነዚህን ማስቀረት ካልተቻለ ፈጣሪም፣ ታሪክም፣ አገርም፣ ልጆቻችንም ተባብረው እንደሚወቅሱን ቅንጣት ያህል አንጠራጠርም። እግዚአብሔር ይህንን ለሰው የማይቻል የሚመስለንን ውድቀት አሸንፈን የምንወጣበትን ጥበብ፣ ትዕግስትና እምነት እንዲሰጠን ዘወትር እንጸልያለን።

ደጀ ሰላማውያን፣ አንባቢዎች ከእኛ በበለጠ የሚያውቁትን የችግር በመዘርዘር ሐዘን ውስጥ ከትተናችሁ እንዳንሔድ ስለመውጫውም የምናስበውን እናካፍል።

ምን ዓይነት ለውጥ፤ አዝጋሚ ወይስ አብዮታዊ?

ቤተ ክርስቲያን ለውጥ አያስፈልጋትም የሚል ሰው የሚገኝ አይመስለንም። ካለም እኛ የምንጽፈው ለእርሱ አይደለም። እሱ በምቾት እንቅልፉ እንዲቀጥል እንተወዋለን። “ፕሮቴስታንታዊ-ተሐድሶ” የሚባለው ፕሮጀክትም የእዚህ ጽሑፍ ዓላማ አይደለም። ከፍ ብሎ የተጠቀሱት ችግሮች ሲቀረፉ “ተሐድሶ” የሚባለው ነገርም ዘላቂ መፍትሔ ያገኛል። አሁን በአጽንዖት መጠየቅ የምንወደው የሚያስፈልገው ለውጥ ምን ዓይነት ነው? የሚል ነው። ከብዙ ሰው ጋር ስንወያይ - ከጳጳሳትም ከምእመናንም ጭምር ብዙዎች የአፈታቱን አቅጣጫና ፍጥነት ሳያስቡበት እናገኛቸዋለሁ። በደምሳሳው ግን አዝጋሚ የሆነ የችግር አፈታት ሒደት የሚመርጡ ናቸው። ሲፈሩም ይታያሉ። “አዝጋሚ ለውጥ ስንት ዓመት የሚፈጅ ነው?” ሲባሉም ቁጥር መናገር ይከብዳቸዋል። በእኛ አመለካከት ደግሞ የችግሩ ስፋት፣ ጥልቀት እና የሚያስከትለው አደጋ ሲታይ “አዝጋሚ” የሚባለው አቅጣጫ “ጅብ ከሄደ ውሻ ጮኸ” የሚያሰኝ እንዳይሆን ስጋት ይገባናል።

ቀደም ብሎ እንደተጠቀሰው አደጋዎቹ መታየት ጀምረዋል። አንዳንዶቹ ደንድነዋል። ችግሮቹ በረጅም ዘመን የተጠራቀሙ እንደመሆናቸውም በረጅም ሒደት ብቻ ይፈቱ ቢባል በእነዚሁ ችግሮች ተጠልፎ እመንገድ መቅረት ይኖራል። በጠቅላይ ቤተ ክህነቱም፣ በአጥቢያም የሚቀርቡ ሐሳቦች እየተኮላሹ የሚቀሩት በዚሁ በተደላደለው በሽታ እየተጠለፉ ነው። (“አብዮት” የሚለውን ቃል ከደም መፋሰስ ወይም ከዓመጻ ጋራ እንዳይያያዝብን እንማጸናለን። “ሥር ነቀል” የሚለውን ቃል መጠቀም አልፈቀድንም። ችግር ችግሩን ብቻ እየመረጠ የሚነቅል ከሆነ እንኳን ባልከፋ።)

እኛ እንደምንለው፣ ቤተ ክርስቲያን የአሥር ዓመት መሠረታዊ የለውጥ እንቅስቃሴ ወይም አብዮት መጀመር ይገባታል። አብዮት በሚለው ፈንታ ሌላም ስም መስጠት ይቻላል። ዘገምተኛ ለውጥ የሚሉት ሰዎች በዚህ ከተስማሙ እኛ ከስሙ ቅሬታ የለንም። ነገር ግን በአዝጋሚ አካሄድ ከተባሉት ችግሮች በ10 ዓመት ሩቡን እንኳን መፍታት አይቻልም። ስለዚህ አብዮታዊ ወይም መሠረታዊ እና ፈጣን ለውጥ ይሻላል።

ለውጡ ፈጣን መሆን የሚገባው በምን ምክንያት ነው?

ሀ. በቤተ ክርስቲያን ላይ የተጋረጡት አደጋዎች እየተፈጸሙ፣ በብዛትም፣ በዓይነትም፣ በሚያስከትሉት ውጤትም እየጨመሩ
    መምጣታቸው በገሐድ መታየት በመጀመሩ፤
ለ. ችግሮቹ እርስ በርስ የሚመጋገቡና የሚደጋገፉ በመሆናቸው፣ አንዱን ሳይነኩ ሌላውን ማቡካት ትርፉ ድካም ስለሆነ እንዲሁም፣
ሐ. አሁን የተንሰራፋው ሥርዓት ብልሹ ቢሆንም ተቋርቋሪዎች እንደማያጣ በመረዳት፤ ለእነዚህ ተቆርቋሪዎች ረጅም ጊዜ መስጠት ለውጡን ያለጥርጥር ስለሚያደናቅፍ ነው።

ከችግሮቹ መጠን አኳያ 10 ዓመት ብዙ አይደለም። ለውጡ አብዮታዊ እንዲባል የተመረጠበትም ምክንያት ከጊዜው ይልቅ በሂደቱ የማይመለስ መሆን እና በሚፈልገው መንፈሳዊ ቆራጥነት ነው። በጥበብ፣ በማስተዋል፣ ነገር ግን በተቻለ ሰብዓዊ ፍጥነት መጓዝ ይጠይቃል። የቀረውን ደሞ ለቤቱ ከእኛ በላይ ቀናዒ የሆነው አምላካችን ይሞላልናል።

ይህንንስ አልን፤ “በ10 ዓመት ምን ምን ይሠራ?” የሚል ጥያቄ ይኖራል። እኛ ነገሩን ሁሉ ማወቅ አይቻለንም። እናውቃለን ብንልም እየዋሸን ነው። ይልቅ አንኳር አንኳር ጥቆማዎች እንስጥ።

የ10 ዓመት ለውጥ አመላካቾች

1.      በመጀመሪያው ዓመት የሲኖዶስ ጉባኤ በጉዳዩ ላይ መክሮ፤ አንድ የለውጥ ጉባኤ ኮሚቴ ይሰይም።

2.     ይህ ኮሚቴ ከአራት ወር ባልበለጠ ጊዜ የቤተ ክህነቱ ተቀጣሪ ያልሆኑ ነጻ ባለሙያዎች ብቻ የሚገኙበት፣ ከ10 የማይበልጡ ሰዎች ያሉበት የጥናት ኮሚቴ ያቋቁም። ለኮሚቴውም የሚያስፈልገውን ያህል ገንዘብ፣ ያለምንም ስስት፣ ጠቀም ያለ በጀት ይመደብለት። ይህ የጥናት ኮሚቴ ምን ምን እንደሚሠራ በዝርዝር በጽሑፍ ይሰጠው። በአጠቃላይ ሥራው ያለውን ችግር ዘርዝሮ፣ በክፍል በክፍል ተንትኖ ማቅረብ ነው። ከዚሁም ጋራ የመፍትሔ አማራጮችን ያቀርባል። ይህንንም የሚያደርገው በሳይንሳዊ የጥናት ዘዴዎች፣ መረጃ ሰብሳቢዎችን አሰማርቶ፣ ተንታኞችን ቀጥሮ፣ ለመፍትሔ አማራጮች ወጥቶ ወርዶ (ካስፈለገው ሌላም አገር ተጉዞ) ይሆናል። እዚህ ውስጥ ማንኛውም የቅ/ ሲኖዶስ አባል ወይም የቤተ ክርስቲያን ሠራተኛ ለአስረጅነት ካልሆነ በኮሚቴ አባልነት ባይገባ ጥሩ ነው እንላለን። በመረጃ ስብሰባውና ትንተናው የተማሩ የሰንበት ትምህርት ቤት ወጣቶች ተሳትፎ ብዙ ይጠቅማል። ይህ የጥናት ኮሚቴ ሦስት ወራት ለዝግጅት፣ ከ8-12 ወራት ለዋናው ሥራ ይሰጠው።

3.     የጥናት ጉባኤው ውጤቱን ለውይይት ያቀርባል። ውይይቱም በየደረጃው የሚካሄድ ይሆናል። በሁሉም አጥቢያ ማድረግ የማይቻልም የማያስፈልግም ይሆናል። ከካህናት፣ ከአብነት መምህራን፣ ከገዳማውያን፣ ከመንፈሳዊ ኮሌጅ ተማሪዎችና መምህራን፣ ከሰንበት ት/ቤት ተማሪዎች፣ ከተለያዩ ማኅበራት ጋራ በተናጠልም በጋራም በጥናቱ ላይ ተወያይቶ ሐሳቦችን ማዳበር።

4.     የጥናት ጉባኤው በውይይቶቹ የተገኙትን ነጥቦች አጠቃሎ ተንትኖ ከጥናቱ ጋራ በአባሪነት ያስቀምጣል። ከጥናቱና ከውይይቶቹ በመነሣትም የመጨረሻ የውሳኔ ሐሳቦችን ከአማራጮች ጋራ ያቀርባል። ይህም ከየአኅጉረ ስብከት የሚውጣጡ ተካፋዮችና ሁሉም ብፁዓን አበው በሚገኙበት የመጨረሻ ውይይት ይካሄድበታል። ብፁዓን አበው በዚህ ጉባኤ እንዲገኙ የሚገባው የጥናቱን ግኝት እንዲሰሙና ለመጨረሻ ውሳኔያቸው እንዲያግዛቸው ነው።

5.     በመጨረሻ ጉዳዩ ለውሳኔ ለቅዱስ ሲኖዶስ ይቀርባል። ጉባኤው ውሳኔ ከማሳለፉ በፊት በጋራ ለሦስት ቀን ሱባኤ ይይዛል። ከዚያም የመፍትሔ አማራጮቹን አስቀምጦ ወደ ቀጣዩ የተግባር እንቅስቃሴ ይገባል።

6.     በተመረጡት አማራጮች መሠረት አዲሱን ሂደት የሚመራ፣ የሚቆጣጠር ሙሉ ሥልጣን ያለው ጊዜያዊ አካል ይቋቋማል። ይኸው አካል ከአንድ ዓመት ያልበለጠ የትግበራ ዝግጅት፣ ጊዜና በጀት ይሰጠዋል። በዚህም ጊዜ ሕጎችን የመከለስና አዳዲሶቹን የማዘጋጀት፣ አወቃቀሮችን የመፈተሽና የመቀየር/ የማሻሻል ሥራ ያከናውናል፤ ሙከራ የሚደረግባቸውን አጥቢያዎች፣ አኅጉረ ስብከት ይመርጣል፤ በጀቱን አቅርቦ ያጸድቃል። በውስጣዊ አሠራርና ሕግ ሳይሆን በሌሎች አማራጮች የሚፈቱ ችግሮችን ለምሳሌ የተለያዩ አባቶችን የማስታረቅ፣ ከመንግሥትና ከሌሎች አካሎች ጋራ ያለውን ግንኙነት የሚመለከቱ አካሄዶችን አርቅቆ ለጳጳሳቱ የለውጥ ጉባኤ ያቀርባል። እርሱም በተራው ለሲኖዶሱ እያቀረበ ሂደቱ ይቀጥላል።

7.     የሙከራ ትግበራው ከ6-9 ወራት ተካሂዶ፤ በገለልተኛ ወገን ግምገማ ይደረጋል። ከግምገማው ውጤት በመነሣት በሕጎቹ፣ በአሠራሮቹ ወዘተ ላይ ማስተካከያ ተደርጎ ሪፖርት ይቀርባል። ከዚህ በመነሣት ቅዱስ ሲኖዶሱ በሕጎቹና አሠራሮቹ ላይ መክሮ ያጸድቃቸዋል፤ የሥራ መመሪያም ይሆናሉ።

8.     በአዲሶቹ አመለካከቶች፣ ሕጎች፣ አሠራሮች ላይ በየደረጃው በየክፍሉ ሥልጠና ይሰጣል። ጊዜያዊ አካሉም የሥራውን ሪፖርት አቅርቦ፣ ቀጣይ ሥራዎቹን ለሚመለከታቸው አካላት አስረክቦ ይሰናበታል፣ ይበተናል።


9.     በአምስተኛው ዓመት በሁሉም አኅጉረ ስብከትና የወረዳ ቤተ ክህነት ደረጃ አዲሱ አሠራር ሙሉ በሙሉ ተግባር ላይ መዋል ይጀምራል። ይህ ዓመት ከሞላ ጎደል የሙከራ ጊዜ ነው የሚሆነው። ሌሎቹ የቤተ ክርስቲያኒቱ ተቋማትም በየፊናቸው የየራሳቸውን አዲስ አሠራር እንዲሁ ይጀምራሉ። በዓመቱ መጨረሻ ተቋማቱ በአዲሱ አሠራር ላይ ሪፖርታቸውን ያቀርባሉ። ጠቅላይ ቤተ ክህነቱ ሪፖርቱን መርምሮ የቀጣዩን አምስት ዓመት አፈጻጸም ዕቅድ ይነድፋል። ሁለተኛው አምስት ዓመት/ ምዕራፍ አሁን ያለው ብልሹ አሠራር ከሥሩ መነቀል የሚጀምርበት ነው። ከፍተኛ ትግስት፣ ጥበብና ጽናት ይፈልጋል። ወሬው ወደ ተግባር የሚቀየርበት ስለሚሆን ውጊያውም ያይላል።

10.   በቀጣዮቹ አምስት ዓመታት ቤተ ክርስቲያናችን በአስተዳደራዊና በመንፈሳዊ ቁመናው ወደ አዲስ ምዕራፍ የምትሸጋገርበትን ዘመን በቁርጠኝነት ለመቀበል የምትዝጋጅበት ነው።

ይህ አሥር ዓመት ለብዙ ሰዎች በጣም ረጅም እንደሚመስል እናውቃለን። ነገር ግን ሥራ ከተሠራባቸው ረጅም አይደሉም። እጅግ ቀርፋፋ የሆነ አስተሳሰብና አሠራር ለረጅም ዘመናት በሰፈነበት ተቋም ውስጥ መሠረታዊ ለውጥ ለመጀመር ከዚህ ያጠረ ጊዜ የሚበቃ አይመስለንም። ከዚህ ባጠረ ጊዜ (ዋናው ጊዜ የመጀመሪያው አምስት ዓመት ነው) የቤተ ክርስቲያኒቱን ሁለንተናዊ  ሕይወት የሚነካ መሠረታዊ ለውጥ መጀመር ከተቻለ ደስታችን ነው።

እንግዲህ እኛ ያለንን አካፈልን። አንዳች የሚረባ ነገር እንዳለበት ከእኛ በተሻሉ ሰዎች ልብ ያድርና ለፍሬ ይበቃል። የደካማ ሰዎች ከንቱ ጩኸት ከሆነም እንዲሁ ይቀራል። ለቤተ ክርስቲያን ይበጃል የምንለውን በማስተዋል የምንነጋገርበትና የምንፈጽምበት የመንፈስ ቆራጥነት ካለን ይህን ዘመን እንሻገረዋለን። በያዝነው መንገድ ከቀጠልን ግን የዛሬ አምስት ዓመት የምንነጋገርው ከአሁኑ በባሰ አዘቅት ውስጥ ሆነን እንደሚሆን ለመገመት ነቢይነት አይጠይቅም።

የአባቶቻችን አምላክ ይርዳን። አሜን።

40 comments:

Anonymous said...

Thanks!

You are come up with excellent idea!
I appreciated it!
May God Bless You all and Our Church!
I beleieve that Yes Dynamic change is necessary b/c of the mentioned reasons!

YFS

frew said...

i beleive it must start soon. you indicated roughly, it needs to be refined. let us go from more general to specific issues. i would expect you to include social aspect in your study, such as how to make aware of ordinary people, mobilise power, appoint consultant, see international experience etc.
God bless you

Anonymous said...

Thanks

you welcome a good idea we have to start to move instead of complain and cry on others. I belive the church needs a dynamic change bwfore we will face a dynamic death.
So good Dejeselam.

Anonymous said...

Many thanks for your inintative! God Bless you!

Shall we start from the government or from the church first? Is it possible to bring such change in the presence of the current government? Is there any change on the historical formal and informal relationship & common interest between the govt and the church admin?

I would be blessed if I can get convincing explanation on this.

TxsHad the church be free froThe interest and impact of the gov

ከውጭ ሀገር said...

ጽሑፉ ከበስተጀርባው ሽምቅ ከሌለበት አንዳንድ የሚታረሙና የሚጨመሩበት ካልሆነ በስተቀር ያስኬዳል።
እንደኔ የሚከተሉትን ቅድመ ሁኔታዎች Preconditions ተግባራዊ ብናደርጋቸው ለለውጡ-ሂደት ፋይዳ ይኖረዋል ብዬ አምናለሁ
1. እስካሁን ድረስ በቤተ ክርስቲያኒቱ ውስጥ ተፈጥረው ያሉትን ችግሮች ‘የእገሌ ወእገሌ’ ሳይሆን የጋራ መሆናቸውን ተማምኖ በልዩ ትኩረት ተቃቅረዋል የተባሉት የቤተ ክህነት አካላት፣ ድርጅቶች፣ ተቋማት፣ ቡድኖች፣ክብደት ሊሰጣቸው የሚችሉ ግለሰዎች በአካል ተገናኝቶ ዕርቅ ማውረድ ይገባል
2. ቀጥሎም የቀጣይ የጋራ ስራ ምን መሆን/መሰራት እንዳለበት በውይይት ተማምኖ ለጋራ ስራው አብሮ ዘብ መሆን
3. እንደጠቀሳችሁት ‘ናሙና ቦታዎች’ ተወስደው ሳይንሳዊ ጥናት ማካሄድና ለጥናቱ -መፍትሔ ተገዢ መሆን (ጥናቱ ‘ግላዊ-መንፈስ’ እንዳይዝ አጥኚዎቹ ሙያቸው በሚፈቅድላቸው ደረጃ ከሁሉም የቤተ ክርስቲያኒቱ አካላት አሳታፊ ቢሆን ተአማኒነት ሊኖረው ይችላል)
4. ለለውጡ የሚሮጥ ሁሉ ከስጋዊ ድብቅ ዓላማ ርቆ ለእግዚአብሔር ቃል መታዝዝና እንዲታዘዝ ማድረግ/ቃልኪዳን መግባት

Anonymous said...

Anonymous Said
God bless u
Gov.& Religous are different
aur ajenda abou our cherch then I agree your solution no tomorow but start now.We start now God will be finished.
Thanks

Anonymous said...

I beleive it must start soon. you indicated roughly, it needs to be refined. let us go from more general to specific issues. i would expect you to include social aspect in your study, such as how to make aware of ordinary people, mobilise power, appoint consultant, see international experience etc.
God bless you

lele said...

Egizeabhare yeradanale batame tero hasabe nawe.tsome 7ken banse ande laye benetsome?

Anonymous said...

Thanks!

Good move

God bless

F

Anonymous said...

ማሕበረ ቅዱሳኖች? የግል ዓላማችሁን ለማሳካት ፈጽሞ አዋጪ ያልሆነ እስትራቴጂ ነድፋችሁ በስሕተት ጎዳና ተጒዛችሁ ምንያህል ሰብአዊ፣ሞራላዊ፣ሃይማኖታዊ፣ፊናንሳዊ ብሎም ሃገራዊ ቀውስ እንዳስከተለላችሁ በተወሰነ መልኩ ወደ ማስታወስ ደረጃ የደረሳችሁ ይመስላል። አሁንም ጉዳዩ ከልብ አምናችሁበት ከሆነ ያስመሰግናችሗል፤ ሌላ ማዳፈኛ ከሆነ ግን ኪሳራው ይብሳል እንጂ አይቀንስም።
ዘአዋሳው

Daniel said...

"በመረጃ ስብሰባውና ትንተናው የተማሩ የሰንበት ትምህርት ቤት ወጣቶች ተሳትፎ ብዙ ይጠቅማል።"????????? Leading Sentence
Doesn't the church have a two sword-edged persons (including from Sunday schools),today? I don't think so!

Anonymous said...

thank u deje selam for sharing this kind of intersting idea we have to pray toghter first and stand up for new change bc no wait until we lost our church

Anonymous said...

Hi DS
Don't you think MK and Sunday Schools are part of the problems????

Temelkach said...

I do have a problem with your idea which states like this" Removing paulos may not solve all our problems" I disagree with that because there are some issues we can't solve as long as he is in power. Example attack on our church by tehadiso. From what I observed so far, no matter how effectively we try to avoid them so that our church is clear of tehadiso ideas, it will happen again, why? because the source is in the church, to make things worse at the top position. So how can removing him may not be a solution?

Anonymous said...

እኛ መች እውነቱን ተናገርና ?( አቡነ )ጳውሎስ መናፍቅ (ኢ ኦርቶዶክሳዊ ናቸው) በሥራቸው መናፍቃን ወይም ግራኝ ካደረሱብን ጉዳት የበለጠውን አድርሰውብናል አሁንም ይቀጥላሉ፤ በእሳቸው ሳያበቃ ቤተክርስቲያኗ ውስጥ መሰል ጠላቶችን በመሰግሰግ ግፉ እሳቸው ካለፉ በኋላም እንዲቀጥል እያደረጉት ነው።
ስለዚህ እውነተኛ ኦርቶዶክሳዊ ነን የምንል ከሆንን በግልጽ ምንፍቅናቸውን በመናገር ታላቅ ዘመቻ ማድረግ ያስፈልጋል፤ ይህ ዘመቻ ደግሞ ከውጭው ዓለም ቢጀመር የተሻለ ይሆናል። በየክፍለዓለማቱ ያሉት ኦርቶዶክሳውያን አባጵውሎስን እና ተከታዮቻቸውን እውቅና መንፈግ DERECOGNIZE ማድረግ አለባቸው፤ ይህ ማለት የተለመደውን ጩኸት መቀጠል አይደለም፤ በግልጽ በተቀናጀ መልኩ በየትኛውም ክፍለዓለም ሲጓዙ ቤተ ክርስቲያን እንዳይገቡ፤ ሥማቸው እንዳይጠራ፤ የቅስቀሳ ዘመቻው ሀገር ውስጥ ላሉትም በደንብ እንዲሰጥ ማድረግ ያስፈልጋል።
ዋናው ችግር አካሔዳችን የፍርሃት እና ብልጣብልጥነት የተሞላው ነው። ማህበረ ቅዱሳንን ጨምሮ ብዙ የቤተክርስቲያን አገልጋዮች ይህን ያውቃሉ፤ ግን ፈራ ተባ እያሉ እየተለማመጡ መኖርን ተያይዘውታል፤ ይህ ደግሞ ምዕመናኑ ጥርት ያለ አቋም እንዳይኖራቸው አድርጓል።
ታዲያ ማን ይናገርልን? ማን ይሙትልን? እኛ በእምነታችን ድፍረት ካጣን ማን ይምጣልን? ዝም ብሎ በየሚዲያ ላይ ርፖርት ማቅረብን እኮ እነሱም ተለማምደውታል…. ያውቃሉ ምን ያመጣሉ ብለውናል። አንባቢውም እግዚአብሔር ያውቃል ብሎ መሸሽ እንጂ ሞቼ እገኛለሁ ሲል ወይም ተግባራዊ ምላሽ ሲጠቁም እና ሲንቀሳቀስ አይታይም። ትልቁ ነገር ግን የቅንጅት ማጣት ነው እንጂ አሁንም ብዙዎች አሉ ለኦርቶዶክስ መስዋዕት ሊሆኑ የሚደፍሩ፤
ስለሆነም በግልጽ ቋንቋ የተዋህዶ ልጆች ተነሱ እያልን የተጣናከረ ዘመቻ ከዳር እስከዳር ማንቀሳቀስ ያስፈልጋል፡ፍርሃቱን እናስወግድ፤ ለመስዋዕትነቱ እንዘጋጅ… ከዚህ ውጪ በብዕር ስም ከማውራት ውጭ ሌሎች እስኪሞቱልን የምንጠብቅ ከሆነ እኛ የአቶዶክስ ደጋፊዎች እንጂ አማኞች አይደለንምና አርፈን እንቀመጥ።

Ye dingil baria said...

Well said Dejeselam!
On top of all these what u missed or forgot deliberately or not is that specially at this time it's linked with z ruling political regime in Ethiopia, which is giving good cover ups and back up of those who r working against our church including z patriarch(who most of z time revealed that he is proud of these gorilla fighters above God), in my view when we get a political solution for all the problems of our land z church problem will also be alleviated simultaneously, above all the power of God will help us in doing so.
On z other hand the enemies of our church (pro protestant - tehadisowoch) will keep their work in fighting against our efforts, as they r doing in blaming u nad Mahibere Kidusan, bcoz ur the real sons nad doughters of Tewahido. So stay strong and be patient.
May our Lord and our Queen protect our church from these evil doers for ever, Amen!!!!!!!!

tade said...

church should be renew because of so many obstacles .

Anonymous said...

the is a wonderful article . i learn a lot. here go deje selam .thank you for this article writer,
We are the problem and we are also the solution.

Anonymous said...

ጥሩ ሃሳብ ነው። ነገር ግን ምእመኑ ሁሉም በሀገር ውስጥ አና ውጭ ያለው በአንድ ልብ አንዲሰራ አና አንድ ሃሳብ አንድኖረን ተደማጭነት ያላቸው አባቶች፣ አናቶች፣ ወንድሞች አና አህቶች ስላለው የቤተክርስትያን ቺግር በግልፅ ለሕዝቡ ማሳወቅ አና ለመፍትሔውም ህዝቡ በአንድነት አንዲሰሩ ማነሳሳት አለባቸው ብዬ አስባለው። እኔ ባለሁበት በዚ በሰሜን አሜሪካ በምኖርበት ከተማ ቤተክርስቲያን በርካታ ምእመን ቢኖርም የሚመጡት ካህናት ስላለው የቤተክርስቲያን ችግር ከምመኑ ጋር አይወያዩም። በጣም የሚገርመው አብዛኛው የከተማችን ምእመን በነሱ ቤት አገር ሰላም ነው። የሚለያዩት በራሳቸው የአስተዳደር ችግር እንጂ በጠቅላላ በ ተዋሀዶ እምነት ላይ የተጋረጠውን አደጋ አያዩም። ስለዚህ ካህናት አና መምህራን አባካችሁ ከሕዝቡ ጋር ስለችግሩ በግልፅ አውሩ፣ ስለመፍትሄውም ምከሩ። እራሳችንን ከምንገነጥል ይልቅ አንድ ሆነን ለመፍትሄው አንትጋ። አምላከ ቤተክርስቲያን ይርዳን!

Anonymous said...

Thanks for opening up for the idea of Tehadeso (finally!). It is about time. We need a structured tehadeso as the paper attempts to outline.

Anonymous said...

ችግሮቹ እርስ በርስ የሚመጋገቡና የሚደጋገፉ በመሆናቸው፣ አንዱን ሳይነኩ ሌላውን ማቡካት ትርፉ ድካም ስለሆነ እንዲሁም፣
very goog views, the problem need to be resolved in holistic approach.
But we shouldn’t penetrate to the battle field with only a fist of kollo and a bullet of gunfire like Sebastopol. We should have well established commitment before we struggle your dangerous enemies such as bad governance and administration, in addition to poverty.
You know? If you don’t have well focused shot and miss your target while marching with unorganized and poorly committed generation, one can imagine the result of the consequence that could be. Tehadisso-protestants are working to raid the massive eotc followers in very organized ways. They will not be kicked out from our church with emotional reaction. By the way, I wrote similar comment to --www.gebrher.com
I believe that God is always blessing the HAMMER till to the end of this world, however, temporarily disturbed. Therefore, just like nehimiya, we should stand and join hands to maintain the damaged church territory and fence by carrying the holy gunfire (tsom-tselot-sigdet) together with those smart ideas you mentioned in this particular post and others, if any. Therefore, we need praying and fasting to get mercy for our bunch of sin and simultaneously posses well established commitment to implement those ideas so that everything would be OK. You know, our battle is not with siga-ena-dem, we should be wise enough too; just like a perfect hit man! and not to lose our target!. Generally, I agree with you.

D/n Haile michael zedebre tsige said...

በዚህ ጉዳይ የቤተክህነት ሰዎች ከፊት ይሆናሉ ማለት ይከብዳል ::
አቡነ ጳውሎስን ብቃወሙም በቤተክህነት ተቀጥረው ያሉ ሰዎች በዚህ ጉዳይ ከፊት መሆን ይከብዳቸዋል ምክንያቱም አቡነ ጳውሎስ ከዚህ በፊት ያደረሱትን ጫና ያውቁታልና ::
አንድ ገጠመኝ ልንገራችሁ:-
የእነ በጋሻው ማኅበር ሰብሳቢ ፍጹም ታደሰ በዑራኤል አከባቢ ወጣቶችና ምዕመናን ጥረት መድረክ ላይ እንዳይገኝ ብከለከልም
ለ2 ወር ሙሉ በሥራ ገበታው ሳይገኝ ስቀር የደብረ ጽጌ ቅዱስ ዑራኤል ደብር ከሥራ እንደተባረረ ማስታወቂያ ካወጣበት በኋላ አሁን የአቡነ ጳውሎስን የማስፈራሪያ ደብዳቤ በማሳየት ቁጭ ብሎ ደመ ወዙ ይቀበላል::
ካህናቱ ስለ ፍጹም "ተሐዲሶ"ነትና ማንነት መረጃው አላቸው ታዲያ አነሱ ምን ያድርጉ አቅም የላቸው::
አሁን ይባስ ብሎ ከፓትርያርኩ መመሪያ አምጥቻለሁ መድረክ ላይ ካልወጠሁ እያለ በለፈው ነሐሴ 29 ግብግብ ነበረ::
አቡነ ጳውሎስ እስካሉ ካህናቱ ችግሩን ብያዉቁም ችግሩን ለመጋፈጥ ድፍረት አይኖራቸውም ::ከዚያ በፊት የአቡነ ጳውሎስ የኃይል ሚዛን ቢያንስ ልቀል ይገባል :: ምዕመናን ሁሉ ከጎናቸው መሆናችንን መረጋገጥ ይጠበቅብናል::
ስለ ወቅቱ የቤተክርሰቲያናችን ችግር ላይ በእንዲህ መልክ ወደ መፍትሔዎች ከመግባታችን በፊት የሚከተሉትን ማድረግ ያለብን ይመስለኛል:-
1. ብያንስ ሁሉም ሰንበት ትምህርት ቤቶችና የሁሉም አጥቢያ አቢያተክርስቲያና ትሰበካ ጉባኤ አመራር አባላት ስለ ጉዳዩ አንድ ዓይነት ግንዛቤና አመለካከት መያዛቸውን ማረጋገጥ
2. በተቻለ መጠን ሁሉም ምዕመናን ስለ "ተሐዲሶ "ምንነት መረጃ እንዳላቸውና በተላይም በሕዝቡ ዘንድ በስህተት ትምህርታቸውና በማታለላቸው ተዋቂ ዘማሪያን ሰባኪያን ወዘተርፈ ነን ባዮችና የ"ተሐዲሶ" መናፍቃን አቀንቃንኞች ከሕዝቡ ኅሊና መውጣታቸውን ወይም በንስሐ ስህተታቸውን አምነው መመለሳቸውን ማረጋገጥ::
3. በቤተክርስቲያኒቱ ዕውቅና የሌላቸው እንደ በEBS የሚተላለፍ ታዖሎጎስ መርሐ ግብር ያሉት የቤተክርሰቲያኒቱ እንዳይደሉ ለምዕመናን በተለያየ ብዙኀን መገናኛ ማሳወቅ
4. "ተሐዲሶ "የለም የሚሉ እንደ አባ ሰረቀ ዓይነት አደናጋሪ መግለጫዎች ግልጽ ማስተካከያ በተለያየ ብዙኀን መገናኛ መስጠት
5.ስለ ተሐዲሶ ያሉ መረጃዎችን ሁሉ ማውጣትና ለምዕመናን በማዳረስ ጠንክሮ መሥራት


የመሳሰሉትን ሳንሰራ ወደዚህ ዓይነት መፍትሔ መሄድ ምዕመናንን ከፍሎ የ"ተሐዲሶ"ን ቤተክርስቲያንን የመክፈል ዓላማ በአጭሩ እኛ እንዳንፈጽመው ትልቅ ጥንቃቄ ይሻል የሚል ሐሳብ አለኝ::
እዚህ ላይ ጽሑፉ ስለ "ተሐዲሶ "ሳይሆን ስለ አስተዳደር ጉዳይ ትኩረት ሰጥቶ ሳለ እኔ ስለ "ተሐዲሶ" ትኩረት መስጠቴ
1 አንደኛ "ተሐዲሶ "የቤተክርስቲየንን ዕድገት አንድነት ጥንካሬ ና በአጠቃለይ የተሻለ ራዕይ ስለማየፈልጉ እነሱ ሳይለዩ ስለቤተክርስቲያን የተሻለ ራዕይ አንድ ላይ መወያየቱ ከጥቅሙ ጉዳቱ ያመዝናል::
2 እነዚህ ሰዎች በዚህ ውይይትም ሆነ መነኛውም መፍትሔ ፍለጋ ላይ ልከሰት የሚችለውን አለመግባባት ሁሉ ልክ ዲያቆን ዳንኤል ክብረት ስለ ማኅበረ ቅዱሳን የሰጠውን አስተያየት እንዳራገቡና ለራሳቸው ዓላማ መጽፈፀሚያ ለመጠቀም እንደሞከሩ እያረገቡ ቤተክርስቲያኒቱን ሰላም ይነሱአታል ::ስብስም እነዚህ ሰዎች በቤተክርስቲያኒቱ ሥር እሰካሉ ድረስ ቤተክርስቲያኒቱን ለመክፈል ልጠቀሙ ይችላሉ::
ስለዚህ ለምዕመናን የቤተክርስቲያኒቱ "ዘመድና ባዳ "ተለይቶ መታወቅ አለበት::
ረድኤተ እግዚአብሔር የወላዲተ አምላክ ምልጃና የቅዱሳን ሁሉ ተራዳእነታቸው አይለየን::

D/n Haile michael zedebre tsige said...

በዚህ ጉዳይ የቤተክህነት ሰዎች ከፊት ይሆናሉ ማለት ይከብዳል ::
አቡነ ጳውሎስን ብቃወሙም በቤተክህነት ተቀጥረው ያሉ ሰዎች በዚህ ጉዳይ ከፊት መሆን ይከብዳቸዋል ምክንያቱም አቡነ ጳውሎስ ከዚህ በፊት ያደረሱትን ጫና ያውቁታልና ::
አንድ ገጠመኝ ልንገራችሁ:-
የእነ በጋሻው ማኅበር ሰብሳቢ ፍጹም ታደሰ በዑራኤል አከባቢ ወጣቶችና ምዕመናን ጥረት መድረክ ላይ እንዳይገኝ ብከለከልም
ለ2 ወር ሙሉ በሥራ ገበታው ሳይገኝ ስቀር የደብረ ጽጌ ቅዱስ ዑራኤል ደብር ከሥራ እንደተባረረ ማስታወቂያ ካወጣበት በኋላ አሁን የአቡነ ጳውሎስን የማስፈራሪያ ደብዳቤ በማሳየት ቁጭ ብሎ "ደመ ወዙን" ይቀበላል::
ካህናቱ ስለ ፍጹም "ተሐዲሶ"ነትና ማንነት መረጃው አላቸው ታዲያ አነሱ ምን ያድርጉ አቅም የላቸው::
አሁን ይባስ ብሎ ከፓትርያርኩ መመሪያ አምጥቻለሁ መድረክ ላይ ካልወጠሁ እያለ በለፈው ነሐሴ 29/2003 ግብግብ ነበረ::
አቡነ ጳውሎስ እስካሉ ካህናቱ ችግሩን ብያዉቁም ችግሩን ለመጋፈጥ ድፍረት አይኖራቸውም ::ከዚያ በፊት የአቡነ ጳውሎስ የኃይል ሚዛን ቢያንስ ልቀል ይገባል :: ምዕመናን ሁሉ ከጎናቸው መሆናችንን መረጋገጥ ይጠበቅብናል::
በወቅቱ የቤተክርሰቲያናችን ችግር ላይ በእንዲህ መልክ ወደ መፍትሔዎች ለመፈለግ ከመግባታችን በፊት የሚከተሉትን ማድረግ ያለብን ይመስለኛል:-
1. ብያንስ ሁሉም ሰንበት ትምህርት ቤቶችና የሁሉም አጥቢያ አቢያተክርስቲያናት ሰበካ ጉባኤ አመራር አባላት ስለ ጉዳዩ አንድ ዓይነት ግንዛቤና አመለካከት መያዛቸውን ማረጋገጥ
2. በተቻለ መጠን ሁሉም ምዕመናን ስለ "ተሐዲሶ "ምንነት መረጃ እንዳላቸውና በተላይም በሕዝቡ ዘንድ በስህተት ትምህርታቸውና በማታለላቸው ተዋቂ ዘማሪያን ሰባኪያን ወዘተርፈ ነን ባዮችና የ"ተሐዲሶ" መናፍቃን አቀንቃንኞች ከሕዝቡ ኅሊና መውጣታቸውን ወይም በንስሐ ስህተታቸውን አምነው መመለሳቸውን ማረጋገጥ::
3. በቤተክርስቲያኒቱ ዕውቅና የሌላቸው እንደ በEBS የሚተላለፍ ታዖሎጎስ መርሐ ግብር ያሉት አሳሳች ሚዲያዎችና ትምህርቶች የቤተክርሰቲያኒቱ እንዳይደሉ ለምዕመናን በተለያዩ መገናኛ ብዙኀን ማሳወቅ
4. "ተሐዲሶ "የለም የሚሉ እንደ አባ ሰረቀ ዓይነት አደናጋሪ መግለጫዎች ግልጽ ማስተካከያ በተለያዩ ብዙኀን መገናኛ መስጠት
5.ስለ ተሐዲሶ ያሉ መረጃዎችን ሁሉ ማውጣትና ለምዕመናን በማዳረስ ረገድ ጠንክሮ መሥራት


የመሳሰሉትን ሳንሰራ ወደዚህ ዓይነት መፍትሔ መሄድ ምዕመናንን ከፍሎ የ"ተሐዲሶ"ን ቤተክርስቲያንን የመክፈል ዓላማ በአጭሩ እኛ እንዳንፈጽመው ትልቅ ጥንቃቄ ይሻል የሚል ሐሳብ አለኝ::
እዚህ ላይ ጽሑፉ ስለ "ተሐዲሶ "ሳይሆን ስለ አስተዳደር ጉዳይ ትኩረት ሰጥቶ ሳለ እኔ ስለ "ተሐዲሶ" ትኩረት መስጠቴ
1 አንደኛ "ተሐዲሶ "የቤተክርስቲየንን ዕድገት አንድነት ጥንካሬ ና በአጠቃለይ የተሻለ ራዕይ ስለማየፈልጉ እነሱ ሳይለዩ ስለቤተክርስቲያን የተሻለ ራዕይ አንድ ላይ መወያየቱ ከጥቅሙ ጉዳቱ ያመዝናል::
2 እነዚህ ሰዎች በዚህ ውይይትም ሆነ መነኛውም መፍትሔ ፍለጋ ላይ ልከሰት የሚችለውን አለመግባባት ሁሉ ልክ ዲያቆን ዳንኤል ክብረት ስለ ማኅበረ ቅዱሳን የሰጠውን አስተያየት እንዳራገቡና ለራሳቸው ዓላማ መጽፈፀሚያ ለመጠቀም እንደሞከሩ እያረገቡ ቤተክርስቲያኒቱን ሰላም ይነሱአታል ::ስብስም እነዚህ ሰዎች በቤተክርስቲያኒቱ ሥር እሰካሉ ድረስ ቤተክርስቲያኒቱን ለመክፈል ልጠቀሙ ይችላሉ::
ስለዚህ ለምዕመናን የቤተክርስቲያኒቱ "ዘመድና ባዳ "ተለይቶ መታወቅ አለበት::
ረድኤተ እግዚአብሔር የወላዲተ አምላክ ምልጃና የቅዱሳን ሁሉ ተራዳእነታቸው አይለየን::

Anonymous said...

ara menawe zeme alachohe yaena dn bagashawen ferede bate kataro?????????????????????????

Anonymous said...

አዎ!ለውጥ ያስፈልጋል ከሚሉ ሰዎች አንዱ ነኝ።የቀረበው ጽሑፍ ከማንኛውም ወገን ይምጣ እጅግ ጠቃሚና የቤተክርስቲያኒቱን ችግር ተደራሽ ያደረገ ነውና እቀበለዋለሁ። ኦርቶዶክሳዊት ቤተክርስቲያን በመንፈሳዊ፤ በታሪካዊ፤ እና በቁሳዊ ሃብት የበለጸገች እንዲሁም ለዚህች ኢትዮጵያ ለምትባል ሃገር ህልውና የሰራች መሆኗ ትልቅ ክብር የነበራት ሆና ሳለ ጽሁፉ እንዳመለከተው በትክክል ዛሬ ዛሬ የቁልቁለት መንገድ ላይ መሆኗን የሚክድ ቢኖር እርሱ በዚህ ዓለም የለም ማለት ይቻላል። ስለሆነም ለውጥ የግድ ያስፈልጋል። ጽሁፉ በእርግጥ አስተዳደራዊና መንፈሳዊ ለውጥን ጠቅሶ በአብዛኛው ለማመላከት የሞከረው በአስተዳደራዊ ጉዳዮች ላይ ብቻ ነው። እንደእኔ ለአስተዳደራዊ ጉድለቶች መነሻው የመንፈሳዊ አስተምህሮና በዚያ ላይ በእምነት የመኖር ጉድለት መከሰት ነው እላለሁ። ችግር አለ ከተባለ ችግሩ ሁለገብ መሆኑ ይሰመርበት። መንፈሳዊ ጉድለቶችም እንደእግዚአብሔር ቃል ይጠኑ፤ ይመርመሩ፤ ይስተካከሉ። ሁሉም ነገር ትክክል ነው የምንል ከሆነ ችግር አለ ማለት አይቻልም። ይሄን ይሄን አትንኩ፤ ይሄን ይሄን ብቻ አውሩ ከሚሉ አስተሳሰቦች ርቀን ችግሮቻችን ሁሉ መርምረን መፍትሄ እናብጅ፤ እሰየው!! በስንት ነገር የማከብራት፤የምወዳት ቤተክርስቲያን በስንት መንገድ በችግር ተከባ ለመውደቅ ስትንገዳገድ በማየት በግሌ ተሸማቅቄ ዳር ሆኜ ስመለከት ቆይቻለሁ።ችግር ቢኖርም የአባ ጳውሎስና የተሃድሶ ወገኖች አድርጎ የሚያቀርቡ ችግር አባባሾችን ስመለከት መፍትሄ የሌላት አድርጌም ቆጥሬአለሁ። በአስተዳደራዊም፤በሃይማኖታዊም ጉዳይ መስተካከል ያለባቸው ችግሮችን ለማረምና ለማስተካከል ለሚነሳሳ ወገን የሃሳብ፤ የገንዘብ፤የቁስ ድጋፍ በግልም በማስተባበር በቡድንም ለማድረግ ዝግጁ ነኝ። ግን እውነተኛ እንሁን።

Anonymous said...

Very good analysis dejeselam! you have identified almost all the problems within the church, but i disagree with the proposed solution. Disagreeing might not be the right word here, what i am trying to say is the revolution will never happen. Why? It is simple! Think about the revolutions in our country and in the rest of the world. In the let sixties it was the REBELLIOUS student movement that has ENDED the reign of feudalism in the country. In early nineties, it was THE REBELLIOUS movement of tplf and eplf that has ended the reign of socialism/communism in the country. If we fast forward to 2011, it was the REBELLIOUS Egyptians that has ended the reign of Mubarak in the country. In all cases, revolution happens when the people REBEL against a system that has made their existence existence miserable. In all cases, the few individuals who are beneficiaries of the corrupted system take deadly measures to thwart and destroy the revolutions. Revolutions happen only when there is a clear defined line that separates the victim from the abuser, the good from evil. Haile Sillasie never assisted the revolutionaries to their success which only can happen at the cost of his rule. The same is true in the all other revolutions. It would be foolish to think and hope meseretawi lewut yemiameta revolution will happen with the help of Abune Paulos. What makes you think Abune Pualos and those who are benefiting from the current corrupted system will allow you to kick start the kind of revolution? Chirash revolutionun finance yadergutal bilo masebma mogninet bicha sayihon higewotinetim chimir new. Everything we witnessed in the past two years only during and after the assembly of Kidus Sinodos is more than enough to conclude that Abune Paulos and his criminal friends, including the government, will allow the kind of revolutionary change within the church on their watch. The only way a revolution can happen is if we organize the people, in this case the Mi'emen, to rebel against the corrupt and illiterate leaders at the helm of our church. I am sure the government will start killing and arresting since such an action by the children of the church, miemen, is a danger for its own existence, but is there any other way to achieve revolution? None at all!

Anonymous said...

The cause of the problems is the ruling party in power,and the problem started in 19183 E.C /1991 G.C when Eprdf came to power and assumed aba Paulos to power the following year. The solution is to get rid of this party and aba paulos. Until then, we will continue to suffer. We can get rid them of power if we unite. They want weak orthodox church because orthodox teaches unity of the country and the people. They are dividing and promoting ethinic politics,and the Orthodox church is a big obstacle for their idea.
Aba Paulos is just working for this group to watch out people/fathers(papasat)who oppose this party.That is why they change them /papasat/ from place to place. So you your suggestion should have included this dicisive solution. If you are genuinely concerned about the church then DO NOT SCARE TO TEL THE TRUTH. It is since 1992/93 following aba Paulos's assumption to become patriarch all the problems manifested now started to occur. So first analyse the cause the effect were expected when the law of the church was broken. And unlike in politics or earthly affairs,in christianity you correct wrong doings, you cannot make wrong actions look like or accepted as right. 'EWUNETIN EWUNET HASETIN HASET BICHA NEW MALET YEMICHALEW.'

Anonymous said...

Correction for the second last comment:

Everything we witnessed in the past two years only, during and after the assembly of Kidus Sinodos, is more than enough to conclude that Abune Paulos and his criminal friends, including the government, will NEVER allow the kind of revolutionary change within the church on their watch.

thx

Anonymous said...

I thank you for your concern about our church. Since our church is a heavenly institution, her solutions has to come from God. All of the papas, priests, deacons and believers have to become real christians and obey the word of God. WE ALL NEED KIDISINA. Forgive me if I make mistake but i would like to read the book of Revilation (Rai Yohannes) To the angel[a] of the church in Sardis write:

as if

To the angel[a] of the ORTHODOX church in ETHIOPIA write:
These are the words of him who holds the seven spirits[b] of God and the seven stars. I know your deeds; you have a reputation of being alive, but you are dead. Wake up! Strengthen what remains and is about to die, for I have found your deeds unfinished in the sight of my God. Remember, therefore, what you have received and heard; hold it fast, and repent. But if you do not wake up, I will come like a thief, and you will not know at what time I will come to you.

May ZEMENE YOHANNES BRINGS US NEW REVILATION TO OUR CHURCH AND COUNTY

Anonymous said...

I thank you for your concern about our church. Since our church is a heavenly institution, her solutions has to come from God. All of the papas, priests, deacons and believers have to become real christians and obey the word of God. WE ALL NEED KIDISINA. Forgive me if I make mistake but i would like to read the book of Revilation (Rai Yohannes) To the angel[a] of the church in Sardis write:

as if

To the angel[a] of the ORTHODOX church in ETHIOPIA write:
These are the words of him who holds the seven spirits[b] of God and the seven stars. I know your deeds; you have a reputation of being alive, but you are dead. Wake up! Strengthen what remains and is about to die, for I have found your deeds unfinished in the sight of my God. Remember, therefore, what you have received and heard; hold it fast, and repent. But if you do not wake up, I will come like a thief, and you will not know at what time I will come to you.

May ZEMENE YOHANNES BRINGS US NEW REVILATION TO OUR CHURCH AND COUNTY

Anonymous said...

yes, it needs a change. but you must think how it could be.

Anonymous said...

GOLECHA BELAWAWATE WATE AYATAFETE.yehawelachohe yega akababe cheger comety eyamasalane comety senekayayer 3amate lehonane nawe.ahone gene malawatte yalabate ASETADADAREW mahoneo holachenem basemamanem meemanano eyatabasacha kabatakeresetayne makeraon maretole.ena lawete yamenefalegawe ega nane gene manee yegamer? endate??eyalen nawen tatakamew egea selahonen hasabe akafelone....

Anonymous said...

I have read entirely and examined thoroughly the ideas that were indicated by DEJE-SELAM. The intended solutions, for the problems, from DEJE-SELAMAWIAN are quite interesting. What I would like to add is the following:
1- Arch-bishops and Bishops should remain in their DIOCESE for October's Holy-Synod convention unless their voice and suggestion are heard. If Arch-bishops and Bishops come to the meeting and discourse one another, the main and the first agenda should be the current situation of ETHIOPIAN ORTHODOX TEWAHEDO CHURCH SIBKET.

2- The patriarch Abune Paulos' power should be limited. All the administrative works of the Holy-Synod should be handled by the Synod members. If the patriarch doesn't accept what the Holy-Synod tells him to do, he should be told to stop his duty or he should be told that Holy-Synod members won't work with him anymore.

3- Begashaw should be suspended for a specific months from giving any service in the ETHIOPIAN ORTHODOX TEWAHEDO CHURCH.

Anonymous said...

It's regrettable that Deje Selam prefers to come up with a seemingly new initiative by ignoring ongoing struggles for our church's institutional development. An example for this is the forthcoming international conference which is scheduled to be held on Sept 30th and Oct. 1st, 2011 at the Reise-Adbarat Kidest Maiam Church in Washington DC by the World Association of Parishioners of the Ethiopian Orthodox Tewahedo Church. For details, please see: www.eotcipc.org.

Repeated attempts to bring the above intitiative to DejeSelam's attention have gone unheeded.

One of our basic problems is that, similar to DejeSelam, we only want to make our own noise and not collaborate with tangible efforts.

Zeraf said...

I think the idea of change and reform is great. However, I was surprised that author failed to include the doctrinal confusions and disagreements that have engulfed the church. How on earth this big problem is not recognized in the analysis?

In any way, I wish good luck to all who try to bring change and well derserved reform at EOTC. I would hope that those changes will trasform the church to a true preacher of the Gospel and good sheepherd. Good luck change seekers!

Anonymous said...

ሀሳቡ አይከፋም ያው ሁላችንም በየጊዜው ቤአደባባዩ ምናራውን በወረቀት ጽፋችሁ አቀረባችሁት ተለየ ነገር የለም፣ ከእናንተም የተለየ ነገር አንጠብቅም፡፡ ያችኑ ጠባብ አጀንዳችሁን ዘወር አድርጋችሁ ነው ያመጣችሁት፡፡ የገረመኝ ነገር ግን ለመሆኑ ክርስቶስ ሐወርያትን ሲጠራ ኢኮኖሚስት፣ ዶክተር፣ ሶሲዎሎጅስት… ብሎ ነው ወይስ እኔ የማስተምራችሁን ተምራችሁ ምስክር ትሆናላችሁ ብሎ፤ ከሁሉ በላይ ደግሞ የእናንተ የማኅበረ ቅዱሳን የጠባብነት ሴራ ዝም ካለ ቤተ ክርስቲያንን ትረጋጋለች፡፡ የቤተ ክርስቲያንን አገልግሎት ሳታውቁ የቤተ ክርስቲያን ችግር ፈችዎች ለመሆን መብቃታችሁ ይይይይ ገገገገ ርርርር ማማማማ ልልልልልልልልለ ወይ ጉድ፡፡፡

Anonymous said...

ሐሳቡ ጥሩ ነው፣ ትንተናው አጠረ፣ መረጃም በጣም ይጎድለዋል፣ ከእውነተኛ ተጨባጭ መረጃዎች መነሳት አለብን፣ አብዮት የሚባለውን አልስማም የቤተ ክርስቲያን ቋንቋ አይደለም፡፡ መነጋገሪያ መሂን ግን ይችላል፡፡ ያልተጠቀሱ አካላት አሉ ለምሳሌ ሕገ ወጥ ባህታውያን፣ ‹የቀበሮ ባሕታውያን›፣ ብቻ ጥሩ ነው

Anonymous said...

I think, It's your invisible dream that can not be act forever.

Anonymous said...

This is to the last Anonymus of September 14.

Why do you say this is a dream not a reality?
If it is because you are against the improvement and rebirth of our church go to hell!! On the other hand if you have good reasons to support this idea of yours let us hear about it and discuss.

Fre said...

ፀልዩ ፀልዩ ፀልዩ!!! አብዝታችሁ ፀልዩ!!! አብዝታችሁ ፀልዩ!!!

Blog Archive

የአቡነ ጳውሎስ "ሐውልተ ስምዕ"

ነጻ ፓትርያርክ ምርጫ ቢሆን ኖሮ ማንን ይመርጡ ነበር? እንበልና ሁሉም ነገር ሥርዓቱን ጠብቆ የተከናወነ የእጩዎች ምርጫ ቢሆን ኖሮ፣ አሁን የምናነሣቸው ጉድለቶች ባይኖሩ ኖሮ፣ 6ኛው ፓትርያርክ እንዲሆን የምትመርጡት ማንን ነበር? (ማሳሰቢያ፦ አሁን ያለው ክፍፍል እና የመንግሥት ተጽዕኖ ባይኖር ኖሮ ተብሎ የሚመለስ ጥያቄ ነው። የምን “ባይኖር ኖሮ ነው” የሚል አስተያየት ካለዎትም እናከብራለን።)