September 7, 2011

ፀበል እየተፀበሉ በነበሩ ወጣቶች ላይ “በተሰነዘረ ድንገተኛ ጥቃት” 2 ወጣቶች ሞቱ


  • የወጣቱ የቀብር ሥነ ሥርዐት “ለጸጥታ” በሚል በአስቸኳይ ተፈጽሟል።
(ደጀ ሰላም፤ ሰፕቴምበር 8/2011)፦ በደቡብ ወሎ ሀገረ ስብከት ደሴ ከተማ በተለምዶ አሬራ እየተባለ በሚታወቅ አካባቢ በሚገኘው የደብረ ሣህል ቅዱስ ዐማኑኤል እና ቅዱስ ራጉኤል ቤተ ክርስቲያን አቅራቢያ በሚገኝ ፀበል ተፀብለው ወደ መኖሪያ ቤታቸው እየተመለሱ በነበሩ ወጣቶች ላይ፣ ዛሬ ጳጉሜን 3 ቀን 2003 ዓ.ም ከሌሊቱ ሰባት ሰዓት በደረሰ ድንገተኛ ጥቃት ሁለት ወጣቶች ሞቱ፡፡


ብርሃኑ ታደሰ የተባለውን ወጣት ለሞት ያበቃው፣ ለጊዜው ማንነታቸው በውል ያልተለዩ ኀይሎች በወጣቶቹ ላይ የድንጋይ ናዳ በማውረድ ባደረሱት የቡድን ጥቃት ነው ተብሏል፡፡ በጥቃቱ ክፉኛ ተጎድቶ ለሞት ከበቃው ብርሃኑ ጋራ የተጸበሉበትን ውኃ ቀድተው ለመያዝ ወደ ኋላ ከሌሎች ባልንጀሮቻቸው ተለይተው ወደ ኋላ የቀሩ ሌሎች አራት ወጣቶች የመቁሰል አደጋ ደርሶባቸዋል፡፡ ፖሊስ የአደጋውን መንሥኤ በማጣራት ላይ እንደሆነ ቢመለከትም የሟቹ ወጣት የቀብር ሥነ ሥርዐት “ለጸጥታ” ሲባል ዛሬውኑ በዚያው የደብረ ሣህል ቅዱስ ዐማኑኤል ቤተ ክርስቲያን መፈጸሙ ተዘግቧል፡፡

ሟች ብርሃኑ በደብረ ሣህል ቅዱስ አማኑኤል ቤተ ክርስቲያን ሰንበት ት/ቤት አባልና በቴክኒክ እና ሙያ ማሠልጠኛ ትምህርቱን በመከታተል ላይ እንደነበር ታውቋል፡፡ አንዳንድ ምንጮች ለጥቃቱ በሰኔ ወር አዲስ አበባ ሀገረ ስብከት የእገዳ ውሳኔ ያስተላለፈባቸው “መምህር ግርማ” የተባሉትን አጥማቂ ተከታዮች እንደሚጠረጥሩ ሲገልጹ፣ ሌሎች ደግሞ ጥቃቱ እስከ አሁን ውሳኔ ባላገኘው የቅድስት አርሴማ እና ጻድቁ አቡነ አረጋዊ ገዳም የይዞታ ውዝግብ ጋራ በተያያዘ የአክራሪ እስልምና ኀይሎች የፈጸሙት ሊሆኑ እንደሚችሉ የዓይን ምስክሮችን በመጥቀስ ያስረዳሉ፡፡

በከተማው ያሉ 12 አጥቢያ አብያተ ክርስቲያን ሰንበት ት/ቤቶች ሐምሌ 19 ቀን 2003 ዓ.ም በወቅታዊ ጉዳይ ባወጡት የጋራ አቋም መግለጫ፣ “በመንፈስ ቅዱስ ጠባቂነት የማያምነውና በሚሠራው ሥራ እምነት ያላተረፈው” ያሏቸውን አጥማቂ ግርማን፣ “ክብደት (ስፖርት) በማንሣት ከ1999-2003 ዓ.ም በአዲስ አበባ ከተማ በ62 ካቴጎሪ ተወዳዳሪ ከሆኑ ግለሰቦች ጋራ በመደራደር አበል በመክፈል ራሱን የሚያስጠብቅና ፍጹም መንፈሳዊነት የማይታይበት ግለሰብ” ነው በሚል በቤተ ክርስቲያን ቅጽር የሚያደርጉትን እንቅስቃሴ ፈጽሞ እንደሚቃወሙት መግለጻቸው ይታወሳል፡፡

በየዓመቱ የተውሣኳን(ጳጉሜን) 5/6 ቀናት በሙሉ እስከ አዲስ ዓመት መባቻ በሚዘከረው የመጥምቁ ቅዱስ ዮሐንስ በዓል ሌሊት ጠበል ወዳሉባቸው ስፍራዎች እና ወደ ወንዝ በሌሊት እየወረዱ መጠመቅ የቆየ ክርስቲያናዊ ትውፊት(ባህል) ነው፡፡ ይልቁንም ጳጉሜን ሦስት ቀን ሰባቱ ሰማያት ተከፍተው(ርኅዎ ሰማይ) የሰዎች ሁሉ ጸሎታት የሚያርጉበት፣ የሰው ልመናው የሚሰማበት “የበረከት ቀን፣ የጸሎት ቀን” እንደሆነ ይታመናል፡፡ በመጽሐፈ ጦቢትም እንደተገለጸው ቀኑ መልአኩ ቅዱስ ሩፋኤል በዓሣ ሐሞት የጦቢትን ዐይን የፈወሰበት፣ ጦቢያን በመንገድ የመራበት፣ በራጉኤል ልጅ ሣራ ጭን ያደረውን አስማንድዮስ የተባለ ጽኑ ጋኔን ድል ነስቶ የሣራን እና የጦቢትን ልጅ የጦቢያን ጋብቻ የባረከበት መታሰቢያ ነው፡፡

5 comments:

Gebre Z Cape said...

በጣም ያሳዝናል፡፡ ምን አይነት ፈተና እና ዜና ነው በየጊዜው የምታሰሙን? አምላክ ይህንን ሕዝብ እና ይህችን ቤ/ያን ረሳት፡፡ ለቤተሰቦች መፅናናትን ይህንን ለፈጸሙ ሰዎች የይቅርታ ልብን ያድልልን፡፡ ክርስቲያኖች አሁን ነው አንድ መሆንና የመረጃ ሰዎች መሆን ያለብን፡፡ የችግሩን መነሻ ለማወቅ ያለው አማራጭ ይህ ነውና፡፡

Anonymous said...

እጅግ በጣም ያሳዝናል ነፍሳቸውን በቀኙ ያኑርላቸው
ቸሩ ፈጣሪ አምላክ ዋስ ጠበቃ ይሁነነን በቃችሁ ይበለን እንጂ ግዜው በጣም ከፍቷል::

Sara Adera said...

እጅግ በጣም ያሳዝናል ነፍሳቸውን በቀኙ ያኑርላቸው
ቸሩ ፈጣሪ አምላክ ዋስ ጠበቃ ይሁነነን በቃችሁ ይበለን እንጂ ግዜው በጣም ከፍቷል::

ዘሐመረኖህ said...

በግፍ የተገደሉትን ወንድሞች ነፍስ ይማርልን ለቤተሰቦቻቸውና ለወዳጅ ዘመዶቻቸው እንዲሁም ለሕዝበ ክርስቲያኑ ሁሉ መጽናናትን ይስጥልን ነገር ግን በቂ ምርመራና ማጣራት ሳይደረግ ምክንያት ፈጥሮ በቶሎ መቅበር ምን ማለት ነው ግራም ነፈሰ ቀኝ ገዳዮቹ የቤተክርስቲያናችን ጠላቶች እንደሆኑ ግልጽ ነው ከግድያው ጀርባ መንግስት ወይም የመንግስት ባለስልጣን እጅ ከሌለበት የገዳዮቹን ማንነት በምርመራ ማወቅ አይከብድም እግዚአበሔር እንባችንን ያድስልን አሜን

asbat dngl said...

እጅግ በጣም ያሳዝናል ነፍሳቸውን በቀኙ ያኑርላቸው
ቸሩ ፈጣሪ አምላክ ዋስ ጠበቃ ይሁነነን በቃችሁ ይበለን እንጂ ግዜው በጣም ከፍቷል::

Blog Archive

የአቡነ ጳውሎስ "ሐውልተ ስምዕ"

ነጻ ፓትርያርክ ምርጫ ቢሆን ኖሮ ማንን ይመርጡ ነበር? እንበልና ሁሉም ነገር ሥርዓቱን ጠብቆ የተከናወነ የእጩዎች ምርጫ ቢሆን ኖሮ፣ አሁን የምናነሣቸው ጉድለቶች ባይኖሩ ኖሮ፣ 6ኛው ፓትርያርክ እንዲሆን የምትመርጡት ማንን ነበር? (ማሳሰቢያ፦ አሁን ያለው ክፍፍል እና የመንግሥት ተጽዕኖ ባይኖር ኖሮ ተብሎ የሚመለስ ጥያቄ ነው። የምን “ባይኖር ኖሮ ነው” የሚል አስተያየት ካለዎትም እናከብራለን።)