September 6, 2011

የደሴ ከተማ ሰንበት ት/ቤቶች በሀ/ስብከታቸው ስላለው የሕገ ወጥ አጥማቅያን፣ ሰባክያን እና ዘማርያን ሁኔታ የሰጡት መግለጫ

(ደጀ ሰላም፤ ሰፕቴምበር 6/2011)፦ የደሴ ከተማ ሰንበት ት/ቤቶች በሀ/ስብከታቸው የሕገ ወጥ አጥማቅያን፣ ሰባክያን እና ዘማርያን መስፋፋት እንደሚያሳስባቸው በመግለጽ ከአዲስ አበባ እና ከሰሜን አሜሪካ አቻዎቻቸው ጋር ተቆጥረዋል። የደሴው ሰ/ት/ቤቶች መግለጫ የሚከተሉትን ዋና ዋና ነጥቦች ይዟል።
  • በሕገ ወጥ አጥማቅያን፣ ሰባክያንና ዘማርያን ዙሪያ ለሚደረገው የመከላከል እንቅስቃሴ ከምእመናን፣ ከየአድባራቱ፣ ሰንበት ት/ቤቶችና ከሚመለከታቸው አካላት የተውጣጣ ኮሚቴ እንዲቋቋምና ጥናት እንዲደረግ ጠይቀዋል፡፡
  • ሀገረ ስብከቱ በሕገ ወጥ ማኅበራት ላይ ያወጣውን መመሪያ ተግባራዊ እንዲያደርግ ጠይቀዋል፡፡
  • ለሕገ ወጥ አጥማቅያኑ፣ ሰባክያኑና ዘማርያኑ ጉዳይ አስፈጻሚ የሆኑ አባቶች ‹‹ኖላዊነታቸውን የዘነጉ›› በመሆናቸው ከዚህ ተግባራቸው እንዲቆጠቡ አሳስበዋል፡፡
  • የአዲስ አበባ ሰንበት ት/ቤቶች ያወጡትን መግለጫ ሙሉ በሙሉ ደግፈዋል፡፡
  • የደቡብ ወሎ ሀገረ ስብከት ከዚህ ቀደም በሕገ ወጡ በጋሻው ደሳለኝ ላይ የእግድ ርምጃ መውሰዱ ይታወሳል፡፡
 የመግለጫውን ሙሉ ቃል ከዚህ በታች ይመልከቱ፡፡

       በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ
‹‹ኢየሱስ ክርስቶስን እንደሚያገለግል በጎ አርበኛ ሆነህ መከራ ተቀበል፡፡››
                                                           (2ኛጢሞ.2፣3)
በቅድስት ቤተ ክርስቲያን ላይ በሕገ ወጥ አጥማቅያን፣ ሰባክያንና ዘማርያን አማካይነት በኢ/ኦ/ተ/ቤ/ክርስቲያን ላይ እየደረሰባት ያለው ችግር እንዲቆም በደቡብ ወሎ ሀገረ ስብከት በደሴ ከተማ የሚገኙ የ12ቱ ሰንበት ት/ቤቶች በጋራ ያወጡት የአቋም መግለጫ
ሀገራችን ኢትዮጵያ እግዚአብሔር አምላኳን በሕገ ልቡና፣ በሕገ ኦሪት እና በሕገ ወንጌል ስታመልክ የነበረች፣ ያለች እና ወደፊትም በማምለክ የምትኖር ናት፡፡ ምንም እንኳን ቤተ ክርስቲያናችን በልዩ ልዩ መልክ ለዘመናት ስትፈተን የቆየች እና ያለች ቢሆንም አባቶቻችን በጥበብ መንፈሳዊ እና ሥጋዊ እግዚአብሔር አምላክን አጋዥ በማድረግ አሁን ላለንበት ዘመን እምነትን፣ ታሪክን፣ ኪነ ሕንፃን፣ ሥነ ጽሑፍን፣ ዜማን… ወዘተ አውርሰውናል፡፡

ቅድስት ቤተ ክርስተያን ባሕረ ጥበባት ስንዱ እመቤት ሆና ሳለ ለግል ጥቅማቸው የሚንቀሳቀሱ አንዳንድ ግለሰቦችና ቡድኖች ብቅ እልም እያሉ ምእመናንን በማደናገር እያወኳት ይገኛሉ፡፡ በተጨማሪም በውጭ ሀገርና በሀገር ውስጥ በሚገኙ የቤተ ክርስቲያን አካላት ባልሆኑ አስተማሪዎቻቸው የተሰጣቸውን ተልእኮ በመያዝ ‹‹መልካም የሆነው ትምህርት እንዳይኖር አብዝተው ይተጋሉ›› እንዳለው ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ ቅድስት ቤተ ክርስቲያናችንን የወንበዴዎች ዋሻ ለማድረግ ሌት ተቀን ከውጭ እየገፉ በቤተ ክርስቲያን መዋቅር ውስጥ ለሆዳቸው ባደሩ አጋዦቻቸው አማካይነት እየተደገፉ ስልታቸውን በመቀያየር የቤተ ክርስቲያንን ትምህርት ሳያውቁ ‹‹እናድሳለን›› በማለት ለዘመናት የኖረችው ቤተ ክርስቲያን ሐዋርያዊ ተልእኮዋን በተገቢ ሁኔታ እንዳትወጣ የሞት ሽረት ትግል እያደረጉ ይገኛሉ፡፡ ነገር ግን ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በወንጌል ‹‹የሲኦል ደጆች አይችሏትም›› እንዳለው በዘመኑ በገጠሟት ፈተናዎች ሁሉ ለሃይማኖታቸው ቀናዒ የሆኑ ጠባቂዎቿን ያሥነሳላታል፣ በድልም ያረማምዳታል፡፡

በመሆኑም እኛ የሰንበት ት/ቤቶች ወጣቶች ቤተ ክርስቲያናችንን እያወኳት ያሉት ግለሰቦች ራሳቸውን አስተካክለው የቤተ ክርስቲያን ዶግማ፣ ቀኖና፣ ሥርዐትና ትውፊት በመጠበቅና በማስጠበቅ ይመለሳሉ ብለን ብንጠብቅም ይባስ ብሎ መልካቸውን እየቀያየሩ በመምጣታቸው ከዚህ እንደሚከተለው የጋራ የአቋም መግለጫ ለማውጣት ተገደናል፡፡
1)    የቤተ ክርስቲያን ሥርዐት ባልጠበቀ መልኩ ‹‹አጠምቃለሁ›› በማለት ምእመናንን በማደናገር ላይ የተሰማራው ‹‹መምህር›› ግርማ የተባለው ግለሰብ በቁጥር 4290/90/03 በቀን 08/10/03 ዓ.ም በአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት የተጣለበትን እገዳ በመጣስ በማን አለብኝነት እየተንቀሳቀሰ በመሆኑ መምህር ግርማና መሰል ግብረ አበሮቹ የቤተ ክርስቲያንን ትእዛዝ እንዲያከብሩና ከእኩይ ተግባራቸው እንዲቆጠቡ እንጠይቃለን፡፡
2)    በደቡብ ወሎ ዞን በሐይቅ ከተማ ‹‹መምህር›› ግርማ በድምፅ ማጉያ ያስተላለፋቸው መልእክቶች ‹‹የዚህ አገር ሰዉም አጋንንቱም አይታዘዙም›› በማለት ምእመኑን ከአጋንንት ጋራ አንድ በማድረግ የተናገረው አባባል ቃል በቃል መረጃው ከእኛ ጋራ ያለን ሲሆን ምእመኑን ከርኩስ መንፈስ ጋራ በማገናኘት የተናገረው የጽርፈት ንግግር የቤተ ክርስቲያንን ክብር የሚነካ፣ የሕዝብን ሉዓላዊነት የሚጋፋ በመሆኑ ግለሰቡ ግለሰቡ በራሱ ማስተካከያ እንዲሰጥ እንዲደረግልን እናሳስባለን፡፡
3)    ‹‹አጥማቂ ነኝ›› ባዩ ‹መምህር› ግርማ በመንፈስ ቅዱስ ጠባቂነት የማያምን እና በሚሠራው ሥራ ላይ እምነት ባለመኖሩ ክብደት(ስፖርት) በማንሣት ከ1999-2003 ዓ.ም በአዲስ አበባ ከተማ በ62 ካቴጎሪ ተወዳዳሪ ከሆኑ ግለሰቦች ጋራ በመደራደር አበል በመክፈል ራሱን የሚያስጠብቅና ፍጹም መንፈሳዊነት የማይታይበት ግለሰብ በመሆኑ በቤተ ክርስቲያናችን ቅጽር ለመንቀሳቀስ የሚያደርገውን ፈጽሞ እንቃወማለን፡፡
4)    በ‹መምህር› ግርማ እየተቸበቸበ ያለውን መቁጠሪያ መነሻው ከየት እንደሆነ የማይታወቅ፣ የቤተ ክርስቲያንን ሥርዐት እና ትውፊት ያልጠበቀ፣ እንዲሁም በሚመለከታቸው የቤተ ክርስቲያን አባቶች ያልተባረከ እና ግለሰባዊ የገንዘብ ጥማቱን ለማርካት ብቻ የዋሃን ምእመናንን በማታለል ላይ ይገኛል፡፡ ለዚህም ማሳያ በደቡብ ወሎ ዞን ሐይቅ ከተማ 6000 መቁጠሪያ እና ቪ.ሲ.ዲ ይዞ ለገበያ ያቀረበ ሲሆን በአራት ቀን ውስጥ(ከረቡዕ - ቅዳሜ) ማለቁና ተጨማሪ አንድ ጆንያ መቁጠሪያ ለቅዳሜ ከሰዓትና እሑድ ሽያጭ ማቅረቡ ምን ያህል ምእመናንን በማታለል የገንዘብ ጥማቱን ለማርካት የሚንቀሳቀስ መሆኑን ያስረዳል፡፡ በመሆኑም ለምእመናን ይኸው ችግሩ ተገልጦ እንዲተላለፍልንና ግለሰቡም በቤተ ክርስቲያን ስም መነገዱን እንዲያቆም በጥብቅ እንጠይቃለን፡፡
5)    በቤተ ክርስቲያን ውስጥ ያሉ ሕገ ወጥ አጥማቅያን፣ ሰባክያንና ዘማርያን ለሆኑት ጉዳይ አስፈጻሚዎች የቆሙለትን ዓላማ በመዘንጋት ኖላዊነታቸውን በመርሳት አንዳንድ የቤተ ክርስቲያን ‹‹አባቶች›› ከዚህ ተግባራቸው እንዲቆጠቡ እያሳሰብን ይህ የማይስተካከል ከሆነ ግን በቀጣይ በዝርዝር በማጣራት ለምእመኑ የምናጋልጥ መሆኑን እንገልጣለን፡፡
6)    ምሥጢረ መለኮትንና ሥርዐተ ቤተ ክርስቲያንን እያፋለሱ ያሉ ሕገ ወጥ ሰባክያንና ዘማርያን በቤተ ክርስቲያናችን መድረክ ላይ እንዳይቆሙ በጥብቅ እያስታወቅን የጠቅላይ ቤተ ክህነት ሰንበት ት/ቤቶች ማ/መምሪያ ሓላፊ በተሐድሶ እንቅስቃሴ ላይ የሰጡት የሚዲያ መግለጫ ትክክል ባለመሆኑ ማስተባበያ እንዲሰጥበት፣ ይህ የማይሆን ከሆነ ግን የተሐድሶ መናፍቃን በቤተ ክርስቲያናችን ላይ እያደረጉ ያለውን እንቅስቃሴ የሚያሳይ መግለጫ በተለያዩ መድረኮች ላይ የምንሰጥ መሆኑን እንገልጻለን፡፡
7)    ከጠቅላይ ቤተ ክህነት ስብከተ ወንጌልና ሐዋርያዊ ተልእኮ መምሪያ ‹‹ደብዳቤ ተጽፏል›› በሚል ሰርገው እየገቡ የሚመጡትን አንዳንድ ሕገ ወጥ ሰባክያንና ዘማርያንን ሀገረ ስብከታቸችን የራሱን ማጣራት እያደረገ እንዲፈቅድ እንጠይቃለን፡፡
8)    በሃይማኖት የሚመስሉን ወንድሞቻችንና እኅቶቻችን የሆኑት የአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት ሰንበት ት/ቤቶች በጋራ ያወጡትን የአቋም መግለጫ ሙሉ በሙሉ እንደግፋለን፡፡ የሚመለከታቸውም የቤተ ክርስቲያን አካላት የአቋም መግለጫውን ተግባራዊ እንዲያደርጉት በጥብቅ እንጠይቃለን፡፡
9)    ሀገረ ስብከቱ በሕገ ወጥ ማኅበራት ላይ የወሰደው እርምጃ ተግባራዊ እንዲያደርግ በአጽንኦት እንጠይቃለን፡፡
10)    የደሴ ከተማ ወረዳ ቤተ ክህነት በሕገ ወጥ አጥማቅያን፣ ሰባክያንና ዘማርያን ዙሪያ ለሚደረገው የመከላከል እንቅስቃሴ እገዛ የሚያደርጉ ከምእመናን፣ ከየአድባራቱ፣ ሰንበት ት/ቤቶችና ከሚመለከታቸው አካላት የተውጣጣ ኮሚቴ እንዲቋቋምና ጥናት እያደረገም ለቤተ ክርስቲያናችን እገዛ እንዲያደርግ ስንል እንጠይቃለን፡፡

የደሴ ወረዳ ቤተ ክህነት በከተማዋ የሚገኙትን ሰንበት ት/ቤቶች አንድነት ለማጠናከር እያደረገ ያለውን መንፈሳዊ ትጋት እያደነቅን ከላይ ያቀረብናቸውን የአቋም መግለጫዎች ተመልክቶ አፋጣኝ መፍትሔ እንደሚሰጠን በማመን ነው፡፡
በመጨረሻም እነዚህ ችግሮች ጊዜውን የጠበቀ መፍትሔ ሳይሰጣቸው ቀርተው ተዳፍነው ከቆዩ ምእመናንና የሰንበት ት/ቤቶች ወጣቶች አባላት አማራጭ መፍትሔ ለመፈለግ የምንገደድ መሆኑን እንገልጻለን፡፡ ስለሆነም ችግሮቹ ከመፈጠራቸው በፊት የሚመለከታቸው አካላት ሁሉ አስፈላጊውን መፍትሔ ይሰጡን ዘንድ እናሳስባለን፡፡ ይህ ባልሆነበት ሁኔታ ለሚፈጠረው ማንኛውም ችግር የሚመለተው አካል ሁሉ ተጠያቂ እንደሚሆን ከወዲሁ እንዲያውቅልን ስንል በአጽንዖት እንገልጻለን፡፡
                                ወስብሐት ለእግዚአብሔር፣ ወለወላዲቱ ድንግል፣ ወለመስቀሉ ክቡር
                                            ሐምሌ 19 ቀን 2003 ዓ.ም
                                                      ደሴ
Post a Comment

Blog Archive

የአቡነ ጳውሎስ "ሐውልተ ስምዕ"

ነጻ ፓትርያርክ ምርጫ ቢሆን ኖሮ ማንን ይመርጡ ነበር? እንበልና ሁሉም ነገር ሥርዓቱን ጠብቆ የተከናወነ የእጩዎች ምርጫ ቢሆን ኖሮ፣ አሁን የምናነሣቸው ጉድለቶች ባይኖሩ ኖሮ፣ 6ኛው ፓትርያርክ እንዲሆን የምትመርጡት ማንን ነበር? (ማሳሰቢያ፦ አሁን ያለው ክፍፍል እና የመንግሥት ተጽዕኖ ባይኖር ኖሮ ተብሎ የሚመለስ ጥያቄ ነው። የምን “ባይኖር ኖሮ ነው” የሚል አስተያየት ካለዎትም እናከብራለን።)