September 1, 2011

እነ መ/ር ዘመድኩን በቀለ ፍርድ ቤት ቀረቡ

(ደጀ ሰላም፤ ሰፕቴምበር 1/2011)፦ በበጋሻው ደሳለኝ ‹የስም ማጥፋት ወንጀል› ክስ የቀረበባቸው ዲያቆን ደስታ ጌታሁን፣ መ/ር ዘመድኩን በቀለ እና መ/ር ሣህሉ አድማሱ ፍርድ ቤት ቀረቡ፡፡ ዛሬ፣ ነሐሴ 25 ቀን 2003 ዓ.ም ጠዋት በፌዴራሉ የመጀመሪያ ደረጃ ፍ/ቤት ቦሌ ምድብ ችሎት የቀረቡት ሦስቱም ተከሳሾች በበጋሻው ደሳለኝ የቀረበባቸውን ክስ እንደማይቃወሙት፣ ነገር ግን የስም ማጥፋት ድርጊት ፈጽመናል ብለው እንደማያማኑ ለችሎቱ ተናግረዋል፡፡ ከእነርሱም መካከል አንደኛ ተከሳሽ ዲያቆን ደስታ ጌታሁን ከከሳሽ ጋራ ያላቸው ልዩነት ሃይማኖታዊ በመሆኑ ክሱ በፍትሕ መንፈሳዊ መሠረት ይታይ ዘንድ ወደ ጠቅላይ ቤተ ክህነቱ መንፈሳዊ ፍ/ቤት እንዲመራላቸው መጠየቃቸው ተገልጧል፡፡


ተከሳሾቹ የተከሰሱበት ጉዳይ በጽሑፍ እንዳልደረሳቸው ለችሎቱ በማስረዳታቸው ዐቃቤ ሕግ የክሳቸውን ጽሕፈት ለሁሉም ተከሳሾች እንዲሰጥ ታዝዟል፡፡ በመጨረሻም ዳኛው ዐቃቤ ሕግ ክሱን ያስረዱልኛል የሚላቸውን ማስረጃዎች እንዲያቀርብ፣ ሦስቱም ተከሳሾች እያንዳንዳቸው የብር 5000 ዋስ ጠርተው እንዲወጡና የሕግ ባለሙያ አማክረው ከጠበቃ ጋራ እንዲቀርቡ ለጳጉሜን ሦስት ቀን 2003 ዓ.ም ቀጠሮ ሰጥተዋል፡፡

በመ/ፓ/ጠ/ቤ/ክ የገዳማት መምሪያ ጸሐፊ የሆኑት ዲያቆን ደስታ ጌታሁን ‹‹የሰባኪው ሕጸጽ››፣ መ/ር ሣህሉ አሰግድ ‹‹በጋሻው ኦርቶዶክሳዊ ነውን?›› በሚሉ ርእሶች ባሳተሟቸው መጻሕፍት የበጋሻው ደሳለኝን ማንነትና በስሕተት የተሞሉ ስብከቶች ነቅሰዋል፤ አደባባይ ከመውጣት ተወግዶ ተቀምጦ እንዲማርና ለፈጸመው ስሕተቱ ንስሐ እንዲገባ መክረዋል፤ ‹‹ራሱ ሕጋዊ ሳይሆን ስሜን የሚያጠፉትን በሕግ እጠይቃለሁ፤ ሓላፊነቱን የሚወስድ ሰው አጣሁ›› በማለት ለሚናገረውም ‹‹ፈረሱም ያው! ሜዳውም ያው›› ብለውታል - በመጽሐፎቻቸው፡፡ መ/ር ዘመድኩን በቀለም በቅርቡ የፕሮቴስታንታዊ-ተሐድሶ-ኑፋቄን አስመልክቶ በተለያዩ መጽሔቶች ላይ በሰጣቸው ቃለ ምልልሶቹ ነው የተከሰሰው፡፡ የበጋሻው ክስ ጠቅላላ ይዘትም ‹‹ሕገ ወጥ ሰባኪ በመባሉ ከኅብረተሰቡ እና ከቤተሰቡ የመለየትና የመገለል በደል እንደተፈጸመበት›› የሚያመለክት ነው ተብሏል፡፡

ፍ/ቤቶች እስከ መጪው ዓመት ጥቅምት ወር ድረስ በሥራ ላይ የማይሆኑበት ሁኔታ በመኖሩ ተከሳሾቹን በእስር ለማሰንበት ቋምጠው በችሎቱ ቅጽር የተገኙ የሚመስሉት ከሳሽ እና ግብረ አበሮቹ (አሰግድ ሣህሉ፣ ትዝታው ሳሙኤል እና የጥቅም አጋራቸው ነው የሚባለው ኤፍሬም ኤርሚያስ) ተከሳሾች የዋስ መብታቸው ተጠብቆላቸው በመውጣቸው ከፍተኛ መከፋት አድሮባቸው ታይተዋል፡፡ በአንጻሩ እንደ ዐቃቤ ሕግ አነጋገር ተከሳሾች የተጠየቁትን ‹‹ጠበቅ ያለ ዋስትና›› ለማቅረብ በችሎቱ እና ከችሎቱ ውጭ በፀረ-ፕሮቴስታንታዊ-ተሐድሶ እንቅስቃሴው ዙሪያ ግንባር የፈጠሩ አካላት እና አባላት ከፍተኛ መረባረብ እና መደጋገፍ አሳይተዋል፡፡
Post a Comment

Blog Archive

የአቡነ ጳውሎስ "ሐውልተ ስምዕ"

ነጻ ፓትርያርክ ምርጫ ቢሆን ኖሮ ማንን ይመርጡ ነበር? እንበልና ሁሉም ነገር ሥርዓቱን ጠብቆ የተከናወነ የእጩዎች ምርጫ ቢሆን ኖሮ፣ አሁን የምናነሣቸው ጉድለቶች ባይኖሩ ኖሮ፣ 6ኛው ፓትርያርክ እንዲሆን የምትመርጡት ማንን ነበር? (ማሳሰቢያ፦ አሁን ያለው ክፍፍል እና የመንግሥት ተጽዕኖ ባይኖር ኖሮ ተብሎ የሚመለስ ጥያቄ ነው። የምን “ባይኖር ኖሮ ነው” የሚል አስተያየት ካለዎትም እናከብራለን።)